Telegram Web Link
🛎 ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፳፮

       አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጋቢት ፳፮ በዚች ቀን የከበረችና የተመሰገነች ድንግሊቱ ኢዮጰራቅስያ አረፈች።

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
      ምሴተ ሐሙስ
  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1974 ዓመታት በፊት "ምሴተ ሐሙስ" በምትባለው በዚህች ዕለት

⓵ በወዳጁ በዓልዓዛር ቤት የዓለማት ፈጣሪ ሲሆን በትሕትና ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል::

⓶ ለእኛ ድኅነት ይሆነን ዘንድ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል::

⓷ በጌቴሴማኒ ላቦቱ እንደ ደም እየተንጠፈጠፈ ጸልዮ "ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ" ሲል አስተምሯል::

⓸ ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ይሁዳ ሊቃነ ካህናቱን አስከትሎ መጥቶ ለ30 ብር አሳልፎ ሰጥቶታል::                   
📖ማቴ 26፥26
📖ዮሐ 13፥1

❖ ይህ ሁሉ ለእኛ ድኅነት ተፈጽሟልና ምስጋናና ክብር ለፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን::


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
    ቅድስት ኢዮጰራቅስያ
  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይኽችም ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ከከበሩ የመንግሥት ወገን ነች፤ የሮሙ ጻድቅ ንጉሥ የቅዱስ አኖሬዎስ የቅርብ ዘመድ ናት፤ መኮንኑ አባቷ በሚሞትበት ጊዜ ለንጉሥ አኖሬዎስ አደራ ሰጣት፡፡

❖ አባቷ የተወላትን የመሬት ግብር እናቷ ልትቀበል ወደ ግብፅ ስትሄድ አስከትላት ሄደች፤ በዚያም ጉዳያቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ወደ አንድ የደናግል ገዳም ገብተው ቆዩ፡፡

❖ ኢዮጰራቅስያ በዚህ ወቅት ዕድሜዋ 9 ዓመት ብቻ ነበር፤ በገዳሙ ውስጥ ያለውን የደናግል የተጋድሎ ሕይወት አይታ ከእነርሱ ጋር መኖርን ወደደች፡፡

❖ እናቷም ጉዳዩዋን ፈጽማ ስትጨርስ እምቢ ብላታለችና ልጇን ይዛ መሄድ አልተቻላትም፤ ይልቁንም ገንዘቧን ሁሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች መጽውታ ከልጇ ጋር እዚያው ገዳም ቀረች፤ በተጋድሎም ጸንታ ኖራ በሰላም ዐረፈች፡፡

❖ ንጉሥ አኖሬዎስም የእናቷን ማረፍ ሰምቶ ኢዮጰራቅስያን ባል ያጋባት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፡፡
❖ እርሷም ‹‹ንጉሥ ሆይ የክብር ባለቤት ለሆነ ለሰማያዊ ሙሽራ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ራሴን ሰጥቻለሁና ቃልኪዳኔን መተላልፍ አይቻለኝም›› ብላ ላከችበት፤ ንጉሡም የዕድሜዋን ማነስና ቆራጥነቷን አይቶ አደነቀ፡፡

❖ ቅድስት ኢዮጰራቅስያም በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረች፤ በየሁለት ቀኑ የምትመገብ ሆነች፤ ቀጥላም በየሦስት ቀን አደረገች፡፡

❖ በመጨረሻም በየሰባት ቀን ሰባት ሰባት ቀን የምትጾም ሆነች፤ በከበረች አርባ ጾምም ከሰንበት በቀር ምንም ምን የማትቀምስ ሆነች፡፡

❖ ሰይጣንም ቀንቶባት ክፉ ሕማም እግሯ ላይ አመጣባት ነገር ግን ጌታችን ፈጥኖ ፈወሳትና እርሷም ራሷ ብዙ ሕሙማንን የምትፈውስበትን ታላቅ ጸጋ ሰጣት፤ እመ ምኔቷም ስለ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ታላቅ ራእይ አየች፤ መልእክትም ተነገራት፡፡
❖ አክሊላትንና አዳራሾችን ለቅድስት ኢዮጰራቅስያ እንደተዘጋጀላት አይታ ለደናግል እኅቶቿ ነገረቻቸው ነገር ግን ለኢዮጰራቅስያ እንዳይነግሯት አስጠነቀቀቻቸው፤ ቅድስት ኢዮጰራቅስያም በሆድ ዝማ ሕማም ጥቂት ታማ መጋቢት 26 ቀን ዐረፈች፡፡

❖ እመ ምኔቷም ‹‹ኢዮጰራቅስያ ስለእኔ ለምናለችና ወደ ጌታዬ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እሄዳለሁና በእኔ ቦታ ሌላ ሰው ሹሙ›› ብላ በቀጣዩ ቀን ዐረፈች፡፡
የቅድስት ኢዮጰራቅስያ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፤ በጸሎቷ ይማረን

📌 መጋቢት 26

ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1. ቅዱሳን ሐዋርያት
2. ቅድስት ድንግል ኢዮጰራቅስያ
3. ቅዱስ ፍርፍርዮስ ሰማዕት

📌 ወርሐዊ በዓላት
1. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2. አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3. አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4. ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5. አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
6. አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ
(የድንግል ጠባቂ)
Forwarded from Bketa @¥
††† እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† መድኃኔ ዓለም †††

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ በዚሕ ዕለት ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት::
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::

*ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት:: ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት:: ራሱንም በዘንግ መቱት:: እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::

*በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት:: በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ 6,666 ገረፉት:: ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት::

*ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት:: ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ::
ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ::

*ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ:: በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ:: አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት::

*በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ:: ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ:: (ማቴ. 27:1, ማር. 15:1, ሉቃ. 23:1, ዮሐ. 19:1)

††† ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ: አምስቱ ቅንዋቱ: ስለ ቅዱስ መስቀሉ: ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን::

††† ከቅዱሳኑ በዚሕች ዕለት:-

††† ከ80 ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ: የገዳማውያን ሞገሳቸው: የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ አርፏል:: 

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት: ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል:: ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው:: 

††† መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን:: 

††† መጋቢት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ)
2.ቅዱሳት አንስት (ከእግረ መስቀሉ ያልተለዩ)
3.ቅዱሳን ባልንጀሮች (በጌታ ስቅለት ጊዜ ከሞት የተነሱ)
4.ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
5.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
6.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (የኢትዮዽያ ንጉሥ)
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል 

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(፩ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#የፍቅር_ሥራ_ይህች_ናት

ባልንጀራውን የሚረዳውን ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ይረዳዋል፡፡ ለወንድሙ የሚነቀፍበትን ስም የሚያወጣውን ፈታሒ በርትዕ እግዚአብሔር እንዲሰደብ ያደርገዋል፡፡ ክፉ ስለ ሠራ ወንድሙን በቤቱ ለብቻው ሆኖ የሚመክረው ሰው ግን በምክሩ ዐዋቂ ይሆናል፡፡ ወንድሙን በዐደባባይ የነቀፈ ግን ኀዘን ያጸናበታል፡፡ ከሰው ተለይቶ ወንድሙን የሚመክር ሰው እነሆ የፍቅሩን ብዛት ያስረዳል፤ በባልንጀሮቹ ፊት የሚነቅፈው ግን የቅናቱን ጽናት ያስረዳል፣ የምቀኝነቱን ጽናት አስረዳ፡፡ 

ወዳጁን ተሠውሮ የሚመክር ሰው ብልህ ባለመድኃኒት ነው:: ያ እንዳዳነው መክሮ አስተምሮ ያድነዋልና፡፡ ወንድሙን በብዙ ሰው ፊት የሚያመሰግነው ሰው እሱ እውነተኛ ጠላቱ ነው፣ በውዳሴ ከንቱ ይጎዳ ብሎ ነውና።

ኀዘን ያለበት የርሕራሄ ምልክቱ የበደሉትን ሁሉ ይቅር ማለት ነው። የጠማማ ምልክቱ ጸብ ክርክር ነው፡፡ ወደ ክብር የሚያደርስ ረብህ ጥቅም ያግኝ ብሎ የሚመክር፣ የሚያስተምር በፍቅር ይመክረዋል፣ ያስተምረዋል፡፡ ቂም በቀል የሚሻ ሰው ፍቅር የለውም፡፡ አንድም እበቀለዋለሁ ብሎ የሚመክር ከፍቅር የተለየ ነው፡፡

ስሙ ይክበርና እግዚአብሔር በፍቅር ይመክራል፣ ያስተምራል፣ እበቀላለሁ ብሎ ያይደል፡፡ እሱስ በምሳሌው የተፈጠረው ሰውን ለማዳን ይገሥጻል፡፡ አንድ ጊዜስ እንኳን ቂም አይዝም፣ መዓትን አያዘጋጅም፡፡ የፍቅር ሥራ ይህች ናት፣ በቅንነት ትገኛለች፡፡ ቂም ለመያዝ እበቀላለሁ አትልም፣ በፍቅር ሰውን መናገር ነው።

ብልህ የሚሆን ቅን ሰው ክብር ይግባውና እግዚአብሔርን ይመስለዋል፡፡ ሰውን ክፉ ስላደረገ እበቀለዋለሁ ብሎ አይገሥጸውም፣ ሊመክረው ወዶ ነው እንጂ ሌሎችንም ለማስፈራት ነው እንጂ። ተግሣጽስ በፍቅር ካልሆነ ተግሣጽ አይባልም፡፡ በጎ ነገር ያደርግልኛል ብሎ በጎ የሚሠራ ኋላ ፈጥኖ ይተዋል፡፡

(#ምክር_ወተግሣጽ_ዘማር_ይስሐቅ - በዲ/ን ሞገስ)
††† እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር:: ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ40 ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ:: ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::

የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ : ቀርነ ሃይማኖት የቆመው : ብዙ ሥርዓት የተሠራው : ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት : ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት : በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል:: "ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው::

††† ዳግመኛ በዚሕ ቀን የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሆነው ሞቱ በመቃብር ውስጥ አድሯል::

††† ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን:: መልካም መሪንም ይስጠን::

††† መጋቢት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

††† "እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው::" †††
(፩ጢሞ. ፪፥፩-፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
2024/09/28 14:18:58
Back to Top
HTML Embed Code: