Telegram Web Link
ተወዳጅ ሆይ! ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲህ ይልሃል፦

✟ አንተ ግን ለድኾች ምጽዋትን ትሰጣለህ፤ እኔም እጄን ዘርግቼ ካንተ እቀበላለሁ፡፡
✟ የታረዙትን በምታለብሳቸው ጊዜ እኔን ታለብሰኛለህ፡፡
✟ የታሰሩትን በምታረጋጋቸው ጊዜ በመካከላቸው ኾኜ በዚያ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በሽተኛውንም በምትጎበኘው ጊዜ ከእርሱ ጋር በአልጋው ላይ ኾኜ ዳግመኛ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በቦታው ኹሉ የራቅሁ አይደለሁም፡፡ ትእዛዜን በምትፈጽምበት ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁና ችግረኞችን የምረዳቸው እኔ ነኝና፤ ለድኾች የምታደርገው ኹሉ ለእኔ ማድረግህ ነው፡፡ እኔም በእርሱ ፈንታ በጎ ዋጋ እከፍልሃለሁና፡፡
✟ በቤትህ ውስጥ እንግዳ በአሳደርክ ጊዜ እነሆ ከእንግዳው ጋር በማደሪያህ አስገባኸኝ፡፡
✟ እንደዚህ ለሚያደርግ ቁጣዬ ከእርሱ ይርቃል፤ ወደ ሕይወት ወደብም አደርሰዋለሁ፡፡ ከክፉ ነገር ኹሉ እጠብቀዋለሁ፡፡ እባርከዋለሁ፡፡ ዘሩንም አበዛለሁ፡፡ ዋጋውንም በሰማይ ባለው በአባቴ ዘንድ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ ዘለዓለማዊ ዕረፍትንም እሰጠዋለሁ፡፡"

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በገብረ እግዚአብሔር ኪደ)
እኛ የሃይማኖት አባቶች ከሌላ የምንዋሰው ንግግርና አስተምህሮ የለንም፤ ዐሠርቱ ቃላትን ማክበርና መተግበር ማስተማርና ማሥረጽ በቂያችን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዐሠርቱ ቃላት የበለጠ ሌላ ሕግ በዓለም ስለሌለ ማለት ነው፤ ቢኖርም ከሱ የተኮረጀ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የኛ አስተምህሮ አትግደል እንጂ ግደል ሊሆን አይችልም፤ የኛ ተግሣጽ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ የሌላውን አትመኝ፣ አታመንዝር የሚል እንጂ በተመሳሳይ የፆታ ጋብቻ ወደ ነውረ ኃጢአት ተሠማራ የሚል ትምህርት መቼውም ቢሆን ከቶ ሊኖረን አይችልም፡፡

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ከዚህ ውጭ ከዘመኑ የወሬ ሱሰኛ መሣሪያን እየተበደርን ከቅዱስ ወንጌሉ ጋር የሚጣረስ ንግግርና አስተምህሮ ማስተላለፍ ለምን አስፈለገ? ይህ ለኛ ኃሣር እንጂ ክብር ሊያስገኝልን አይችልም፤ ከእንደዚህ ያለ ድርጊትም መራቅ አለብን፤ የኛ ደንበኛና ዘላለማዊ ፖለቲካ ቅዱስ ወንጌል ነው፤ ዘላለማዊውን ትተን ጊዜያዊውን፣ መለኮታዊውን ትተን ሰዋዊውን አንከተል፡፡ ይህ ለኛ የሞራል ዝቅጠት ያስከትልብናል፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርም ከኛ የሚጠብቁት ትክክለኛውን ቃለ ቅዱስ ወንጌል ማስተማር ነው፤ ለዓለሙ ፖለቲካ ግን የራሱ ባለቤቶች አሉለት፡፡ እኛ በፖለቲከኞች ላይ ያለን ሥልጣንና መብት ማስተማርና መምከር ነው፤ ያም ሆኖ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም እኩል ልጆቻችን መሆናቸውን አውቀን በፍቅር በመመልከት ነው፡፡ ሲጋጩብንም የማስታረቅና የማቀራረብ፤ የመምከርና የማሳመን እንጂ ወደ አንዱ ተለጥፎ ሌላውን ዘልፎ መናገር የቆምንለት ቅዱስ ወንጌል አይፈቅድልንም፡፡

ፓለቲከኞችም ባልዋሉበትና ባልተፈቀደላቸው፣ ሌላው ቀርቶ የተቋቋሙበት ሕገ መንግሥቱ እንኳ የማይፈቅድላቸውን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም ስሕተት ነው፤ ተቀባይነትም የለውም፤ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ለፖለቲከኞቹም አይበጅም፡፡ ሁሉም ድንበሩን ጠብቆ በጋራ ጉዳዮች ላይ በፍቅርና በመከባበር ተመካክሮና ተግባብቶ መስራት ያሻል፤ በዚህ መንፈስ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተናበው ቢሰሩ በሀገር ላይ ሰላም ይሰፍናል፣ ልማት ይፋጠናል፣ ዕድገት ይመዘገባል፤ ስለዚህም በዚህ ዙሪያ ሁላችንም ከምር ልናስብበት ይገባል።

(ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ➛ የበዓለ ሲመት መልእክት የተወሰደ)
#ምን_ይጠቅምሃል?

ከእግዚአብሔር ባልሆነ ክብር መክበርን ለምን ትሻለህ? ክብርን ፍለጋ ከቆላ ወደ ደጋ፣ ከደጋ ወደ ቆላ ትወጣ ትወርዳለህ ለመሆኑ ክብር ከወዴት ናት ያለችው? ክብር እኮ ባለክንፉ መልአክ ክንፍ ስላለው የማያገኛት፤ እጅና እግር የሌለው ቶማስ ክንፍ ይቅርና እጅና እግር እንኳን ሳይኖረው የሚያገኛት ስጦታ ናት።

ዝጉሃዊ ባሕታዊ ከደጅ ሳይወጣ በበዓት ተከትቶ በሩን ዘግቶ የሚያገኛት ከሰማይ እንጅ ከምድር ያልሆነች ናት። ከእግዚአብሔር እንጅ ከሰው አይደለችም።

ክብርን መሬት ለመሬት አገር ላገር እየዞርህ መፈለግህን ተው። ሰው በተሰበሰበበት ሕዝብ በበዛበት ዐደባባይ ተገኝቼ ካልተናገርሁም አትበል። እንደዚህ ባሉ ቦታዎች ያገኘኸውን ክብር ከአንድ ቀን በኋላ አታገኘውም። ቅዱስ ጳውሎስ ከበርናባስ ጋር በሊቃኦንያ ከተሞች በሰበከ ጊዜ ሕዝቡ ተገረሙበት በሊቃኦንያም ቋንቋ አማልክት በሰው አምሳል መጡልን አሉ።
ነገር ግን በበነጋው ጳውሎስን የሞተ እስኪመስላቸው ድረስ በድንጋይ ወገሩት።

ትናንት ዕጣን ሊያጥኑለት መሥዋዕት ሊያቀርቡለት ለነበረው ሰው ድንጋይ ያነሡበታል ብለህ ታስባለህ? ሰዎች ያመጡልህን ክብር መልሶ ለመውሰድ ጊዜ አይፈጅባቸውም። እግዚአብሔር ግን ከሰጠህ አይወስድብህም። ሰዎች ስላልሰጡህ ክብር ማዘንህ በፊትህ መጥቆር ይታወቅብሃል፤ ነገር ግን ያ ክብር ከእግዚአብሔር ካልሆነ ምን ይጠቅምሃል?
ከእግዚአብሔር በሆነ ጊዜ ደግሞ አንዳች ነገር ሳይቀንሱ ያመጡልሃል።

የደብረ ጽሙናው አባ ሲኖዳ በሕይወት ሳሉ በገዳማቸው ዙሪያ ከሚኖሩ ሰዎች ክብርን አልተቀበሉም ነበር። እንዲያውም ይባስ ብሎ ከገዳማቸው አሳደዷቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር ክብራቸውን ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ገለጠው። ያሳደዷቸው ሰዎች በሕይወት ባያገኟቸውም አፅማቸው ባረፈበት ቦታ ሂደው ይቅርታ ጠየቋቸው። በሕይወት ሳሉ ማንም አልተከተላቸውም በባዶ እግራቸው ከገዳሙ ወጡ። ክብራቸው ሲገለጥ ግን በፈረስ በበቅሎ አፅማቸውን ጭነው አመጧቸው።

የክብር ቀን አለ፤ ዛሬ ይሁን ብለህ አታስቸግር።
የመገለጥ ጊዜ አለ፤ አሁን ግለጠኝ ብለህ ፈጣሪህን አትለምን። የምትከበርበት አገር አለህ ያለ ቦታህ መጥተህ አክብሩኝ አትበል። አብርሃምን ያከበረው በካራን ሳይሆን በከነዓን መሆኑን አስብ። ያለ ሀገርህ በባዕድ ምድር ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ቢሰጥህ ምን ይጠቅምሃል? ክብር ደስታን የሚሰጠው በግብፅ ሳይሆን በከነዓን ሲሆን ነው። ዮሴፍ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከነዓንን አለመርሳቱን አስብ። ግብጽ በሰጠችው ክብር ራሱን አላስታበየም። ይልቁንም ራሱን እንደ ፈላሲ ቆጠረ እንጅ። በሚሞትበትም ጊዜ አጥንቶቹ ሳይቀር በግብጽ እንዳይቀሩ ለልጆቹ አሳሰባቸው።

ሰማያዊ ሀገር አለህ። በዚያ የተዘጋጀልህን ክብርም ታውቃለህ። የግብጹን ተወው። አገርህ ስትገባ አሁን ያማረህን ክብር ትወርሰዋለህ።

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ
Forwarded from YeneTube
ወላይታ ሶዶ በአታ ለማርያም ቤተክርስቲያናችን እየፈረሰችብን ነዉ ድምፅ ሁኑን

በወላይታ ሶዶ በአታ ለማርያም ቤተክርስትያን ይዞታ "ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል" በሚል ምክንያት በጸጥታ አካላት በጉልበት እየፈረሰች ነው

በአንድ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ስጦታ ሰጪነት በተገኘ መሬት ላይ የተተከለችው በወላይታ ሶዶ ከተማ የምትገኘው ዋዱ በአታ ለማርያም ቤተክርስቲያን
የወላይታ ዞን ስፍራውን ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል በሚል ምክንያት መቃኞ ህንጻ መቅደሱን ለማፍረስ የጸጥታ ኃይል ያሰማራ ሲሆን የጸጥታ አካላት የጦር መሳርያ በመጠቀም ምዕመናንን ከአከባቢው ለማራቅ ቢሞክሩም አሁን ድረስ ህዝቡ ቤተክርስቲያኒቷን ከበ በመያዝ የማፍረስ ተግባሩን ለማስቆም እየሞከረ ይገኛል። ድምፅ ሁኑን

@Yenetube @Fikerassefa
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††

††† እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕት "ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም "*+

=>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

+ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

+እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

+እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

+በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

=>ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው::

+በመንኮራኩር አበራየው:: ለአናብስት ጣለው:: አካላቱን ቆራረጠው:: በእሳትም አቃጠለው:: ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ:: በፍፃሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ 3 አክሊላት ወርደውለታል::

+ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል:: ስሙን የጠራ: መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም:: (ማቴ. 10:41)

=>አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን:: አይተወን:: አይጣለን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን::

=>የካቲት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
2."6,304" ሰማዕታት (በቅ/ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

=>+"+ እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን:: +"+
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. 73)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
† እንኳን ለኢትዮዽያዊቷ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† እመ ምዑዝ (እም ምዑዝ) †

††† ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሐዋርያዊት: ጻድቅትና ሰማዕት ናት::
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-
=>ወር በገባ በ29 በቤተክርስቲያናችን ታስበው
ከሚውሉት እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳን ከገባላቸው
(ከሰጣቸው) እናቶች ኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅት
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ትገኛለች::
ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ማን ናት? ምን ቃል ኪዳን
ተሰጣት? ያደረገችውን ተጋድሎ በጥቂቱ እንመልከት:-
✞✞ ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ
ይወስዳል፡፡ (ማቴ. 10፡40) ✞✞

=>በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቂት ወረዳ ጥባ
ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና
ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ
ምዑዝ ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት
ገዳም ትገኛለች፡፡

+ይህች ገዳም ከአዲስ አበባ በደሴ ወደ ጎንደር
በሚወስደው መንገድ 665 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ
ገራገር (ፍላቂት) ከምትባለው ከተማ በመውረድ በእግር
2፡30 እንደተጓዙ ከ370 ዓመት ባለይ ያስቆጠረችውን
እመ ምዑዝ ኪዳነምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በአንድ
ቀን የሠራቻትና ለጌታ በአራቱም አቅጣጫ የሰገደችውን
ታላቅና ድንቅ ቤተመቅደስ ያገኛሉ፡፡

+የዚህች ታላቅ ገዳም መስራች ኢትጵያዊት ሰማዕትና
ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በደቡብ ጎንደር ደራ ፎገራ
አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አዋሳኝ ከተታ
ማርያም ተብሎ በሚጠራ ቦታ በሚያዚያ 4 ቀን ተፀንሳ
ታህሳስ 29 በጌታ ልደት ቀን ተወለደች፡፡

+አባቷ ላባ እናትዋ ወንጌላዊት የተባሉ እግዚዘብሔርን
የሚወዱ ትዕዛዙን የሚከብሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡
መሀን ሆነው ልጅ ባመውለዳቸው እያዘኑ ተግተው ወደ
እግዚአብሔር በመፀለያቸው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን
የመሰለች ልጅ: በፀሎትዋ ለሀገር ለወገን የምትበቃ
ሰጥቷቸዋል፡፡

+ከዚያም 80 ሲሆናት ለልጅነት ጥምቀት ወደ ቤተ
መቅደስ በወሰዷት ጊዜ ከጥምቀት በኋላ ስጋ አምላክ
ስትቀበል (ስትቆርብ) "ሕይወት የሆነውን ቅዱስ ስጋህን
ክቡር ደምህን የሰጠኸኝ አምላኬ ክብር ምስጋና ይግባህ"
ብላ አመስግናለች፡፡ ስመ ክርስትናዋ ማርያም ፀዳለ
ሲሆን የአለም ስሟ 'ሙዚት' ነው፡፡ ፍቅርተ ክርስቶስ
የምንኩስና (የቆብ) ስሟ ነው፡፡

+እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አባ ዳንኤል ከሚባል
አባት መፅሐፍን እየተማረች ካደገች በኋላ ለአቅመ ሄዋን
ስትደርስ እናትና አባቷ ሊድሯት በመፈለጋቸው ዘርዓ
ክርስቶስ ለሚባል ከደጋግ ሰዎች ወገን ለሆነ ሰው
አጋቧት፡፡

+ማታ እንደ ሙሽሮች ደምብ ወደ ጫጉላ ቤት ሲገቡ
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ዘርዓ ክርስቶስን "ወንድሜ ሆይ!
እኔ የእናት አባቴን ፍቃድ ለመፈፀም ነው እንጂ ስጋዊ
ሙሽራ መሆን አልፈልግም ፡፡ ፍላጎቴ የእግዚአብሔር
ሙሽራ መሆን ነው" በማለት ብታማክረው ቅዱስ ዘርዓ
ክርስቶስም ፀጋ እግዚአብሔር የበዛለት ሰው ነበርና "እኔም
እናት አባቴን ላክበር ፈቃዳቸውን ለመፈፀም ነው እንጂ
የስጋ ፈቃድ የለኝም በማለት ተነጋገሩ::

+በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ ለቤተሰቦቻቸው: ለአገሬው
እንደ ባልና ሚስት ግን በንፅህና ለ40 ዓመት ሁለቱም
በድንግልና ኖረዋል፡፡

+ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅዱስ ሚካኤል
መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቢግራቸውም ሁለቱም
"ይህስ አይሆንም" ብለው ለ40 ቀን በጾም: ፀሎት:
በትጋት ጸልየዋል፡፡ መልአኩ ተገልጦ "ይህ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው ሁለታችሁም ድንግልናችሁ አይፈርስም ብሎ
ነግሮአቸዋል፡፡

+ከዚያም ወንድ ልጅ ወልደዋል:: ህፃኑ በተወለደ በ7
ዓመቱ በቅዱስ ሚካኤል እቅፍ ገነትን ለ7 ቀናት ከጎበኛት
በኋላ ወደ ምድር ሲመልሰው "በእናት አባቴ አምላክ
ይዤሃለሁ ወደዚች ወደ ከፋች ዓለም አትመልሰኝ" ብሎ
ቢለምነው ቅዱስ ሚካኤልም ከአምላክ ጠይቆ በብሔረ
ህያዋን የህፃናት አለቃ ተብሎ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡
ስሙም ዳግማዊ ቂርቆስ ተብሏል፡፡

+ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶና ቅዱስ ዘርዓ ክርስቶስም ልጅ
ከወለዱ በኋላ እንደ ቀደሞው በቅድስና: በንፀህና ፀንተው
ኑረዋል፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው አፄ
ሱስንዮስ ሃይማኖቱን ለውጦ 'ሁለት ባህርይ የሚሉ
ካቶሊኮችን በመቀበሉ ክርስቲያኖችን እየገደለ ነው' የሚል
ወሬ ሰምተው ወደ ንጉሱ በመሄድ ሳይፈሩ ስለ ተዋህዶ
ሃማኖታቸው በንጉሱ ፊት መስክረዋል፡፡

+ንጉሱም በጣም የበዛ መከራን አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ
በበዛ ቁጥር እነርሱም እየፀኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሱን
ሠራዎቶች ሳይቀር አሳመኑ:: 60,000 ክርስቲያኖችም
ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

+ንጉሱም በጣም የበዛ መከራ አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ
በበዛ ቁጥር እነርሱም እየጸኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሱን
ሰራዊቶች እያሳመኑ ቢያስቸግሩ በሰማዕትነት አንገታቸውን
አስቆርቷቸዋል፡፡ አንገታቸውም ሲቆረጥ ከሁለቱም ደም
ውሃ ወተት ፈሷዋል፡፡

+በዚያን ዘመን ከእነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ጋር
ሰማዕትነት ከተቀበሉት ውስጥ የማህበረ ስላሴው ጻድቁ
አምደ ስላሴ: የጎረጉር ማርያም አባ መርአዊ: የመሲ
ኪዳነ ምህረት እመ ወተት እና ከ60 ሺ በላይ ክርስቲያኖች
ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡

+ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንገቷ ከተቆረጠና ሰማእትነት
ከተቀበለች በኋላ ወደ ምድር መልሶ አንገቷን ከቀሪው
የሰውነቷ ክፍል ጋር አዋህዶ ከአንቅልፍ አንደሚነቃ ሰው
ቀስቅሶ አስነስቷቷል፡፡
ከዚያም ከአቡነ ማርቆስ ስርዓተ ምንኩስናን በመቀበል
ዋልድባ ገዳም ለ4 ዓመት አገልግላለች፡፡

+ከዚህም ከ500 የሚበልጡ ተከታዮችዋን መነኮሳትን
አስከትላ በሰሜን ወሎ ቆቦ ወረዳ ወደምትገኘውና በፃድቁ
በአባ ጉባ ተመስርታ ጠፍታ ወደ ነበረችው ራማ ኪደና
ምህረት አንድነት ገዳም በመሄድ ገዳሟን አቅንታ: የወንድ
የሴት ብላ ስርዓት ሰርታ: ገዳሟን አስተካክላ: 500
የሚሆኑ አገልጋች መነኮሳትን አኑራ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ
ጀምራለች፡፡

+በመንገዷም ላይ ሰውን የሚበሉ ወደ ሚኖሩበት አካባቢ
በመድረስ እነርሱም እርሷንና 60 የሚሆኑ አገልጋዮችዋን
ዓይኖቻቸውን በጉጠት በማውጣት ለ4 ወራት በጨለማ
ቤት ውስጥ ዘግተውባቸዋል፡፡ ከአራት ወር በኋላም በዓል
አድገው ለመብላት ከቤት ቢያወጧቸው መልካቸው እንደ
ፀሐይ የሚያበራ ቢሆንባቸው "አንቺ ሴት ምንድን ናችሁ?"
ብለው ጠይቀዋታል፡፡

+እርሷም ክርሰቲያን መሆናቸውንና እነሱ የስላሴ ሕንፃ
የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው
ብትመክራቸው "ምን አንብላ?" ብለዋታል፡፡ እርሷም
ከራማ ኪዳነ ምህረት ስትነሳ የእህል ዘርን በአገልጋዮቿ
አሲዛ ነበርና ስንዴውን በአንድ ቀን ዘርታ: በቅሎ: ታጭዶ:
ደርቆ: ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡

+እርሷ ቀምሳ ብታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት
የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም
እንደዚህ እያደረጉ እየሰሩ እንዲበሉ አስተምራ: አስጠምቃ
ከ6 የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክላላቸዋለች፡፡
+ከዚያም የተወሰኑ አገልጋዮችን አስቀምጣላቸው ወደ
ኢየሩሳሌም በመሄድ ለ7 ዓመታት በአየሩሳሌም ከኖረች
በኋላ የእመቤታችን በዓል ለማክበር ወደ ግብፅ በመሄድ
ላይ ሳለች በመንገድ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታ
ስትፀልይ እመቤታችን በስዕሏ ላይ ተገልጣ: ቦታዋ
በኢትዮጵያ መሆኑን ነግራ: እጇን ዘርግታ "ወደ ኢትዮጵያ
ሂጂ" ብላ ነገረቻት::

+በኋላ በብርሃን አምድና በቅዱስ ሚካኤል እየተመራች
አሁን ወደ ምትታወቅበትና የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ወደ
ተገለፀበት እመ ምዑዝ ኪዳነ ምህረት ቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስ አንድነት ገዳም ደርሳለች፡፡
+በቦታው ስትደርስ የቦታው ልምላሜ የሚያስደስት ነበርና
"ይህች ቦታ ምን ታምር!" ብላለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን
ድረስ ምንታምር በመባል ይጠራል፡፡

+ምንታምር ላይ ከአገልጋዮቿ ጋር በመሆን አርፋ ሳለ
ከኢየሩሳሌም መርቶ ያመጣት የብርሃን አምድ በዚያ ቦታ
ላይ በስፋት ረቦ (ከምድር እስከ ሰማ ተተክሎ) ብታየው:
መልአኩም "ቦታሽ ይሄ ነው" ብሎ ቢነግራት በዚያው
ተቀምጣለች፡፡

+የቦታው ባለ አባት "ይህን ቦታ ልቀቂ" ቢሎ ቢጠይቃት
"እግዚአብሔር የሰጠኝ ቦታዬ ነው" ብላዋለች፡፡ እርሱም
ለክስ ወደ ጎንደር በመሄድ አፄ ሱስንዮስ አርፈው አፄ
ፋሲል ነግሰው ነበርና እሳቸውን ፍርድ ቢጠይቃቸው በዝና
ያውቋት ነበርና "ቤተ ክርስቲያን ካልተሰራ ትልቀቅልህ:
ከተሠራ ግን ሌላ ቦታ ይሰጥሃል" የሚል ፍርድ አስፈርዶ
ነበር::

+ሲመለስ ቅዱስ ሚካኤል ቀድሞ "ቶሎ ቤተ ክርስቲያን
ስሪ እንዲህ የሚል ፍርድ ተፈርዷል ብሎ ነግሯት ‹‹ታህሳስ
14 ቀን ከነግህ ፀሎት በኋላ በሰንሰልና በስሚዛ
ግድግዳዋን: በአይጥ ሀረግ ማገር አድርጋ: የግድግዳ
ቤተ መቅደስ በዕለተ አርብ: በአንድ ቀን ሰርታ ታህሳስ 16
ቀን እሁድ ታቦተ ኪዳነ ምህረትን አስገብታ ቅዳሴ
አስቀድሳለች::››

+ቅዳሴውም ከተፈፀመ በኋላ ጌታችን ከቅዱስ መንበሩ
ላይ እንዳለ ሆኖ ከእናቱ ከእመቤታችን ጋራ ታያቸው፡፡
ከመንበሩ ወርዶም ይህን ቦታ በባረከው ጊዜ የስሚዛው
ቤተ መቅደስ በአራቱም አቅጣጫ ለፈጣሪው ሰገደ፡፡

+የመሬት መናወጥም ሆነ:: ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም
"ልታጠፋን መጣህን? ቤተ ክርሰቲያኔንስ ልታፈርሳት
ነው?" ብላ ብትጠይቀው "ይህ የሰንሰል ቤተ መቅደስሽ
ዳግም እስከምመጣ ድረስ ሳይፈርስ: ሳይታደስ ፀንቶ
ይኖራል፣ በውስጡም እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ
የክሀድያንና ፣ መናፍቃን እግር አይገባበትም፣ በውስጧ
ቁርባንን የተቀበሉ ሁለ ኃጢያታቸው ይሰረይላቸዋል፣
ዘወትር ምህረቴ በረከቴ ከእነርሱ ጋር ይኖራል" በማለት
ተናግሮ ተሰወራቸው፡፡

+ከዚያም በኋላ መነኮሳትና መነኮሳይያት የቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስን የትሩፋት ዜናዋን ሰምተው ከየአቅጣጫው
ተሰበሰቡ፡፡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም በአምላክ ሀይል
ተጋድሎአቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ታስተምራቸው ፣
ትመክራቸው፣ በተግባርም እያሳየቻቸው ለብዙ ዘመናት
ከኖሩ በኋላ በገዳሙ ላይ የአጋንንት ፆር እንዳይነሳ
ወንዶቹን ለብቻ ሴቶቹን ለብቻ አደረገች፡፡

+ዘወትርም እንዳይተያዩ የእግዚአብሔር መልዐክ
በቅድስተ ፍቅርተ ክርሰቶስ ፀሎት ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከዚህ
ኃላፊ ዓለም መለየቷ በቀረበ ጊዜ ሁለት መላዕክት ወደ
እርሷ መጥተው በብርሃን ሰረገላ ጭነው ወደ ደብረ ነባት
(ወደ ብሔረ- ህያዋን) ወስደው በዚያ ቅዱስ ቁርባንን
አቀብለው ወደ ቦታዎ መለሷት፡፡

+መልዐኩም "ከጻማ: ከድካም: ከመታረዝ: ከረሐብ
ከጥም: ከመትጋት: ከእንባ: ከዚህ ዓለም የምትለይበት
ጊዜ እነሆ ደረሰ" አላት፡፡ የካቲት 27 ቀንም ወደ ምስራቅ
እጇን ዘርግታ ቆማ ስትጸልይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ
ከደስታ ብርሀን ጋር ያማረ ሽታ መላ::

+ጌታችን ከአዕላፋት መላዕክትና ቅዱሳን ጋር ወደ እርሷ
መጣ፡፡ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ሰገደች፡
ተንበረከከች: እጅግም አለቀሰች፡፡ ከወደቀችበት ቦታ
አንስቶ ‹‹ላጠፋሽ አልመጣሁም ወዳጄ ላከብርሽ ነው
እንጂ›› አላት፡፡

+"የዘለአለም መንግስት አዘጋጅቼልሻለሁና ደስ ይበልሽ"፡፡
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ቃል ኪዳን እንዲገባላት
ተማጸነችው:: ጌታችንም ‹‹ሁሉም እንደ ቃልሽ ይሁንልሽ::
በስምሽ ስሜ ተጨምሯልና ለቤተ ክርስቲያንሽ መባ
የሰጠ፣ የተላከ ፣የተቀበረ፣ ቤተ መቅደስሽ መጥቶ
የተሳለመ ፣ እስከ 12 ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን
ሰጠሁሽ::

+በረከቴም በቤቱና በልጆቹ በገንዘቡም ላይ ይደር::
የገድልሽ መጽሐፍ ባለበት አጋንንት (ሰይጣናት)
አይቀርቡም:: በአዝመራ ስምሽን በጠሩት ጊዜ የለመለመ
ይሁን:: በጸሎትሽ የተማጸነ ሁሉ ባለጤና ይሁን::

+ስምሽን በእውነት የሚጠራ የከበረ ነው፡፡ ያለመጠራጠር
በቀናች ሐይማኖት የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ: ያጻፈ:
ያነበበ: የተረጎመ በሐይማኖት የሰማ: እስከ ቀዝቃዛ ውሃ
ድረስ የሰጠ ኃጢያቱ ይሰረይለታል::
ስለ ድካምሽ ስለ ትሩፋትሽ 7 አክሊሎችን እና ይህን ሁሉ
ቃል ኪዳን ሰጠሁሽ፡፡ ላልምረው ቦታሽን
አላስረግጠውም›› ብሏት ወደ ሰማይ አረገ፡፡

+በማግስቱ ትንሽ ህመም ታመመች ደናግል መነኮሳትን
ጠርታ የእረፍት ቀኗ መድረሱን ነገረቻቸው:: ከመካከላቸው
አንዷን ለገዳሙ አስተዳዳሪነት መርጣ በፍቅር ስም
ተሰናበተቻቸው፡፡ የዳዊት መዝሙርንም ስትጸልይ የካቲት
29 ቀን እሁድ አጥቢያ ጠዋት በጌታ በዓል አንቀላፋች
(ነፍሷ ከስጋዋ ተለየች)፡፡

+ጌታችንም ከእናቱ: ከቅዱሳኑ ጋር መጥቶ ነፍሷን
ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም ገነት ወሰዳት፡፡ ቅዱሳንም
ከመላእክት ጋር እልል እያሉ እያመሰገኑ ወደ ዘለዓለም
ቦታ ገነት አስገቧት፡፡ ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ መቃብር
ላይ 40 ቀናት ብርሃን ሲበራበት ታይቷል፡፡

+በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት: በመቂት ወረዳ ጥባ
ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ
በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ ምዑዝ
ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት ገዳምም
በዓላቶቿ የሚከበሩት ታህሳስ 16 የቅዳሴ ቤቷ እንዲሁም
የካቲት 29 ቀን በዓለ እረፍቷ ይከበራል፡፡

††† ከቅድስት እናታችን በረከት አምላክ አይለየን::

††† የካቲት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
2.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
3.ቅዱሱ ሕፃን (የፍቅርተ ክርስቶስ ልጅ)
4.ቅዱስ ቢላካርዮስ ዘሃገረ አርሞኒ (አረጋዊ: ደራሲ: ጻድቅና ሰማዕት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ

††† "መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ:: አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ::
ውበት ሐሰት ነው:: ደም ግባትም ከንቱ ነው::
እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች:: ከእጇ ፍሬ ስጧት:: ሥራዎቿም በሸንጐ ያመስግኗት::" †††
(ምሳሌ. 31:29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!†††

††† ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ †††

††† ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

*የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ደርሶ ነበር::

*ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

*ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

*የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

*እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

*ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

*ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

*ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

*ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

*"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

*ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)*ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

*ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

††† አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች)
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም መጥምቁ ዮሐንስን አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

††† የካቲት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
(ታላቁ ነቢይና ካህን መጥምቁ ዮሐንስ ሔሮድስ በግፍ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ ቅድስት ራሱ ለ15 ዓመታት ዙራ አስተምራ አርፋለች:: በዚህ ዕለትም በልሑክት (በሸክላ ዕቃ) የተገኘችበት በዓል ይከበራል:: በዓሉም "ተረክቦተ ርዕሱ" በመባል ይታወቃል:: )
2.አባ ሚናስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

††† "ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ::" †††
(ማቴ. 11:7-15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት ሠላሳ(፴)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
👉📌 👉 ለሰንበት ትምህርት ቤታችን አባላት በሙሉ:-

የሰንበት ትምህርት ቤታችን አባል የሆነችው ውቤ ኃይሉ  ታናሽ ወንድም በስደት በሊቢያ ባሕር ለመሻገር መሄዱን ጠቅሳ ከታገተበት ሰዎች እጅ ለመውጣት  ደላሎቹ ከ700ሺ ብር በላይ ስለጠየቁ የሰንበት ተማሪ አባሎቻችን በእግዚአብሔር ስም የቻላቹት አግዙን ብላ ሰንበት ትምህርት ቤቱን ጠይቃለችና የተቻለንን ያክል እናግዛት።

እንዲሁም ኃይለ መስቀል ብላችሁ በጸሎታችሁ አስቡት ።

1000498493673
ውቤ ሀይሉ

ኆኅተ ጥበብ ሰንበት ትምህርት ቤት
👏👏👏👏👏👏👏ቅበላ👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏👏
               ቅበላ   ቅበላ_
መቼም ቅበላ የሚለው ቃልን ስንሰማ ሁላችንም ጀሮ ላይ አንድ ነገር ያቃጭላል እሱም ፆም ከመግባቱ በፊት የምናደርገው ተግባር ነው።
በመሰረቱ ቅበላ ማለት በእንግድነት ለሚመጣው እንግዳ ለእንግዳው የሚመጥነውን ያህል ክብር ለመስጠት አዘጋጅቶና ተዘጋጅቶ መቀበል ነው::
ስለዚህ ለአንድ ነገር ቅበላ ስናደርግ ያንን የምንቀበለውን ነገር በሚመጥን መልኩ መሆን አለበት። ለምሳሌ አንድ መንፈሳዊ መነኩሴ ወደ ቤታችን በእንግድነት ቢመጣ ለመነኩሴው ቅበላ የምናደርግለት እሱን ሊመጥን በሚችል መልኩ ነው የፀሎት ቤት አዘጋጅተን እግሩን አጥበን ጉልበት ስመን መኝታ ክፍሉ ውስጥ ቅዱሳት ስዕላትን ወይም መፅሐፍ ቅዱስ አስቀምጠን.  .  . የመሳሰሉትን ነገሮች እንደ እኛ አቅም አዘጋጅተን ልንቀበለው እንችላለን። አልያ ደግሞ አንድ ህፃን ልጅ ወደ ጎጆአችን በእንግድነት ቢመጣ መኝታ ክፍል አዘጋጅተን የተረት መፃሕፍቶችን አሰናድተን የህፃናት ፊልም ከፍተን የህፃናት መጫወቻ አወጋጅተን ቅበላ ልናደርግለት እንችላለን።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ ፆምንም ስንቀበል ከፆም ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ አለብን እንጅ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ተግባር ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው። ፆም ሊገባ ነው ብለን ሆዳችን እስኪተረተር የምንበላ ጨንጓራችን እስኪላጥ የምንጠጣ ዝሙት የምንፈፅም በየ ጭፈራ ቤቱ የምንዞር ከሆነ ይህ የፆም ቅበላ ይባላልን? በጭራሽ አይባልም።እንደውም ይህ የሚያሳየው ፆሙን ሳንፈልግ እንደምንቀበለው ነው።
"ነብይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብይን ዋጋ ይወስዳል" ማቴ 10:41 እንዳለ ጌታችን ፆምን ስንቀበል በፆም ስም በፆም ተግባር መሆን አለበት።
እንደውም አንዳንድ የበቁ አባቶች የአብይ ፆም ሊገባ ሲል ፆሙን በፆም ይቀበሉታል።በእርግጥ ይህ ለእኛ ሊከብደን ይችላል ቢሆንም ፆሙን በፆም መቀበል ቢያቅተን እንኳን ፆሙን ከፆም ጋር በሚስማሙ መልካም ተግባራት መቀበል እንችላለን።
ፆም ከመግባቱ በፊት ንስሐ መግባት ፣ የበደሉንን ይቅር ማለት ፣ የበደልናቸውን ይቅርታ መጠየቅ ፣ የተጣላናቸውን መታረቅ ፣ መመፅወት ፣ ፆሙ የበረከት እንዲሆንልን መፀለይ ፣ መንፈሳዊ ምግባራትን መላበስ ፣ ከመጠን ያለፈ ደስታን ከራስ ማራቅና የመሳሰሉትን ከእኛ ጋር የሚስማሙትን መንፈሳዊ ተግባራት ከንስሐ አባታችን ጋር ተመካክረን ተግባራዊ በማድረግ ቅበላ ማድረግ ይኖርብናል።
በዚህ መሰረት የሚፈፀም ቅበላ ፆሙ ከመግባቱ በፊት መንፈሳችን እንዲዘጋጅ ከማድረጉም ባለፈ እግዚአብሔር ከፆሙ በፊት አስቀድሞ እንዲባርከን ያደርጋል።
ወዳጄ ሆይ የአንተ ቅበላ ከየትኛው ነው? መቼም በስካር በከርስ መሙላት በጭፈራና በዝሙት ቅዱሱን እንግዳ #ፆምን እንደማትቀበል ተስፋ አደርጋለሁ።
አበው "ከምግብ ብቻ በመከልከል እንጾማለን አትበሉ .. ከክፉ ግብር መራቅ ጾማችንን ትክክል ታደርጋለች" ይላሉ::
በዚህም የአባቶቻችን ልጆች እንባላለን አባቶቻችን የወረሷትን መንግስት በእውነት እንወርሳለን::
.
.
.
ኦ ጌታ ሆይ! ቸሩ አምላኬ ሆይ ሀጢያቴ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝቶ በደሌ ስፍር መለኪያ ጠፍቶለት ክፉዋ ምላሴ ፤ የተበረዘው ጭንቅላቴ ፤ የደነደነው ልቤ ሳያሰለችህ ሳያስቀይምህ ቀናትን በሳምንታት ሳምንታትን በወራት ወራትን በአመታት ተክተህ ለዚህች ቀን ስላደረስከኝ በደካማ አንደበቴ አመሰግንሀለሁ።
እንደ እውነቱ ዘመኑ ዓመተ ምህረት ባይሆን ኑሮ እኔ ገና ድሮ ነበር የምቀሰፍ! ገና ድሮ ነበር የምጠፋ! ግን አምላኬ ሆይ አንተ እንደ ሰው ስላልሆንክ ለፍርድ አልቸኮልክም በፍቅር ታገስከኝ በስስት ዓይንም ተመለከትከኝ።
ኦ አምላኬ ሆይ! እኔዋ ደካማይት ልጅህ ያለፈውን ፆም በቅጡ ሳልጠቀምበት ፍቃድህን ሳልፈፅም ደካሞችን ሳልረዳ የደከሙትን ሳልጎበኝ ያዘኑትን ሳላፅናና የሰጠህኝን ቅዱስ ቀናት እንዲሁ በከንቱ አሳለፍኩ።
ጌታ ሆይ እኔ ደካማ እንደሆንኩ ታውቃለህ አንተ እኮ የልብና የኩላሊትን የምትመረምር ቅዱስ አምላክ ነህ። እናም ድካሜን ታውቃለህ ስንፍናዬን ታውቃለህ አምላኬ ሆይ ታዲያ እንደዚህ ደካማ ሰው ሁኜ ፆምህን እንዴት ልፆም እችላለሁ? እንዴት 40 የፆም ቀናት በፍቃድህ ላሳልፍ እችላለሁ?
የድንግል ልጅ አማኑኤል ሆይ አንተ ካልረዳኸኝ አንተ ካልደገፍከኝ ታዲያ ይህን ነገር እንዴት ልወጣው እችላለሁ? አንተ እኮ መቅደላዊት ማርያምን ወደ ቅድስትነት ሙሴ ፀሊምን ከገዳይነት ወደ ባህታዊነት ሳኦልን ወደ ሰባኪነት ለውጠሀል። ጌታዬ ሆይ ታዲያ እኔን አንተ ካላገዝከኝ በእኔ አቅምማ እንዴት ይሆናል?
የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ መድኃኒአለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእናትህ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በቅዱሳን መላዕክት አማላጅነት በፃድቃን ሰማዕታት ፀሎትና ምልጃ እያመንኩና እየተማፀንኩ ከሰይጣን ፍላፃዎች ሁሉ እንድትታደገኝና ለደካማዋ ልጅህ ትደርስላት ዘንድ በሀጢያት በተዳደፌ አንደበቴ እለምንሀለሁ!
፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
ፆሙ የበረከትና የፍሬ እንዲሆንልን ከወዲሁ እመኛለሁ!
#ዘወረደ
(የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት )

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡

‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው #ጾመ_ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን #ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

#ሕርቃል_ማን_ነው?
#ለምንስ_በስሙ_ተሰየመ?
በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60 ሺህ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3 ሺህ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም ቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል። እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገ*ደ*ለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡

በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

«#ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «#የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት፣ ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.3፥13፡፡

ሳምንቱ #ሙሴኒ ይባላል። ይህ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ» ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡ /ዘፀ.24፥18፤ 1ኛ.ነገ.19፥8፤ ማቴ. 4፥1-4/፡፡
††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሃገሩ ሮሃ (ሶርያ አካባቢ) ሲሆን ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን የተመለከተ) ይባላል::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ሃገር ይህ ቀረው የማይባል ኃጢአተኛ ሰው ነበር:: ታዲያ ምንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍፁም ልቡ ይወዳት ነበርና በመዳን ቀን ጥሪ ለንስሐ አበቃችው::

ከዚያች ዕለት ጀምሮም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው : ንጹሕ የቤተ ክርስቲያን መስዋዕት : ጽኑዕ የበርሃ ምሰሶ ሆነ:: ድንግል እመቤታችንም ከነሥጋው ወደ ሰማያት ወስዳ ገነትና ሲዖልን አሳይታ : ከአዳም : ኖኅ : አብርሃም : ሙሴ : ዳዊትን ከመሰሉ ቅዱሳን ጋር አስተዋውቃ : ከዚህም በላይ የሆነና በሰብአዊ አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢር አሳይታ ወደ ምድር መልሳዋለች::

ቅዱስ ጐርጐርዮስ በሰማይ (በገነት) በነበረው ቆይታ ክብረ ቅዱሳንን ተመልክቶ አድንቋል:: በተለይ በፍጹምነት ድንግልናቸውን የጠበቁ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደናግል አኗኗራቸው ከአምላክ እናት : ከሰማይ ንግሥት : ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ጋር መሆኑን አይቷል::

"የለበሱት ልብስም በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የሚቻል አይደለም" ይላል:: የደናግል ፊታቸው ከፀሐይ 7 እጅ ያበራልና ግርማቸው ያስፈራል::

ቅዱሱ ሰው በዚያው በሰማይ ሳለ ደግሞ ይህንን ተመለከተ:: አንድ አረጋዊ : ጽሕሙ ተንዠርግጐ : የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሶ ይመጣል:: ቅዱሳን መላእክት በፊት በኋላ : በቀኝ በግራ ከበውት ሳለ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ጀመረ::

"እግዚኦ እግዚእነ : ጥቀ ተሰብሐ ስምከ በዲበ ምድር (አቤቱ ጌታችን : በምድር ሁሉ ስምህ የተመሰገነ ሆነ)" ሲል . . . መላእክቱ በዝማሬ አጀቡት:: በዚህ ጊዜም ታላቅ መናወጥ ሆነ:: ደናግሉም የቅዱሱን ሽማግሌ በረከቱን ተሳተፉ::

ይህ አመስጋኝ ሽማግሌ ልበ-አምላክ : ጻድቅ : የዋህና የእሥራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር:: በምን ታወቀ ቢሉ :- በበገናው:: አንድም እመቤታችን "አባቴ ዳዊት!" ብላ ስትጠራው ጐርጐርዮስ ሰምቷልና::

በመጨረሻም እመቤታችንን በፍጹም ክብርና ግርማ ተመልክቷት ሐሴትን አድርጓል:: እመ-ብርሃንም "ተወዳጅና ንጹሕ ሰው ነህ" ስትል ቅዱስ ጐርጐርዮስን አመስግናዋለች:: ስለዚህ ዓለምም እንዲህ የሚል መልእክትን ልካለች::

"ልጆቼ ሆይ! ከብርሃን ጨለማን : ከደግነት ክፋትን : ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን . . . ምነው መምረጣችሁ? እኔ ስለ እናንተ በየቀኑ እየለመንሁ እነሆ አለሁ:: ወደ ጨለማ ገሃነም እንዳትወርዱ እባካችሁ ንስሐ ግቡ!"

ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ለቅዱሱ ሰው ነግራው : ቅዱስ ዳዊትን አስከትላ : በግሩማን መላእክት ታጅባ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት (የእሳት መጋረጃዎች ወደ ተተከሉበት ድንኳን) ገባች:: በዚያም ተመሰገነች::

ለዛም አይደል ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ:-
"ይዌድስዋ መላእክት ለማርያም በውስተ ውሳጤ መንጦላዕት : ወይብልዋ : በሐኪ ማርያም ሐዳስዩ ጣዕዋ::" ሲል ያመሰገናት::

ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከሰማይ ቆይታ መልስ ያየውን ሁሉ ጽፎ ለአበው ሰጥቷል:: ስለዚህም ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን ያየ) ይሰኛል:: ቅዱሱ ተረፈ ዘመኑን በተጋድሎ ፈጽሞ በዚህች ቀን አርፏል::

††† የቅዱሱ እመቤት ድንግል እመ ብርሃን መዓዛ ፍቅሯን ታብዛልን::

††† መጋቢት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት (ዘሃገረ ሮሃ)
2.አቡነ መክፈልተ ማርያም ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
3.አባ መከራዊ ዘሃገረ ኒቅዮስ (አረጋዊ: ጻድቅ: ጳጳስና ሰማዕት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(፩ጢሞ. ፩፥፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from Bketa @¥
2024/09/29 16:27:13
Back to Top
HTML Embed Code: