Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

🕊  † ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ  †  🕊

ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ነው:: ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት:አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር:: ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: በሥርዓት አድጎ: መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል::

ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምሕሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል:: መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር::

ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ: ሲያደንቁዋቸውም ሰማ:: እርሱ በዛ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምሕሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው:: እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚሕ በጣም ርቅው: ንጽሕናቸውን ጠብቀው: ከሰውና ከኃጢአት ተይለው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ" አሉት::

ቅዱስ አቡናፍር "በዚሕ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ:: ዓለም እንኩዋ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም" አሉት:: ይሕንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም::

ከመምሕሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ:: ለብዙ ቀናት ከተጉዋዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ:: ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ::

ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ:: አካባቢው የውሃ ጠብታ የማይገኝበት: ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኩዋ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት: ልምላሜ ሣዕር የሌለበት: ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር:: በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም::

ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር:: ቅዱሳኑን ይሕ አያሳስባቸውም:: ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም: ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና:: አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ:: በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ [በቀልት] በቀለች:: ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ [ንጹሕ ምንጭ] ፈለቀች::

ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ:: ዓመታት አለፉ:: ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ:: በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለ፷ [60] ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ:: የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን [የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው] ላከላቸው::

ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ:: እንደ እሳትም ነደደ:: አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ:: ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ: ሰገዱና አማተቡ:: ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ቅዱሳን መላዕክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጉዋት:: የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይሕን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች: ቅርንጯም ደርቃለች::

ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት::

ከሰው [ ከዓለም ] ርቀው: ንጽሕ ጠብቀው: ዕጸበ ገዳሙን: ግርማ አራዊቱን: ጸብዐ አጋንንትን ታግሠው የኖሩ: ስማቸውን የምናውቀውንም ሆነ የማናውቃቸውን እንድናከብራቸው ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓትና በዓል ሠርታለች::

አምላካችን ከአበው ባሕታውያን ጸጋ በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አባ አቡናፍር ገዳማዊ [ስም አጠራሩ የከበረ:
ሽምግልናው ያማረ አባት]
፪. አበው ቅዱሳን ባሕታውያን [ ዛሬ የሁሉም ቅዱሳን ባሕታውያን [በተለይም የስውራኑ] ዓመታዊ በዓል ነው::

- ከሰው: ከዓለምና ከኃጢአት ርቀው
- ንጽሕ ጠብቀው
- ዕጸበ ገዳሙን
- ድምጸ አራዊቱን
- ግርማ ሌሊቱን
- የሌሊቱን ቁር
- የመዓልቱን ሐሩር
- ረሐቡን: ጽሙን: መራቆቱን . . . ሁሉ
ስለ ፍቅረ-ክርስቶስ ሲሉ ታግሠውታልና::

"ዛሬም በየበርሃው የወደቁ: ስለ ዓለም ምሕረትን
የሚማጸኑ አሉ::"

አምላካቸው በረከታቸውን ያድለን።

፫. የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ከግብጽ እንዲመለስ የነገረበት [ተዝካረ ሚጠታ ለእግዝእትነ ማርያም]
፬. አፄ ይኩኖ አምላክ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩፡ ኪዳነ ምሕረት ማርያም
፪፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ
፫፡ አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፬፡ ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሠ ሮሜ
፭፡ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፮፡ ቅዱስ ሐርቤ ንጉሠ ኢትዮጵያ

" . . . ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ: ከዚሕም በላይ በእሥራትና በወኅኒ ተፈተኑ . . . ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: ዕብ.፲፩፥፴፮] (11:36) "

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                       †                       

[ ይህም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው።  ]

†   🕊   †    🕊   †

💖

❝ ይህም ለሐዋርያት የተሰጠ በሁለተኛው ልደት ፣ ከእነርሱ በተወለዱት ክርስቲያኖች ሁሉ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ነው። እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ከቤተክርስቲያን ማኅበር [ አንድነት ] አይለይም።

ይህም ጰራቅሊጦስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው። በክርስትናው ዕለት ጥምቀት በሚጠመቁት ሁሉ ላይ የሚያድርም እርሱ ነው። ክርስቲያን የሚሆኑትም በአንዲት የሐዋርያት ጉባኤ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ብሎ ካህኑ እፍ ባለባቸው ጊዜ ነው። ያን ጊዜም መንፈስ ቅዱስ በተጠመቁት ሁሉ ላይ በርግብ አምሳል ያድራል።

ይህም በተጠመቀበት ዕለት በጌታችን ላይ በርግብ አምሳል የወረደው ፣ በራሱ ላይም የተቀመጠው ፣ በነቢያት አንደበትም የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው። ❞

[ ርቱዓ ሃይማኖት  ]

🕊

❝ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት በእኛ ውስጥ ሳያድር በፊት እግዚአብሔር አብን አባት ብለን መጥራት አንችልም ነበር። ስለዚህም በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን ያልተቀበሉ እርሱን አባት ብለው መጥራት እንዳይችሉና " አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ... " ብለውም መጸለይ እንዳልተፈቀደላቸው እንገነዘባለን። ለዚህ እንዳይበቁ የሚያደርጋቸው ዋነኛው ምክንያት በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ ባለማደሩ ነው። ❞

[ ፊልክስዩስ ]

†   🕊   ክብርት ሰንበት   🕊   †

†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

❇️አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ❇️

=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም
ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ
እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡

+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ
ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን
በፍትሕ
እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::

+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው::
ላኪው አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ
ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::

+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው
ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ
ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::

+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው
አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ
መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና
ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል
ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::

+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው
አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን
"ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል"
ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር)
ተጠራርጎ ሸሸ::

+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)
አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም
"አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡

+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና
ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::

+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ
ተአምራትን ሰርተዋል:-

1.ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ
ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2.ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን
አቁመዋታል::

+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ
እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው
ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ
ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡

✞ አባ ለትጹን የዋህ ✞

=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን
በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን
የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::

+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው
ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት
ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ
የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል
ደረሱ::

+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ
ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት
የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ:
አልምረውም" አላቸው::

+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ::
አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን
መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ:
ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት
አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል
አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ
እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::

+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ
ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::

✞ አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞

=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ
አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት
ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60
ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው
አላየም::

+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል::
በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል::
እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና
በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::

=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት
ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::

=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::ቅዱሳኑንም
አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን
ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::የጻድቅ አፍ ጥበብን
ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::የአምላኩ ሕግ በልቡ
ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                          †                           

🕊        †      የጽድቅ በር     †        🕊

💛

[   እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው .... ! ]

..............................

❝ የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፡ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ ፡ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡

የነፍስን ፆር [ ከዲያብሎስ የሚከፈትን ውጊያና የስጋ ፈቃድን ] ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡ ❞

[  ቅዱስ ዮሐንስ ሃፂር  ]

†   🕊              †                🕊   †

አንድ ወንድም ገና በጧቱ ራበውና ከሦስት ሰዓት በፊት ላለመብላት ከፍላጎቱ ጋር ታገለ፡፡ ሦስት ሰዓት ሲሆን ደግሞ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ልቆይ ብሎ ራሱን አስገደደ፡፡ ስድስት ሰዓት ሲሆን ዳቦውን ቆርሶ ሊበላ ተቀመጠ ፤ ሆኖም "አይ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ልቆይ" አለና እንደገና ተነሣ፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጸሎት ሲያደርስ የዲያብሎስን ኃይል ከእጁ ሥራ ላይ [ ይሠራ ከነበረው ነገር ላይ ] እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው ፣ ረሃቡም ጠፋ፡፡"

[ ከበረሐውያን ሕይወትና አንደበት   ]


         †              †               †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊     ጾ መ ሐ ዋ ር ያ ት     🕊

▷  ❝  በዚያ ጊዜም ይጦማሉ ❞

[   " በመ/ር አምኃ በላይ ... ! "   ]

[                       🕊                       ]
-----------------------------------------------

❝ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን ? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል ፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።

በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም ፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና ፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።

በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም ፤ ቢደረግ ግን ፥ አቁማዳው ይፈነዳል ፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል ፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ❞

[ ማቴ . ፱ ፥ ፲፭ ]


🕊                        💖                     🕊
                             👇
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
††† እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ድምያኖስ †††

††† አባ ድምያኖስ ተወልደው ያደጉት ግብጽ ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ቅዱሳት መጻሕፍትንና በጐ ምግባራትን ተምረዋል:: ዕድሜአቸው ወደ ወጣትነቱ ሲጠጋ ሥርዓተ መነኮሳትን ለማጥናት ወደ ገዳመ አባ ዮሐንስ ሔዱ:: በዘመኑ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ፈተና ሳያልፍ እንዲመነኩስ አይፈቀድለትም ነበር::

አንድ ሰው ሊመነኩስ ካሰበ በትክክል መናኝ መሆኑ ቢያንስ ለሦስት ቢበዛ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት እንዲፈተን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታዝዛለች:: ይኸውም "ሥርዓተ አመክሮ" ይባላል:: ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ መቆየት ከፈለገ ግን ይፈቀድለታል::

በዚህም መሠረት አባ ድምያኖስ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በአጭር ታጥቀው ገዳሙን አገልግለዋል:: ገዳሙም ይገባሃል በሚል ዲቁና እንዲሾሙ አድርጓል:: ከዚህ በኋላ ከአባቶች ተባርከው: ገዳሙንም ተሰናብተው ወጡ:: ነገር ግን የወጡት ወደ ዓለም ሳይሆን ራቅ ወዳለ ገዳም ነው::

የረድዕነት ዘመናቸውን ጨርሰዋልና አዲስ በሔዱበት ገዳም ወደ መደበኛው ገድል ተሸጋገሩ:: ያም ማለት በጾም: በጸሎት: በስግደት: በትሕርምት: በትሕትናና በፍቅር ሙሉ ጊዜአቸውን ማሳለፍ ጀመሩ:: በእንዲሕ ያለ ግብርም ዘመናት አለፉ::

የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ አባ ጴጥሮስ በእረኝነት ሥራ የሚያግዛቸው ሰው እንዲፈለግላቸው በጠየቁት መሠረት ትምሕርትም: ጽሕፈትም: በጐ ምግባራትም የተሟላለት ሰው እንደ አባ ድምያኖስ አልተገኘምና ያለፈቃዳቸው ወደ እስክንድርያ ተወስደው የፓትርያርኩ ረዳት ሆነው ተሾሙ:: በረዳትነት በቆዩበት ጊዜ በወንጌል አገልግሎትና በመንኖ ጥሪት ሕዝቡንና ሊቀ ጳጳሳቱን አስደስተዋል::

ልክ አባ ጴጥሮስ ሲያርፉ ሕዝቡና ሊቃውንቱ በአንድ ድምጽ አባ ድምያኖስን ለፓትርያርክነት መርጧቸዋል::

ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት በዘመነ ፕትርክናቸው ከግል የቅድስና ሕይወታቸው ባለፈ እነዚህን ፈተናዎች በመወጣታቸው ይመሰገናሉ::
1.ሕዝቡ ከሃይማኖታቸው እንዳይወጡና በምግባር እንዳይዝሉ ተግተው አስተምረዋል::

2.በአካል ያልደረሱባቸውን በጦማር (በመልዕክት) አስተምረዋል::

3.በዘመናቸው የተነሱትን መናፍቃን ተከራክረው : የተመለሰውን ተቀብለው : እንቢ ያሉትን አውግዘዋል::

4.ከአንጾኪያ ፓትርያርክ የመጣውን የኑፋቄ ጦማር (መልዕክት) በይፋ ተቃውመው አውግዘዋል::

ለአርባ ሦስት ዓመታት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ያገለገሉት አባ ድምያኖስ ከብዙ ትጋት በኋላ በመልካም ሽምግልና በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ከግብጽ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር ውስጥም አርባ አምስተኛ ሆነው ተመዝግበዋል::

††† ልመናቸው : ክብራቸው : ጸጋ ረድኤታቸው አይለየን::

††† ሰኔ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ድምያኖስ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት : ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. ፳፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from M.A
አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ "እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህን ቆሻሻ አንተ ቤት ላራግፈው?" ቢልህ፣ "ውይ የሚጥልበት ቢያጣ ነው። ባይቸገር ወደ እኔ አይመጣም ነበር" ብለህ ደጅህን ከፍተህ ታስገባዋለህ? በፍጹም፤ እንደውም "እንዴት ብታስበኝ ነው? ምነው ስታየው ቤት አልመሰለህም? እንዴት ሰው በሚኖርበት ቤት ቆሻሻ ካልደፋሁ ትላለህ? ስትል ለጠብ ትጋበዛለህ። መደፈርህ እያንገበገበህ  "እምቢ!" ብለህ ትቆጣለህ። በእርግጥም ያስቆጣል።

ግን ሌላ የሚከፋ ሽታ ያለው ቆሻሻን ጭኖ ለመጣ ባላጋራ እኮ በፈቃድህ የከፈትከው ቤት አለ። "የምን ቤት?" ብለህ ብትጠይቀኝ "ልብህ ነዋ" ብዬ እመልስልሃለሁ፤ "ማን ይኖርበታል?" ካልኸኝም "እግዚአብሔር ነዋ" እልሃለሁ።

አንተ ለመኖሪያ ቤትህ ጽዳት የምትጠነቀቀውን ያህል የያዕቆብ አምላክ ለሚያርፍበት ኅሊናህ ተጠንቅቀህ ታውቃለህ? ሰይጣን ጭኖ የሚያመጣውን የኃጢአት ቆሻሻ ሁሉ እሺ ብለህ ወደ ልብህ በማስገባት የፈጣሪህን መቅደስ ለምን ታቆሽሻለህ? ንጹሑ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ሊያቆሽሽ በመጣ ሰይጣን ላይ እንዴት አልተቆጣህም? ድፍረቱ ለምን አላብከነከነህም?

እግዚአብሔር አንተ ልትኖርበት ከምትፈልገው ንጹሕ ቤት የበለጠ ጽዱ መቅደስ የማይፈልግ ይመስልሃል?

(Dn Abel Kassahun Mekuria )

ምንጭ ፦ ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
2024/06/26 00:05:16
Back to Top
HTML Embed Code: