Telegram Web Link
Forwarded from Dawit Gebeyehu
ጉባኤ ኒቆዲሞስ 3.jpg
1.1 MB
Forwarded from Nahom
ሰላም እንዴት አደራችሁ? በየወሩ በአባታችን በኒቆዲሞስ ስም የምንሰባሰብበትና ቃለ እግዚአብሔርን የምንማማርበት እንዲሁም በመንፈሳዊ መርሀግብራት ጥሩ ትምህርት የምንወስድበት ጉባኤ ኒቆዲሞስ ነገ ሐሙስ 2/11/16 ይካሄዳል። ስለዚህ ከአሁኑ ቀጠሮአችሁን አስተካክሉና ነገ 11፡45 ላይ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ እንገናኝ። (የ 2016 ዓ.ም የመጨረሻ ጉባኤ ኒቆዲሞስ መሆኑንም አስቡ)።
Forwarded from Nahom
በነገራችን ላይ አባታችን ቅዱስ ኒቆዲሞስ ዛሬ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው ረድኤት በረከቱ ይደርብን።
✍️"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡
ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮኽ እንደ ሰማ ኹሉ ይደነግጣል፤ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፤ ባንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፤ ከፍጡራን ወገኖች ኹሉ ይልቅ ሰይጣን አንቺን ይጠላል"

📌ምንጭ
📚 አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
የውዳሴ ማርያም መተርጕማን እንደሚያስተምሩት ቅዱስ ኤፍሬም ቢረሌ፣ መርጠብ፣ ብርጭቆ፣ ኩዝ፣ ካቦ እየሠራ የዓመት ልብሱን የዕለት ምግቡን
እያስቀረ ይመፀውት ነበር፡፡ ሲመፀውትም በሥላሴ፣ በመላእክት፣ በጻድቃን ወይም በሰማዕታት ስም አይመፀውትም፤ በእመቤታችን ስም ይመጸውት ነበር እንጂ፡፡ ከእናንተ መካከል “ንቋቸው አጥቅቷቸውን ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ በፍጹም! ንቋቸው፤ አጥቅቷቸውም አይደለም፡፡ የእመቤታችን
ፍቅር ባያደርሰው ነው እንጂ፡፡ በመኾኑም እመቤታችንን እጅግ ከመውደዱ
የተነሣ ኹል ጊዜ “ምነው የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ፤ እንደ
ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ፤ እንደ ልብስ ለብሼው፤ እንደ ምግብ ተመግቤው
ጠግቤው በበዛልኝ” እያለ ይመኝ ነበር፡፡ ያሹትን መግለጽ ለእግዚአብሔር
ልማዱ ነውና ገልጾለት አስቀድመን እንደተናገርነው “አኃዝ እግዚኦ መዋግደ
ጸጋከ- አቤቱ የጸጋህን ሞገድ ግታልኝ” እስኪል ድረስ 14 ሺሕ ድርሳናትንና ተግሳጻትን ደርሷል፤ የሚጸልየውም ጸሎት ከሉቃስ ወንጌል “በ6ኛው ወር ገብርኤል መልአክ” ከሚል አንሥቶ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን አውጥቶ 64
ጊዜ ይጸልይ ነበር /ሉቃ.1፥26/፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ግን (ዕለቱ ሰኑይ
ጊዜው ነግህ ነው) የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ
እመቤታችን መጣች፡፡ የብርሃን ምንጣፍ ተነጥፏል፡፡ የብርሃን ተዘርግቷል፡፡
ከዚያ ላይ ኹናም “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” አለችው፡፡ እሱም ታጥቆ
እጅ ነሥቶ ቆመ፡፡ “ወድሰኒ” አለችው፡፡ እዚህ ጋር አንዳንድ ልበ ስሑታን የሚያነሡት ጥያቄ ስላለ መልስ ሰጥተንበት እንለፍ፡፡ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን “አመስግነኝ” ስላለችው ክብር፣ ውዳሴ፣ ልዕልናን የፈለገች መስሏቸው “ማርያም በፍጹም እንዲህ አታደርግም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃት ማርያም ትሑት ናት” የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ኤፍሬም “ምነው የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ፤ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ፤ እንደ ልብስ ለብሼው፤ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው በበዛልኝ” እያለ ይመኝ ስለ ነበር እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰምቶለት እንጂ እመቤታችን ልዕልናን ፈልጋ አመስግነኝ ያለችው አይደለም፡፡ እመቤታችንን የሚቀድስ ማንኛውም ሰው በእመቤታችን ላይ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለም፡፡ እርሱ ይከብራል፤ የሰሙትም ኹሉ ይከብራሉ እንጂ /ቅዳ.ማር. ቁ.172/፡፡

ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደረሰ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ውዳሴ ማርያምን ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፤ ኤፍሬም ለብሐዊ ተናግሮታል። ሶርያዊ በሀገሩ ነው፤ ለብሐዊ በተግባሩ ይሰኛል። ይህም ቅዱስ ኤፍሬም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀመዝሙር ነው። ያዕቆብ ዘንጽቢንም ቁጥሩ ከሠለስቱ ምእት ነው። ለአውግዞተ አርዮስ ሲሄድ አስከትሎት ሂዶ ነበር። አርዮስን አውግዘው ሃይማኖት መልሰው ተመልሰው ካደሩበት ቦታ ዐምደ ብርሃን ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ሌሊት በሕልሙ ራእይ ያያል። ራእዩን እንደ ገለጽክልኝ ባለቤቱንም ግለጥልኝ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ነው። ለቤተክርስቲያን ዐምድ ጽንዕ ነውና ፤ በትምህርቱ የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋልና እንዲህ ባለ አርአያ አየኸው አለው። ባስልዮስም ቁጥሩ ከሠለስቱ ምእት ነው። መምህርን ካወጡበት ሳያገቡ ትቶ መሄድ ፈሊጥ (ሥርዓት) አይደለምና መምህሩን ካወጣበት አግብቶ ስለ ሦስት ነገር ይሄዳል፤ መጀመሪያ እንዲህ ካለ ሰው ጋር ቢጫወቱ መንፈሳዊ ነገር ይገኛልና ብሎ ሁለተኛ በጆሮ የሰሙትን በዐይን ቢያዩት ይረዳልና ብሎ ሦስተኛ የመንፈስቅዱስ ነው ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን ብሎ ሄደ። ነገር ግን ሲደርስ እንዳየው ሆኖ አላገኘውም። በወርቅ ወንበር ተቀምጦ በወርቅ አትሮንስ የወርቅ ወንጌል አዘርግቶ ካባ ላንቃ ለብሶ ኩፋር ጠምጥሞ መነሳንሱን ቢያዩ የሐር፤ መያዣውን ቢያዩ የወርቅ መነሳንስ ይዞ ሲያስተምር አግኝቶታል። ቅዱስ ኤፍሬምም ለመንፈስቅዱስ ሁለት ግብር አለውን? ብሎ ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ አራት ነገር አይቶ ተረድቷል። 
መጀመሪያ ከአፉ ነጸብራቀ እሳት እየወጣ ሕዝቡን ሲዋሀዳቸው ያያል፤ ይህም ትምህርቱ ነው።

ሦስተኛ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ እያረፉ እንደ ቆሎ ሲረግፉ ያያል።
ይህን መናፍቃን ፍጡር ፈጣሪ ይመስል ያቃጥላልን ብለው እንቃወማለን ይላሉ ቅዱስ ባስልዮስ ከከዊነ እሳት ማዕረግ ደርሶ ነበርና ያቃጥላል።

አራተኛ "ስሙን ያያውቅ ሀገሩን ያይጠይቅ ኤፍሬም ሶርያዊ ኤፍሬም ለብሐዊ ብላችሁ ጥሩልኝ ከማዕዝነ ቤተክርስቲያን ባንዱ ቁሞ ይጸልይላችኋል" ብሎ አስጠርቶ በአስተርጓሚ ሲጫወቱ ጨዋታው ባይከተትለት አባቴ ጸልይና ያንተ ቋንቋ ለእኔ ይገለጥልኝ አለው። ጸልዮ የባስልዮስ ቋንቋ ጽርዕ ነው፤ ለኤፍሬም የኤፍሬም ቋንቋ ሱርስት ነው ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ሲጫወቱ አድረው ሲነጋ አሰናብተኝ ልሂድ አለው። መች ልትሄድ አምጥቶሃላ ልትኖር ነው እንጂ ብሎ ሕዝባዊ ነው ቢሉ ዲቁና ዲያቆን ነው ቢሉ ቅስና ሹሞ ከሀገረ ስብከቱ ሀገር ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጠው።

ባስልዮስም ይህን መልበሱ ስለ ክብረ ወንጌል ነው ዛሬ ካህናት አክሊል ደፍተው ኩፋር ጠምጥመው ካባ ላንቃ ለብሰው ሥጋውን ደሙን እንዲያከብሩ እንዲለውጡ እርሱስ በውስጥ የሚለብሰው ማቅ ነበር። ከዚህ በኋላ ከአዋልደ ነገሥት የምትሆን አንዲት ሴት ነበረች። ኃጢአቷን እየጻፈች የምታኖር። ስለምን ቢሉ ለመንገር ብትፈራ። አንድም ቢበዛ አንድ ቀን መጥታ እንደ ተጠቀለለ ይዛ አባቴ በዚህ ያለው ይፋቅልሽ በለኝ አለችው። ይፋቅልሽ አላት ገልጣ ብታይ አንዲት ቀርታ አየች፤ ይህችንሳ አለችው። ይህስ ለቅዱስ ኤፍሬም ቢቻል እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት። አሁን ለርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም። ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ከሚገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና። ዳግመኛም ስትመጥ ስትሄድ ድካም ያለባት ነውና ቀኖና ይሁናት ብሎ ነው። ሄዳ አባቴ በዚህ ያለው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ በለኝ አለችው። ይህስ ለሊቀጳጳሱ ለባስልዮስ ቢቻለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም አላት። አሁን ለርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም። ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ከሚገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና ነው። 
ዳግመኛም ስትሄድ ስትመጣ ድካም ያለባት ናትና ቀኖና ይሁናት ብሎ። ስትሄጅ ግን እንደቀደመው በሕይወተ ሥጋ አታገኚውም ሙቶ ሊቀብሩት ይዘውት ሲሄዱ ታገኛለሽ ሳትጠራጠሪ ካስክሬኑ ላይ ጣይው ይፋቅልሻል አላት።ብትሄድ ሞቶ ሊቀብሩት ይዘውት ሲሄዱ አገኘት። ሳትጠራጠር ከአስክሬኑ ላይ ብትጥለው ተፍቆላታል። ይህም የካህናትን መዓርግ ደግነት ያጠይቃል። በሕይወተ ሥጋም ሳሉ ከሞቱም በኋላ ኃጢአት እንደሚያስተሰር። ስምዖን ዘዓምድ የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀመዝሙር ነው። አብሮት ተምመሯል። ሊጠይቀው መጣ። ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል እያለ ሲያስተምር ሰማው። ኦ እግዝእትየን ከማን አገኘሐው መምህራችን ለእነገረን አለው። ነግሮናል እንጂ አልነገረንም ይመስክር ይመስክር ተባብለው ከመቃብሩ ላይ ቢሄዱ ዐሥሩ ጣቶቹ እንደፋና እያበሩ ተነስቶ "በሕይወትየ እብለኪ ሠላም ለኪ፤ ኦ ቅድስት ድንግል ከመ ስምዖን ዘዓምድ። ወድኅረ ሞትየሰ ኵሎሙ አዕዕምትየ ይብሉኪ ወይዌድሱኪ ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል ከመ ኤፍሬም ሶርያዊ" ብሎ መስክሮላታል።
ይህም ለቅዱስ ኤፍሬም ጸጋው ክብሩ ነው። ከሞተ በኋላ የሚናገረውን ዐውቆ ማመስገን። ሶርያዊ በሀገሩ ያሰኘው እስከዚህ ነው። ለብሐዊ በተግባሩ ሞ ቢረሌ መርጠብ ብርጭቆ ኩዝ ካቦ እየሰራ የዓመት ልብሱን የዕለት ምግቡን እያስቀረ ይመጸውት ነበር። ሲመጸውትም በሥላሴ በመላእክት በጻድቃን ስም አይመጸውትም በእመቤታችን ስም ይመጸውት ነር። ስለምን ነው ቢሉ የእመቤታችን ፍቅር ባያደርሰው ነው።
እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሳ እመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደመባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እያለ ሲመኝ ይኖር ነበር። የሻቱትን መግለጽ ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና ገልጾለት ከአራት ሺህ በላይ ድርሰት ደርሷል።

ከዕለታት በአንድ ቀን በዕለተ ሰኑይ ጊዜው ነግህ ነው የነግህ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን ትመጣልች። የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል የብርሃን ድባብ የዘረጋል። ከዚያም ላይ ሁና "ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም" ትለዋለች። እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል። ወድሰኒ ትለዋለች። "ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ሰማያውያን መላእክት አንቺን ማመስገን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል?" አላት። "በከመ አለበወከ መንፈስቅዱስ ተናገር" አለችው። በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና። "እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ(ይህ ነገር አንደምን ይሆንልኛል?) ብትለው መልአኩ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ (መንፈስቅዱስ ይጸልልሻል)" ብሏት ነበርና። ከዚህ በኋላ ባርክኒ ይላታል። በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ ትለዋለች። ተባርኮ ምስጋናዋን ይጀምራል።

ሲያመሰግናትም ደቀመዝሙር ቅኔ ቆጥሮ እንዲቀኝ ድርሰት አስቦ እንዲጽፍ አይደለም። ብልህ ደቀመዝሙር ያጠናውን ቀለም ከመምህሩ ፊት ሰተት አድርጎ እንዲያደርስ እንደዚያ ነው እንጂ። ስታስደርሰውም ከሰባት ከፍላ አስደርሳዋለች። ስለምን ቢሉ በሰባቱ ዕለታት መመስገን ፈቃዷ ቢሆን አንድም ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዋ ናቸውና በዕለተ እሑድ ትመሰላለች፤።
በዕለተ እሑድ አሥራወ ፍጥረታት፤ አራቱ ባሕርያት ተገኝተዋል። ከሷም ለዘኮነ ምክንያተ ፍጥረት በሕላዌሁ እንዲለው አሥራወ ፍጥረት ጌታ ተገኝቷልና። በዕለተ ሰኑይ ትመሰላለች፤።

በዕለተ ሰኑይ ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ መልቶ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎታል። አንዱን እጅ ከላይ ሰቅሎታል ሐኖስ ነው። አንዱን እህ በዙሪያው ወስኖታል። አንዱን እጅ አጽንቶ የብርሃን ማኅደር አድርጎታል፤ ጠፈር ነው። ጠፈር የእመቤታችን፤ ብርሃን የጌታችን ምሳሌ ነው። ይህማ ጠፈር ምሳሌ ሆነች እንጂ የዕለቲቱ ምሳሌ ሆነቻ ብሎ ዕለቲቱ የእርሷ ጠፈር ከእርሷ የነሳው ሥጋ ብርሃን የጌታችን ምሳሌ አድርጎታል።
በዕለተ ሠሉስ ትመሰላለች፤ በዕለተ ሠሉስ “እግዚአብሔርም፦ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ እንዲሁም ሆነ።” እንዳለ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፤ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት በማጭድ የሚታጨዱ አዝርዕት ለሥጋውያን ምግብ እንዲሆኑ ተገኝተዋል። ከእርሷም የመንፈሳውያን ምግብ የሚሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷልና።

በዕለተ ረቡዕ ትመሰላለች። በዕለተ ረቡዕ ለይቁሙ ብርሃናት በገጸ ሰማይ ባለ ጊዜ ለሥጋውያን ምግብ የሚሆኑ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተገኝተዋል። ከእርሷም ለመንፈሳውያን ምግብ የሚሆን ጌታ ተገኝቷልና።

በዕለተ ሐሙስ ትመሰላለች። በዕለተ ሐሙስ “እግዚአብሔርም አለ፦ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ” እንዳለ በእግራቸው የሚሽከረከሩ፣ በክንፋቸው የሚበሩ በልባቸው የሚሳቡ በደመነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል። ከሃ ተገኝተው በረው በረው የሄዱ አሉ ፤ ከውሃ ከዚያው የቀሩም አሉ። በረው በረው የሄዱት ያልተጠመቁ (ኢጥሙቃን) ምሳሌ ሲሆን ከውሃው የቀሩት የተጠመቁ (የጥሙቃን) ምሳሌ ነው። በልባቸው የሚሳቡ የሰብአ ዓለም፤ በእግራቸው የሚሽከረከሩ ከትሩፋት ወደ ትሩፋት የሚሄዱ የባሕታውያን፤ በክንፋቸው የሚበሩ ተመስጦ ያላቸው የሰማዕታት ምሳሌ፤ ዕለቲቱ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ ባሕር የጥምቀት፣ ምሳሌ ነው።

በዕለተ ዐርብ ትመሰላለች። በዕለተ ዐርብ በኵረ ፍጥረት አዳም ተገኝቷል፤ ዳግማይ አዳም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ተገኝቷልና በዕለተ ዐርብ ትመሰላለች።

በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት ትመሰላለች። በዕለተ ቀዳሚት ሥጋዊ ዕረፍት ተገኝቷል። “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ” እንዲል ከእርሷም የመንፈሳውያን ዕረፍት ጌታ ተገኝቷልና።

አዳኝ ከሆነው ልጅሽ እመቤታችን ጽንዕት በድንግልና ፀጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን።

#ጽንዕት #በድንግልና #ሥርጉት #በቅድስና #እመቤታችን #ጸጋውን #ክብሩን #እንዳይነሳን #ለምኚልን#አእምሮውን #ልቡን #በልቡናችን #ሳይብን #አሳድሪብን::




አዘጋጅ ፦ ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ
💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️
Forwarded from M.A
#የሐሙስ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡

  ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡

ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ

https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_14.html?m=1
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ †  እንኩዋን ለቅዱሳት እናቶቻችን አትናስያ እና ኢዮዸራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  † ]

†  🕊   ቅድስት አትናስያ   🕊  †

የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም መኑፍ በሚባል አውራጃ በ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ::

ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ: እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: መንፈስ ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች::

መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች::

ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት: ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች::

በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር:: በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ::

እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ" ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው::

የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች::

ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም  ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነውና::

እነርሱ ሱባኤ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ ቀረባት:: [መዝ.፳፪] (22)

ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::

ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች::

ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ::

መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: "የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ::

ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ ፯ [7] ጊዜ ይወድቃልና: ፯ [7] ጊዜ ይነሳል::"


†  🕊  ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል  🕊

ይህቺ ቅድስት እናት የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔው የገባችው ገና በ፮ [6] ዓመቷ ነው:: አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮዸራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብፅ ገዳማት ይሔዳሉ:: በዚያ ደናግል ጌታችንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች::

ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት:: የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች:: እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሂድ" ብትላትም ያቺ የ፮ [6] ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም" አለቻት::

እናት የሕጻን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሺው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላም እናት ታማ ዐረፈች:: ቅድስት ኢዮዸራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች::

ትዕግስት: ትሕትና: ፍቅር: ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ:: እህል የምትቀምሰው በ፯ [7] ቀን አንዴ ብቻ ሆነ:: ለጸሎት ስትቆምም እስከ ፵ [40] ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር:: ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት::

በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር:: እርሷ ግን ታገሰችው:: እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች:: በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግስቱ በቃች:: ድንግል ኢዮዸራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ::

የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው: ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  †  ነሐሴ ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅድስት አትናስያ ቡርክት
፪. ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል
፫. ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት

[   †  ወርኀዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪. ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫. ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬. ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ [ታላቁ]
፭. ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮. አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
፯. ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ [ከ ፲፪ [12]ቱ ሐዋርያት]

" ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ_ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" [፩ጢሞ.፩፥፲፭] (1:15)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ነሐሴ ፪ (2) ቀን።

እንኳን #በአባ_ዮሐንስ_ሐጺር ምክር ለንስሐ በቅታ ከዘማዊነት ለተመለሰች #ለቅድስት_አትናስያና ከነገሥታት ወገን ለሆነች #ለቅድስት_ኢዮጰራቅስያ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከዲያቆናዊት_ኢዮኤልያና ዕረፍት፣ #ከሰማዕቱ_ደሚናና ሰማዕታት ከሆኑ ወንድሞቹ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                           
#ቅድስት_አትናስያ፦ የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።

ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።

እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም "ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ" አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር "በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና"። ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ "ለምን ታለቅሳለህ" አለችው እርሱም "ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና" አላት።

ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች "ምን ይሻለኛል" አለችው "ንስሐ ግቢ" አላት እርሷም "እግዚአብሔር ይቀበለኛልን" አለችው እርሱም "አዎን" አላት እርሷም "ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ" አለችው እርሱም "ነዪ ተከተይኝ" አላት። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ "እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ" አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።

በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አትናስያ በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                          
#ድንግሊቱ_ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ፦ የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ ዐረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ "ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ" አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ ዐረፈችና ቀበሩዋት።

ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጣንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።

ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።

ከዚህም በኋላ ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ። ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።

በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና ነሐሴ 2 ቀን በሰላም ዐረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።

ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን ዐረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ደናግል በቅዱሳት ኢዮጰራቅስያና ኢዮኤልያ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 2 ስንክሳር።

                           
"#ሰላም_ለአትናስያ_ለተሊወ_ክርስቶስ_ፌማ። በምክረ ዮሐንስ ሐጺር ወአኮ ከማ። ሶበ መነነት ዓለም ወገደፈት ትርሲተ ዘማ። ነፍሳ ወሰዱ መላእክት እንዘ የኀልዩ በዜማ በዕለተ አዕረፈት ዮም እምሕማም ወፃማ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 2።

                          
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግል ድኅሬሃ። ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ። ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበኃሤት"። መዝ 44፥14-15 ወይም መዝ 86፥5። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 2፥8-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 16፥13-19። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 12፥38-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ አባት አባ ስምዖን ዘዓምድ እና ቅድስት ሶፍያ ቡርክት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

†  🕊  ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ  🕊  †

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ይህ ቅዱስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በሶርያ [ንጽቢን] ውስጥ ሲሆን ዘመኑም ፬ [4] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባ ስምዖን ዘዓምድ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የልጅነትና የተማሪ ቤት ባልንጀራ ነው::

ሁለቱንም ያስተማራቸው ደግሞ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ነው:: ቅዱሳኑ አባ ስምዖንና ቅዱስ ኤፍሬም ለአገልግሎት ከተለያዩ በኋላ አንድ ቀን ተገናኙ::
ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን
"እመቤቴ" እያለ ደጋግሞ በጉባኤ ሲያመሰግናት በመስማቱ "ወንድሜ! ይህን ምሥጢር ማን አስተማረህ?" አለው::

ቅዱስ ኤፍሬምም "ተገልጾልኝ ነው" እንዳይል ውዳሴ ከንቱን ፈርቶ "ቅዱስ ያዕቆብ ነው ያስተማረኝ" ቢለው በአባ ስምዖን ጠያቂነት ወደ መቃብሩ ሔደው ቅዱሱን ከሞት ቀስቅሰውታል:: እርሱም የእመቤታችንን ክብርና የቅዱስ ኤፍሬምን ጸጋ መስክሮ ዙሮ ዐርፏል::

በዚህ የተገረመው ቅዱስ ስምዖን ለቅዱስ ኤፍሬም ሰግዶለት: እመቤቴን ስንቅ ይዞ ወደ በርሃ ሔደ:: ተጋድሎን: ጾምና ጸሎትን በእረኝነት ሕይወት [በሰባት ዓመቱ] የጀመረው ቅዱስ ስምዖን በርሃ ከገባ በኋላ በእጅጉ አሳደገው:: ቅዱሱ በወገቡ የሚሻክር ገመድ አሥሮ: ምግብ ሳይበላ ዕለት ዕለት ያጠብቀው ነበር::

ከጊዜ በኋላ ገመዱ ሆዱን ቆርጦት ወደ ውስጥ ገብቶ ነበርና ሲራመድ በእግሩ ደም ጠብ ጠብ ሲል ይታይ ነበር:: ይሕንን መመልከት ጭንቅ የሆነባቸው መነኮሳት ለአበ ምኔቱ ተናግረው ቁስሉን አድነውና ገመዱን አውጥተው ከገዳም አባርረውታል::

እርሱ ግን ይህንን የሚያደርገው ሕማማተ ክርስቶስን ለመሳተፍ ነው:: ከገዳም ከተባረረ በኋላ ቅዱሱ በበርሃ ውስጥ ወደ ሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አራዊት: እባብና ጊንጥ ከበውት ይጸልይ ነበር:: እግዚአብሔር ግን በራዕይ ለገዳሙ አበ ምኔት ተገልጾ "ወዳጄን ስምዖንን ካልመለስከው አልምርህም" አለው::

በዚህ ምክንያት መነኮሳት በጭንቅ ፈልገው አግኝተው: ከእግሩ ወድቀው ይቅርታ ጠይቀውታል:: እርሱ ግን ከመነሻውም የሚቀየም ልብ አልነበረውም:: ቅዱስ ስምዖን ወደ ገዳሙ ተመልሶ ለዘመናት በተጋድሎ ጸንቶ ቀጠለ::

እግዚአብሔር ግን ቅዱሱን ከገዳሙ ወጥቶ ወደ አንዲት ምሰሶ እንዲሔድ ስላዘዘው አሥራ አምስት ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ምሰሶ ላይ ቆመ:: ከዚህች ቀን በኋላ ነው እንግዲህ "ስምዖን ዘዓምድ [የምሰሶው አባት]" የተባለው:: ቅዱሱ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያለ ምንም ዕረፍት እንቅልፍ እና መቀመጥ ቆሞ
ጸልዩዋል::

ቦታዋ ለከተማ ቅርብ በመሆኗ ብዙዎችን ፈውሷል:: በእርሱ ስብከት ወደ ሃይማኖት የተመለሱ: ንስሐ የገቡ ቁጥር የላቸውም:: አንዳንዴ ክፉ ሰዎች መጥተው እርሱን በማየት ብቻ ይለወጡ ነበር:: ከቆመባቸው ዘመናት አሥራ ሁለት ዓመታት ያህልን ያሳለፈው በአንድ እግሩ ቆሞ: ሌላኛው እግር ቆስሎ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ የሰይጣን ዱላ ነበር::

ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ ከእነዚህ የተጋድሎ ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል:: የዕረፍቱ ዜናም ከቤተ መንግስት እስከ ቤተ ክህነት ሁሉን አስደንግጧል:: እርሱ ለመንጐቹ ዕረፍት ያልነበረው ታላቅ አባት ነበርና:: ሊቃነ ጳጳሳት ገንዘውት: መኳንንት ተሸክመውት ሥጋው በክብር ዐርፏል:: ብዙ ተአምራትም ተደርገዋል::


†  🕊  ቅድስት ሶፍያ ቡርክት  🕊  †

† ይሕች ቅድስት እናት ኢጣሊያዊት [የአሁኗ ጣልያን አካባቢ] ስትሆን የነበረችው በ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: ትውልዷ የነገሥታቱ ዘር ውስጥ እንደ መቆጠሩ እጅግ የተከበረች ሴት ነበረች:: ምንም ሥጋዊ ክብሯ እንዲህ ከፍ ያለ ቢሆንም መንፈሳዊነቷ የሚደነቅ ነበር::

ከነገሥታቱ ዘር ካገባችው ባሏም ሦስት ሴቶች ልጆችን አፍርታለች:: በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲመጣ ስለ ልጆቿ ስትል ሃገሯን ጥላ ተሰደደች:: ስለ ክርስትናም በባዕድ ሃገር መጻተኛ ሆነች:: ያም ሆኖ ክፉዎቹ እግር በእግር ተከትለው ደረሱባት::

ቅድስት ሶፍያ ከዚህ በላይ መሸሸትን አልፈለገችም:: ከልጅነታቸው ለተባረኩ ልጆቿ ገድላተ ሰማዕታትን ታስጠናቸው ነበርና አሁን የነገር መከናወኛ ደርሷል:: ልጆቿን ቁጭ አድርጋ አዋየቻቸው::

"ልጆቼ ! ክርስቶስን የወደደ ክብሩ በሰማይ እንጂ በምድር አይደለም:: ገድላቸውን ያነበባችሁትን ቅዱሳት አንስትን አስቡ" አለቻቸው:: ሦስቱ ሕፃናትም "እናታችን አትጨነቂ:: እኛ ለአምላክ ፍቅር ተገዝተናል:: ስለ ስሙም ደምን ልንከፍል ቆርጠናል:: ብቻ የእርሱ ቸርነት: ያንቺም ምርቃን አይለየን እንጂ" አሏት:: ቅድስት ሶፍያ በሰማችው ነገር እጅግ ደስ አላት::

ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት አደባባይ አደረጉ:: ቅድስቷ እናት ሦስቱንም ሕፃናት በመኮንኑ ፊት አቀረበች:: አንድ በአንድ ጠየቃቸው:: ሁሉም ግን መልሳቸው የተጠናና ተመሳሳይ ሆነበት:: "እኛ የክርስቶስ ነን" ነበር ያሉት:: መኮንኑ በቁጣ ሦስቱንም እያከታተለ አስገደላቸው::

ቅድስት እናት ሶፍያ በእንባ እየታጠበች ልጆቿን
በየተራ ቀበረች:: ስለ ሃይማኖቷ ክብሯን: ሃገሯን: ሃብቷን: መንግስቷን ሰጠች:: ከምንም በላይ ግን ልጆቿን ሰጠች:: ከዚህ በኋላ ግን በመጨረሻው ወደ ልጆቿ መቃብር ሒዳ በእንባ ለመነች::
"ልጆቼን አይ ዘንድ ናፍቄአለሁና ጌታ ሆይ! ውሰደኝ" አለች:: ከደቂቃዎች በኋላም እዚያው ላይ ዐረፈች:: የአካባቢው ሰዎች ደርሰው እርሷንም ከልጆቿ ጋር ቀበሯት::

† መድኃኔ ዓለም ከታላቁ አባ ስምዖንና ከቅዱሳት አንስት በረከትን ያድለን:: ትዕግስታቸውንም ያሳድርብን::

🕊 

[  † ነሐሴ ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት    ]

፩. ታላቁ አባ ስምዖን ዘዓምድ
፪. ቅድስት ሶፍያ ቡርክትና ደናግል ልጆቿ

[   † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯. ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ [ዓምደ ሃይማኖት]

† "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል:: እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል:: በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል:: በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ:: ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ:: ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ::" [መዝ. ፺፩፥፲፪ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/30 01:21:19
Back to Top
HTML Embed Code: