Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from M.A
አማላጂቱ ሆይ፦ በጭንቅ፣ በኃጢአትና በበደል ውስጥ ያለን እኛ ምልጃሽን እንፈልጋለንና ይቅር ባዩ ተወዳጅ ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን፣ ይቅርታውንና ምህረቱን ይልክልን ዘንድ ለምኝልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኩዋን ለአበው ሰማዕታት ቅዱስ ዮልዮስና ቅዱስ ኮቶሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †  ]

†††

†  🕊  ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት 🕊  †

ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ [አድናቆት]: ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::

ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት [በ፫ኛው መቶ ክ/ዘ] ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: [መዝ.፸፰፥፫]

እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና ፫፻ አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::

በወቅቱ ክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

፩. የታሠሩ ክርስቲያኖችን ቁስላቸውን እያጠበ ያጐርሳቸዋል::

፪. ቀን ቀን አገልጋዮቹን አስከትሎ የሰማዕታቱን ሥጋ እየሰበሰበ: ሽቱ ቀብቶ ይገንዛቸዋል:: አንዳንዶቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲልክ ሌሎቹን ራሱ ይቀብራቸዋል::

፫. ሌሊት ሌሊት በ፫፻ው አገልጋዮቹ እየታገዘ የሰማዕታቱን ዜና: ቀለም በጥብጦ: ብራና ዳምጦ: ብዕር ቀርጾ: ሲጽፍና ሲጠርዝ ያድራል:: በተረፈችው ጥቂት ሰዓት ደግሞ ይጸልያል:: ቅዱስ ዮልዮስ በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::

ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር:: ምርቃናቸውም "ለሰማዕትነት ያብቃህ" የሚል ነው:: በእርግጥ ይህ ለዘመኑ ሰዎች ምርቃት ላይመስለን ይችል ይሆናል:: እርሱ ግን ይህንን ሲሰማ ሐሴትን ያደርግ: እጅም ይነሳቸው ነበር:: በዘመኑ ትልቁ ምርቃት ይሔው ነበርና::

እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::

ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ ፭፻ ሰዎችን አስከትሎ ወደ ሃገረ ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::

በዚህ ተአምር የደነገጠው መኮንኑ አርማንዮስ ከነ ሠራዊቱ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንም ትቶ ቅዱስ ዮልዮስን ተከተለው:: ቀጥሎም ጉዞ ወደ ሃገረ አትሪብ ሆነ:: በዚያም ብዙ መከራን ተቀብሎ ጣዖታቱን አወደማቸው::

እዚህም የአትሪብ መኮንን ደንግጦ ከነ ሠራዊቱ አምኖ ቅዱሱን ተከተለው:: በመጨረሻ ግን ሰማዕትነት እንዳይቀርበት ስለሰጋ ቅዱስ ዮልዮስ ተአምራት ማድረጉን ተወ:: በፍጻሜውም የ፫ኛው ሃገር መኮንን ቅዱስ ዮልዮስ ከቤተሰቡና ከ፩ ሺህ ፭ መቶ ያህል ተከታዮቹ ጋር: ፪ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል:: ቅዱሱም የክብር ክብርን አግኝቷል::


†  🕊  ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕት  🕊  †

ይህ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ አረማዊ ሲሆን የክርስቶስን ስም ሰምቶ አያውቅም:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘ በፋርስ [አሁን ኢራን] ሳቦር የሚባል ክፉ ንጉሥ ነግሦ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ ነበር:: እርሱ የሚያመልከው ፀሐይና እሳት ነውና::

የዚህ ንጉሥ ልጆቹ 'ልዑል ኮቶሎስና ልዕልት አክሱ' ይባላሉ:: በቤተ መንግስት ውስጥ ስላደጉ የሚያመልኩት የአባታቸውን ጣዖት ነበር:: በፋርስ መንግስት ውስጥ ከነበሩ የጦር አለቀቆችና ሃገረ ገዥዎች አንዱ ጣጦስ ይባላል::

ይህ ሰው እጅግ ብሩህ የሆነ ክርስቲያን ነበርና ዘወትር ከንጹሕ አገልግሎቱ ተሰነካክሎ አያውቅም:: ትንሽ ቆይቶ ግን ክርስቲያን መሆኑን ሳቦር ስለ ሰማ ሠራዊት ይልክበታል:: "ሒዱና ጣጦስን መርምሩት: ክርስቲያን ከሆነና አማልክትን እንቢ ካለ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሉት" አላቸው::

በአጋጣሚ የንጉሡ ልጅ ኮቶሎስና ጣጦስ በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ነበሩና ሊያስጥለው ወዶ ሔደ:: ኮቶሎስ ቅዱስ ጣጦስ ታስሮ በእሳት ሊቃጠል ሲል ደረሰ:: ወዲያውም ወደ እሳቱ ውስጥ ጨመሩት:: እነርሱ ፈጥኖ አመድ ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር:: ግን አልሆነም::

ቅዱስ ጣጦስ በእሳት መካከል ቁሞ አላቃጠለውም:: እንዲያውም በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት እሳቱ ብትንትን ብሎ ጠፋ:: ኮቶሎስ ተገርሞ ቅዱሱን ባልንጀራውን "ወንድሜ! ሥራይ [መተት] መቼ ተማርክ ደግሞ?" ሲል ጠየቀው::

እርሱ እስከዚያች ሰዓት ኃይለ እግዚአብሔርን አልተረዳምና:: ቅዱስ ጣጦስ ግን "ወንድሜ! አትሳሳት: እኛ ክርስቲያኖች መተትን አናውቅም:: በፈጣሪያችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን ሁሉን ማድረግ እንችላለን" ሲል መለሰለት::

ኮቶሎስ ተገርሞ "አሁን እኔ በክርስቶስ ባምን እንዳንተ ማድረግ እችላለሁ?" ቢለው ቅዱሱ "አዎ ትችላለህ!" አለው:: ወዲያውም "እሳት አንድዱልኝ" አለና እጣቱን በመስቀል ምልክት አስተካክሎ ወደ እሳቱ ቢያመለክት እሳቱ ፲፪ ክንድ ርቆ ተበትኖ ጠፋ::

በዚያችው ሰዓት ቅዱስ ኮቶሎሰ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንና የአባቱን ቤተ መንግስት አቃሎ ወደ እስር ቤት ገባ:: አባቱ ሳቦር ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ "ምከሪው" ብሎ እህቱን አክሱን ላከበት::

ቅዱስ ኮቶሎስ ልትመክረው የመጣችውን እህቱን አሳምኖ የክርስቶስ ወታደር አደረጋት:: አስቀድሞ ቅዱስ ጣጦስ: አስከትሎም ቅድስት አክሱ ተገደሉ:: በፍጻሜው ግን ቅዱስ ኮቶሎስን እግሩን አስረው በየመንገዱ ጐተቱት:: በጐዳናም አካሉ እየተቆራረጠ አለቀ:: ክርስቲያኖች በድብቅ መጥተው የ፫ቱንም ሥጋ በክብር አኑረዋል::

አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታትን ባጸናበት ጽናት ሁላችንም ያጽናን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

🕊

[  † መስከረም ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
፪. ፲፻፭፻ [1,500] ሰማዕታት [የቅዱስ ዮልዮስ ማሕበር]
፫. ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕት
፬. ቅድስት አክሱ ሰማዕት
፭. ቅዱስ ጣጦስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ ባላን ሰማዕት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫. ቅዱስ ደቅስዮስ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፬. አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፭. አባ ዻውሊ የዋህ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
" ሰውን ከአባቱ: ሴት ልጅንም ከእናቷ . . . እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና:: ለሰውም ቤተሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል:: ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: መስቀሉን የማይዝ በሁዋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: " [ማቴ.፲፥፴፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖   መስከረም ፳፫ [ 23 ]    ❖

[  ✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን ወሰማዕት አውናብዮስና እንድርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞  ]


† 🕊 ቅዱሳን አበው አውናብዮስ ወእንድርያስ 🕊

፬ኛው መቶ ክ/ዘ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ ከዋክብት ይባላል:: ምናልባትም በዓለም ላይ ላለፌት ፩ ሺህ ፭ መቶ ዓመታት ያንን ዘመን መልሶ ማየት አልተቻለም::

-  ያ ዘመን ብዙ ሰማዕታት ነበሩበት::
-  ያ ዘመን ብዙ ሊቃውንት ነበሩበት::
-  ያ ዘመን ብዙ ጻድቃን ነበሩበት::
-  ያ ዘመን ብዙ ደናግል ነበሩበት::
-  ያ ዘመን ብዙ መነኮሳት ነበሩበት::
-  ያ ዘመን ብዙ ባህታውያን [ግኁሳን] ነበሩበት::

ዘመኑ ዘመነ ብርሃን ነው:: እልፍ አእላፍ ቅዱሳን በዚህ ዘመን አብርተዋልና:: ጠላት ሰይጣንን ከቦታው አሳድደው አስጨንቀውታል:: በዚህ ዘመነ ብርሃን ከወደ ምሥራቅ ካበሩ ከዋክብት መካከል ደግሞ በዚህ ዕለት አባቶቻችን ቅዱሳን አውናብዮስና እንድርያስን እናዘክራለን::

ቅዱሳኑ ባለ ብዙ ሃብት ነበሩ:: ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከደናግል: ከሊቃውንቱም አሉበት:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

በተጠቀሰው ዘመን በቅዱስ ጊዮርጊስ ሃገር በልዳ ከከበሩ ወገኖች ተወልደዋል::

የቅዱሳኑ ወላጆች ክርስቲያኖች: በዚያውም ላይ ባለ ሥልጣኖችና ሃብታሞች ነበር:: ልጆቻቸውን [አውናብዮስንና እንድርያስን] ሥጋዊውንም: መንፈሳዊውንም ትምሕርት አስተምረዋቸዋል:: ወጣት በሆኑ ጊዜ ወላጆቻቸው የዚህን ዓለም ነገር ሲያስቡላቸው: እነሱ ግን የተሻለውን እድል ያስቡ ነበር::

ዘወትር ገድላተ ቅዱሳንን ያነቡ: ዜና አበውን ይሰሙ ነበርና ይመንኑ ዘንድ ልቡናቸው አወካቸው:: በአንዲት ሌሊት ግን በመንፈስ ቅዱስ አጋዘዥነት ወስነው: ከሃገራቸው ልዳ ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

ክብር ለቅዱሳኑ አባ ሮማኖስና አባ በርሶማ ይሁንና ወቅቱ በሶርያ ምድር ገዳማዊ ሕይወት ተስፋፍቶ: ብዙ አድባራት በበርሃ ውስጥ ነበሩ:: ፪ቱ ቅዱሳንም በአንዱ ገዳም ውስጥ ገብተው አገለገሉ::

ተጋድሏቸውን እያበረቱ እስከ ምንኩስና ደረጃም ደረሱ:: ተጋድሏቸው በጾም: በጸሎትና በትእግስት ብቻ አይደለም:: በትሕትና በፍቅር በደግነትና በመታዘዝም ጭምር ነበር እንጂ::

የምንኩስናና የገዳማዊ ሕይወት ጠላት 'ፍቅረ ዓለምና ፍትወት እንስሳዊት' ናቸው:: አንድ ሰው ከዚህ ዓለም ቁሳቁስ ሳይርቅ መናኝ መሆን አይችልም:: ቅዱሳኑ ግን በመንኖ ጥሪት ይህችን ዓለም ከነኮተቷ ናቁዋት: አቃለሏት::

የሥጋ ፈቃዳቸውን ያጠፉ ዘንድ ሰውነታቸውን በጾምና በጸሎት: ዕረፍትም በማሳጣት ቀጧት:: እግዚአብሔር ደግሞ ስለዚህ ፈንታ ጸጋውን አበዛላቸው:: ቅዱሳኑ በሶርያ ገዳማት ለዘመናት ከተጋደሉ በሁዋላ ወደ ግብጽ ለመውረድ ወሰኑ:: ምክንያታቸው ደግሞ :-

፩ኛ. ከውዳሴ ከንቱ ለመራቅ
፪ኛ. ከቅዱሳን አበው ለመባረክ እና
፫ኛ. ለተሻለ ተጋድሎ ለመብቃት ነበር:: እየጸለዩ እያመሰገኑም ግብጽ: ቀጥሎም ገዳመ አስቄጥስ ደረሱ::

ታላቁ ርዕሰ መነኮሳት አባ መቃርስን ፊት ለፊት ቢያገኙት ደስ አላቸው:: ሐሴትንም አደረጉ:: እግዚአብሕርን በማደሪያዎቹ ማግኘት ይቻላልና:: የታላቁ ቅዱስ ደቀ መዝሙር ሆነው: በድንግልና ተጠብቀው: በተጋድሎ በርትተው በቦታው ለ፫ ዓመታት ቆዩ::

እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ፈልጐአቸው ነበርና በዚያ ሰሞን በከተማ የነበሩ ሊቃውንት ወደ ገዳም መጡ:: ገዳማውያንንም ዻዻስ ስላረፈብን "የምንሾመው መልካም እረኛን ስጡን" አሏቸው::

ገዳማውያኑ ሱባኤ ገብተው ቢጠይቁ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ አውናብዮስን መረጠ:: አበውም ቅዱሱን ዽዽስና ሲሾሙት ወንድሙን እንድርያስን ረዳት አደረጉት:: ፪ቱ ቅዱሳን ከበርሃ ወደ ከተማ መውጣታቸውን ተከትሎ ተጋድሏቸውን ለማበርታት ወሰኑ::

ምክንያቱም ለአንድ ገዳማዊ ከተማ ውስጥ ከመኖር በላይ ፈተና የለምና:: ቅዱሳኑ ቀን ቀን ድውያንን ሲጠይቁ: ሙታንን ሲቀብሩ: ሕዝቡን ሲያስተምሩ: ሥጋውን ደሙን ሲያቀብሉ ውለው ሌሊት ይጋደላሉ::

ለፈቃደ ሥጋቸው ሳያደሉ እንዲህ ባለ ቅድስና ኖረው ደግሞ ሌላ ፈተና መጣ:: የከተማው ሃገረ ገዢ አረማዊ በመሆኑ "ለጣዖት ስገዱ: ክርስቶስን ካዱ" ይል ጀመር:: ቅዱሳኑ ሕዝቡን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሊያስተምሩ ወደዋልና መኮንኑን "ተው! ተሳስተሃል" አሉት::

በዚህ ምክንያትም ብዙ ስቃይ ገጠማቸው:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት ሰማዕት ሆነዋል:: ጌታም ስለ ድንግልናዊ ሕይወታቸው: ስለ ወንጌል አገልግሎታቸውና ስለ ሰማዕትነታቸው ፫ አክሊላትን አቀዳጅቷቸዋል::

አምላከ አበው ቸርነቱን ይላክልን:: የቅዱሳኑን በረከትም ያሳድርብን::

🕊

[  † መስከረም ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱሳን ጻድቃን አውናብዮስ ወእንድርያስ [ሰማዕታት]
፪. ቅዱስ ጐርጐርዮስ መንክራዊ
፫. ቅድስት ቴክላ ድንግል
፬. ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሰማዕት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል

" በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኩዋ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: " [፩ዼጥ.፫፥፲፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  †  እንኩዋን ለቅዱስ ጐርጐርዮስ መነኮስ ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እና ለቅዱስ አድሊጦስ ሐዋርያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ †  ]


† 🕊 ቅዱስ ጐርጐርዮስ መነኮስ 🕊

በዚህ ስም ተጠርተው: ለምዕመናን አብርተው ያለፉ አባቶቻችን ብዙ ናቸው:: ለምሳሌም :-

-  ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
-  ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
-  ጐርጐርዮስ ዘሮሜ
-  ጐርጐርዮስ መንክራዊ
-  ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ
-  ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓትን መጥቀስ እንችላለን::

ከእነዚህ ዐበይት ጐርጐርዮሶች አንዱ ገዳማዊው ቅዱስ ዛሬ የሚከበረው ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ የተወለደው በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በላይኛው ግብጽ አካባቢ ነው:: ወላጆቹ እጅግ ባለ ጠጐች በመሆናቸው የሚፈልገውን ሁሉ አሟልተው አሳድገውታል::

በተለይ ደግሞ ሥጋዊ [የዮናናውያንን ጥበብ] እንዲማር አድርገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰደውታል:: በዚያም ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ከሥርዓቱ ጋር አጥንቶ እጅግ አንባቢ ስለ ነበረ አናጉንስጢስ [አንባቢ] ሆኖ ተሾመ::

አንባቢ በሆነባቸው ዘመናትም ወጣ ገባ ሳይል ያገለግል ነበርና ጣዕመ መንፈስ ቅዱስ አደረበት:: ስለዚህም አንደበቱ ጥዑም [ለዛ ያለው] ነበር:: ትንሽ ቆይቶም አበው 'ይገባሃል' ብለው ዲቁናን ሾሙት:: አሁንም ታጥቆ ያለ ዕረፍት ማገልገሉን ቀጠለ::

ዘመኑ ነጫጭ ርግቦች [የተባረኩ መነኮሳት] የበዙበት ነበርና ቅዱስ ጐርጐርዮስ አዘውትሮ ወደ ገዳም እየሔደ ይጐበኛቸው: በእጆቻቸውም ይባረክ ነበር:: በተለይ ሊቀ ምኔት ታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ [አባ ባኹም] በቅርቡ ነበርና ሁሌ እየሔደ ይጨዋወተው ነበር::

ትንሽ ቆይቶ ግን ቅዱሱ የምናኔ ፍላጐቱ እየጨመረ ሔደ:: አንድ ቀን ከገዳም ውሎ ሲመለስ ወላጆቹ ጥያቄ ጠየቁት:: "ልናጋባህ እንፈልጋለንና ምን ትላለህ?" አሉት:: እርሱም ጭራሹኑ እንደማይፈልግ መለሰላቸው:: ሊያሳዝኑት አልፈለጉምና ድጋሚ አልጠየቁትም::

ትንሽ ቆይተውም ተከታትለው ዐረፉ:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወላጆቹን ቀብሮ: ሃብት ንብረቱን ሸጦ ጉዞ ጀመረ:: ወደ አባ ዻኩሚስ ደርሶም ያን ሁሉ ገንዘብ በታላቁ ቅዱስ ፊት አፈሰሰው:: "ምን ላድርገው ልጄ?" ቢለው "አባቴ! ፈጣሪህ ያዘዘውን" አለው::

አባ ዻኩሚስም መነኮሳት በመብዛታቸው ቤት አልነበረምና ብዙ ቤቶችን አነጸበት:: የቅዱሱ ገንዘብ ገዳም ከታነጸበት በሁዋላ ምናኔን አንድ ብሎ ጀመረ::

ቅዱሱ ባጭር ታጥቆ: በጾምና ጸሎት: ውሃ በመቅዳት: በመጥረግ: ምግብ በማዘጋጀት: እግዚአብሔርንም አበውንም አስደሰተ:: ቅዱሱ ምንም ቢናገሩት አይመልስም:: ማንንም ቀና ብሎ አያይም::

"እሺ" ከማለት በቀር ትርፍ ቃል አልነበረውም:: በጸሎት እንባው: በስግደት ደግሞ ላቡ ይንቆረቆር ነበር:: ፍቅሩ: ትዕግስቱ: ትሕትናውና ታዛዥነቱ እጅግ ብዙ ዓለማውያንን ማረከ:: ስለ እርሱ የሰሙ ኃጥአን ሔደው ምንም ሳይናገራቸው በማየት ብቻ ይማሩ ነበር:: ፊቱ ብሩህ: ደግና ቅን በመሆኑ እርሱን ማየቱ በቂ ነበር::

ለ፲፫ ዓመታት በገዳመ ዻኩሚስ ከተጋደለ በሁዋላ ወደ ገዳመ ቅዱስ መቃርስ ከ፪ኛው አባ መቃርስ ጋር ተጉዋዘ:: በዚያም በዓት ወስኖ ከሰው ጋር ሳይገናኝ ፯ ዓመታትን አሳለፈ:: በጸጋ ላይ ጸጋ: በበረከት ላይ በረከት ሆኖለት በ፳፪ኛ ዓመቱ አባቶችን ሰበሰባቸው::

መንገድ ሊሔድ መሆኑን ነግሯቸው "በጸሎት አስቡኝ" አላቸው:: በማግስቱ በዚህ ቀን ሲመጡ ግን በፍቅር ዐርፎ አገኙት:: መነኮሳትም በክብር ገንዘው: ከበረከቱ ተሳትፈው: በታላቅ ዝማሬ ቀብረውታል::


†  🕊 ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ 🕊  †

ኢትዮዽያዊቷ ቅድስትእናት ክርስቶስ ሠምራ ቅንነቷ: ደግነቷና ቅድስናዋ እጅግ የበዛ ነው:: አንድ ቀን ግን ገና በትዳር ውስጥ እያለች: ከአገልጋዮቿ አንዷን ትጠራትና ታዛታለች:: ያቺ አገልጋይ ግን የታዘዘችውን ጀሮ ዳባ ልበስ ብላ ሳትታዘዛት ትቀራለች::

ደጋግማ ብትነግራትም ልትሰማት አልቻለችም:: ያን ጊዜ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልትገስጻት ብላ ጠጠር ብትወረውርባት ያች አገልጋይ ወድቃ ሞተችባት:: ቅድስቲቱ እጅግ ደንግጣ አለቀሰች:: የምታደርገውንም አጣች::

ወዲያው ግን ፈጠን ብላ: ወገቧን ታጥቃ ትጸልይ ጀመረች:: "ጌታየ ሆይ! ከሞት አስነሳልኝና ዓለምን ትቼ በቀሪ ዘመኔ አንተን አገልለግልሃለሁ" ብላ ፈጣሪን በብዙ እንባ ተማጸነችው:: ያን ጊዜም አገልጋዩዋ ከሞት ተነሳችላት::

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጊዜን አላጠፋችም:: ልጆቿን በቤት ትታ: ሃብትን ብረቷን ንቃ: አንድ ልጇን አዝላ: ቤቷን እንደ ተከፈተ ትታው ወደ ገዳም ወጣች:: በዚህ ዕለትም [መስከረም ፳፬ ቀን] ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገባች::


†  🕊 ቅዱስ አድሊጦስ ሐዋርያ 🕊 †

ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በግሪክ አቴና [ATHENS] ውስጥ ሲሆን በነገድ እሥራኤላዊ ነው:: በአደገባት አቴና ከተማ ሥርዓተ ኦሪትን ከወገኖቹ: የግሪክን ፍልስፍና ደግሞ ከአርዮስፋጐስ ተምሯል:: መድኃኔ ዓለም ዘመነ ስብከቱ ሲጀምር ግን አድሊጦስ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ አደመጠው: ተማረከበትም::

ወዲያውም "ጌታ ሆይ! ልከተልህ?" ሲል ጠየቀው:: ልብን የሚመረምር ጌታም ፈቅዶለት ከ፸፪ቱ አርድእት ደመረው:: ከዚያም ከጌታችን ዘንድ ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ: ለወንጌል አገልግሎት ተሠማርቶ በርካታ አሕዛብን አሳምኗል:: በመጨረሻም ተወልዶ ባደገባት አቴና በዚህች ቀን ገድለውታል::

አምላከ ቅዱሳን በትእግስት: በፍቅርና በትሕትና ይሸልመን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[  †  መስከረም ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ገዳማዊ
፪. ቅድስ ክርስቶስ ሠምራ [ደብረ ሊባኖስ የገባችበት]
፫. ቅዱስ አድሊጦስ ሐዋርያ [ከ፸፪ቱ አርድእት]
፬. አቡነ ሰላማ

[   †  ወርኀዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት [መምሕረ ትሩፋት]
፪. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፫. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
፬. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤዺስቆዾስ]
፭. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮. ፳፬ቱ "24ቱ" ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፯. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም [ኢትዮዽያዊ]

" ፍቅር ያስታግሳል:: ፍቅር ያስተዛዝናል:: ፍቅር አያቀናናም:: ፍቅር አያስመካም:: ፍቅር አያስታብይም:: ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም:: አያበሳጭም:: ክፉ ነገርን አያሳስብም:: ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም:: ሁሉን ይታገሣል። ሁሉን ያምናል:: ሁሉን ተስፋ ያደርጋል:: በሁሉ ይጸናል::" [ቆሮ.፲፫፥፬]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/15 16:56:54
Back to Top
HTML Embed Code: