Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊                       †                           🕊

               
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ !



ኦ ! በመስቀልህ የተበላሸውን ዓለም ያሳመርከው !

                            🕊                   

" ኦ ! በመስቀልህ በቀኝ የተሰቀለውን ሽፍታ አንተን ወደ ማመን የመለስከው ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት አስቀድሞ መግባትንም የሰጠኸው ሆይ ፣ እኔንም ወደ ቅዱሳን የደስታቸው አዳራሽ አግባኝ ፤

ኦ ! በመስቀልህ በጎችህን የሰቡ እንዲሆኑ ያደረግካቸው ፣ በደምህም ነጠብጣብ ያተምካቸው ሆይ ፣ ለእኔም ሕይወት ሰጭ የሆነውን መስቀልህን ስጠኝ ፣ ያንተን ማኅተም ተሸክሜ በጠላት ላይ እበረታታበት ዘንድ ፤

ኦ ! በመስቀልህ የእሳትን ጦር ከሱራፌል እጅ ፣ የሚያስደነግጠውንም ሰይፍ ከሱራፌል እጅ ያስወገድህ ፣ አዳምንም ወደ ወጣበት ወደ ገነት ዐጸድ ይገባ ዘንድ ያበቃኸው ሆይ ፣ እኔንም ወደ ቅዱሳን ርስታቸው እንድገባ አብቃኝ ፣እኔ አገል ጋይህ ነኝና ፤

ኦ ! በመስቀልህ የተበላሸውን ዓለም ያሳመርከው ፣ የአረጀውንም ዓለም ያደስከው ፣ ያደፈውንም ዓለም የቀደስከው ሆይ ፣ የእኔንም ነፍሴንና ሥጋዬን አድስ ፤

ኦ ! በመስቀልህ በተቀደሰው ቀኝህ የተተከለችውን የወይንህን ተክል እንድታፈራ ያደረግካት ፣ አማንያንንም እንድታፈራ ያበቃሃት ሆይ ፣ እኔ ባርያህም የሃይማኖትን አበባ እንዳብብ ፣ የንስሐንም ፍሬ እንዳፈራ አብቃኝ ፤ "

               
🕊   { ውዳሴ መስቀል }   🕊


🕊 እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሰን 🕊 † 


🌼    --------------- † ---------------    🌼
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ 

[  ✞  🌼  እንኩዋን ለብርሃነ መስቀሉ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  🌼 ✞  ]


🕊  ✞ ቅዱስ ዕፀ መስቀል ✞  🕊

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ ከግራ ቁመት:
¤ ከገሃነመ እሳት:
¤ ከሰይጣን ባርነት:
¤ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

" እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ " እንዳለ ሊቁ::

ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት::

እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት [ዘፍ.፬፥፲፭]  ጀምሮ

¤ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት [ዘፍ.፳፪፥፮]
¤ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል [ዘፍ.፳፰፥፲፪]
¤ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ [ዘፍ.፵፰፥፲፬]
¤ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ_በትር [ዘጸ.፲፬፥፲፭]
¤ የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት [ዘኁ.፳፩፥፰]  ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: [መዝ.፶፱፥፬]

በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም: መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

ቅዱስ_ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: [፩ቆሮ.፩፥፲፰  ገላ.፮፥፲፬]

አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::


†  🕊   በዓለ መስቀል  🕊  †

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም::

መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ፪፻፸ ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ [ሔለና] በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች::

መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት ፲ ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ፲ ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም ፲፯ ቀን ተቀድሷል::

ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ [ግሸን ማርያም] ተለብጦ ተቀምጧል::


†  🕊 ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ  🕊 † 

ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ [ሰማርያዊ] ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ ጐልጐታ ነን" አሉት::

እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::


†  🕊  ቅድስት ታኦግንስጣ  🕊   †

በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

🕊

[  †  መስከረም ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፪. ቅድስት እሌኒ ንግስት
፫. ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
፬. ቅዱስ መቃርስ ሊቀ ዻዻስ
፭. ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ
፮. ብጽዕት ታኦግንስጣ ሮማዊት
፯. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ቀዳሜ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ ዘብዴዎስ]
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ
፯. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ [ዘደሴተ ቆዽሮስ]

" የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: " [፩ቆሮ.፩፥፲፰-፳፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from M.A
ንግሥት እሌኒን እናወድሳት ዘንድ ይገባል፡፡ ክብር የሚገባውን የአምላካችንን የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኝ እንደሆነ ብላ በእምነት ለመፈለግ ተግታለችና፡፡

የጌታችን መስቀል ቅዱስ ስጋው የተቆረሰበት ክቡር ደሙ የፈሰሰበት ከሁሉ የተለየ ከሁሉ የተቀደሰ ሁሉንም የሚቀድስ እንደሆነ አስቀድማ ተገንዝባለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል፡፡

ንግሥትነቷን በዓለማዊ ቅምጥልናና ምቾት ታሳልፈው ዘንድ አልወደደችም፤ ይልቁንስ የተወደደውን መስቀል ትፈልግ ዘንድ በመንፈስ ብርቱ ሆና በስጋ ደከማለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

እጅግ የከበረውን መስቀል ትፈልግ ዘንድ ስትጀምር በራሷ መታመን አልታበየችም ይልቁንስ ሁሉን ስለክርስቶስ ትቶ የወጣ ባህታዊ ኪራኮስን ታማክር ዘንድ ወዳለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

በተዋህዶ የከበረ የአብ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ይዞ እንዳላስቀረው ሞትንም ድል አድርጎ እንደተነሳ ሁሉ ክቡር መስቀሉም ተቀብሮ ለዘላለም እንደማይኖርና ከተቀበረበትም እንደሚወጣ አምናለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

ከጌታችን መስቀል ጋር የተቀበሩት መስቀሎች ብዙ ናቸው የጌታየን እንዴት እለየዋለሁ? ብላ ሳትጨነቅ የክርስቶስ መስቀል ክብሩን ራሱ እንደሚገልፅ በልቧ ተማምና እስክታገኝው ደክማለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል፡፡
2024/09/27 18:12:16
Back to Top
HTML Embed Code: