Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ኢትዮጵያ ከመላእክት ጋር የሚዘምር ማሕሌታዊ ከካህናተ ሰማይ ጋር የሚያጥን ካህን የምታፈራ ሀገር ናት። ለሰማይ አገልጋዮችን ገና ሳይሞቱ የምትልክ፣ ከተዋጊዎች መካከል ወደ ድል ነሺዎች መልእክተኛ የምትልክ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለች ናት?

ቅዱስ ያሬድ በትሕትናው ከትል ተማረ። ትሑታንን ከፍ የሚያደርግ ፈጣሪም ከፍ አደረገውና ከመላእክት ጋር ዘመረ። ትልዋን ከዛፍ አውርዶ ቢጨፈልቃት ኖሮ ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ያልነጠፈው የምስጋና ጅረት በሀገራችን ባልፈሰሰ ነበር። ኃይል አለኝ ብለህ የምትጨፈልቃቸው ትሎች ሰማይ የሚያደርሱህ መምህራኖችህ እንዳይሆኑ ተጠንቀቅ ይላል የታሪኩ ተግሣፅ።

ቅዱስ ያሬድ እግሩን በጦር እየተወጋ እንኩዋን ዝማሬው ሰማያት ወስዶት አልተሰማውም ነበር። የእኛው ሲላስ የእኛው ጳውሎስ ቅዱስ ያሬድ ሆይ በዘመርክባት ሀገርህ ዛሬ ብዙ ጦር ተሰክቶባታል። ከአንተ ዜማ በቀር ዛሬም መጽናኛ የለንምና በምልጃህ አስበን።

ጥዑመ ልሳን ያሬድ: ሊቀ ጠበብት ያሬድ: ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ!!

(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት እና ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


† 🕊 ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት 🕊 †

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እንዲያውም ለዘመነ ሰማዕታት መሪና አስተማሪ እርሱ ነበር::
እስኪ በጥቂቱ ነገሩን ከሥሩ እንመልከተው::
በ፫ ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ: ገላውዴዎስ: ፊቅጦር: መቃርስ: አባዲር: ቴዎድሮስ [፫ቱም]: አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ::

ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ :- ማርታ: ሶፍያ: ኢራኢ: ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ /ሞተ/::

የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ::

በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪዻዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪዻዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው::

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች::

ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ :- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ::

ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ::

አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ-ቤተክርስቲያኖች ይዘጉ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ:: አዽሎን: አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ::

በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ::
- ምድር በደም ታጠበች::
- ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ::
- እኩሉ ተገደለ: እኩሉ ተቃጠለ: እኩሉ ታሠረ: እኩሉም ተሰደደ:: በዚህ ጊዜ 'መራሔ ትሩፋት' ቅዱስ ፋሲለደስ ለሰማዕትነት ይበቁ ዘንድ ስለ ራሱና ስለ ወገኖቹ ጸለየ::
ቅዱስ ሚካኤልም በግርማ ወርዶ ቅዱሱን ወደ ሰማይ አወጣው:: ከቅዱሳን ጋር በገነት አስተዋውቆት: ክብረ ሰማዕታትን አሳይቶት: ከጌታ ዘንድ አስባርኮት: ከሕይወት ውሃ ምንጭም አጥምቆ መለሰው::ቅዱስ ፋሲለደስም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ በንጉሡ ፊት ቆመ::

ንጉሡ ፈራ እርሱ ግን በፈጣሪው ስም መሞት እንደሚፈልግ ነገረው:: ሊያባብለው ሞከረ አልተሳካም እንጂ:: ከዚያም አስሮ ወደ አፍራቅያ [አፍሪካ] ላከው:: መጽሩስ የሚባል መኮንንም ቅዱሱን አሰቃየው::

እርሱ የሁሉ የበላይ ሲሆን ስለ ክርስቶስ ሁሉን ተወ:: አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት በምጣድ ላይ ጠበሱት: አበራዩት በወፍጮም ፈጩት:: እርሱ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ሁሉን ታገሰ:: ሁለት ጊዜ ገድለውት ከሞት ተነሳ:: በተአምራቱ ምክንያትም ከከተማው ሕዝብ ግማሹ ያህል ከአሕዛባዊነት ተመልሶ ሰማዕት ሆነ::

በመጨረሻም በዚህ ዕለት አንገቱን ሲቆርጡት ደምና ወተት ፈሶታል:: መላእክትም እርሱን ለመቀበል ዐየሩን ሞልተውታል:: ከልዑላኑ ወገንም የቅዱስ ፋሲለደስን ሚስትና ልጆችንጨምሮ አንድም የተረፈ የለም:: ሁሉም በሰማዕትነት አልፈዋል::

† 🕊 እናታችን ቅድስት ታኦድራ 🕊

ይህች ቅድስት እናታችን የትእግስት እመቤት ናት:: ትእግስቷ: ደግነቷ ፈጽሞ ይደነቃል:: ታሪኳ ደግሞ በሆነ መንገድ ከቅድስት እንባ መሪና ጋር ይገናኛል::

ቅድስት ታኦድራ ግብጻዊት ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በእስክንድርያ ነው:: ከሕጻንነቷ ጀምራ ቅን ነበረች:: ምንም እንኳ የምናኔ ሰው ብትሆንም ወላጆቿ ያመጡላትን ባል 'እሺ' ብላ አገባች:: ለተወሰነ ጊዜም በሥጋ ወደሙ ተወስነው ከባሏ ጋር በሥርዓቱ ኖሩ::

ለቤተ ክርስቲያን ከነበራት ፍቅር የተነሳ ጠዋት ማታ ትገሰግስ ነበር:: አንድ ቀን ግን መንገድ ላይ የሆነ ፈተና ጠበቃት::ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በመልኳ ምክንያት ለኃጢአት ተግባር ይፈልጋት የነበረ አንድ ጐረምሳ ድንገት ያዛት:: ታገለችው: ግን ከአቅሟ በላይ ነበር:: ጮኸች የሚሰማትም አልነበረም:: ሰውየው የሚፈልገውን ፈጽሞ: ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ይህንን መቻል ለአንዲት ንጽሕት ወጣት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ መረዳቱ አይከብድም::

እጅግ መጥፎ ሰው በቀለኛም ለመሆን ከዚህ በላይ ምክንያት አይኖርም:: ቅድስቷ ግን ከወደቀችበት ተነስታ መሪር እንባን አለቀሰች:: ሕመሟን ችላ ወደ ቤቷ ላትመለስ ወደ በርሃ ተጓዘች:: ወደ ገዳም ገብታ በወንድ ስም 'አባ ቴዎድሮስ' ተብላ መነኮሰች:: በአካባቢው የሴቶች ገዳም አልነበረም::

የሚገርመው በገዳም ውስጥ ሆና ያንን ጨካኝ ሰው ይቅር አለችው:: ቀጥላም ስለ እርሱ ኃጢአት ንስሃን ወስዳ ከባዱን ቀኖና ተሸከመችለት:: ይሔ ነው እንግዲህ ሕይወተ ቅዱሳን ማለት: ራስን አሳልፎ ለጠላት መስጠት:: [ዮሐ.፲፭፥፲፫] ፈተናዋ ግን ቀጠለ::

ወንድ መስለዋት 'በአካባቢው ከምትገኝ ሴት ጸንሰሻል' ብለው ከገዳም አባረሯት:: ያልወለደቺውንም ልጅ ታሳድግ ዘንድ ሰጧት:: አሁንም በአኮቴት ተቀብላ ለ፯ ዓመታት በደረቅ በርሃ ተሰቃየች:: ልጁንም አሳደገች:: ከዚያም ከባድ ንስሃ ሰጥተው ተቀበሏት:: ቅድስት ታኦድራ እንዲህ ስትጋደል ኑራ በዚህች ቀን ዐርፋለች:: በዕረፍቷም ቀን ክብሯ ተገልጧል::

† ቸር አምላክ የቅዱሳኑን ትእግስትና መንኖ ጥሪት አይንሳን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[ † መስከረም ፲፩ [ 11 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፪. ቅድስት ታኦድራ እናታችን
፫. ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ሐዋርያዊ [ሐዋ.፲ን] ያንብቡ]
፬. ቅድስት በነፍዝዝ ሰማዕት
፭. ፫ "3ቱ" ገበሬዎች ሰማዕታት [ሱርስ: አጤኬዎስና መስተሐድራ]

† " ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን:: " † [ሮሜ. ፰፥፴፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለቅዱሳን አባቶቻችን ሊቃውንት ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†   🕊   ጉባኤ ኤፌሶን    🕊   †      

† ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ያከበሩትን: እርሱም ያከበራቸውን ሰዎች 'ቅዱሳን' ትላለች:: ራሱ ባለቤቱ "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ-እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" ብሏልና:: [ዼጥ.፩፥፲፭] (1:15) እነዚህንም ቅዱሳን 'መላእክት: አበወ ብሊት: ነቢያት: ሐዋርያት: ሰማዕታት: ጻድቃን: ሊቃውንት: ደናግል: መነኮሳት: ባሕታውያን' ወዘተ. ብለን: ክፍለ ዘመን ሰጥተን በአበው ሥርዓት እናስባለን::

ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም አንዱንና ትልቁን ቦታ ቅዱሳን ሊቃውንት ይወስዳሉ:: 'ሊቅ' ማለት 'ምሑር: የተማረ: ያመሰጠረ: ያራቀቀ: የተፈላሰፈ: በእውቀቱ የበለጠ: የበላይ: መሪ: ሹም: ዳኛ' . . . ወዘተ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል::

ወንጌል ላይም ጌታችን መድኃኔ ዓለም ኒቆዲሞስን "አንተ ሊቆሙ ለእሥራኤል-አንተ የእሥራኤል መምሕር (አለቃ) ነህ" ብሎታል:: [ዮሐ.፫፥፲] (3:10) ስለዚህም 'ሊቃውንት' ማለት በእውቀት ከሁሉ በላይ የሆኑ እንደ ማለት ነው::

ዘመነ ሊቃውንት ተብሎ የሚታወቀው ከ3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ ፮ [6] ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን እንደ እንቁ ያበሩ: ብርሃንነታቸው በሰው ፊት የበራ ብዙ አበው ተነስተዋል:: ቅዱሳን ሊቃውንት ከሌሎች ምሑራን ቢያንስ በእነዚህ ነገሮች ይለያሉ :-

፩. እንደ ማንኛውም ሰው ከተማሩ በኋላ እውቀቱ ይባረክላቸው ዘንድ ጠዋት ማታ በጾምና በጸሎት ይጋደላሉ::
፪. አብዛኞቹ ቅዱሳን ሊቃውንት ገዳማዊ ሕይወትን ጠንቅቀው ያውቃሉ::
፫. ምሥጢር ቢሰወርባቸው ሱባኤ ይገባሉ እንጂ በደማዊ ጭንቅላት አይፈላሰፉም::
፬. ፍጹም መናንያን በመሆናቸው ሃብተ መንፈስ ቅዱስ እንጂ የሚቀይሩት ልብስ እንኳ የላቸውም::
፭. እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቃል ከማስተማራቸው በፊት በተግባር ይኖሯታል::
፮. እረኞች ናቸውና ዘወትር ለመንጋው ይራራሉ::
፯. ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ግፍን ተቀብለዋል::
፰. በኃይለ አጋንንት የመጡ መናፍቃንን ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ለብሰው: መጻሕፍትን አልበው: ጥቅስ ጠቅሰው መክተዋል::
፱. ምግብናቸውንም ፈጽመው ዛሬ በገነት ሐሴትን ያደርጋሉ::

† የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምትቀበላቸው የቅዱሳን ጉባኤያት ፫ [3] ብቻ ናቸው::

፩ኛ. በ፫፻፳፭ [325] (፫፻፲፰ 318) ዓ/ም በኒቅያ ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት ያደረጉትን
፪ኛ. በ፫፻፲፰ [381] (፫፻፸፫ 373) ዓ/ም በቁስጥንጥንያ ፻፶ [150] ው ሊቃውንት ያደረጉትን: እንዲሁም
፫ኛ. በ፬፻፴፩ [431] (፬፻፳፬ 424) ዓ/ም በዚህች ቀን ፪፻ 200ው ሊቃውንት ያደረጓቸውን ጉባኤያት ትቀበላለች::
ይሕስ እንደ ምን ነውቢሉ :-
በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው:: ትምሕርቱ ክርስቶስን 2 አካል: ባሕርይ ነው [ሎቱ ስብሐት!] የሚል ነበር:: በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር:: ምክንያቱም ጌታችንን ወደ ፪ [2] የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው:: [ላቲ ስብሐት]

ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም:: በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ [የቁስጥንጥንያ ንጉሥ] ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ::

ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው:: በ፬፻፴፩ [431] ዓ/ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ፪፻ [200] ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ::

የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ:: አፈ ጉባዔው ሊቀ ማሕበር ማር [ቅዱስ] ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው:: ምላሽም አሳጣው:: ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን: ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ: በምሳሌም እያሳየ አስረዳ::

የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ: አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ:: ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት 12 አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ:: እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ:: ይነበባሉ: ይተረጎማሉ::

ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ [የእግዚአብሔር እናቱ] ናት" የሚል ነው:: እመቤታችንን የአምላክ እናት: ዘላለማዊት ድንግል: ፍጽምት: ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና::

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን:: እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው:: ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ" ብሎ ረገመው:: ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ::

እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሂዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች::

† አምላከ ሊቃውንት ዛሬም ያሉንን አባቶች ይጠብቅልን: ያንቃልን:: ከቅዱሳን ሊቃውንት በረከትም አይለየን:: የእመ ብርሃን ፍቅሯንም ያሳድርብን::

🕊

[  †  መስከረም ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱሳን ፪፻ [200] ው ሊቃውንት [በኤፌሶን የተሰበሰቡ]
፪. ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት
፫. ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ
፬. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
፭. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፮. ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ

[    †  ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፫. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፭. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፮. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ሰማዕት]
፯. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፰. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

† " ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" † [ሐዋ. ፳፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ዓመታዊ የተዓምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

"በዛቲ ዕለት እግዚአብሔር ገብረ : በእደ ባስልዮስ መንክረ::"
[በዚህች ዕለት እግዚአብሔር በባስልዮስ እጅ ድንቅን አደረገ]


† 🕊 ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ  🕊

† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ አርእስተ ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ [ባስልዮስ የሚሉ አሉ] : እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው ፭  ወንድና ፩ ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ [ቅድስት ማቅሪና] ገዳማዊት ስትሆን ፭ ቱም ወንዶች ዻዻሳት መሆናቸው ነው::

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::

†  🕊 ቅዱስ ባስልዮስ  🕊  † 

ገዳማዊ ጻድቅ: ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ: የብዙ ምዕመናን አባት: የቂሣርያ ሊቀ ዻዻሳት: ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት [ከፍጹምነት] የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ፬ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው::

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::

በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ [በዘመኑ አጠራር ባሪያ] ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ [መተተኛ] ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት ፮ ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::

ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::

በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ " ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን?" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ፵ ቀን በሁዋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ፬ አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ፫ ቀን በሁዋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ፫ ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::

በ፮ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ፱ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::

እንዲህ በ፫: በ፫ ቀናት እየተመላለሰ ለ፲፫ ጊዜ ጠየቀው:: በ፴፱  ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ፵ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ያን ሰው ከመሃል አቁሞ "እግዚኦ በሉ" አላቸው::

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ፵ ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር ፮  ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[ † መስከረም ፲፫ [ 13 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፪. አባ ይስሐቅ ባሕታዊ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. እግዚአብሔር አብ
፪. ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
፫. ፻፱ "99ኙ" ነገደ መላዕክት
፬. ቅዱስ አስከናፍር
፭. "13ቱ" ግኁሳን አባቶች
፮. ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯. አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

† " እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል:: እኔ ወደ አብ እሔዳለሁና:: አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ:: ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ::" † [ዮሐ.፲፬፥፲፪] 

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ አጋቶን ወአቡነ ያሳይ ዘመንዳባ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

†  🕊 አባ አጋቶን ዘዓምድ  🕊

ታላቁ ጻድቅ በትውልድ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩበት ዘመንም ከ፬ ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ ፭ ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው:: በእርግጥ 'አጋቶን ' በሚባል ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ቅድሚያውን ፪ ቱ ይወስዳሉ:: አንደኛው አባ አጋቶን ለ፴ ዓመታት ድንጋይ ጐርሰው የኖሩት አባት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: እኒህኛው 'ዘዓምድ ' ይባላሉ:: ምክንያቱም ለ፶ ዓመታት አንድ ምሰሶ ላይ ያለ ዕረፍት ጸልየዋልና ነው::

አባ አጋቶን ገና ከልጅነታቸው መጻሕፍትን የተማሩ ሲሆኑ ምናኔን አጥብቀው ይፈልጓት ነበር:: በዚህም ራሳቸውን በትሕርምት እየገዙ: በዲቁና ማዕርጋቸውም እያገለገሉ እስከ ፴፭ ዓመታቸው ቆዩ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ 'ይገባሃል' ብለው ቅስናን ሾሟቸው::

የማታ ማታ የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ተምኔተ ልባቸውን ፈጽሞላቸው ወደ በርሃ ሔዱ:: ወቅቱ የግብጽ ገዳማት በቅዱሳን ሕይወት የበሩበት ነውና እዚህም እዚያም አበውና እናቶች ይገኙ ነበር::

አባ አጋቶንም የከዋክብቱ አበው አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም ደቀ መዝሙር ሆነው ገቡ:: አስፈላጊውን የምንኩስና ፈተና ካለፉ በኋላም ምንኩስናን ከእነዚህ አባቶች ተቀበሉ:: በዚያው በገዳመ አስቄጥስ በጽኑ ገድል ተጠምደው ለ፲፭ ዓመታት አገለገሉ::

ጻድቁ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ቅዱሳንን ተጋድሎ ጠዋት ማታእያነበቡ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑ ነበር:: በተለይ የታላቁን ስምዖን ዘዓምድን ገድል ሲያነቡ ሕሊናቸውን ደስ ይለው: ይህንኑ ገድል ይመኙ ነበር:: እድሜአቸው ፶ ዓመት በሞላ ጊዜ በልቡናቸው እንደ አባ ስምዖን ዘዓምድ ለመጋደል ወሰኑ:: ይህን ለገዳሙ አባቶች ቢያማክሯቸው አበው:- "ይበል! ሸጋ ምክር ነው:: እግዚአብሔር ያስፈጽምህ!" ብለው መርቀው አሰናበቷቸው:: አባ አጋቶን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ ከገዳሙ ወጡ:: በጣምም ወደ ዓለም ሳይገቡ: ከዓለም በጣም ሳይርቁ አንድ ረዥም ምሰሶ አገኙና ከላዩ ላይ ወጡ::

ከዚህች ዕለት ጀምረው ጻድቁ ለ፶ ዓመታት ከዚያች ዓምድ ወርደው: ለሥጋቸውም ዕረፍትን ሰጥተውት አያውቁም:: ማዕከለ ገዳም ወዓለም ናቸውና ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት አጽናኝ አባት ሆኑ:: ለአካባቢውም የብርሃን ምሰሶ ሆኑ:: የታመመ ቢኖር ይፈውሱታል:: የበደለውን በንስሃ ይመልሱታል:: ሰይጣን የቋጠረውን ይፈቱታል:: ለራሳቸው ግን ከጸሎት: ከጾምና ከትሕርምት በቀር ምንም አልነበራቸውም::

፩. አጥማቂ ነን እያሉ ሕዝቡን ያስቱ የነበሩ ሰዎችን እየጠሩ እንዲህ የሚያስደርጋቸውን ጋኔን ከእነሱ አስወጥተዋል::
፪. እርሳቸውን ያልሰሙት ግን መጨረሻቸው ጥፋት ሆኗል::
፫. ፍጹም ወንጌልን በሕይወትና በአንደበት መስክረዋል::
፬. ሕዝቡን በንስሃ አስጊጠዋል::
፭. ተግሳጽ የሚገባውን ገስጸዋል::

ጻድቁ አባ አጋቶን ዘዓምድ ከእነዚህ የቅድስና ዘመናት በኋላበተወለዱ በ፻ ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈው በክብርና በዝማሬ ተቀብረዋል::


†  🕊  አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ  🕊  †

እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ፲፬ ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ፯ ቱ ከዋክብት [አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ] እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::

ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ፲፬ ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ: ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::

ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ፯ቱ አበው በዚያ ነበሩና ፯ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::

አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ፪ቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::

አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ መድኃኔ ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::

ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::

አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም ፲፬ ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::

† አምላከ ጻድቃን በምልጃቸው የበዛች ኃጢአታችንን ይቅር ይበለን::

🕊

[  † መስከረም ፲፬ [ 14 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. አባ አጋቶን ዘዓምድ
፪. አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
፫. አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና [ጣና]
፬. ቅዱስ ዴግና ቀሲስ

[  † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. አቡነ አረጋዊ [ዘሚካኤል]
፪. ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫. ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ሙሴ [የእግዚአብሔር ሰው]
፭. አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯. እናታችን ቅድስት ነሣሒት
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
† " ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም:: " † [ማቴ. ፲፥፵፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/11/16 07:30:20
Back to Top
HTML Embed Code: