Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

[  መስከረም ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]


†   🕊  ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት  🕊  †

ቅዱሳን ነቢያት እጅግ ብዙ ናቸው:: ከፈጣሪያቸው የተቀበሉት ጸጋም ብዙና ልዩ ልዩ ነው:: ያም ሆኖ ከሁሉም ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ይበልጣል:: መጽሐፍ እንደሚል ከእርሱም በፊት ቢሆን ከእርሱ በሁዋላ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሳምና:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ዓለም በተፈጠረ በ፫ ሺህ ፮ መቶ [3,600] ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት ፸፭ [75] ራሱን ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ተከብረው: ለ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ደግሞ በባርነት: በድምሩ ለ፬፻፴ [430] ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል::

በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ ፪ [2] ከተሞችን [ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን] ገንብተዋል:: ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ:: ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል::

ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ 'እንበረም'ና 'ዮካብድ' ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው:: ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል:: ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይፈጁ ነበር:: ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል::

በኋላም በ፫ [3] ወሩ ዓባይ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት [የፈርኦን ልጅ ናት] ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: 'ሙሴ' ያለችውም እርሷ ናት:: 'ዕጉዋለ ማይ / እማይ ዘረከብክዎ' [ከውሃ የተገኘ] ለማለት ነው:: ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል:: ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና::

ቅዱስ ሙሴ ፭ [5] ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል:: እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው ፵ [40] ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ:: ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና:: [ዕብ.፲፩፥፳፬] (11:24)

አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ:: በዚያም ለ፵ [40] ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ: ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ:: ልጆንም አፈራ:: ፹ [80] ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው:: ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው::

ቅዱስ ሙሴም ከወንድሙ አሮንና ከአውሴ [ኢያሱ] ጋር ግብጻውያንን በ፱ [9] መቅሰፍት: በ፲ [10] ኛ ሞተ በኩር መታ:: እሥራኤልንም ነጻ አወጣ:: ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም::

- እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል::
- ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል::
- ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል::
- ውሃን ከጨንጫ [ከዓለት] ላይ አፍልቁዋል::
- በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል::
- በ7 ደመና ጋርዷቸዋል::
- ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል::

ስለዚህ ፈንታ ግን ወገኖቹ ብዙ አሰቃይተውታል:: እርሱ ግን ደግ: ቅንና የዋህ ሰው ነውና ብዙ ጊዜ ራሱን ለእነሱ አሳልፎ ሰጥቷል:: "ሙሴሰ የዋህ እምኩሎሙ ደቂቀ እሥራኤል" እንዲል:: [ዘኁ.፲፪፥፫] (12:3) ቅዱስ ሙሴ ለ፵ [40] ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ፭፻፸ [570] ጊዜ ተነጋግሯል::

ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር:: ታቦተ ጽዮንንና ፲ [10]ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል:: "የቀረው የቅዱሱ ሕይወት በመጻሕፍተ ኦሪት [በብሔረ ኦሪት] ውስጥ የተጻፉ አይደሉምን?"

እኔ ግን ደካማ ነኝና ይህቺ ትብቃኝ:: ቅዱስ: ክቡር: ታላቅ: ጻድቅ: ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ፻፳ [120] ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል: ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል:: መቃብሩንም ሠውረዋል:: [ይሁዳ.፩፥፱] (1:9)


†   🕊  ቅዱስ ዘካርያስ ካህን  🕊   †

ስም አጠራሩ የከበረ: ሽምግልናውም ያማረ ቅዱስ ዘካርያስ የቅድስት ኤልሳቤጥ ባል: የመጥምቁ ዮሐንስም አባት ነው:: በእሥራኤል ታሪክ የመጨረሻው ደግ ሊቀ ካህናት ነው:: ይህ ቅዱስ ሰው ከአሮን ወገን ተወልዶ: በሥርዓተ ኦሪት አድጐ: በወጣትነቱ መጻሕፍተ ብሉያትን ተምሮ: ሊቀ ካህንነቱን እጅ አድርጉዋል::

በጐልማሳነቱም ቅድስት ኤልሳቤጥን አግብቶ በደግነትና በምጽዋት አብሯት ኑሯል:: ከኢያቄምና ከሐና ጋር ቅርብ ወዳጆች ነበሩና አልተለያዩም:: ቅዱሱ ዘወትር ለማስተማር: ለመስዋዕትና ለማዕጠንት ይተጋ ነበር:: ጸሎቱና እጣኑም ወደ ቅድመ እግዚአብሔር ይደርስለት ነበር::

እስኪያረጅ ድረስ ባይወልድም አላማረረም:: ደስ የሚለው ደግሞ እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን ከወላጆቿ ተቀብሎ ለ፲፪ [12] ዓመታት ያሳደጋት እርሱ ነው:: ዘወትር መላእክት ከበው ሲያገለግሏት እየተመለከተ ይመሰጥ ነበረ::

የልጅ አምሮቱን የሚረሳው ከእርሷ ጋር ሲሆን ነው:: እንደ አባት አሳደጋት: እንደ እመቤትም ጸጋ ክብር አሰጥታዋለች:: እድሜው መቶ ዓመት በሆነ ጊዜ በቅዱስ ገብርኤል ተበስሮ ዮሐንስን አገኘ:: ለ፱ [9] ወራት የተዘጋ አንደበቱ ሲከፈት "ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እሥራኤል" ብሎ ትንቢትን ተናገረ::

ሔሮድስ ሕጻኑን ሊገድለው በፈለገ ጊዜም ሕጻኑን ቅዱስ ዮሐንስን ወስዶ በክንፈ ኪሩብ ላይ አስቀመጠውና መልአክ ወደ በርሃ ወሰደው:: ቅዱስ ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደሱ መካከል ፸: ፹ [70: 80] ዓመት በንጽሕና ባገለገለበት ቦታ ላይ ገደሉት::

ሥጋውን አምላክ ሰውሮት የፈሰሰ ደሙ እንደ ድንጋይ ረግቶ ሲጮህ ተገኝቷል:: ለ፷፰ [68] ዓመታትም ደሙ ሲፈላ ኑሯል:: በ፸ [70] ዘመን ጥጦስ ቄሣር አይሁድን ሲያጠፋቸው ደሙ ዝም ብሏል:: ይህ ቅዱስ: ጻድቅ: ነቢይና ካህን ስሙ በተጠራ ጊዜ ሲዖል ደንግጣ ነፍሳትን እንደምትሰጥ ሊቃውንት ነግረውናል:: [ማቴ.፳፫፥፴፭] (23:35)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
......................................................

†   🕊   ቅዱስ አሮን ካህን    🕊   †

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የቅዱሱ ካህን የአሮን በትር ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ: አብባ: አፍርታ የተገኘችው በዚህ ቀን ነው:: ዳታን: አቤሮንና ቆሬ ከተከታዮቻቸው ጋር በፈጠሩት ሁከት ምድር ተከፍታ ከዋጠቻቸው በሁዋላ እግዚአብሔር የ፲፪ [12]ቱን ነገደ እሥራኤል በትር ሰብስቦ ሲጸልይበት እንዲያድር ሙሴን አዞት: እንዲሁ ሆነ::

በነጋም ጊዜ ይህቺ ደረቅ የነበረች በትረ አሮን 12 ፍሬ [ለውዝ: ገውዝ: በኩረ ሎሚ] አፍርታ ተገኘች:: [ዘኁ.፲፯፥፩-፲፩] (17:1-11) ለጊዜው ክህነት ከቤተ አሮን እንዳይወጣ ምልክት ሆናለች:: ለፍጻሜው ግን ምሳሌነቷ ለድንግል ማርያም ነው:: እመ ብርሃን የወንድ ዘር ምክንያት ሳይሆናት አምላክን ወልዳ ተገኝታለችና::

" ጸናጽል ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን: ወዓዲ በትር እንተ ሠረጸት: ወጸገየት: ወፈረየት" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: [ ቅዳሴ ማርያም ]

የእነዚህ ቅዱሳን ነቢያትና ካህናት አምላክ ደግነታቸውን አስቦ: ከግራ ቁመት: ከገሃነመ እሳትም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

[ †  መስከረም ፰ [  8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ቅዱስ ዘካርያስ ካህን (ጻድቅ ነቢይ)
፫. ቅዱስ አሮን ካህን
፬. ቅዱስ ዲማድዮስ ሰማዕት

" ሙሴ ካደገ በሁዋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ:: ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና:: ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ:: ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና::" [ዕብ.፲፩፥፳፬] (11:24)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤፤ †

[  † መስከረም ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †  ]


† 🕊  ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት 🕊  †

† ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን የመላእክት ሁሉ አለቃቸው በፈጣሪው ኃይል ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ከመጀመሪያው ሰው አዳም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ: አምነው ለሚጠሩት ረዳት ነው:: ዘወትርም ያድናቸው ዘንድ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል:: [መዝ.፴፫፥፯] (33:7)

¤ እግራችን እንዳይሰናከል ዘወትር ይጠብቀናል:: [መዝ.፺፥፲፩] (90:11)
¤ የቅዱስ ሚካኤል ስሙ ድንቅ ነው:: [መሳ.፲፫፥፲፰] (13:18)
¤ ከእርሱ በቀርስ የሚያጸና ማን አለና! [ዳን.፲፥፳፩] (10:21)
¤ ለሕዝቡም የሚቆም ታዳጊ መልአክ ነው:: [ዳን.፲፪፥፩] (12:1)
¤ በፊቱ ሲቆምም ስለ ክብሩ ጫማ አውልቆ: ባጭር ታጥቆ ነው:: [ኢያ.፭፥፲፫] (5:13)

+ ይህ ድንቅ መልአክ ከሺህ ዓመታት በፊት በሮም ከተማ ይህንን ድንቅ ተአምር በዚህች ዕለት መሥራቱን ቤተ ክርስቲያን ትመሰክራለች:: በድሮው የሮም ግዛት 'ሩፍምያ' የምትባል ከተማ ነበረች:: ይህች ከተማ ክርስቲያኖችም: ኢአማንያንም ተቀላቅለው የሚኖሩባት ናት::

በከተማዋ የክርስቲያኖች ቁጥር ትንሽ ቢሆንም በእምነት ግን ጠንካሮች ነበሩ:: በተለይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ መጋቢ ባለ ፍጹም እምነት ሰው ነበር:: በቦታው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመኖሩም ብዙ ተአምራት ይደረጉ ነበር:: ተበለጥን የሚል ስሜት የተሰማቸው አሕዛብ [ዮናናውያን] ግን ይሕንን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ተማማሉ::

በቀጥታ ሔደው ቢያፈርሱት ወይም ቢያቃጥሉት በሕግ እንደሚጠየቁ ያውቃሉና በሥጋዊ ጭንቅላታቸው ዘዴ ያሉትን መከሩና ወሰኑ:: በከተማዋ ዳር የሚያልፍ አንድ ትልቅ ወንዝ አለ:: በሞላ ጊዜ ያገኘውን ሁሉ ጠርጐ የሚወስድም ነበር::
ታዲያ ክፋተኞቹ ሌሊት ሌሊት እየተነሱ የሚሔድበትን መንገድ ዘግተው: ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አቅጣጫ መንገድ ከፈቱለት:: ከቀናት በኋላ ከባድ ዝናብ በዚህች ቀን ጣለ:: ወንዙ ትልቅ ነውና ያገኘውን ሁሉ እያገላበጠ ደረሰ::

በወቅቱ በቅዱሱ መልአክ መቅደስ ውስጥ ከመጋቢው በቀር ሰው አልነበረምና አስፈሪ ድምጽ ሰምቶ ቢወጣ ወንዙ እየደነፋ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እየመጣ ነው:: አሰበው: ከደቂቃዎች በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳልነበረ ሊሆን ነው::
እርሱ አንድ ተስፋ ነበረውና ወደ ውስጥ ገብቶ ቅዱስ ሚካኤልን ተማጸነ:: ከዚያ ላለመውጣትም ወሰነ:: ትንሽ ቆይቶ በታላቅ ኃይል ወንዙ ደረሰ:: በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ሚካኤል በግርማ ከሰማይ ወርዶ በወንዙ ፊት ቆመ::

መጋቢውንም "ጽና: አትፍራ" ብሎት በያዘው የብርሃን በትረ-መስቀል መሬትን አንድ ጊዜ መታት:: በዚያች ቅጽበትም ትልቅ ሸለቆ ተፈጠረ:: ወንዙም በሸለቆው ውስጥ አልፎ ሔደ::
+የሚገርመው ሸለቆው የተፈጠረው በቤተ ክርስቲያኑ በታች ነው:: ቅዱስ ሚካኤል ግን መጋቢውን ባርኮት በክብር ዐረገ:: በማግስቱ ክርስቲያኖቹ ይህንን አይተው ደስ አላቸው:: መልአኩንም አከበሩት:: አሕዛብ ግን አፈሩ::


† 🕊 ቅዱስ ቢሶራ ሰማዕት  🕊  †

† በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያን መሆን ብቻ የሚያስከፍለው ዋጋ ብዙ ነበር:: ከምንም በላይ መከራው የጸናባቸው ግን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ:: ክደው ያስክዳሉ በማለት አብዝተው ያሰቃዩአቸው ነበር:: ቶሎም አይገድሏቸውም:: መከራውን ከማራዘም በቀር::

ከእነዚህም አንዱ አባ ቢሶራ ነው:: እርሱ በምድረ ግብፅ 'መጺል' ለምትባል ሃገር ኤዺስ ቆዾስ ነበረ:: በእድሜው አረጋዊ: በትምሕርቱ ምሑር: በምግባሩ ቅዱስና በእረኝነቱም የተመሠከረለት በመሆኑ በምዕመናን ዘንድ ተወዳጅ ነበር::

መከራው እየገፋ ሲመጣ ግን ቅዱሱ በመፍራት ፈንታ የሰማዕትነት ፍቅር አደረበት:: ስለ ሃይማኖት መሞትን እና ቶሎ ወደ ክርስቶስ መሔድን ናፈቀ:: ነገር ግን መልካም እረኛ ነውና በጐቹን [ምዕመናንን] እንዲሁ ሊተዋቸው አልወደደም:: ሰብስቦ ምን እንዳሰበ አማከራቸው:: የሰሙት ነገር ክርስቲያኖችን አስለቀሳቸው::

"አቡነ ለመኑ ተኀድገነ-አባታችን ለማን ትተኸን ትሔዳለህ?" ሲሉም ከእግሩ ወደቁ:: እርሱ ግን አስረድቷቸው: አጽናንቷቸውም በእንባ ተሰናበታቸው:: አንዳንዶቹ ደግሞ "አብረንህ እንሞታለን" ብለው ተከተሉት:: ቅዱስ አባ ቢሶራን ከብዙ ስቃይ በኋላ አረማውያን ከነተከታዮቹ በዚህ ቀን ገድለውታል::


†   🕊  ቅዱስ ያሳይ ንጉሥ  🕊  †

† በቀደመው ዘመን መንግስታቸውን ትተው ከመነኑ ነገሥታት አንዱ ቅዱስ ያሳይ ነው:: ምናኔ በቁሙ ከባድ ነው:: መንግስትን: ዙፋንን: ክብርን ትቶ መመነንን ደግሞ ከማድነቅ በቀር እንዲህ ብለው ሊገልጹት ይከብዳል::

ቅዱስ ያሳይም መንግስቱን ትቶ ልምላሜ ወደሌለበት ደረቅ በርሃ ሔደ:: በዚያም ከአንዲት ዛፍ በቀር ምንም ነገር አላገኘም:: በዚያች ደረቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ለዓመታት በጾምና በጸሎት ተጋደለ::

በዘመነ ተጋድሎው ከዛፏ አልወረደም: ሰውም አይቶ አያውቅም:: በመጨረሻም ስለ ቅድስናው ዛፏ ለምልማለች:: እርሱም በዚህች ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን ተራዳኢ መልአክን ይዘዝልን:: ከወዳጆቹ በረከትም አይለየን::

🕊

[  † መስከረም ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ቢሶራ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ያሳይ ንጉሥ
፬. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት [ ልደቱ ]
፭. "14,730" ሰማዕታት [ የቅዱስ ፋሲለደስ ማሕበር ]

† " የፋርስ መንግስት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቁዋቁዋመኝ:: እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ:: እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት:: " † [ዳን.፲፥፲፫] (10:13)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: ✞✞✞

† ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፱ †

+ #ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት +

=> # ቅዱሳት_መጻሕፍት እንደሚነግሩን የመላእክት ሁሉ
አለቃቸው በፈጣሪው ኃይል ብዙ ድንቆችን ሠርቷል::
ከመጀመሪያው ሰው #አዳም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ: አምነው
ለሚጠሩት ረዳት ነው:: ዘወትርም ያድናቸው ዘንድ በሚፈሩት
ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል:: (መዝ. 33:7)

¤እግራችን እንዳይሰናከል ዘወትር ይጠብቀናል:: (መዝ.
90:11)
¤የቅዱስ ሚካኤል ስሙ ድንቅ ነው:: (መሳ. 13:18)
¤ከእርሱ በቀርስ የሚያጸና ማን አለና! (ዳን. 10:21)
¤ለሕዝቡም የሚቆም ታዳጊ መልአክ ነው:: (ዳን. 12:1)
¤በፊቱ ሲቆምም ስለ ክብሩ ጫማ አውልቆ: ባጭር ታጥቆ
ነው:: (ኢያ. 5:13)

+ይህ ድንቅ መልአክ ከሺህ ዓመታት በፊት በሮም ከተማ ይህንን
ድንቅ ተአምር በዚህች ዕለት መሥራቱን ቤተ ክርስቲያን
ትመሰክራለች:: በድሮው የሮም ግዛት ' # ሩፍምያ ' የምትባል
ከተማ ነበረች:: ይህች ከተማ ክርስቲያኖችም: ኢአማንያንም
ተቀላቅለው የሚኖሩባት ናት::

+በከተማዋ የክርስቲያኖች ቁጥር ትንሽ ቢሆንም በእምነት ግን
ጠንካሮች ነበሩ:: በተለይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ መጋቢ ባለ
ፍጹም እምነት ሰው ነበር:: በቦታው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ
ክርስቲያን በመኖሩም ብዙ ተአምራት ይደረጉ ነበር:: ተበለጥን
የሚል ስሜት የተሰማቸው አሕዛብ (ዮናናውያን) ግን ይሕንን
ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ተማማሉ::

+በቀጥታ ሔደው ቢያፈርሱት ወይም ቢያቃጥሉት በሕግ
እንደሚጠየቁ ያውቃሉና በሥጋዊ ጭንቅላታቸው ዘዴ ያሉትን
መከሩና ወሰኑ:: በከተማዋ ዳር የሚያልፍ አንድ ትልቅ ወንዝ
አለ:: በሞላ ጊዜ ያገኘውን ሁሉ ጠርጐ የሚወስድም ነበር::

+ታዲያ ክፋተኞቹ ሌሊት ሌሊት እየተነሱ የሚሔድበትን መንገድ
ዘግተው: ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አቅጣጫ መንገድ ከፈቱለት::
ከቀናት በሁዋላ ከባድ ዝናብ በዚህች ቀን ጣለ:: ወንዙ ትልቅ
ነውና ያገኘውን ሁሉ እያገላበጠ ደረሰ::

+በወቅቱ በቅዱሱ መልአክ መቅደስ ውስጥ ከመጋቢው በቀር
ሰው አልነበረምና አስፈሪ ድምጽ ሰምቶ ቢወጣ ወንዙ እየደነፋ
ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እየመጣ ነው:: አሰበው: ከደቂቃዎች
በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳልነበረ ሊሆን ነው::

+እርሱ አንድ ተስፋ ነበረውና ወደ ውስጥ ገብቶ ቅዱስ
ሚካኤልን ተማጸነ:: ከዚያ ላለመውጣትም ወሰነ:: ትንሽ ቆይቶ
በታላቅ ኃይል ወንዙ ደረሰ:: በዚህ ጊዜ ግን ቅዱስ ሚካኤል
በግርማ ከሰማይ ወርዶ በወንዙ ፊት ቆመ::

+መጋቢውንም "ጽና: አትፍራ" ብሎት በያዘው የብርሃን በትረ-
መስቀል መሬትን አንድ ጊዜ መታት:: በዚያች ቅጽበትም ትልቅ
ሸለቆ ተፈጠረ:: ወንዙም በሸለቆው ውስጥ አልፎ ሔደ::

+የሚገርመው ሸለቆው የተፈጠረው በቤተ ክርስቲያኑ በታች
ነው:: ቅዱስ ሚካኤል ግን መጋቢውን ባርኮት በክብር ዐረገ::
በማግስቱ ክርስቲያኖቹ ይህንን አይተው ደስ አላቸው::
መልአኩንም አከበሩት:: አሕዛብ ግን አፈሩ::

+"+ # ቅዱስ_ቢሶራ_ሰማዕት +"+

=>በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያን መሆን የሚያስከፍለው ዋጋ ብዙ
ነበር:: ከምንም በላይ መከራው የጸናባቸው ግን የቤተ
ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ:: ክደው ያስክዳሉ በማለት አብዝተው
ያሰቃዩአቸው ነበር:: ቶሎም አይገድሏቸውም:: መከራውን
ከማራዘም በቀር::

+ከእነዚህም አንዱ አባ ቢሶራ ነው:: እርሱ በምድረ ግብፅ
'መጺል' ለምትባል ሃገር ኤዺስ ቆዾስ ነበረ:: በእድሜው
አረጋዊ: በትምሕርቱ ምሑር: በምግባሩ ቅዱስና በእረኝነቱም
የተመሠከረለት በመሆኑ በምዕመናን ዘንድ ተወዳጅ ነበር::

+መከራው እየገፋ ሲመጣ ግን ቅዱሱ በመፍራት ፈንታ
የሰማዕትነት ፍቅር አደረበት:: ስለ ሃይማኖት መሞትን እና ቶሎ
ወደ #ክርስቶስ መሔድን ናፈቀ:: ነገር ግን መልካም እረኛ ነውና
በጐቹን (ምዕመናንን) እንዲሁ ሊተዋቸው አልወደደም:: ሰብስቦ
ምን እንዳሰበ አማከራቸው:: የሰሙት ነገር ክርስቲያኖችን
አስለቀሳቸው::

+"አቡነ ለመኑ ተኀድገነ-አባታችን ለማን ትተኸን ትሔዳለህ?"
ሲሉም ከእግሩ ወደቁ:: እርሱ ግን አስረድቷቸው: አጽናንቷቸውም
በእንባ ተሰናበታቸው:: አንዳንዶቹ ደግሞ "አብረንህ እንሞታለን"
ብለው ተከተሉት:: ቅዱስ አባ ቢሶራን ከብዙ ስቃይ በሁዋላ
አረማውያን ከነ ተከታዮቹ በዚህ ቀን ገድለውታል::

+"+ # ቅዱስ_ያሳይ_ንጉሥ +"+

=>በቀደመው ዘመን መንግስታቸውን ትተው ከመነኑ ነገሥታት
አንዱ ቅዱስ ያሳይ ነው:: ምናኔ በቁሙ ከባድ ነው::
መንግስትን: ዙፋንን: ክብርን ትቶ መመነንን ደግሞ ከማድነቅ
በቀር እንዲህ ብለው ሊገልጹት ይከብዳል::

+ቅዱስ ያሳይም መንግስቱን ትቶ ልምላሜ ወደሌለበት ደረቅ
በርሃ ሔደ:: በዚያም ከአንዲት ዛፍ በቀር ምንም ነገር
አላገኘም:: በዚያች ደረቅ ዛፍ ላይ ወጥቶ ለዓመታት በጾምና
በጸሎት ተጋደለ::

+በዘመነ ተጋድሎው ከዛፏ አልወረደም: ሰውም አይቶ
አያውቅም:: በመጨረሻም ስለ ቅድስናው ዛፏ ለምልማለች::
እርሱም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>አምላከ ቅዱሳን ተራዳኢ መልአክን ይዘዝልን:: ከወዳጆቹ
በረከትም አይለየን::

=>መስከረም 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ቢሶራ ሰማዕት
3.ቅዱስ ያሳይ ንጉሥ
4.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት (ልደቱ)
5."14,730" ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስ ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

=>+"+ የፋርስ መንግስት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን
ተቁዋቁዋመኝ:: እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ #ሚካኤል
ሊረዳኝ መጣ:: እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት::
+"+ (ዳን. 10:13)

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †


[   † መስከረም ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †  ]


†   🕊  በዓለ ስዕለ አድኅኖ   🕊   †

ይህች ቀን በቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳት ስዕላት የሚነገርባት ክብርት ቀን ናት:: 'ስዕለ አድኅኖ' ማለት 'እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥበት: አንድም በቅዱሳኑ አማካኝነት ጸጋ የሚገኝበት: የሚያድን ስዕል' ማለት ነው::

ስለዚህ ነገር አንዳንዶቹ ሊነቅፉን ይፈልጋሉ:: እኛ ግን ከማን እንደ ተማርነው እናውቃለን:: ከመነሻው እኛ ስዕልን አናመልክም:: ይልቁኑ አምልኮን እንፈጽምበታለን እንጂ:: ስዕልን ለሰው ልጆች የሰጠ ራሱ ባለቤቱ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል::

እንዲያውም የመጀመሪያው ሰዐሊ ራሱ አምላካችን ነው:: አዳምን እንደ መልኩ: በምሳሌው ሲፈጥረው መላእክት የእግዚአብሔርን ምስል አዳም ላይ አይተዋልና:: [ዘፍ.፩፥፳፮] (1:26) ለሙሴም ስዕለ ኪሩብን እንዲስል ያዘዘ ራሱ ነው:: [ዘጸ.፳፭፥፳፪] (25:22) በዚያም ላይ ሆኖ ሙሴና አሮንን ሲነጋገራቸው ኑሯል::

በመቅደሰ ሰሎሞንም ተመሳሳይ ነገርን እናገኛለን:: [፪ዜና.፯፥፲፪] (7:12) , ፩ነገ.፱፥፩] (9:1) በሐዲስ ኪዳንም ጌታ ስዕለ ኪሩብ ያለበትን መቅደስ ቤቴ [ማቴ.፳፩፥፲፫] (21:13): የአባቴ ቤት [ዮሐ.፪፥፲፮] (2:16) ሲለው: በቅዱስ ሰውነቱ ሲመስለውም [ዮሐ.፪፥፳፩] (2:21) እንመለከታለን:: ቅዱስ ዻውሎስ ለገላትያ ሰዎች ስለ ስዕለ ስቅለት ሲያስታውሳቸው [ገላ.፫፥፩] (3:1): ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ በደም የተረጨች ልብስ ብሎ ያላትን መተርጉማን ያትታሉ:: [ራዕይ.፲፱፥፲፫] (19:13)

በትውፊት ትምሕርት ደግሞ የመጀመሪያው ስዕል በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ላይ የተሳለ ሲሆን ስዕሉም የእመቤታችን ነው:: "ሚካኤል በክነፊሁ ጾራ መንጦላዕተ ደመና ሠወራ" እንዳለ ቅዱስ ያሬድ:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቃርዮስና ለቬሮኒካ ፲፪ [12] ዓመት ደም ይፈሳት ለነበረችው ሴት) መልክአ ገጹን ሠጥቷቸዋል::

['ቬሮኒካ' በላቲን 'ቬሮን-ኢኮን' 'እውነተኛ መልክ' እንደ ማለት ነው]

ቀጥሎም ዮሐንስ ወንጌላዊ ለጢባርዮስ ቄሣር ስዕለ ስቅለቱን ሲስልለት ቅዱስ ሉቃስ ደግም የእመቤታችን 'ምስለ ፍቁር ወልዳን' ስሏል:: ከዚያም ሲያያዝ ይሔው ከእኛ ደርሷል::

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በከተሞች አካባቢ ቅርጾች በዝተዋልና ይሔ አላስፈላጊ መዋስ [ያውም ከመናፍቃን] ቢቀር መልካም ነው ባይ ነኝ:: ኋላ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ ከባድ ነውና::


†   🕊   ጼዴንያ    🕊   †

በዚህች ቀን ቅዱስ ሉቃስ የሳላትና ሥጋን የለበሰችው: ከፊቷም ወዝ የሚወጣትና ድውያንን የምታድነው የድንግል ማርያም ስዕለ አድኅኖ ወደ ጼዴንያ ከወዳጇ ከብጽዕት ማርታ ዘንድ ገብታለች:: ቅድስት ማርታ ሃብት ንብረቷን በአብርሃማዊ ተግባር [በምጽዋትና እንግዳን በመቀበል] ላይ ያዋለች ክብርት ሴት ናት::

ለእመ ብርሃን ካላት ፍቅር የተነሳ እንቅልፍ አልነበራትም:: ተግታ ታገለግላትም ነበር:: ስዕሏን እንዲያመጣላት የላከችው ኢትዮዽያዊው መነኩሴ አባ ቴዎድሮስ የስዕሏን ተአምራት ባየ ጊዜ ለራሱ ለመውሰድ ሞክሮ ነበር:: [እርሱ ምን ያድርግ! እኔም ብሆን ይህንኑ ነበር የማደርገው]

ነገር ግን ከሁሉም በተሻለ የምትወዳት ቅድስት ማርታ ነበረችና በድንቅ ተአምር: በዚህች ቀን ወደ ጼዴንያ ገብታለች:: ቅድስት ማርታም ያለ ዕረፍት ስታገለግላት ኑራ ዐርፋለች:: ይህቺ ክብርት ስዕለ አድኅኖ የአሁን መገኛ 4 መረጃዎች አሉ:-

፩. ያለችው ኢትዮዽያ ውስጥ [ደብረ ዘመዳ በሚባል ገዳም] ነው:: የመጣችውም ከግማደ መስቀሉ ጋር ነው::
፪. ያለችው በቀደመ ቦታዋ ነው::
፫. የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወስደዋታል::
፬. በፈጣሪ ጥበብ ተሰውራለች::


†   🕊  ልደታ ለማርያም  🕊   †

በግብጽ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ: ማለትም በአስቄጥስ ደብረ አባ መቃርስ የእመቤታችንን ዜና ሕይወት የሚናገር ፩ [1] መጽሐፍ አለ:: መጽሐፉ እንደሚለው እመ ብርሃን ድንግል ማርያም የተጸነሰችው ታሕሳስ ፲፯ [17] ቀን ነው:: በዚህ ሒሳብ መሠረት ደግሞ እመ አምላክ የተወለደችው መስከረም 10 ቀን ነው:: ዓለማቀፍ ትውፊቱ ግን ነሐሴ ፯ [7] ተጸንሳ: ግንቦት ፩ [1] ቀን መወለዷን ያሳያል::


†  🕊 ተቀጸል ጽጌ / አጼ መስቀል  🕊  †

'ተቀጸል ጽጌ' ማለት 'መስቀል ሆይ! በአበባ አጊጥ' እንደ ማለት ሲሆን 'አጼ መስቀል' ደግሞ አጼ ገብረ መስቀልን: አንድም አፄ ዳዊት ቀዳማዊን ይመለከታል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

በሃገራችን ኢትዮዽያ የነገረ መስቀሉ ትምሕርት ከመጣ ጀምሮ መስቀል ይከበራል:: በአደበባባይ ግን እንዲከበር ያደረጉት የቅዱስ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል ናቸው:: በወቅቱ ንጉሡ: ሠራዊቱ: ዻዻሱና ሕዝቡ በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር-መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው: ከጠላትም ያድነናል" እያለ ይዘምር ነበር::

የአበባ ጉንጉንም ለመስቀሉና ለንጉሡ ይቀርብ ነበር:: ከ፰፻ [800] ዓመታት በሁዋላም አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ባስመጡ ጊዜ መስከረም ቀን ተተክሎ ታላቅ በዓልም ሆኖ ተከብሯል::


†   🕊   ንግሥተ ሳባ    🕊   †

ይሕቺ ደግ ኢትዮዽያዊት ከ፫ [3] ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች::

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች:: [ማቴ.፲፪፥፵፪] (12:42) በስምም "ሳባ: አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ዕረፍቷ ነው::

እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ጣዕሟን ፍቅሯን: ጸጋ በረከቷን: ከስዕሏም ረድኤት ትክፈለን:: የቅዱሳኑም ክብር አይለየን::

🕊

[  † መስከረም ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም
፪. በዓለ ስዕለ አድኅኖ
፫. ቅዱስ እፀ መስቀል [ተቀጸል ጽጌ]
፬. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፭. ቅድስት ማርታ ዘጼዴንያ
፮. ቅድስት ዮዲት ጥበበኛዋ
፯. ንግስተ ሳባ / ማክዳ / አዜብ
፰. ቅድስት መጥሮንያ ሰማዕት
፱. አፄ ዳዊት ንጉሥ
፲. ቅድስት አትናስያና ፫ [3] ልጆቿ

[   †  ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ
፫. ቅዱስ  ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፬. ቅድስት እሌኒ ንግስት
፭. ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

" የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር:: ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው ? " [ገላ.፫፥፩] (3:1)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ኢትዮጵያ ከመላእክት ጋር የሚዘምር ማሕሌታዊ ከካህናተ ሰማይ ጋር የሚያጥን ካህን የምታፈራ ሀገር ናት። ለሰማይ አገልጋዮችን ገና ሳይሞቱ የምትልክ፣ ከተዋጊዎች መካከል ወደ ድል ነሺዎች መልእክተኛ የምትልክ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለች ናት?

ቅዱስ ያሬድ በትሕትናው ከትል ተማረ። ትሑታንን ከፍ የሚያደርግ ፈጣሪም ከፍ አደረገውና ከመላእክት ጋር ዘመረ። ትልዋን ከዛፍ አውርዶ ቢጨፈልቃት ኖሮ ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ያልነጠፈው የምስጋና ጅረት በሀገራችን ባልፈሰሰ ነበር። ኃይል አለኝ ብለህ የምትጨፈልቃቸው ትሎች ሰማይ የሚያደርሱህ መምህራኖችህ እንዳይሆኑ ተጠንቀቅ ይላል የታሪኩ ተግሣፅ።

ቅዱስ ያሬድ እግሩን በጦር እየተወጋ እንኩዋን ዝማሬው ሰማያት ወስዶት አልተሰማውም ነበር። የእኛው ሲላስ የእኛው ጳውሎስ ቅዱስ ያሬድ ሆይ በዘመርክባት ሀገርህ ዛሬ ብዙ ጦር ተሰክቶባታል። ከአንተ ዜማ በቀር ዛሬም መጽናኛ የለንምና በምልጃህ አስበን።

ጥዑመ ልሳን ያሬድ: ሊቀ ጠበብት ያሬድ: ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ!!

(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት እና ቅድስት ታኦድራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


† 🕊 ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት 🕊 †

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እንዲያውም ለዘመነ ሰማዕታት መሪና አስተማሪ እርሱ ነበር::
እስኪ በጥቂቱ ነገሩን ከሥሩ እንመልከተው::
በ፫ ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ: ገላውዴዎስ: ፊቅጦር: መቃርስ: አባዲር: ቴዎድሮስ [፫ቱም]: አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ::

ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ :- ማርታ: ሶፍያ: ኢራኢ: ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ /ሞተ/::

የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ::

በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪዻዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪዻዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው::

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች::

ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ :- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ::

ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ::

አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ-ቤተክርስቲያኖች ይዘጉ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ:: አዽሎን: አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ::

በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ::
- ምድር በደም ታጠበች::
- ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ::
- እኩሉ ተገደለ: እኩሉ ተቃጠለ: እኩሉ ታሠረ: እኩሉም ተሰደደ:: በዚህ ጊዜ 'መራሔ ትሩፋት' ቅዱስ ፋሲለደስ ለሰማዕትነት ይበቁ ዘንድ ስለ ራሱና ስለ ወገኖቹ ጸለየ::
ቅዱስ ሚካኤልም በግርማ ወርዶ ቅዱሱን ወደ ሰማይ አወጣው:: ከቅዱሳን ጋር በገነት አስተዋውቆት: ክብረ ሰማዕታትን አሳይቶት: ከጌታ ዘንድ አስባርኮት: ከሕይወት ውሃ ምንጭም አጥምቆ መለሰው::ቅዱስ ፋሲለደስም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ በንጉሡ ፊት ቆመ::

ንጉሡ ፈራ እርሱ ግን በፈጣሪው ስም መሞት እንደሚፈልግ ነገረው:: ሊያባብለው ሞከረ አልተሳካም እንጂ:: ከዚያም አስሮ ወደ አፍራቅያ [አፍሪካ] ላከው:: መጽሩስ የሚባል መኮንንም ቅዱሱን አሰቃየው::

እርሱ የሁሉ የበላይ ሲሆን ስለ ክርስቶስ ሁሉን ተወ:: አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት በምጣድ ላይ ጠበሱት: አበራዩት በወፍጮም ፈጩት:: እርሱ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ሁሉን ታገሰ:: ሁለት ጊዜ ገድለውት ከሞት ተነሳ:: በተአምራቱ ምክንያትም ከከተማው ሕዝብ ግማሹ ያህል ከአሕዛባዊነት ተመልሶ ሰማዕት ሆነ::

በመጨረሻም በዚህ ዕለት አንገቱን ሲቆርጡት ደምና ወተት ፈሶታል:: መላእክትም እርሱን ለመቀበል ዐየሩን ሞልተውታል:: ከልዑላኑ ወገንም የቅዱስ ፋሲለደስን ሚስትና ልጆችንጨምሮ አንድም የተረፈ የለም:: ሁሉም በሰማዕትነት አልፈዋል::

† 🕊 እናታችን ቅድስት ታኦድራ 🕊

ይህች ቅድስት እናታችን የትእግስት እመቤት ናት:: ትእግስቷ: ደግነቷ ፈጽሞ ይደነቃል:: ታሪኳ ደግሞ በሆነ መንገድ ከቅድስት እንባ መሪና ጋር ይገናኛል::

ቅድስት ታኦድራ ግብጻዊት ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በእስክንድርያ ነው:: ከሕጻንነቷ ጀምራ ቅን ነበረች:: ምንም እንኳ የምናኔ ሰው ብትሆንም ወላጆቿ ያመጡላትን ባል 'እሺ' ብላ አገባች:: ለተወሰነ ጊዜም በሥጋ ወደሙ ተወስነው ከባሏ ጋር በሥርዓቱ ኖሩ::

ለቤተ ክርስቲያን ከነበራት ፍቅር የተነሳ ጠዋት ማታ ትገሰግስ ነበር:: አንድ ቀን ግን መንገድ ላይ የሆነ ፈተና ጠበቃት::ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በመልኳ ምክንያት ለኃጢአት ተግባር ይፈልጋት የነበረ አንድ ጐረምሳ ድንገት ያዛት:: ታገለችው: ግን ከአቅሟ በላይ ነበር:: ጮኸች የሚሰማትም አልነበረም:: ሰውየው የሚፈልገውን ፈጽሞ: ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ይህንን መቻል ለአንዲት ንጽሕት ወጣት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ መረዳቱ አይከብድም::

እጅግ መጥፎ ሰው በቀለኛም ለመሆን ከዚህ በላይ ምክንያት አይኖርም:: ቅድስቷ ግን ከወደቀችበት ተነስታ መሪር እንባን አለቀሰች:: ሕመሟን ችላ ወደ ቤቷ ላትመለስ ወደ በርሃ ተጓዘች:: ወደ ገዳም ገብታ በወንድ ስም 'አባ ቴዎድሮስ' ተብላ መነኮሰች:: በአካባቢው የሴቶች ገዳም አልነበረም::

የሚገርመው በገዳም ውስጥ ሆና ያንን ጨካኝ ሰው ይቅር አለችው:: ቀጥላም ስለ እርሱ ኃጢአት ንስሃን ወስዳ ከባዱን ቀኖና ተሸከመችለት:: ይሔ ነው እንግዲህ ሕይወተ ቅዱሳን ማለት: ራስን አሳልፎ ለጠላት መስጠት:: [ዮሐ.፲፭፥፲፫] ፈተናዋ ግን ቀጠለ::

ወንድ መስለዋት 'በአካባቢው ከምትገኝ ሴት ጸንሰሻል' ብለው ከገዳም አባረሯት:: ያልወለደቺውንም ልጅ ታሳድግ ዘንድ ሰጧት:: አሁንም በአኮቴት ተቀብላ ለ፯ ዓመታት በደረቅ በርሃ ተሰቃየች:: ልጁንም አሳደገች:: ከዚያም ከባድ ንስሃ ሰጥተው ተቀበሏት:: ቅድስት ታኦድራ እንዲህ ስትጋደል ኑራ በዚህች ቀን ዐርፋለች:: በዕረፍቷም ቀን ክብሯ ተገልጧል::

† ቸር አምላክ የቅዱሳኑን ትእግስትና መንኖ ጥሪት አይንሳን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[ † መስከረም ፲፩ [ 11 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፪. ቅድስት ታኦድራ እናታችን
፫. ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ሐዋርያዊ [ሐዋ.፲ን] ያንብቡ]
፬. ቅድስት በነፍዝዝ ሰማዕት
፭. ፫ "3ቱ" ገበሬዎች ሰማዕታት [ሱርስ: አጤኬዎስና መስተሐድራ]

† " ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን:: " † [ሮሜ. ፰፥፴፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/15 07:22:50
Back to Top
HTML Embed Code: