Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from Sintu.D
"ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።" ማቴ 10፡39-40

እንኳን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል አደረሳችሁ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖   ሐምሌ ፭    ❖

[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ዼጥሮስ ወዻውሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ 🕊 ]

ፍጡር ቢከብር ከእመ ብርሃን ቀጥሎ የእነዚህን ቅዱሳን ያህል የሚከብር አይኖርም:: ለቤተ ክርስቲያን ያልሆኑላት ምንም ነገር የለምና እርሷም "ብርሃኖቼ: ዐይኖቼ: ዕንቁዎቼ" ብላ ትጠራቸዋለች::


🕊  † ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት †  🕊

የዮና ልጅ ስምዖን ዼጥሮስ [ኬፋ] የተባለው በጌታችን ንጹሕ አንደበት ነው:: ይሔውም ዓለት [መሰረት] እንደ ማለት ነው::

¤ በቤተ ሳይዳ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሳ በማጥመድ አድጐ

¤ ሚስት አግብቶ ዕድሜው ፶፮ [56] ሲደርስ ነበር ጌታችን የተቀበለው:: በዕድሜውም ሆነ በቅንዐቱ: በአስተዋይነቱም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ተብሏል:: ለሐዋርያትም አለቃቸው ሆኗል:: [ማቴ.፲፮፥፲፯] (16:17) , [ዮሐ.፳፩፥፲፭] (21:15)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ለሰራው ስሕተት ንስሃ ገብቶ ምሳሌም ሆኗል:: ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ እረኝነቱ ሐዋርያትን ጠብቆ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲያበቃ ከበዓለ ሃምሳ በሁዋላም ለሁሉም ሃገረ ስብከት አካፍሏል:: ምንም የርሱ ክፍል ሮሜ ብትሆንም አርድእትን ስለ ማጽናት በሁሉም አሕጉራት ዙሯል::

በስተእርጅናው ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል:: አሕዛብ ግብራቸው እንደ እንስሳ ነውና በአባታችን ላይ ቀልደዋል:: እርሱ ግን ሁሉንም ታግሷል:: የቅዱሱን ታሪክ ለመናገር ከመብዛቱ የተነሳ ይከብዳልና ልቡና ያለው ሰው ሊቃውንትን ሊጠይቅ እንደሚገባ እመክራለሁ::

ቅዱስ ዼጥሮስ መልካሙን ገድል ተጋድሎ በ፷፮ [66] ዓ/ም የኔሮን ቄሳር ወታደሮች ሲሰቅሉት ለመናቸው:: "እባካችሁን? እኔ እንደ ጌታየ ሆኜ መሰቀል አይገባኝም" አላቸው:: እነሱም ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል:: በበጐ እረኝነቱም የማታልፈውን ርስት ከነመክፈቻዋ ተቀብሏል:: በሰማዕትነት ሲያርፍም ዕድሜው ወደ ፹፰ [88] አካባብ ደርሶ ነበር::

†  የቅዱስ ዼጥሮስ መጠሪያዎች :-

፩. ሊቀ ሐዋርያት
፪. ሊቀ ኖሎት [የእረኞች / ሐዋርያት አለቃ]
፫. መሠረተ ቤተ ክርስቲያን
፬. ኰኩሐ ሃይማኖት [የሃይማኖት ዐለት]
፭. አርሳይሮስ [የዓለም ሁሉ ፓትርያርክ]

🕊 † ቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ † 🕊

የቤተ ክርስቲያን መብራቷ ቅዱስ ዻውሎስን እንደ ምን ባለ አማርኛ እንገልጠዋለን?

¤ ስለ እርሱ መናገርና መጻፍ የሚችልስ እንደ ምን ያለ ሰው ነው?
¤ የዓለምን ነገር ሲጽፍ በኖረ እጄስ እንደ ምን እጽፈዋለሁ?
¤ ይልቁኑስ የርሱን ፲፬ [14] ቱን መልዕክታትና ግብረ ሐዋርያትን መመልከቱ ሳይሻል አይቀርም::

ቅዱስ ዻውሎስ ከነገደ ብንያም ሳውል የሚባል የጠርሴስ ሰው ሲሆን ምሑረ ኦሪት: ቀናተኛና ፈሪሳዊ ነበር:: ጌታ በደማስቆ ጐዳና ጠርቶ በ፫ [3] ቀናት ልዩነት ምርጥ ዕቃ አደረገው:: ይህ የሆነው በ፵፪ [42] ዓ/ም: ጌታ ባረገ በ፰ [8] ኛው ዓመት ነበር:: ከዚያማ ብርሃን ሆኖ አበራ:: ጨው ሆኖ አጣፈጠ::

ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም: ከእንግሊዝ እስከ እልዋሪቆን [የዓለም መጨረሻ] ወንጌልን ሰበከ:: ስለ ወንጌል ተደበደበ: ታሠረ: በእሳት ተቃጠለ:: በድንጋይ ተወገረ: በጦር ተወጋ:: ባፍም በመጣፍም ብሎ አገለገለ:: በየቦታውም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ሠራ:: ለ፳፭ [25] ዓመታት ቀንና ሌሊት ያለ መታከት ወንጌልን ሰበከ::

እርሱን የመሰሉ: እርሱንም ያከሉ ብዙ አርድእትን አፍርቶ: በ፷፯ [67] ዓ/ም በኔሮን ቄሳር ትእዛዝ አንገቱ ተቆርጧል:: ከ፲፬ [14] ቱ መልዕክታቱ ባሻገር ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን ሲጽፍ አግዞታል:: ልክ ቅዱስ ዼጥሮስ ማርቆስን እንዳገዘው ማለት ነው::

🕊 † የቅዱስ ዻውሎስ መጠሪያዎች ፦

፩. ሳውል [ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ]
፪. ልሳነ ዕፍረት [አንደበቱ እንደ ሽቱ የሚጣፍጥ]
፫. ልሳነ ክርስቶስ [የክርስቶስ አንደበቱ]
፬. ብርሃነ ዓለም
፭. ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን [የቤተ ክርስቲያን መቅረዝ]
፮. የአሕዛብ መምሕር
፯. መራሒ [ወደ መንግስተ ሰማያት የሚመራ]
፰. አእኩዋቲ [በምስጋና የተሞላ]
፱. ንዋይ ኅሩይ [ምርጥ ዕቃ]
፲. መዶሻ [ለአጋንንትና መናፍቃን]
፲፩. መርስ [ወደብ]
፲፪. ዛኅን [ጸጥታ]
፲፫. ነቅዐ ሕይወት [የሕይወት ትምሕርትን ከአንደበቱ
ያፈለቀ]
፲፬. ዐዘቅተ ጥበብ [የጥበብ ምንጭ / ባሕር]
፲፭. ፈዋሴ ዱያን [ድውያንን የፈወሰ] . . .

ጌታችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ብርሃን ያብራልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[ †  ሐምሌ ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫. ቅዱሳን ፸፪ [72] ቱ አርድእት [ዛሬ ሁሉም ይታሠባሉ]
፬. ቅዱስ ሳቁኤል ሊቀ መላእክት
፭. ቅድስት መስቀል ክብራ [የቅዱስ ላሊበላ ሚስት]
፮. ቅዱሳን ዘደብረ ዓሣ
፯. ቅዱሳት አንስት [ዴውርስ: ቃርያ: አቅባማ: አቅረባንያና አክስቲያና-የቅዱስ ዼጥሮስ ተከታዮች]

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፪. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፫. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፬. ቅድስት አውጋንያ [ሰማዕትና ጻድቅ]

"ጌታ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው:: "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይሕንን አልገለጠልህምና ብጹዕ ነህ:: እኔም እልሃለሁ:: አንተ ዼጥሮስ ነህ:: በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ:: የገሃነም ደጆችም አይችሏትም:: የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ:: በምድር የምታሥረው ሁሉ በሰማያት የታሠረ ይሆናል:: በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል::"  [ማቴ.፲፮፥፲፯] (16:17)

" በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና:: የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል:: መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይሕንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል:: " [፪ጢሞ.፬፥፮] (4:6)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ † እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

🕊  †  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!  †  🕊


🕊  † ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ †  🕊

† ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር [በሥራ የሚገኝ] ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ፷ [60] ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

🕊  †   ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ  †   🕊

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፭መቶ [500] ዓመት አካባቢ የነበረ
¤ እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤ በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤ መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤ በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን::

[  † ሐምሌ ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ [ከሰባ ሁለቱ አርድእት]
፪. ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
፫. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬. ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
፭. ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

[  †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል

" እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ:: " † [፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"

             #ሐምሌ_፮ (6) ቀን።

እንኳን እንደ እርሱ ያሉ #ኤልያስና_ኄኖክ ወደ አሉበት ብሔረ ሕያዋን ለተሰወረው #ለነቢዩ_ለቅዱስ_ዕዝራ_ሱቱኤል_ለዕርገቱ_በዓል #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት_ለአንዱ_ጳውሎስ ለተባለው #ለቅዱስ_ጴጥሮስ_ደቀ_መዝሙር #ለቅዱስ_መርቄሎስ_ለዕረፍቱ_መታሰቢያ በዓልና አሰቀድማ ኃጢያተኛ ለነበረች በንስሐ ከተመለሰች በኋላ ብዙ ለተጋደለች ለኢየሩሳሌም ሰዎች ለሆነች #ለቅድስት_ንስተሮኒን_ለዕረፍቷ_መታሰቢያ_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚተረሰቡ፦ #ከሐዋርያው_ከቅዱስ_በርተሎሜዎስ#ከአንድ_ሽህ ሰማዕታትና ከማርቆስ ዘጠነኝ ከሚሆን #ከሊቀ_ጳጳሳት_ከአባ_ላድያኑ_ከመታሰቢያቸው፣ በሰማዕትነት ከዐረፈች #ከቅዱስ_አብሮኮሮንዮስ_እናት ከገድለኛዋ #ከቅድስት_ቴዎዳስያ፣ ከርሷ ጋርም ሰማዕት ከሆኑ #ከሁለት_መኳንንቶችና #ከዐሥራ_ሁለት_ሴቶች እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።


                            
ነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ሱቱኤል፦ ይህም ነቢይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጽፍ ነበር እርሱም ከሌዊ ወገን ነበረ። ከእግዚአብሔርም ጋራ ግሩም የሆነ ነገርን መናገር ጀመረ እንዲህም አለ "ምድርን በፈጠርካት ጊዜ አዳምን ታስገኝ ዘንድ አዘዝካት አስገኘችውም"።

ሁለተኛው የጥፋት ውኃ በጊዜው እንደ መጣና ሁሉን እንዳጠፋ ተናገረ ኖኅ አብርሃምና ዳዊት እንዴት እንደ ተመረጡ ደግሞ ተናገረ። ዳግመኛም ነፍስ ከሥጋዋ እንደምትወጣና ሰባት ቀኖች እንደምትዞር ከዚያም በኋላ እንደ ሥራዋ ወደተዘጋጀላት ቦታዋ እንደ ምትገባ ተናገረ። ከዚያም ስለ ፍርድ ቀን ተናገረ። ከእግዚአብሔር ከጌትነቱ ብርሃን በቀር ፀሐይና ጨረቃ መብራትና ብርሃንም እንደሌሉ ተናገረ።

ዳግመኛም በልቧ እጅግ በምትጨነቅ በምታዝንና በምትተክዝ ሴት አምሳል ጽዮንን አያት ልብሶቿም የተቀደዱ ነበሩ ልጇም ወደ ጫጒላው ቤት በገባበት ቀን እንደሞተ ነገረችው። ከዚህም በኋላ እርሷን ከማየቱ የተነሣ ፈርቶ በድንጋፄ እስከ ወደቀ ድረስ ፊቷ በድንገት እንደ መብረቅ በራ።

ደግሞም ዐሥራ ሁለት ክፎችና ሦስት ራሶች ያሉት ንስር ከባሕር ሲወጣ ከክንፎቹም ውስጥ ራሶች ሲወጡ አየ እኒህም በየዘመናቸው ገዝተው የጠፉ ነገሥታት ናቸው። ደግሞም ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስ መወለድ ተናገረ እንዲህም አለ "አንበሳ እያገሣ ከበረሀ ወጣ በሰው አንደበትም ሲናገር ንስሩንም ሲገሥጸው ሰማሁት" አለ።

ዳግመኛም ስለ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "በሌሊት ታላቅ ነፋስ ከባሕር ሲወጣ አየሁ ከማዕበሉ የነተሣ ባሕሩ ይታወክ ነበር ነፋሱም እንደ ሰው አምሳል ሁኖ ከባሕር ሲወጣ አየሁ"። ደግምሞ ከብዙ ኃይልና ክብር ጋር በሰማይ ደመና ማረጉንም በአብ ቀኝ መቀመጡንም አይቶ ተናገረ። ዳግመኛም በፈሳሹ ማዶ ያኖራቸው ዘጠኙ ነገድ እንደሚሰበሰቡ ተናገረ።

ከዚህም በኋላ የነቢያት መጻሕፍትና የአባቶችን ትውልድ የያዙ መጻሕፍት ተደምስሰው መጥፋታቸውን በአሰበ ጊዜ ወደ በረሀ ገብቶ በጾምና በጸሎት ምሕላ ያዘ። ከእርሱም ጋር አምስት ጠቢባን ጸሐፊዎችን ወሰደ።

ከዕንጨቱም አንጻር ቃል ጠርቶት "ዕዝራ አፍህን ክፈት" ብሎ ኅብሩ እሳት የሚመስል ውኃን የተመላ ጽዋን ሰጠው። ያንንም ጽዋ ጠጣ ያን ጊዜም ልቡናው ጥበብን አገሣ። ተገልጾለትም መጻሕፍትን ሁሉ ሰበሰበ ለእነዚያም ሰዎች ልዑል አምላክ ዕውቀትን ሰጣቸው። መጻሕፍትንም ሁሉ በየተራቸው ጻፈ።

በዚያም አርባ ቀን ኖሩ እነዚያ ግን ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታም ይመገባሉ እርሱ ግን ቀን ይጽፋል ማታም ዝም አይልም በእነዚያ አርባ ቀኖችም ሁሉ መጻሕፍት ተጻፈ። ከዚህም በኋላ ልዑል እንዲህ ሲል ተናገረው "የዕውቀት ምሥጢር ጥበብም ምሥጢር እንደ ፈሳሽ ውኃም ያለ ዕውቀት ላላቸው ታስተምራቸው ዘንድ ይህን ተመልከት" እንዳለውም አደረገ።

በአራተኛውም ዘመን ከሚቈጠሩ ከብዙ ሱባዔ ባምስተኛው ሱባዔ ይህ ዓለም ከተፈጠረ ከአምስት ሺ ዘመን በኋላ ጨረቃ ሠርቅ አድርጋ ጨለማዋን ባጣች ባሥረኛው ዎን በሦስተኛው ወር በዘጠና አንድ ሐምሌ 6 ቀን እንደእርሱ ያሉ ደጋግ ሰዎች ወዳሉበት ዕዝራን ወሰዱት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ በቅዱስ ዕዝራ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                           
#ሐዋርያው_ጳውሎስ_የተባለ_ቅዱስ_መርቄሎስ፦ ይህም ከባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው። እርሱም ሐዋርያትን አገልግሎአቸዋል ወንጌልንም ለመስበክ ከእነርሱ ጋር ሔደ የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን መልእክቶች አደረሰ በመከራውም ጊዜ አገለገለው ከእርሱም ጋር መከራ ተቀበለ ከእርሱም አልተለየም። ወደ ሮሜ አገርም ከርሱ ጋር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን አስተማረ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን ከአረማውያን ብዙዎቹን መለሳቸው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ይህ ረድእ መርቄሎስ መጥቶ ከመስቀል ላይ አወረደው በከበሩ ልብሶችም ከሽቱ ጋር ገነዘው። በሣጥንም አድርጎ ከምእመናን በአንዱ ቤት አኖረው።

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙርም እንደሆነ በኔሮን ዘንድ ወነጀሉት ንጉሡም ወደ እርሱ አቅርቦ ጠየቀው እርሱም ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ እንደሆነ አመኑ ደግሞም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ ታመነ። ስለዚህም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ገረፈውም ዘቅዝቀው ሰቅለውም ከበታቹ ጢስን አጤሱበት።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ "እንዴት ሁነህ መሞት ትሻለህ በምን አይነት ሞት ልግደልህ ንገረኝ" አለው። ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰ "እኔ ሕይወት በሆነ በክርስቶስ ስም መሞት እሻለሁ አንተ ግን በፈለግኸው ዓይነት ግደለኝ ፈጥነህም ወደ ፈለግኸው አድርሰኝ"።

ያን ጊዜም ንጉሡ ኔሮን እንዲገርፉትና እንደ መምህሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት አዘዘ ሐምሌ 6 ቀን እንዲሁም አደረጉበት። የሰማዕታትንና የሐዋርያትን አክሊል ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                             
#ቅድስት_ንስትሮኒን፦ እርሷም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ውስጥ ነበረች። አስቀድማ ኃጢአተኛ ነበረች ከዚያም በኋላ ንስሓ ገብታ ወደ እግዚአብሔር በተቃጠለ ልብ ተመለሰች የሥጋን ፍላጎቶች ሁሉ ናቀች እመምኔት እስከሆነች ድረስ በበጎ ሥራ ሁሉ ትሩፋትንና ተጋድሎን አበዛች።

እኅቶችም ከገድል ብዛትና ምግብን ከመተው የተነሣ ሥጋዋ እንዳለቀ አይተው "ሥጋሽን እንድተረጂ ጥቂት እህል በወጥ ብዪ" አሏት። አብዝተውም ግድ ባሏት ጊዜ "ልጆቼ ሆይ ወደ ቀድሞ ልማዴ እንዳልመለስ ጥቂት ወጥ ስለ መብላት አትድከሙ ስለዚህ ወጥ አልበላም አለቻቸው"። ከዚህ በኋላ ሐምሌ 6 ቀን በሰላም ዐረፈች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ንስትሮኒን በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
                              + + +
#የቅድስ_አብሮኮሮንዮስ_እናት_ገድለኛዋ #ቴዎዳስያ ከእርሷ ጋርም በሰማዕትነት ያዐረፉ #ሁለቱ_መኳንቶችና_ዐሥራ_ሁለት_ሴቶች፦ ይህም እንዲህ ነው ይቺ ቅድስት ልጇ አብሮኮሮንዮስን "ክርስቲያን ነው" ብለው እንደወነጀሉትና ለሞት እስቲደርስ ጽኑዕ ሥቃይን እንዳሠቃዩት ሰማች። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚያች ሌሊት ተገለጠለት ከሥቃዩም አዳነው ያለ ምንም ጉዳት ጤናማ ሆነ።

እሊህ ሁለት መኳንንትና ዐሥራ ሁለት ሴቶች ከእናቱ ጋር በአዩት ጊዜ እጅግ አደነቁ እንዲህ ብለውም ጮኹ "እኛ በአብሮኮሮንዮስ አምላክ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን" መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማትም የክብር አክሊልን ተቀበሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእኒህ ሰማዕታት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 6 ሰንክሳር።

                            
"ሰላም ለመርቄሎስ ጳውሎስሃ ዘተሰመየ። እንተ ገነዞ ለጴጥሮስ ግንዘተ ሠናየ። ሶበ መኰንን ይቤሎ እመ ትፈርህ ሥቃየ። ንግረኒ ዘትፈቅድ መዊተ አየ። ይቤሎ በዘተፈቅድ ትቀትለኒ ኪያየ"። ሊቀ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሐምሌ 6።

                             
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ አድኀንካ ለነፍሰየ እሞት። ወለአዕይንትየኒ እምአንብዕ። ወለእገርየኒ እምዳኅፅ"። መዝ 55፥13። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 15፥33-45፣ 1ኛ 2፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 16፥14-18። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 24፥15-36። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል የነቢዩ የቅዱስ ዕዝራ የስዋሬ በዓልና የሐዋርያው የቅዱስ መርቄሎስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
2024/09/29 11:24:39
Back to Top
HTML Embed Code: