Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †


[  †  መስከረም [ ፭ ] 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †  ]

†  🕊   " ቅድስት ሐጊያ ሶፍያ "   🕊  †

ዘመነ ሰማዕታት በሚል በሚታወቀው ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ብዙ ቅዱሳት እናቶቻችን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ አንገታቸውን ሰጥተዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸው እጅግ የሚያምር ነበር:: ከእነዚህ ቅዱሳት እናቶቻችን አንዷ ዛሬ የምናከብራት ሐጊያ ሶፊያ ናት::

በዚህ ስም ከሚጠሩት አንዷ ስትሆን በቀደመ ሕይወቷ ክርስቶስን አታውቅም ነበር:: ጣዖትን የሚያመልኩ ወላጆቿ አሳድገው አጋቧት:: ከትዳሯም ፪ [2] ቡሩካት ሴቶች ልጆች ወልዳለች:: ስማቸውም አክሶስናና በርናባ ይባላል:: ልጆቿ ልብ እያገኙ በሔዱ ጊዜ ቅድስት ሶፍያ ስለ እውነተኛው አምላክ ትመራመር ገባች::

በወቅቱ የነበሩ ብዙ ሃይማኖቶችን መዘነች:: ከክርስትና በቀር ግን ሌሎቹ ሚዛን እንደማይመቱም አስተዋለች:: "እውነኘተኛው አምላክ ሆይ! ምራኝ: እርዳኝም" ስትል ጸለየች:: መድኃኔ ዓለም ለጠሩት አያሳፍርምና ፈጥኖ በጐውን ጐዳና አሳያት::

ድኅነት ለልጆቿም ይሆን ዘንድ ሁለቱንም ጠርታ ስለ ክርስትና አማከረቻቸው:: ደስ ብሏቸው ተቀበሏት:: እርሷም ጊዜ ሳታጠፋ ወደ ዻዻስ ሒዳ ማሕተመ ክርስትና: ሃብተ ውልድናን ትቀበል ዘንድ ከልጆቿ ጋር ተጠመቀች:: በቅድስናና ደስ በሚያሰኝ አኗኗርም እስከ መከራ ቀን ቆየች::

የመከራ ጊዜ ሲደርስም ልጆቿን ጠርታ "ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንሙት" አለቻቸው:: ቡሩካቱ አክሶስናና በርናባም ደስ እያላቸው "እሺ" አሏት:: ወዲያውም በመኮንኑ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ከመካድና ከስቃይ ሞት የትኛውን እንደሚመርጡ ቢጠየቁ እነርሱ መሞትን መረጡ:: ወደ እሥር ቤትም ከተቷቸው::

ቅድስት ሶፍያ [፪] 2 ልጆቿ ይጸኑላት ዘንድ አዘውትራ ገድለ ሰማዕታትን እና ክብራቸውን ትተርክላቸው ነበር:: በተለይ የታላቁዋን አንጌቤናይት [እመቤት] ሶፍያንና የ፫ [3] ልጆቿን [ዺስጢስ: አላዺስና አጋዺስ] ተጋድሎ እየነገረች ታጸናቸው ነበር::

ከእሥር በኋላ ግርፋት ታዞባቸው እናት ራቁቷን ስትገረፍ መልአክ ወርዶ ሲጋርዳት ልጆች በማየታቸው ደስ አላቸው:: ቅድስት ሐጊያ ሶፍያና ፪ [2] ልጆቿ እጅግ የበዛ ስቃይን ስለ ቀናች እምነት ተቀበሉ:: ምላስ እስከ መቆረጥም ደረሱ:: በመጨረሻ ግን በዚህች ቀን ተገድለው አክሊለ ሰማዕታትን ገንዘብ አደረጉ::

የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የሁሉን ቅዱሳን ቤት ሠርቶ የእርሷን በመዘንጋቱ ለራሱ ባሰራው ቤተ መንግስት ላይ ተአምር ታይቷል:: ለ፫ ያህል ጊዜ ስሙን ሲያስቀርጽ መልአክ እየወረደ ይፍቀው: የሶፍያንም ስም ይጽፈው ነበር::

በመጨረሻም ንጉሡ ልጁን እስከ መገበር ደርሶ ቤተ መንግስቱ የቅድስት ሶፍያና የ፪ ልጆቿ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል:: ምንም ለ፫ ጊዜያት ያህል ሙሉ እድሳት ቢደረግለትም ዛሬ አሕዛብ የያዙትን ይህንን ቅርስ ንጉሡ የሠራው ከ፲፻፯፻ [1700] ዓመታት በፊት ነው::


†  🕊 ቅዱስ ማማስ ሰማዕት  🕊

የሰማዕቱ ወላጆች ቴዎዶስዮስና ታውፍና ሲባሉ ማማስ የሚለው የስሙ ትርጉም 'ዕጉዋለ ማውታ - እናት አባቱ የሞቱበት' ማለት ነው:: ለምን እንደዚህ ተባለ ቢሉ :- በዘመነ ሰማዕታት ስደት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይዘውት ተሰደው ነበር:: ማምለጥ ባይችሉ ይዘው አሠሯቸው::

በእሥር ቤትም ከስቃዩ ብዛት ፪ [2] ቱም ልጃቸውን ማማስን እንዳቀፉት ሕይወታቸው አለፈች:: ሕጻኑ ሲያለቅስ የተመለከተች አንዲት ሴትም ራርታ እነርሱን አስቀብራ: እርሱን አሳድጋዋለች:: ስሙንም 'ማማስ' ብላዋለች::

ቅዱሱ ባደገ ጊዜ የወላጆቹን ጐዳና በመከተሉ ተይዞ ለፍርድ ቀረበ:: ክርስቶስን አልክድም በማለቱም ብዙ ስቃይን አሳልፎ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል:: ቅዱስ ማማስ ከዐበይት ሰማዕታት አንዱ ሲሆን በአንበሳ ጀርባ ላይም ይቀመጥ ነበር::


🕊  አቡነ አሮን መንክራዊ  🕊

ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ አሮን በ፲፬ [14] ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ኢትዮዽያዊ ሲሆኑ በገዳማዊ ሕይወታቸው: በሐዋርያዊ አገልግሎታቸውና ነገሥታቱን ሳይፈሩ በመገሰጻቸው ይታወቃሉ:: በተለይም ሕይወታቸው በተአምር የተሞላ ስለነበር 'አሮን መንክራዊ' [ድንቅ አባት] ተብለው ይጠራሉ::

አንዳንድ ጊዜም 'አሮን ዘመቄት /ዘደብረ ዳሬት/' በሚልም ይጠራሉ:: የአቡነ አሮን ወላጆች ገብረ መስቀልና ዓመተ ማርያም የሚባሉ ሲሆን ከልጅነታቸው ጀምረው በቅዱስ ቃሉ የታነጹ ነበሩ:: ምናኔን በደብረ ጐል: ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጀምረው ብዙ ገዳማትን መሥርተዋል:: በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፍርተዋል::

ለወንጌል አገልግሎት በወጡበት ጸሐይን አቁመው: ሕዝቡን ድንቅ አሰኝተዋል:: እንኳን ሰዉ ይቅርና አጋንንትም ያደንቁዋቸው ነበር:: ነገሥታቱንም ስለ ኃጢአታቸው በገሰጹ ጊዜ ራቁትነት: እሥራት: ግርፋትና ስደት ደርሶባቸዋል::

ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ወሎ መቄት ውስጥ በሚገኘው ገዳማቸው ዐርፈው ተቀብረዋል:: ገዳሙ እስካሁን ያለ ሲሆን ድንቅ ጥበበ እግዚአብሔር የሚታይበት ነው:: ጣራው ክፍት ሲሆን ዝናብ አያስገባም::

†  🕊  አፄ ልብነ ድንግል  🕊  † 

እኒህ ንጉሥ ኢትዮዽያን ለዓመታት (ከ፲፻፭፻ [1500] እስከ ፲፻፭፻፴፪ [1532] ዓ/ም) ቢያስተዳድሩም ፲፭ ቱ ዓመት ያለቀው በስደት ነው:: ከደጋጉ አፄ ናዖድና ንግሥት ወለተ ማርያም ተወልደው: በሥርዓቱ አድገው ቢነግሡም: በክፉ መካሪዎች ጠንቅዋይ ወደ ቤታቸው ገብቶ ሃገሪቱን ለመከራ ዳርጉዋታል::

ዛሬም ድረስ ጠባሳው ያለቀቀው የግራኝ ወረራ ለ፲፭ ዓመታት ሃገሪቱን ያለ ካህንና ቤተ ክርስቲያን አስቀርቷት ነበር:: ብዙ ክርስቲያኖችም ሰልመው ቀርተዋል:: አፄ ልብነ ድንግል ግን ደብረ ዳሞ ገዳም ውስጥ ገብተው ንስሃ ጀመሩ: አለቀሱ: ተማለሉ::

እመቤታችን ተገልጣም "ይቅርታን በነፍስህ እንጂ በሥጋህ አታገኝም" አለቻቸው:: እርሳቸውም ሱባኤውን ቀጥለው: 'ስብሐተ ፍቁርን': 'መልክአ ኤዶምን' የመሰሉ መጻሕፍትን ደርሰው በዚህች ቀን በ ዓ/ም ዐርፈዋል:: እኛ ክርስቲያኖችም እናከብራቸዋለን::

የቅዱሳኑ አምላክ የወዳጆቹን ፈተና አስቦ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቡንም ከስደት ይሰውርልን:: ከበረከታቸውም አይለየን::

🕊

[  † መስከረም ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፪. ቅዱሳት አክሶስናና በርናባ
፫. ቅዱስ ማማስ ሰማዕት
፬. ቅዱሳን ቴዎዶስዮስና ታውፍና
፭. አቡነ አሮን መንክራዊ
፮. አፄ ልብነ ድንግል

[  †  ወርኀዊ የቅዱሳን  በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፭. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፮. ቅድስት አውጋንያ [ሰማዕትና ጻድቅ]

" ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን: ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን:: ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን::" [ሮሜ.፮፥፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

        †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                  🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን  †


[  † መስከረም [ ፮ ] 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †   ]

†   🕊  ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ  🕊  †

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢሳይያስን ያህል ትንቢት የተናገረ ነቢይ አይገኝም:: ከትንቢቱ ብዛትና ከምስጢሩ ጉልህነት የተነሳ: አንድም ደፋር ስለ ነበር 'ልዑለ ቃል' ተብሎ ተጠርቷል:: ቅዱስ ኢሳይያስ የተወለደው ከክርስቶስ ልደት ፰፻ [800] ዓመታት በፊት ሲሆን ለነቢይነት የተመረጠው ገና በወጣትነቱ ነበር::

ወላጆቹ  'ኢሳይያስ' [መድኃኒት] ያሉት በትምሕርቱ: በትንቢቱ የጸጋ መድኃኒትነት ስላለው ነው:: እርሱ በነቢይነት በተሾመበት ወራት ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ: ንጉሡ ደግሞ ዖዝያን ይባሉ ነበር:: በሊቀ ካህናቱና በንጉሡ መካከል በተነሳ ጠብ ንጉሡ የበላይነቱን ለማሳየት ሃብተ ክህነት ሳይኖረው ሊያጥን ወደ ቤተ መቅደስ ገባ::

ይህንን የተመለከተው ኢሳይያስ ሊገስጸው ሲገባ 'ወዳጄ ነው' በሚል ዝም አለው:: ፈታሒ እግዚአብሔር ግን ዖዝያንን በለምጽ መታው:: የግንባሩን ለምጽ በሻሽ ቢሸፍነው ከሻሹ ላይ ወጣበት:: በእሥራኤል ለምጽ ያለበት እንኩዋን በዙፋን ከተማ ውስጥም መቀመጥ አይችልምና አስወጡት:: በእርሱ ፈንታም ኢዮአታም ነግሷል::

ኢሳይያስ ደግሞ እግዚአብሔር በሰጠው አንደበት ሙያ አልሠራበትምና ከንፈሩ ላይ ለምጽ ወጣበት:: እርሱንም ወስደው ጨለማ ቤት ዘጉበት:: ሃብተ ትንቢቱንም ተቀማ:: ቅዱሳን ትልቁ ሃብታቸው ንስሃቸው ነውና በዚያው ሆኖ ንስሃ ገባ: ተማለለ: ጾመ: ጸለየ::

እግዚአብሔርም ንስሃውን ተመለከተለት:: ከዚያም ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ኢሳይያስ እግዚአብሔርን በረዥም [ልዑል] ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ: ኪሩቤል ተሸክመውት: ሱራፌል [፳፬ [24] ቱ ካህናተ ሰማይ] "ቅዱስ: ቅዱስ: ቅዱስ" እያሉ ሲያመሰግኑት ተመለከተ:: [ኢሳ.፮፥፩] (6:1)

አበው ሲተረጉሙ "አንተ ያፈርከው ዖዝያን እነሆ ሞተ:: እኔ ግን መንግስቴ የዘለዓለም ነው" ሲለው ነው ይላሉ:: ያን ጊዜ እግዚአብሔር "ወደ ሕዝቤ ማንን እልካለሁ?" አለ:: ኢሳይያስም "ጌታየ! እኔ ከንፈሮቼ የረከሱ አለሁ" አለው:: እግዚአብሔርም ሱራፊን ላከለት:: መልአኩም ፍሕም [እሳት] በጉጠት አምጥቶ ከንፈሩን ቢዳስሰው ነጻ:: ሃብተ ትንቢቱም ተመለሰለት:: ይኸውም የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ነው::

ከዚህች ቀን በኋላ ግን ኢሳይያስ የተለየ ሰው ሆነ:: ማንንም የማይፈራ እውነተኛ የልዑል ወታደር ሆነ:: ከኦዝያን በሁዋላ በየዘመናቸው 4ቱንም ነገሥታት ገሰጸ:: እነዚህም ኢዮአታም: አካዝ: ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው::

ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ፲፬ [14] ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከ ፻፹፭ ሺህ [185,000] በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ: ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት ፻፹፭ ሺህ [185] ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: [፩ነገ.፲፰፥፲፫] (18:13) , [፲፱፥፩]

ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበርና ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች: ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የሚል ነበር:: [ኢሳ.፯፥፲፬]

በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት:: "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ:: እንዳንተ ያለ ማንም የለም:: ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው:: 'ድንግል' የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን 'ወልድ-ወንድ ልጅ' የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ" አሉት::

ይሕንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም:: በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው:: ነቢዩም መጥቶ ንጉሡን አለው :- "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ::"

ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ: ደከመ:: ንጉሡ ወደ ፈጣሪ :- "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትሕ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ" ሲል ተማጸነ:: ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ::

ሕዝቅያስን በለው :- "ጸሎትህን ሰምቼ: ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብየ ምሬሐለሁ:: በዘመንህም ላይ ፲፭ [15] ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው" አለው:: ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይሕንኑ ነግሮ "እስከ ፫ ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ" አለው::

ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይሕ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው:: ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ ፲ [10] መዓርጋትን ወደ ሁዋላ መለሳት::

ልዑለ ቃል ቅዱስ ኢሳይያስ ለ ፸ [70] ዘመናት ሕዝቡን አስተምሮ: ነገሥታቱን ገስጾ: ፷፰ [68] ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ጽፎ አረጀ:: በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ምናሴ ግን ይባስ ብሎ ጣዖትን አቆመ: ለጣዖትም ሰገደ:: ቅዱሱ ይህንን ሲያደርግ ዝም አላለውም:: በአደባባይ ገሰጸው እንጂ::

በዚህ የተበሳጨ ምናሴም ሽማግሌውን ነቢይ በእንጨት መጋዝ ለሁለት አሰነጠቀው:: ቅዱስ ኢሳይያስ በዚህ ዓይነት ሞት በጐ ሕይወቱንና ሩጫውን ፈጸመ:: የተናገራቸው ትንቢቶች ግልጽ ስለ ሆኑ 'ደረቅ ሐዲስ' በመባል ይታወቃሉ::

ቸሩ አምላክ 'ደሃ ተበደለ: ፍርድ ተጉዋደለ' የሚሉ መምሕራን አባቶችን አይንሳን:: ከነቢዩም በረከቱን ይክፈለን::

[  † መስከረም ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ [ልዑለ ቃል]
፪. ቅድስት ሰብልትንያ ሰማዕት
፫. አባ ያዕቆብ ገዳማዊ
፬. ቅዱስ አናቲሞስ ኤዺስ ቆዾስ

[  †  ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል


" ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር:: ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች:: እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች:: እሺ ብትሉ: ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ:: እንቢ ብትሉ ግን: ብታምጹም ሰይፍ ይበላቹሃል:: የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯልና:: " [ኢሳ.፲፥፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን  †


[  † መስከረም 7 [ ፯ ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †  ]


እንኩዋን ለቅድስት ኤልሳቤጥ: ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊቅ እና አባ ሳዊርያኖስ ክቡር ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ


[  †  🕊 ቅድስት ኤልሳቤጥ  🕊  †  ]

በወንጌላዊው አንደበት የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከነገደ ሌዊ ነው:: ሐረገ ሙላዷም ከቅዱስ አሮን ካህን ወገን ይመዘዛል:: ከአሮን በቴክታና በጥሪቃ ወርዶ ሔርሜላ ላይ ይደርሳል::

ይህቺ ሔርሜላ የምትባል ደግ ሴት ማጣት ["ጣ" ጠብቆ ይነበብ] የሚባል የተባረከ ሰው አግብታ ፫ [3] ቡሩካት ልጆችን ወለደች:: የመጀመሪያዋን 'ማርያም' አሏት:: እርሷ ቅድስት ሰሎሜን ወለደች:: ሁለተኛዋን 'ሶፍያ' አሏት:: እርሷ ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደች::

ሦስተኛዋ ግን የተለየች ናት:: 'ሐና' ብለው ሰየሟት:: እርሷም የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ወለደች:: በዚህም መሠረት ድንግል ማርያም: ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሰሎሜ የእህትማማች ልጆች ናቸው::

ቅድስት ኤልሳቤጥ እድሜዋ በደረሰ ጊዜ ስም አጠራሩ የከበረ: ደግ ካህን ለሆነ: ለቅዱስ ዘካርያስ አጋቧት:: እርሷ የሊቀ ካህናቱ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር:: ምንም ልጅ ባይኖራትም ዘወትር በጸሎትና በጾም: ምጽዋትንም በማዘውተር: ነዳያንንም በማሰብ የምትኖር እናትም ነበረች::

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: [ሉቃ.፩፥፮] (1:6)

የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ [አድናቆት] ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ፺ [90] የዘካርያስ ፻ [100] ደግሞ ደርሶ ነበር::

ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው:: ቅድስቲቷ መስከረም ፳፮ [26] ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች::

ድንግል እመቤታችን ወደ እርሷ መጥታ 'ሰላም' ባለቻት ጊዜ ምንም ያሳደገቻት ልጇ ማለት ብትሆን: መንፈስ ቅዱስ ስለ ሞላባት እመ ብርሃንን አመስግናታለች:: ቡርክት: ብጽእት: ከፍጥረተ ዓለሙ የከበረች መሆኗንም መስክራለች::

በማሕጸኗ ያለ የ፮ [6] ወር ጽንስም የእመ አምላክን ድምጽ ቢሰማ በደስታ ዘሏል:: ለፈጣሪውም ስግደተ-ስባሔ አቅርቧል:: ቅድስት ኤልሳቤጥ አክላም "ወምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ-የጌታየ እናቱ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይገባኛል?" ስትል በትኅትና ተናግራለች:: ከጌታ እናት ጋር ለ፫ [3] ወራት በአንድ ቤት ቆይታለች::

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ፪ [2] ዓመት ከ፮ [6] ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ፫ [3] ፭ (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ ፭ [5] ፯ (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት:: ኤልሳቤጥ ማለት 'እግዚአብሔር መሐላየ ነው': አንድም 'የጌታ አገልጋይ' ማለት ነው::


[ † 🕊 ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊቅ  🕊 †  ]

ይህ አባት የተዋሕዶ ሃይማኖታችን ምሰሶ ነው:: በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን በግብጽ ተወልዶ አድጐ: በልጅነቱ መጻሕፍትን ተምሮ: የምናኔ ሕይወትን መርጧል:: ቆይቶም የታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ ረድእ ሆኖ ተምሯል: አገልግሎታል::

በጉባኤ ኤፌሶን ጊዜም ቅዱስ ቄርሎስን ተከትሎ ሒዶ ተሳትፏል:: በ፬፻፵፬ [444] ዓ/ም ታላቁን ሊቅ ተክቶ የእስክንድርያ ፳፭ [25] ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሹሟል:: ለ፯ [7] ዓመታትም መጽሐፈ ቅዳሴውን [እምቅድመ ዓለምን] ጨምሮ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: በመልካም እረኝነትም ሕዝቡን ጠብቇል::

ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለ፻፶ [150] ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::

በ፬፻፶፩ [451] ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ዻዻሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፪ [2] ተከፈለች::

በጉባኤው የነበሩ ፮፻፴፮ [636] ዻዻሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" [ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ] ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" [የውሾች ስብሰባ]: "ጉባኤ አብዳን" [የሰነፎች ጉባኤ] ተብሏል::

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ወደ ጋግራ ደሴት ከ፯ [7] ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት:: በዚያም ለ፫ [3] ዓመታት ቆይቶ በ፬፻፶፬ [454] ዓ/ም ዐረፈ::

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከማረፉ በፊት በተሰደደባት ደሴተ ጋግራ ለ፫ [3] ዓመታት ብዙ መከራ ከመናፍቃን ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱና በትምሕርቱ ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሷል::

ቤተ ክርስቲያን እርሱን 'አበ ተዋሕዶ' [የተዋሕዶ እምነት አባትና አርበኛ] ትለዋለች:: የተነጨ ጺሙ: የረገፉ ጥርሶቹና የፈሰሰ ደሙ ዛሬም ድረስ ትልቅ ምስክርና የሃይማኖት ፍሬ ነውና::
"ያስተጻንዕ ህየ እለ ኀለዉ ደቂቀ:
ዘተነጽየ እምነ ጽሕሙ ወእም አስናኒሁ ዘወድቀ:
ፍሬ ሃይማኖቱ ፈነወ ብሔረ ርሑቀ" እንዲል::


[  † 🕊 ታላቁ አባ ሳዊርያኖስ  🕊 †  ]

የዚህን ቅዱስ ሰው ስም የሚጠራ አፍ ክቡር ነው:: ጣዕመ ሕይወቱ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም:: እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የበቀለ: ፴ ፡ ፷ : ፻ [30: 60: 100] ፍሬዎችን ያፈራ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ነው:: በትውልድ ሮማዊ ሲሆን የተወለደው በ፫፻፱ [309] ዓ/ም ነው::

ወላጆቹ በዚህ የንጉሥ ዘመዶች: በዚያ ደግሞ ባለጠጐች ነበሩ:: እነርሱ ለልጃቸው ጥበብን መርጠዋልና የግሪክን ፍልስፍና: የዮናናውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ:: ከዚያ በአንድ ልቡ ብሉይን: ሐዲስን ተምሮ ሲጠነቅቅ ወላጆቹ ዐረፉ::

ቅዱሱ ሳዊርያኖስም "የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት አለብኝ" ብሎ ቀን ቀን ያለፈውን: ያገደመውን ሁሉ ሲያበላ: ሲያጠጣ: ነዳያንን ሲጐበኝ ይውላል:: ምሽት ሲል ደግሞ ወደ ቅዱሱ ንጉሥ [አኖሬዎስ] ቤተ መንግስት ገብቶ: ወገቡን ታጥቆ ከንጉሡ ጋር ሲጸልይና ሲሰግድ ያድራል::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ውዳሴ ከንቱ ሲበዛበት ንብረቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ገብላ ወደምትባል ሃገር ሒዶ መነኮሰ:: ባጭር ጊዜም የብዙ ነፍሳት አባት ሆነ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የገብላ [ኤላ] ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: በዘመነ ሲመቱም እንቅልፍን አልተመለከተም:: ባጭር ታጥቆ ያላመኑትን ለማሳመን ደከመ እንጂ::

ጌታ ከእርሱ ጋር ነውና አይሁድን: መተተኞችንና አሕዛብን ሁሉ አሳምኖ ኤላ [ገብላ] አንድ የክርስቶስ መንጋ ሆነች:: የሚገርመው ከደግነቱ የተነሳ ሰይጣንን እንዳይገባ ከልክሎት በመንገድ ላይ ቁሞ ሲያለቅስ ይታይ ነበር:: ቅዱስ ሳዊርያኖስ ብዙ ድርሳናትን ደርሶ: እልፍ ፍሬንም አፍርቶ: በተወለደ በ፻ [100] ዓመቱ በ፬፻፰ [408] ዓ/ም ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

የእነዚህ ሁሉ ከዋክብት ቅዱሳን አምላክ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን:: ክፉውንም ሁሉ ያርቅልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[  †  መስከረም ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ
፪. ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊቅ [የተዋሕዶ ሃይማኖት አባት]
፫. ታላቁ ቅዱስ ሳዊርያኖስ
፬. ቅድስት ሐና [የእመ ብርሃን እናት-ልደቷ ነው]
፭. ቅዱሳን አጋቶን: ዼጥሮስ: ዮሐንስ: አሞንና እናታቸው ራፊቃ [ሰማዕታት]

[   †  ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [ የባሕታውያን አለቃ ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯. ቅዱስ አግናጥዮስ [ ለአንበሳ የተሰጠ ]

" ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማሕጸኗ ውስጥ ዘለለ:: በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት:: በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች:- 'አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ: የማሕጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው:: የጌታየ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? . . . ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብጽዕት ናት::" [ሉቃ.፩፥፵፩] (1:41)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

[  መስከረም ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]


†   🕊  ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት  🕊  †

ቅዱሳን ነቢያት እጅግ ብዙ ናቸው:: ከፈጣሪያቸው የተቀበሉት ጸጋም ብዙና ልዩ ልዩ ነው:: ያም ሆኖ ከሁሉም ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ይበልጣል:: መጽሐፍ እንደሚል ከእርሱም በፊት ቢሆን ከእርሱ በሁዋላ እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሳምና:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ዓለም በተፈጠረ በ፫ ሺህ ፮ መቶ [3,600] ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት ፸፭ [75] ራሱን ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ተከብረው: ለ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ደግሞ በባርነት: በድምሩ ለ፬፻፴ [430] ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል::

በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ ፪ [2] ከተሞችን [ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን] ገንብተዋል:: ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ:: ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል::

ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ 'እንበረም'ና 'ዮካብድ' ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው:: ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል:: ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይፈጁ ነበር:: ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል::

በኋላም በ፫ [3] ወሩ ዓባይ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት [የፈርኦን ልጅ ናት] ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: 'ሙሴ' ያለችውም እርሷ ናት:: 'ዕጉዋለ ማይ / እማይ ዘረከብክዎ' [ከውሃ የተገኘ] ለማለት ነው:: ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል:: ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና::

ቅዱስ ሙሴ ፭ [5] ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል:: እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው ፵ [40] ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ:: ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና:: [ዕብ.፲፩፥፳፬] (11:24)

አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ:: በዚያም ለ፵ [40] ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ: ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ:: ልጆንም አፈራ:: ፹ [80] ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው:: ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው::

ቅዱስ ሙሴም ከወንድሙ አሮንና ከአውሴ [ኢያሱ] ጋር ግብጻውያንን በ፱ [9] መቅሰፍት: በ፲ [10] ኛ ሞተ በኩር መታ:: እሥራኤልንም ነጻ አወጣ:: ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም::

- እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል::
- ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል::
- ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል::
- ውሃን ከጨንጫ [ከዓለት] ላይ አፍልቁዋል::
- በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል::
- በ7 ደመና ጋርዷቸዋል::
- ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል::

ስለዚህ ፈንታ ግን ወገኖቹ ብዙ አሰቃይተውታል:: እርሱ ግን ደግ: ቅንና የዋህ ሰው ነውና ብዙ ጊዜ ራሱን ለእነሱ አሳልፎ ሰጥቷል:: "ሙሴሰ የዋህ እምኩሎሙ ደቂቀ እሥራኤል" እንዲል:: [ዘኁ.፲፪፥፫] (12:3) ቅዱስ ሙሴ ለ፵ [40] ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ፭፻፸ [570] ጊዜ ተነጋግሯል::

ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር:: ታቦተ ጽዮንንና ፲ [10]ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል:: "የቀረው የቅዱሱ ሕይወት በመጻሕፍተ ኦሪት [በብሔረ ኦሪት] ውስጥ የተጻፉ አይደሉምን?"

እኔ ግን ደካማ ነኝና ይህቺ ትብቃኝ:: ቅዱስ: ክቡር: ታላቅ: ጻድቅ: ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ፻፳ [120] ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል: ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል:: መቃብሩንም ሠውረዋል:: [ይሁዳ.፩፥፱] (1:9)


†   🕊  ቅዱስ ዘካርያስ ካህን  🕊   †

ስም አጠራሩ የከበረ: ሽምግልናውም ያማረ ቅዱስ ዘካርያስ የቅድስት ኤልሳቤጥ ባል: የመጥምቁ ዮሐንስም አባት ነው:: በእሥራኤል ታሪክ የመጨረሻው ደግ ሊቀ ካህናት ነው:: ይህ ቅዱስ ሰው ከአሮን ወገን ተወልዶ: በሥርዓተ ኦሪት አድጐ: በወጣትነቱ መጻሕፍተ ብሉያትን ተምሮ: ሊቀ ካህንነቱን እጅ አድርጉዋል::

በጐልማሳነቱም ቅድስት ኤልሳቤጥን አግብቶ በደግነትና በምጽዋት አብሯት ኑሯል:: ከኢያቄምና ከሐና ጋር ቅርብ ወዳጆች ነበሩና አልተለያዩም:: ቅዱሱ ዘወትር ለማስተማር: ለመስዋዕትና ለማዕጠንት ይተጋ ነበር:: ጸሎቱና እጣኑም ወደ ቅድመ እግዚአብሔር ይደርስለት ነበር::

እስኪያረጅ ድረስ ባይወልድም አላማረረም:: ደስ የሚለው ደግሞ እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን ከወላጆቿ ተቀብሎ ለ፲፪ [12] ዓመታት ያሳደጋት እርሱ ነው:: ዘወትር መላእክት ከበው ሲያገለግሏት እየተመለከተ ይመሰጥ ነበረ::

የልጅ አምሮቱን የሚረሳው ከእርሷ ጋር ሲሆን ነው:: እንደ አባት አሳደጋት: እንደ እመቤትም ጸጋ ክብር አሰጥታዋለች:: እድሜው መቶ ዓመት በሆነ ጊዜ በቅዱስ ገብርኤል ተበስሮ ዮሐንስን አገኘ:: ለ፱ [9] ወራት የተዘጋ አንደበቱ ሲከፈት "ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እሥራኤል" ብሎ ትንቢትን ተናገረ::

ሔሮድስ ሕጻኑን ሊገድለው በፈለገ ጊዜም ሕጻኑን ቅዱስ ዮሐንስን ወስዶ በክንፈ ኪሩብ ላይ አስቀመጠውና መልአክ ወደ በርሃ ወሰደው:: ቅዱስ ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደሱ መካከል ፸: ፹ [70: 80] ዓመት በንጽሕና ባገለገለበት ቦታ ላይ ገደሉት::

ሥጋውን አምላክ ሰውሮት የፈሰሰ ደሙ እንደ ድንጋይ ረግቶ ሲጮህ ተገኝቷል:: ለ፷፰ [68] ዓመታትም ደሙ ሲፈላ ኑሯል:: በ፸ [70] ዘመን ጥጦስ ቄሣር አይሁድን ሲያጠፋቸው ደሙ ዝም ብሏል:: ይህ ቅዱስ: ጻድቅ: ነቢይና ካህን ስሙ በተጠራ ጊዜ ሲዖል ደንግጣ ነፍሳትን እንደምትሰጥ ሊቃውንት ነግረውናል:: [ማቴ.፳፫፥፴፭] (23:35)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
......................................................

†   🕊   ቅዱስ አሮን ካህን    🕊   †

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የቅዱሱ ካህን የአሮን በትር ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት ለምልማ: አብባ: አፍርታ የተገኘችው በዚህ ቀን ነው:: ዳታን: አቤሮንና ቆሬ ከተከታዮቻቸው ጋር በፈጠሩት ሁከት ምድር ተከፍታ ከዋጠቻቸው በሁዋላ እግዚአብሔር የ፲፪ [12]ቱን ነገደ እሥራኤል በትር ሰብስቦ ሲጸልይበት እንዲያድር ሙሴን አዞት: እንዲሁ ሆነ::

በነጋም ጊዜ ይህቺ ደረቅ የነበረች በትረ አሮን 12 ፍሬ [ለውዝ: ገውዝ: በኩረ ሎሚ] አፍርታ ተገኘች:: [ዘኁ.፲፯፥፩-፲፩] (17:1-11) ለጊዜው ክህነት ከቤተ አሮን እንዳይወጣ ምልክት ሆናለች:: ለፍጻሜው ግን ምሳሌነቷ ለድንግል ማርያም ነው:: እመ ብርሃን የወንድ ዘር ምክንያት ሳይሆናት አምላክን ወልዳ ተገኝታለችና::

" ጸናጽል ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን: ወዓዲ በትር እንተ ሠረጸት: ወጸገየት: ወፈረየት" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: [ ቅዳሴ ማርያም ]

የእነዚህ ቅዱሳን ነቢያትና ካህናት አምላክ ደግነታቸውን አስቦ: ከግራ ቁመት: ከገሃነመ እሳትም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

[ †  መስከረም ፰ [  8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ቅዱስ ዘካርያስ ካህን (ጻድቅ ነቢይ)
፫. ቅዱስ አሮን ካህን
፬. ቅዱስ ዲማድዮስ ሰማዕት

" ሙሴ ካደገ በሁዋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ:: ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና:: ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ:: ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና::" [ዕብ.፲፩፥፳፬] (11:24)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
2024/09/27 20:18:34
Back to Top
HTML Embed Code: