Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
▬▬▬▬▬▬   ♱    ▬▬▬▬▬▬

[ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ ! ]

🕊

❝ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው ፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ። ❞

❝ አንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላቸው አውግዣለሁ። ❞

[ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ]


🕊                        💖                     🕊
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
▬▬▬▬▬▬   ♱    ▬▬▬▬▬▬

[ 🕊 ሥ ራ ህ ን ሥ ራ ! 🕊 ]

🕊

❝ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል ፣ ያንን መስራት የእሱ ፈንታ ነው፡፡ ቢቻለው አሱን ማገድ የዲያቢሎስ ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ ሥራው እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሠይጣን ሊያግድህ ይጥራል፡፡ ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፡፡ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል፡፡ የሐሜት ጐርፍ ያስወርድብሃል፡፡ ደራሲያን እንዲጠይቁህ እጅግ ስመጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገሩብህ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ...

አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል ፣ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎቹንም በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፡፡ ሥራህን ሥራ !

ዋሾዎች ይዋሹ ፣ ጠበኞች ይጣሉ ፣ ማኀበሮችም ይወስኑ ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ ፣ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ ፣ አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈጸም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ፡፡ ....

ዓላማህ እንደ ኮከብ የፀና ይሁን ፤ ተወው ዓለም እንደፈለገው ይነታረክ ፣ ይጨቃጨቅ ፣ ጥቃት ይደርስብህ ፣ ትበደል ፣ ትሰደብ ፣ ትታማ ፣ ትቆስልና ፣ ትናቅ ይሆናል፡፡ ሃይለኛ ያጐሳቁልህ ፣ ወዳጆች ይተውህ ፣ ሰዎችም ይንቁህ ይሆናል፡፡ አንተ ግን በፀና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ፀንተህ ፣ የሰጠኸኝን ሥራ ፈፀምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ ለማለት እሰክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማ እና የተፈጠርክበትን ግብ ተከተል ! ❞

ስምከ ሕያው ዘኢይመውት

[ ከ፲፱፻፴፪ - ፲፱፻፹፪ ዓ.ም ]

❝ ሰው የተመኘውን ከሠራ የሚጠብቀው ሞቱን ነው ! ❞
            
[ ታላቁ አቡነ ጎርጎርዮስ ]


🕊                        💖                     🕊
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
                        †                           

🕊   ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ    🕊

                         🕊                         

❝ የሃገሬ ሕዝብ ሆይ ! ለሃገርህ : ለሃይማኖትህ ባትጋደል ትውልድ ይፋረድህ:: ለጣልያን ግን እንኳን ሰው ዛፍ ቅጠሉ መሬቱ እንዳይገዛለት አውግዣለሁ። ❞

[ ሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ]

🕯

ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው ነጻነትን አተሙ። አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለሀገር ፣ ለቤተ ክርስቲያን ፣ ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም [ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም] በሰማዕትነት አለፉ፡፡

❝ ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው ፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው። ❞ [ መዝ.፻፲፱፥፻፳፱ ]

🕊

የአባታችን የአቡነ ጴጥሮስ በረከት ይደርብን።


🕊                  🕯                   🕊
02
02
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
                          🕊                         


" ብዙ አባቶች የሉአችሁም " [ ፩ቆሮ.፬፥፲፭ ]


         †               †                †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለእናታችን ቅድስት መሪና ሰማዕት እና ቅዱስ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊 † ታላቋ ቅድስት መሪና ሰማዕት [ SAINT MARINA THE GREAT ]  †  🕊

† እናታችን ቅድስት መሪና ስም አጠራራቸው ከከበረ : ተጋድሏቸው ካማረ ታላላቅ ሴት ሰማዕታት አንዷ ናት:: ተወልዳ ያደገችው ከዋናው ዘመነ ሰማዕታት በፊት በ፪ [2] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሶርያ አካባቢ ነው:: አባቷ ዳኬዎስ የሚባል ጣዖት አምላኪ ቢሆንም እናቷ ግን ክርስቲያን ነበረች::

ነገር ግን እናቷ ገና በ፭ [5] ዓመቷ ሞተችባትና ለሞግዚት ተሰጠች:: የእግዚአብሔር ጥበብ ሆኖ ሞግዚቷ ደግ ክርስቲያን ነበረችና ለ፲ [10] ዓመታት ሃይማኖተ ክርስቶስን እና ምግባረ ጽድቅን አስተማረቻት:: ዕድሜዋ ፲፭ [15] ዓመት ሲሆን አባቷ ዳኬዎስ አረፈ::

በዘመኑ ዳኬዎስ የሚሉት [ቅዱስ መርቆሬዎስን የገደለው] ክፉ ንጉሥ ነበርና ክርስቲያኖችን አሳደዳቸው:: ይህን ዜና ቅድስት መሪና ስትሰማ ደስ አላት:: እጅግ ባማረ ንጽሕና እንደ ኖረች ሁሉ በክርስቶስ ስም ደሟን ለማፍሰስ አስባ ወደ ንጉሡ መኮንን ሔደች::

† አበው እንዳስተማሩን ከሴቶች ሰማዕታት በውበትና ደም ግባት እንደ ቅዱሳት :-

- መሪና
- አርሴማ እና
- ጣጡስ የሚያክል የለም:: ዐይንን ማፍዘዝ የሚችል ውበት ነበራቸው::

መኮንኑ መልኩዋን ዐይቶ ሰውነቱ ተናወጠ:: "ጣዖት አምልኪና የእኔ ሚስት ሁኚ" አላት:: እርሷ ግን መኮንኑን ከነ ጣዖቱ አቃለለችው:: "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ" አለችው::

መኮንኑ ካነጋገሯ የተነሳ ተቆጥቶ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ:: መሬት ላይ ጥለው በብረት ዘንግ ቢመቷት አካሏ እየተቆረጠ ብዙ ደም ፈሰሰ:: ወስደውም ጨለማ ውስጥ ጣሏት:: ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አድኗት: አጽንቷትም ዐረገ::

በማግስቱ በመጋዝ አካሏን ቆራርጠው ጣሉ:: ዳግመኛ ሊቀ መላእክት አዳናት:: ወደ ጨለማ ክፍል ወስደው ሲጥሏት ትልቅ ዘንዶ መጣባት:: እጆቿ ተዘርግተው እጸለየች ዋጣት:: እርሷ ግን ጸሎቷን ቀጠለች:: ከደቂቃዎች በሁዋላ ግን ዘንዶው ለ፪ [2] ተሰነጠቀና እጆቿ እንደተዘረጉ ወጣች::

በሌላ ቀን ግን ሰይጣን ፊት ለፊት መጥቶ ታገላት:: ከሰማይ ነጭ ርግብና መስቀል ወርዶላታልና አልቻላትም:: ከእግሯ በታች ጥላ ደጋግማ ረገጠችው:: ሰይጣንም በሐፍረት እየጮኸ ሔደ::
"ለሰይጣን ኬደቶ ከመ አሣዕን በእግር" እንዲል:: [እንዲህ ነበሩ የቀደመው ዘመን እናቶቻችን]

መኮንኑ ከክርስትና ያስወጣት ዘንድ በትልቅ ጋን ውሃ አስፈልቶ "በዚያ ላይ ቀቅሏት" አለ:: ድንገት ግን ከሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ: ውሃውን አቀዝቅዛ : ፫ [3] ጊዜ በውሃው አጠመቀቻት:: [እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልጠመቀችም ነበርና]

ርግቧ የብርሃን ልብስ አልብሳ: አክሊለ ክብር ደፋችላት:: መኮንኑ ተስፋ ስለ ቆረጠ "አንገቷን በሰይፍ ምቱ" አለ:: በዚያች ሰዓት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ "ብጽዕት መሪና ብጽዐን ይገባሻል" አላት::

"ስምሽ በሚጠራበት: መታሰቢያሽ በሚደረግበት ሁሉ በዚያ ረድኤት: በረከት ይበዛል:: አንቺን ያከበረውን አከብረዋለሁ:: ከርስትሺም አስገባዋለሁ" ብሏት ጌታችን ዐረገ::

ወታደሮቹ አንገቷን በሰየፉ ጊዜ ታላቅ መነዋወጽ ሆነ:: ድውያን ተፈወሱ: ዕውሮች አዩ: አንካሶች ረቱ: የማይሰሙትም ሰሙ:: ቅዱሳን መላእክትም ከሰማያት ወርደው የቅድስት መሪናን ነፍስ በዝማሬ አሳረጉ::


🕊  †  ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት  †  🕊

† ለንጊኖስ ማለት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዘመን የዺላጦስ ወታደር የነበረ ሰው ነው:: ስለ ጌታችን ተአምራት በየጊዜው ይሰማ ነበር:: ሔዶ እንዳያገኘው ግን አይሁድን ይፈራ ነበር:: እነርሱ "በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ከምኩራብ ይባረር" ብለው ነበርና:: [ዮሐ.፱፥፳፪] (9:22)

ጌታችን በተሰቀለባት ዕለተ ዐርብ ግን ጭንቅ ሆነበት:: ጌታን እንዲሰቅሉ ከታዘዙ ወታደሮች እንደ አንዱ ተመርጦ ነበርና በዘዴ "አሞኛል" ብሎ እስከ ፱ [9] ሰዓት ድረስ ቆየ::

በሁዋላ ግን አይሁድ "በክርስቶስ ሞት ያልተባበረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው" የሚል አዋጅ በማስነገራቸው እየፈራ ቀራንዮ ሲደርስ "ጐኑን ውጋው" ብለው ረዥምና ጥቁር ጦር ሰጡት:: ለንጊኖስ ወደ ጌታችን ዐይን ተመለከተ:: እያየው እንዳልሆነ ገመተ::

ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ ለይቷልና ጦሩን ጨብጦ ወደ ጌታ ጐን ልኮ ወጋው:: ከጌታ ቀኝ ጐንም በ"ለ" አምሳል ትኩስ ደምና ውሃ ፈሰሰ:: አንዷ ፍንጣቂ ሔዳ የታወረች ዐይኑ ላይ ዐርፋ ዐይኑን አበራች::

ለለንጊኖስ ታላቅ ደስታ ሆነ:: ለእኛ ግን ማየ ገቦና ደመ ገቦ ፈለቀልን:: የጌታችን ትእግስቱና ቸርነቱ ግን ይደንቃል::
"ከመ ኢየሐስብ ቦቱ ዘኩናተ እዱ ርግዘቶ::
በኃጣውኢሁ ለዘኢፈቀደ ሞቶ::
ምሕረቶ እሴብሕ ወዐዲ ትዕግስቶ::" እንዳሉ ሊቃውንት::

ጌታችን ከተነሳ በሁዋላ ለንጊኖስ ወደ ቅዱስ ዼጥሮስ ዘንድ ሒዶ ስለ እውነት : ስለ ሃይማኖትም ተማረ:: ተጠምቆ: ምድራዊ ወታደርነቱን ትቶ እየሰበከ ከኢየሩሳሌም ወደ ቀዸዶቅያ ወረደ:: ለዘመናትም ጌታችን ክርስቶስን በሥርዓተ ወንጌል አገለገለ::

በመጨረሻም በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን አይሁድ አሳደዱት: አንገላቱት:: የነርሱ ወገን ስለነበረም መከራ አጸኑበት:: የጽድቅ አርበኛና የክርስቶስ ሐዋርያ ቅዱስ ለንጊኖስ ግን ጸና:: በዚህች ዕለትም አይሁድ አንገቱን ቆርጠውት ለሰማዕትነት በቃ:: ቅዱሱ በሕይወቱም በዕረፍቱም ተአምራትን ሠርቷል::

† እግዚአብሔር በቸር ጥሪው ሁላችንም ወደ ቀናው የጽድቅ ጐዳና ይጥራን:: ከሰማዕታቱም ረድኤት በረከት ይክፈለን::

🕊

[   † ሐምሌ ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅድስት መሪና እናታችን [ታላቋ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ለንጊኖስ ሐራ [ሐዋርያና ሰማዕት]
፫. ቅዱስ አብጥልማዎስ

[    †  ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል

† " ወደ ጌታ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም:: ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጐኑን በጦር ወጋው:: ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ:: ያየውም መስክሯል : ምስክሩም እውነት ነው:: እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ : እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል:: ይህ የሆነ :- "ከእርሱ አጥንት አይሰበርም" የሚል የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው:: ደግሞም ሌላው መጽሐፍ:- "የወጉትን ያዩታል" ይላል::" † [ዮሐ.፲፱፥፴፫] (19:33)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ሐምሌ_፳፫ (23) ቀን።

እንኳን #ለመናገሻ_ገነተ_ጽጌ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ቤተ_ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) #ለቅዳሴ_ቤቱ_ዓመታዊ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                           
#የበዓሉ_አንገርጋሪ_ግእዝ_ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "ተቀደሲ ወንሥኢ ኃይለ ኦ #ቤተ_እግዚአብሔር እስመ ናሁ ንጉሥኪ በጽሐ ዘያበርግህ ለኪ በኃይሉ ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ ለዛቲ ቤት ሐነፃ ወልድ ለዛቲ ቤት ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ"። ትርጉም፦ #ቤተ_እግዚአብሔር ሆይ ተቀደሺ ኃይልንም ልበሺ ንጉሥሽ እያበራ ወደ አንቺ ደርሷልና፡፡ ይእቺን ቤት አስቀድሞ አብ ሠራት ወልድ አነፃት መንፈስቅዱስ ፈፀማት፡፡ #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ

                         
#የዕለቱ_መዝሙር፦ "#አመ_ሕንፂሃ_ለገነተ_ጽጌ አንሶሰወ ውስተ መርህባ #ንጉሠ_ነገሥት_ምኒልክ፡፡ ምስለ ሠራዊቲ ዖዳ ማቴዎስ ቀደሳ ወአተባ በዕፀ መስቀሉ"። ትርጉም፦ ቅዳሴ ቤቷን ባከበረ ጊዜ ተመላለሰ በአደባባዯ #ንጉሠ_ነገሥት_ምኒልክ፡፡ከሠራዊቶቹ ጋር ዞራ ማቴዎስ አከበራት በመስቀሉ ደግሞ ባረካት። #ድርስ_ወረብ

                             

                           
የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለረዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠሩ ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት የባረኳትም ሊቀ ጳጳሱ ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ልመናው አማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!!!ተአምረ ጊዮርጊስ ተአምር17 ላይ።

                               

                            
#የበዓሉ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወንሰግድ ውስተ መካነ ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ። ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ። አንተ ወታቦተ መቅደስከ"። መዝ131፥7-8 ወይም መዝ90፥13። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 12፥23-30።
       
                           
#የበዓሉ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል። እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትተሐወክ። ወይረድኣ እግዚአብሔር ፍጽመ"። መዝ 45፥4-5 ወይም መዝ 121፥23። የሚነበቡት መልዕክታት ኤፊ 2፥13-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 2፥4-11 እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 16፥13-20። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ቤት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዘዮሐንስ እና ለሰማዕቱ አባ ኖብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  †  አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ  †  🕊

† ኢትዮጵያዊው ጻድቅ የተወለዱት በ፲፫ [13] ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሸዋ [መርሃ ቤቴ] ነው:: ወላጆቻቸው ዘካርያስ እና ሶፍያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ : እመ ብርሃንን የሚወዱና ለነዳያን የሚራሩ ነበሩ::

ደጉ ዘካርያስ መስፍን ሲሆን እርሱ በሌለበት የሸዋ ገዢ ሊያገባት በመሞከሩ ቅዱስ ገብርኤል ቀስፎታል:: ሕዝቡ ገዢነቱን ለዘካርያስ ሰጥተውታል:: ከቆይታ በኋላም ድንግል ማርያም የተባረከ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን "ዮሐንስ" አሉት:: በሒደት ግን ዘዮሐንስ [የዮሐንስ] ተብሏል::

ቅዱሱ ዘዮሐንስ እስከ ሰባት ዓመቱ ድረስ በእናቱ እቅፍ ቆይቶ ወደ ትምሕርት ገብቷል:: ጸጋ እግዚአብሔር ጠርቶታልና በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አደን ይወድ ነበርና ሊያድን ሲወጣ 'ብርሕት ደመና' ድንገት ነጥቃ ከኢትዮጵያ [ሽዋ] ወደ ኢየሩሳሌም [ጐልጐታ] አደረሰችው::

ደስ ብሎት ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ደመናዋ ወደ ሃገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከሰማይ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ወርደው ባረኩትና "ክፍልህ ከእኛ ጋር እንዲሆን መንን" አሉት::

ዘዮሐንስ ወላጆቹንና ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ [ዲቁና ነበረውና] ሃያ አምስት ዓመት ሞላው:: ያን ጊዜ ወላጆቹ "እንዳርህ" ቢሉት "የለም! አይሆንም" አላቸው:: አርጅተው ነበርና ስለእነርሱ ዕረፍት ጸለየ:: ፈጣሪም ሰምቶታልና ሁለቱም በክብር ተከታትለው ዐረፉ::

ሕዝቡ በወላጆቹ ፈንታ "እንሹምሕ" ቢሉት "እንቢ" ብሎ ወርቁን : ብሩን : ርስቱን : ቤቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ::ጊዜው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በሃምሳ ዓመት አካባቢ ሲሆን አባ ሕዝቅያስ አበ ምኔት ነበሩ::
[ከዚህ በኋላ አንቱ እያልን እንቀጥል]

አባ ዘዮሐንስ ለሰባት ዓመታት ገዳሙን ረድተው መነኮሱ:: እንደ ልማዱ ደመና ነጥቆ ወስዷቸው ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ተቀብለዋልና በደብረ ሊባኖስ ለሃያ አምስት ዓመታት አገለገሉ:: ቤተ መቅደሱን በመዓልት ሰባት ጊዜ በሌሊት ሰባት ጊዜ ያጥኑ : እልፍ እልፍ ይሰግዱ : ተግተው ይጸልዩ : ይታዘዙም ነበር::

ከዚያም በፈጣሪ ትዕዛዝ በትግራይና በሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ወንጌልን ሰብከዋል:: እድሜአቸው ሰባ በሆነ ጊዜ ወደ ጌታ መቃብር [ጐልጐታ] ሔደው ተሳልመው በእርሱ [በጌታ] ትዕዛዝ ወደ ደራ [ጣና ዳር] ተመለሱ::

በአካባቢውም ገብርኤልና መስቀል ክብራ የሚባሉ ደጋግ ባለ ትዳሮች ነበሩና በእንግድነት ከቤታቸው አደሩ:: ቤቱ በቅጽበት በበረከት ሞላ:: እነርሱም የጻድቁን አምላክ አመሰገኑ::

ቀጥሎም በመስቀል ክብራ መሪነት ጻድቁ ዘዮሐንስ ወደ ክብራን ገብርኤል ደሴት ገቡ:: [በነገራችን ላይ ደሴቱ ክብራን የተባለ መስቀል ክብራ በምትሰኘው ደግ ሴት ስም ነው:: እርሷና ባሏ ገብርኤል የተቀደሱ ሰዎች ነበሩና::]

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ ወደ ደሴቶቹ [ክብራንና እንጦንስ ኢየሱስ] እንደ ገቡ ደሴቶቹ በግማሹ የስውራን ቤት : እኩሉ ደግሞ የጣዖት [ዘንዶ] አምላኪዎች መኖሪያ ነበር:: ጻድቁ ክብራን ገብርኤልንና እንጦንስ ኢየሱስን የመሠረቱት በ1315 ዓ/ም አካባቢ በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን ነው:: በአካባቢው ዘንዶ ይመለክ ነበርና ያንን በጸሎታቸው አጥፍተው ሕዝቡን አጥምቀዋል::

በዚያም ገዳሙን የወንድና የሴት ብለው ከፈሉ:: የወንዶች ክብራን ሲሆን ሴት አይገባበትም:: አበ ምኔቱም ራሳቸው ጻድቁ ነበሩ:: የሴቶች እንጦንስ ኢየሱስ ከካህናት በቀር ወንድ አይገባበትም:: እመ ምኔቷም እናታችን ቅድስት ክብራ [መስቀል ክብራ] ሆነች::

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ በክብራን ለሰላሳ አምስት ዓመታት ተጋድለዋል:: ለጸሎት ከመቆማቸው ብዛት እግራቸው አብጦ : ቆሳስሎ ነበር:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ይገለጽላቸው : ያነጋግራቸውም ነበር::

እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርተው: ለወንጌል እንደሚገባ ኑረው: በተወለዱ በመቶ አምስት ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ጌታችንም በስማቸው ለተማጸነና ገዳማቸውን ለሳመ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ልደታቸው ደግሞ ኅዳር ፲፫ [13] ቀን ይከበራል:: ገዳማቸው [ክብራን ገብርኤልና እንጦንስ ኢየሱስ] ድንቅ ነውና እንድታዩት ተጋብዛቹሃል::


🕊  †  ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት  †  🕊

† በምድረ ግብጽ ከታዩ ታላላቅ ከዋክብት አንዱ ቅዱስ ኖብ በሃገረ ንሒሳ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ዘመኑም ዘመነ ሰማዕታት [፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነው:: ወላጆቹ በልጅነቱ ብዙ ሃብት ትተውለት ያርፋሉ:: ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ካህኑ ስለ ምናኔና ሰማዕትነት ሲሰብክ ይሰማዋል::

ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ በቤቱ የነበረውን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ መስቀለ ክርስቶስን ሊሸከም ወደ ዐውደ ስምዕ [የምስክርነት አደባባይ -የክርስቲያኖች መገደያ ቦታ] ተጓዘ:: በዚያም በጉባዔ መካከል ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ ምክንያት በሰብዓዊ አካል ሊሸከሙት የማይችሉትን መከራ በልጅ ገላው ተቀብሏል::

በዚያው ልክም ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: በተአምራቱና በጣዕመ ስብከቱም ከመቶ ዘጠና ሺህ በላይ አሕዛብን ወደ ክርስትና መልሶ ሁሉም ተሰይፈዋል:: በእሳት: በስለት: በሰይፍ: በባሕርና በየብስ መከራን ከተቀበለ በኋላ በዚህች ቀን አክሊለ ክብርን ይቀበል ዘንድ አንገቱን ተከልሏል::

ጌታችን የገባለት ቃል ኪዳኑ ግሩም ነውና ዛሬ በግብጽ በድምቀት ይከበራል:: ምንም በእድሜ ልጅ ቢሆን ቤተ ክርስቲያን አባ [አባታችን] ኖብ ትለዋለች::

† ቸር ጌታ መድኃኔ ዓለም በጻድቁና በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን [ኢትዮጵያዊ]
፪. ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት
፫. መቶ ዘጠና ሺህ ሰማዕታት [የአባ ኖብ ማኅበር]
፬. አባ ተክለ አዶናይ ዘደብረ ሊባኖስ
፭. አቡነ ተወልደ መድኅን [ኢትዮጵያዊ]
፮. አባ ስምዖን ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
፯. ቅድስት ክብራ [መስቀል ክብራ] ዘእንጦንስ ኢየሱስ

[    † ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤጲስቆጶስ]
፫. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮. ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፯. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም [ኢትዮጵያዊ]

† "ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም::" † [ኤፌ. ፩፥፲፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
2024/09/29 17:27:00
Back to Top
HTML Embed Code: