Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ሊቃውንት ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†   🕊   ጉባኤ ኤፌሶን    🕊   †      

† ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ያከበሩትን: እርሱም ያከበራቸውን ሰዎች 'ቅዱሳን' ትላለች:: ራሱ ባለቤቱ "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ-እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ብሏልና:: [ዼጥ.፩፥፲፭] (1:15) እነዚህንም ቅዱሳን 'መላእክት: አበወ ብሊት: ነቢያት: ሐዋርያት: ሰማዕታት: ጻድቃን: ሊቃውንት: ደናግል: መነኮሳት: ባሕታውያን' ወዘተ. ብለን: ክፍለ ዘመን ሰጥተን በአበው ሥርዓት እናስባለን::

ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም አንዱንና ትልቁን ቦታ ቅዱሳን ሊቃውንት ይወስዳሉ:: 'ሊቅ' ማለት 'ምሑር: የተማረ: ያመሰጠረ: ያራቀቀ: የተፈላሰፈ: በእውቀቱ የበለጠ: የበላይ: መሪ: ሹም: ዳኛ' . . . ወዘተ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል::

ወንጌል ላይም ጌታችን መድኃኔ ዓለም ኒቆዲሞስን "አንተ ሊቆሙ ለእሥራኤል-አንተ የእሥራኤል መምሕር (አለቃ) ነህ" ብሎታል:: [ዮሐ.፫፥፲] (3:10) ስለዚህም 'ሊቃውንት' ማለት በእውቀት ከሁሉ በላይ የሆኑ እንደ ማለት ነው::

ዘመነ ሊቃውንት ተብሎ የሚታወቀው ከ3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ ፮ [6] ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን እንደ እንቁ ያበሩ: ብርሃንነታቸው በሰው ፊት የበራ ብዙ አበው ተነስተዋል:: ቅዱሳን ሊቃውንት ከሌሎች ምሑራን ቢያንስ በእነዚህ ነገሮች ይለያሉ :-

፩. እንደ ማንኛውም ሰው ከተማሩ በኋላ እውቀቱ ይባረክላቸው ዘንድ ጠዋት ማታ በጾምና በጸሎት ይጋደላሉ::
፪. አብዛኞቹ ቅዱሳን ሊቃውንት ገዳማዊ ሕይወትን ጠንቅቀው ያውቃሉ::
፫. ምሥጢር ቢሰወርባቸው ሱባኤ ይገባሉ እንጂ በደማዊ ጭንቅላት አይፈላሰፉም::
፬. ፍጹም መናንያን በመሆናቸው ሃብተ መንፈስ ቅዱስ እንጂ የሚቀይሩት ልብስ እንኳ የላቸውም::
፭. እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቃል ከማስተማራቸው በፊት በተግባር ይኖሯታል::
፮. እረኞች ናቸውና ዘወትር ለመንጋው ይራራሉ::
፯. ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ግፍን ተቀብለዋል::
፰. በኃይለ አጋንንት የመጡ መናፍቃንን ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ለብሰው: መጻሕፍትን አልበው: ጥቅስ ጠቅሰው መክተዋል::
፱. ምግብናቸውንም ፈጽመው ዛሬ በገነት ሐሴትን ያደርጋሉ::

† የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምትቀበላቸው የቅዱሳን ጉባኤያት ፫ [3] ብቻ ናቸው::

፩ኛ. በ፫፻፳፭ [325] (፫፻፲፰ 318) ዓ/ም በኒቅያ ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት ያደረጉትን
፪ኛ. በ፫፻፲፰ [381] (፫፻፸፫ 373) ዓ/ም በቁስጥንጥንያ ፻፶ [150] ው ሊቃውንት ያደረጉትን: እንዲሁም
፫ኛ. በ፬፻፴፩ [431] (፬፻፳፬ 424) ዓ/ም በዚህች ቀን ፪፻ 200ው ሊቃውንት ያደረጓቸውን ጉባኤያት ትቀበላለች::
ይሕስ እንደ ምን ነውቢሉ :-
በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን 2 አካል: ባሕርይ ነው [ሎቱ ስብሐት!] የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ ፪ [2] የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: [ላቲ ስብሐት]

ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ [የቁስጥንጥንያ ንጉሥ] ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ::

ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ፬፻፴፩ [431] ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ፪፻ [200] ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር [ቅዱስ] ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ [የእግዚአብሔር እናቱ] ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን የአምላክ እናት: ዘላለማዊት ድንግል: ፍጽምት: ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሂዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::

† አምላከ ሊቃውንት ዛሬም ያሉንን አባቶች ይጠብቅልን: ያንቃልን:: ከቅዱሳን ሊቃውንት በረከትም አይለየን:: የእመ ብርሃን ፍቅሯንም ያሳድርብን::

🕊

[  †  መስከረም ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱሳን ፪፻ [200] ው ሊቃውንት [በኤፌሶን የተሰበሰቡ]
፪. ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
፫. ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ
፬. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
፭. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፮. ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ

[    †  ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፫. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፭. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፮. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ሰማዕት]
፯. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፰. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

† " ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" † [ሐዋ. ፳፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ዓመታዊ የተዓምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

"በዛቲ ዕለት እግዚአብሔር ገብረ : በእደ ባስልዮስ መንክረ::"
[በዚህች ዕለት እግዚአብሔር በባስልዮስ እጅ ድንቅን አደረገ]


† 🕊 ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ  🕊

† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ አርእስተ ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ [ባስልዮስ የሚሉ አሉ] : እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው ፭  ወንድና ፩ ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ [ቅድስት ማቅሪና] ገዳማዊት ስትሆን ፭ ቱም ወንዶች ዻዻሳት መሆናቸው ነው::

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::

†  🕊 ቅዱስ ባስልዮስ  🕊  † 

ገዳማዊ ጻድቅ: ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ: የብዙ ምዕመናን አባት: የቂሣርያ ሊቀ ዻዻሳት: ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት [ከፍጹምነት] የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ፬ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው::

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::

በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ [በዘመኑ አጠራር ባሪያ] ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ [መተተኛ] ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት ፮ ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::

ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::

በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ " ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን?" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ፵ ቀን በሁዋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ፬ አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ፫ ቀን በሁዋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ፫ ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::

በ፮ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ፱ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::

እንዲህ በ፫: በ፫ ቀናት እየተመላለሰ ለ፲፫ ጊዜ ጠየቀው:: በ፴፱  ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ፵ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ያን ሰው ከመሃል አቁሞ "እግዚኦ በሉ" አላቸው::

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ፵ ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር ፮  ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[ † መስከረም ፲፫ [ 13 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፪. አባ ይስሐቅ ባሕታዊ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. እግዚአብሔር አብ
፪. ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
፫. ፻፱ "99ኙ" ነገደ መላዕክት
፬. ቅዱስ አስከናፍር
፭. "13ቱ" ግኁሳን አባቶች
፮. ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯. አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

† " እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል:: እኔ ወደ አብ እሔዳለሁና:: አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ:: ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ::" † [ዮሐ.፲፬፥፲፪] 

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአቡነ ያሳይ ዘመንዳባ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

†  🕊 አባ አጋቶን ዘዓምድ  🕊

ታላቁ ጻድቅ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩበት ዘመንም ከ፬ ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ ፭ ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው:: በእርግጥ 'አጋቶን ' በሚባል ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ቅድሚያውን ፪ ቱ ይወስዳሉ:: አንደኛው አባ አጋቶን ለ፴ ዓመታት ድንጋይ ጐርሰው የኖሩት አባት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: እኒህኛው 'ዘዓምድ ' ይባላሉ:: ምክንያቱም ለ፶ ዓመታት አንድ ምሰሶ ላይ ያለ ዕረፍት ጸልየዋልና ነው::

አባ አጋቶን ገና ከልጅነታቸው መጻሕፍትን የተማሩ ሲሆኑ ምናኔን አጥብቀው ይፈልጓት ነበር:: በዚህም ራሳቸውን በትሕርምት እየገዙ: በዲቁና ማዕርጋቸውም እያገለገሉ እስከ ፴፭ ዓመታቸው ቆዩ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ 'ይገባሃል' ብለው ቅስናን ሾሟቸው::

የማታ ማታ የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ተምኔተ ልባቸውን ፈጽሞላቸው ወደ በርሃ ሔዱ:: ወቅቱ የግብጽ ገዳማት በቅዱሳን ሕይወት የበሩበት ነውና እዚህም እዚያም አበውና እናቶች ይገኙ ነበር::

አባ አጋቶንም የከዋክብቱ አበው አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም ደቀ መዝሙር ሆነው ገቡ:: አስፈላጊውን የምንኩስና ፈተና ካለፉ በኋላም ምንኩስናን ከእነዚህ አባቶች ተቀበሉ:: በዚያው በገዳመ አስቄጥስ በጽኑ ገድል ተጠምደው ለ፲፭ ዓመታት አገለገሉ::

ጻድቁ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ተጋድሎ ጠዋት ማታእያነበቡ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑ ነበር:: በተለይ የታላቁን ስምዖን ዘዓምድን ገድል ሲያነቡ ሕሊናቸውን ደስ ይለው: ይህንኑ ገድል ይመኙ ነበር:: እድሜአቸው ፶ ዓመት በሞላ ጊዜ በልቡናቸው እንደ አባ ስምዖን ዘዓምድ ለመጋደል ወሰኑ:: ይህን ለገዳሙ አባቶች ቢያማክሯቸው አበው:- "ይበል! ሸጋ ምክር ነው:: እግዚአብሔር ያስፈጽምህ!" ብለው መርቀው አሰናበቷቸው:: አባ አጋቶን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ ከገዳሙ ወጡ:: በጣምም ወደ ዓለም ሳይገቡ: ከዓለም በጣም ሳይርቁ አንድ ረዥም ምሰሶ አገኙና ከላዩ ላይ ወጡ::

ከዚህች ዕለት ጀምረው ጻድቁ ለ፶ ዓመታት ከዚያች ዓምድ ወርደው: ለሥጋቸውም ዕረፍትን ሰጥተውት አያውቁም:: ማዕከለ ገዳም ወዓለም ናቸውና ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት አጽናኝ አባት ሆኑ:: ለአካባቢውም የብርሃን ምሰሶ ሆኑ:: የታመመ ቢኖር ይፈውሱታል:: የበደለውን በንስሃ ይመልሱታል:: ሰይጣን የቋጠረውን ይፈቱታል:: ለራሳቸው ግን ከጸሎት: ከጾምና ከትሕርምት በቀር ምንም አልነበራቸውም::

፩. አጥማቂ ነን እያሉ ሕዝቡን ያስቱ የነበሩ ሰዎችን እየጠሩ እንዲህ የሚያስደርጋቸውን ጋኔን ከእነሱ አስወጥተዋል::
፪. እርሳቸውን ያልሰሙት ግን መጨረሻቸው ጥፋት ሆኗል::
፫. ፍጹም ወንጌልን በሕይወትና በአንደበት መስክረዋል::
፬. ሕዝቡን በንስሃ አስጊጠዋል::
፭. ተግሳጽ የሚገባውን ገስጸዋል::

ጻድቁ አባ አጋቶን ዘዓምድ ከእነዚህ የቅድስና ዘመናት በኋላበተወለዱ በ፻ ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በክብርና በዝማሬ ተቀብረዋል::


†  🕊  አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ  🕊  †

እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ፲፬ ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ፯ ቱ ከዋክብት [አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ] እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::

ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ፲፬ ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ: ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::

ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ፯ቱ አበው በዚያ ነበሩና ፯ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::

አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ፪ቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::

አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::

ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::

አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም ፲፬ ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::

† አምላከ ጻድቃን በምልጃቸው የበዛች ኃጢአታችንን ይቅር ይበለን::

🕊

[  † መስከረም ፲፬ [ 14 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. አባ አጋቶን ዘዓምድ
፪. አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
፫. አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና [ጣና]
፬. ቅዱስ ዴግና ቀሲስ

[  † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. አቡነ አረጋዊ [ዘሚካኤል]
፪. ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫. ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ሙሴ [የእግዚአብሔር ሰው]
፭. አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯. እናታችን ቅድስት ነሣሒት
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
† " ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም:: " † [ማቴ. ፲፥፵፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት እና ለአቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን። †  ]

†በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


† 🕊 ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት  🕊 †  

† በሕገ ወንጌል የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ:: [ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ] ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕ.፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል::

በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ ሰው በርካታ ቅዱሳንን [እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን: ኒቆዲሞስን . ..] አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::

በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ፮ ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ:: ለ፮ ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ:: በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው::

"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ:: [ሉቃ.፯፥፲፰] በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ:: ጌታም ከ፸፪ቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: [ሉቃ.፲፥፲፯]

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል:: በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን [ዽዽስናን] ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ፸፪ቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም:: በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ፯ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ፮ቱ ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ [አስተዳዳሪ] ሆኗል:: ፰ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት: ማሕደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው:: [ሐዋ.፮፥፭]

አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት' ሲባል እንደዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ 'በራት ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለ፩ ዓመት ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ እሰፋ' አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው' ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት::

እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ፫፻ ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋየን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል [የመምሕሩ ርስት ነው] ሔደ:: ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ:: መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ መላእክትም ተሰማ:: ሕዝቡና ዻዻሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ ጽዮን [በተቀደሰችው ቤት] አኖሩት:: እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ፭ ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት:: ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው:: መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ አላት: አምላክ ለዚህ አድሏታልና:: እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ::

ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች:: በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት ፲፯ : ዕረፍቱ ጥር ፩ ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም ፲፭ ቀን ነው::

† 🕊 አቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ 🕊

ጻድቁ በ፲፬ኛው ክ/ዘመን ከተነሱ አበው አንዱ ሲሆኑ ገዳማቸው ደብረ ሐንታ ወሎ ውስጥ ይገኛል:: አቡነ ገብረማርያም በተጋድሏቸው: በተአምራቸውና በወንጌል አገልግሎታቸው ይታወቃሉ:: ይልቁኑ ግን የሚታወቁት ለእመቤታችን በነበራቸው ፍቅር ነው:: ያንን ጥዑም ማሕሌተ ጽጌ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር ሆነው የደረሱ እርሳቸው ናቸውና:: በገዳማቸው ብርሃን እስኪበራ ድረስ በንጹሕ የማኅሌት አገልግሎታቸው ድንግል ማርያምንና ቸር ልጇን አስደስተው: በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

🕊 አባ ጴጥሮስ ዘጠራው 🕊

በደብረ ጠራው: ሠንሠለት ለብለው: ከእህል ተከልክለው: በጾምና ጸሎት ተወስነው ይኖሩ ነበር:: ፈጣሪን ፳፬ ሰዓት "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ እያመሰገኑ ሲርባቸው ደረቅ ሣር ነጭተው ይበሉ ነበር:: ከብዙ ተጋድሎ በኋላም ያረፉት በዚህ ቀን ነው::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
† አምላከ ቅዱስ እስጢፋኖስ በረድኤት ይጐብኘን:: ከወዳጆቹ በረከትም ተካፋዮች ያድርገን::

🕊

[ † መስከረም ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት [ፍልሠቱ]
፪. አቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ
፫. አባ ዼጥሮስ ዘሃገረ ጠራው

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪. ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ [አፈ በረከት]
፫. ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
፬. ቅድስት እንባ መሪና
፭. ቅድስት ክርስጢና

† " እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት::" † [ሐዋ. ፮፥፰-፲፭]


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/09/26 00:55:05
Back to Top
HTML Embed Code: