Telegram Web Link
Forwarded from Bketa @¥
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥



❖በዚች ቀን የክቡር ፋሲለደስ ልጅ የከበረ አውሳብዮስ በሰማዕትነት ሞተ፤ ይህም የከበረ ፋሲለደስ ለአንጾኪያ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ነው ለመንግሥት ልጆችም አባታቸው ነው እርሱም ከፋርስ ሰዎች ጋር በጦርነት ውስጥ እያለ ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክርስቶስን ክዶ ጣዖትን እንዳመለከ ሰማ።

❖ እጅግ አዝኖ ወደ ልጁ ወደ አውሳብዮስ ልኮ ይህን ነገረው የከበሩ የቤተ መንግሥት ሰዎች ዘመዶቹን ዳግመኛ ጠራቸው እነርሱም የንጉሥ ልጅ ዮስጦስ አባዲር ገላውዴዎስና ቴዎድሮስ ከእርሳቸውም ጋር ያሉትን ጠርቶ ስለ ከሀዲው ንጉሥ ነገራቸው።



❖ ሁሉም እጅግ አዘኑ ዳግመኛም እንዲህ አላቸው እኔ ስለ ፈጣሪዬ ስለ ክርስቶስ ስም ደሜን አፈሳለሁ ሁሉም በዚህ በጎ ምክር ተስማምተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ፤ ጠላቶቻቸውንም ድል አድርገው ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋር ወጥቶ በደስታ ተቀበሏቸው።



❖ ከዘህም በኋላ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ህርማኖስ ለቅዱሳኑ ጣዖትን እንዲአቀርብላቸውና አንዲሰግዱለት ንጉሡን መከረው ንጉሡም ህርማኖስ እንደ መከረው አደረገ።

❖ በዚያንምም ጊዜ ቅዱሳንን ጠርቶ እነዲህ አላቸው እኔ እጅግ እንደምወዳችሁ እናንተ ታውቃላችሁ አሁንም ለአጵሎን ሰግዳችሁ ልቤን ደስ ታሰኙ ዘንድ ከእናንተ እሻለሁ።



❖ ቅዱሳንም ሰምተው እጅግ ተቆጡ አውሳብዮስም ንጉሡን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ ንጉሡም ሸሽቶ ተሸሸገ ከንጉሥም ባለሟሎች ብዙዎችን ሠራዊቱንም ጭምር ገደለ የከበረ ፋሲለደስም ባይከለክላቸው ከንጉሥ ቤት ምንም ሰው ባልቀራቸው ነበር።



❖ ከዚህም በኋላ ደግሞ አውሳብዮስን ወደ ግብጽ አገር ወስደው በዚያ ይገድሉት ዘንድ ህርማኖስ ንጉሡን መከረው እርሱ በዚች ሀገር ከኖረ ያገር ሰዎችን በላይህ ያስነሣብሃልና ያሰብከውን ምንም ምን መሥራት አትችልም አለው።



❖ ንጉሡም ቅድስ አውሳብዮስን ጽኑዕ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ ወደ ግብጽ አገር ወደ ቅፍጥ ገዥ ሉልያኖስ ዘንድ እንዲወስዱት ጻፈ ወደ መኰንን ሉልያኖስም በደረሰ ጊዜ በመንኰራኵር ሕዋሳቱን በመቁራረጥ በግርፋት አሰቃዩት፤ ደግመኛም በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት ጌታችንም መልአኩን ልኮ ከመከራው ሁሉ አዳነው አጽናንቶና አረጋግቶ ያለ ጉዳት አስነሣው፤ ነፍሱንም ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ወሰዳት የጻድቃንና የሰማዕታትንም መኖሪያ አየ ለርሱና ለአባቱ ለዘመዶቹም ያዘጋጀላቸውን ቦታዎች አይቶ ነፍሱ እጅግ ደስ አላት።



❖ ከዚህም በኋላ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአከ ወርዶ እሳቱን እንደ ጠል አቀዝቅዞ ያለ ጥፋት የከበረ አውሳብዮስን አወጣው።



❖ መኳንንቱም እንዲህ ብለው መከሩት መኰንን ሆይ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ እዘዝ ከእርሱም ትግል ታርፋለህ እርሱም የአውሳብዮስን የከበረች ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።



ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ሐዋርያውና ሰማዕቱ ቅዱስ ፖሊካርፐስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይኽም ቅዱስ ሐዋርያና ሰማዕት የሆነው ፖሊካርፐስ ከ70 ዓ.ም እስከ 156 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ ከመሰከረላቸው ከ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ ይኸውም የሰርምኔስ ዻዻስ የነበረ ነው፡፡

❖ ይኽም ቅዱስ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ ነው፤ አቡነ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ የቅዱስ ፖሊካርፐስ ባልንጀራው ነበር፡፡

❖ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከ46 ዓመታት በላይ በፍጹም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በ86 ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው በሰማዕትነት ገድለውታል፡፡

❖ የቅዱስ ፖሊካርፐስ የሰማዕትነቱ ዜና የተገኘው የራሱ የሆነችው የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነቱን በአካል በተከታተሉ ወንድሞች አማካኝነት ጽፋ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከበተነችው መልእክት ነው።

❖ በጥንቷ ቤተክርስቲያን የሰማዕታት የሰማዕትነታቸው ሁኔታ ሳይፈሩ ሰውነታቸውን ለሰይፍ ለስለት እንዴት እንደሰጡ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር እንዴት ይጨክኑ እንደነበር በሙሉ ዜና ገድላቸው እየተጻፈ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይሰራጭነበር፤ እንደ አግናጥዮስ ሁሉ (በሮም) ፖሊካርፐስ ሰማዕት በሆነበት ጊዜም በሰምርኔስ ከተማ የሕዝብ በዓል ተደርጎ ነበር፤ እንደልማዳቸው በዓሉ በሚከበርበት በእስታድየማቸው የአራዊት ትርኢት ነበር።

❖ አሬኒከስ የተባለ አንድ ክርስቲያንም የአሕዛብ ጣዖታትን ካላመለክህ ለአራዊት እንሰጥሃለን ብለውት አሻፈረኝ ብሎ በመፅናቱ በዚያ በአራዊት ተበልቶ ሰማዕት ሆነ።

❖ በዚህ ጊዜም ሕዝቡ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲፀኑ የሚያስተምራቸው ዋነኛው ፖሊካርፐስ ነው እርሱ ተይዞ ይምጣ እያሉ ጮሁ።

❖ ቅዱስ ፖሊካርፐስ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት ፀንቶ በከተማዋ ቢቆይም ምእመናን እንዲሸሽ እያለቀሱ ስለለመኑት ባጠገብ ወዳለች መንደር ሸሸ።

❖ በዚያ ሳለ ሰማዕት እንደሚሆን በራእይ ተረድቶ እንደሚሞት ለወንድሞችና እህቶች ነገራቸው፤ ወዲያው በጥቆማ ተይዞ ወደ ሰምርኔስ ከተማ እያንገላቱ ወስደው ሕዝብ በተሰበሰበበት በበዓሉ አደባባይ አቆሙት።

❖ እርሱም ክርስቶስ በሕዝብ አደባባይ ቆሞ የተቀበለውን መከራ እያሰበ የመከራው ተካፋይ ስላደረገው በፍጹም ደስታ መከራውን ይቀበል ነበር፤ በሕዝቡ ፊት አቁሞ የሚያናዝዘው ሹም ክርስቶስን እንዲክድ ብዙ ማግባቢያዎችንና ማስፈራሪያዎችን ቢያቀርብለትም ያለፍርሃት ፀንቶ ክርስቲያንነቱን ስለመሰከረ በእሳት እንዲቃጠል ተፈረደበት፤ በኋላ የሚያመልጠን መስሏቸው ለማጠር ሲዘጋጁ አይቶ “ወደ እሳቱ እንድገባ ያበረታኝ ጌታዬ በእሳቱ ውስጥም ፀንቼ እንድቆይ ያስችለኛል” አላቸው፤ ወታደሮቹ እጅና እግሩን አስረው ወደ እሳቱ ሲያቀርቡት አይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ በማለት የመጨረሻ ጸሎት አደረገ፤

✍️"አቤቱ ልዑል እግዚአብሔር የተወደደው ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በልጅህ አንተን እንድናውቅ ሆነናል፤ የመላእክትና የኀይላት እንዲሁም የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ አንተ ነህ፤ ፍጥረታትም ሁሉ የሚኖሩት ባንተ ነው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ለዘላለማዊ ሕይወት ትንሣኤ ያለፍርሃት ከክርስቶስ መከራ ተካፋይ ከሆኑት ከሰማዕታት ወገን እንድቆጠር ስላደረግኸኝ እና በዚህች ቀንና ሰዓት በሚገባ ስላስተማርኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ እንደ እነርሱ ዛሬ በፊትህ ተቀብያለሁና እንደ መልካምና የተወደደ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበልልኝ፤ አንተ አስቀድመህ እንዳሳየኸኝ እና እንዳዘጋጀኸኝ አንተ እውነተኛና ታማኝ አምላክ ነህና ስለሁሉ ነገር አመሰግንሃለሁ፣ አከብርሃለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ከሰማያዊው ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ከተወደደው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብርና ምስጋና ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን”
❖ የጸሎቱ ይዘት ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ከምታስተምረው ምሥጢረ ሥላሴ ጋር አንድ አይነት ሲሆን ይህንኑም የመሰለ ጸሎት አላት::

❖ በዚህም የቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጥንታዊና ከምንጮቹ ከሐዋርያት የተረከበችው ለመሆኑ ታላቅ ማስረጃ ነው::

❖ ቅዱሱ ጸሎቱን ሲጨርስ በእሳቱ ውስጥ ወረወሩት፤ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ተአምር የሚሠራ እግዚአብሔር ለምእመናን መጽናኛ የሚሆን ድንቅ ተአምርን አደረገ።

❖ እሳቱ የቅዱሱን ሰውነት ዙሪያውን እንደግድግዳ ከቦ የማያቃጥለው ሆነ ሕዝቡም እሳቱ እንዳላቃጠለው ባዩ ጊዜ በጦር ተወግቶ ይሙት እያሉ ጮሁ፤ ወታደሮቹም በጦር ወጉትና በዚህ ሰማዕትነቱን ፈጸመ::

❖ ክርስቲያኖች እንዳያመልኩት በሚል የከበረ ሥጋውን አቃጠሉ፤ በዚህ ጊዜ ደስ የሚያሰኝ የእጣንና የሽቶ መአዛ ሸተተ፤ ክርስቲያኖችም ተረፈ አፅሙን በክብር ወሰደው ቀበሩት ቤተክርስቲያንም በስሙሠሩለት።

የቅዱስ ፖሊካርፐስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን



በዚችም ዕለት የከበሩ የአባ ቡላና የሦስት መቶ ሰማንያ ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
ሌባ አጥር ዘሎ ቤት ሰርስሮ ኪስ በርብሮ ምድራዊ ሐብትን ገንዘብን ጥሪትን ይሰርቃል፡፡ መናፍቃን የቤተክርስቲያንን ቅጽር ዘለዉ የሰዉ ህሊናን በጥርጣሬ ሰርስረዉ ከምግባርና ከሃይማኖት አራቁተዉ ነፍሳትን ይዘርፋሉ ሰለዚህ ከኪስ ሌባ ይልቅ የምግባርና የሃይማኖት ዘራፊዎችን ተጠንቀቁ፡፡

(ከአባቶች እንደበት)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

🛎 ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፳፬

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ሃያ አራት በዚች ቀን የከበረ አባት ኤጲስቆጶስ አጋቢጦስ አረፈ።

❖ ይህም አባት በከሀድያን ነገሥታት በዲዮቅልጥያኖስና በመክስምያኖስ ዘመን ነበር፤ ወላጆቹም ደጎች ምእመናን ነበሩ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምረውት ዲቁና ተሾመ።

❖ ከዚህም በኋላ እናትና አባቱን ትቶ ወደ አንድ ገዳም ሔዶ የሸመገሉ መነኰሳትን አገለገለ፤ ከእርሳቸውም በጎ አምልኮትን ተማረ አረጋውያኑንም እያገለገለ በገድል ተጠመደ ያለማቋረጥም በጾም በጸሎትና በስግደት ይተጋል ከጥዋትም እስከ ምሽት በመጾም የሽንብራ አሠር የሚመገብ ሆነ።

❖ ከእንቅልፍም ጋር ሊታገል በወደደ ጊዜ ከሽምብራ አሠር ጋር አመድ እየተመገበ ሰማንያ ቀን ኖረ በዚህም ተጋድሎ ውስጥ እያለ ኃይሉ ግን ይጨመርለት ነበር፤ ለአረጋውያንም አገልግሎቱን አላስታጐለም ሲጠራቸውም ጌቶቼ ይላቸዋል የጽድቅንና የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ፈጸመ።

❖ እግዚአብሔርም የሚያስደንቁ ብዙዎች የሆኑ ታላላቅ ተአምራቶችን በእጆቹ ገለጠ፤ ከእርሳቸውም አንዲቷን ብላቴና አዳናት እርሷም እንደ ዕንጨት የደረቀች እስከምትሆን ብዙ ዘመን ጭንቅ በሆነ ደዌ ታማ የኖረች ናት።
❖ ዳግመኛም ብዙ ሰዎችን ያጠፋውን ታላቅ ከይሲ በጸሎቱ ገደለው፤ ከሰውና ከእንስሳም አስጨናቂ የሆኑ በሽታዎችን አሰወገደ፤ የተጋድሎውና የኃይሉ ጽናት ወሬው በተሰማ ጊዜ ስሙ ሉክያኖስ የሚባል መኰንን ወደርሱ ልኮ አስመጥቶ ያለ ውዴታው በግድ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው እርሱ ግን ተጋድሎውን አልተወም ጾምንም ጸሎትንም የትሩፋትን ሥራ የሚጨመር ሆነ እንጂ የቀደመ ሥራውን አልተወም በጥቂት ቀኖችም ዲዮቅልጥያኖስንና መክስምያኖስን እግዚአብሔር አጠፋቸው አምላክን የሚወድ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ ይህም ቅዱስ ከጭፍራ ውስጥ ይወጣ ዘንድ ምክንያት የሚሻ ሆነ።

❖ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅግ የሚወደው መልከ መልካም የሆነ ወጣት ብላቴና ነበር ክፉ ጋኔንም ተጫነበት በቀንም በሌሊትም ታላቅ ሥቃይን የሚያሠቃየው ሆነ ቅዱስ አጋቢጦስንም ከሚያውቁት ውስጥ አንድ ሰው በአየው ጊዜ የወታደር አለቃ አጋቢጦስ ቢመጣ በአዳነህ ነበር አለው የታመመውም እርሱ በንጉሥ ጭፍራ ሥርዓት ውስጥ ያለ በውኑ ይህን ሥራ መሥራት ይችላልን አለ ሰውዬውም ገድሉንና ሥራውን ሁሉ አስረዳው፤ ጋኔን ያደረበትም በእውነት ሊያድነኝ ይችላልና ከዚህ ከአስጨናቂ ደዌ ያድነኝ ዘንድ የወታደር አለቃ አጋቢጦስን ፈጥናችሁ አምጡልኝ አለ።

❖ ንጉሥም ይህን በአወቀ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን እንዲአመጡለት አዘዘ በመጣ ጊዜም በወጣቱ ላይ ጸለየ በከበረ መስቀልም አማተበው በዚያንም ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል ዳነ ንጉሡም በዚህ ደስ ብሎት ቅዱስ አጋቢጦስን አከበረው ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ አለው እርሱም ንጉሡን ከወታደርነት ውስጥ አሰናብተኝ አለውና አሰናበተው አስቀድሞ ወደ ነበረባትም ቦታው ተመለሰ ብዙ ዘመናትም እጅግ እየተጋደለ ኖረ።

❖ ከዚህም በኋላ የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ይዞ ቅስና ሾመው ይህም ኤጲስቆጶስ በሞተ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን ይሾምላቸው ዘንድ ሕዝቡ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት እርሱም ሾመላቸው መልካም ተናጋሪዎች የሆኑትን የክርስቶስን መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው።

❖ እግዚአብሔርም የትንቢትን ጸጋ የተሠወረውንም የማወቅ ድንቆች ተአምራቶችንም የማድረግ ሀብትን ሰጠው። በሥውር ኃጢአትን የሚሠሩትን ኃጢአተኞች የሚገሥጻቸው ሆነ በንስሐም እስኪመለሱ ከመቅደስ ያርቃቸዋል።
❖ ዳግመኛም በገድሉ መጽሐፍ ተጽፎ የተገኘ የታላቅ ወንዝ ወራጅ ውኃን በመስቀሉ አቁሞ ወደ ሌላ መንገድ መለሰው የዕውር ዐይኖችንም ገለጠ ለምጻሞችንም አነጻ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዛላላሙ አሜን።

              
🛎 በዚችም ዕለት የከበሩ በጋዛ ሰማዕት የሆኑ ጢሞቴዎስና የቆጵሮስ ሀገር ሚናስ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
             
📌 የካቲት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
2.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት (ዘጋዛ)
3.ቅዱስ ሚናስ ዘቆዽሮስ


📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
Forwarded from ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት (ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት)
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ  ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 11ኛ ዓመት በዓለ ሲመት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ እየተከበረ ይገኛል።

ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ
††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አቡፋና †††

††† ታላቁ አባ አቡፋና፦
በምድረ ግብጽ ተጋድሏቸውን የፈፀሙ፣
በመዐልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊትም አምስት ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልዩ የነበሩ፣
በአርባ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ እህል ይቀምሱ የነበሩና ሙሉ ዘመናቸውን በበርሃ በታላቅ ጽሙና የፈፀሙ አባት ናቸው።

ጻድቁ በጣም የሚታወቁት ከማበጡ የተነሳ እጅግ ግዙፍ በነበረ እግራቸው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለ መድኃኔ ዓለም ፍቅር አልቀመጥም፤ አልተኛም ብለው ለአሥራ ስምንት ዓመታት በመቆማቸው ነው።

አሥራ ስምንት ዓመት የመቆማቸው ዜናስ እንደምን ነው ቢሉ፦
አንድ ቀን "እኔ ግን ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ይሆን?" ሲሉ አሰቡ። በእርግጥ ይህንን ሐሳብ ብዙ ሰዎች ሊያስቡት ይችላል። ሐሳቡ ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው።
፩. "ጠቃሚ ነው።" ያልኩት አንድ ሰው ሞት እንዳለ ካወቀ ወይም 'መቼ ነው የምሞተው' ብሎ ካሰበ ንስሐ ይገባል፤ ክፋትን ይተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ወገኔ ሁሉ እንደ አውሬ ሲባላ፣ ደም ሲያፈስ፣ ክፋትን ሲጐነጉን የሚውል "እሞት ባይ" ሳይሆን "እኖር ባይ" ሆኖ ነውና።
ግን ሞት በቅርቡ እንዳለ በኃያሉ አምላክ ፊት ራቁቱን ለፍርድ እንደሚቀርብ ለወገኔ ማን በነገረው!
፪. "ያልተፈቀደ ነው።" ያልኩት ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው።
"ኢትበሉ ለጌሰም (ለነገ አትበሉ።)" የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ።
ማቴ. ፮፥፴፬
ሰው (በተለይ ዓለማዊው) የሚሞትበትን ቀን ቢያውቅ አጭር ጊዜ ከሆነ ሽብር ጭንቀት ይበላዋል። ወዲህ ደግሞ ጊዜው ረዥም ቢሆን እንደ ሰብአ ትካት (ማለትም በኖኅ ዘመን እንደ ነበሩ ሰዎች) 'ብዙውን ልዝናናበት (ኃጢአት ልሥራበት')ና ንስሐ እገባለሁ።' ይላልና ነው።

በዚያውም ላይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ሰውና የነቢያት አለቃ ቅዱስ ሙሴ የሞቱን ጊዜ ጠይቆ እጅግ መቸገሩን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ጌታ "ዓርብ ቀን ትሞታለህ።" ብሎት ለሁለት ዓመታት ዓርብ ዓርብ ሲገነዝ ሲፈታ ኑሯል።

በመጨረሻም ዓርብ ቀን ድንገት መልአከ ሞት መጥቶበታል። ስለዚህ "ወድልዋኒክሙ ንበሩ - ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። መባላችንን አስበን ልንኖር ግድ ይለናል።
ማቴ. ፳፬፥፵፬

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አቡፋና ይህንን የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ "ተርፈከ አሠርቱ ወሰመንቱ - አሥራ ስምንት ቀርቶሃል።" አላቸው። እርሳቸውም "ጌታዬ አሥራ ስምንት ምን?" ሲሉ ቢጠይቁትም ሳይመልስላቸው ተሠወረ።

ከደቂቃ እስከ ኢዮቤልዩ ብዙ አሥራ ስምንቶች አሉ። እርሳቸው ግን "አሥራ ስምንት ቀን ነው!" ብለው ለጌታ ተሳሉ። ስዕለታቸውም "ከዚህ በኋላ አልቀመጥም።" የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቆሙ። ሞት አልመጣም።

"አሥራ ስምንት ሱባኤ ይሆን!" ብለው አሥራ ስምንት ሱባኤ (መቶ ሃያ ስድስት ቀናት) ቆመው ጸለዩ። አሁንም ሞት አልመጣም። "አይ! አሥራ ስምንት ወር ሊሆን ይችላል።" ብለው ለአሥራ ስምንት ወራት (ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር) ቆመው ተጉ። አሁንም ግን ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ይህን ጊዜ ግን ወደ ፈጣሪ ለመኑ። "ጌታዬ! ያልከኝ ምን አሥራ ስምንት ነው?"
ቅዱስ መልአኩም መጥቶ "አቡፋና ሆይ! የቀረህ አሥራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና።" ብሏቸው ተሰወረ። ልብ በሉልኝ "እስክሞት አልቀመጥም።" ብለው ተስለዋል።

ቅዱሱ ገዳማዊ በቃላቸው የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ነበሩና ለአሥራ ስምንት ዓመታት እንደተተከለ ምሰሶ ቆመው ጸለዩ፣ ጾሙ። እንዲህ ያሉትን ቅዱሳን ሊቃውንት፦
"ሰላም ለከ ጽኑዕ ከመ ዓምድ
ዘኢያንቀለቅሎ ሞገድ።"
(ማዕበለ ዓለም የማያናውጸው ብርቱ ምሰሶ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል።) የሚሏቸው።

ስለ ቅዱሱ የተጻፈ አርኬም፦
"ሰላም ለቁመተ አቡፋና ዘአልቦ ኑታጌ
እስከ ተመሰለ እግሩ ከመ እግረ ነጌ።" ይላል። ከመቆም ብዛት አካላቸው ደቆ እግራቸው የዝሆን እግር እስኪመስል ወፍሮ ነበርና።

††† አባ አቡፋና በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን አርፈዋል።

††† ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ እንጦኒ (Anthony) በትውልዱ ከሶርያ ዐረቦች ሲሆን በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ካህናትን ይደበድብ፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ያቃጥል ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ ሲጠራው ግን ደግ፣ ጻድቅና ምርጥ ዕቃ ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻም ከብዙ መከራ በኋላ ለሰማዕትነት በቅቷል።

††† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ትጋት፣ ጽናት፣ ፍቅርና በረከት ያድለን። ከማስተዋልም አያጉድለን።

††† የካቲት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፪.ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞናና ሉቅያ ድንግል (የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት)
፬.ቅዱስ ቶና ዲያቆንና ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሚናስ ዘሃገረ ቁስ

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

††† "ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።" †††
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from Zemen Asnake
Forwarded from Bketa @¥
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


🔔 ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፳፮


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ሃያ ስድስት በዚች ዕለት ዖዝያ ይባል የነበረ ዕውነተኛ ነቢይ ሆሴዕ አረፈ፤ ዳግመኛም ይህ ነቢይ በአራቱ የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ትንቢት ተናገረ፤ እሊህም ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝ፣ ሕዝቅያስ ናቸው።
❖ በትንቢቱም ድንቆች ሥራዎችን ተናገረ የእስራኤልንም ልጆች ገሠጻቸው የአመንዝራ ልጆች ብሎም ጠራቸው እግዚአብሔርም ቍጣውን ከእርሳቸው እንደማይመልስ አስረዳቸው፤ እንዲህም አለ የእስራኤል ልጆች ቍጥራቸው እንደማይሠፈርና እንደማይቈጠር የባሕር አሸዋ ቢሆን ከጥቂት በቀር አይተርፍም አለ፤ ስለ አሕዛብም በእግዚአብሔር ማመን ተናገረ እንዲህም አለ እኔ ወገኖቼ ያልሆኑትን እጠራቸዋለሁ እነርሱም ይሰሙኛል።


❖ ዳግመኛም ስለ መድኃኒታችን መከራ መቀበልና በከበረ ደሙ ስለ መዳናችን ስለ ትንሣኤውም እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ እሱ በመከራ ገርፎ ያድነናል እርሱም በመከራ አቍስሎ ይቅር ይለናል ሲያድነንም በሁለተኛው ቀን ነው በሦስተኛውም ቀን ድነን በሱ ፊት እንነሣለን እግዚአብሔርንም አውቀን እንከተለው ዘንድ ስለ ሞት ሥልጣን መሻር ስለ መቃብርም መሸነፍ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ሞት ይዘህ ማስቀረትህ መቃብርስ ድል መንሳትህ ወዴት ነው ትንቢትን እየተናገረ ሰባ ዓመት ያህል ኑሮ በበጎ ሽምግልና አረፈ።



ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።



🔔 በዚችም ዕለት የከበሩ ሳዶቅና ከእርሱ ጋር የሆኑ ሁለት ሺህ ስምንት ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ፤ ይህንንም የከበረ ሳዶቅን ለፀሐይ ይሰግድ ዘንድ የፋርስ ንጉሥ ብርህም ፈለገው ቅዱሱም ለፈጣሪው እንጂ ለዚች ለምትታይ ፀሐይ ልሰግድ ከእናቴ ማሕፀን አልወጣሁም ብሎ መለሰለት።


❖ ብርህም ንጉሥም መልሶ ለዚች ፀሐይ አምላክ አላትን አለው ቅዱስ ሳዶቅም ዓለሙን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ አምላክ ነው አለው፤ ንጉሡም የቅዱስ ሳዶቅን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የከበረ ሳዶቅም ቁሞ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ከዚህም በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ ቆረጡት።

❖ ያን ጊዜ ከሰማይ ብርሃን በላዩ ወረደ ከዚያ ያሉትም ሁሉ አይተው እኛ ሁላችንም በቅዱስ ሳዶቅ አምላክ የምናምን ክርስቲያን ነን ብለው ጮኹ ንጉሡም ሁሉንም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ ቊጥራቸውም ሁለት ሺህ ስምንት ነፍስ ናቸው።

በረከታቸውም ከኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን ።



📌 የካቲት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ (ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት)

2.ቅዱስ ሳዶቅ ሰማዕት

3."808" ሰማዕታት (ከቅ/ሳዶቅ ጋር የተሰየፉ)



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ

2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ

3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ

4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን

5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
6. አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የድንግል ጠባቂ)
ተወዳጅ ሆይ! ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲህ ይልሃል፦

✟ አንተ ግን ለድኾች ምጽዋትን ትሰጣለህ፤ እኔም እጄን ዘርግቼ ካንተ እቀበላለሁ፡፡
✟ የታረዙትን በምታለብሳቸው ጊዜ እኔን ታለብሰኛለህ፡፡
✟ የታሰሩትን በምታረጋጋቸው ጊዜ በመካከላቸው ኾኜ በዚያ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በሽተኛውንም በምትጎበኘው ጊዜ ከእርሱ ጋር በአልጋው ላይ ኾኜ ዳግመኛ ታገኘኛለህ፡፡
✟ በቦታው ኹሉ የራቅሁ አይደለሁም፡፡ ትእዛዜን በምትፈጽምበት ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር እኖራለሁና ችግረኞችን የምረዳቸው እኔ ነኝና፤ ለድኾች የምታደርገው ኹሉ ለእኔ ማድረግህ ነው፡፡ እኔም በእርሱ ፈንታ በጎ ዋጋ እከፍልሃለሁና፡፡
✟ በቤትህ ውስጥ እንግዳ በአሳደርክ ጊዜ እነሆ ከእንግዳው ጋር በማደሪያህ አስገባኸኝ፡፡
✟ እንደዚህ ለሚያደርግ ቁጣዬ ከእርሱ ይርቃል፤ ወደ ሕይወት ወደብም አደርሰዋለሁ፡፡ ከክፉ ነገር ኹሉ እጠብቀዋለሁ፡፡ እባርከዋለሁ፡፡ ዘሩንም አበዛለሁ፡፡ ዋጋውንም በሰማይ ባለው በአባቴ ዘንድ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ ዘለዓለማዊ ዕረፍትንም እሰጠዋለሁ፡፡"

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በገብረ እግዚአብሔር ኪደ)
2024/09/29 02:27:20
Back to Top
HTML Embed Code: