Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለታላቁ አባ በርሶማ እና ለቅዱስ አሞጽ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†   🕊   ታላቁ አባ በርሶማ   🕊   †

† ታላቁ ገዳማዊ ሰው ቅዱስ በርሶማ ከኋለኛው ዘመን ጻድቃን አንዱ ሲሆን ተወልዶ ያደገውም በግብጽ ምስር(ካይሮ) ውስጥ ነው:: ዘመኑ በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: የታላቁ በርሶማ ወላጆች ክርስቲያኖች ነበሩና ያሳደጉት በሃይማኖትና በምግባር እየኮተኮቱ ነው::

ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንዲማር አድርገውት ወጣት በሆነ ጊዜ አንድ ሰሞን ተከታትለው ዐረፉ:: በወቅቱም ስለ ሃብት ክፍፍል ዘመዶቹ ተናገሩት:: ነገር ግን አንድ ጉልበተኛ አጐት ነበረውና ንብረቱን ሁሉ ቀማው:: ቅዱስ በርሶማ በልቡ አሰበ:- "እንዴት ነገ ለሚጠፋ ገንዘብ ፍርድ ቤት እሔዳለሁ?" አለ::

ቀጥሎም ይህችን ዓለም ይተዋት ዘንድ ወሰነ:: ከቤቱም እየዘመረ ወደ በረሃ ገሰገሰ:: "ምንት ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ - ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ካጐደለ ምን ይረባዋል::" [ማቴ.፲፮፥፳፮] (16:26) እያለም ጉዞውን ቀጠለ:: ልብሱን በመንገድ ለኔ ቢጤዎች ሰጥቶ ራቁቱን በአምስት ኮረብታዎች ውስጥ ተቀመጠ::

በዚያም የቀኑ ሐሩር: የሌሊቱ ቁር [ብርድ] ሲፈራረቅበት ለብዙ ዓመታት ኖረ:: እርሱ ግን ያ ሁሉ መከራ እያለፈበት ደስተኛ ነበር:: ዘወትር የዳዊትን መዝሙር ያለ ማቋረጥ ይዘምራል:: ገድላተ ቅዱሳንን እያነበበ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀናል:: ያነበባትንም ነገር በተግባር ይፈጽማል::

ይህ ቅዱስ ስለ ራቁትነቱ እንዳይከፋው ዘወትር ራሱን "በርሶማ ሆይ! ከእውነተኛው ዳኛ ፊት ራቁትህን መቆምህ አይቀርምና የዛሬውን ጊዜአዊ ራቁትነትህን ታገስ" እያለ ይገስጽ ነበር:: እርሱ ለጸሎት ከቆመ የሚቀመጠው ከቀናት በኋላ ነው:: ያለ ዕለተ ሰንበት እህልን አይቀምስም::

ምግቡም የሻገተ እንጀራና ክፍቱን ያደረ ውኃ ነበር:: በእንዲህ ያለ ተጋድሎ እያለ ውዳሴ ከንቱ ስለ በዛበት ሸሽቶ ወደ ምሥር ሔዶ በቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አደረ:: በዚያም እንዳስለመደ ለሠላሳ ዓመታት ተጋደለ::

በቦታው የጉድጓድ ውኃ ነበርና ሁሌ ሌሊት ወደ ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ ነበር:: እንደ ስለት የሚቆራርጠውን ውርጭም ይታገሥ ነበር:: በዚያ አካባቢ ብዙ ሰውና እንስሳትን የፈጀ አንድ ዘንዶ ነበርና በአካባቢው ሰው አያልፍም ነበር::

ታላቁ በርሶማ ግን ወደ ዘንዶው ዋሻ ሔደና ጸለየ:: "ጌታ ሆይ! በስምህ ለሚያምኑ የሰጠሃቸውን ሥልጣን አትንሳኝ?" ብሎ (ማር. 16:18) "በአንበሳና በዘንዶ ላይ ትጫናለህ::" የሚለውን መዝሙር ዘመረ:: [መዝ.፺፥፲፫] (90:13)

ዘንዶውንም "ና ውጣ::" ብሎ አዘዘው:: ወዲያው ወጥቶ ሰገደለት:: የጻድቁ ሰው አገልጋይም ሆነ:: የአካባቢው ሰውም እጅግ ደስ አላቸው:: ብዙ ጊዜም አገልግሏቸዋል:: [በሥዕሉ ላይ የምታዩት እርሱው ነው::]

ታላቁ አባ በርሶማ የሚያርፍበት ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዝሙሩን "እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ 'የብርቱ [የእግዚአብሔር] ልጅ' ብሎ ለሚጠራኝ በረድኤት እመጣለታለሁ::" ብሎ: ምላሱን በምላጭ ቆርጦ ጣለውና አሰምቶ ዘመረ::

"እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ . . . እግዚአብሔር ያበራልኛል: ያድነኛልም:: ምን ያስፈራኛል::" አለ:: [መዝ.፳፮፥፩] (26:1) ልብ በሉልኝ! የሰው ልጅ ምላስ ከሌለው መዘመርም: መናገርም አይችልም:: ቅዱሳን ግን ሲበቁ ልሳን መንፈሳዊ ይሰጣቸዋል:: ከዚህ በኋላ በትእምርተ መስቀል አማትቦ ዐረፈ::

ፓትርያርኩን አባ ዮሐንስን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትና የምስር ሹማምንት ገንዘውት ከበረከቱ ተካፈሉ:: ገድሉ እንዳስቀመጠው በዘመኑ ሁሉ ምንጣፍ ላይ ተኝቶ አያውቅም:: "ማዕከለ ሥጋሁ ወምድር ኢገብረ መንጸፈ" እንዲል:: ያረፈውም በ1340 ዓ/ም ነው::


†  🕊   ቅዱስ አሞጽ ነቢይ   🕊  †

† አሞጽ ማለት "እግዚአብሔር ጽኑዓ ባሕርይ ነው: አንድም እግዚአብሔር ያጸናል::" ማለት ነው:: "ተወዳጅ ሰው" ተብሎም ይተረጐማል:: የነበረው ቅ.ል.ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት ሲሆን አባቱ ቴና እናቱ ሜስታ ይባላሉ:: ትውልዱም ከነገደ ስምዖን ነው::

በትውፊት ይህ ቅዱስ ነቢይ የነቢዩ ኢሳይያስ አባት ነው የሚሉ ቢኖሩም ሁለቱ አሞጾች የተለያዩ መሆናቸውን ሊቃውንት ይናገራሉ:: ቅዱስ አሞጽ ዘጠኝ ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ስለ ነገረ ድኅነት ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል::

ስለ ሃገራችን ኢትዮጵያም እንዲህ ብሏል :-
"የእሥራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር::"
ቅዱሱ ነቢይ ወገኖቹን አብዝቶ ይገስጻቸው ስለ ነበር ተቆጥተው በዚህች ቀን ገድለውታል::

† የቅዱሳን አምላክ አዲሱን ዘመን ቅዱሳኑን አብዝተን የምናስብበት ያድርግልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ታላቁ አባ በርሶማ
፪. ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
፫. ቅዱስ ያዕቆብ ዘምስር
፬. አባ መግደር [እግዚአብሔር በጸሎቱ ይማረን]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

- የለም

† " መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም::" † [፪ጢሞ. ፬፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ዘመን ማን ነው? ዘመን ማለት እኛ ነን..ስንከፋ የሚከፋ ደግ ስንሆን ደግ የሚሆን የእኛው ነጸብራቅ ነው ዘመን። ለዚህ ነው አበው በአንጋረ ፈላስፋ "ዘመን ማለት አንተ ነህ፡፡ አንተ ሰላማዊ ስትሆን ሰላማዊ ትሆናለች፡፡ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋለች፡፡" በማለት የተናገሩት።

እናም ዘመን እኛ እኛም ዘመን ነንና ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው በዕሜያችን ስንት ጊዜ እያለፈ እንደ ኾነ እያሰብን ራሳችንን እንዲህ ብልን እንጠይቅ፡- “ቀናት እየሮጡ ነው፣ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው፣ የዕድሜዬ መንገድም እየተጋመሰ ነው፤ ታዲያ ምን በጎ ምግባር ያዝኩ? ከዚህ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው፤ ታዲያ ምን የጽድቅ ሥራ ሠራሁ? በዚህ ዕድሜዬ (ዘመኔ) መሥራት የነበረብኝ ምግባር ትሩፋት ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ አልችልም፤ ታዲያ ዕድሜዬ (ዘመኔ) ሲገፋ ማድረግ የማልችላቸውን የጽድቅ ሥራዎች (ፆም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ አገልግሎት፣… ዕድሜ ሲገፋ ይከብዳሉና) እንደ አቅሜ እያደረግኩ ነውን?” በማለት ልቡናችንን እንጠይቅ።"

“አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።” ሰቆ.ኤር 5፥21
🌼🌼"በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። 🌼የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ 🌼ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። 🌼ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።>  መዝሙረ ዳዊት 65፥9
እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገርዎት🌼
መልካም በዓል ይሁንላችሁ ውድ የኢትዮጵያ ቻናል ቤተሰቦች
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

🌼    እንኳን አደረሳችሁ !    🌼


[  †  መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]  🌼


†  🕊  ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ 🕊

ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ከ፲፪ [12] ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ በርተሎሜዎስ ነው:: [ማቴ.፲፥፫] (10:3) ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በስፋት ሲተረክ አንሰማም:: ቅዱሱ ሐዋርያ እንደ ሌሎቹ ወንድሞቹ ዓለምን በወንጌል ትምሕርት አብርቷል:: በትውፊት ትምሕርት መሠረት 'በርተሎሜዎስ' የሚለውን ስም ያወጣለት ጌታችን ሲሆን ትርጉሙም 'ተክሎችን የሚያጠጣ' ማለት ነው::

ከሐዋርያትም ጌታ አስቀድሞ የስም ቅያሪ ያደረገለት ለእርሱ እንደ ሆነ ይታመናል:: በርተሎሜዎስ የግብርና ሥራውን ትቶ: የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ: ከዋለበት እየዋለ: ካደረበትም እያደረ ምሥጢረ ወንጌልን ተምሯል::

ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላም ከሐዋርያት ጋር ዓለምን በዕጣ ተካፍሏል:: ሃገረ ስብከቱም 'እልዋህ' እና 'አርማንያ' ናቸው:: የአርማንያ መንበርም የእርሱ ነው:: ቅዱሱ ገድሉ እንደሚለው አሕዛብን በስብከቱና በሚያስደነግጡ ተአምራቱ አሳምኗል::

ከቅዱስ ዼጥሮስ: ከቅዱስ እንድርያስ: ከክርስቶፎሮስና ከሌሎቹም ሰባክያን ጋር ዓለምን ዙሯል:: ሙታንን አስነስቶ: ድውያንን ፈውሶ: አጋንንትን አውጥቶ: ብዙወችን ወደ ሕይወት መልሷል:: የደረቁ እንጨቶችም በእጁ ላይ እንዳሉ ለምልመው: አብበው ያፈሩ ነበር::

ቅዱስ በርተሎሜዎስ እያስተማረ ወደ ኢትዮዽያም ደርሶ እንደ ነበር ይነገራል:: በመጨረሻም 'ለሚስቶቻችን ንጽሕናን አስተምረሃል' በሚል ተከሶ: ንጉሥ አግሪዻ በሰቅ [ጸጉር] ጠቅልሎ: አሸዋ ሞልቶ: ባሕር ውስጥ ጥሎታል:: በዚያውም ዐርፏል::


†  🕊  ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ  🕊  †

ይህቺ ሃገረ ቁልዝም ግብጽ ውስጥ የምትገኝ ስትሆን ብዙ ቅዱሳንን አፍርታለች:: በተለይ የአባ እንጦንስና የልጆቹ ማረፊያ ከመሆኗ ባሻገር ቅዱስ አባ ሚልኪም ወጥቶባታል:: ቅዱሱ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ: የስለት ልጅም ነው:: ጥሩ ክርስቲያኖች የነበሩት ወላጆቹ እጅግ ባለጸጐችም ነበሩ::

በስለት መንታ ልጆችን [ሚልኪና ስፍናን] ወልደው: በሥርዓት አሳድገዋል:: ቅዱስ ሚልኪ በሕጻንነት ወራቱ ስቆና ከሕጻናት ጋር ተጫውቶ አያውቅም:: ብሉያትና ሐዲሳትን ጠንቆቆ ካጠና በኋላ እድሜው ፲፱ [19] ሲደርስ ወላጆቹ "እንዳርህ" አሉት:: የልቡን እያወቀ "እሺ" አላቸው::

ቀጥሎም "ባልንጀሮቼን ልጋብዝበት" ብሎ: ፲፻ [1,000] ወቄት ወርቅ ተቀብሎ: በፈረስ ተቀምጦ ሔደ:: መንገድ ላይ መቶውን ለተከተሉት: ፱ [9] መቶውን ወቄት ለነዳያን: ፈረሱን ደግሞ ለአንድ ደሃ ሰጥቶ: ጡር [ጢር] ወደ ሚባል በርሃ ገሰገሰ::

መጥፋቱ በቤተሰብ ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: እናቱም ዐይኗ ተሰወረ:: እርሱ ግን አባ አውጊን ከሚባል ባሕታዊ ሒዶ ደቀ መዝሙሩ ሆነ:: ለ፫ [3] ዓመታትም ተፈትኖ መነኮሰ::

*ከዚያም በጠባቡ ጐዳና ገብቶ በጾም: በጸሎት: በትሩፋት ከፍ ከፍ አለ:: ከቅድስናው ብዛት የተነሳ አጋንንት ገና ከርቀት ሲያዩት ይሸሹት ነበር:: የነካቸውም ሁሉ ይፈወሱለት ነበር:: በእርሱ ጸሎትም በፋርስና በሮም ሰላም ሆነ::

አንድ ቀን የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ሲሔድ የአገረ ገዥውን ልጅ ዘንዶ በልቶት ሲለቀስ ደረሰ:: ጸሎት አድርጐ ዘንዶውን ጠራውና "እንደ ነበረ አድርገህ ትፋው" ሲል አዘዘው:: ዘንዶውም ተፋው: ሰይጣኑም ሸሽቶ አመለጠ::

ሃገረ ገዥው ደስ ቢለው ፫፻ [300] ቤቶች ያሉት ገዳም ለማር ቅዱስ ሚልኪ አነጸለት:: በዚያም ፫፻ [300] መነኮሳት ተሰብስበው ትልቅ ገዳም ሆነ:: ማር ሚልኪ ሁሉን ካሰናዳ በኋላ "ከዚህ አልወጣም" ብሎ በዓቱን ዘጋ:: ሰይጣን ግን "አስወጣሃለሁ" ብሎ ፎክሮ ሒዶ በንጉሡ ልጅ አደረባትና አሳበዳት::

"ከሚልኪ በቀር የሚያሰወጣኝ የለም" አለ:: ንጉሡ ወታደሮቹን ጠርቶ "ሒዳችሁ: አባ ሚልኪን ይዛችሁ ብትመጡ ሽልማት: ካልሆነ ግን ሞት ይጠብቃችሁአል" አላቸው:: እነርሱም በጭንቅ አግኝተው "እንሒድ" አሉት:: "በሮም ከተማ በር ላይ እንገናኝ" አላቸው::

ልክ በዓመቱ እነርሱ ሮም ሲደርሱ ማር ሚልኪ ደመና ጠቅሶ ከተፍ አለ:: ልጅቱንም አቅርቦ ሰይጣንን "እየታየህ ውጣ" አለው:: ወደል ጐረምሳ ሆኖ ወጣ:: ወስዶም አሰረው:: ከቀናት በኋላ ሕዝቡና ንጉሡ እያዩ ማር ሚልኪ ደመና ላይ ተቀምጦ: ሰይጣኑን የድንጋይ ገንዳ አሸክሞ እየነዳ ወሰደው::

ሕዝቡም ደስ ብሏቸው በታላቅ ዝማሬና እልልታ ሸኙት:: ሰይጣኑንም ለዘለዓለም አሰረው:: ቅዱስ ሚልኪ በገዳሙ ለዓመታት ከተጋደለ በኋላ በዚህች ቀን ቅዱሳን አባ እንጦንስ: መቃርስ: ሲኖዳና ሌሎችም መጥተው: በክብር ተቀብለውት ዐርፏል:: አበው 'ትሩፈ ምግባር' ይሉታል::


†  🕊 ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት 🕊

ከዘጠኙ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በብርሃናት ላይ ተሹሟል:: ለሃገራችን ልዩ ፍቅር ያለው መልአኩ ከሔኖክ ጀምሮ የብዙ ቅዱሳን ረዳት ነው:: ዛሬ በዓለ ሲመቱ ነው::


†   🕊  ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ   🕊  †

ታላቁ ጻድቅ: የትእግስትም አባቷ ቅዱስ ኢዮብ በጭንቅ ደዌ ለብዙ ዘመናት በመከራ ከኖረ በኋላ በዚህች ቀን በፈሳሽ ውሃ (በዮርዳኖስ) ታጥቦ ሰውነቱ ታድሷል:: ክብርም ተመልሶለታል:: በፈሳሽ ውሃ የምንጠመቅበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

የበርተሎሜዎስ አምላክ ፍቅሩን: የሚልኪ አምላክ ትሩፋቱን: የራጉኤል አምላክ ረድኤቱን: የኢዮብ አምላክ ትእግስቱን ያሳድርብን::

🕊

[  † መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ] 🌼

፩. ርዕሰ ዓውደ ዓመት
፪. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፫. ቅዱስ /ማር/ ሚልኪ [ትሩፈ ምግባር]
፬. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፭. ቅዱስ ኢዮብ ተአጋሲ
፮. ሜልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ] 🌼

፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

" የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት:: መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ :- የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው:: ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና:: ለታሠሩትም መፈታትን: ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ: የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ: የተወደደቺውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል::' ተብሎ የተጻፈበትን ሥፍራ አገኘ::" [ሉቃ.፬፥፲፯] (4:17)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🌻 እንኩዋን ለታላቁ #ነቢይና_ሰማዕት_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ 🌻

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ሚያዚያ 15 ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

=>መስከረም 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
2.ቅዱስ ዳስያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዲዲሞስ ሰማዕት
4.ቅድስት መሪና

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ #ጌታ_ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ #ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው #ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †

[  † እንኳን ለጻድቁ አባ ሙሴ እና አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊   አባ ሙሴ ዘሲሐት  🕊   †

† ገዳመ ሲሐት የሚባሉ ብዙ ቦታዎች አሉ:: ቅድሚያውን የሚይዘው ግን የግብጹ ነውና ዛሬ የዚህን ገዳም አንድ ቅዱስ እናስባለን:: ሕይወታቸውም በእጅጉ አስተማሪ ነው:: ቅዱሱ አባ ሙሴ ይባላሉ:: የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ናቸው::

እኒህ ጻድቅ አንድ ነገር ከሌሎች ቅዱሳን ይለያቸዋል:: ከምግባርና ትሩፋት በቀር አንድም የእግዚአብሔር ቃል አያውቁም:: ዝም ብለው በየዋሕነት ይኖሩ ነበር እንጂ:: ተወልደው ባደጉበት በምድረ ግብጽ በቅን ሕይወት ኑረው: በወጣትነታቸው ወደ ደብረ ሲሐት ገቡ::

በዚያም በብሕትውና ዘግተው በጾምና ጸሎት ተወስነው ለ፵፭ [45] ዓመታት ኖሩ:: እጅግ የዋሕ ሰው ናቸውና ከጸጋ [ከብቃት] ደረሱ:: ሰው በአካባቢው አልነበረምና አብረው የሚውሉት ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: አራዊቱም ጻድቁን ያጫውቷቸው: ይታዘዙላቸውም ነበር:: በፈንታው ደግሞ አባ ሙሴ በተአምራት ዝናብ ያዘንቡላቸው: ምግብም ይሰጧቸው ነበር::

አባ ሙሴ ልብስ አልነበራቸውምና በቅጠል ይሸፈኑ ነበር:: የምግባቸው ነገርማ "በመጠነ ኦፍ" ይላል . . . ትንሽ ድንቢጥ የምትበላውን ያህል ቀምሰው: ጥርኝ ውሃም ተጐንጭተው ነበር የሚኖሩት:: በሁዋላ ግን እጅግ ከመብቃታቸው የተነሳ ዐይናቸውን ሲገልጡ 'ገነት' [የአትክልት ሥፍራ] ይታያቸው ነበር:: ከዚያም ለበረከት ቆርጠው ይበሉ ነበር::

ሰይጣን እርሳቸውን ይጥል ዘንድ እጅግ ቢጥርም አልተሳካለትም:: በስተ መጨረሻ ግን የሚጥልበት መንገድ ተከሰተለት:: ምንም ባለ መማራቸው ሊፈትናቸውም ተነሳ:: አንድ ቀን ከበአታቸው በር ላይ ከአራዊት ጋር ተቀምጠው ሳለ ሰይጣን ሽማግሌ መነኩሴ መስሎ እየተንገዳገደ መጣ::

አራዊቱ ደንግጠው ሲሸሹ እርሳቸው ግን ሳያማትቡ ሮጥ ብለው ደገፉት:: ወደ በዓታቸውም አስገቡት:: ማታ ላይ ሲጨዋወቱ "ማንነትዎን ይንገሩኝ" አላቸው:: ለአባ ሙሴ ሰይጣኑ የበቃ አባት መስሏቸዋልና የ፵፭ [45] ዓመታት ድንግልናዊ የተባሕትዎ ሕይወታቸውን ነገሩት::

እርሱም በፈንታው ሐሰቱን ቀጠለ:: "እኔ ግፍ እየሠራሁ በዓለም እኖር የነበርኩ ሰው ነኝ:: ነገር ግን ዓለምን ትቼ ላለፉት ፵ [40] ዓመታት በበርሃ በንስሃ ኑሬአለሁ:: ያም ሆኖ አንዲት ሴት ልጅ አለችኝና 'ማን ያገባታል' ብየ ስጨነቅ አንተ እንደምታገባት ተገለጠልኝ" አላቸው::

አባ ሙሴ ደንግጠው "እንዴት ድንግልናየንና ሕይወቴን ትቼ አገባለሁ?" ሲሉም ጠየቁ:: ሰይጣን ግን ቃለ እግዚአብሔር እንደማያውቁ ተረድቷልና "አንተ ከአብርሃም: ከያዕቆብ: ከዳዊት ትበልጣለህ? እነሱ አግብተው የለ!" ብሎ ቢገስጻቸው አንዳንዴ አለ መማር ክፉ ነውና አባ ሙሴ ሸብረክ አሉ: ተረቱ::

ከዚያም ተያይዘው ጉዞ ወደ ዓለም ሆነ:: መንገድ ላይ ግን መነኩሴ ነኝ ያለው ሰይጣን ወደቀና የሞተ መሰለ:: አባ ሙሴ በእንባ ቀብረውት ሲሔዱ ተኖ ጠፋ:: አባ ሙሴ ቀና ሲሉ ሰይጣን በምትሐት የሠራውን ያማረ ግቢና ቆንጆ ሴት አዩ:: ወደ እሷ እቀርባለሁ ሲሉ አውሎ ንፋስ ማጅራታቸውን መትቶ ጣላቸው::

አባ ሙሴ ከወደቁበት ሲነሱ ያዩት ነገር ሁሉ ሰይጣናዊ ምትሐት መሆኑን አወቁ:: ወደ በአታቸው መጥተው ከገነት ፍሬ ቢቀምሱ ጸጋ እግዚአብሔር ተለይቷቸዋልና መራራ ሆነባቸው:: እያለቀሱ ከበዓታቸው ወጡ::

መንገድ ላይ ያው ሰይጣን ነጋዴ መስሎ: "መንገድ ልምራዎት" ብሎ ምንም ከሌለበት በርሃ ላይ ጥሏቸው ተሰወረ:: የሚያደርጉት ጠፋባቸው:: ረሃቡ: ጥሙ: ከፈጣሪ ጸጋ መለየቱ አቃጠላቸው:: አሁንም አንዲት ሴት መነኩሴ ድንገት መጥታ ወደ በዓቷ አስገባቻቸው::

የማይገባውን ድርጊት እናድርግ ብላ አባበለቻቸው:: ይባስ ብላ ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ አሳመነቻቸው:: ወዲያውም ወደ ሌላ በርሃ ወስዳ "አወቅኸኝ?" አለቻቸው:: "የለም" አሏት:: እዚያው ላይ ተቀይራ ጋኔን መሆኗን አሳይታቸው ተሠወረች::

አባ ሙሴ በዚያው ሥፍራ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጡ:: አለቀሱ: ተንከባለሉ:: እንባቸው እንደ ዥረት ፈሰሰ:: ልቡናቸው ሊጠፋ ደረሰ:: ወደ ፊታቸው አፈር እየረጩ: "ወየው" እያሉ ሲያለቅሱ ጌታችን መልአኩን ላከላቸው::

እንደ ቀድሞውም ፊት ለፊት ታይቶ አጽናናቸው:: "አይዞህ! ፈጣሪ እንባህንና ንስሃህን ተቀብሏል" ብሎ ወደ ስውራን ከተማ ወሰዳቸው:: በዚያም ለ፯ [7] ቀናት ቆይተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: አባ ሳሙኤልም ቀብሯቸዋል::


†  🕊  አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ  🕊   †

† ጻድቁ የነበሩት በ፲፫ [13] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የተወለዱት ትግራይ ውስጥ ነው:: ዛሬም ድረስ የብዙ ስውራን ቤት እንደ ሆነ የሚታወቀውን ደብረ_ሐዘሎንም እርሳቸው እንደ መሠረቱት ይነገራል:: አባ አንበስ ከገዳማዊ ትሩፋታቸው ባሻገር በአንበሶቻቸው ይታወቁ ነበር::

የትም ቦታ ሲሔዱ በአንበሳ ጀርባ ላይ ነበር:: በእርግጥ አባቶቻችን ከዚህም በላይ ብዙ ድንቆችን ማድረግ ይችላሉ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነውና:: ጻድቁ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ: የሳሙኤል ዘዋልድባና የአባ ብንያሚን ባልንጀራ ናቸው:: ዛሬ ደግሞ ዕረፍታቸው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፈተና አስቦ እኛን ከመከራ ይሰውረን:: በቃል ኪዳናቸው ይጠብቀን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

🕊

[  † መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት
፪. አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ
፫. አበው ኤዺስ ቆዾሳት
፬. አባ ዲዮናስዮስ
፭. አባ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ በትንከል ዲያቆን

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯. ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ [ዓምደ ሃይማኖት]

† " በመጠን ኑሩ: ንቁም:: ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና:: በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት::" † [፩ዼጥ.፭፥፰] (5:8)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  🌼  መስከረም [ ፬ ] 4 ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት 🌼  †

[ †  🕊  እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ እና ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።  🕊 †  ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊 ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን  🕊  †

† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ አውሴ ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያትሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ ፹ [80] ዓመቱ: ኢያሱ ደግሞ ፵ [40] ዓመቱ ነበር::

ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ [፵] 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምሕሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም:: አውሴን ኢያሱ ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው::

ኢያሱ ማለት " መድኃኒት" ማለት ነው:: ለዚሕም ምክንያቶች አሉት :-

፩. ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል: ምድረ ርስትን አውርሷል::
፪. ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ [ጥላ] እንዲሆን ነው::

ቅዱስ ኢያሱ በበርሃው ለዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዞታል [አገልግሎታል] : እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል:: በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን: ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው [፹] 80 እየሆነ ነበር::

† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን [አስተዳዳሪ] እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:

¤ ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ:
¤ ሕዝቡን አሻግሮ:
¤ የኢያሪኮን ቅጥር [፯] 7 ጊዜ ዙሮ:
¤ በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ:
¤ የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ:
¤ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::

የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዛን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል: በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚሕች ዕለትም ለ፲፪ [12] ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም [በኤሎም ሸለቆ] አቆመ::

ሰባት አሕጉራተ ምስካይ [የመማጸኛ ከተሞችን] ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ፵ [40] ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ :- "እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: [ኢያ.፳፬] (24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::

ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ ፫ [3] ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ፫ [3] ወገን [በነፍስ: በሥጋ: በልቡና] ድንግል ናት:: አንድም በ፫ [3] ወገን [ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት] ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው አባሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" [የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ] ሲል ያመሰገናት::

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ፹ [80] ዓመት: በተወለደ በ፻፳ [120] ዓመቱ [ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ፻፲ [110] ዓመቱ ይላል] በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ፴ [30] ቀናት አለቀሱለት::


†  🕊  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  🕊  †

† አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው::

ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል:: ከእርሷ ጋር ለ፲፭ [15] ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ፸ [70] ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::

ሶስት መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::

† እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው :-

¤ ወንጌላዊ
¤ ሐዋርያ
¤ ሰማዕት ዘእንበለ ደም
¤ አቡቀለምሲስ [ምሥጢራትን ያየ]
¤ ታኦሎጐስ [ነባቤ መለኮት]
¤ ወልደ ነጐድጉዋድ
¤ ደቀ መለኮት ወምሥጢር
¤ ፍቁረ እግዚእ
¤ ርዕሰ ደናግል [የደናግል አለቃ]
¤ ቁጹረ ገጽ
¤ ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ [ከጌታ ጎን የሚቀመጥ]
¤ ንስር ሠራሪ
¤ ልዑለ ስብከት
¤ ምድራዊው መልዐክ
¤ ዓምደ ብርሃን
¤ ሐዋርያ ትንቢት
¤ ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
¤ ኮከበ ከዋክብት

† በዚህች ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ: ከአባቱ ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች::


†   🕊   አባ ሙሴ ዻዻስ   🕊  †

እሥራኤላዊ ሲሆኑ ከአቡነ ሰላማ ቀጥለው የመጡ የሃገራችን ዻዻስ ናቸው:: ፍጹም ገዳማዊና ትጉህ: ባለ ረዥም ዕድሜ ጻድቅም ናቸው::

ገዳማቸው ወሎ ውስጥ ቢገኝም አስታዋሽ ያጣ ይመስላል:: መናንያኑ ለዕለት እንኩዋ የሚቀምሱት አጥተው ሲቸገሩ መመልከቱ እጅግ ያማል::

† በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር:: ቸሩ ጌታ ስም አጠራራቸው ካማረና ከከበረ ወዳጆቹ በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[  † መስከረም [ ፬ ] 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  🌼  ]

፩. ቅዱስ ኢያሱ ወልደ ነዌ [ነቢይና መስፍን]
፪. ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ [ልደቱ]
፫. ቅዱሳን ዘብዴዎስና ማርያም ባውፍልያ
፬. አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት
፭. አባ ሙሴ ዻዻስ

[  † ወርኀዊ በዓላት  🌼   ]

፩. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

† " አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" † [ኢያሱ.፳፬፥፲፬] (24:14)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
2024/11/15 07:55:16
Back to Top
HTML Embed Code: