Telegram Web Link
እመምኔት ሆነች እመምኔት ከሆነች በኋላ በግል ፀባዩዋ ላይ የታየ ለውጥ አልነበረም እንደድሮ ትህትናዋን ለብሳ እናቶችን ታገለግል ነበር።የቅዱስ ፓኩሚየስን ( ጳጉሚስ) የገዳማዊ ኑሮ ሥርዓት እንደገና በስራ ላይ እንዲውል ያደረገች ቅድስት ናት፡፡ካለችበት ቦታ ወደ ፈለገችው ቦታ ልክ እንደቀሙት ቅዱሳን ወዲያውኑ ሰከንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ትደርስ ነበር ገነት እና የተሰወሩ የቅዱሳን ያሉበትን ቦታ በየጊዜው ትጎበኝ ነበር ።ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ድንግል እናቱ እና ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ ከሌሎች ብዙ ቅዱሳን ጋር መጥተው ያረጓጓት ነበር።የሰዎችን ችግር ማንም ሳይነግራት አውቃ እስከነ መፍትሄው ነግራ ታጽናናቸው ነበር።በሽተኞችን ትፈውስ ነበር ያዘነውን ታረጋጋ ነበር ገዳሙን ከነረበት ችግር አላቃ ወደ ትልቅ ገነትነት ለውጣዋለች ።

እናም ብዙ ልጆችን(መነኮሳያት) አፍርታ እነርሱም እንደእርሷ የበቁ ለመሆን ችለዋል፡፡መሞት አይቀርምና ገዳሙን በደንብ ካስተደረች በኋላ በክብር አርፋች፡፡ጸሎትና በረከቷ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በታላቋ እናት ታማቭ ኢሪኒ ጸሎት ይማረን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

✞ ጥቅምት ፳፩ [ 21 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞


†  🕊   እግዝእትነ ማርያም  🕊   †

እመቤታችን ድንግል ማርያም የወልደ እግዚአብሔር እናቱ ናትና ሁሉን ትችላለች:: እርሱን ከሃሊ [ሁሉን ቻይ] ካልን እርሷን "ከሃሊት" ልንላት ይገባል:: ልክ ልጇ ሁሉን ማድረግ ሲችል በትእግስት ዝም እንደሚለው እመ ብርሃንም ስንት ነገር እየተደረገ: በእርሷ ላይም አንዳንዶቹ ስንት ነገርን ሲናገሩ እንደማትሰማ ዝም ትላለች::

እኛ ኃጥአን ንስሃ እስክንገባ ድረስም "ልጄ! የዛሬን ታገሣቸው?" እያለች ትለምንልናለች:: ቸሩ ልጇም ሊምረን እንጂ ሊያጠፋን አይሻምና "እሺ እናቴ!" እያለ ይኼው በዚህ ሁሉ ክፋታችን እስከ ዛሬ ድረስ አላጠፋንም::

- ቸር ነው
- መሐሪ ነው
- ይቅር ባይ ነው
- ታጋሽ ነው
- ርሕሩሕ ነው
- ቂምም የለውም:: በንስሃ ካልተመለስን ግን አንድ ቀን መፍረዱ አይቀርምና ወገኖቼ ንስሃ እንግባ: ወደ እርሱም እንቅረብ::

ይህቺ ዕለት ለእመቤታችን እሥረኞችን የምትፈታባት ናት:: የሰው ልጅ በ፫ ወገን እሥረኛ ሊሆን ይችላል:: በሥጋዊው :- አጥፍቶም ሆነ ሳያጠፋ ሊታሠር ይችላል:: በመንፈሳዊው ግን ሰው በኃጢአት ማሠሪያ የሚታሠረው በጥፋቱ ብቻ ነው::

ሌላኛው ማሠሪያ ደግሞ ማዕሠረ ደዌ [በደዌ ዳኝነት] መታሠር ነው:: መታመም የኃጢአተኛነት መገለጫ አይደለም:: ምክንያቱም ከቅዱሳን ወገን ከ፹ % [ፐርሰንቱ] በላይ ድውያን ነበሩና::

ታዲያ በዚህች ዕለት እመ በርሃን 3ቱንም ማሠሪያዎች እንደምትፈታ እናምናለን:: በእሥር ቤትም: በኃጢአትም ሆነ በደዌ ማሠሪያ የታሠርን ሁላችን በዚሁ ዕለት እንድትፈታን የአምላክ እናትን እንለምናት::

በ፫ቱም ማሠሪያዎች የታሠሩ ወገኖቻችንንም እያሰብን "ይባእ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን-የእሥረኞች ጩኸት ወደ አንተ ይድረስ" እያልን [መዝ.፸፰፥፲፩] ልንጸልይ ይገባል::

- እመ ብርሃንንም እንደ ሊቃውንቱ :-

"እማእሠረ ጌጋይ ፍትሕኒ ወላዲተ ክርስቶስ አምላክ:
እምነ ሙቃሔ ጽኑዕ ወእማዕሠር ድሩክ:
ከመ ፈታሕኪዮ ዮም ለማትያስ ላዕክ::" እንበላት::


†  🕊   ቅዱስ አልዓዛር ሐዋርያ  🕊  † 

ቅዱስ አልዓዛር በሃገረ ቢታንያ ከእህቶቹ ማርያና ማርታ ጋር ይኖር ነበር:: ሦስቱም ድንግልናቸውን ጠብቅው ጌታችንን ያገለግሉት ነበርና አልዓዛርን ከ፸፪ቱ አርድእት ማርያና ማርታን ደግሞ ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል::

በወንጌል ጌታችን ይወዳቸው እንደነበር ተገልጧል:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወድ የሚያበላልጥ ሆኖ አይደለም:: ይልቁኑ በምሥጢር እነርሱ ተወዳጅ የሚያደርጋቸውን ሥራ ይሠሩ እንደነበር ሲነግረን ነው እንጂ::

ቅዱስ መጽሐፍ እንደነገረን ጌታችን በነአልዓዛር ቤት በእንግድነት ይስተናገድ ነበር:: በመጨረሻዋ ምሴተ ሐሙስም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሐዋርያቱ ያቀበላቸው በእነዚህ ቅዱሳን ቤት ውስጥ ነው::

ቅዱስ አልዓዛር በጽኑዕ ታሞ አርፏል:: ቅዱሳት እህቶቹ ማርያና ማርታ ከታላቅ ለቅሶ ጋር ዕለቱኑ ቀብረውታል:: [ዮሐ.፲፩]

ቸር ጌታችን ክርስቶስ ከ4 ቀናት በኋላ ሊያስነሳው ይመጣል::

ለስም አጠራሩ ስግደት: ክብር: ጌትነት ይድረሰውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ባረፈ በአራተኛው ቀን ወደ ቢታንያ ደረሰ:: ማርታ ቀድማ ወጥታ ከእንባ ጋር ተቀበለችው::

'አዳም ወዴት ነህ' ያለ [ዘፍ.፫] የአዳም ፈጣሪ 'አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት' አለ:: ቸርነቱ: ባሕርዩ ያራራዋልና ማርያም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አብሮ አለቀሰ::

ከዚያም በባሕርይ ስልጣኑ "አልዓዛር አልዓዛር" ብሎ አልዓዛርን አስነሳው:: ይሕች ተአምርም በአይሁድ ዘንድ ግርምት ሆነች:: ለጌታም የሞት ምክንያት አደረጉዋት:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታስተምራለች:: [ዮሐ.፲፩፥፩ -ፍጻሜው]

ቅዱስ አልዓዛር ጌታችን ካስነሳው በኋላ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ [ቁጥሩ ከ፸፪ቱ አርድእት ነውና] : ለ፵ ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ: በ፸፬ ዓ/ም አካባቢ ቆዽሮስ ውስጥ አርፏል::


†    🕊   ፍልሠት   🕊   † 

ይህቺ ዕለት ለቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ስትሆን ይህ የተደረገውም በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ቅዱሱ ያረፈው ቆዽሮስ ውስጥ ነው:: ግን ባልታወቀ ጊዜና ምክንያት ወደ ኢየሩሳሌም ሒዷል::

አንድ ቀንም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲቆፍሩ አንድ አንድ ሳጥን አገኙ:: በላዩ ላይ ደግሞ "ይህ የጌታ ወዳጅ የአልዓዛር ሥጋ ነው" የሚል ጽሑፍ አግኝተው ደስ ተሰኝተዋል:: በታላቅ ዝማሬና ፍስሐም ከኢየሩሳሌም ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሠውታል::

የጌታችን ቸርነቱ: የአልዓዛር በረከቱ ይድረሰን::


†  🕊 አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም 🕊  †

እኒህ ጻድቅ ሰው ግብጻዊ ሲሆኑ በሰፊው የሚታወቁት በኢትዮዽያና በኢየሩሳሌም ነበር:: ገና በወጣትነት የጀመሩትን የተጋድሎ ሕይወት ገፍተው በበርሃ ሲኖሩ የወቅቱ የግብጽ ሲኖዶስ ከበርሃ ጠርቶ የኢየሩሳሌም ዻዻስ እንዳደረጋቸው ይነገራል::

በቅድስት ሃገርም በንጽሕናና በመንኖ ጥሪት ወንጌልን እየሰበኩ ኑረዋል:: አባ ዮሐንስ የነበሩበት ዘመን ፲፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የወቅቱ የኢትዮዽያ ንጉሥ ደጉ አፄ ዳዊት ነበሩ::

ንጉሡ የግብጽ ክርስቲያኖችን ደም ለመበቀል [በወቅቱ ከሊፋዎች ያሰቃዩዋቸው ነበር) እስከ ላይኛው ግብጽ ወርደዋል:: በሃገር ውስጥ ያሉ ተንባላት አባሪዎቻቸውንም ቀጥተዋል:: በዚህ የተደናገጠው የግብጹ ሡልጣን 'አስታርቁኝ' ብሎ ስለ ለመነ ለእርቅ የተመረጡ አባ ዮሐንስና አባ ሳዊሮስ ዘምሥር ናቸው::

እነዚህ አባቶች በ፲፫፻፺ዎቹ አካባቢ ወደ ኢትዮዽያ ከመጡ በኋላ አልተመለሱም:: ምክንያቱም ደጉ አፄ ዳዊት እጅግ ስለ ወደዷቸው 'አትሔዱም' ብለው ስላስቀሯቸው ነው:: እንዲያውም ለግማደ መስቀሉ መምጣት ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉት አባ ዮሐንስ ሳይሆኑ አይቀሩም:: ዛሬ የጻድቁ ዕረፍታቸው ነው::

አምላከ ቅዱሳን ስለ ድንግል እናቱ ብሎ ከኃጢአት ሁሉ ማሠሪያ ይፍታን:: የወዳጆቹን በረከትም አያርቅብን::

🕊

[  † ጥቅምት ፳፩ [ 21 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. እግዝእትነ ማርያም
፪. ቅዱስ አልዓዛር ሐዋርያ
፫. አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
፬. ቅዱስ ኢዩኤል ነቢይ
፭. ቅዱስ ማትያስ ረድእ

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪. አበው ጎርጎርዮሳት
፫. አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬. አቡነ አምደ ሥላሴ
፭. አባ አሮን ሶርያዊ
፮. አባ መርትያኖስ ጻድቅ

" ጌታ ኢየሱስም 'ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?' አላት... ይሕንም ብሎ በታላቅ ድምጽ 'አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና' ብሎ ጮኸ:: የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ:: ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ:: ጌታ ኢየሱስም 'ፍቱትና ይሂድ ተውት' አላቸው::" [ዮሐ.፲፩፥፵-፵፬]


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
#ቅዱስሲኖዶስ

" በጦርነትና በግጭት የመጣ ሰላም፣ የተገነባ ሀገር የለም !! ... ችግሩ በእርቅ እንዲፈታ ለሁሉም ወገኖቻችን የሰላም ጥሪ እናቀርባለን " - ቅዱስ ሲኖዶስ

የጥቅምት 2017 ዓ/ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ተጠናቋል።

ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት 11 እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ መደበኛ ስብሰባውን ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል።

የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎ በቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ተሰጥቷል።

ከመግለጫው የተወሰደ ፦

" በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየተከሰተ ባለው የሰላም እጦት፣ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ፣ አካል እየጎደለ፣ ማኅበራዊ ትሥሥር እየተናደ፣ ሰብአዊ ክብር እየተጎዳ፣ መብት እየተጣሰ፣ በዜጎች ላይ ሥጋትና አለመረጋጋት እየበዛ ሀብትና ንብረት እየወደመ ስለሆነ ጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ 

ስለሆነም በጦርነትና በግጭት የመጣ ሰላም፣ የተገነባ ሀገር የለምና በሀገራችን እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ካለፈው በመማር በጥበብ፣ በማስተዋልና በሰለጠነ አካሄድ በሰላማዊ መንገድ በመወያየት ችግሩ በእርቅ እንዲፈታ ለሁሉም ወገኖቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ጥሪውን በአጽንኦት ያቀርባል፡፡ "


(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት)

/ ሙሉ መግለጫ ከላይ ተያይዟል /

@tikvahethiopia
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ✞

✞ ጥቅምት ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞


†  🕊  ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ  🕊  † 

✞ ቅዱስ ሉቃስ :-

- ሐዋርያ ነው
- ወንጌላዊ ነው
- ሰማዕት ነው
- ዓቃቤ ሥራይ [ዶክተር] ነው
- የጥበብ ሰው [ሰዓሊ] ነው

- ዘጋቢ [የሐዋርያትን ዜና ሕይወት የጻፈ] ነው:: ይሕስ እንደምን ነው ቢሉ :-

በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን መነሻ አካባቢ: በተወደደች የጌታ ዓመት ከእሥራኤላውያን ወገኖቹ ቅዱስ ሉቃስ ተወልዷል:: ያደገውም መቄዶንያ አካባቢ ነው:: ጌታችን ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምር ከተከተሉት የ፭ ገበያ ሕዝብ መካከል ፻፳ውን ለቤተሰብነት መምረጡ ይታወቃል::

ታዲያ እንዲጠቅም አውቆ ቅዱስ ሉቃስን ከ፸፪ቱ አርድእት ደምሮታል:: ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ለ፫ ዓመት ከ፫ ወር: ከዋለበት እየዋለ: ካደረበትም እያደረ የቃሉን ትምሕርት: የእጆቹን ተአምራት በጥሞና ይከታተል ነበር::

ጌታችን ለዓለም ድኅነት ተሰቅሎ: ሙቶ: ከተነሳ በኋላ ስለዚህ ቅዱስ የሚናገር አንድ የወንጌል ክፍል እናገኛለን:: በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ላይ ከምናያቸው የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ይህ ቅዱስ እንደ ሆነ አባቶች አስተምረውናል::

በእርግጥ 'ቀለዮዻ' የሚለው ስም በዘመኑ የብዙዎች መጠሪያ ቢሆንም እርሱም ጌታን ከመከተሉ በፊት በዚህ ስም ይጠራ እንደ ነበር ይታመናል:: በወቅቱ ታዲያ ፪ቱ ደቀ መዛሙርት [ሉቃስና ኒቆዲሞስ] ወደ ኤማሁስ ሲሔዱ ጌታ መንገድ ላይ ተገልጦ እያጫወታቸው አብሮ ተጉዟል::

እነርሱም ማንነቱን አላወቁምና ስለ ራሱ ለራሱ እየሰበኩለት ተጉዘዋል:: ከሐዘናቸው ብዛት ማስተዋል ተስኗቸው: ቀቢጸ ተስፋም ወሯቸው ነበርና መድኃኒታችን ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ተረጐመላቸው::

በዚህ ጊዜም ከነገሩ ማማር: ከምሥጢሩ መሥመር ጋር እየገረማቸው ልቦናቸው ይቃጠል [ይቀልጥባቸው] ነበር:: "አኮኑ ይነድደነ ልበነ" እንዲል:: ወደ ኤማሁስ ሲደርሱ ግን ደጐች ናቸውና "በቤት ካላደርክ: ራት ካልበላህ" ብለው ግድ አሉት::

በማዕድ ሰዓት ግን ቡራኬውን ሰጥቷቸው: ቸር አምላክነቱን ገልጦላቸው ተሰወራቸው:: እነርሱም በሐሴት ከኤማሁት ተመልሰው እየሮጡ ኢየሩሳሌም ደርሰው ትንሳኤውን ሰበኩ::

የመንገዱ ርዝመትም አልታወቃቸውም ነበር:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሉቃስ እንደ ሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ: መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::


†   🕊   ቅዱሱ ዶክተር  🕊    †

✞ በትውፊት ትምሕርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከመከተሉ በፊት ሥራው ሐኪምነት [ዶክተር] ነበር:: በዚህም አበው "አቃቤ ሥራይ / ባለ መድኃኒት" ይሉታል:: በተሰጠው ሙያም ብዙዎችን አገልግሏል::

የጌታ ደቀ መዝሙር ከሆነ በኋላ ደግሞ "አቃቤ ሥራይ ዘነፍስ-የነፍስ ሐኪም" ተብሏል:: እንዲያውም አባቶቻችን ሐዋርያትን ያክማቸው ነበር ይባላል:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት አብዛኞቹ በሽተኞች ነበርና ነው:: ከደግነታቸው የተነሳም እልፍ አእላፍ ድውያንን በተአምራት ሲፈውሱ እነርሱ ግን በስቃይ ይኖሩ ነበር::

ሕመማቸው ሲጠናባቸው ግን ቅዱሱ ዶክተር ሉቃስ ይራዳቸው ነበር:: ይሕንንም ቅዱስ ዻውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ላይ "የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ: ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል" ሲል ገልጾታል:: [ቆላ.፬፥፲፬]


†   🕊   ዘጋቢው ሐዋርያ  🕊   †

ቅዱስ ሉቃስ እንደ ዛሬው ነገሮች ምቹ ባልነበሩበት ዘመን እጅግ አድካሚ የሆነ ጉዞ አድርጐ የሐዋርያትን ዜና ሕይወት ዘግቦልናል:: ልክ ወንጌሉን ለታኦፊላ [ቴዎፍሎስ] ደቀ መዝሙሩ እንደ ጻፈለት ግብረ ሐዋርያትንም ለእርሱ በትረካ መልክ አቅርቦለታል::

ሲጽፍለትም "ሰማሁ" እያለ ሳይሆን: አብሮ እያለ ያየውንና የተሳተፈበትን ነው:: አተራረኩም በአንደኛና በ፫ኛ መደብ አድርጐ እያቀያየረ ነው:: ማለትም አንዳንዴ "እኛ" እያለ ሌላ ጊዜ ደግሞ "እነርሱ" እያለ ነበር የሚተርክለት::

መጽሐፉም ፳፰ ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ ዕርገት ጀምሮ በኢየሩሳሌምና በአሕዛብ የነበረውን ስብከተ ወንጌል ገልጦ: የቅዱስ ዻውሎስን ጉዞዎች በሰፊው ዳስሶ ይጠናቀቃል::


†  🕊  ወንጌላዊው ሐዋርያ 🕊   †

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን እንዲጽፉ ከተመረጡ [ከተፈቀደላቸው] ሐዋርያት አንዱ ነው:: በቤተ ክርስቲያንም "ዘላሕም" እየተባለ ይጠራል:: ለዚህም ምክንያቱ :-

፩. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት: በላምና በአህያ መካከል መወለዱን በመጻፉ
፪. ጌታችንን "መግዝአ ላሕም-የሚታረድ ሜልገች [ላም]" ብሎ በመግለጹ እና
፫. ከ፬ቱ እንስሳ [ኪሩቤል] አንዱ [ገጸ ላሕም] ይራዳው: ይጠብቀውም ስለ ነበር ነው::

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በ፳፪ኛው ዓመት ሲሆን ይኼውም በ፶፮ ዓ/ም አካባቢ ማለት ነው:: ሲጽፍም ብቻውን አልነበረም:: ልክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር እንደ ሆነው ሁሉ: ቅዱስ ሉቃስም የጻፈው ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ጋር ነው:: ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት አብረው ለስብከተ ወንጌል ተጉዘዋልና::

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ በነ ዘካርያስ ቤተሰብ ጀምሮ: ብሥራተ ገብርኤልን: ክብረ ድንግል ማርያምን: የጌታን ልደት: እድገት: መጠመቅ: ማስተማር: መሰቀል: መሞት: መነሳትና ማረግ በቅደም ተከተል ይተርክልናል::


†  🕊 ጥበበኛው [ሰዓሊው] ሐዋርያ 🕊  †

ቅዱስ ሉቃስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች ሌላኛው ደግሞ ጐበዝ ሰዓሊ የነበረ መሆኑ ነው:: በሐዲስ ኪዳንም የመጀመሪያውን የእመቤታችንን ስዕል [ምስለ ፍቁር ወልዳን] የሳለው እሱ ነው::

አንድ ቀን የአምላክ እናት ባለችበት ከጌታ አስፈቅዶ የሳላት ስዕለ አድኅኖ ሥጋን የለበሰች: ከፊቷ ወዝ የሚወጣ: የምታለቅስ: ስትወጋ የምትደማና ድውያንን የምትፈውስ ሆና ተገኝታለች:: ይህች ስዕል ዛሬ ሃገራችን ኢትዮዽያ ውስጥ አለች ይባላል::


†   🕊  ሰማዕቱ ሐዋርያ  🕊   †

ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ባለ ሕይወት ሲመላለስ በትጋት [ያለ ዕረፍት] ወንጌልን እየሰበከ ነበር:: በ፷፮ እና በ፷፯ ዓ/ም ብርሃናተ ዓለም ዼጥሮስ ወዻውሎስ በኔሮን ቄሣር እጅ ሲገደሉ የሮም ግዛት ክርስቲያኖች ኃላፊነት በእርሱ ላይ ነበረ::

ከወንጌሉና ግብረ ሐዋርያቱ ባለፈ በመልእክታት: አንድም እየዞረ ክርስቲያኖችን አጸና: አሕዛብንም አሳመነ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ዝናውን የሰማው ኔሮን ሊገድለው ፈለገ:: በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሉቃስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሲላስ የሚባለውን ሽማግሌ መርጦ መጽሐፎቹን ሁሉ አስረከበው::

በድፍረትም ወደ ኔሮን ቄሣር ቀርቦ ተናገረው:: ንጉሡም "ክርስቶስን አምልኩ የምትል ቀኝ እጅህ መቆረጥ አለባት" ብሎ እጁን ከትክሻው በሰይፍ ለይቶ መሬት ላይ ጣለው:: ሁሉ ሰው ሲደነግጥ ቅዱሱ ተጐንብሶ የወደቀች እጁን አነሳትና እንደ ነበረችው አደረጋት::

በዚያ የነበሩ አሕዛብም "ግሩም" አሉ:: መልሶ ግን "አሁን እጄ ሥራዋን ስለ ጨረሰች አልፈልጋትም" ብሎ እንደ ገና ለይቶ ጣላት::
"ከመ ያርኢ ኃይለ ቅድመ ኔሮን ወተዓይኑ:
አስተላጸቃ ወሌለያ ለምትርት የማኑ:
እስመ ላዕሌሁ ተሰውጠ ለክርስቶስ ስልጣኑ::" እንዲል::

በዚህ ጊዜም ይህንን ድንቅ ያዩ ፬፻፸፯  ያህል አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል:: የስብከት ዘመኑም ከ፴፮ ዓመታት በላይ ነው::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
✞ አምላከ ቅዱስ ሉቃስ ምሥጢሩን: ፍቅሩን: ጥበቡን ይግለጽልን:: ከሐዋርያው በረከትም ያሳትፈን::

🕊

[   † ጥቅምት ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ሲላስ አረጋዊ [የቅዱስ ሉቃስ ረድእ]
፫. ቅዱስ ታኦፊላ
፬. ፬፻፸፯ "477" ሰማዕታት [የቅዱስ ሉቃስ ማሕበር]

[  †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል መላእክ
፪. ቅዱስ ደቅሲዮስ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፫. አባ እንጦኒ [የመነኮሳት አባት]
፬. አባ ጳውሊ
፭. ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት

" የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ! ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን: በእኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ: እኔ ደግሞ ስለ ተማርከው ቃል እርግጡን እንድታውቅ: በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ:: " [ሉቃ.፩፥፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት አባ ዮሴፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊 ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት አባ ዮሴፍ 🕊 

† በእስክንድርያ [ግብጽ] ሊቀ ዽዽስናን ከተሾሙና በጐ ሥራን ከሠሩ አበው አንዱ አባ ዮሴፍ ነው:: እርሱ ለግብጽ ፶፪ኛ ፓትርያርክ ነውና በ9ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ እንደ ነበር ይታመናል::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-
በግብጽ የሚኖሩ የዘመኑ ክርስቲያን ባልና ሚስት ወደ ፈጣሪ ለምነው ልጅ ሲወልዱ 'ዮሴፍ' አሉት:: እጅግ ሃብታሞች ቢሆኑም እርሱ ገና ልጅ እያለ ሁለቱም ዐረፉ:: ሕጻኑ ዮሴፍም ዕጓለ ሙታን [ወላጅ አልባ] ሆነ:: ሕጻኑ ሲያለቅስ የተመለከተ አንድ ደግ ጐረቤቱ ግን ወደ ቤቱ ወሰደው::

እንደ ልጁ ተንከባክቦ: ክርስትናንም አስተምሮ አሳደገው:: እድሜው ፳ ሲደርስም "የወላጆችህን ንብረት ንሳ" ብሎ አወረሰው:: ወጣቱ ዮሴፍ ግን "አኮኑ ዝንቱ ኩሉ ኃላፊ-ይህ ሁሉ ሃብት ጠፊ አይደለምን" ብሎ ናቀው::

ለነዳያንም በትኖት እያመሰገነ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገሰገሰ:: በዚያም የአሞክሮ ጊዜውን ፈጽሞ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበለ:: ለዓመታትም በዲቁና ገዳሙን እያገለገለ: እየተጋደለ ኖረ::

የአባ ዮሴፍን ደግነት የሰማው የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ማርቆስም ከገዳም አውጥቶ በመንበረ ዽዽስናው እንዲራዳውና ሕዝቡን እንዲያስተምርለት ወደ ከተማ አመጣው::

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን አባ ዮሴፍ ወደ ፓትርያርኩ አባ ማርቆስ ቀርቦ "አባቴ! ወደ ገዳሜ አሰናብተኝ:: ለመነኮስ በከተማ መኖር ፍትሕ አይደለምና" ሲል ተማጸነው:: ፓትርያርኩም "እሺ" ብሎ ቅስናን ሹሞ አሰናበተው::

ወደ ገዳመ አስቄጥስ ከተመለሰ ጀምሮ አባ ዮሴፍ በዓት ለየ:: እስከ ፶፱ ዓመቱም ድረስ በጾምና በጸሎት በበዓቱ ጸንቶ ኖረ:: በአጠቃላይ በገዳም የኖረባቸው ዓመታትም ፴፱ ደረሱ::

በዚህ ጊዜ ግን የወቅቱ ፓትርያርክ አባ ስምዖን [ከአባ ማርቆስ በኋላ ፫ ፓትርያርኮች ዐርፈዋል] በማረፉ ግብጽ እረኛን ስትፈልግ ነበር:: 'ማንን እንሹም' እያሉ ሲጨነቁ አንድ ሰው ጉቦ ሰጥቶ ሊሾም መሆኑን አበው ሰሙ:: ይህ ሰው ደግሞ ጭራሹኑ ልጅ ያለው ነው::

አባቶች ተሯሩጠው ያ ጉቦኛ ባለ ሚስት እንዳይሾም አደረጉ:: ቀጥለው ማንን እንደ ሚሾሙ ሲጨነቁ የሁሉም ሕሊና ስለ አንድ ሰው [አባ ዮሴፍ] ያስብ ነበር:: ሁሉም ተሰብሳቢዎች ስለ ነገሩ ተጨዋውተው አባ ዮሴፍን ይሾሙ ዘንድ ቆረጡ::

ተሰብስበው በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ ተባባሉ:: "ወደ በዓቱ ስንደርስ ቤቱ ክፍት ከቆየን ፈቃደ እግዚአብሔር ነው:: ዝግ ከሆነ ግን ፈጣሪ አልፈቀደም ማለት ነው" ሲሉ ተስማሙ:: ምክንያቱም የአበው በዓት ቶሎ ቶሎ አይከፈትምና::

ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነበረበትና ልክ ሲደርሱ እንግዳ ሊሸኝ በዓቱን ከፍቶ አገኙት:: እንዳያመልጣቸው ተረባርበው ያዙት:: ግጥም አድርገው አሥረው "አክዮስ-ይደልዎ-ይገባዋል" እያሉ ሥርዓተ ሲመት አደረሱለት:: እርሱ [አባ ዮሴፍ] ግን "እኔ ኃጢአተኛ ነኝ: አይገባኝም: ልቀቁኝ" እያለ ይጮህ ነበረ::

አበው ግን ሥርዓተ ሢመቱን ፈጽመው ወስደው በመንበረ ዽዽስና: በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዙፋን ላይ አስቀመጡት:: በቁጥርም ፶፪ኛ ሁኖ ተቆጠረ:: አምላክ ደጉን ሰው ጠቁሟቸዋልና ለቤተ ክርስቲያን ይተጋ ጀመር::

ሕዝቡን እያስተማረ: አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ: መጻሕፍትን እየተረጐመ: ተአምራትን እየሠራ: በመንኖ ጥሪት ለ፲፱ ዓመታት አገልግሏል:: ወቅቱም ተንባላት [አማሌቃውያን] በምድረ ግብጽ የሰለጠኑበት ነበርና ብዙ ችግሮችን አሳልፏል::

የግብጹ ሱልጣንም ሊገድለው ፪ ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም:: ፪ ጊዜም ለአባ ዮሴፍ የሰነዘረው ሰይፍ በመልአክ እየተመለሰ ተመልክቶ ትቶታል:: አባ ዮሴፍ በዘመኑ ተሰዶ የነበረውን የኢትዮዽያ ዻዻስ አባ ዮሐንስንም ከተሰደደበት ወደ ሃገራችን
እንደ መለሰው በዜና ሕይወቱ ተጽፏል:: አባ ዮሴፍ እንዲህ ተመላልሶ በ፸፰ ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† ቸር አምላክ በጻድቁ ሊቀ ዻዻሳት ጸሎት ይማረን:: ከበረከቱም ይክፈለን::

🕊

[  † ጥቅምት ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አባ ዮሴፍ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት
፪. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ኢላርዮስ
፬. ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል
 

" ኤዺስ ቆዾስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና:: የማይኮራ: የማይቆጣ: የማይሰክር: የማይጨቃጨቅ: ነውረኛ ረብ የማይወድ: ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ: በጐ የሆነውን ነገር የሚወድ: ጠንቃቃ: ጻድቅ: ቅዱስ: ራሱን የሚገዛ ይሁን:: " † [ቲቶ.፩፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

[  † ጥቅምት ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †  ]


† 🕊 ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ 🕊 † 

† በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::

ታላቁ ቅዱስ አብላርዮስ ደግሞ ካለ ማመን ወደ ማመን: ከማመን ወደ መመንኮስ: ከመመንኮስ ወደ መጋደል: ከመጋደል ወደ ትሕርምት: ከዚያም ወደ ፍጹምነት የደረሰ: በምድረ ሶርያም ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው::

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም [በበርሃ] ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ [ኤሌዎን ዋሻ] በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ፹ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

ይህ ከሆነ ከ፳ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል:: ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው ዛሬ የምናከብረው ታላቁ ጻድቅ አባ አብላርዮስ ነው::

ቅዱስ አብላርዮስ ሶርያዊ ሲሆን የተወለደው በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: በቀደመ ሕይወቱ ክርስትናን ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ነበር:: ለዚህ ምክንያቱ የወላጆቹ ኢ-አማንያን መሆን ነው::

ገና በልጅነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልስፍና: የዮናናውያንን ጥበብ ተምሮ ፈላስፋ ሁኗል:: በ፲፮ ዓመቱም በምድረ ሶርያ አሉ ከሚባሉ የጥበብ ሰዎች አንዱ ሆነ:: ቅዱሱ ማንበብና መጠየቅን አብዝቶ ይወድ ነበር::

የሚያነበው ነገር በሶርያ ቢያጣ በ፲፯ ዓመቱ ተጨማሪ ጥበብን [እውቀትን] ፍለጋ ወደ ግብጽ [እስክንድርያ] ወረደ:: በዚያ ግን ከሰማቸው ትምሕርቶች አንዱ ልቡን ገዛው:: በወቅቱ በግብጽ ላይ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ስለ ምድራዊው ያይደለ ስለ ሰማያዊው ጥበብ ሲያስተምር ሰምቶ ተገረመ::

ቅዱስ አብላርዮስ በዚህ ሰዓት የሰበሰባቸውን የፍልስፍና መጻሕፍት ጥሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነብ ጀመረ:: ቅዱስ እለ እስክንድሮስም የሚከብድበትን እያፍታታ ተረጐመለት:: በአጭር ጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ተጠመቀ::

በዚያው ዓመትም ከከተማ ወጥቶ ወደ በርሃ ገባ:: ከአባ እንጦንስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሆኖ መነኮሰ:: በዚያም በጾምና በጸሎት: በመታዘዝና በትሕትና ለዓመታት ኖረ:: ቀጥሎም ወሬ ነጋሪ መጥቶ ወላጆቹ ማረፋቸውን ነገረው::

በዚህ ጊዜ ቅዱስ አብላርዮስ ከአባ እንጦንስ ዘንድ ተባርኮ: ማኅበሩንም ተሰናብቶ ሶርያ ገባ:: የወላጆቹን ሃብትና ንብረት በሙሉ መጽውቶ ወደ ሶርያ በርሃ ወጣ:: በወቅቱ በአካባቢው ምንኩስና እየተነቃቃ ነበርና የቅዱሱ መምጣት ይበልጥ አጠናከረው::

ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ኤዺፋንዮስን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፈራ:: በአካባቢውም ታላቅ መካሪ: ናዛዥ: አጽናኝ: መሪ ሆነ:: ከብዙ ተአምራቱ ባለፈ ሃብተ ትንቢት የተሰጠው አባት ነውና እጅግ ክቡር ነበር::

የገድሉን ነገርማ ማን ተናግሮ ይፈጽመዋል!

እርሱ ከዕለተ ሰንበት በቀር እህልን አይቀምስም:: ለዚያውም እሑድ በነግህ [ጧት] ትንሽ ሳር ነጭቶ ከመብላት በቀር ሌላ የሚበላው አልነበረውም:: እንዲህ ባለ የበርሃ ሕይወት ለ፷፫ ዓመታት ኖረ:: በዓለም የኖረበትን ፲፯ ዓመት ብንደምረው ፹ ይሆናል:: ቅዱሱ በተወለደ በ፹ ዓመቱ በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በዚህች ቀን ዐርፏል::

አምላከ ቅዱስ አብላርዮስ ጥበቡን: ፈሊጡን: ሕይወቱን ይግለጽልን:: ከበረከቱም አይለየን::

🕊

[   † ጥቅምት ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ
፪. ቅድስት ጸበለ ማርያም
፫. ቅድስት አውስያ
፬. አባ ዻውሎስ ሊቀ ዻዻሳት

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤዺስቆዾስ]
፫. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም [ኢትዮዽያዊ]
፮. "፳፬ቱ" ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፯. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፰. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን

" ወንድሞች ሆይ ! መጠራታችሁን ተመልከቱ:: እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች: ኃይለኞች የሆኑ ብዙዎች: ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም:: ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝነት መረጠ . . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ:: ነገር ግን:- የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ::" [፩ቆሮ.፩፥፳፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/11/06 01:25:24
Back to Top
HTML Embed Code: