Telegram Web Link
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፴


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሠላሳ በዚች ቀን የከበሩ ድናግል ጲስጢስ፡ አላጲስና፡ አጋጲስ በሰማዕትነት ሞቱ፤ የተባረከች እናታቸው ሶፍያም ከአንጾኪያ ከከበሩ ወገኖች ውስጥ ናት።

❖ እነዚህንም ሦስት ልጆች በወለደቻቸው ጊዜ በእሊህ ስሞች ጠራቻቸው ትርጓሜያቸውም ሃይማኖት፡ ተስፋ፡ ፍቅር ነው የራሷም ስም ትርጓሜው ጥበብ ማለት ነው።

❖ ጥቂትም በአደጉ ጊዜ ወደ ሮሜ ከተማ ወስዳ በጎ አምልኮን እግዚአብሔርን መፍራትን የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማረቻቸው በከሀዲውም የሮሜ ንጉሥ በአርያኖስ ዘንድ ወሬያቸው ተሰማ ወደርሱም ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘና አመጡአቸው እናታቸውም በማስተማር ትመክራቸውና ታጸናቸው ነበር፤ እንዲህም ትላቸዋለች ልጆቼ ተጠበቁ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ክብር በማየት ልባችሁ እንዳይደክምና ከዘላለማዊ ክብር እንዳትርቁ ከሙሽራው ከክርስቶስ ጋር ሁናችሁ ወደ ሰማያዊ ሠርግ እንድትገቡ ጠንክሩ፤ ዕድሜያቸውም የታላቂቱ ዐሥራ ሁለት፡ የሁለተኛዪቱ ዐሥር፡ የሦስተኛዪቱ ዘጠኝ ነው።

❖ እናታቸውም ወደ ንጉሥ በአቀረበቻቸው ጊዜ ታላቂቱን ጲስጢስን እኔን ስሚ ከቤተ መንግሥቴ ታላላቆች ለአንዱ አጋባሻለሁ ብዙ ስጦታም እሰጥሻለሁ ለአጵሎን ስገጂ አላት፤ እርሷም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ሰደበች እርሱም ተቆጥቶ በብረት ዘንጎች እንዲደበድቧት ጡቶቿንም እንዲቆርጡ እሳትንም ከብረት ምጣድ በታች በማንደድ ባሩድ ሙጫ ሰሊጥን በውስጡ አድርገው እጅግ አፍልተው ወደዚያ ይጨምሩዋት ዘንድ አዘዘ።

❖ በጨመሩዋትም ጊዜ እየጸለየች በብረት ምጣዱ ውስጥ ቆመች ከቶ እሳት አልነካትም፤ የምጣዱም ግለት ጸጥ ብሎ እንደ ጥዋት ጊዜ ጤዛ ቀዝቃዛ ሆነ ከዚያ ያሉ ሰዎችም አድንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑት ብዙዎችም በክብር ባለቤት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ራሶቻቸውንም ቆረጡዋቸውና በሰማዕትነት ሞቱ።

❖ ከዚህም በኋላ የቅድስት ጲስጢስን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ምስክርነቷንም ፈጽማ የምስክርነት አክሊልን ተቀበለች እናቷም ሥጋዋን አንሥታ ወሰደች፤ ዳግመኛም ሁለተኛዋን አላጲስን አቀረቧትና ደበደቧት ጽኑዕ ግርፋትንም ገረፏት ከጋለ ብረት ምጣድ ውስጥ ጨመርዋት በዚያንም ጊዜ ቀዝቅዞ እንደጥዋት ጤዛ ሆነ ንጉሡም ከዚያም እንዲአወጧትና ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ምስክርነቷንም አድርሳ በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለች እናቷም ሥጋዋን ወሰደች።

❖ ቅድስት ሶፍያም ከሥቃይ የተነሣሳ እንዳትደነግጥ ስለ ልጅዋ ስለ አጋጲስ ትፈራ ነበር ታጽናናትና እንድትታገሥ ታደርጋት ነበር በዚያንም ጊዜ ወስደው ከመንኰራኩር ውስጥ ጨመርዋት እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ ያንን መንኰራኩር ሰበረው እርሷም በደኅና ወጣች ዳግመኛም እሳትን አንድደው ከውስጡ እንዲጥሏት አዘዘ እርሷም ፊቷን በመስቀል ምልክት አማትባ ወደሚነደው እሳት ተወርውራ ገባች በዚያንም ጊዜ እሳቱ እንደ ጥዋት ውርጭ የቀዘቀዘ ሆነ ከዚያ ያሉትም ሰዎች ብርሃን የለበሱ ሁለት ሰዎች ከነጫጭ ልብሶች ጋር ሲጋርድዋት አይተው እጅግ አደነቁ ብዙዎችም በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ራሶቻቸውንም ቆርጠዋቸው በሰማዕትነት ሞቱ ያቺንም የዘጠኝ ዓመት ልጅ የከበረች አጋጲስን ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ምስክርነቷንም ፈጸመች ሁሉም የማያልፍ የማይጠፋ ሰማያዊ መንግሥትን ወረሱ።

❖ የከበረች ሶፍያም የሦስት ልጆቿን ሥጋቸውን ወስዳ ገነዘቻቸው ወደ ከተማውም ውጭ አድርሳ በዚያ ቀበረቻቸው በሦስተኛውም ቀን ወደ መቃብራቸው ሔዳ አለቀሰች ነፍሷንም ይወስድ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነች ልመናዋንም ተቀብሎ ነፍሷን ወሰደ ምእመናን ሰዎችም መጥተው ገንዘው ከልጆቿ ጋር ቀበሩዋት።

❖ በከሀዲው ንጉሥ ላይ ግን እግዚአብሔር ጭንቅ የሆነ ደዌ ላከ ዐይኖቹም ፈረጡ ዐጥንቶቹም እስከሚታዩ ሥጋው ሁሉ ተሠነጣጠቀ እጆቹም ተቆራረጡ ከእርሱም ደምና መግል ፈሰሰ ትልም ይወድቅ ነበር ሁለመናውም ተበላሽቶ በክፉ ሞት ሞተ። ስለ እነዚያ ደናግል ጌታ ተበቅሎታልና።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ዕለት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚናስ አረፈ እርሱ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሰባተኛ ነው። ይህም አባት ብዙ መከራ ደርሶበታል መልካም ተጋድሎውንም ፈጽሞ መንጋዎቹን በመጠበቅ እግዚአብሔርን አገለገለው የሹመቱም ዘመን ዘጠኝ ዓመት ነው በፍቅር በሰላም አረፈ።


ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ዕለት የከበረች ጤቀላ ከእርሷ ጋር ከሚኖሩ አራት ደናግል ጋር ፎላ በሚባል ኃጥእ ቄስ እጅ በሰማዕትነት ሞተች፤ ይህም ፎላ የሚባል ቄስ በዓመፅ የሰበሰበው ብዙ ገንዘብ እንዳለው በከሀዲ መኰንን ዘንድ ነገር ሠሩበት መኰንኑም ገንዘቡን ሁሉ እንዲወርሱት አዘዘ ፎላም ወደ መኰንኑ ሒዶ ገንዘቡን እንዲመልስለት ማለደው፤ መኰንኑም ስለ እነዚህ ደናግል ሰምቶ ወደርሱ እንዲአመጡአቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ፎላን መኰንኑ ለፀሐይ ይሰግዱ ዘንድ እሊህን ደናግል ብትሸነግላቸው ገንዘብህን እመልስልሃለሁ አለው።

❖ ፎላም ሊሸነግላቸው ጀመረ ደናግሉም አንተ የሰይጣን ልጅ የክብር ባለቤት ክርስቶስን እንክደው ዘንድ እንዴት ትፈትነናለህ አንተ ቀድሞ መምህራችን የነበርክ ስትሆን ብለው ዘለፉት፤ መኰንኑም ቃላቸውን በሰማ ጊዜ በጅራፍ እንዲገርፏቸው አዘዘ እነርሱ ግን መናገራቸውን አልተዉም ሥቃይንም አልፈሩም።

❖ መኰንኑም ፎላን የበከተ ብትበላ ደምንም ብትጠጣ ገንዘብህን እመልስልሃለሁ አለው ፎላም እንዳለው አደረገ፤ ዳግመኛም እሊህን ደናግል ብትገድላቸው ገንዘብህን እመልስልሃለሁ አለው በሰማም ጊዜ ልቡናውን አጽንቶ ሊገድላቸው ሔደ እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ልቡ በገንዘብ ፍቅር ተነድፎዋልና።

❖ ደናግሉም እንዲህ አሉት ከሀዲ ሆይ የመድኃኒታችንን ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን በእጅህ ተቀብለን አልነበረምን ስለ ገንዘብ ፍቅር እኛን የክርስቶስን በጎች ታጠፋ ዘንድ እንዴት መጣህ እንዲህም እያሉ ሰልፍ እንደተማረ አርበኛ ሰው በሰይፍ ራሶቻቸውን ቆረጠ።

❖ መኰንኑም የፎላን ብላሽነትና ድንቊርና አይቶ በሰይፍ ገደለው ነፍሱንም ገንዘቡንም ሃይማኖቱንም አጣ፤ የደናግሉም ስማቸው ጤቅላ ማርያ ማርታ አመታ ዓበያ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ቀን ስሙ መርቅያኖስ የሚባል ለጣዖት የሚሰግድ የሮም ንጉሥ ልጅ የከበረች ኦርኒ በሰማዕትነት አረፈች::

📌 በዚችም ዕለት ተገዳይ የሆነ መነኰስ የከበረ አክርስጥሮስ አረፈ፤ ይህም አባት በዮርዳኖስ ገዳም የሚኖር ነበር::
††† እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስ እና ለ150ው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዼጥሮስ ሰማዕት †††

††† የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት:: ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ 5 ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራዕይ ዼጥሮስ ወዻውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት:: በወለደችው ጊዜም በራዕዩ መሠረት "ዼጥሮስ" አለችው::

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተው በሊቀ ዻዻሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ: ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ:: ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ዼጥሮስን የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት::

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር:: ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ: አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር:: ለ14 ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ::

አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው:: ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ዽዽስናው ላይ አልተቀመጠም:: በሁዋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ::

ሕዝቡ "ከእሱ በፊት እኛን ግደሉን" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ዼጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ:: በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ:: ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ:: ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

††† የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. 32:13): በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. 10:41) ይገባል::

††† ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!

††† የካቲት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."150"ቅዱሳን ሊቃውንት ዻዻሳት (በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙበት: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑበት /ጉባዔ ቁስጥንጥንያ/ በ381 ዓ/ም::
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት እነዚህ ይጠቀሳሉ:-
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ
*ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት
*ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም)
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
4.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
5.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. 20:28)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
õ-3 Eñ5 + ¤ ØÈ- è«ru
ASR by NLL APPS
ድርሳነ ቅዱስ ራጉኤል ዘውርሃ የካቲት
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት አንድ(፩)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Daniel:
††† እንኳን ለታላቁ ገዳማዊ አባ ጳውሊ እና ለጻድቁ አባ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ ጳውሊ †††

††† በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ /ዐቢይ/ THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው። አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን።

ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው። በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል። ሕይወቱ በጐላ በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው።

ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል።

ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለአርባ ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል፤ አስተምሯል። በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት።

ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። አኗኗራቸውም በቡድንም በነጠላም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው። ይህም ሲያያዝ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደረሰ። በዚህ ዘመን ግን አባ ጳውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይህንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው። ለሰማንያ ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ። ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ።

ይህ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት። በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ። ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ።

እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል። ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል።

አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ። "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?"
ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ።

"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል። በእርግጥም ከአንተ ሃያ ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ፣ በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ፣ ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኳ የማትመጥነው በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው።" ብሎት ተሠወረው።

ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ። እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ። በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)። በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው። ለሰማንያ ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል። ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ - ሽቻለሁና ላግኝ፤ ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ።

ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው። መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ። ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት።

ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ጳውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር፤ ይመስገን።" ሲል ፈጣሪውን ባረከ። ቅዱስ ጳውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኳን ደህና መጣህ።" አለው። ሁለቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ።

ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት። ለምሳሌ፦
የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ፣
የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣
የመጀመሪያው ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ጳውሊ እና የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን ማንሳት እንችላለን።

ቅዱስ ጳውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ። ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ጴጥሮስን ወልደዋል። ሁለቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው። ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም።

ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ጴጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለጳውሎስ (ጳውሊ) መስጠቱ ነበር። ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ።

ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ጳውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው። በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ። በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል።" ሲል ነገረው።

በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ጳውሊ ሐሳብ ተለወጠ። ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን።" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ። በመቃብር ሥፍራ ለሦስት ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው።

በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት። እየጾመ ይጸልይ ይሰግድ ገባ። ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለሰማንያ ዓመታት ኖረ። (አንዳንድ ምንጮች ግን ለዘጠና ዓመታት ይላሉ።) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በኋላ ነው።

ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ቅዱስ ጳውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል። በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል። ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል። ለሰማንያ ዓመታት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች።

††† ጻድቅ፣ ቡሩክ፣ ቀዳሚው ገዳማዊ፣ መላእክትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ጳውሊ ክብር ይገባል!

††† አባ ለንጊኖስ †††

††† ጻድቁ ከኪልቅያ እስከ ሶርያ ከሶርያ እስከ ግብጽ ድረስ በተጋድሎ የተጓዙ አባት ናቸው። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽም የደብረ ዝጋግ (ግብጽ፤ እስክንድርያ) አበ ምኔት ሆነው አገልግለዋል።

ሙታንን አስነስተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ከድንቅ ነገራቸው ሰይጣን የእርሳቸውን የምንኩስና ቆብ ዐይቶ ደንግጦ መሸሹን እንጠቅሳለን።
"ኀበ ኢኀሎከ ሶበ ቆብዓከ ርዕየ
ሰይጣን ተኃፊሮ እፎኑመ ጐየ።" እንዲል።
(አርኬ)

††† አምላክ በበረከታቸው ይባርከን።
የካቲት ፪ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (የባሕታውያን ሁሉ አባት)
፪.ቅዱስ አባ ለንጊኖስ ሊቀ ምኔት (ደብረ ዝጋግ)
፫.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
††† ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
፫.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ (የሃይማኖት
ጠበቃ)
፬.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ
፭.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፮.አባ ሕርያቆስ ዘሐገረ ብሕንሳ

††† "የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ። ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ። ተፈተኑ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ። ሁሉን እያጡ፣ መከራን እየተቀበሉ፣ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።" †††
(ዕብ ፲፩፥፴፭-፴፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት ሁለት(፪)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"        
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


                  📌  ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፫


           አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ሦስት በዚች ቀን ተጋዳይ የሆነ መነኰስ አባ ያዕቆብ አረፈ።


❖ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ ይህን ዓለም ትቶ መነኰሰና በአንዲት ዋሻ ውስጥ የሚኖር ሆነ ያለ ማቋረጥም በቀንና በሌሊት ሁልጊዜ ይጾማል ይጸልያል በመስገድም ይተጋ ነበር ከበዓቱም ወጥቶ ወደ መንደር አይገባም የሴት ፊትም አያይም እንዲህም ሁኖ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

❖ ከዚህም በኋላ ዲያብሎስን ከሚከተሉት ክፉዎች ሰዎች ውስጥ ምክንያት ፈጥረው አንዲቷን አመንዝራ ሴት ወደርሱ እንድትገባ አደረጓት በገባችም ጊዜ የኃጢአትን ሥራ እያስታወሰች በፊቱ መጫወት ጀመረች ቅዱስ ያዕቆብም ገሠጻት በገሀነም እሳትም ዘላለም ሲቃጠሉ መኖርን አሳሰባት ደንግጣም ንስሓ ገባች እግዚአብሔርንም የምታገለግል ሆነች።

❖ ሰይጣንም መፈታተኑን አልተወውም ከሀገር ታላላቆችም በአንዱ ሰው በሴት ልጁ ላይ አደረ የሚጥላትና የሚያንከባልላት ሆነ ወደ አባ ያዕቆብም ይወስዳት ዘንድ እርሱም ሊያድናት እንደሚችል አሳሰበው አባቷም ወደ አባ ያዕቆብ አደረሳትና በላይዋ ይጸልይ ዘንድ ለመነው እርሱም በላይዋ ሲጸልይ ዳነች አባቷም ያ ሰይጣን እንዳይመለስባት ብሎ ከታናሽ ብላቴና ወንድሟ ጋር ከአባ ያዕቆብ ዘንድ ተዋት።

❖ ከዚህም በኋላ ከእርሷ ጋር በኃጢአት እስከ ጣለው ድረስ እርሷን በማሳሰብ በሌሊትም በቀንም በዝሙት ጦር ሰይጣን ተዋጋው በኃጢአትም በወደቀ ጊዜ ስለ ርሷ እንደይገዱሉት ፈርቶ ኃጢአቱ እንዳይገለጥ ከወንድሟ ጋር ገደላት ሰይጣንም ደግሞ ቀቢጸ ተስፋ በልቡ አሳደረበት ወደ ዓለም ሊሔድ ከበዓቱ ወጣ።

❖ የኃጢአተኛውን ሞት የማይወድ መሐሪ ይቅር ባይ እግዚአብሔርም፤ ጻድቅ የሆነ መነኰስ ወደርሱ ላከ በጐዳናው ሲጓዝ ተገናኘውና ሰላምታ ሰጠው እንዲህም ብሎ ጠየቀው ወንድሜ ሆይ ምን ሁነሃል አዝነህ ተክዘህ አይሃለሁና የደረሰብህስ ምንድን ነው፤ እርሱም የሆነውን ሁሉ ከዚያች ብላቴና ጋር በኃጢአት እንደ ወደቀና ከወንድሟ ጋር እንደገደላት ነገረው፤ ያ ጻድቅ መነኰስም አትፍራ ተስፋም አትቁረጥ እግዚአብሔር መሐሪ ይቅር ባይ ምሕረቱ የበዛ ነውና አለው።

❖ ከዚህም በኋላ የጾም የጸሎት የስግደት ቀኖናን እንዲይዝ አዘዘው፤ እርሱም ተመልሶ ከአንድ ፍርኩታ ውስጥ ገባ በውስጡም ራሱን እሥረኛ አደረገ በታላቅ ድካምና በብዙ ችግርም ላይ ታገሠ በመጾም በመጸለይ አብዝቶ በመስገድም ሁልጊዜ ይተጋል ከምድር የሚበቅል ሥርንም የሚመገብ ሆነ አብዝቶ እያዘነ እግዚአብሔር ይቀበለኝ ይሆን ብዙ በደሌንስ ይተውልኝ ይሆን ይላል እንዲህም በመጸጸት እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ።

❖ እግዚአብሔርም ንስሓውን እንደተቀበለለት ሊገልጥ ወዶ በሀገር ውስጥ ረኃብን አመጣ ለዚያች አገር ኤጲስቆጶስም በፍርኩታ ውስጥ ከሚኖር ከመነኰስ ያዕቆብ ጸሎት በቀር ይህ ረኃብ አያልፍም አለው።

❖ በዚያንም ጊዜ ኤጲስቆጶሱ ከእርሱ ጋር ካህናቱንና የዚያችን አገር ሰዎች ይዞ ተነሣ ወደ ቅዱስ ያዕቆብም ደርሰው ስለ ርሳቸው ይጸልይ ዘንድ ለመኑት እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸውና ዝናምንም እንዲአወርድላቸው አባ ያዕቆብም እኔ እግዚአብሔርን በኃጢአቴ ያሳዘንሁት ኃጢአተኛና በደለኛ ሰው ነኝ አላቸው ኤጲስቆጶሱም ስለርሱ እግዚአብሔር ያለውን ነገረው።

❖ ከዚህም በኋላ ወደ ሕዝብ መካከል ወጣ እያለቀሰ ጸለየ እንዲህም አለ አቤቱ በጌትነትህ ክብር ፊት የረከሰች እፌን እንዴት እገልጣለሁ በኃጢአት ብዛት የጠቆረ ፊቴንስ እንዴት ቀና አደርጋለሁ ነገር ግን እንደ ይቅርታህ ገናናነት እንደ ቸርነትህም ብዛት ሕዝብህን ይቅር በል አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና በዚያንም ጊዜ ብዙ ዝናም ወረደ እርሱም ጸሎቱንና ንስሓውን እግዚአብሔር እንደ ተቀበለው ኃጢአቱንም እንደ ተወለት አወቀ።

❖ ከዚህም በኋላ አስቀድሞ እንደሚሠራው ተግቶ መጸለዩንና መሰገዱን አላጐደለም ነፍሱንም ዳግመኛ በኃጢአት ውስጥ እንዳትወድቂ ተጠበቂ በማለት ይገሥጻት ነበር ከዚህም በኋላ ዕድሜውን አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


🔔 በዚችም ዕለት የባሕታውያን አለቃ ኑሮው የመላእክትን ኑሮ የሚመስል ከትሩፋቱም የሃይማኖት ፍሬ የተገኘ የከበረ አባት ዕብሎይ አረፈ።

                                                                                                                                                  
🔔  በዚችም ቀን የሶርያዊ ቅዱስ ኤፍሬም የሥጋው ፍልሰት ሆነ፤ እንደ ቤተክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ.ም ነው፤ ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ፤ (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም) ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ዽዽስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር::



❖ የሰማዕትነት የሐዋርያነት የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው፤ ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ፤ ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በሁዋላ ሙሉ የጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምህርት ነው፤ የሚገርመው መምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይህንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::



📌 የካቲት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1. ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት በዓለ ፍልሰቱ)

2. ቅዱስ አባ ዕብሎይ ገዳማዊ

3. አባ ያዕቆብ መስተጋድል



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ማርያም

2.ፋኑኤል

3.ቅዱሳን ዘካርያስ ወስምኦን

4.አባ ዜና ማርቆስ ጻድቅ

5.አባ መድኀኒነ እግዚኦ
😭 በመናገሻ ገነተ ጽጌ (በአራዳ) ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመ ነውር 😭

😭 #ጥር_30_ዕለተ_ሐሙስ_ከምሽቱ_6:00 ሰዓት ላይ ያለ ማዘዣና ያለ ዕውቅና ሕግን በተላለፈ መልኩ በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ የየፖሊስና የፌደራል ልብስ የለበሱ ጥይት የታጠቁ አካላት ሰተት ብለው በመግባት ድፍረት የተመላበትን ተግባር ፈጽመዋል።

😭 የዕለቱን የጥበቃ አካላት በማስፈራራትና በመዛት "በቤተክርስቲያኑ ውስጥ መሳሪያ ተቀምጧል" በሚል የዲያቆናትና ካህናትን ቤት ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እየበረገዱ ሕጋዊ የሆኑ (የቤ/ክ ሎጎ ያለባቸውን) ባንዲራዎች እያወረዱ በመውሰድ እንዲሁም በአካባቢው ምዕመናን የተገዙ ከ250 ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የቤ/ክ ሎጎ ያለባቸውን ብዛት ያላቸውን ባንዲራዎች : የታቦት ማሳመሪያ የዲኮር ዕቃዎች በእግር እየረገጡ ክብራቸውን ባዋረደ መልኩ ተወስደዋል።

😭 የፖሊስና የፌደራል አካል ነን ብለው የመጡት አካላት ግቢውን በሚያውክ መልኩ ስለገቡ በጊዜው የነበሩ አካላት ወደ አስተዳዳሪው በመደወል እንዲመጡ ለማደረግ የቻለ ሲሆን የሕግ አካላት ነን ያሉት ግን አስተዳዳሪውን በማዋከብና ለብዙ ዓመታት የቤ/ክ እና የሀገር ቅርስ ያለበትን ሙዚየም ክፈቱ እስከማለት ለመጠየቅ ችለዋል የደብሩ አስተዳዳሪ ግን " ሕዝብና አገልጋዮች በሌሉበት ለዚያውም በዕኩለ ሌሊት አልከፍትም" በማለት አቋማቸውን አሳይተዋል።

😭  ይህ የቤ/ክን እና የምዕመናንን ክብር ባልጠበቀና እንደ ወንጀለኛ በዕኩለ ሌሊት መፈጸሙ ነውር ሆኖ ሳለ በካህናትና ዲያቆናቱ ላይ የተፈጸመው እንግልት ደግሞ እጅጉን አሳፋሪ ነበር በጊዜውም የነበሩ የአይን ምስክሮች እንደነገሩን አንዳንድ ካህና በተፈጸመው አዝነው አምርረው እስከማልቀስ ደርሰዋል።

😭 በቀጣይነትም ዳግም ይህ ነገር ለመፈጸሙ ምንም ዋስትና ስለሌለን የቤ/ክኑ አስተዳደር አካል ፥ የሰ/ት/ቤቱ አመራር ፥ የአካባቢው ወጣትና ምዕመናን በጋራ በመሆን ጉዳዩን በባለቤትነት የፈጸሙት አካላት የወሰዷቸውን ንብረቶች እንዲመልሱና የፈጸሙት የቤተ ክርስቲያንን ክብር የተገዳደረ መሆኑን እስከሚመለከት አካል ሔደው ሊጠይቁ ይገባል።

😭 አሁን ላይ ማንም እየተነሳ መሳሪያ አንግቦ ሕገ መንግሥቱን በተጻረረ መልኩ ቤ/ክ ድረስ ገብቶ የፈለገውን ነገር እያደረገ ነገም ካህናት ብቻ የሚነኩትን ቅዱሱን ታቦትና ንዋየ ቅዱሳቱን ላለመንካቱ ምንም ዋስትና የለንም።

😭 የደብሩ አስተዳደር የሰንበት ት/ቤቱ አመራርና አባላት የአካባቢው ወጣቶችና ምዕመናን በኃላፊነት ከመላው ምዕመን ጋር የተፈጸመውን ተግባር አውግዘን የተወሰዱ ንብረቶች ተመልሰው የተፈጸመውን ተግባር ልንጋፈጥ ይገባናል።

👉 ስለ መናገሻ ገነተ ጽጌ (አራዳ) ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያገባኛል 💒
2024/09/29 22:19:06
Back to Top
HTML Embed Code: