Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ሰኔ ፲፩ (11) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያውያኑ_ጻድቃን ነገረ ማርያምን ወደ ግእዝ ቋንቋና አራቱ ወንጌልን ወደ ተለያየ ቋንቋ ለተረጎሙት #ለአቡነ_መዝሙረ_ድንግል ለዕረፍታቸው በዐልና #በግብጽ_ቤተ_ክርስቲያ_ጨምር_ቅድስና ለተሰጣቸው #ለአብረ_ገብረ_ኢየሱስ_ለዕረፍታቸው በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                       ✝️ ✝️ ✝️
#አቡነ_መዝሙረ_ድንግል፦ የተባሉት ጻድቅ አገራቸው ጎጃም ነው፤ ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ባለ ውለታ ናቸው። ጻድቁ በአምስት ሊቃውንት እየተመሩ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ አራቱን ወንጌላት ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም በግእዝ፣ በአረማይክ፣ በዕብራይስጥና በዐረብኛ ጽፈው በአራት ዓምት ያዘጋጁ ታላቅ አባት ናቸው። ዛሬም በሞጊና ገዳም ይገኛል።

ከዚህም ሌላ ነገረ ማርያምንም በግእዝና በዕብራይስጥ አዘጋጅተው ጽፈውታል። ሌሎችንም በርካታ መጻሕፍት ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች እየተረጎሙ ጽፈው ያስቀመጡ ነበር። በጣም ጸሎተኛ፣ ደራሲ፣ ባሕታዊ፣ ጻድቅና መናኝ የሆኑት አቡነ መዝሙረ ድንግል ዐርፈው የተቀበሩት ጣና ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ነው። ከአቡነ መዝሙረ ድንግል እግዚአብሔር አምላክዐ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

                        ✝️ ✝️ ✝️
#አቡነ_ገብረ_ኢየሱስ፦ የተባሉት ኢትዮጵያዊ ጻድቅ በአገራችን ብዙ ተአምራትን በማድረግ ወንጌል ሲሰብኩ ከኖሩ በኋላ የግብጽ ገዳማትን ለመሳለም ወደ ግብጽ ወርደው አባ መቃርስ ገዳም ገቡ። ከዚያም ወጥተው በአባ ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ገብተው በዚያ ብዙ ጊዜ ተቀመጡ። አቡነ ገብረ ኢየሱስ ታላቅ የሆነ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባት ስለሆኑ በዚህም ግብጻውያን ይቀኑባቸው ነበር።

ስልሳ ስድስተኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ገብረ ክርስቶስ ባረፉ ጊዜ ኤጲስቆጶሳቱ ተሰብስበው ወደ አባ መቃርስ ገዳም ወደ አስቄጥስ መጥተው ለከበረች ሹመት የሚገባውን እየመረመሩ ሁለት ወር ተቀመጡ። በዚህም ጊዜ በአባ ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ለሚኖሩት ለጻድቁ አቡነ ገብረ ኢየሱስ የታዘዘ መልአክ ተገልጦላቸው "ለኤጲስ ቆጶሳቱ ለዚህች ለከበረች ሹመት የሚገባው ስሙ ገአርጊ የሚባል በመካከላችሁ አለና እርሱን ሹሙት አትዘኑ" በላቸው ብሎ ነገራቸው። አቡነ ገብረ ኢየሱስም "ከመካከላችሁ ስሙ ገአርጊ የሚባል ጻድቅ አለና እርሱን ሹሙት" ብለው መልአኩ የነገራቸውን መልእክት ነግረዋቸው አባ ገአርጊን ስልሳ ሰባተኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾመዋቸዋል።

አባ ገአርጊም ስማቸው አባ ቄርሎስ ተብሎ ከተሾሙ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ አገልግለዋል። በወቅቱ የነበረው የግብጻውያኑ ንጉሥ በጣም ብዙ ሚስቶች የነበሩት ቢሆንም አቡነ ገብረ ኢየሱስ ሄደው በድፍረት አስተምረውትና ገሥጸውት በአንድ ሚስት ብቻ እንዲጸና አድርገውታል። የጻድቁ አባታችን ገዳላቸው በጣና ይገኛል። ሰኔ11 ቀን ዐርፈው የተቀበሩት ግን በዛው በግብጽ በቊስቋም ገዳም ነው። ግብጻውያን የቅድስና ማዕረግ ሰጥተዋቸው ታቦት ቀርጸውላቸው በዓላቸውን በሚገባ ያከብሩላቸዋል። ከአቡነ ገብረ ኢየሱስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳት በዓላት።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

              #ሰኔ ፲፩ (11) ቀን።

እንኳን በጦርነት ድል አድራጊው ከቤተ መንግሥት ወገን ለሆነ #በንጽሕናው_የመላእክት_አርያ_ላለው #ለከበረ_ሰማዕት_ለቅዱስ_ገላውዴዎስ ለተጋድሎው ፍጻሜ #ለዕረፍቱ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #በመድኃኒታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም በእስክንድርያ ከተማ ከሠራችበት #ከአርባ_ሰማዕታት #ከቅዳሴ_ቤተ_ክርስቲያንና #ከእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳሳት
#ከቅዱስ_ክርዳኑ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                       ✝️ ✝️ ✝️
#ሰማዕቱ_ቅዱስ_ገላውዴዎስ፦ ይህ ቅዱስ ምድራዊ መንግሥትንና የዚህን ዓለም ክብር የናቀ ነበረ መልካም ገድልንም ተጋደለ። የማይጠፋ ሰማያዊ መንግሥትንና የማያልቅ ክብርንም ወረሰ።

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብጥልዎስ ነው እርሱም ለሮሜ ንጉሥ ለኑማርያኖስ ወንድሙ ነው መልኩም እንደ እስራኤል ያዕቆብ ልጅ እንደ ዮሴፍ ውብ ነበር። እርሱም በጦርነት ላይ የበረታ ነበር። የአንጾኪያ ተወላጆችም ይመኩበት ነበር። ስለ ደም ግባቱና ጽናቱ በሁሉ ዘንድ የተወደደ ነበር። እርሱንም ከመውደዳቸው ብዛት የተነሣ ጠላቶችን ድል እንዳረጋቸው እነርሱም ድል ሁነው በውርደት በብዙ ድንጋጤ ከፊቱ እንደሸሹ አድርገው ሥዕሉን ሥለው በከተማው መግብያ በር ላይ ያኖሩት ነበር።

ቅዱስ ገላውዴዎስ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዘወትር ያነብ ነበር። የሮሜ ንጉሥም ዜናውን ሰምቶ ሊያየው ወደደ ልጁ ገላውዴዎስንም ይልክለት ዘንድ ወደ አባቱ ላከ እርሱም ላከለት። በደረሰም ጊዜ በደስታ ሊቀበለው ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋራ ወጣ በአየውም ጊዜ ደስ ተሰኘበት የሮሜ ከተማ ሰዎች ሁሉም ደስ አላቸው። ከእነዚያ ወራቶችም በኋላ ከቊዝ አገር ሰዎችና ከአርማንያ ታላቅ ጸብ ተነሣ ይህም ቅዱስ ገላውዴዎስ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ታምኖ ወደ እነርሱ ወጣ ድልም አደረጋቸው ንጉሣቸውንም ያዘው ጣዖታቶቻቸውንም ሰበራቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ ዲዮስቆሮስም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክዶ አምልኮ ጣዖትን በአጸና ጊዜ እጅግ አዘነ ፊቅጦር የሚባል የኅርማኖስ ልጅ ወዳጅ ነበረው ሁልጊዜም የመጻሕፍትን ቃል ይሰሙ ነበር ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት ያነቡ ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ ተስማሙ። በዚያ ጊዜም ሰይጣን በሽማግሌ አምሳል ታያቸው ያዘነላቸውም መስሎ እንዲህ አላቸው "ልጆቼ ሆይ መልካምች ጐልማሶች ናችሁ የነገሥታት ልጆችም ናችሁ። ስለ እናንተ እፈራለሁ አዝንላችኋለሁም እኔም ከንጉሡ ጋር ትስማሙ ዘንድ ለአማልክትም ታጥኑ ዘንድ እመክራችኋለሁ ሲአዝዛችሁም ትእዛዙን አትተላለፉ እናንተም ክርስቶስን በቤታችሁ አምልኩት ይህ ንጉሥ ኃይለኛ ርኅራኄም የሌለው ጫካኝ ነውና" አላቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር የሚነጋገራቸው ሰይጣን እንደሆነ አስገነዘባቸው "ክፋትን ሁሉ የተመላህ የሐሰት አባት ሆይ ከእኛ ራቅ አንተ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ሕግ ትቃረናለህና" አሉት። ያን ጊዜም መልኩን ለውጦ እንደ ጥቁር ባሪያ ሆነ እንዲህም አላቸው "እነሆ ከንጉሥ አጣልቼ ደማችሁን እንዲአፈስስ አደርገዋለሁ" ሰይጣኑም ይህንን ብሎ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ሔዶ "ፊቅጦርና ገላውዴዎስን ካልገደልካቸው በአንተ ላይ ይነሣሉ አንተንም ገድለው መንግሥትህን ይወስዳሉ እነርሱም የመንግሥት ልጆች ናቸውና" አለው።

ስለዚህም ንጉሡ ወደ ቅዱስ ገላውዴዎስ ልኮ ወደርሱ አስመጣው ለጣዖታቱም እንዲሠዋ ለመነው የአባቱንም ሹመት ይሾመው ዘንድ ቃል ገባለት ሰምቶም አልታዘዘለትም። ንጉሡም ክፉ ቃልን ሊናገረው አልደፈረም ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን በድፍረት ይናገረው ነበር ያለ መፍራትም ንጉሡንና የረከሱ አማልክቶቹን ሰደበ። ኅርማኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን ወደ ግብጽ እንዲልከውና በዚያ እንዲገድሉት ንጉሡን መከረው እርሱ እንደ ልጄ እንደ ፊቅጦር ዐመፀኛ ነውና።

ንጉሡም ወደ እንዴናው ገዥ እንዲህ ብሎ ጻፈ "ገላውዴዎስ ትእዛዛችንን አልተቀበለም ቃላችንንም አልሰማም አንተም ወደ ትዕዛዛችን ይመለስ እንደሆነ በብዙ ድካም ሸንግለው ይህ ካልሆነ ራሱን በሰይፍ ቁረጥ"። ቅዱስ ገላውዴዎስ ወደ እስክንድርያ ይወስዱት ዘንድ ንጉሡ እንደ አዘዘ በአወቀ ጊዜ የእኅቱ ባል የሆነ ሲድራማኮስን ጠርቶ ክብር ይግባውና ጌታችንን በማመን እንዲጸና ወገኖቹንም እንዲያጸናቸው አደራ አለውና በሰላምታ ተሰናበተው።

ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስም በደረሰ ጊዜ አርያኖስ አይቶ ደነገጠ ተነሥቶም እጁን ሳመው እንዲህም ብሎ ለመነው "ጌታዬ ገላውዴዎስ ሆይ ይህን ሥራ አትሥራ የንጉሥንም ትዕዛዝ አትተላለፍ። ቅዱስ ገላውዴዎስም እንዲህ ሲል መለሰለት "ንጉሥ ያዘዘህን ልትፈጽም እንጂ በነገርህ ልታስተኝ አልተላክሁም" አለው። መኰንኑም እስከሚቆጣ ድረስ እንዲህ እርስበርሳቸው ይነጋገሩ ነበር በመኰንኑም እጅ ጦር ነበር ቅዱስ ገላውዴዎስ ወጋው ነፍሱንም ክብር ይግባውና በጌታችን እጅ ሰኔ 11 ቀን ሰጠ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። ምዕመናንም መጥተው የቅዱስ ገላውዴዎስን ሥጋ ወሰዱ በመልካም አገናነዝም ገነዙት ከቅዱስ ፊቅጦር ሥጋ ጋርም በሣጥን ውስጥ አኖሩት። የስደቱም ዘመን እስኪሚፈጸም ጠበቁት።

ከዚህም በኋላም የቅዱስ ፊቅጦር እናት ቅድስት ሶፍያ ወደ እንዴናው አገር መጣች የቅዱሳን ገላውዴዎስንና የፊቅጦርን ሥጋቸውንም ወስዳ ወደ አንጾኪያ አደረሰች። የቅዱስ ገላውዴዎስ ሥጋ አስዩጥ በሚባል አገር ይኖራል የሚልም አለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል በቅዱስ ገላውዴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላሀሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 11 ስንክሳር።

                         ✝️ ✝️ ✝️
"#ሰላም_ለቅዳሴ_ቤትከ_ኢየሱስ_ክርስቶስ_መድኃኒነ። በእስክንድርያ ዘኮነ። ኀቤከ እግዚኦ አንቃዕዶና አዕይንተነ። ከመ ተሀበነ እምቅኔ ኃጢአት ግዕዛነ። ንጸንሐከ ንሕነ እምዘመን ዘመነ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሰኔ_11

                         ✝️ ✝️ ✝️
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወኢትፈርህ እምግርማ ሌሊት። እምሐፅ ዘይሠርር በመዓልት። እምግብር ዘየሐውር በጽልመት"። መዝ 90፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 5፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 5፥7-12 እና የሐዋ ሥራ 16፥35-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥16-32። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም አቡነ ገብረ ኢየሱስ፣ አቡነ መዝሙረ ድንግልና የቅዱስ ገላውዴዎስ የዕረፍት በዓል። በሁላችንም ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
💐💐💐💐💐💐💐💐

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

"በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ::"
(ራዕይ. 12:7)

👉👉👉 እንኳን ለመላእክት አለቃ ለሊቀ መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!!!

   
††† በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ

👉 ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)

👉 ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ

👉 ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ

👉 ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
አባ ዮስጦስ ሊቀ ዻዻሳት (የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር)

👉 አባ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት ይከበራሉ።


የቅዱስ ሚካኤል ምልጃው እና ፈጣን ተራዳኢነቱ አይለየን።

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

ኆኅተ ጥበብ ሰንበት ትምህርት ቤት

💐💐💐💐💐💐💐💐
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊

በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ ቅዱስ ላሊበላ: ቅድስት አፎምያና ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ ይከበራሉ::

💖

🕊 † ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት †  🕊

ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ : አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ፺፱ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን ፵ ዘመን በበርሃ መርቷል: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: [ዘፍ.፵፰፥፲፮, ኢያ. ፭፥፲፫, መሳ. ፲፫፥፲፯, ዳን. ፲፥፳፩, ፲፪፥፩, መዝ. ፴፫፥፯, ራዕይ. ፲፪፥፯] ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::

ቅዱስ ሚካኤልን በዚሕች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን:-

፩. በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን
፪. ቅድስት አፎምያን መርዳቱን
፫. ቅዳሴ ቤቱን [ ግብፅ ውስጥ ]
፬. ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን
፭. ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን
፮. ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና

††† ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን::


🕊   †  ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ  †   🕊

† በ፲፪ [12] ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
- በብሥራተ መልአክ ተወልዷል
- ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል
- የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጓል
- በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም
- ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል
- በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር
- ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር:: ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት [ጠርዝ] ብቻ ነበር::

በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል
- በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን [ላስታን] ገንብቷል
- ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው::

ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ: በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚሕች ቀን አርፏል:: ጌታችን ስምህን ያከበረ: ዝክርህን የዘከረ: ከቤትህ ያደረውን: ከርስተ መንግስተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል::

††† በረከቱን: ክብሩን ያድለን::


🕊  †  ቅድስት አፎምያ  †   🕊

ከቅዱስ አስተራኒቆስ ጋር በተቀደሰ ትዳር የኖረች
- ምጽዋትን ያዘወተረች
- በፍቅረ ቅዱሳን የጸናች
- ንጽሕናዋን ጠብቃ ሰይጣንን ያሳፈረች ደግ እናት ናት:: ዛሬ የቅዱስ ሚካኤልን ስዕል ታቅፋ: በትእምርተ መስቀልም አማትባ አርፋለች: ቅዱሱ መልአክም ወደ ገነት አሳርጓታል::

🕊  †  ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ  †  🕊

የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ:
- በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ:
- በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ:
- በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ:
- ምጽዋትን ያዘወተረ: አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
- በዚህች ቀን አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::

† አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ በረከት ይክፈለን:: አሜን:: †

🕊

[ † ሰኔ ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፫. ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ
፬. ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
፭. ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
፮. አባ ዮስጦስ ሊቀ ዻዻሳት [የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር]
፯. አባ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ሰማዕት]
፭. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ:: † [ራዕይ.፲፪፥፯] (12:7)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ † እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል እና ለጻድቁ አባ ዮሐንስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 †  ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት  †  🕊

† ቅዱስ ገብርኤል :-

- በራማ ከሚኖሩ ሊቃናት አንዱ::
- አርባብ በሚባሉ አሥር ነገዶች ላይ አለቅነትን የተሾመ::
- የስሙ ትርጓሜ "እግዚእ ወገብር" [ጌታና አገልጋይ] አንድም "አምላክ ወሰብእ" [የአምላክ ሰው መሆን] ማለት የሆነ::
- በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ያረጋጋ::
- ብርሃናውያን መላእክትን የሚመራ::
- በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አብሣሪነቱ በስፋት የተነገረለት::
- በተለይ ደግሞ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የመሆን ዜና ይሸከም ዘንድ ያደለው::
- ከድንግል ማርያም ጎን በፍጹም የማይርቅ::
- በፈጣን ተራዳኢነቱ ብዙ ቅዱሳንን ያገለገለ ታላቅ ቀናዒ መልአክ ነው::

በዚሕች ዕለት እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ባቢሎን ልኮታል:: ሊቀ መላእክት ነቢዩ ዳንኤልን ከአናብስቱ ጥርስ እንዳዳነው መጽሐፍ ነግሮናል::

ይልቁኑ ታላቁ ነቢይ ዳንኤል የተማረኩ ወገኖቹን መመለስ እያሰበ በሃዘን ሲጸልይ በዚሕ ቀን ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ዳስሶታል:: ባርኮታል:: አጽናንቶታል:: ለዳንኤል በዋነኛነትም ሦስት ምሥጢራትን ገልጾለታል:-

፩. የቤተ እሥራኤልን ከሰባ ዘመን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ::

፪. የክርስቶስን ሰው መሆንና መሞት::

፫. የሐሳዌ መሲሕን በመጨረሻ ዘመን መምጣት ነግሮታል:: ስለዚህም እኛ ቅዱስ ገብርኤልን እንድናከብረው : በጸሎትም እንድንጠራው አባቶቻችን አዝዘውናል::

🕊 † አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም †  🕊 

† ጻድቁ ሃገራቸው መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ሲሆን የታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ባልንጀራ ናቸው:: ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በክርስትና አድገው : ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው ወደ ገዳም መንነዋል::

ከታላቁ ኮከበ ገዳም አባ ኢላርዮን ሥርዓተ መነኮሳትን አጥንተው አባ ኤስድሮስን በረድዕነት አገልግለዋል::

ከብዙ ዓመታት ትሕርምትና ገዳማዊ ሕይወት በኋላ የቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል:: በጵጵስናቸው ዘመን አንድ ከባድ ስሕተት ሠርተው ነበር::

እርሱም ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ከምእመናን የተሠበሠበውን ገንዘብ ለግል ጉዳያቸው አውለው ልብሳቸውና ቤታቸው ወርቅ በወርቅ ሆኖ ነበር:: ፈጣሪ ግን ይሕንን ብክነት ከእርሳቸው ያርቅ ዘንድ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን ላከው::

እርሱም በምክንያት ከቆጵሮስ ኢየሩሳሌም ገባ:: ጓደኛ ናቸውና አሳምኖ የወርቅ ንብረቶቹን ሁሉ ወሰደ:: ለነዳያንም ሰጣቸው:: አባ ዮሐንስ ሊቁን "እቃየን ካልመለስክ" ብለው ቢይዙት ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጸልዮ ዐይናቸው እንዲታወር አደረገ:: አንዳንዴ የታወረ ልብ የሚገለጠው እንዲሕ ነውና::

በደቂቃዎች ልዩነት ዐይነ ስውር የሆኑት አባ ዮሐንስ አለቀሱ:: ሊቁንም "ራራልኝ : አማልደኝ?" አሉት:: እርሱም ጸልዮ አንድ ዐይናቸውን ብቻ አበራላቸው:: "ለምን?" አሉት:: "ተግሳጽ ነው" አላቸው::

ከዚያች ቀን በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ልቡናቸው ተመለሱ:: ቤታቸውን ገዳም አደረጉት:: በሚደነቅ ቅድስና : ፍቅርና ሐዋርያዊ አገልግሎት ምዕመናንን አገልግለው በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፈዋል::

† የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ረድኤት : የአባ ዮሐንስ በረከት አይለየን::

🕊

[ †  ሰኔ ፲፫ [ 13 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት [ወደ ዳንኤል የወረደበት]
፪. አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
፫. አባታችን ቃይናን [ከአዳም አራተኛ ትውልድ]
፬. አባ ማትያን ጻድቅ

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. እግዚአብሔር አብ
፪. ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫. ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬. ቅዱስ አስከናፍር
፭. አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮. ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯. አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

" . . . በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን: ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ:: በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ:: አስተማረኝም: ተናገረኝም:: እንዲህም አለ :- "ዳንኤል ሆይ! ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ::" † [ዳን. ፱፥፳-፳፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
2024/11/20 09:40:19
Back to Top
HTML Embed Code: