Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
በደብረ ሊባኖስ ውስጥ የቆየችው ቅድስት እናት ተጋድሎዋን የፈጸመችው ግን ጣና ሐይቅ ውስጥ ነው:: በተለይ ለ፳፪ [22] ዓመታት ሐይቁ ውስጥ አካሏ አልቆ: አሣ በሰውነቷ ውስጥ እስከሚያልፍ ድረስ ተጋድላለች:: በቀኝና በግራ ፲፪ [12] ጦሮችን ተክላም ጸልያለች::

ብዙ ኃጥአንን አማልዳ: ፲፪ [12] ክንፎችን አብቅላ: ከፍ ከፍ ብላለች:: ከርሕራሔዋ ብዛት የተነሳ ሰይጣንን እንኩዋ ለማስታረቅ ሞክራለች:: ጌታም ከሲዖል ነፍሳትን እንድታወጣ ፈቅዶላታል:: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያረፈችው በዚህ ዕለት ሲሆን አጽሟ ዛሬ በራሷ ገዳም [ጣና ዳር] ይገኛል::

[ † 🕊  ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ  🕊 † ]

ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል ሃገር የፈለቀ የንጋት ኮከብ: ጻድቅ: ገዳማዊ: ዻዻስ: ሐዋርያ: ሰማዕትና ሊቅ ነው:: የዚህን ቅዱስ ተጋድሎ እንደ እኔ ያለው ሰው አይቻለውም:: የእርሱ ሕይወት ክርስትና ምን እንደ ሆነ ያሳያል::

- " ቅዱስ ቶማስ " ከልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተማረ
- ገና በወጣትነቱ መንኖ ገዳም የኖረ
- መርዓስ በምትባል ሃገር ዽዽስና ተሹሞ በእረኝነት ያገለገለ
- በሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስትና የመለሰ
- በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው::

ጨካኞቹ ቅዱሱን ለ፳፪ [22] ዓመታት አካሉን እየቆራረጡ ለጣዖታቸው ያጥኑ ስለ ነበር ፪ [2] እግሮቹ: ፪ [2] እጆቹ: ፪ [2] ጀሮዎቹ: ፪ [2] አፍንጫዎቹ: ፪ [2] ዐይኖቹ: ሁሉ አልነበሩም:: ነገር ግን እንዲህም ሆኖ አልሞተም ነበር::

በመጨረሻም በዘመነ መናፍቃን አርዮስን ካወገዙት ፫፻፲፰ [318]ቱ ሊቃውንት እንዳንዱ ተቆጥሯል:: ቅዱስ ቶማስ ዽዽስና በተሾመ በ፵ [40] ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል:: የጻድቃንን: የሰማዕታትን: የሐዋርያትንና ሊቃውንትን አክሊልም ተቀብሏል::

† የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች †

፩. ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ
፪. ፍስሐ ፅዮን
፫. ሐዲስ ሐዋርያ
፬. መምሕረ ትሩፋት
፭. ካህነ ሠማይ
፮. ምድራዊ መልዐክ
፯. እለ ስድስቱ ክነፊሁ [ባለ ስድስት ክንፍ]
፰. ጻድቅ ገዳማዊ
፱. ትሩፈ ምግባር
፲. ሰማዕት
፲፩. የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ
፲፪. ፀሐይ ዘበፀጋ
፲፫. የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ
፲፬. ብእሴ እግዚአብሔር [የእግዚአብሔር ሰው]
፲፭. መናኒ
፲፮. ኤዺስ ቆዾስ [እጨጌ]

† እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:: †

አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ ምልጃ ክብራቸውን ያድለን:: በረከታቸውም በዝቶ ይደርብን::

🕊

[  † ነሐሴ ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት [ መምሕረ ትሩፋት ]
፪. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ [ ጻድቅት ]
፫. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፬. አበው አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ

[  †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ ጻድቅ ኤዺስቆዾስ ]
፫. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፬. "24ቱ" ካኅናተ ሰማይ [ ሱራፌል ]
፭. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም

† " ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል::" † [ማቴ.፲፥፵] (10:40)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from Bketa @¥
ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ
ኦርቶዶክሳውያን እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ የዕረፍት መታሰቢያ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ
!!
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት እና ለታላቁ አባ ቢጻርዮን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ †  🕊 ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት 🕊 † ]

† ቅዱሱ በ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘ የነበረ አረማዊ ሰው ሲሆን ከከሃዲው መክስምያኖስ ወታደሮችም አንዱ ነበር:: "ሊቀ መሓዛት" ይሉታል: የጐበዛዝቱ አለቃም ነበር:: ይህ ሰው ምንም ክርስቲያን አይሁን እንጂ በልቡ ቅንነት ተገኝቶበታል:: እንደ አሕዛብ ልበ ድንጋይ አልነበረም::

በወጣትነቱም አንዲት ደመ ግቡ ሴት አግብቷል:: ይህች ሴት 'ኤልያና' ስትባል የተባረከች ክርስቲያን ናት:: እርሱ ግን አያውቅም:: ከተጋቡ ከዓመታት በሁዋላ ጌታ እግዚአብሔር ስለ ሚስቱ ጸሎት በጐ ጐዳና ሊመራው ፈለገ::

እንድርያኖስ ሁሌም በየቀኑ ክርስቲያኖች ደማቸውን ሲያፈሱ ይመለከታል:: የትእግስታቸው መጠንም ይገርመው ነበር:: በተለይ አብዛኞቹ በመከራው ደስተኞች ነበሩ:: ነገሩ ግራ ቢያጋባው ፳፬ [24] ባለንጀሮች ሊገደሉ ወደ ታሠሩበት ቦታ ሒዶ ጠየቃቸው::

"ምን ልታገኙ ነው ግን ይሕንን ሁሉ ስቃይ በአኮቴት [በምስጋና] የምትቀበሉት?" ቢላቸው "በሰማይ በክርስቶስ ዘንድ የሚጠብቀንን የክብር ሕይወት ሥጋዊ አንደበት አከናውኖ መናገር አይቻለውም:: ዝም ብሎ 'ዕጹብ: ዕጹብ' እያሉ የሚያደንቁት ነው እንጂ" አሉት::

እርሱም ተደላድሎ ተቀምጦ "እስኪ በደንብ አስረዱኝ" አላቸው:: ከዓለም መፈጠር እስከ ጌታችን የማዳን ሥራ: አልፎም ስለ ፍርድ ቀን በጥዑም አንደበታቸው አስተማሩት:: ቅዱስ እንድርያኖስ በቅጽበት ልቡ ወደ ክርስቶስ ፍቅር ሸፈተ::

በፍጥነት ተነስቶ የራሱን ስም ከሰማዕታቱ ፳፭ [25]ኛ አድርጐ አጻፈ:: ንጉሡ ይሕንን ሲሰማ "አብደሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የለም! ዛሬ ገና ከእብደቴ ተመለስኩ" በማለቱ ከ፳፭ [25]ቱ ቅዱሳን ጋር ታሠረ:: ቅድስት ኤልያና [ሚስቱ] ነገሩን ስትሰማ ፈጽሞ ደስ አላት::

ወደ እስር ቤት ሒዳ "አይዞህ በርታ! ስለ ክርስቶስ የሞትክ ቀን ብቻ እኮራብሃለሁ" ብላ: እግራቸውን አጥባቸው ተመለሰች:: በሚገደሉበት ቀንም ልሰናበታት ብሎ ቅዱስ እንድርያኖስ ቢመጣ ቅድስት ኤልያና ቤቷን ዘግታ ገሠጸችው:: እርሷ ክዶ የመጣ መስሏት ነበር::

እርሱ ግን የሚስቱን የእምነት ጥንካሬ ተረዳ:: ቅዱሱና ፳፬ [24]ቱ ቅዱሳን ለቀናት ብዙ መከራን እየተቀበሉ ሰነበቱ:: አካላቸውን እየቆራረጡ: ደማቸውን እያፈሰሱ ሆዳቸውንም እየቀደዱ መከራን አጸኑባቸው:: በመጨረሻው በዚህች ቀን ሲገደሉ ቅድስት ኤልያና "የእኔን ባል አስቀድሙት" አለች:: [የሌሎቹን አይቶ እንዳይደነግጥ ነው]

እንዳለችውም የእርሱንና የባልንጀሮቹን ጭን ጭናቸውን እየሰበሩ ገድለዋቸዋል:: ቅድስት ኤልያናንም መሣፍንቱ "ካላገባንሽ" እያሉ ሲያስቸግሯት ተሰዳ ሒዳ ከሰማዕታቱ መቃብር ላይ አለቀሰች:: ጌታም ጠርቷት እዚያው ዐረፈች::

[ †  🕊 ታላቁ አባ ቢጻርዮን  🕊 † ]

ታላቁ ገዳማዊ ሰው የመጀመሪያ መነኮሳት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ሲሆን ዓለምን ንቆ ከመነነ በሁዋላ ከአባ እንጦንስ ዘንድ መንኩሷል:: ከእርሳቸው ዘንድ በረድእነት ለብዙ ዓመታት አገልግሏል:: አገልግሎቱን በፈጸመ ጊዜም አስኬማን ተቀብሎ ወደ በርሃ ወጥቷል::

ምንም የራሱን ገዳም ባይመሠርትም በ4ኛው መቶ ክ/ዘ የምናኔ ሕይወት እንዲስፋፋ ካደረጉ አበው እርሱ ዋነኛው ነው:: በተጋድሎ ዘመኑም የሚታወቅባቸው ነገሮች አሉ:: ከእነሱም ጥቂት እንጠቅሳለን:: አባ ቢጻርዮን :-

፩. ጾሙም ሆነ ጸሎቱ በ፵ [40] ቀናት የተወሰነ ነበር:: ጾምን ከጀመረ ያለ ፵ [40] ቀን እህል አይቀምስም:: ለጸሎት ከቆመም የሚቀመጠው ከ፵ [40] ቀናት በሁዋላ ነው::
፪. ሁሌም በየበርሃው እየዞረ ያለቅሳል:: "ምነው" ሲሉት "ወገኖቼ አለቁብኝ: ደሃም ሆንኩ" ይላቸው ነበር:: እንዲህ የሚለው አጋንንት ብዙ ነፍሳትን እየነጠቁ ሲወስዱ ስለሚመለከት ነው::
፫. በየገዳማቱ እየለመነ ለነዳያን ያከፋፍል ነበር::
፬. ሐፍረቱን ከሚሸፍን ጨርቅ በቀር ምንም ልብስ አይለብስም ነበር::
፭. ውዳሴ ከንቱን አምርሮ ይጠላ ነበር::
፮. በባሕር ላይ ተራምዶ ሲሔድና እግሮቹ ሳይርሱ ሲቀሩ አበው ተመልክተዋል::
፯. መርዝነት ያለውን ውሃም ጣፋጭ አድርጐታል::

† ቅዱሱ ድውያንን ፈውሶ: አጋንንትን ከአካባቢው አሳዶ: ብዙ ፍሬ አፍርቶ: ገዳም ውስጥ በገባ በ፶፯ [57] ዓመቱ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

† ቸር አምላክ በክብረ ቅዱሳን ይከልለን:: ከበረከታቸውም ያብዛልን::

[  † ነሐሴ ፳፭ [ 25 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እንድርያኖስ ሰማዕት
፪. "24ቱ" ሰማዕታት [ማሕበሩ]
፫. ቅድስት ኤልያና [ሚስቱ]
፬. ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ኤልያኖስና እህቱ አውዶክስያ [ሰማዕታት]

[  † ወርሐዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪. ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫. ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭. አቡነ አቢብ [አባ ቡላ]
፮. ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

† " ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን: የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው:: እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእርሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና: በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር:: በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ:: እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን:: ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን::" † [፪ቆሮ.፭፥፲፰] (5:18)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለእናታችን ብጽዕት ሣራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

[ †  🕊 ቅድስት ሣራ ብጽዕት  🕊 † ]

† አበው እናታችን ሣራን " ቡርክተ ማሕጸን" ይሏታል:: [የቅዱሱ ዘር የይስሐቅ እናት ናትና] በዚያውም ላይ የደጉ ሰው የአብርሃም ሚስት ናት:: ልክ በዓለም ታሪክ "ከጠንካራና ስኬታማ ወንዶች ጀርባ ጠንካራ ሴቶች አሉ" እንደሚባለው ከአብርሃም አባታችን ስኬታማ የቅድስና ሕይወት ጀርባ ብጽዕት ሣራ አለች::

ለአብርሃም አባታችን መጽሐፍ የተናገረው ክብር ሁሉ ለቅድስት ሣራ ይገባታል:: አንድም ገንዘቧ ነው:: ቅድስቷ እናት ደጉ አብርሃምን ያገባችው ገና በከላውዴዎን [በ፪ቱ ወንዞች መካከል] ሳለ ነው:: ገና ከልጅነቷ ጀምራ አብርሃምን "ጌታየ" እያለች ታገለግለው እንደ ነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል:: [፩ዼጥ.፫፥፭] (3:5)

በዚህም ከብራበታለች: ገናበታለች እንጂ አልተጐዳችበትም:: አብርሃም ወደ ካራን ሲወጣ "ለምን?" አላላችም:: እንዲሁ ለፈቃደ እግዚአብሔር ታዘዘች እንጂ:: በካራን ታራን ቀብረው: በፈጣሪ ትዕዛዝ ወደ ከነዓን ሲፈልሱም ቅድስት ሣራ አልተቃወመችም::

ለፈጣሪዋ ትዕዛዝና ለባሏ ስትል ርስቷን: ሃገሯን: ዘመዶቿን ሁሉ ትታ ሔዳለች:: ይሔውም በጐ ምናኔ ነው:: እናታችን ሳራ በከነዓን የተመቸ ነገር አልገጠማትም:: ከአንዴም ሁለቴ በረሃብና በድርቅ ምክንያት ወደ ግብጽ እና ጌራራ ተሰደዋል::

በዚያም ፈርዖን "እነካለሁ" ቢል እግዚአብሔር ተቆጥቶ: ፈርኦንንና ግብጽን በደዌ መታ:: በዚህም ክብረ ሣራን ተመለከትን:: ከስደት መልስም በኬብሮን [በተመሳቀለ መንገድ ላይ] ድንኩዋን ሠርተው የወጣ የወረደውን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ኑረዋል::
[ልብ በሉልኝ ይህን ትጋትና ደግነት ያሳየችውን ቅድስት ሣራን ልናከብራት ይገባል]

እድሜ ዘመኗን ያሳለፈችው እንግዳ በመቀበል: እግዚአብሔርን በማምለክ ነው:: ምንም እንኩዋ ማሕጸኗ ለጊዜው ቢዘጋ ተስፋ አልቆረጠችም:: ለአብርሃምም ከአጋር እንዲወልድ ፈቃድ ሰጥታለች::

ዕድሜዋ ፹፱ [89] ዓመት በሆነ ጊዜ ሰይጣን እንግዳ እንዳይመጣ ለ፫ [3] ቀናት ቢያስቀርባቸው እንደ ባሏ እርሷም ፫ [3] ቀናትን ያለ ምግብ አሣልፋለች:: በ፫ [3]ኛው ቀን ሥላሴን በቤቷ አስተናግዳለች:: ስለ ክብሯም ከ፫ [3] መሥፈሪያ ዱቄት ለውሳ ያዘጋጀችውን እንጐቻ ሥላሴ በልተውላታል:: [ምንም ሥላሴ ምግብን ባይመገቡም]

የሥላሴ በዚያች ድንኩዋን ውስጥ መስተናገድ ታላቅ ምሥጢር አለው:: ከግብዣው በሁዋላም እግዚአብሔር አለ :- "አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ . . . እንዲሁ ከርሞ እመለሳለሁ: ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች" አለው::

ያን ጊዜ ሣራ በውሳጤ ሐይመት [በድኩዋኑ ውስጥ] ሆና ሰምታ ሣቀች:: ለምን ሳቀች ቢሉ :- እጅግ ደስ ቢላት! አንድም ቢገርማት:: ይሕስ በምን ይታወቃል ቢሉ :- ልጇ "ይስሐቅ" የተባለው "ለእናቱ ሣቅን: ደስታን ያመጣ" ለማለት ነውና::

ሥላሴም :- "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ: እንዘ ትብል ዓዲየኑ እስከ ይእዜ: ወእግዚእየኑ ልሕቀ: ቦኑ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር - ሣራን ምን አሳቃት? ለእግዚአብሔርስ የሚሳነው ነገር አለን" ብለዋል::

ቅድስት ሣራ በ፺ [90] ዓመቷ ይስሐቅን ወልዳ በቀሪ ዘመኖቿ በደስታ ኑራለች:: በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፋ: አባታችን አብርሃም ከታላቅ ሐዘን ጋር ቀብሯታል:: ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ ብጽዕት ሣራን በበጐ ምሳሌ መስሏታል:: [ዕብ.፲፩፥፲፩] (11:11)

[ †  🕊 ቅዱሳን ሞይስስና ሣራ  🕊 † ]

† እነዚህ ቅዱሳን ግብጻውያን የአንድ እናት: የአንድ አባት ልጆች ሲሆኑ የነበሩትም በዘመነ ሰማዕታት ነው:: ከወላጆቻቸው ጋር በሥርዓተ ክርስትና አድገው ዕድሜአቸው ለአካለ መጠን ሲደርስ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው::

ያን ጊዜ ቅዱስ ሞይስስ እህቱን ቅድስት ሣራን ጠርቶ "እህቴ! እኔ ወደ ገዳም መሔዴ ስለሆነ አንቺ ባል አግብተሽ: ሃብት ንብረቱን ወርሰሽ ኑሪ" አላት:: ቅድስት ሣራ ግን መልሳ "እንዴት እኔን በዚህ ዓለም ወጥመድ ውስጥ ትተወኛለህ? ሁለታችንም ከአንድ ማሕጸን ነን:: ስለዚህ ላንተ የምትፈልገው ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛልና እኔም መናኝ ነኝ" አለችው::

ቅዱስ ሞይስስ የልቡናዋን መጨከን ሲያይ ነዳያንን ሰበሰበ:: ገንዘቡን: ቤቱን: ሃብቱንና ንብረቱን ሁሉ በየስልቱ ለነዳያን አካፈለ:: ሳይዘገይም እህቱን ይዞ ወደ በርሃ ተጉዋዘ:: እርሷን ከደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ከወንዶች ገዳም ውስጥ መነኮሰ::

ለ፲ [10] ዓመታት ሁለቱም ለፈጣሪያቸው በጾምና በጸሎት: ከስግደት ጋር ሲገዙ: ለአባቶችና እናቶች ደግሞ በትሕትና ሲታዘዙ ኖሩ:: በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም ቀን ተገናኝተው አያውቁም ነበር:: አንዱ ለሌላኛው ተግቶ መጸለይን ግን ቸል አላሉም::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ [የመከራ] ነውና መከራው እየገፋ ሲመጣ ቅዱስ ሞይስስ አንድ ነገር አሰበ:: በክርስቶስ ስም ደሙን ለማፍሰስም ወሰነ:: ወደ ከተማ ከመውጣቱ በፊት ግን ለቅድስት ሣራ መልዕክት ላከባት:: "እኔ ወደ ምስክርነት እየሔድኩ ስለሆነ ቸር ሁኚ" የሚል ነበር መልእክቱ::

እርሱ ይህንን ብሎ ወደ ከተማ ሲሔድ ግን መንገድ ላይ እህቱን አገኛት:: ገርሞት የፍቅር ሰላምታን ከተለዋወጡ በሁዋላ "እንዴት መጣሽ?" ቢላት "ወንድሜ! ቀድሞም ነግሬሃለሁ:: ላንተ የምትፈልገው የድኅነት መንገድ ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛል" አለችው::

ሁለቱም ተያይዘው ወደ መከራ አደባባይ ደረሱ:: በዚያም ስመ ክርስቶስን ሰብከው: ብዙ መከራንም ተቀብለው በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነዋል::

† አምላከ ቅድስት ሣራ ደግነቷን: መታዘዟን ያሳድርብን:: ከበረከቷ: ከሌሎችም ቅዱሳን በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፳፮ [ 26 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ብጽዕት ሣራ [የአብርሃም ሚስት]
፪. ቅዱሳን አባ ሞይስስና እህቱ ሣራ [ሰማዕታት]
፫. ቅዱሳን አጋቦስና ቴክላ [ሰማዕታት]

[   † ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
፫. አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬. ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭. ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

" እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና:: እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም :- ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት:: እናንተም ከሚያስደግጥ ነገር አንዳች እንኩዋ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆቿ ናችሁ::" † [፩ዼጥ.፫፥፭] (3:5)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

#ነሐሴ ፳፮ (26) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጲያውያኑ_ጻድቃን ለአባታችን #ለአቡነ_ሀብተ_ማርያምና ታላቁ ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ ላቀኑ #ለአቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ ለጽንሰታቸው ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል በዓል በሰላም አደረሰን።




#አቡነ_ሀብተ_ማርያም_ጽንሰት፦ " የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች።

ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጽሕ ጋብቻ እግዚአብሔር በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትግሥት በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን።

እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ "ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል የሚል መጣባት፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና"፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል" እንዳለ።

"ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል" የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደ ሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣሞች፣ ከጦጦችና ከዝንጆሮች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር።

በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስለአየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ።

መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። "አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ" አላት። "ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን"። "ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም" አለችው። "ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር" አለችው።

ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ "በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ" ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም "ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ" አለችው። ጌታ "በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም" እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም" አለችው።

ያም ባሕታዊ "ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል"።

ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ "የፈጣሪየ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ" አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሁኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ሜሉን ገቹን አርደው ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ ...ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው። ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።


#አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ፦ አገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ከቅዱስ ዘክርስቶስና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ክብራ ተወለዱ፡፡ የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኲስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡

አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ "የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራሂድ" አላቸው፡፡ አባታችንም "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?" በማለት መልአኩን ቢጠይቁት "ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ 6 ወራት ያህል በቅዱሳን በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበው ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡

ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐፄ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ "የማንን ታቦት እናስገባ?" ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ "ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡

አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኰሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ጠቅጥቀው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኵሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳኵሚስን፣ ጳኵሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኰሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኰሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው አገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኰሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት መነኰሳት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

[  †  ነሐሴ ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

[ 🕊 † ፲፪ [ 12 ]ቱ አበው ደቂቀ እሥራኤል † 🕊 ]

እነዚህ አበው የአብርሃምና የይስሐቅ የልጅ ልጆች የያዕቆብ ደግሞ ልጆች ናቸው:: ትውልድ ከአዳም እስከ ቅዱስ ያዕቆብ አንድ ሐረግ ይዞ መጥቶ እዚህ ላይ ሲደርስ ይበተናል:: አባታችን ያዕቆብን እግዚአብሔር ሲባርከው እሥራኤል አለው:: ትርጉሙም "ሕዝበ እግዚአብሔር: ወልድ ዘበኩር [የበኩር ልጅ]: ከሃሊ: ነጻሪ [አስተዋይ] እንደ ማለት ነው::

ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል:: ከወንድሙ ኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሶርያ በሔደ ጊዜ ከ፪ [2]ቱ ሚስቶቹ [ልያና ራሔል] ፰ [8] ልጆችን: ከ፪ [2]ቱ የሚስቶቹ ደንገ ጥሮች [ዘለፋና ባላ] ፬ [4] ልጆችን: በድምሩ ፲፪ [12] ልጆችን ወልዷል::

- ልያ የወለደቻቸው :-
፩. ሮቤል
፪. ስምዖን
፫. ሌዊ
፬. ይሁዳ
፭. ይሳኮር እና
፮. ዛብሎን ይባላሉ::

- ራሔል የወለደቻቸው :-
፯. ዮሴፍና
፰. ብንያም ይባላሉ::

- ባላ :-
፱. ዳን እና
፲. ንፍታሌምን ስትወልድ

- ዘለፋ :- ደግሞ
፲፩. ጋድና
፲፪. አሴርን ወልዳለች::

- ፲፪ [12]ቱ  ደቂቀ እሥራኤል [ያዕቆብ] ማለት እኒህ ናቸው::

ከ፲፪ [12]ቱ በቅድስና ዮሴፍ ከፍ ቢልም እግዚአብሔር ለክህነት ሌዊን: ለመንግስት ደግሞ ይሁዳን መርጧል:: ከእነሱ ዘርም ዓለምን ለማዳን ተወልዷል:: ፲ [10]ሩ አበው በተለይ በዮሴፍ ላይ ግፍ ሠርተው የነበረ ቢሆንም በኋላተጸጽተዋል:: እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታስባቸዋለች:: [ዘፍ. ከ፳፰-፴፩] (28-31)

[ 🕊 †  ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል † 🕊 ]

እሥራኤል ከግብፅ ባርነት ወጥተው ከነዓንን ከወረሱበት ዘመን ጀምረው መሳፍንትና ካህናት ያስተዳድሯቸው ነበር:: በወቅቱ ታዲያ ክህነት ከምስፍና ተስማምቶለት ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናትና ልጆቹ [አፍኒና ፊንሐስ] ያስተዳድሩ ጀመር::

በዘመኑ ደግሞ ማሕጸኗ ተዘግቶባት ዘወትር የምታለቅስ ሐና የሚሏት ደግ ሴት ነበረች:: እግዚአብሔር የእርሷን ጸሎትና የሊቀ ካህናቱን ምርቃት ሰምቷልና ቅዱስ ልጅን ሰጣት:: "ሳሙኤል" አለችው:: "ልመናየን አምላክ ሰማኝ" ማለት ነውና::

ሐና ስዕለቷን ትፈጽም ዘንድ ሳሙኤልን በ፫ [3] ዓመቱ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠችው:: በዚያም ስብሐተ እግዚአብሔርን እየሰማ: ማዕጠንቱን እያሸተተ: ከደብተራ ኦሪቱ ሳይለይ በሞገስ አደገ:: የኤሊ ልጆች [አፍኒና ፊንሐስ] በበደል ላይ በደልን አበዙ::

ወቅቱ የአሁኑን ዘመን ይመስል ነበር:: ሁሉም ሰው ክፋተኛ የሆነበት በመሆኑ እግዚአብሔር ርቆ ስለ ነበር ትንቢትና ራዕይ ብርቅ ነበር:: አምላክ ተቆጥቷልና ሳሙኤልን በሌሊት ፫ [3] ጊዜ ጠራው:: ነቢዩም ታጥቆ የፈጣሪውን ቃል ሰማ:: በዚሕም የተነሳ ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ተማረከች:: ከ፴፬ [34]ሺ በላይ ሕዝብ በኢሎፍላውያን አለቀ:: አፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ:: ኤሊም ወድቆ ሞተ::

ከዚህች ቀን በኋላ ቅዱስ ሳሙኤል በእሥራኤል ላይ ነቢይና መስፍን ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ ሁሉ እንደሚገባው እየኖረ: የእግዚአብሔርን ለእሥራኤል: የእሥራኤልን ለእግዚአብሔር ሲያደርስ ኑሯል:: ሕዝቡ ንጉሥ በፈለጉ ጊዜ ሳዖልን ቀብቶ አነገሠላቸው:: እርሱ [ሳዖል] እንደ ሕጉ አልሔደምና ፈጣሪ ናቀው::

ሳሙኤል ግን ደግ አባት ነውና ክፋተኛውን [ሳዖልን] ከጌታው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ብዙ ደከመ: አለቀሰም:: እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን:- "አትዘን! እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም ዳዊትን አግኝቸዋለሁና እርሱን በእሥራኤል ላይ አንግሠው" አለው:: ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ ቤተ ልሔም ሔዶ: ከእሴይ ልጆችም መርጦ ልበ አምላክ ዳዊትን ቀባው: አነገሠውም::

ቅዱስ ሳሙኤል በተረፈው ዘመኑ ለፈጣሪው እየተገዛ ኑሯል:: ነቢዩ ዘወትር ከእጁ የሽቱ ሙዳይና የቅብዐት እቃ [ቀንድ] አይለይም ነበረ:: እነዚህም የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸውና አባ ሕርያቆስ :-
"ሙዳየ ዕፍረት ወቀርነ ቅብዕ ዘሳሙኤል" ብሎ አመስግኗታል::

ነቢዩም በወገኖቹ መካከል በዚሕች ቀን አርፏል:: እሥራኤልም አልቅሰውለታል:: ዛሬ ቅዱሱ ነቢይ ለአገልግሎት የተጠራበት ቀን ነው::

[ 🕊 † ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት † 🕊 ]

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል: ገብርኤል: ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::

በ፫ [3]ቱ ሰማያት ካሉት ፱ [9]ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ [የሥልጣናት] መሪ [አለቃ] ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብርን ያሳራው: ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት::

ቸሩ አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ይማረን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ፲፪ "12ቱ" ደቂቀ ያዕቆብ [ እሥራኤል ]
፪. ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ [ የተጠራበት ]
፫. ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት
፬. ቅዱስ ብንያሚንና እህቱ አውዶከስያ [ ሰማዕታት ]
፭. ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ሣራ
፮. አባ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮዽያ [ የተሾሙበት ]

[  † ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪. አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
፫. ቅዱስ መቃርስ [ የመነኮሳት ሁሉ አለቃ ]
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት [ ንጉሠ ኢትዮዽያ ]
፮. ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯. ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

"እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች ናቸው:: አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው:: ባረካቸውም:: እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው::" [ዘፍ.፵፱፥፳፰] (49:28)

" በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረዥም ተራራ ወሰደኝ:: የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ: ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ . . . አሥራ ሁለት ደጆችም ነበሯት:: በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ:: የአሥራ ሁለቱም የእሥራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር::" [ራዕይ.፳፩፥፲፩] (21:11)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/05 19:16:26
Back to Top
HTML Embed Code: