Telegram Web Link
+ +  +እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን እና ላለንበት ሀገር ሰላምን ይስጥልን አሜን++

መጽሐፈ ስንክሳር፣
ከዲ/ን ዮርዳኖስ ማስታወሻ
          
+++መልካም ዕለተ ረቡዕ መልካም ቀን+
+++
"ከንቱ ውዳሴ በመንገድ ሁሉ የሚከተልህ የተሸሸገና ጭንብል ያጠለቀ ሌባ ነው። አሳዳጅ በመሆኑ በጣም ደህንነት በሚሰማህ አሳቻ ሰዓት ሳታውቀው ይዘርፈሀል፤ ይገድልህማል። "

ቅዱስ ጎርጎርዮስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፪


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሁለት በዚች ቀን ደሙ በግፍ የፈሰሰ ጻድቁ አቤል አረፈ እርሱም ወንድሙ ቃየል የገደለው የሙታን በኵር የሆነ ነው።


❖ ምክንያቱም አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ እንዳይበላው የታዘዘውን ዕፅ በላ ያን ጊዜ በእርሱና በልጆቹ ላይ ሞት ሠለጠነ ለኃጢአትም ተገዥ ሆነ፤ ሰይጣንም ሰውን ለማሳት ሠለጠነ ከዚህም በኋላ አዳም ከገነት ወጥቶ ወደታችኛዋ ምድር ወረደ ስለ በደሉና የፈጣሪውንም ትእዛዝ በመተላለፉ ፈጽሞ እያዘነና እያለቀሰ መቶ ዓመት ኖረ።


❖ ከዚህም በኋላ አዳም ሔዋንን በግብር አወቃት ፀንሳ ቃየልንና እኅቱን ኤልዩድን ወለደች ሁለተኛም ዐወቃት አቤልንና እኅቱን አቅሌማን ወለደቻቸው አዳምም ሔዋንን እነሆ ልጆችሽ አካለ መጠን አደረሱ ጐለመሱ ቃየል የአቤልን እኅት አቅሌማን ያግባት አቤልም የቃየልን እኅት ኤልዩድን ያግባት አለ።

❖ ቃየልም እናቱን ሔዋንን እንዲህ አላት ለእኔ ከእኔ ጋር የተወለደች እኅቴን ማግባት ይገባኛል አቤልም ከእርሱ ጋር የተወለደች እኅቱን ያግባ ቃየል ከእርሷ ጋር የተወለደ ኤልዮድም እናቷ ሔዋንን የምትመስል እጅግ የምታምር መልከ መልካም ናትና።

❖ አዳምም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ ጭንቅ ሆነበት ቃየልንም አብራህ የተወለደች እኅትህን ታገባት ዘንድ አይገባህም አለዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቅርቡና መሥዋዕቱን ለተቀበለው ይሁን አለው።

❖ መሥዋዕትንም በአቀረቡ ጊዜ የአቤልን መሥዋዕት እግዚአብሔር ተቀበለ የቃየልን ግን አልተቀበለም ስለዚህም ቃየል ፈጽሞ አዘነ ሰይጣንም ተገናኘውና ምን ያሳዝንሃል አለው ቃየልም ለወንድሜ ለአቤል እኅቴን እተውለት ዘንድ አባቴ አዘዘኝ አለው።

❖ ሰይጣንም ምክርን ከኔ ስማ ወንድምህን ወደ ውኃ ምንጭ ይዘኸው ሒድ ውኃንም ሲጣጣ ራሱን በደንጊያ ምታው በሞተ ጊዜ ሁለቱንም ታገባቸዋለህ የሚከለክልህ ማነው አለው ለቃየልም የሰይጣን ምክር ደስ አሰኘው ልቡም በዝሙት እሳትነት ነደደ ሰይጣን እንዳስተማረውም ወንድሙን አቤልን ገደለው ለሴት ስለ መቅናትም ጻድቁ አቤል በወንድሙ እጅ ሞተ እንዲህም ሞት ወደ ዓለም ገባ፤ እግዚአብሔርም ቃየልን ወንድምህ አቤል ወዴት ነው አለው።

❖ ቃየልም አላውቅም በውኑ እኔ የአቤል ጠባቂው ነኝን አለው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው ቃየል ምን አድርገሃል የወንድምህ የአቤል ደም ጩኸት ከምድር ወደኔ ደርሷል፤ አሁንም በእጅህ የፈሰሰውን የወንድምህን ደም ትጠጣ ዘንድ አፍዋን የከፈተች ምድር የተረገመች ትሁን አንተ ታርሳታለህና በረከቷን ትሰጥህ ዘንድ አትጨምርም በምድር ላይ ፈሪ ተቅበዝባዥ ሁን።

❖ ይህም መርገም ዘሩ በጥፋት ውኃ ከምድር ገጽ እስከ ሚደመሰስ በቃየል ላይ የበዛ ሆነ፤ የክብር ባለቤት ጌታችንም ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ሲዘልፋቸው እንዲህ አላቸው ስለዚህ ነቢያትን ሊቃውንትን ጥበበኞችን ወደናንተ እልካለሁ ከነርሱ የምትገድሉት አለ የምትሰቅሉትም አለ በምኵራባችሁ የምትገርፉት አለ ካንድ አገር ወዳንድ አገር ታሳድዷቸዋላችሁ።

❖ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በዓለም የፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርስ ዘንድ።

❖ ጳውሎስም አለ ቃየል ካቀረበው መሥዋዕት ይልቅ አቤል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር ያቀረበው መሥዋዕት ተሻለ ስለ እርሱም ደግ እንደሆነ መሰከረለት መሥዋዕቱንም በመቀበሉ ምስክሩ እግዚአብሔር ነው ደግ እንደሆነም ከሞተ በኋላ ተናገረ።

❖ ከዚህም በኋላ አዳም ልጁን በአጣው ጊዜ ወንድምህ አቤል ወዴት አለ ብሎ ቃየልን ጠየቀው ቃየልም በቁጣ አላውቅም እኔ የአቤል ጠባቂው ነውኝን ብሎ መለሰ አዳምም ልጁን ይፈልግ ዘንድ ወደ ዱር ሮጠ በወንዝ ዳርም በድኑን አገኘና አንገቱን አቅፎ ማን ገደለህ አለው ከበድኑም ወንድሜ ቃየል ገደለኝ የሚል ቃል ወጣ፤ አዳምና ሔዋንም በልጃቸው በአቤል ሞት ሃያ ስምንት ዓመት ያህል ሲያለቅሱ ኖሩ።

❖ ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ አዳም መጥተው የዓለሙ ሁሉ አባቶች አባት አዳም የምሥራች እነሆ ልጅህ አቤል የገነትን ዛፎች ተሳለመ ነፍሱም እንደ ተወደደ መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ዐረገች አሉት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የአባቶቻችንም በረከት ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✍️ በዚችም ቀን የከበረ አባት አላኒቆስ ኤጲስቆጶስ በሰማዕትነት ሞተ እርሱ ጣዖታቱን እንዲአቃልሉ ለሰዎች እንደሚያስተምራቸው ከሀዲው ንጉሥ በሰማ ጊዜ ይዘው ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ።



❖ የንጉሥ መልክተኞች መላካቸውን የተመሰገነ አላኒቆስ ሰምቶ በሀገረ ስበከቱ ያሉትን ሕዝቦች ሰበሰባቸውና የቁርባን ቅዳሴን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው።

❖ ከዚህም በኋላ በቀናች ሃይማኖት ጽኑ ከእንግዲህ ፊቴን አታዩኝም አላቸው፤ እነርሱም አለቀሱ ሊአስተዉትም አልተቻላቸውም ወጥቶም ራሱን ለንጉሥ መልክተኞች አሳልፎ ሰጠ እነርሱም ወስደው ለእንዴናው አገር መኰንን ሰጡት፤ እርሱም ወደ ሀገረ እንድኩ ወስዶ በዚያ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱም በሰለቸው ጊዜ ትከሻውን በሰይፍ ይሠነጥቁ ዘንድ ራሱንም ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ መሞቱን አውቆ አማንያን ከሆኑ መርከበኞች አንዱን እንዲህ ብሎ አዘዘው ወደ ወደቡ ስትደርሱ ሥጋዬን በኮረብታ ላይ አድርግ እርሱም እንዳዘዘው አደረገ።

❖ ከዚህም በኋላ ምእመናን ሰዎች መጥተው ሥጋውን ወስደው ገነዙት የስደቱም ወራት እስቲያልፍ በእነርሱ ዘንድ አኖሩት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተደረጉ።


ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✍️ በዚችም ዕለት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቴዎናስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ስድስተኛ ነው፤ ይህም ቅዱስ አዋቂ ብልህ በቀናች ሃይማኖትም የጸና በሥራው ሁሉ ያማረ ስለ ዕውቀቱም ሰዎች ሁሉ የሚወዱትና የሚሹት ሆነ።

❖ በዚያም ወራት ከሀዲያንን በመፍራት በሥውር ከዋሻ ውስጥ በቀር በግልጥ ሊጸልዩና ሊቀድሱ ለክርስቲያኖች አልተቻላቸውም ነበር ይህም አባት አብያተ ክርስቲያናትን እስከሠሩ ድረስ አግባባቸው በእመቤታችንም በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከከሀዲያንም ብዙዎችን መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃችው።

❖ በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ተፍጻሜተ ሰማዕት የሆነ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስን ያጠመቀው እርሱ ነው፤ በተሾመ በአምስተኛ ዓመቱም አናጒንስጢስነት ሾመው በዐሥራ ሁለተኛም የሹመቱ ዓመት ቅስና ሾመው።

❖ በዚህም አባት ዘመን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ገጽ ነው የሚል ከሀዲ ሰባልዮስ በእስክንድርያ አገር ተነሣ ይህም አባት አውግዞ ለየው የከፋች ሃይማኖቱንም አጠፋት።

❖ ዳግመኛም በዘመኑ ቆዝሞስና ድምያኖስ ወንድሞቻቸው እናታቸው ቴዎዳዳም በሰማዕትነት ሞቱ ይህም አባት ያማረ ጒዞውን በመጓዝ እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።
📌 በዚችም ዕለት በአባ ሲኖዳ ገዳም ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያኗ የከበረችበት ነው በጸሎቷም የተገኘ በረከቷ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።



📌 ጥር 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አቤል ጻድቅ

2.ቅዱስ ቴዎናስ ሊቀ ዻዻሳት

3.ቅዱስ አላኒቆስ ሰማዕት

4.ቅድስት ሳቤላ ነቢዪት

5.ቅዳሴ ቤቷ ለድንግል (በደብረ አባ ሲኖዳ)



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ

2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ

3.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)

4.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)

5.ሊቁ አባ ሕርያቆስ

6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
Daniel:
እንኩዋን ለቅዱሳን "ሕጻናተ ቤተ ልሔም" እና "አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ሕጻናተ ቤተ ልሔም "*+

=>በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች::

+በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14, ሕዝ. 44:1) ተፈትሖም አላገኛትም:: ልማደ አንስትም አልጐበኛትም:: ምጥም አልነበረባትም::

+በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ: የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም: በሁዋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ::

+ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው 12 ነገሥታት በየግላቸው 10 10 ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ::

+12ቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ 9 ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ:: 3ቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከ30ሺ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ::

+እነዚህም መሊኩ የኢትዮዽያ (የሳባ ንጉሥ ተወራጅ): በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው:: ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሔሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ::

+እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በሁዋላ በጐል ድንግል ማርያምን: ክርስቶስን: ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ:: ለ2 ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል: ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ::

+በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ:: "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል:: ወርቁን: እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ:: 3 ጊዜ እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕጻን: በ2ኛው እንደ ወጣት: በ3ኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል::

+ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ሰጠቻቸው:: እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የ2 ዓመቱን መንገድ በ40 ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም:: ተአምራትንም ሠርቷል::

+ሰብአ ሰገል ቅዱስ መልአክ እንደ ነገራቸው በሔሮድስ ዘንድ ሳይሆን በሌላ ጐዳና ተጉዘው ሃገራቸውን መግባታቸውን ንጉሡ ሰማ:: እንደ ዘበቱበት ሲያውቅም የሚያደርገው ጠፍቶበት ወደ ቤቱ ገባ::

+በሕሊናው የሚመላለሰውም አንድ ነገር ብቻ ነበር:: የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን (እርሱስ የሰማይና የምድር ሁሉ ንጉሥ ነው) እንዴት ሊያጠፋው እንደሚችል ያስብ ነበር:: በዚያች ሰዓትም ሰይጣን በሰው ተመስሎ ወደ እርሱ ቀረበ::

+ሕጻኑን እንዴት ሊገድለው እንደሚችል ነግሮት: በዓለም ታይቶ የማይታወቀውን ጭካኔ አስተማረው:: ርጉም ሔሮድስም ሠራዊቱን ጠርቶ "አዋጅ ንገሩልኝ" አላቸው::

+እነርሱም "በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ: በይሁዳም የምትገኙ እናቶች:- አውግስጦስ ቄሣር ሕጻናትን በማርና በወተት አሳድገህ ለሹመት አብቃልኝ: ለእናቶቻቸውም ወርቅና ብር ስጥልኝ ስላለ 2 ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ አምጡ" እያሉ አዋጁን ነገሩ::

+የቤተ ልሔምና የአካባቢዋ እናቶችም ያላቸው አንድም: ሁለትም እየያዙ: የሌላቸው ደግሞ እየተዋሱ ወደ ሔሮድስ ዘንድ ይዘዋቸው መጡ:: ያን ጊዜ አውሬው ሔሮድስ እናቶችን በአንድ ቦታ እንዲታጐሩ አድርጐ ሕጻናቱን በወታደሮቹ አሳፍሶ ወደ ተራራ አወጣቸው::

+በሥፍራውም ተወዳዳሪ በሌለው ጭካኔ 1,200 ወታደሮቹን አሰልፎ ሕጻናቱን አሳረዳቸው:: ሰይፍ የበላቸው የቤተ ልሔም ሕጻናት ቁጥርም 144,000 ሆነ::

+የሕጻናቱ ደም ከተራራው እንደ ጐርፍ ወረደ:: የእናቶች የጡት ወተትም በመሬት ላይ ይፈስ ነበርና ተቀላቀለ:: የቤተ ልሔም እናቶች አንጀታቸው በእጥፉ ተቆረጠ:: ታላቅ ሰቆቃም አካቢውን ሞላው:: ዋይታም ሆነ::

+ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ እንዳለው ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ:: "ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች:: የሉምና መጽናናት አልቻለችም" (ማቴ. 2:18, ኤር. 31:15)

+ሰይጣን ግን አላማው እንዳልተሳካና ድንግልና አምላክ ልጇ መሸሻቸውን ሲያውቅ ይህንኑ ለሔሮድስ ሹክ አለው:: ስለዚህም ንግሥተ አርያም ድንግል ማርያምና ወልደ አምላክ ልጇ በስደት ለ3 ዓመት ከ6 ወር ተንገላቱ::

+እንደ ገናም ክፉ ሰዎች መጥተው ለሔሮድስ አሉት:- "አንተ የምትሻው በዘካርያስ ቤት አለና ግደለው::"
ሔሮድስም ወታደሮቹን ልኮ: ሕጻኑን ቅዱስ ዮሐንስን ቢያጣው ደጉን ነቢይ: አረጋዊ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ መካከል ገድሎታል::

+በጊዜው የሚፈርድ እግዚአብሔርም ስለ ሕጻናቱ ደም ተበቅሎ ሔሮድስን አጠፋው:: ወደ እመቀ እመቃትም አወረደው:: 144 ሺው ንጹሐን ሕጻናት ግን ስልጣነ ሰማይ ተሰጣቸው:: ከእነርሱ በቀር ማንም በማያውቀው ምሥጢርና ዜማ ፈጣሪያቸውን ይሠልሱትና ይቀድሱት ዘንድም አደላቸው:: (ራዕ. 14:1)

+አባ ሕርያቆስ በሐዳፌ ነፍስ ድርሰቱ "ያስምዓነ ቃለ መሰናቁት ዘሕጻናት-የሕጻናትን የመሰንቆ ድምጽ ያሰማን" እንዳለ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+እነዚህ 144 ሺህ ንጹሐን ሕጻናት ዛሬ በሰማይ ለምዕመናን ምሕረትን: ለጨካኞች ፍርድን ይለምናሉ:: በፍርድ ቀንም በጌታ ፊት በክብር ቅንዋቶቹን ይዘው ይመጣሉ::

<< ክብራቸው ታላቅ ነውና ለቅዱሳን ሕጻናት ምስጋና ይሁን !! >>

+*" አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ "*+

=>በሃገራችን እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ቅዱሳን አንዱ አባ ሊባኖስ ናቸው:: እርሳቸው እንደ ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳንና አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ከውጪ ሃገር የመጡ ናቸው::

+የነበሩበት ዘመንም 5ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻና 6ኛው መቶ ክ/ዘመን ውስጥ ነው:: ጻድቁ አባ ሊባኖስን "አባ መጣዕ" እያሉ መጥራት የተለመደ ነው:: "መጣዕ" ማለት ኤርትራ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በተጋድሏቸው የቀደሱት ቦታ ነው:: ጥንተ ታሪካቸውስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+አባ ሊባኖስ ትውልዳቸው ከሮም ታላላቅ ሰዎች ነው:: አባታቸው አብርሃም: እናታቸው ደግሞ ንግሥት ይባላሉ:: በብሥራተ መልአክ ተጸንሰው ስለ ተወለዱ ስማቸውም በዚያው "ሊባኖስ" ተብሏል::

+"ሊባኖስ" እመ ብርሃን የተወለደችበት ቅዱስ ሥፍራ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ "ደጋ" ማለት ነው:: ምሥጢራዊ ትርጉሙ ግን ለጻድቅነት ያገለግላል:: አባ ሊባኖስ በሃገራቸው ሮም ከወላጆቻቸው ጋር አድገው ለአካለ መጠን ሲደርሱ ከወደ ቁስጥንጥንያ ሸጋ ብላቴና አጭተው አጋቧቸው::

+ወጣቱ አባ ሊባኖስ ግን ማታ "ወደ ጫጉላ አልገባም" ብለው እንቢ አሉ:: ለዚያች ሌሊት ብቻ ከአባታቸው ጋር እንዲያድሩ ተፈቀደላቸው:: መጻሕፍትን የተማሩ ነበሩና በሌሊት ምን እንደሚያደርጉ ሲያወጡ: ሲያወርዱ ቅዱስ መልአክ ከሰማይ ወርዶ 3 ጊዜ "ሊባኖስ" ብሎ ጠራቸው::

+"እነሆኝ ጌታየ!" ቢሉት ከአባታቸው ጐን ነጥሎ እያጫወተ ሳይታወቃቸው ከሮም ግብጽ (ገዳመ ዳውናስ) አደረሳቸው::

+በጊዜው ታላቁ ኮከብ ቅዱስ ዻኩሚስ ነበር:: አባ ሊባኖስን አስተምሮ አመነኮሳቸው: በዓትም ለየላቸው:: በዚያ ለተወሰነ ጊዜ እንደቆዩም ቅዱሱ መልአክ መጥቶ "ለዘለዓለም መጠሪያህ በዚያ ነውና ወደ ኢትዮዽያ ሒድ" አላቸው::
+እየመራም ከግብጽ አክሱም አደረሳቸው:: አባ ሊባኖስም በዚያ በዓት ወቅረው ይጸልዩ ጀመር:: ጥቂት ቆይተውም ለስብከተ ወንጌል ተሰማሩ:: በተለይ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በስብከት ከአክሱምሸዋ (ግራርያ) ደርሰዋል::

+ተመልሰው ወደ አክሱም ሔደው: ጸበልን አፍልቀው ነበርና ድውያንን ፈወሱ:: ሙትን አስነሱ:: በዚህ የቀኑት የአካባቢው ሰዎች ግን "ምትሐተኛ ነህ" ብለው አባረሯቸው:: ጻድቁም ዶርቃ በምትባል ቦታ ለ3 ዓመት ሲኖሩ በአክሱም ዝናብ አልዘንብ አለ::

+ጥፋታቸው የገባቸው የአክሱም ካህናት ወደ ጻድቁ ሔደው "ይማሩን" ቢሏቸው ዘንቦላቸዋል:: አባ ሊባኖስ ግን ወደ ሽዋ ተመልሰው በደብረ አስቦ ለመኖር ቢሞክሩ አልተሳካም:: ስሙ የአንተ: ማደሪያነቱ ግን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ነውና ወደ "መጣዕ" ሒድ አላቸው መልአኩ::

+እርሳቸውም ወደ መጣዕ (ኤርትራ) ወርደው ታላቅ ገዳም አነጹ:: ጸበሎችን አፈለቁ:: ብዙ አርድእትንም አፈሩ:: በዚያም በቅድስናና በገቢረ ተአምራት ኑረው ጥር 3 ቀን በ140 ዓመታቸው ዐርፈዋል:: የላሊበላውን ቤተ አባ ሊባኖስን ጨምሮ በርካታ አብያተ መቃድስ በሃገራችን አሏቸው::

=>የሕጻናቱና የጻድቁ አምላክ እኛን ይማረን:: ከበረከታቸውም ያሣትፈን::

=>ጥር 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1."144 ሺ" ቅዱሳን ሕጻናት
2.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
3.አባ አሞን መስተጋድል

=>ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ካህናት (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
7.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ

=>+"+ አየሁም: እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር:: ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም: የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ . . . ደርዳሪዎችም በገና እንደ ሚደረድሩ ያለ ድምጽ ሰማሁ:: በዙፋኑም ፊት: በአራቱም እንስሶችና በሊቃውንቱ ፊት አዲስ ምስጋና አመሰገኑ:: ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም:: ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው:: ድንግሎች ናቸውና:: +"+ (ራዕ. 14:1)

    <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ሦስት(፫)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
+ +  +እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን እና ላለንበት ሀገር ሰላምን ይስጥልን አሜን++

መጽሐፈ ስንክሳር፣
ከዲ/ን ዮርዳኖስ ማስታወሻ
          
+++መልካም ዕለተ አርብ መልካም ቀን+
+++
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ሦስት(፫)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Daniel:
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

++ እንኩዋን ለፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ ሐዋርያ: ወልደ ነጐድጉዋድ ዓመታዊ የፍልሠት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ++

++ ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ ++

=>አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው:: ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል::

+ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው:: ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል::

+ከእርሷ ጋር ለ15 ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

+ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል:: ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ70 ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::

+3 መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::

+" ቅዱሱ በኤፌሶን "+

=>ይህቺ ኤፌሶን የሚሏት ሃገር መገኛዋ በቀድሞው ታናሽ እስያ (አሁን ቱርክ አካባቢ) ሲሆን ብዙ ሐዋርያት አስተምረውባታል:: ያም ሆኖ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያመጣች አልነበረችምና ቅዱስ ዮሐንስ ሊሔድ ተነሳ::

+ከደቀ መዛሙርቱ መካከልም ቅዱስ አብሮኮሮስን (ከ72ቱ አርድእት አንዱ ነው) አስከትሎ እየጸለዩ በመርከብ ላይ ተሳፈሩ:: ሐዋርያት አበው መከረኞች ናቸውና ማዕበል ተነሳባቸው:: በጥቂት አፍታም መርከባቸው በማዕበሉ ተበታተነች::

+ቅዱስ አብሮኮሮስ በስባሪ ላይ ተሳፍሮ ወደ አንዲት ደሴት ደረሰ:: ግን ከንጹሑ መምሕሩ ቅዱስ ዮሐንስ ተለይቷልና አለቀሰ:: ፍቁረ እግዚእ ግን ያለ ምግብና ውሃ ማዕበለ ባሕር እያማታው ለ40 ቀናት ቆየ::

+እርሱ በፈጣሪው ፍቅር የተመሰጠ ነበርና አለመመገቡ አልጐዳውም:: በ40ኛው ቀን ግን ደቀ መዝሙሩ ወዳለበት ደሴት ማዕበሉ አደረሰው:: 2ቱ ቅዱሳን ተፈላልገው ተገናኙ:: እጅግም ደስ ብሏቸው ፈጣሪን አመሰገኑ::

+አምላካቸው ወደዚህች ደሴት ያመጣቸው በጥበቡ ነውና ሲዘዋወሩ 2 ነገርን አስተዋሉ:: 1ኛ የደሴቷ ሁሉም ነዋሪ የሚያመልኩት ጣዖትን ነው:: 2ኛ አብዛኞቹ ልዑላን (የቤተ መንግስት ውላጆች) ናቸው:: ሮምና የሚሏት አንዲት ሴት ደግሞ እነዚህን ሁሉ እየመገበች ታስተዳድራለች::

+ቅዱሳኑ በቦታው በቀጥታ ትምሕርተ ወንጌልን ቢናገሩ እንደ ማይቀበሏቸው ስለ ተረዱ ሌላ ፈሊጥን አሰቡ:: እንዳሰቡትም ወደ እመቤት ሮምና ቤት ሒደው በባርነት ተቀጠሩ::

+ለእርሷም "ድሮ የአባትሽ ባሮች የነበርን ሰዎች ነን" ስላሏት 2ቱን ቅዱሳን እሳት አንዳጅና ገንዳ አጣቢ አደረገቻቸው:: ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ እነዚህ ቅዱሳን የካዱትን ይመልሱ ዘንድ በባርነት ግፍን ተቀበሉ:: የመከር (የማሳመኛ) ጊዜ ሲደርስም አንዳች አጋጣሚ ተፈጠረ::

+ቅዱሳኑ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲገቡ ሰይጣን በውስጥ ኖሮ ደንግጧልና እወጣለሁ ብሎ ሲሮጥ የንጉሡን ልጅ ረግጦ ገደለው:: ሮምናና የአካባቢው ሰዎች ከበው ሲላቀሱ ቅዱሳኑ ቀረቡ::

+ሮምና ግን በቁጣ "ልትሣለቁ ነው የመጣችሁ?" በሚል ቅዱስ ዮሐንስን በጥፊ መታችው:: መላእክት እንኩዋ ቀና ብለው ሊያዩት የሚከብዳቸው ሐዋርያ ይህንን ታገሰ:: በጥፊ ወደ መታችው ሴት ቀረብ ብሎም "አትዘኚ! ልጁ ይነሳል" አላትና ጸለየ::

+ወደ ሞተውም ቀረብ ብሎ በጌታችን ስም አስነሳው:: በዚህ ጊዜም ሮምናን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ለቅዱስ ዮሐንስ ሰገዱ:: እርሱ ግን ሁሉንም አስነስቶ ትምሕርተ ሃይማኖትን: ፍቅረ ክርስቶስን ሰበከላቸው::

+በስመ ሥላሴ አጥምቆ: ካህናትን ሹሞ: ቤተ ክርስቲያንም አንጾላቸው ወጥቷል:: በሁዋላም ለሮምናና ለደሴቷ ሰዎች ክታብ (መልዕክትን) ጽፎላቸዋል:: ይህች መልዕክት ዛሬ 2ኛዋ የዮሐንስ መልዕክት ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትታወቃለች::

+ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ የተጉዋዘው ወደ ኤፌሶን ነው:: በዚህች ከተማ የምትመለክ አርጤምስ (አርጢሞስ) የሚሏት ጣዖት ነበረች:: አርጤምስ ማለት መልክ የነበራት ትዕቢተኛ ሴት ስትሆን አስማተኛ ባሏ ነው እንድትመለክ ያደረጋት::

+ቅዱስ ዻውሎስ ብዙ ምዕመናን ከእርሷ እንዲርቁ ማድረግ ችሏል:: ጨርሶ ያጠፋት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ነው:: በቦታውም ብዙ ግፍ ደርሶበት: በርካታ ተአምራትን አድርጉዋል:: ቤተ ጣዖቱንም በተአምራት አፍርሶታል::

+" የፍቅር ሐዋርያ "+

=>ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን 'የፍቅር ሐዋርያ' ትለዋለች:: ለ70 ዘመናት በቆየ ስብከቱ ስለ ፍቅር ብዙ አስተምሯል:: ፍቅርንም በተግባር አስተምሯል:: በየደቂቃውም "ደቂቅየ ተፋቀሩ በበይናቲክሙ - ልጆቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ" እያለ ይሰብክ ነበር::

+በተለይ ደግሞ ከፈጣሪው ክርስቶስ ጋር የነበረው ፍቅር ፍጹም የተለየ ነበር:: በዚህ ምክንያትም ጌታ ባረገ ጊዜ እንዲህ ብሎታል:- "ለፍጡር ከሚገለጥ ምሥጢር ከአንተ የምሠውረው የለኝም" ብሎታል::

+ቀጥሎም በንጹሕ አፉ ስሞታል:: ሊቁ:-
"ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዓሞ:
ንጽሐ ኅሊናሁ ወልቡ ለዐይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ" እንዳለው:: (መልክዐ ኢየሱስ)

=>ቅዱስ ዮሐንስ ከእመቤታችንም ጋር ልዩ ፍቅር ነበረው:: እርሷ እንደ ልጇ ስትወደው: እርሱ ደግሞ እንደ እናቱ ልቡ እስኪነድ ድረስ ይወዳት ነበር:: እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎ ያገኛት እመቤቱ ናትና::

+ከዚያ ሁሉ ጸጋና ማዕረግ የመድረሱ ምሥጢርም ድንግል ናት:: ለ15 ዓመታት በጽላሎተ ረድኤቷ (በረዳትነቷ ጥላ) ተደግፎ አብሯት ሲኖር ብዙ ተምሯል:: ከመላእክትም በላይ ከብሯል:: ከንጽሕናዋ በረከትም ተካፍሏል::

+ስለ ድንግል ማርያምም "ነገረ ማርያም" የሚል ድርሰት ሲኖረው "የሰኔ ጐልጐታንም" የጻፈው እርሱ ነው::

+ድንግል ባረፈችበት ቀንም ልክ እንደ ልጇ ክርስቶስ እርሷም ስማው: ታቅፋው ዐርፋለች:: ሊቃውንቱ ለዚህ አይደል በንጹሕ ከንፈሮቿ መሳምን (መባረክን) ሲሹ:-
"በከመ ሰዓምኪ ርዕሰ ዮሐንስ ቀዳሚ:
ስዒሞትየ ማርያም ድግሚ" ያሉት::

+ታላቁ ቅዱስ ሐዋርያ ዕድሜው 90 ዓመት በሆነው ጊዜ በዚህች ዕለት ተሰውሯል:: ከዚያ አስቀድሞም የዓለምን ፍጻሜ ተመልክቷል:: ዛሬ ያለበትን የየሚያውቅ ቸር ፈጣሪው ነው::

=>እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው:-
*ወንጌላዊ
*ሐዋርያ
*ሰማዕት ዘእንበለ ደም
*አቡቀለምሲስ (ምሥጢራትን ያየ)
*ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
*ወልደ ነጐድጉዋድ
*ደቀ መለኮት ወምሥጢር
*ፍቁረ እግዚእ
*ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
*ቁጹረ ገጽ
*ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
*ንስር ሠራሪ*ልዑለ ስብከት
*ምድራዊው መልዐክ
*ዓምደ ብርሐን
*ሐዋርያ ትንቢት
*ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
*ኮከበ ከዋክብት

=>በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር::

=>ቅዱስ ዮሐንስን የወደደ ጌታ በፍቅሩ ይጠግነን:: ከእናቱ ፍቅር አድርሶ በሐዋርያው በረከት ያስጊጠን::

=>ጥር 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ
(ፍቁረ እግዚእ)
2.አባ ናርዶስ ጻድቅ (ዘደብረ ቢዘን)
3.ቅዱስ ጊዮርጊስ
4.ቅዱስ ማርቴና

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

=>+"+ በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ: የእናቱም እህት: የቀለዮዻም ሚስት ማርያም: መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር:: ጌታ ኢየሱስም እናቱን: ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ' አላት:: ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነሁዋት' አለው:: ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት:: +"+ (ዮሐ. 19:25)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር አራት(፬)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
2024/09/30 14:22:33
Back to Top
HTML Embed Code: