Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን "እንድራኒቆስ ወአትናስያ" እና ለአቡነ "ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞  🕊 ]


🕊 † ጻድቃን እንድራኒቆስ ወአትናስያ  †  🕊

ሁለቱ ቅዱሳን ባል እና ሚስት [ባለትዳር] ናቸው:: የነበረበት ዘመን ፬ [4] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እስኪ እግዚአብሔር የቀደሰው ጋብቻ ምን እንደሚመስል እንመልከት::

እንድራኒቆስና አትናስያ በዘመናቸው ከልጅነት ጀምረው ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰሙ : ለወላጆቻቸው የሚታዘዙ ነበሩ:: ዘመኑ ደርሶ በሚገባው የተክሊል ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጸሙ:: ፵ [40] ቀን ከተፈጸመ በሁዋላ ከምንም ነገር በፊት ፪ [2] ቱ ቁጭ ብለው ተወያዩ::

የውይይታቸው ርዕስ ደግሞ "ፈጣሪያችን በምን እናስደስተው" የሚል ነበር:: ውይይታቸው የጠናቀቀው በእነዚህ ውሳኔዎች ነው::

፩. ሁልጊዜም እንግዳ መቀበል አለብን::

፪. ነዳያን ከቤታችን ሊጠፉ አይገባም::

፫. ጸሎት : ጾምና ስግደት በቤት ውስጥ አይቁዋረጥም::

፬. አብሮ ለመተኛት መቸኮል የለብንም::

እነርሱ መልካምን አስበዋልና አምላክ የሰጣቸውን ሃብት ሲመጸውቱ ኖሩ:: ከዘመናት የቅድስና ጉዞ በሁዋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ፪ [2] ልጆችን አከታትለው ወለዱ:: ወንዱን "ዮሐንስ" : ሴቷን ደግሞ "ማርያም" አሏት::

እነርሱን ከወለዱ በሁዋላ እንደ ገና ሌላ ውሳኔ አሳለፉ:: "ይህንን ላደረገልን ጌታ ከዚህ በሁዋላ አልጋ እንለያለን" ብለው ለ፲፪ [12] ዓመታት በጾምና በጸሎት ተወሰኑ::

ሕጻናቱ ዮሐንስና ማርያም በቅንነት አድገው እድሜአቸው ፲፪ [12] ሲሆን ፪ [2] ቱም በአንድ ቀን ታመው ሞቱ:: ይህ ለአንድ ወላጅ የመጨረሻው አሰቃቂ ፈተና ነው:: ሁሉቱም [እንድራኒቆስና ሚስቱ አትናስያ] ልጆቻቸውን ታቅፈው ወስደው ቀበሩ::

እንድራኒቆስ ከቀብር በሁዋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ:: ግን እንዲህ አለ :-
"አምላከ ኢዮብ! አንተ ሰጠኸኝ:: አንተም ነሳኸኝ:: ስምህ ለዘለዓለም ይባረክ" ብሎ ሔደ:: እናት አትናስያ ግን ከሐዘን ብዛት ልቡናዋ ሊሠወር ጥቂት ቀረው::

የልጆቿ መቃብር ላይ ተደፍታ ስታለቅስ ቅዱስ መልአክ ልቡናዋን ወደ ሰማይ አሳረገው:: ልጆቿ ዮሐንስና ማርያም በገነት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ሐሴትን ሲያደርጉም ተመለከተች:: ወዲያው ወደ ቤት ተመልሳ ለባሏ እንድራኒቆስ ያየችውን ነገረችውና ደስ አላቸው::

እዛው ላይ "ለዚህ ውለታው ከነፍሳችን ውጪ የምንሰጠው የለም" ብለው ሊመንኑ ተስማሙ:: እጅግ ሃብታሞች ነበሩና ነዳያንን ሰብስበው : ሃብት ንብረታቸውን : ቤት ርስታቸውን አካፍለው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዱ::

እርሷ ከሴቶች ገዳም : እርሱ ደግሞ ከወንዶቹ ገቡ:: ለ፲፪ [12] ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ተገዙ:: በእነዚህ ዘመናት ተያይተው : አንዱ ስለ ሌላው ሰምቶ አያውቅም:: በጸሎት ግን ያለማቁዋረጥ ይተሣሠቡ ነበር::

ከ፲፪ [12] ዓመታት በሁዋላ የፍቅር አምላክ በሁለቱም ልቡና በተመሳሳይ ሰዓት : ተመሳሳይ ሐሳብን አመጣ:: እርሱ ከአበ ምኔቱ [ታላቁ_አባ_ዳንኤል] : እርሷም ከእመ ምኔቷ አስፈቅደው ወደ ኢየሩሳሌም ከቅዱሳት መካናት ለመባረክ ጉዞ ጀመሩ:: በየፊናቸው ጥቂት እንደተጉዋዙ እርስ በርስ ተያዩ::

እርሷ ለየችው:: እርሱ ግን ጭራሽ ሊለያት አልቻለም:: ይህም ጥበበ እግዚአብሔር ነው:: ፪ [2] ቱም እየተጫወቱ : እየጸለዩ በሰላም ተባርከው ወደ ግብጽ ተመለሱ:: በእነዚህ ጊዜያት ቅድስት አትናስያን የሚለያት አልነበረም:: አካሏ በገድል ከመለወጡ ባሻገር የለበሰችው እንደ ወንድ መነኮሳት ነበር::

ወደ ገዳመ_አስቄጥስ ሲደርሱ ጸጋው ተሰጥቶታልና አባ_ዳንኤል ባልና ሚስት መሆናቸውን አወቀ:: "ለምን አብራችሁ አትኖሩም?" አላቸው:: "እኛ ደስ ይለናል" አሉት:: ከዚያ እርሷ እያወቀችው: እርሱ ሳያውቃት ለ፲፪ [12] ዓመታት አብረው በቅድስና ኖሩ::

ከእነዚህ ዘመናት በሁዋላ ግን ሐምሌ ፳፰ [28] ቀን ቅድስት አትናስያ ታመመች:: አባ ዳንኤል ሥጋውን ደሙን አቀብሏትም ዐረፈች:: ሊገንዟት ሲቀርቡ ቅዱስ እንድራኒቆስ መልኩዋን ልብ ቢለው ሚስቱ ናት::

በአንድ ጊዜ ሚስቱንና የሚወደውን ባልንጀራ በማጣቱ አለቀሰ:: እርሷን ቀብረው ወደ በዓቱ ተመልሶ "ጌታ ሆይ! ውሰደኝ?" አለ:: እርሱም ተከትሏት ዐረፈ:: አባ ዳንኤል እርሱንም ቀብሮ ጥዑም ዜናቸውን ጻፈ::


🕊  †  አባ ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ †  🕊 

ታላቁ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ: ሐዋርያና ሰማዕት አቡነ_ፊልዾስ የጻድቁ አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆኑ የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ፩ ሺህ ፪መቶ ፷፮ [1266] ዓ/ም ነው:: ከልጅነታቸው ጀምረው ምሥጢር ተመራማሪና መጻሕፍትን መርማሪ የነበሩት ጻድቁ የመነኑት ገና በ፲፭ [15] ዓመታቸው ነበር::

+በደብረ_ሊባኖስ በአሞክሮ ለ፫ [3] ዓመታት ቆይተው መንኩሰዋል:: ለ፳፪ [22] ዓመታትም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው አገልግለዋል:: አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፻፫፻፮ [1306] ዓ/ም ነሐሴ ፳፬ [24] ቀን ሲያርፉ የተተኩት አባ ኤልሳዕ ቢሆኑም ለ፫ [3] ወራት ቆይተው ዐርፈዋል::

በ1307 ዓ/ም አቡነ ፊልዾስ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት [እጨጌ] ሁነዋል:: ገዳሙንም ለ፳፰ [28] ዓመታት መርተዋል:: ከዚያም በዘመነ አፄ ዓምደ ጽዮንና በአፄ ሰይፈ አርዕድ ብዙ ስደት: መከራ: እሥራትና ግርፋት ደርሶባቸዋል:: ምክንያቱ ደግሞ እውነትን መናገራቸውና ነገሥታቱን መገሰጻቸው ነበር:: በስደትም ለ፮ [6] ዓመታት ከ፱ [9] ወራት ቆይተዋል::

ሃገሪቱን በስብከተ ወንጌል ካበሩ ፲፪ [12] ቱ_ንቡራነ_እድ አንዱ የሆኑት እጨጌ አባ ፊልዾስ በተወለዱ በ፸፬ [74] ዓመት ከ፱ [9] ወራቸው በ፲፻፫፻፵፩ [1341] ዓ/ም ዐርፈዋል:: የተቀበሩት በደብረ_ዕንቁ ሲሆን ካረፉ በ፻፵ [140] ዓመት አቡነ_መርሐ_ክርስቶስ ዐጽማቸውን አፍልሰዋል::

ከቅዱሳኑ እንድራኒቆስ ወአትናስያ እና ከጻድቁ አቡነ ፊልዾስ በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  †  ሐምሌ ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን ጻድቃን እንድራኒቆስና አትናስያ
፪. አቡነ ፊልዾስ ጻድቅ [ዘደብረ ሊባኖስ]

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪. ቅዱሳን አበው [አብርሃም : ይስሐቅና ያዕቆብ]
፫. ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
፬. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ [ሰማዕት]

" ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል:: ከሚስቱም ጋር ይተባበራል:: ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ:: ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው:: እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርትስቲያን እላለሁ:: ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጐ ይውደዳት:: ሚስቱም ባሏን ትፍራ:: " [ኤፌ.፭፥፴፩] (5:31)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †

[ † እንኩዋን ለሐዋርያው "ቅዱስ እንድርያስ" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳቸሁ † ]

- መሐሪ እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ በዛ : ሰውነታችሁ ከፋ ሳይል በአባታዊ ርሕራሔው ጠብቆ ይሔው ወርኀ ሐምሌን በሰላም አስፈጸመን:: አይመስለንም እንጂ በእነዚህ ፴ [30] ቀናት ሚሊየኖች አንቀላፍተዋል:: ሚሊየኖች በደዌ ዳኝነት ተይዘዋል:: በርካቶቹም ከሃይማኖታቸው ወጥተዋል::

ታዲያ እኛ ይህ ሁሉ ያልደረሰብን በጐ ስለሆንን አይደለም:: ይልቁኑ ቸርነቱ በእኛ ላይ ስለበዛ ብቻ ነው እንጂ:: አሁንም በሰላም ከአዲሱ ዘመን እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::

በዚህች ዕለት ደግሞ እነዚህን ቅዱሳን እናከብራለን:-

†  🕊 ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ  🕊

ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

ከእርሱም እያገለገለ ለ፮ [6] ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው [ወልደ ዘብዴዎስ] ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

ጌታ ከጾም [ከገዳመ ቆረንቶስ] በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: [ዮሐ.፩፥፵፯] (1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት "ለሐዋርያ  እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ:: ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ::" ብሏል:: [መልክዐ ስዕል]

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ [ፈጣን] አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: [ዮሐ.፮፥፭] (6:5) ለ፫ [3] ዓመታት ከ፫ [3] ወት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ : በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ : ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኩዋል::

ይህች ቀን ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ የተነጋገረባትና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ያዳነባት ናት:: ቅዱስ እንድርያስ ፴ [30] ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጉዋል::

ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር [እንዲሁ ሰው] መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ::
ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::
ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::
" እንዲል::

"ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ ያረፈው ታሕሳስ ፬ [4] ቀን ነው::

†  🕊  ቅዱስ ዻውሎስ መናኒ  🕊  †

ይህ ቅዱስ መላ ሕይወቱ ድንቅ ነው:: በ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ሲሆን የተባረከች ሚስት እና ፪ [2] ቡሩካን ልጆች የነበሩት አባት ነው:: ቅዱስ ዻውሎስ የነዳያን አባት : እጅግ ባለ ጸጋ : ቤተሰቡን የቀደሰና ባለ ሞገስ ሰውም ነው::

ታዲያ ምጽዋት ወዳጅ ነውና ሲመጸውት : ሲመጸውት ሃብቱ አለቀ:: አሁንም መመጽወቱን አላቆመምና ቤቱ : ንብረቱ አልቆ ከነ ቤተሰቡ ነዳያን ሆኑ:: እርሱ ግን ያለ ምጽዋት ማደር አይችልምና አንድ ሃሳብ መጣለት:: ሚስቱንና ልጆቹን መሸጥ እንዳለበት ወሰነ::

እነርሱ እንደ መሪያቸው ፍጹማን ናቸውና በደስታ ሃሳቡን ተቀበሉት:: መጀመሪያ ትልቁ ልጅ ተሸጠ:: ገንዘቡ ግን አሁንም በምጽዋት አለቀ:: ቀጥሎ ትንሹ ልጅ ተሸጠ:: አሁንም በምጽዋት አለቀ:: ፫ [3] ኛ ደግ ሚስት ተሸጠችና እርሱም ተመጸወተ::

በመጨረሻ ቅዱስ ዻውሎስ ራሱንም ሽጦ መጸወተና ይህ ድንቅ ሥራ ተጠናቀቀ:: [ነገሩ ግራ እንዳያጋባን "ተሸጡ" ስንል ለአሕዛብ ወይም ለሌላ ሰው አይደለም:: ፬ [4]ቱም የተሸጡት ለገዳማት ሲሆን ገዥዎቹ አበ ምኔቶቹ ናቸው::] ቅዱስ ዻውሎስ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መትቶ ምጽዋትንም : ገዳማዊ ሕይወትንም አትርፏል::

በሁዋላ ወደ ተሸጠበት ገዳም ገብቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ:- "ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝን ሁሉ ላንተ መልሼ ይሔው መጥቻለሁ::" ጌታም ከሰማይ መለሰለት:- "ወዳጄ ሆይ! ባንተ ደስ ብሎኛል:: ተቀብዬሃለሁ" አለው:: ፬ [4]ቱም ቅዱሳን በንጹሕ ተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈው የማታልፈውን ርስት ወርሰዋል::

†  🕊  ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት  🕊  †

ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል : ገብርኤል : ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::

በ፫ [3] ቱ ሰማያት ካሉት ፱ [9] ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ [የሥልጣናት] መሪ [አለቃ] ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብርን ያሳራው : ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::

በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ_ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት:: ዛሬ ደግሞ የሊቀ መልአኩ ቅዳሴ ቤቱ ነው::

†  🕊  ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም  🕊  †

እነዚህ ወጣቶች በ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ሲሆን ከተወለዱባት ገሊላ ወደ ግብጽ [ገዳመ አስቄጥስ] በምናኔ መጥተዋል:: ለ፳ [20] ዓመታትም በክህነት አገልግሎትና በተጋድሎ ኑረዋል::

አንድ ቀን መናፍቃን [አርዮሳውያን] በወታደር ተከበው መጥተው በገዳሙ እንቀድሳለን አሉ:: የራሳቸውን መስዋዕት መንበሩ ላይም አኖሩ:: ከዛ ያሉ አበው አዘኑ:: ወጣቶቹ መርቆሬዎስና ኤፍሬም ግን ለአምላካቸው ቀኑ::

ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መናፍቃኑን "በክርስቶስ አምላክነት የማያምን በዚህ መቅደስ ውስጥ አይሰዋም" ብለው በድፍረት የመናፍቃንን መስዋዕት ወደ ውጪ በተኑት:: በዚያች ሰዓት መናፍቃኑ ፪ [2]ቱን ቅዱሳን ወደ መሬት ጥለው ደበደቧቸው:: ረገጧቸው:: የቅዱሳኑ አጥንቶችም ተሰባበሩ:: በመጨረሻ በስቃዩ ብዛት ፪ [2]ቱም በአንድነት ዐረፉ::

የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አምላክ ተረፈ ዘመኑን የንስሃ : የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን:: ከወዳጆቹም በረከትን ያድለን::

[  † ሐምሌ ፴ [ 30 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ዻውሎስ መናኒ [ከቤተሰቡ ጋር]
፫. ቅዱስ ሱርያል [እሥራልዩ] ሊቀ መላእክት
፬. ቅዱሳን መርቆሬዎስና ኤፍሬም [ሰማዕታት]
፭. ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት [ፍልሠቱ]
፮. እናታችን ማርያም ክብራ ኢትዮዽያዊት [የዐፄ ናዖድ ሚስት]
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
[   †  ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ [ሐዋርያ]
፪. አባ ሣሉሲ ክቡር
፫. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
፬. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፭. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት

" ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት:: ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ : ሲከተሉትም አይቶ:- "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው:: እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት:: ትርጉዋሜው "መምሕር ሆይ!" ማለት ነው:: "መጥታችሁ እዩ" አላቸው:: መጥተው የሚኖርበትን አዩ:: በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ:: አሥር ሰዓት ያህል ነበረ:: ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ዼጥሮስ ወንድም  እንድርያስ ነበረ:: " [ዮሐ.፩፥፵፯] (1:47)

" እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ:: በኀዘን ወይም በግድ አይደለም:: "በተነ:: ለምስኪኖች ሰጠ:: ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል" ተብሎ እንደ ተጻፈ። " [፪ቆሮ.፱፥፯] (9:7)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ሐምሌ ፴ (30) ቀን።

እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሱርያል (እስራልዩ) ቤተ ክርስቲያኑ ለከበረችበት (ለቅዳሴ ቤቱ) በዐል፣ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ አስገራሚ ተአምር በማድረግ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ማትያስን ከእስር አስፈትቶ ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ላዳነበት፣ ክብርንና ብልጽግናን ንቆ ለተወ ራሱን ስለ ጽድቅ ለሸጠ #ለቅዱስ_ጳውሎስ_ለዕረፍት በዐል፣ ለቅዱሳን ለገሊላ ሰዎች  #ለመርቆሬዎስና_ለኤፍሬም ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን  ከሚታሰበው፦ ከእስክድርያው ሊቀ ጳጳሳት #ከአባ_ጢሞቴዎስ ከምስር በአስቄጥስ ወደ አለወደ አባ መቃረስ ገዳም ከሥጋው ፍልሰት፣ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትን በረከት ያሳትፈን።

                         
በዚችም ቀን #የእስራልዩ_ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ይኸውም #ቅዱስ_ሱርያል መልአክ ነው። የቅዱስ ሱርያል አማላጅነቱና ረድኤቱ ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

                           
በዚችም ቀን #ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ ተአምራትን አደረገ። እንድርያስ በጽርዕ አገር እያለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ተገልጦ እንዲህ አለው "ማትያስን ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና"። እንድርያስም ጌታችንን እንዲህ አለው "የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ ነገር ግን ፈጥኖ የሚያወጣውን ከመላእክት አንድ ላክ እንጂ"። 

ጌታችንም ለእንድርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት "ስማ ሀገሪቱን ወደዚህ ነዪ ከልዃት በውስጧ ከሚኖሩ ሁሉ ጋር ትመጣለች አንተና ደቀ መዘሙሮችህ ግን ጠዋት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ባሕር ሒዱ የተዘጋጀ መርከብንም ታገኛላችሁ እርሱም ያደርስሃል" ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ በክብር ዐረገ።  በነጋ ጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተነሥቶ ወደ ወደብ ደረሰ ጥሩ መርከብንም አየ ጌታችንንም በሊቀ ሐመር አምሳል አየው ጌታችን እንደሆነ አላወቀም "ሊቀ ሐመር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን" አለው ጌታም "የእግዚእብሔር ሰላም ይደርብህ" አለው እንድርያስም ደግሞ "በዚህ መርከብ ወዴት ትሔዳለህ" አለው "ሰውን ወደ ሚበሉ ሰዎች አገር እሔዳለሁ" አለው እንድርያስም ሊቀ ሐመሩን "ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር ትጭነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ" አለው ሊቀ ሐመሩም "እሺ" ብሎ ወደ መርከቡ አወጣቸው። በባሕሩ ላይም ሲጎዙ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው "ጌታህ ምን ኃይል አደረገ" እንድርያስም ጌታችን ከአደረጋቸው ተአምራቶች ይነግረው ጀመረ ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ነበርና። 

ከዚህም በኋላ ሊቀ ሐመሩ እነደሚአንቀላፋ ሰው ሆነ ያንጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተኛ በዚያን ጊዜም ጌታችን እንድርያስንና ሁለቱን አርድእቱን ይሸክሙአቸው ዘንድ መላእክትን አዘዛቸውና ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አኖሩዋቸው።  እንድርያስም ከእነቅልፍ በነቃ ጊዜ መረከብን አላገኘም እጅግም አደገቀ ለደቀ መዛሙርቱም እንድህ አላቸው "ልጆቼ ሆይ በመርከብ ውስጥ ከጌታችን ጋር ነበርን ግን አላወቅንም"። 

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ተነስቶ ጸለየ ክብር ይግባውና ጌታችንም በመልካም ጎልማሳ አምሳል ተገለጸለት እንዲህም አለው "ወዳጄ እንድርያስ አትፍራ እኔ ይህን አድርጌአለሁና አንተ በሦስት ቀን አልደርስም ብለህ ነበር ስለዚህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ኃይል እንዳለኝ የሚሳነኝምእንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንግዲህም ወደ ከተማው ገብተህ ማትያስን ከእሥር ቤት አውጣው ከእርሱ ጋር ያሉትንም ሁሉ"። 

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ ማትያስ ወዳለበትም እስር ቤት ሔደ። በደረሰም ጊዜ የወሀኒ ቤቱ ደጀ ራስዋ ተከፈተች በገባ ጊዜም ማትያስን ተቀምጦ ሲዘምር አገኘው እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሳጣጡ እንድርያስም ማትያስን "ከሁለት ቀን በኋላ አውጥተው እንደ እንስሳ አርደው ይበሉኛል አልክ አንተ በጌታችን ዘንድ ያየናትን ያቺን ምሥጢር ረሰሃትን በምንናገርበት ጊዜ ሰማይና ምድርን ይናወጣሉ" አለው።  ማትያስም "ወንድሜ ሆይ እንሆ ይህን አወቅሁ ነገር ግን በዚች ከተማ ውስጥ ሥራዬን እንድፈጽም የጌታችን ፍቃድ እንደ ሆነ እኔ እናገራለሁ እርሱ ራሱ "እንሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እንኳችኋለሁ" ብሏልና ወደ ዚህም እሥር ቤት በጨመሩኝ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ጠራሁት እርሱም ሃያ ሰባት ቀን ሲፈጸም ወንድምህ እንድርያስን ወዳንተ እልከዋለሁ እርሱም ከእሥር ቤት ያወጣሃል ከአንተ ጋራ ያሉትን ሁሉ ያወጣችዋል ብሎ ገለጠልኝ እንሆም ደርሰሃል የምትሠራውን አስተውል" አለው። 

እንድርያስም ወደ እስረኞች በተመለከተ ጊዜ እንደ እንስሳ ሣር ሲበሉ አይቶ አዘነ አለቀሰም ሰይጣንንም ከሠራዊቱ ጋር አሠረው ከዚህ በኃላ አንድርያስና ማትያስ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር ማለዱ እጆቻቸውንም በእሥረኞች ሁሉ ላይ ጫኑ አእምሮአቸውም ተመለሰ ከከተማው ውጭ ወጥተው በዚያ በአንድነት እንድቀመጡ አዘዙአቸው።

እኒያ ሐዋርያትም የሚሆነውን ያዩ ዘንድ ወጥተው በሀገሩ ጎዳና ዳር ተቀመጡ የከተማው ሰዎችም እነደ ልማዳቸው የሚበሉትን ከእሥረኞቹ ውስጥ ሊአመጡ መጡ የእሥር ቤቱን ደጅ ክፍት ሆኖ አገኙ እሥረኞችም አልነበሩም ደነግጠውም "በእኛ የደረሰብን ምንድነው ወዮልን" አሉ ያን ጊዜም ሰይጣን በሰው መስሎ ሐዋርያት ይህን እንዳደረጉ ነገራቸው የአሉበትንም አመለከታቸው የከተማው ሰዎችም በመቀዳደም ሮጡ እንድርያስንና ማትያስንም ይዘው በከተማው ጥጋጥግ አስጎተቱአቸው በሌሊትም በእሥር ቤት ያሳድሩአቸው ነበር ሦስት ቀናትም እንዲህ አደረጉባቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ። 

ከዚህም በኋላ ሰለ ከተማዋ ሰዎች ድኀነት ወደ እግዚአብሔር ጸለዪ ጸሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ በላዩ ምስል ወደአለበት የዕብነ በረድ ምሶሶ ቀርበው በመስቀልመ ምልክት አመተቡት እንዲህም አሉት "አንተ ምሶሶ ፍራ ከበታችህም እንደ ጥፋት ውኃ ያለ ብዙ ውኃን በዚች ከተማ ላይና በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ላይ አውጣ" ያን ጊዜም ከምሶሶው ሥር ብዙ ውኃ መነጨ የከተማው ሰዎችንም ያሠጥማቸው ዘንድ ገነፈለ ሰዎችም ከከተማው ወጥተው ሊሸሹ ወድደው ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ያዙ ውኃውም በዝቶ ከበባቸው ማምለጥም አልቻላቸውም ውኃውም እስከ እስከ አንገታቸው ደረሰ ያን ጊዜም አለቀሱ እንዲህም አሉ "ወዮልን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ የመጣው በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች በእግዚአብሔር አገልጋዮች ምክንያት ነው እኛም በአምላካቸው እናምናለን"።

ቅዱስ እንድርያስም "የዕብነ በረደ ምሰሶ እንግዲህስ በቃህ እነሆ የጥፋት ጊዜ አለፈ" ያን ጊዜም ውኃው ተገታ ውኃውም እንደተገታ የከተማው ሰው አይተው ወደ ሐዋርያት ሔዱ ስለዚያች ከተማ ሰዎች ድኅነትም ቁመው እጆቻቸውን ዘርግተው ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ አገኙአቸው ሐዋርያትን "ይቅር በሉን" ብለው ለመኑአቸው። ሐዋርያትም "በሕያው እግዚአብሔር እመኑ እንጂ አትፍሩ" አሏቸው ሐዋርያትም ሁለተኛ ጸለዩ በውኃ ስጥመት የሞቱትንም ሙታን አስነሡአቸው በዚያም ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበሏቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው። ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተምረው በቀናች ሃይማኖት አጸኑአቸው እንዲህም አሏቸው ያዘዝናችሁን ጠብቁ ከእናንተ በኃላ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
ለሚነሡ ልጆቻችሁም አስተምሯቸው።

ከዚህም በኃላ የአራዊትን ጠባይ ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት ክብር ይግባውና ጌታችንም ይህን የአራዊት ጠባይ አራቀላቸው። ሰዎች የሚመገቡትንም የሚመገቡ የዋሆች ሆኑ። አባቶቻችን ሐዋርያትም ብዙ ተአምራትን አደረጉ በሽተኞችን ሁሉ ፈወሱ ከዚህም በኃላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ግሪክ አገር ተመለሰ።  ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁንእኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ቅዱስ እንድርያስና በቅዱስ ማትያስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእርሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ከአባ መርቆሬዎስና ከአባ ማትያስ ከሁሉም ኤጲስ ቆጶሳት ከክርስቲያን ወገኖችም ሁሉ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                          
#ብልጽግናን_ንቆ_የተወ_አባ_ጳውሎስ፡- ይህም ቅዱስ ባለ ጸጋ ነበር። ደግ የሆነች ሚስትና የተባረኩ ልጆችንም ነበሩት፡፡ መነኰስ ሊሆን ወደደ ሚስቱንና ልጆቹንም ጠርቶ "እነሆ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር እሸጣችሁ ዘንድ ወደድኩ" አላቸው እነርሱም "አሳዳሪያቸን ነህና የወደድከውን አድርግ" አሉት።

ከዚያም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ሚስቱንም ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት አመ ምኔቱንም ጠራትና እንዲህ አላት "ለገዳምሽ አገልጋይ ትሆን ዘንድ ሚስቴን ልሸጥልሽ  አወዳለሁ" እርሷም "እሺ" አለችው የመሸጫዋንም ደብዳቤ ጻፈ የሺያጭዋን ዋጋ ተቀብሎ ለድኆች ሰጠ ልጆቹንም ወደ አበ ምኔቱ ወስዶ እንደ እናታቸው ሸጣቸው ለአበ ምኔቱም አሳልፎ ሰጣቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ራሱንም ለገዳሙ አለቃ ሸጠ አለቃውንም "ወደ ቤተ ክርስቲያን  ልገባ እሻለሁ" አለው፡፡ በገባም ጊዜ በሩን በላዩ ዘጋ። እጆቹን ዘርግቶ ቆመ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ "አቤቱ በፍጹም ልቡናዬ ወዳንተ እንደ መጣሁ፣ አንተ ታውቃለህ"  ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ "ሀሳብህን ሁሉ አወቅሁ በፍጹም ልቤም ተቀበልሁህ"

ከዚህም በኋላ ከመነኵሶ አስጨናቂ የሆኑ የገዳሙን ሥራዎች ሁሉ እንደ ባሪያ እየሠራ ኖረ ራሱንም ከሁሉ እጅግ አዋረደ ነገር ግን ስለ መዋረዱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው። ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከዚህም በኋላ ሐምሌ 30 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጳውሎስ ጸሎት ይማሰን ለዘላለሙ አሜን።

                          
#ሰማዕታት_ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም፡- እሊህም ከአክሚም ከተማ የመጡ የሚዋደዱ በመንፈስ ቅዱስ ወንድማማቾች  በሥጋም ዘመዳሞች ነበሩ መንፈሳዊ ስምምነትንም ተስማምተው በላይኛው ግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም መነኰሱ፡፡ በጾም በጸሎትና በስግደት በታላቅ እየተጋደሉ በገዳሙ ውስት ሃያ ዓመት ዓመት ያህል ኖሩ፡፡

ከዚህም በኋላ ጠላት ሰይጣን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአርዮሳውያን ችግርን በአመጣ ጊዜ አርዮሳውያኑ በአርዮሳዊ ንጉሥ ትእዛዝ መሥዋዕት ሊሠው ወደ ኦርቶዶክሳዊ  ቤተ ክርስቲያን ሊሠዉ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ፡፡ እኒህ ቅዱሳንም አምላካዊ ቅንአትን ቀንተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡና አርዮሳውያን ያኖሩትን መሥዋዕት በተነኑት። እንዲህም አሏቸው "በሥሉስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ መሥዋዕትን ያሳርግ ዘንድ አይገባውም"።

ያን ጊዜም አርዮሳውያን ይዘው ደበደቧቸው ታላቅ ግርፋትንም ገረፏቸው ዐጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በምድር ላይ ጥለው ረገጧቸው ነፍሶቻቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ ምእመናንም መጥተው ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖርዋቸው ከእነርሱም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን መርቆሬዎስ  ኤፍሬም ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                     
አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ጳውሎስ በሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት እንዲሁም በሁላችን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ይደር ለዘላለሙ አሜን። በሐምሌ ወር የሚነገበብ ንባብ ደረሰ ተፈጸ። እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 30 ስንክሳር።

                             
"#ሰላም_ዕብል_ለቤትከ_ቅዳሴሃ። ድኅረ ፈጸመ በቊስጥንጥንያ ሕንፄሃ። ሱርያል ገሀደ ተአምሪከ አሜሃ። እምዘይት ማኅቶት ዘሥዕልከ ተቀቢዖ ሶቤሃ። ዐይነ ዕውረሰ በቅጽበት በርህ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_30

                          ✝️ ✝️ ✝️
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "ይቤ ወመጽአ መንፈስ አውሎ። ወተለዓለ ማዕበል። የዐርጉ እስከ ሰማይ"። መዝ 106፥25-26። የሚነበበው ወንጌል ማር 6፥47-53።

                           ✝️ ✝️ ✝️
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "እምውኂዝ እምሰጠት ነፍስነ። እምሰጠት ነፍስነ እማየ ሀከክ። ይትባረክ እግዚአብሔር አምላክነ ዘኢያግብአነ ውስተ መሥገርተ ማዕገቶሙ"። መዝ 123፥4-5። የሚነበበው ወንጌል ማር4፥35-41። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።


@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
“ የልጅነት ልጄን አድኑልኝ። ሁለት የልብ ክፍተት ህመም አለበት ፤ ለህክምና 665 ሺህ ብር ተጠይቄአለሁ ” - የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህር

የ2 ዓመት ከ5 ወር ልጃቸው የታመመባቸው አቶ ገ/መድህን መብርሃቱ የተባሉ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ለህክምና የተጠየቁት ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማጸኑ።

ቃላቸውን ለቲክቫህ የሰጡት የህፃኑ አባት፣ “ ህፃኑ ሁለት የልብ ክፍተት አለበት። ጥቁር አንበሳ የህፃናት ልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሂጄ ነበር ‘ወረፋው ብዙ ነው’ አሉኝ ” ብለዋል።

“ የግል ህክምና ሂጄ ደግሞ ‘ልጄህ በአስቸኳይ ካልታከመ አደጋ ላይ ነው’ አሉኝ። ለህክምናው 665 ሺህ ብር ተጠይቄአለሁ። ይህ ገንዘብ በጣም ከአቅሜ በላይ ነው ” ሲሉ አክለዋል።

“ መምህር ነኝ። የማስተምረው መቐለ ዩኒቨርሲቲ ነው። ይሄ የልጅነት ልጄ ነው። ገና 29 ዓመቴ ነው " ያሉት መምህሩ፣ " የኢትዮጵያ ህዝብ ያቅሙን በማዋጣት የልጅነት ልጄን በማትረፍ ይተባበረኝ ” ሲሉ ተማጽነዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው ሀኪም ቤት ደብዳቤ ለህክምና የተጠየቀው ገንዘብ 665 ሺህ ብር መሆኑን፣ ሌላኛው የህክምና ውጤት ደግሞ፣ ህፃኑ ሁለት የልብ ክፍተት እንዳለበት ያስረዳል።

መርዳት ለምትሹ፣ የንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000543793508 (ገብረመድህን መብራህቱ ኣብርሃ)፣ ለመደወል 0914178980 (አባት)፣ 0946482480 ተ/ወይኒ ፍሰሃ (እናት) መጠቀም ይቻላል።
 
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Forwarded from TIKVAH-ETHIOPIA
#ጾመፍልሰታ

ጾመ ፍልሰታ ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ/ም ይጀምራል።

ጾሙን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከቅዱስነታቸው መልዕክት ፦

" የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን !

ጾም ፈቃደ ሥጋን በማድከምና ፈቃደ ነፍስን በማጎልበት ምሕረተ እግዚአብሔር መሻታችንን የምናሳይበት መንፈሳዊ ማመልከቻ ነው ፤ ጾም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው።

ቀደምት አበው በጾም ምክንያት ፦
° ከጥፋት ድነዋል፤
° የለመኑትንም አግኝተዋል፤
° ምስጢርም ተገልጾላቸዋል፤
° ዲያብሎስንም ድል አድርገውበታል፡፡

እኛም ዛሬ ጾምን ስንጾም በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን ብሎም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ስጋትን እየጫረ ያለው የጥፋት እንቅስቃሴ እግዚአብሔር እንዲያስቆምልን ከልብ በመጸለይ ሊሆን ይገባል።

ይህንንም ስናደርግ በጸሎት ብቻ ሳይሆን ንስሐ በመግባት እና ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል እንደዚሁም የሰላም የፍቅርና የዕርቅ ሰው ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም ሊሆን ይገባል፡፡

ችግሮችንና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በምክክር ለመፍታት የሚደረገው ጥረትም በእጅጉ ሊደገፍ ይገባል፤ ግጭትና ጦርነት ከሚያጠፋን በቀር ሊያተርፍልን የሚችል አንዳች ጥቅም የለም፡፡

በመሆኑም በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ
ላይ ያላችሁ ልጆቻችን እባካችሁ ፦

ለሰላም ለውይይት እና ለሰው ልጆች መብት መከበር ቅድሚያ ስጡ፤

ግድያ ፣ ዕገታ ፣ አብያተ ሃይማኖትን መዳፈር ፣ ዘረፋና ቅሚያ ፣ የሴት ልጅን መድፈርና ሰውን ማንገላታት አቁሙ፤

እነዚህ ድርጊቶች ሰብአዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ ፣ እግዚብሔርን የሚያስቆጡ፣ በታሪክም የሚያሳፍሩ ናቸውእነዚህን ሳናርም የምንጾመው ጾም ትርጉም ስለሌለው ንስሐ ገብተን ከእንደዚህ ያለው ድርጊት ርቀን ጾሙን መጾም ይገባል፤ ይህን ስናደርግ ጾማችን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ ይኖረዋል፡፡ "

(የቅዱስነታቸው ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያይዟል)

ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን በሙሉ መልካም የፍልሰታ ጾም ይሁንላችሁ !


@tikvahethiopia
2024/09/29 23:21:03
Back to Top
HTML Embed Code: