Telegram Web Link
ለክብርሽ ተደርሶ፥ ለፍቅር የተቆመ፤
ሥሙር ማኅሌትሽ፥ በቸር ተፈጸመ፤
ድንግል እመቤቴ፦
የኛ መከራ ግን፥ አለቅጥ ረዘመ!

እንኳን አደረሰን!

( Deacon Yordanos Abebe)
#ኅዳር_7

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሊቀ_ሰማዕት

ኅዳር ሰባት በዚህችም ቀን የልዳ ሀገር የሆነ የሰማዕታት አለቃ የታላቁ መስተጋድል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ዳግመኛም ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው በውስጧ ድንቆች ተአምራት እንደሚሠሩ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ሊአፈርሳት አሰበ ስሙ አውህዮስ የሚባለውንም መኰንን ከብዙ ሠራዊት ጋር ላከው፤ ያም መኰንን በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ወዳለበት አዳራሽ በትዕቢት ሆኖ ገባ። በሥዕሉም ፊት በብርጭቆ መቅረዝ መብራት ነበረ በቤተ ክርስቲያኒቱና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ እየዘበተ በእጁ በያዘው በትር የመብራቱን መቅረዝ መትቶ ሰበረው የመቅረዙም ስባሪ ወደ ከሀዱው ራስ ደርሶ መታው ራሱንም ታመመ ፍርሃትና እንቅጥቅጥም መጣበት ወድቆም ተዘረረ ባልንጀሮቹም ወደ አገሩ ሊወስዱት ተሸከሙት በክፉ አሟሟትም ተጐሳቊሎ ሞተ ወስደውም ከባሕር ጣሉት ወገኖቹም ወደ ሀገራቸው አፍረው ተመለሱ።

ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ በልዳ ሀገር ያለች የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳት ዘንድ ራሱ ተነሥቶ ሔደ በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መታው ሰባት ዓመት ያህልም ዐይኖቹ ታውረው አእምሮውንም አጥቶ ቁራሽ እንጀራም እየለመነ ኑሮ ሞተ።

ክብር ይግባውና ጌታችንም የቤተ መንግሥቱን ሰዎች አስነሣበት እርሱን አስወግደው ጻድቅ ሰው ቁስጠንጢኖስን በእግዚአብሔር ፈቃድ አነገሡት እርሱም በአዋጅ የጣዖታትን ቤቶች ዘግቶ አብያተ ክርስቲያናትን ከፈተ ለክርስቲያን ወገኖችም በሁሉ ዓለም ተድላ ደስታ ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር)
"ዲያብሎስ በእናንተ ላይ እጅግ ክፉ ነገርን በማምጣት አሳዝኖአችኋልን? እናንተም ኢዮብን አብነት አድርጋችሁ እግዚአብሔር ይመስገን በማለት አሳዝኑት፡፡ ዲያብሎስን ድል ማድረግ ስትሹ ይህን መሣርያ ዘወትር ያዙ፤ ምስጋና፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  †  እንኩዋን ለቅዱስ "ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ †  ]  

🕊 † ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ  †  🕊

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ፯ ዓመታት ስቃይ በሁዋላ ተሰይፏል:: ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ [አንስጣስዮስ] እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም [ልዳ] ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፳ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት [የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ] ሰዎች ዘንዶ [ደራጎን] ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ፸ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ [ዐውደ ስምዕ] ደረሰ::

ከዚያም ለተከታታይ ፯ ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: ፫ ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ "የሰማዕታት አለቃቸው" : "ፀሐይና የንጋት ኮከብ" በሚል ይጠራል::
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ::
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ::" እንዲል መጽሐፍ::

ከ፯ ዓመታት መከራ በሁዋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: ፯ አክሊላትም ወርደውለታል::

ይህቺ ዕለት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ቅዳሴ ቤቱ ናት:: እርሱ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂጥ ዓመታት በሁዋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው: አጽሙን አፍልሠው በዚህች ቀን ቀድሰዋታል::

ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በሁዋላ ተአምረኛ ነውና አንዷን እንመልከት:: በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት [ነገሥታት] መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የ፵፯ ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ::

በ፫፻፭ ዓ/ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ:: የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ላይ ተሳለቀ::

ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው:: እንደ እብድ ሆኖ ሞተ:: ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ:: ይሕን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ:: ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዐይኑን አጠፉት::

እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን [ደወሉን] ለቀቀበት:: ራሱን ቢመታው ደነዘዘ:: የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለ፯ ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮሰ ይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል::

አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት: ከበረከቱም ይክፈለን::


🕊 † ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ †  🕊

በቤተ ክርስቲያን "ጊዮርጊስ" የሚባሉ ብዙ ቅዱሳን አሉ:: ከልዳዊው ቀጥሎም ይህንን ግብጻዊ ሰማዕት እንጠቅሳለን:: ስሙ ጊዮርጊስ የተባለውም በታላቁ ሰማዕት አማላጅነት ስለ ተገኘ ነው::

አባቱ ኅዳር ፯ ቀን የሊቀ ሰማዕታትን ቅዳሴ ቤት ሊያከብር ሒዶ ስለተማጸኑ የሚስቱ ማሕጸን ተከፍቶለት ልጅ ወልዷል:: ስሙንም ጊዮርጊስ ብሎታል:: ባደገም ጊዜ እጅግ ብርቱ ክርስቲያን ሆነ::

የግብጻዊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብርታቱ ምንድን ነው ቢሉ :-ንጹሕ አምልኮቱ ጾምና: ጸሎቱ: በጐ ምጽዋቱ ነው:: "ስም ይመርሕ ኀበ ግብር - ስም ወደ ተግባር ይመራል" እንዲሉ አበው የሰማዕቱን ስም ይዞ እሱም ይሔው እድል ገጠመው::

በአጋጣሚ ወላጆቹ ሲሞቱ የሚኖረው ከከተማው መኮንን ቤት ነበር:: ምክንያቱም የመኮንኑ ሚስት እህቱ ናትና:: ችግሩ ግን መኮንኑ አርማንዮስ ጣዖት አምላኪ: በዚያ ላይ ጨካኝ መሆኑ ነው::

አንድ ቀን ግብጻዊ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመኮንኑን ሴት ልጅ ወደ በርሃ ወስዶ የደብረ ቁስቁዋም መነኮሳትን ዝማሬ አሰማት:: ክርስትናንም አስተማራት:: ይህንን የሰማው መኮንኑ ግን በብስጭት ቅዱስ ጊዮርጊስንና የራሱን ሴት ልጅ በአደባባይ አሰይፏቸዋል:: የክብርን አክሊልም ተቀዳጅተዋል::


🕊  † ቅዱሳን ዘኖቢስና ዘኖብያ † 🕊   

እነዚህ ቅዱሳን እናትና ልጅ ናቸው:: ዘኖብያ እናቱ ስትሆን ዘኖቢስ ደግሞ ወጣት ልጇ ነው:: የቅዱሳኑ ሃገር ደግሞ ተበይስ ትባላለች:: በዘመነ ሰማዕታት ድንቅ በሆነ ሕይወታቸውና ተአምራቸው እንደ ኮከብ አብርተዋል:: ከ፭ ጊዜ በላይም ከተደገሰላቸው የሞት ወጥመድ በእግዚአብሔር ኃይል አምልጠዋል::

" ክርስትናችን አንክድም: ከክርስቶስ ፍቅር አንለይም በማለታቸው :-

፩. ልብሳቸውን ገፈው: በዓየር ላይ ሰቅለው: ደማቸው እስኪንጠፈጠፍ ገረፏቸው:: በክርስቶስ ኃይል ተረፉ::

፪. የእንጨት መስቀሎችን አሰርተው በአደባባይ ቸንክረው ሰቀሏቸው:: ከዚህም ዳኑ::

፫.. ሁለት ወንበሮች ላይ ችንካሮችን ተክለው በዚያ ላይ አስቀመጧቸው:: አሁንም በፈጣሪ ኃይል ዳኑ::

፬. ጥልቅ ጉድጉዋድ ተቆፍሮ: እሳትም ነዶ በዚያ ውስጥ ተጨመሩ:: ቅዱስ መልአክ ግን ወርዶ አጠፋላቸው::

፭. አንዴ ደግሞ በቤት [በውሽባ ቤት] እሳት ነዶ በውስጥ ተጨመሩና ተዘጋባቸው:: እግዚአብሔር ግን ከዚህም ታደጋቸው:: ስለ ክብራቸውም ቅዱስ መልአክ ወርዶ እነሱን አክብሮ: መኮንኑን ዙፋኑን አሸክሞ በአደባባይ አዙሮታል::

አንዴም ጋን አሸክሞ በሁዋላቸው አስከትሎታል:: በነዚህ ሁሉ ድንቆች ብዙ ሕዝብ እያመነ በሰማዕትነት ሙቷል:: በመጨረሻ በዚህ ቀን ዘኖብያና ዘኖቢስ ሲሰየፉ መብረቅ ወርዶ ፶፬ አሕዛብን ገድሏል:: በዚህም መኮንኑ ተገርሞ በክርስቶስ አምኗል::


🕊  †  አባ ሚናስ ዘተመይ †  🕊

ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ጣዕመ ሕይወቱ ድንቅ ነው:: ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው በተክሊል አጋቡት:: ወደ ሙሽራይቱ ገብቶም "እህቴ! ይህ ዓለም ኃላፊ ነውና ለምን በድንግልና አንኖርም?" አላት::

እርሷም በደስታ "ይሁን" አለችው:: ለበርካታ ዓመታትም ቀን ቀን ሥራቸውን ሲሠሩ: እንግዳ ሲቀበሉ ይውላሉ:: ሌሊት ደግሞ ወገባቸውን ታጥቀው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ያድራሉ::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ከዓመታት የቅድስና ሕይወት በሁዋላም ቅዱስ ሚናስ ሚስቱን አስፈቅዶ በርሃ ገብቷል:: በተጋድሎ ሳለም እግዚአብሔር ለእረኝነት መርጦት: ተመይ በምትባል የግብጽ አውራጃ ላይ ዽዽስናን ተሹሟል:: በዚያም እስካረጀ ድረስ ተጋድሎ በዚህች ቀን ዐርፏል::

እንደ ደመና የከበቡን የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አምላክ በቸርነቱ ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[  † ኅዳር ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት [ቅዳሴ ቤቱ]
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ
፫. ቅዱሳን ዘኖቢስና ዘኖብያ [ሰማዕታት]
፬. ቅዱስ ሚናስ ዘተመይ
፭. ቅዱሳን መርቆሬዎስና ዮሐንስ [ጻድቃን ወሰማዕት]
፮. አባ ናሕርው ሰማዕት

[   †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላገዳማዊ
፮. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯. ቅዱስ አግናጥዮስ [ለአንበሳ የተሰጠ]

" የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ:: በመጋዝ ተሰነጠቁ:: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: " [ዕብ.፲፩፥፴፭-፴፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  †  እንኩዋን ለቅዱሳን ኪሩቤል [ዐርባዕቱ እንስሳ] : ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ወአባ ቅፍሮንያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ †  ]


🕊  †  ዐርባዕቱ እንስሳ   †   🕊

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ [፻] : በክፍለ ነገድ አሥር [፲] አድርጉዋቸዋል:: አቀማመጣቸውንም በ፫ ሰማያትና በ፲ ከተሞች [ዓለማት] አድርጉዋል::

መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር: ራማና ኢዮር' ይባላሉ:: አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ :-

፩. አጋእዝት [የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል: አህን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው]
፪. ኪሩቤል [አለቃቸው ኪሩብ]
፫. ሱራፌል [አለቃቸው ሱራፊ]
፬. ኃይላት [አለቃቸው ሚካኤል]
፭. አርባብ [አለቃቸው ገብርኤል]

፮. መናብርት [አለቃቸው ሩፋኤል]
፯. ስልጣናት [አለቃቸው ሱርያል]
፰. መኩዋንንት [አለቃቸው ሰዳካኤል]
፱. ሊቃናት [አለቃቸው ሰላታኤል]
፲. መላእክት [አለቃቸው አናንኤል] ናቸው::

ከእነዚህም ፦ - አጋእዝት : - ኪሩቤል - ሱራፌልና - ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር [በ፫ኛው ሰማይ] ነው:: - አርባብ: - መናብርትና - ስልጣናት ቤታቸው ራማ [፪ኛው ሰማይ] ነው:: - መኩዋንንት : - ሊቃናትና - መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር [በ፩ኛው] ሰማይ ነው::

መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው:: አይራቡም: አይጠሙም: አይዋለዱም: አይሞቱም:: ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው:: ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ: ቅዱስ: ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው:: ምግባቸውም ይሔው ነው::

ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም:: "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ: ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል:: በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ [አገልጋይ] ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም: ለመዓትም ይላካሉ::

ምሕረትን ያወርዳሉ:: ልመናን ያሳርጋሉ:: ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ:: ስነ ፍጥረት [አራቱ ወቅቶች] እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ::

- ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ [ዘካ.፩፥፲፪]
- ምሥጢርን ይገልጣሉ [ዳን.፱፥፳፩]
- ይረዳሉ [ኢያ.፭፥፲፫]
- እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ [መዝ.፺፥፲፩]
- ያድናሉ [መዝ.፴፫፥፯]
- ስግደት ይገባቸዋል [መሳ.፲፫፥፳, ኢያ.፭፥፲፫, ራዕ.፳፪፥፰]
- በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ [ማቴ.፳፭፥፴፩]
- በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ::

ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ደግሞ ትልቁን ሥፍራ ዛሬ የምናከብራቸው ነገደ ኪሩቤል [ዐርባዕቱ እንስሳ] ይይዛሉ:: መንፈሳውያን ከመሆናቸው በላይ መንበረ ጸባኦትን እንዲሸከሙ ስላደላቸው ክብራቸው ታላቅ ነው:: ከመላእክት ወገንም ቅሩባን እነርሱ ናቸው::

ዘወትርም ስለ ፍጥረታት [ሰዎች: እንስሳት: አራዊትና አዕዋፍ] ምሕረትን ይለምናሉ:: ለዚህም ነው በ፬ እንስሳት [በሰው: በንስር: በላምና በአንበሳ] መልክ የተሳሉት:: ቅዱስ መጽሐፍም ስለ እነርሱ ብዙ ይላል:: [ሕዝ.፩፥፭, ራዕ.፬፥፮, ኢሳ.፮፥፩]

በተለይ ግርማቸው እንደሚያስፈራ ተጽፏል:: "ምሉዓነ ዐዕይንት - ዐይንን የተሞሉ" ይላቸዋል:: ይህንንም መተርጉማን "ምሥጢር አዋቂነታቸውንና ግርማቸውን ያጠይቃል" ሲሉ ተርጉመውታል::

ዐርባዕቱ እንስሳን ፬ ሆነው በስዕል ብናያቸውም "ከመ ርዕየተ እለ ቄጥሩ" እንዲል እያንዳንዱ ከወገብ በላይ አራት በመሆናቸው ተሸካሚዎቹ ፲፮ መልክ አላቸው:: በ፪ ክንፋቸው ፊታቸውን: በ፪ቱ እግራቸውን ሸፍነው በ፪ ክንፋቸው ይበራሉ:: ይህም ብዙ ምሥጢር ሲኖረው ዋናው ግን አርአያ ትእምርተ መስቀል ነው::

"፬ቱ" እንስሳ [ኪሩቤል] በሐዲስ ኪዳንም ልዩ ክብር አላቸው:: ፬ቱ ወንጌል ሲጻፍ እየተራዱ ስላጻፉ በስማቸው ተሰይሟል:: ቅዱስ ማቴዎስን ገጸ ሰብእ: ቅዱስ ማርቆስን ገጸ አንበሳ: ቅዱስ ሉቃስን ገጸ ላህም: ቅዱስ ዮሐንስን ገጸ ንስር እየተራዱ ስላጻፏቸው እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ "ዘብእሲ ማቴዎስ": "ዘአንበሳ ማርቆስ": "ዘላሕም ሉቃስ" እና "ዘንስር ዮሐንስ" እየተባሉ ይጠራሉ::

እነዚህ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ስለ መራዳታቸውም በብዙ ገድላትና ድርሳናት ላይ ተጽፏል:: የራሳቸውን "ድርሳነ ዐርባዕቱ እንስሳን" ጨምሮ በገድለ አባ መቃርስና በገድለ አባ ብስንድዮስ ላይ በስፋት ግብራቸው ተጽፏል::

እኛም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ክብራቸውን: ረድኤታቸውንና ምልጃቸውን አምነን ዘወትር እናከብራቸዋለን:: አባቶቻችን እንዲህ እያሉ እንደ ጸለዩ :-

"ሰላም ለክሙ ኪሩባውያን አፍራሱ:
ለመሐይምን ወጻድቅ እንተ ወርቅ አክሊለ ርዕሱ:
ኀበ ዝ አምላክ ለእለ ትጸውርዎ በአትሮንሱ:
ለእለ ጌገዩ ወለእለሂ አበሱ:
ሰአሉ መድኃኒተ ወምሕረተ ኅሡ::" [አርኬ]


🕊 † ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ † 🕊

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ /የመከራ ጊዜ/ ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር:: ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ፵ ዓመታት ዘመቻ አብያተ-መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ::
ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::

የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆንጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ: ቀርነ-ሃይማኖት የቆመው: ብዙ ሥርዓት የተሠራው: ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት: ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት: በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል::

ይህቺ ቀን ታላቁ ንጉሥ በፈለገ ኮቦር ቅዱስ መስቀልን የተመለከተባት ናት:: መክስምያኖስን ሊወጋ ወደ ሮም በተጉዋዘ ጊዜ በሰማይ ላይ መድኅን መስቀል ተዘርግቶ በላዩ ላይ "ኒኮስጣጣን" የሚል በዮናኒ ልሳን ተጽፎበት ተመልክቷል::

ይህንንም "በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ" ማለት ነው ብለው ተርጉመውለታል:: እርሱም በጋሻው: በጦሩ: በሰይፉ: በፈረሱ ላይ የመስቀል ምልክትን አድርጐ ማሕደረ ሰይጣን መክስምያኖስን ድል ነስቶታል:: እኛንም በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን::


🕊  †  አባ ቅፍሮንያ ጻድቅ  †   🕊

ይህ ቅዱስ ሰው በቀደመ ሕይወቱ አረማዊ ነበር:: ነገር ግን በውስጡ ቅንነት ተገኝቶበታልና እግዚአብሔር በቸር አጠራሩ ወደ ቤቱ አመጣው:: አባቱ አረማዊ: በዚያውም ላይ አገረ ገዢ ነበርና ለቅፍሮንያ ይህንኑ እያስተማረ አሳድጐታል::

አንድ ቀን ግን ፈጣሪ ጥሪውን ላከለት:: ይኸውም ገና ወጣት ሳለ የገዳም አበው ያዩትና ትንቢት ይናገሩለታል:: "ይህ ሰው በጐ ክርስቲያን: ምርጥ ዕቃም ይሆናል" ሲሉት እንኩዋን ሌሎቹ ለእርሱ ለራሱም ምንም አልመሰለውም ነበር:: በዚህ መንገድ [በአረማዊነቱ] ዓመታት አልፈው ቅፍሮንያ የከተማው መኮንን [አገረ ገዢ] ሆነ::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
የግብጽ አረማውያን ገዢዎች እንደ ትልቅ ሥራ የሚያዩት አድባራትን ማቃጠል: ገዳማትን መመዝበር ነውና እርሱም ለዚሁ ሥራ ተነሳ:: ሠራዊትን አስከትቶ በሠረገላው ተጭኖ ወደ አንድ ገዳም ደረሰ:: ልክ የገዳሙን መሬት ሲረግጥ ግን በአንዴ ልቡናው ተሰበረ::+ሠራዊቱን ወደ ከተማ አሰናብቶ እርሱ ብቻውንወደ ገዳሙ ዘለቀ:: ወደ አበ ምኔቱም ቀርቦ ሰገደላቸውና እንዲያጠምቁት ተማጸናቸው:: እርሳቸውም አስተምረው አጠመቁት:: በዚያውም መንኖ መነኮሰ::

ለዘመናትም በጠባቡ መንገድ ተጋድሎ ከጸጋ [ከብቃት] ደረሰ:: በአካባቢው ሰውና እንስሳትን የፈጀውን ዘንዶም ባሪያ አድርጐ ለ፲ ዓመታት ገዝቶታል:: ከብዙ ተጋድሎ በሁዋላም በዚህ ቀን ዐርፏል::

አምላከ ቅዱሳን መላእክት እነርሱን ለረድኤት ይላክልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[  †  ኅዳር ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን 4ቱ እንስሳ [ኪሩቤል]
፪. ቅዱስ አፍኒን ሊቀ መላእክት
፫. አባ ቅፍሮንያ ጻድቅ
፬. ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ንጉሥ [ዘምስለ ቅዱስ መስቀል]
፭. ቅድስት እግዚእ ክብራ

[   †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. አባ ብሶይ [ቢሾይ]
፫. አቡነ ኪሮስ
፬. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፭. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ቱ ሐዋርያት]

" በዙፋኑም መካከል: በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በሁዋላ ዓይኖች የሞሏቸው አራት እንስሶች ነበሩ:: ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል:: ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል:: ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው:: አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል:: አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሏቸው::" [ራዕይ.፬፥፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለአበው ቅዱሳን ፫፻፲፰ ቱ ሊቃውንት" ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊    †   ጉባኤ ኒቅያ   †    🕊

በዚህች ዕለት [ኅዳር ፱ ቀን] በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ ፫፻፲፰ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል::

የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: ፳፻፫፻፵፰ ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም ፳፩ ቀን ነበር:: ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና ፫፻፲፰ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: ፫፻፲፰ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት :-
፩. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ [በዘመነ ሰማዕታት ለ፳፪ ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው]
፪. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ [ስለ ቀናች እምነት ለ፶ ዓመታት የተጋደለና ለ፲፭ ዓመታት በስደት የኖረ ነው]
፫. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ [ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው]
፬. ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ [በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው]
፭. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ [ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለ፲፭ ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው]
፮. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ [ከሕጻንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው]
፯. ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን [በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው]
፰. ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ [ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ:
ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው]
፱. ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ [ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው]

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ ፫፻፲፰ቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ: ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው::

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ:: የእርሱ ኑፋቄ [ፈጣሪያችንን ፍጡር ነው ማለቱ] መነሻው ከእርሱ በፊት ነው:: መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው::

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር:: የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር::

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው:: የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች ፪ [፫] ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ::

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ: በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል:: በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል:: ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል:: ድያድርስ ሉቅያኖስን: ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል::

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ: በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ:: በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት
ቅዱስ ጴጥሮስ [አስተማሪው] መከረው:: ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው::

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ
እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው:: እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም [ሎቱ ስብሐት!] ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ [ኢሳ.፱፥፮, መዝ.፵፮፥፭, ፸፯፥፷፭, ዘካ.፲፬፥፬, ዮሐ.፩፥፩, ፲፥፴, ራዕይ.፩፥፰, ሮሜ.፱፥፭] አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከ፪ቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ [ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ] ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውነት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

ከሚያዝያ ፳፩ እስከ መስከረም [፳፩]  ተጠቃለው ገቡ:: በ፫፻፳፭ ዓ/ም [በእኛው በ፫፻፲፰ ዓ/ም] ለ፵ ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በ፬ቱ ፓትርያርኮች [እለእስክንድሮስ: ሶል ጴጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ] መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት:: በጉባኤው መጨረሻም :-

፩. አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ::
፪. ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ::
፫. ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ::
፬. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ::
፭. በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ::

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ ፫፻፲፱ኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል:: አባቶችም ሥራቸውን
ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል::

በየዘመኑም ዐርፈው ለክብረ መንግስተ ሰማያት በቅተዋል:: እኛም እነሆ "አባቶቻችን
መምሕሮቻችን :
መሠረቶቻችን :
ብርሃኖቻችን :
ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[   † ኅዳር ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱሳን ፫፻፲፰ ቱ ሊቃውንት
፪. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፬. አባ ይስሐቅ ሊቀ ጳጳሳት
፭. ሊቁ አካለ ወልድ

[    † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. አባ በርሱማ ሶርያዊ [ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት]
፪. አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
፫. የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፬. አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
፭. ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

" እውነት እላቹሃለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል:: በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል:: ደግሞ እላቹሃለሁ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል:: ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና::" † [ማቴ.፲፰፥፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
               †      

         

" የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።" [ማቴ.፲፩፥፲፭]



         †              †               †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡  †

† ኅዳር ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †


🕊 † ቅድስት ሶፍያ ወቅዱሳት አንስት † 🕊

እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ [ቡሩካት] እናቶቻችን እንዘክር:: "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል:: እርሷ 'ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት እምቡሩካን: ኅሪት እምኅሩያን ናትና::

ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች:: እርሷ እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ ናትና::

እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት: ልዩ" ማለታችን ነው::

፩. "ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች ሰዎች [ቅዱሳን] ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ: ከገቢር: ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው: ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: [ተአምረ ማርያም]

፪. "ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::

"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: [ቅዱስ ያሬድ] ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: [መጽሐፈ ቅዳሴ]

፫. ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው:: እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

፬. እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና ወልዳ ወተትን [ሐሊበ ድንግልናዌን] ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና::

የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት እናቶቻችንን እንመልከት:: እናቶቻችን ስናከብር የምንጀምረው በቅድስት ሔዋን ነው:: ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ በጐ ነገሯ: ደግነቷ: ንስሃዋ አይነገርላትም:: ሆኖም እናታችን ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት::

ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና:: "ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ" እንዲል:: [ድጓ]

ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል: እድና: ሣራ: ርብቃ: አስኔት: ሲፓራ: ሐና: ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን በበጐው መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል:: በዘመነ ሥጋዌም ቅዱሳቱ ሐና: ኤልሳቤጥ: ማርያም: ሶፍያ: ሰሎሜ: ዮሐና እና ፴፮ [36] ቱ ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል::

ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ ፪ ሺህ ዓመታት የተነሱ አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም:: በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ: ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ: አጋንንቸትን የረገጡ: በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን ቤተ ክርስቲያን አፍርታለች::

ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን:: አንድም እናምናለን:: ግን ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው የበርካታ እህቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት ነው:: ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል::

ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እህቶቼ! አንድ ነገር ልንገራችሁ:: በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ: አጊጠው በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ: ለብዙ ምዕመናንም የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ::

የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው:: አፈር በልቷቸዋል:: ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል:: በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ በዘለዓለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል: በጥልቁ ውስጥ አሉ::

እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ:: ይህ ዓለም ጠፊም: አጥፊም ነውና:: እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ በኋላ ለ100 ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና:: ምርጫችን ዘለዓለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን::


🕊 †  " እለ ቅድስት ሶፍያ "  † 🕊

ቅድስት ሶፍያና አብረዋት በዚህ ዕለት የሚከበሩ ቅዱሳት አንስት በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም የነበሩ ክረስቲያኖች ናቸው:: አብዛኞቹ መልክ [ደም ግባት] ከጠባይ ጋር የተስማማላቸው ነበሩ:: ነገር ግን ከምድራዊው ክብር ሰማያዊውን መርጠው ለመንፈሳዊው ሙሽርነት ወደ ገዳም ገቡ::

ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል በጸጋና በሞገስ: በትምሕርትም የምትበልጥ ቅድስት ሶፍያ ናትና እመ ምኔት አድርገው ሾሟት:: እርሷም ለገዳሙ በጐውን ሥርዓት ሠራች:: ሁሉም [ደናግሉም መነኮሳይያቱም] በአንድነት ይጾማሉ: ይጸልያሉ: ይሰግዳሉ: የቅዱሳንን ተጋድሎ ያነባሉ:: ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉ::

እርስ በርስ ደግሞ ፈጽመው ይፋቀራሉ:: በዚህ ሕይወት አንዳንዶቹ እስከ ፸ ዓመት ቆዩ:: የቅድስናቸው ዜና ሲሰማ በሮም ግዛት ያሉ ወጣት ሴቶች እየመጡ ይቀላቀሏቸው ነበር:: ቅድስት ሶፍያም የሕይወትን መንገድ ታሳያቸው ነበር::

ከዚህ ሁሉ በኋላ ከሐዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ለጦርነት ወደ ፋርስ ሲሔድ ስላያቸው ባንድነት ሰብስቦ ሁሉንም በሰይፍ አስመታቸው:: ቅድስት ሶፍያም አብራ ሰማዕት ሆነች:: ስለ ቅዱሳኑ የሚበቀል ጌታም ቅዱስ መርቆሬዎስን ልኮ በጦርነቱ መካከል በጦር ወጋው:: ዑልያኖስ ወደ ዘለዓለም ኩነኔ ሲሔድ: ቅዱሳት አንስት ወደ ገነት ሔደዋል::


" ባሕረ ሐሳብ "

ዳግመኛ በዚህ ቀን: በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ባሕረ ሐሳብ በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቷል:: ሊቁ ቅዱስ ድሜጥሮስ [የግብጽ ፲፪ኛ ፓትርያርክ] መንፈስ ቅዱስ ቀመረ ባሕረ ሐሳብን ገልጾለት በዓለም ላሉ ሊቃነ ዻዻሳት ልኮላቸው በዚህች ዕለት በሮም ከተማ ተሰበሰቡ::

ሊቃውንትም ሐዋርያት ካስተማሩት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ቢያገኙት በደስታ ተቀብለውታል:: እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ለ፩ ሺህ ፯ መቶ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን እየተገለገለችበት ይገኛል::

የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ዛሬም እንደ እነርሱ ያሉትን አያሳጣን:: በጸሎታቸው ምሮ ከበረከታቸው ይክፈለን::

🕊

[ ኅዳር ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፪. ደናግለ ሮሜ [ሰማዕታት]
፫. ቅዱስ ዻውሎስ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ
፭. ጉቡዓን ኤዺስ ቆዾሳት

[ ወርኀዊ የቅዱሳን  በዓላት ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫. አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፭. ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፮. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፯. ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ::" [፩ዼጥ.፫፥፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

💖                  🕊                   💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/20 01:44:41
Back to Top
HTML Embed Code: