Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለቅዱሳን ፯ቱ ደቂቅ እና ለአቡነ ሰላማ ካልዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ † 🕊 ቅዱሳን ፯ ቱ ደቂቅ 🕊 † ]

† እነዚህ ፯ ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: ፯ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ፪ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::

በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::

ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ ለጣዖትም ያልሰገደ ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ እጅ እግሩ ለእስር ደረቱ ለጦር አንገቱ ለሰይፍ ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::

የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ ፯ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::

ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ወጣ::

ከመውጣቱ በፊት ግን ፯ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::

ዓለምን ንቀው ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር [በጐች አሉት] ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::

አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ፯ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::

ያ የበጐች ባለቤት [ወታደር] ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::

ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ፫፻፸፪ ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::

በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን ፬፻ ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::

በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት: ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል:: ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው:: እርሱም "አዎ ናት" ብሎት አለፈ::

ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ: እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር:: በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ:: [ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው:: የነገሠውም በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው]

በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም ሊቀ ዻዻሱም [አባ ቴዎድሮስ ይባላል] ተገረሙ:: አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው ፯ቱንም ሲጸልዩ አገኟቸው:: ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር:: ፯ቱም ለ፯ ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ::

ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሳኤ ሙታን የለም" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው:: በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃየማኖት ተመልሰዋል:: ፯ቱ ቅዱሳን ግን በ፯ኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል:: ንጉሡ በ፯ የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል::

[ † 🕊 አቡነ ሰላማ ካልዕ  🕊 † ]

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ፲፻፫፻፵ እስከ ፲፻፫፻፹ ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን [፹፩ ዱን] ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ፴ ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም :-

◉  ስንክሳር
◉  ግብረ-ሕማማት
◉  ላሃ-ማርያም
◉  ፊልክስዩስ [መጽሐፈ መነኮሳት]
◉  መጽሐፈ-ግንዘት
◉  ድርሳን ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::

ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው አባ-ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ [፪ኛው] ሰላማ በ፩ ሺህ ፫፻፹ ዓ/ም ከ፵ ዓመታት ትጋት በሁዋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም :-
◉  መተርጉም [መጻሕፍትን የተረጐሙ]
◉  ብርሃነ አዜብ [የኢትዮዽያ ብርሃን]
◉  መጋቤ ሃይማኖት ተብለው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን እንዳጸናቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

[ † ነሐሴ ፳ [ 20 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [፭ኛ ቀን]
፪. ቅዱሳን ፯ቱ ደቂቅ
፫. አቡነ ሰላማ ካልዕ [መተርጉም]
፬. ቅድስት ሔዛዊ

[ †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪. ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫. ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፬. አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭. ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
፮. ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት

† "በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ:: ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን::" † [፪ቆሮ.፲፫፥፲፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † ✝️ 🌻 እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት: ንግሥተ ሳባ እና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ✝️ 🌻  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

[ † 🕊 ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት 🕊 † ]

† ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት ምግባር ከሃይማኖት ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት:: ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::

ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው::

ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው ፲፪ [12] አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት::

ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል:: እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::

ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም::

መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን አየች::

እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ [ቆጽለ ዘይት] ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::

በ፫ [3]ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::

እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው :- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ [የሃይማኖት] ምሳሌ ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ ማሕተመ ጥምቀት [ሜሮን] ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::

ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት::

እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች :- "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች:: በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት:: የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::

በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "፫ [3] ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች::

በዘመኑ ቅዱሳን ሐዋርያት [በተለይ እነ  ቅዱስ ዻውሎስ] በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ:: ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::

በ፫ [3]ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር መርዓተ ክርስቶስ [ሰማያዊ ሙሽራ] መሆን ነው" አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::

በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር:: ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::

ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ:: የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::

በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት::

ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ፴ ሺህ [30,000] በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::

ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም: የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::

✝️ 🌻  ንግሥተ ሳባ  🌻  †  ✝️

† ይሕቺ ኢትዮዽያዊት ከ፫ [3] ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች::

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን [በፈጣሪ] አንደበትም ተመስግናለች:: [ማቴ.፲፪፥፵፪] (12:42) በስምም " ሳባ: አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::

[ † 🕊 ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት 🕊 † ]

† ይሕቺ ቅድስት የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱ የመስቀሉ ወዳጅ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት:: ይህቺም ቅድስት የተወለደቺው በዚሁ ዕለት ነው::

† የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እህት እናቶቻችንን ከክፋትም ከጥፋትም ይሠውርልን:: ለሃገርም ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን:: በረከታቸውም ይደርብን::

[ † ነሐሴ ፳፩ [ 21 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [6ኛ ቀን]
፪. ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት [ሰማዕት]
፫. ቡርክት ንግሥተ ሳባ [ልደቷ]
፬. ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት [ልደቷ]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪. አበው ጎርጎርዮሳት
፫. አቡነ ምዕመነ ድንግል
፬. አቡነ አምደ ሥላሴ
፭. አባ አሮን ሶርያዊ
፮. አባ መርትያኖስ ጻድቅ

† " ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች:: የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና:: እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ::" † [ማቴ.፲፪፥፵፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚክያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ † 🕊  ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ  🕊 † ]

† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን [አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር] : መጻዕያትን [ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን] የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: [ሐዋ.፲፩፥፳፯] (11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: [ቅዳሴ ማርያም]

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: [ዮሐ.፬፥፴፮] (4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ::" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: [ማቴ.፲፫፥፲፮ (13:16), ፩ጴጥ.፩፥፲] (1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤ አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት:
¤ አራቱ ዐበይት ነቢያት:
¤ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

† አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት :-

- ቅዱስ አዳም አባታችን
- ሴት
- ሔኖስ
- ቃይናን
- መላልኤል
- ያሬድ
- ኄኖክ
- ማቱሳላ
- ላሜሕ
- ኖኅ
- አብርሃም
- ይስሐቅ
- ያዕቆብ
- ሙሴና
- ሳሙኤል ናቸው::

† አራቱ ዐበይት ነቢያት ፦

- ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
- ቅዱስ ኤርምያስ
- ቅዱስ ሕዝቅኤልና
- ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

† አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ፦

- ቅዱስ ሆሴዕ
- አሞጽ
- ሚክያስ
- ዮናስ
- ናሆም
- አብድዩ
- ሶፎንያስ
- ሐጌ
- ኢዩኤል
- ዕንባቆም
- ዘካርያስና
- ሚልክያስ ናቸው::

† ካልአን ነቢያት ደግሞ :-

- እነ ኢያሱ
- ሶምሶን
- ዮፍታሔ
- ጌዴዎን
- ዳዊት
- ሰሎሞን
- ኤልያስና
- ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
- የይሁዳ [ኢየሩሳሌም]:
- የሰማርያ [እሥራኤል]ና
- የባቢሎን [በምርኮ ጊዜ] ተብለው ይጠራሉ::

† በዘመን አከፋፈል ደግሞ :-

- ከአዳም እስከ ዮሴፍ [የዘመነ አበው ነቢያት]:
- ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል [የዘመነ መሳፍንት ነቢያት]
- ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት [የዘመነ ነገሥት ነቢያት]
- ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ [የዘመነ ካህናት ነቢያት] ይባላሉ::

† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ፰ መቶ [800] ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው::
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

ሚክያስ አባቱ ሞራት [ሞሬት] ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::

ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በሦስቱ ነገሥታት [በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ] ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::

አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ: ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::"

"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ [መስፍን] ካንቺ ዘንድ ይወጣልና::" አለ::

ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት ኢየሱስክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::

ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና: በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::

† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::

[  † ነሐሴ ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ

[   † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫. ቅዱስ ደቅስዮስ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፬. አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፭. አባ ጳውሊ የዋህ

† " ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" † [ሚክ. ፮፥፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  †  እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ † 🕊  ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት  🕊 † ]

† ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ፫፻፭ [305] (312) ዓ/ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል:: ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው [ያደለው] ይቀበለዋል::

ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው:: ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::

በ፬፻፶፩ [451] ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች::

በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" [ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ] ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" [የውሾች ስብሰባ] : "ጉባኤ አብዳን" [የሰነፎች ጉባኤ] ተብሏል::

የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም::" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው: ጥርሱንም አርግፈው: ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት::
በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ፬፻፶፬ [454] ዓ/ም ዐረፈ::

እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ [ክፉ ሴት ናት] ድንገት ሞቱ:: ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም:: በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር:: መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን::" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ::

የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው:: ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር:: ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ: ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው:: መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር::

ለምሳሌ አውጣኪን [የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው::] አወገዘው:: እነሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም:: ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና:: የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም:: ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር::

አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ:: [መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ:: እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም::] ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ:: ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው::

የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው: የሾምከውን ገደሉ:: ሌላ ጳጳስም ሾሙ::" ብለው መልዕክት ላኩለት:: በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ:: ይህን አዋጅ ተከትሎ ሰላሳ ሺ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ::

ገዳዮቹ ወንድ: ሴት: ሕፃን: ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ:: ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል::
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ::

ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት:: ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት:: ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል:: ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው::

† አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

[  † ነሐሴ ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ሰላሳ ሺ የእስክንድርያ [ግብጽ] ሰማዕታት
፪. ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል

† " በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን:: " † [፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
2024/09/30 19:29:35
Back to Top
HTML Embed Code: