Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
[ 🕊 † ቅዱስ ያዕቆብ ርዕሰ አበው † 🕊 ]

† የአባቶች አለቃ የተሰኘ ቅዱስ ያዕቆብ ለሁለቱ ታላላቅ አባቶቹ እርሱ ሦስተኛቸው ነው:: እነርሱን መስሎ: እነርሱንም አህሎ በጐዳናቸው ተጉዟል:: በፈቃደ እግዚአብሔር ብኩርናን ከኤሳው ተቀብሎ ወደ ሶርያ ሲሸሽ ቤቴል [ፍኖተ ሎዛ] ላይ ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ግሩም ራዕይን አይቷል::ይህችውም የወርቅ መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት::
"አንቲ ውዕቱ ሰዋስው ዘርእየ ያዕቆብ" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም [ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ]

ተነስቶም "ዛቲ ይእቲ ኈኅታ ለሰማይ: ዝየ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር - ይህች የሰማይ ደጅ ናት: ቤተ እግዚአብሔርም ይታነጽባታል::" ብሎ ትንቢት ተናግሯል::

ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል:: ከሁለቱ ሚስቶቹ [ልያና ራሔል] : ከሁለቱ ደንገጥሮች አሥራ ሁለት ልጆችን ወልዷል::

ከአጐቱ ከላባ ዘንድ ለሃያ አንድ ዓመታት አገልግሎ: ሃብት ንብረቱን ጠቅልሎ ወደ ርስቱ ከነዓን ሲመለስ ለብቻው ራቅ ብሎ ይጸልይ ገባ:: በዚያም እግዚአብሔር ሲታገለው አደረ:: [ይኸውም የፍቅርና የምሥጢር ነው::] ለጊዜው ጌታ ያዕቆብን "ልቀቀኝ?" ቢለው "ካልባረከኝ አለቅህም?" አለው:: ጌታም ስሙን "እሥራኤል" ብሎ ባርኮታል::

ቅዱስ ያዕቆብ በስተእርጅና ብዙ መከራ አግኝቶታል:: ልጁን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሽጠው "አውሬ በላው" ብለውታልና በለቅሶ ዓይኑ ጠፋ:: በረሃብ ምክንያትም በመቶ ሰላሳ ዓመቱ ከሰባ አምስት ያህል ቤተሰቦቹ ጋር ወደ ግብጽ ወረደ:: በዚያም ለሰባት ዓመታት ኑሮ በመቶ ሰላሳ ሰባት ዓመቱ ዐርፏል:: ልጆቹም ቀብረውታል::

† በሰማይና በምድር ከሞላው ከአባቶቻችን በረከት ፈጣሪያቸው አብዝቶ: አትርፎ: አትረፍርፎም ያድለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አብርሃም [ የአባቶች አለቃ ]
፪. ቅዱስ ይስሐቅ [ የአባቶች አለቃ ]
፫. ቅዱስ ያዕቆብ [ የአባቶች አለቃ ]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪. ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
፫. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ
፬. ቅዱሳን እንድራኒቆስና አትናስያ

† " አብርሃምንና ይስሐቅን: ያዕቆብንም: ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግስት ባያችሁ ጊዜ: እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል::" † [ሉቃ. ፲፫፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር ዓመታዊ የፍልሠት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ 🕊 † ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር  † 🕊 ]

† በቤተ ክርስቲያን ያሉ አበው ሊቃውንት እንደሚሉት ከቅዱሳን በቁመቱ የአባ አርሳኒን ያክል ረዥም አልነበረም:: እርሱ እንደ ዝግባ ቀጥ ያለ ነበር:: በዚያው ልክ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስን [ዛሬ የምናከብረውን] ያህል አጭር አልነበረም:: በዚህ ምክንያት ይሔው ለዘለዓለም " ዮሐንስ_ሐጺር- አጭሩ አባ ዮሐንስ" ሲባል ይኖራል::

ሊቃውንትም ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ :-
"ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ:
ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ" ይላሉ:: "ቁመቱ እጅግ ያጠረ: ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን" እንደ ማለት ነው::

ቅዱሱ የተወለደው በ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ነው:: ወላጆቹ ምንም ከሥጋዊ ሃብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጐውን ሕይወት አስተምረውታል:: ወደ ምናኔ የገባው ገና በ፲፰ [18] ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል::

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው: በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን "ምን አጠፋሁ?" ብሎ እንኩዋ ሳይጠይቅ "አባቴ ሆይ! ማረኝ?" እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር::

ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው: እርሱም እርሱው ተደብድቦ: እርሱው ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ ፯ [7]ቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል::

አባ ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም:: አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምሕርት ስለ ነበረ ነው እንጂ::

አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምሕሩ ቀርቦ "አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀው:: [የአካባቢው ጅብ መናጢ ነበር] አባ ባይሞይ ግን "ይዘህልኝ አምጣው" አለው:: ትዕዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርሃ ወርዶ: ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል::

ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው:: "ምን ላድርገው አባ?" አለው:: "ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው:: ከዚያ አምጥተህ አብላኝ" ሲል መለሰለት:: ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ "እሺ" ብሎ ወስዶ ተከለው::

ከዚያም ለ፪ [2] ዓመታት ሳይታክት ውሃ አጠጣው:: ውሃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ ፲ [10] ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር:: ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ::

በ፫ [3]ኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ: ደግሞም አፈራ:: ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምሕሩ "አባቴ! እንካ ብላ" ብሎ ሰጠው:: አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም:: እጅግ አደነቀ: አለቀሰም::

ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት አላቸው :- "ንሱ ብሉ: በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው::" ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለ፲፪ [12] ዓመት አስታሞታል::

መምሕሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው:: "ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው" ብሏቸው ዐርፏል:: ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በሁዋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል:: ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኩዋል::

መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር:: ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጥና ገንዘቡን ለነዳያን ያን ያካፍል ነበር::

አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ [ተመስጦ] መጣበት:: ሰማያት ተከፍተው: ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት ሚካኤል እና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ::

"እጹብ: እጹብ" እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ "ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?" ቢለው "እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል - ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?" ብሎታል:: ገዢውም ደንግጦ "እብድ መነኩሴ" ብሎት ሔዷል::

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ ባቢሎን [የአሁኗ ኢራቅ] ሒዶ ከተመለሰ በሁዋላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል:: ለ፬፻ [400] ዓመታት በዚያው ቆይቷል::

በ፰፻፳፭ [825] ዓ/ም ግን በአባ ዮሐንስ ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ ገዳመ_አስቄጥስ ተመልሷል:: ቅዱሱ ያረፈው ጥቅምት ፳ [20] ቀን ሲሆን ዛሬ ሥጋው የፈለሠበት ነው:: በዚህ ዕለትም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና የታላቁ ቅዱስ_መቃርስ ሥጋ በተገናኙ ጊዜ ግሩም ተአምር ተደርጉዋል:: ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገባም ታላቅ የብርሃን ጐርፍ ሲፈስ ታይቷል::

ሰማያዊ መዓዛም አካባቢውን ሞልቶታል:: ከዻዻሳቱ አንዱ እባረካለሁ ብሎ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ቢገልጠው አካባቢው ተናወጠ:: መባርቅትም [መብረቆች] ተብለጨለጩ:: ደንግጠው ቶሎ ቢያለብሱት ጸጥታ ሆኗል:: በዚህ ሁሉ ደስ ያላቸው አበው ቅዱሱን በዝማሬ ሲያወድሱት ውለዋል::

† አምላከ ቅዱሳን የሐጺር ቅዱስ ዮሐንስን መታዘዙን: ትሕትናውን: ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን:: በበረከቱም ይባርከን::

🕊

[  † ነሐሴ ፳፱ [ 29 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር [ፍልሠቱ]
፪. ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
፫. ቅዱሳን ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ [ሰማዕታት]
፬. አባ ባስልዮስ ጻድቅ [ዘትግራይ]

[  † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪. ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫. ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፭. ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
፮. ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ [ጻድቅና ሰማዕት]

† " እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ 'የማንጠቅም ባሪያዎች ነን: ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል' በሉ::" † [ሉቃ.፲፯፥፲] (17:10)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ እና ለቅዱስ ሚልክያስ ነቢይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

† መሐሪ እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ በዛ: ሰውነታችሁ ከፋ ሳይል በአባታዊ ርሕራሔው ጠብቆ ይሔው ወርኀ ነሐሴን በሰላም አስፈጸመን:: አይመስለንም እንጂ በእነዚህ ሰላሳ ቀናት ሚሊየኖች አንቀላፍተዋል: ሚሊየኖች በደዌ ዳኝነት ተይዘዋል: በርካቶቹም ከሃይማኖታቸው ወጥተዋል::

እኛ ይህ ሁሉ ያልደረሰብን በጐ ስለሆንን አይደለም:: ይልቁኑ ቸርነቱ በእኛ ላይ ስለበዛ ብቻ ነው እንጂ:: አሁንም በሰላም ከአዲሱ ዘመን እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::
በዚህች ዕለት ደግሞ እነዚህን ቅዱሳን እናከብራለን::

[ 🕊 † ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ † 🕊 ]

† ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ዓሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

ከእርሱም እያገለገለ ለስድስት ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው [ወልደ ዘብዴዎስ] ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

ጌታ ከጾም [ከገዳመ ቆረንቶስ] በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ::" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: [ዮሐ.፩፥፵፯] (1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት
"ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ [ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ::]" ብሏል::
[መልክዐ ስዕል]

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ [ፈጣን] አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: [ዮሐ.፮፥፱ (6:9), ፲፪፥፳፪ (12:22) ለሦስት ዓመታት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ: ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል::

ይህች ቀን ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ የተነጋገረባትና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ያዳነባት ናት::
ቅዱስ እንድርያስ ሰላሳ ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሰላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል::

ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር [እንዲሁ ሰው] መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ:
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ:
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ::" ብሎታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ ያረፈው ታኅሣሥ 4 ቀን ነው::

[ 🕊 † ቅዱስ ሚልክያስ ነቢይ † 🕊 ]

† ሚልክያስ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ሲሆን "የመጨረሻው ነቢይ" እየተባለ ይጠራል:: ለዚህ ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው::
፩ኛ. ከእርሱ በኋላ የተጻፈ ጥሬ የትንቢት መጽሐፍ የለም::
፪ኛ.እርሱ ካረፈ በኋላ ያለው ዘመን "ዘመነ ካህናት" በመሆኑ ምንም ነቢያት በየጊዜው ባይጠፉ ጐልተው የተነገረላቸው ጥቂቶቹ ናቸው::

ቅዱሱ የተወለደው ቅ/ል/ክርስቶስ ስድስት መቶ ዓመት አካባቢ ሲሆን ከሚጠት [ከባቢሎን ምርኮ መልስ] ሕዝቡን ገስጿል:: ሕዝቡ ከሰባ ዓመት መከራ እንኳን ተመልሶ ኃጢአትን መሥራትን ቸል አላለም ነበር::

በተለይ የልጅነት ሚስታቸውን የሚያታልሉትን ገስጿል:: [ሚል.፪፥፲፬] (2:14) ስለ አሥራትና በኩራትም ተናግሯል:: [ሚል.፫፥፰] (3:8) እመቤታችን ድንግል ማርያምንም በንጽሕት አዳራሽ መስሎ ተናግሯል::
"ጽርሕ ንጽሕት ዘሚልክያስ" እንዳሉ አባ ሕርያቆስ:: [ቅዳሴ ማርያም]

ነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ ፈጣሪውን አገልግሎ: ሕዝቡን መክሮ ዐርፏል:: ሚልክያስ ማለት "መልአክ: አንድም የተላከ" ማለት ነው:: ነገዱ ከነገደ ይሳኮር ነው::

† አምላከ ቅዱሳን አሥራ ሁለቱን ወራት እንደ ባረከልን አሥራ ሦስተኛዋንም ለንስሐ ቀድሶ ይስጠን:: ከቅዱሳኑም በረከትን ያካፍለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፴ [ 30 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ሚልክያስ ነቢይ
፫. አባ ሙሴ ዘሃገረ ፈርማ

[  † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ [ሐዋርያ]
፪. አባ ሣሉሲ ክቡር
፫. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፭. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት

† "ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ:: ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል:: 'መፋታትን እጠላለሁ' ይላል የእሥራኤል አምላክ: የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር::" † [ሚል. ፪፥፲፭]

† " ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃቹሃል:: እናንተም 'የሰረቅንህ በምንድን ነው?' ብላቹሃል:: በአሥራትና በበኩራት ነው:: እናንተ: ይህ ሕዝብ ሁሉ እኔን ሰርቃቹሃልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ::" † [ሚል. ፫፥፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለተባረከ ወር ጳጉሜን እና ለቅዱሳኑ ዮሐንስ መጥምቅ : ዑቲኮስ ሐዋርያና ቀሲስ አባ ብሶይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊 †   ወርኀ ጳጉሜን  † 🕊  ]

† እግዚአብሔር አዝማናትን የፈጠራቸው ለሰው ልጆች ጥቅም መሆኑ ይታወቃል:: እርሱ ባወቀ: በረቂቅ ሥልጣኑ ዓለምን ፈጥሮ: ጊዜያትን እንዲከፍሉ ብርሃናትን [ፀሐይ: ጨረቃ: ከዋክብትን] ፈጥሮልናል::

ጊዜያትንም በደቂቃ: በሰዓት: በቀን: በሳምንት: በወር: በዓመታት: በኢዮቤልዩ: በክፍላተ ዘመናት እንድንቆጥር ያስማረንም እርሱ ነው:: የሰከንድ ፭ መቶ ፵ ሺህ [540,000] ክፋይ ከሆነችው 'ሳድሲት' እስከ ትልቁ ቀመር ፭፻፴፪ [532 ዓመት] ድረስ እርሱ ለወደዳቸው እንዲያስተውሉት ገልጧል::

በየዘመኑም በቅዱስ ድሜጥሮስ: በቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ : በቅዱስ አቡሻኽር እና በሌሎቹም አድሮ መልካሙን አቆጣጠር አስተምሯል:: ሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የአሥራ ሦስት ወራት የፀሐይ ጸጋ [thirteen months sun shine] ያላት: አራቱ ወቅቶች የተስማሙላት ናት::

† ሌላው ዓለም ወሮችን 31,30,29 [28] እያደረገ
ሲጠቀም እኛ ግን እንደ ኖኅ [ዘፍ.፰፥፩-፭] (8:1-15) አቆጣጠር ወሮችን በሠላሳ ቀናት ወስነን: ጳጉሜንን ለብቻዋ እናስቀምጣለን:: ጳጉሜን 'ኤጳጉሚኖስ' ከሚል የግሪክ [ጽርዕ] ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም 'ትርፍ: ጭማሪ' እንደ ማለት ነው::

የወርኀ ዻጉሜን አምስቱ [ስድስቱ] ቀናትም ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ እንደ መሆናቸው ብዙ ምሳሌያት [ምሥጢራት] አሏቸው:: ዋናው ግን በዚህ ጊዜ ዳግም ምጽዓት ይታሠባል:: ጊዜውንም በጾምና በጸሎት ሊያሳልፉት ይገባል:: ግን በፈቃድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም::

[ 🕊 †  ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ  † 🕊 ]

¤ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
¤ በማኅጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
¤ በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
¤ እሥራኤልን ለንስሐ ያጠመቀ
¤ የጌታችንን መንገድ የጠረገ
¤ ጌታውን ያጠመቀና
¤ ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::

† ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን :-
ነቢይ:
ሐዋርያ:
ሰማዕት:
ጻድቅ:
ገዳማዊ:
መጥምቀ መለኮት:
ጸያሔ ፍኖት:
ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::

† ቅዱሱ በዚህች ዕለት ወደ እሥር ቤት ገብቷል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሔሮድያዳን በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር:: ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ: ዘኢያደሉ ለገጽ - ፊት አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው::

ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው: ያከብረውም ነበር:: በኋላ ግን ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት: በተለይ ደግሞ ከሰባት ቀናት በኋላ ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ
ጥሎታል:: ለሰባት ቀናት በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አንገቱን እንዴት እንዳስቆረጠው ዕለቱን ጠብቀን እንመለከታለንና የዚያ ሰው ይበለን::

[ 🕊 †  ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ † 🕊 ]

† ቅዱሱ ሐዋርያ ጭራሽ ከነስማቸው እንኳ እየተዘነጉ ከሔዱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቁጥሩም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ነው:: በወጣትነት ዘመኑ የጌታችን ደቀ መዝሙር መሆንን መርጦ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ምሥጢረ ወንጌልን ጠንቅቆ ተምሯል::

መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም እንደ መጠኑ ተቀብሎ ለአገልግሎት ወጥቷል:: በመጀመሪያ የወንጌላዊው ዮሐንስ ተከታይ ሁኖ ብዙ ምሥጢራትን ተካፍሏል:: ቀጥሎም ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ ብዙ አሕጉራትን በስብከተ ወንጌል አዳርሷል::

በመጨረሻም በእስያ አካባቢ ለብቻው ተጉዞ: ብዙ ነፍሳትን ማርኮ: ጣዖታትን አጥፍቷል:: ስለዚህ ፈንታም በእሳት: በስለትና በግርፋት ብዙ መከራዎችን አሳልፏል:: በዚህች ቀንም በበጐው እርግና [ሽምግልና] ዐርፏል::

[ 🕊 †  ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ  † 🕊 ]

† ከ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ካህናት አንዱ የነበረው አባ ብሶይ ለአገልግሎት ወጥቶ ሲመለስ የቤተሰቦቹ ቤት ሰው አልነበረበትም:: "የት ሔዱ?" ብሎ ቢጠይቅ "ወንድምህ አባ ሖር እና እናትህ ቅድስት ይድራ ወደ እስክንድርያ ሔደዋል:: በዚያም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ተሰውተዋል::" አሉት::

በማግስቱ የኔ ብጤዎችን ጠርቶ ሃብቱን: ንብረቱን: ቤቱን አካፈላቸው:: ለራሱ ግን አንዲት በትር እና ሦስት የዳቦ ቁራሾች ይዞ ጉዞ ተነሳ:: ወደ እስክንድርያ እንደ ደረሰ አፈላልጐ የቤተሰቦቹን መቃብር አገኘ:: ከፊታቸው ወድቆም የናፍቆት ለቅሶን አለቀሰ::

ወዲያውም እንዲህ አላቸው:- "ፈጥኜ ወደ እናንተ ስለምመጣ ጠብቁኝ:: ደግሞም ጸልዩልኝ::" ከዚያ ተነስቶ በመኮንኑ ፊት ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት መሰከረ:: በዚህ ምክንያት ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል:: ከወገኖቹም ጋር ተቀብሯል::

† አምላከ ቅዱሳን ተረፈ ዘመኑን ባርኮ ለአዲሱ ዘመን በቸር ያድርሰን:: ከወዳጆቹም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ [የታሠረበት]
፪. ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ [ከሰባ ሁለቱ አርድእት]
፫. ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ [ሰማዕት]
፬. አባ ጳኩሚስ /ባኹም [የሦስት ሺ ቅዱሳን አባት]
፭. አባ ሰራብዮን /ሰራፕዮን [የአሥር ሺ ቅዱሳን አባት]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

- የለም

[  † " ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው:: የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ::" † [ማቴ. ፲፩፥፯-፲፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

       #የተባረከ_የጳጒሜን_ወር_ባተ

            #ጳጒሜን ፩ (1) ቀን።

እንኳን #ለወንጌላዊው_ለቅዱስ_ዮሐንስ ረድእ #ለሐዋርያውና_ለሰማዕቱ_ለከበረ_ቅዱስ_ዑቲኮስ ለዕረፍት በዓል፣ #ለአባ_ሖር_ወንድም ለሰማዕቱ #ለቀሲስ_ቅዱስ_አባ_ብሶይ_ለዕረፍት በዓል አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_ጳኩሚስና_ከአባ_ሰራብዮን ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                            
#በዚች_ቀን_መጥምቀ_መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ማግባት የለብህም ብሎ ይገስጸው ስለነበር በሳምንቱ በልደቱ ቀን መስከረም 2 እስኪገለው በዛሬው ዕለት ወደ እስር ቤት ያስገባበት ነው።

                            
#የሐዋርያው_የቅዱስ_ዮሐንስ_ረድእ_ቅዱስ_ዑቲኮስ፦ ይህም ቅዱስ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ሲያገለግለውና ሲታዘዘው ኖረ። ከዚያም ከሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ጋራ ሔደ እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲሰብክ አዘዘው በአረማውያንና በዮናናውያንም መካከል ሰበከ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደማወቅ ብዙዎችን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።

የጣዖታት ቤቶችን አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ከሀድያንም ብዙ መከራ ደረሰበት መታሠርና ብዙ ቀኖች ግርፋቶችን በመቀበል የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ እሥር ቤት ከምግብ ጋር መጥቶ ይመግበዋል።

ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጣሉት እሳቱም ከቶ አልነካውም ሁለተኛም ለአንበሶች ጣሉት እነርሱም እንደ በጎች ሆኑለት።

ከዚህም በኋላ ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ሔደ ሲሔድም የእግዚአብሔር መልአክ ይመራውና ያጸናናው ነበር ተጋድሎውንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ጳጉሜን 1 ቀን ወደ እግዚአብሔር ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ዑቱኮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
                     

                           
#የአባ_ሖር_ወንድም_ቀሲስ_ቅዱስ_ብሶይ፦ ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ አገር ክብር ካላቸው ወገኖች ውስጥ ነው ስለ ዕውቀቱና ስለ ሃይማኖቱ ጽናት ቅስና ተሾመ።

ወንድሙ አባ ሖርና እናቱ ወደ ግብጽ አገር ሒደው በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሥጋቸውን ያይ ዘንድ ሔደ። ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ሰጠ ከሦስት እንጀራና ከሚመረጐዛት ከአንዲት የሰኔል በትር በቀር ምንም አልያዘም ነበር።

ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የዘመዶቹ በድን ወዳለበት ሰዎች መርተው አደረሱት የእናቱንና የወንድሙንም ሥጋ በአየ ጊዜ ከእርሳቸው ስለ መለየቱ መሪር ልቅሶን አለቀሰ።

ከዚህም በኋላ ወደ መነኰንኑ ሒዶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ለመኰንኑም የአባ ሖር ወንድም እንደሆነ ነገሩት መኰንኑም ታላቅ የደንጊያ ምሰሶ በሆዱ ላይ እንዲአቆሙበት አዘዘ ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ።

ከዚህም በኋላ ደግሞ ሥጋውን ከወንድሙና ከእናቱ ሥጋ ደግሞ ቊጥራቸው ሰማንያ ስምንት ከሆነ ከሌሎች ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአንድነት ያቃጥሉ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ወደ እሳት በጨመሩአቸውም ጊዜ ከቶ እሳቱ አልነካቸውም።

ምዕመናን ሰዎችም መጥተው የከበሩ የአባ ሖርና የወንድሙ የአባ ብሶይን የእናታቸውንም ሥጋ ወሰዱ። አገርዋ ዲብቅያ የሚባል የቅድስት ዳሞንንም ሥጋ አገሩ በረሞን ከሚባል የቅዱስ ቢማኮስም ሥጋ ጡልያ ከሚባል አገር የመጣ የውርሱኑፋን ሥጋም አብስላሲ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሷቸው በመርከብ ጫኗቸው። የስደቱ ወራት እስከሚፈጸም አክብረው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው።

ከዚህም በኋላ አብያተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ ከእርሳቸውም ተአምራት ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኑ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጕሜን 1 ስንክሳር።

                             
"#ሰላም_ለዑቲኮስ_ዘተሰምየ_ሱታፎ። ለወንጌላዊ ዮሐንስ ለንጹሐ መላእክት ዘተዐጽፎ። መኰንን ዕልው አመ ውስተ እሳት ገደፎ። ካዕበኒ እምህየ ለአናብስት አኅለፎ። በአናብስት ስእኑ ይግሥሥዎ ወእሳት ይልክፎ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጒሜን_1

                            
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ጽድቀ ወምጽዋተ ያበድር እግዚአብሔር። እግዚአብሔር ይሁብ ክብረ ወሞገሰ። እግዚአብሔር ኢያስተፄንሶሙ እምበረከቱ ለእለ የሐውሩ በየዋሃት"። መዝ 83፥11። የሚነበቡት መልዕክታት ፊል 1፥12-25፣ 1ኛ ዮሐ 5፥1-6 እና የሐዋ ሥራ 18፥21-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 14፥1-7። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም፡ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

                        
እንኳን #ለጾመ_ዮዲት_ለጾመ፤ የኢትዮጵያ ንጉሥ #ዐፄ_ናኦድ_ስምንተኛው_ሺህ እንዳያዩት ለጾሙት  (የፈቃድ ጾም) እግዚአብሔር አምላከ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                        
  "ሰብአ ነነዌ #ጸዊሞሙ_ተማኅሊሎሙ ድኅኑ እሞቶሙ" ትርጉም፦ የነነዌ ሰዎች #ጾመውና_ምሕላ ይዘው ከሞት ዳኑ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው_ላይ

                         
እግዚአብሔር አምላክ ጾሙንና ጸሎቱን ተቀብሎ በአዲሱ ዓመት በዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ በአገራችን ኢትዮጵያዊ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት አስወግዶ ሰላም፣ ፍቅርን፣ አድነትንና መተሳሰብን ይላክል፤ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን በቅዱስ ሲኖዶስ በአባቶችን ዘንድ ያለው መከፍፈል አስወግዶ አንድ ያድርግልን። መልካም የጾምና የጸሎት ዕለታት ለሁላችንም ይሁንልን።
2024/09/27 22:20:46
Back to Top
HTML Embed Code: