Telegram Web Link
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፲፰

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ አፅሙ ተቃጥሎ ተደቁሶ የተበተነበት ነው።

❖ መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል፤ ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ።
❖ ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው፤ የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል።
❖ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው፤ እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ አሳምኖ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል።
❖ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር፤ በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው፤ እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ።
❖ ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ፤ ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ፤ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል።
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ።
❖ ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል፤ ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል።
❖ ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ "ዝርወተ አጽሙ" ትባላለች፤ በቁሙ "አጥንቱ የተበተነበት" እንደ ማለት ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው፤ ሰባ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ።
❖ በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ፤ ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት፤ ያለ ርኅራኄም አካሉን አሳረሩት፤ ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት፤ በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት።
"ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል።
❖ እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ፤ ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው፤ ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው፤ ሰባው ነገሥታት ግን አፈሩ።
ከሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ያካፍለን፤ በጸሎቱ ይማረን

📌 በዚችም ዕለት በገድል የተጸመደ የከበረ አባት ለቅዱስ ኤፍሬምም መምህሩ የሆነ የሀገረ ንጽቢን ኤጲስቆጶስ አባ ያዕቆብ አረፈ።
❖ ይህም ቅዱስ ተወልዶ ያደገው በንጽቢን ከተማ ነው እርሱ ግን ሶርያዊ ነው ከታናሽነቱም የምንኵስና ልብስ መልበስን መረጠ ከጠጉር የተሠራ ማቅንም ለበሰ በጾሞ በጸሎት ተወስኖ በቀን በሌሊት በበጋ ሐሩር በክረምት ቁር የሚጋደል ሆነ ያንንም ማቅ ከቶ ከሥጋው ላይ አያወጣውም ነበር ምግቡም ቅጠላቅጠል ነው የሚጠጣውም የዝናብ ውኃ ብቻ ነው ስለዚህ ሥጋው ብሩህ ሆነ ነፍሱም እጅግ በራች።

❖ እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢትን ድንቆች ተአምራቶችንም የመስራት ጸጋን ሰጠው ለሰዎችም ከመሆኑ በፊት የሚሆነውን ይነግራቸውና እንዲሁም ይሆናል።

❖ ተአምራቱም እጅግ ብዙ ነው በአንዲትም ቀን ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ ያለማፈር ሲጫወቱና ሲሣለቁ አያቸው የውኃውንም ምንጭ አደረቀ የራሳቸውንም ጠጉር ነጭ ሽበትን አደረገ በተጸጸቱና የውኃውን ምንጭ እንዲመልስላቸው እየሰገዱ በለመኑት ጊዜ የውኃቸውን ምንጭ መለሰላቸው እንዳይታበዩም ይገሠጹ ዘንድ የራሳቸውን ጠጉር ነጭ እንደሆነ ተወው።
❖ በአንዲት ዕለትም በጎዳና አልፎ ሲሔድ አንዱን ሰው እንደሞተ ሰው አስተኝተው ሰዎችን አገኛቸው መገነዣ ልብስም ይሰጣቸው ዘንድ ቅዱሱን ለመኑት እርሱ ግን በጸሎቱ ሰውዬውን ምውት አደረገው ስዎችም ወደርሱ በተሰበሰቡ ጊዜ ሙቶ አገኙት ተጸጽተውም ሁለተኛ ያድንላቸው ዘንድ ለመኑት አዳነላቸውም ።
❖ ትሩፋቱና ደግነቱም በተሰማ ጊዜ መርጠው በሀገር ንጽቢን ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት የክብር ባለቤት የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮሳውያን ተኵላዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ ።

❖ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስም የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ ከተማ በሰበሰባቸው ጊዜ ይህ አባት አብሮ አለ ከእርሳቸውም ጋር አርዮስን አውግዞ ከክርስቲያን አንድነት ለየው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓትና በሁሉ ምእመናን ዘንድ የታወቀች የሃይማኖት ጸሎትን ሠራ።

❖ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስም በደረሰ ጊዜ የሞተውን ሰው በጉባኤው ውስጥ አስነሥቷል፤ የፋርስ ንጉሥም መጥቶ ሀገረ ንጽቢንን በከበባት ጊዜ ይህ ቅዱስ ያዕቆብ የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጣ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ጎበዛዝቶችን ነደፏቸው ፈረሶችም ማሠሪያቸውን ቆርጠው ፈረጠጡ የፋርስ ንጉሥም አይቶ ታላቅ ፍርሀትን ፈራ ተነሥቶም ሸሽቶ ወደኋላው ተመለስ፤ ነፍሱን የመንጋዎቹንም ነፍስ ጽድልት ብርህት አድርጎ ገድሉን በፈጸመ ጊዜ አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በዚችም ዕለት ከአራት ቀኖች በኋላ ጌታችን ከመቃብር ያስነሣው የአልዓዛር እኅቶች የማርያና የማርታ መታሰቢያቸው ሆነ፤ በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ "እንተ ዕፍረት ባለ ሽቱ" ተብለው የሚጠሩ ሁለት እናቶች ነበሩ፤ ሁለቱም ስማቸው "ማርያም" ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን "ማርያም ኃጥዕት ከኃጢአት የተመለሰች" ሁለተኛዋን ደግሞ "ማርያም እኅተ አልዓዛር በቢታንያ የነበረችው" ብለው አበው ይጠሯቸዋል።
❖ በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 12 ቁጥር 1 ላይ ያለችው የአልዓዛር እኅት (ድንግሊቱ) ናት፤ ዛሬ የምናስባት ይህችን እናታችንን ነው።
❖ ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተምርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት፤ ወላጆች ባልነበሩበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።
❖ በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው፤ አልዓዛርን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ማርያምና ማርታን ደግሞ ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል፤ ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር፤ ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ፤ በአራተኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርታ በጌታ ፊት ሰግዳ
👉አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች።
❖ ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ፤ ወዲያውም በሥልጣነ ቃሉ አዝዞ አልዓዛርን አስነሳው፤ ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ ስድስት ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ፤ እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው።
❖ በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የሦስት መቶ ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች፤ መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው።

❖ በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል፤ ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል፤ ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል፤ ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ" ብሎናል።
📚(ቅዳሴ ማርያም)
❖ ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜም ሲቀብሩትም ነበረች፤ ትንሣኤውንም ዐይታለች፤ ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች፤ ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ በዓሏ ከእኅቷ ቅድስት ማርታ ጋር ይከበራል።

የቅዱሳኑ በረከት ረድኤት ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን

📌 ጥር 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ጊዮርጊስ መክብበ ሰማዕታት (ዝርወተ ዓጽሙ)
2.ቅዱሳት ደናግል ማርያ እና ማርታ (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንፅቢን (ከ318ቱ)
4.ቅዱስ ባኮስ ኢትዮዽያዊ (አቤላክ / አቤሜሌክ)



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ
3.አባ አኖሬዎስ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
††† እንኳን ለጻድቅ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን †††

††† በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
*ክርስትና ያበበበት::
*መጻሕፍት የተደረሱበት::
*ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
*ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::

ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ:-
¤አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤አባ ሰላማ ካልዕ::
¤አቡነ ያዕቆብ::
¤ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::

በተጨማሪም:-
¤12ቱ ንቡራነ ዕድ::
¤7ቱ ከዋክብት::
¤47ቱ ከዋክብት::
¤5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ): የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::

ከእነዚህ ቅዱሳን የጻድቁ ፍሬዎች አንዱ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ናቸው:: ጻድቁ አንዳንዴ "አፍቀረነ እግዚእ" እየተባሉም ይጠራሉ:: ትርጉሙም "ጌታ ወደደን" እንደ ማለት ነው::

ያፍቅረነ እግዚእ የነበሩት በ14ኛው መቶ ክ/ዘ ሲሆን ቁጥራቸው ከ7ቱ ከዋክብት ነው:: ጻድቁ ከልጅነት ጀምሮ በሥርዓቱ ከማደጋቸው ባሻገር እጅግ የተማሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል::

ለምናኔ ከወጡ በሁዋላ ከኖሩባቸው ቦታዎችም 3ቱ ተጠቃሽ ናቸው:: የመጀመሪያውና ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ደግሞ ደብረ በንኮል ነው:: ጻድቁ በዚህ ገዳም ከታላቁ ቅዱስ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሥርዓተ ገዳምን : ትኅርምተ አበውን : ተጋድሎተ ቅዱሳንን አጥንተው ለመዓርገ ምንኩስና በቅተዋል::

በገዳሙም ለተወሰነ ጊዜ አገልግለው ወደ ጣና አካባቢ ከአቡነ ያሳይና ከአባ ሳሙኤል ዘዋሊ ጋር መጥተዋል:: የመምጣታቸው ምክንያትም ስብከተ ወንጌልን ለማዳረስና ገዳማትን ለመመሥረት ነው::

ሶስቱ ቅዱሳን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በሁዋላ አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ ደግሞ ማንዳባን አቀኑ:: ያፍቅረነ እግዚእም ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ጣና ውስጥ ገዳም አቅንተው ኑረዋል:: ይህ ገዳማቸው ዛሬም ድረስ በስማቸው ይጠራል::

ጻድቁ አፍቀረነ እግዚእ 3ኛው የሚታወቁበት ገዳም ማኅበረ ዴጌ (ጻድቃነ ዴጌ) ሲሆን ገዳሙ በአክሱም ዙሪያ ይገኛል:: እርሳቸው 3ሺ ቅዱሳን የተሠወሩበትን ገዳም በማገልገላቸውም ዛሬም ድረስ በአካባቢው የታወቁ ሆነዋል::

በተረፈም አክሱም አካባቢ ሌሎች ገዳማትን እንዳቀኑም ይነገርላቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ : በስብከተ ወንጌልና ገዳማትን በማስፋፋት ከኖሩ በሁዋላ በዚህች ቀን ዐርፈው ለክብሩ : ለርስቱ በቅተዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ይቅር ብሎ በረከታቸውን ያሳድርብን::

††† ጥር 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቁ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ (አፍቀረነ እግዚእ ዘጉጉቤ - ጣና ውስጥ - ከሰባቱ ከዋክብት አንዱ)
2.አባ ባሱራ
3.ቅድስት ኔራ
4.ቅድስት በርስጢና
5.አባ ዝሑራ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ታቦታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 አካባቢ ይገኛል)
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† ቅዱሳንን ታስቡ ዘንድ ቸል አትበሉ::

††† "እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:28-31)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፳


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሃያ በዚች ዕለት ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ በሽተኞችንም ይፈውሱ ዘንድ ጌታችን መርጦ ከላካቸው ከሰብዓ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረ ሐዋርያ አብሮኮሮስ አረፈ።


❖ ይህም ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን ከሐዋርያት ጋር ሁኖ ሳለ የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተሞላ፤ እርሱንም ሐዋርያት መርጠውት ከሰባቱ ዲያቆናት ጋር የተቆጠረ ሆነ እነርሱ መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዕውቀትም ያላቸው እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለርሳቸው ምስክር ሆነ።



❖ ከዚህም በኋላ ለወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ከእርሱም ጋር ወደ ብዙ አገሮች ሔደ በቢታንያ አገር በኒቆምድያ ከተማ ላይ በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾመው።

❖ እርሱም የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናናውያንም ብዙዎችን መልሶ ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው የወንጌልንም ትእዛዞች እንዲጠብቁ አስተማራቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠርቶ ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው።



❖ ከዚህም በኋላ ያቺን አገር ወደሚከቧት አገሮች ወጣ በውስጣቸውም የከበረ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎችንም ከስሕተት መለሳቸው አይሁድንም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ነገር ግን ብዙ መከራና ስደት ደርሶበታል ስለ ክርስቶስ ስም ተጋድሎውንም ሲፈጽም ጌታችንንም አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ።



ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


📌 በዚችም ቀን በግብጽ አገር እልፈንት ከሚባል ከተማ የከበረ ቀሲስ አክሎግ በሰማዕትነት ሞተ፤ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ዲዮስቆርስ የናቱ ስም አፎምያ ነው::

📌 በዚችም ዕለት የሰማዕቱ የቅዱስ ብሕኑ መታሰቢያው ነው የወንጌሉ ዘወርቅ ቅዱስ ዮሐንስም ቤተክርስቲያኑ የከበረችበትና ሥጋው ወደ ሮሜ የፈለሰበት ነው፤ ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች "ዮሐንስ" ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው።

❖ የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ በሆነ መንገድ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

❖ ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ፤ ስሙን ዮሐንስ ብለው እንደሚገባም አሳድገው ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት።

❖ ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ፤ ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ የምትፈልገውን ጠይቀኝ፤ ምን ላደርግልህ ትወዳለህ" አለው፤ ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ፤ በወርቅም አስለብጠው" አለው፤ አባትም የተባለውን ፈጸመ።

❖ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም፤ ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል፤ ሲቀመጥም ሲነሳም ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር፤ ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ፤ ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ።

❖ በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል፤ በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው፤ የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር።

❖ አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ፤ ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም፤ አባትህ ያዝንብኛል" አለው፤ ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ።

❖ አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም ይቅርብህ" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ፤ ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ፤ ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ ቆዳውና አካሉም ተገናኘ፤ ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት፤ በእንዲህ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራእይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው።

❖ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሔዶ ቢጠይቀው "ራእዩ ከእግዚአብሔር ነው" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው፤ ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ "እባካችሁ አስጠጉኝ" አላቸው፤ ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም፤ ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት።

❖ በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ፤ በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር።

❖ በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ" አለው፤ እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ" አላት "እሺ" አለችው "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት፤ ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ የወርቅ ወንጌሉን ለዩት፤ ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት፤ እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ" አላቸው።

❖ በዚያች ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ፤ ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ፤ እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው፤ ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች፤ አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው፤ ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል።

በረከቱ ረድኤቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን


📌 በዚችም ዕለት የአባ ኖኅ፣ የአባ ስልዋኖስና፣ የአባ አብድዩ መታሰቢያቸው ነው የሰማዕት መርምህናምም ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበትና ተአምራቱ የተገለጠበት ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።


📌 ጥር 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ (ሰማዕትና ጻድቅ)

2.ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)

3.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ (ቅዳሴ ቤቱ)

4.አባ አብድዩ ጻድቅ

5.ቅዱስ ብሕኑ ሰማዕት
6.ቅዱስ አብሮኮሮስ ሐዋርያ (የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር)

7.አባ ኖሕ



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር

2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት

3.ቅዱስ አሞንዮስ

4.ቅዱስ ካሌብ ንጉሠ ኢትዮዽያ

5.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፳፩


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሃያ አንድ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም የዕረፍቷ በዓል መታሰቢያ ነው።

❖ ያን ጊዜ እመቤታችን በልጅዋ በጌታችን በፈጣሪያችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበረ ከዚህም ዓለም እንደምትለይ መንፈስ ቅዱስ ነገራት ከዚህም በኋላ ከደብረ ዘይት ደናግል መጡ ጌታችን ነግሮዋቸዋልና እርሷም ነገረቻቸው።


❖ በዚያንም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ጸለየች

ልጄ ወዳጄ ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም ሕያዋን እንደሆኑ ሐዋርያትን ሁሉንም ነፍሳቸውንም የለየሃቸውን አምጣቸው አንተ የሕያዋንና የሙታን አምላክ ነህና ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

❖ በዚያንም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ከኤፌሶን አገር ዮሐንስን ደመና ተሽክማ ወደ እመቤታችን ማርያም አደረሰችው ሰገደላትና በፊቷ ቁሞ እንዲህ አላት ሰላምታ ይገባሻል ጌታችንን ፈጣሪያችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሺው ጸጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ አንቺ ከዚህ ዓለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘላለም ሕይወት ትሔጂአለሽና፤ ይህም ስሙ ክቡር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቆች ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኋላ ነው።

❖ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እግዚአብሔርንም እንዲህ ብላ አመሰገነችው ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን አንተ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና አሁንም ነፍሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊአሳርጓት ከሚመጡ መላእከቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ።

❖ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደ ሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ።

❖ ወዲያውኑ ሁሉም ሐዋርያት የሞቱትም ከመቃብራቸው ተነሥተው ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት።

❖ በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠች ሐዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አወቅሁ ከዚህ ከሥጋዬም ወጥቼ ወደዘላለም ሕይወት እሔዳለሁ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ ከዚህም ዓለም እንደምለይ ከወዴት አወቃችሁ ።

❖ ጴጥሮስና ሐዋርያት ሁሉም ወዳንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን በደመና ላይም በተጫን ጊዜ ወዳንቺ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን አሏት።

❖ እመቤታችን ማርያምም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ፤ የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል።

❖ ጸሎቷንና ምስጋናዋን ስትጨርስ ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ።

❖ በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክት አጅበው እያመሰገኑት መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት በዚያንም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተደረጉ ዕውሮች አይተዋልና፣ ሐንካሶች ቀንተው ሔደዋልና ደንቆሮዎች ሰምተዋልና ለምጻሞች ነጹ አጋንንትም ከሰዎች ወጥተው ሔዱ ዲዳዎች ተናገሩ በሽታና ደዌ ያለበት ሁሉ ዳነ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዳለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌያቸው ይፈወሳሉና።

❖ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጅዋን እንዲህ አለችው በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስደነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም እፈራለሁ ጌታችንም ከእርሳቸው ለማንም በአንቺ ላይ ሥልጣን የለውም አላት።

❖ ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኑዋት እጅዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው በዚያንም ጊዜ ጌታችን ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጐናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሐዋርያትን አዘዛቸው።

❖ ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃንን እያየች ነበር የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስም እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋህጄ አስነሥቼ መላእክት በውስጡ በፊትሽ ሁነው በሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ በአለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ አላት።

❖"እመቤታችንም እንዲህ አለች አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ ሁለተኛም ልመናዬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ በስሜ ወዳንተ የሚለምነውን ሁሉ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወዳንተ የሚለምነውን ከመከራው ሁሉ አድነው በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሀሊ ነህና መታሰቢያዬን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል።

❖ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት የለመንሺኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም አይጠፋም።

❖ እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴሴማኒ ሊወስዷት ሐዋርያት ገንዘው ተሸከሟት፤ አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊአቃጥሉ ወጡ ከእርሳቸው አንዱ ከምድር ላይ ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን ዐልጋዋን ያዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በዐልጋዋ ላይ ተንጠለጠሉ።

❖ ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ እለምንሻለሁ በሐዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ ።

❖ በቀበሩዋትም ጊዜ ከዚያ ሦስት ቀን ኖሩ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን በጥር ወር በሃያ አንድ በዚች ቀን ነበረ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩዋት።
❖ ሐዋርያ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲአሳርጓት እመቤታችንን አገኛት መላእክትም ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ና እጅ ንሣ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሩዋትም ነገሩት ቶማስም ሥጋዋን እስከማይ አላምንም አላቸው።

❖ ሥጋዋንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው።

❖ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን ስለ አላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው።

❖ ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ስጣቸው እነርሱም እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በተስፋ ኖሩ።

❖ የእመቤታችንም የዕድሜዋ ዘመን ስልሳ አራት ዓመት ነው በአባትና እናቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተ መቅደስም ዐሥራ ሁለት ዓመት፣ በዮሴፍም ቤት ሠላሳ አራት ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታ ዕርገት በኋላ በወንጌላዊ ዮሐንስ ቤት ዐሥራ አራት ዓመት ነው።

የሕይወት የድኅነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በጸሎቷም ከክፉ ነገር ይጠብቀን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።


📌 ጥር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.በዓለ አስተርዕዮ ማርያም (እመቤታችን ከእረፍቱዋ በሁዋላ ለደቀ መዛሙርት በዚሁ ቀን ተገልጣ ነበር)

2.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (ታላቅ ሊቅና ጻድቅ)

3.ቅድስት ኢላርያ እናታችን (የዘይኑን ንጉሥ ልጅ)

4.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ

5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሰማዕት

7.አባ ፊቅጦር



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.አባ ምዕመነ ድንግል

2.አባ አምደ ሥላሴ

3.አባ አሮን ሶርያዊ

4.አባ መርትያኖስ

5.አበው ጎርጎርዮሳት
††† "ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን::
እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን::
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ::
አንተና የመቅደስህ ታቦት::
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ::
ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው::
ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት. . ."
(መዝ. 131:7)

††† "ወዳጄ ሆይ! ተነሺ::
ውበቴ ሆይ! ነዪ::
በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!
ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና:
መልክሽን አሳዪኝ::
ድምጽሽንም አሰሚኝ::"
(መኃ. 2:13)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/09/29 20:32:41
Back to Top
HTML Embed Code: