Telegram Web Link
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰዉ ድንገተኛ የመሬት ናዳ ምክንያት የወገኖቻችን ሕይወት በማለፉ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ሰላማዊ እረፍትን፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።
††† እንኳን ለቅዱሳኑ ገብርኤል ሊቀ መላእክት: ቂርቆስ ወኢየሉጣ: በጥላን ጠቢብ እና ሰማዕታተ እስና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት:: በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር:: የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው:: በዛው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር::

ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች:: እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ::

ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ" አለችው:: ንጉሡ ተቆጣ:: "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል" አለችው:: ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ: ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው:: ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል" አለችው::

አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው:: "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ:: "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል:: መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል" አለው::

ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ: ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል" አለው:: በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ::
እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው::

ሰውነታቸውን ቸነከረ: አካላቸውን ቆራረጠ: ዓይናቸውን አወጣ:: ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው:: በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ: አረር: ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት::

የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው:: በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር:: የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል:: ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው:: ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ::

"ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናሕ እናቴንም አጽናት" ሲል ለመነ::
"እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ:
እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል::
በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ::

ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ: አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት" አለችው:: ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው:: በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው:: የነደደውን ውኃ አደረገው:: ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል::

††† ቅዱስ በጥላን ጠቢብ †††

††† ቅዱሱ ከአሕዛብ ወላጆቹ ተወልዶ: ያደገውም በጣዖት አምልኮ ነው:: በሙያው እጅግ የተመሠከረለት ሐኪም ነበር:: የሃገሩ ሰዎች "ጠቢብ" እያሉም ይጠሩታል:: በጥላን ምንም ጣዖት አምላኪ ቢሆን በተፈጥሮው ተመራማሪና ቅን ነበር::

አንድ ካህንም በጐረቤቱ ነበርና ዘወትር ስለ ሃይማኖት ይከራከሩ ነበር:: ካህኑ ሌሊት ሌሊት ስለ በጥላን ተግቶ ይጸልይ ነበርና ተሳክቶለት አሳመነው::

አንድ ቀን በጥላን መንገድ ሲሔድ እባብ ሰው ነድፎ ለሞት ደርሶ አየውና ጸሎት አድርሶ ስመ ክርስቶስን ቢጠራ የተነደፈው ድኖ እባቡ ሞተ::

በዚህ ተዓምር ደስ ብሎት ወደ ካህኑ ሒዶ ተጠመቀ:: ከዚያም ጾም ጸሎትን ጀመረ:: በየቦታው እየዞረ ሕሙማንን እንደ ቀድሞው በመድኃኒት ሳይሆን በጸሎት ያድናቸው ነበር:: ስላዳናቸውም በርካቶቹ ወደ ክርስትና መጡ::

የአካባቢው ሰው: ወላጆቹን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሆኑ:: በመጨረሻም ቅዱስ በጥላን: ቤተሰቦቹ: ካህኑና ከደዌ የዳኑት ወገኖቹ በአካባቢው ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ሰብከው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና †††

††† እስና ማለት ግብጽ ውስጥ የምትገኝ የቀድሞ አውራጃ ናት:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በከተማዋ በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የእንዴናው መኮንን መጥቶ "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: ሕዝቡ በአንድ ድምጽ መለሱ:- "ይሕማ ፈጽሞ ሊደረግ አይችልም::" መኮንኑ ተቆጥቶ "ሁሉንም ግደሉ" አለ::

ወታደሮቹ ሰው አልመረጡም:: ከታዘለ ሕፃን አልጋ ላይ እስካለ ሽማግሌ: ከጤነኛ እስከ ሕመምተኛ: ሁሉንም ጨፈጨፏቸው:: ከተማዋ በደም ተነከረች:: ከከተማዋ ክርስቲያኖች ወሬ ለመንገር አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም:: ሁሉም ስለ ክርስትና ደማቸውን አፈሰሱ::

††† ጌታችን ስለ ሰማዕታቱ ብሎ: ደማቸውንም አስቦ በሃይማኖታችን ያጽናን:: ከመከራም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያድለን::

††† ሐምሌ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ቂርቆስ ወእሙ ኢየሉጣ
3.ቅዱስ በጥላን ጠቢብ ሰማዕት እና ማኅበሩ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
2.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
3.አቡነ ስነ ኢየሱስ
4.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ መራቆት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን::' ተብሎ እንደተጻፈው ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለታላቁ ሰማዕት ማር ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም †††

††† ለስም አጠራሯ ክብር ይሁንና እመ ብርሃን ድንግል ማርያም በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታለች:: በዓሉ ከሰላሳ ሦስቱ የእመቤታችን በዓላት እንደ አንዱ አይቆጠርም:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሊቃውንት በዓታ ከበዓታ ጋር ይስማማል ብለው የታኅሣሥ ሦስትን በዓል ከሰላሳ ሦስቱ ደምረውታል::

እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ሁለት ጊዜ ሲሆን:-
1.ዛሬ የምናከብረውና በተወለደች በሰማንያ ቀኗ የገባችበት ነው:: (ከግንቦት 1 ጀምረን እናስላው: 80 ቀን ይመጣል::)
ኦሪት እንዳዘዘው ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና ንጽሕት ሕፃን ድንግል ማርያምን ታቅፈው: የርግብ ልጆች (ግልገሎች): ዋኖስም ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሒደዋል::
ካህናቱ ዘካርያስና ስምዖን ወጥተው በደስታ ተቀብለዋቸዋል:: እመቤታችን ለወላጆቿ ማኅጸን የከፈተች በኩር ናትና በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋታል::

2.ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደ ስዕለታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋት ተመልሰዋል::

እግዚአብሔር ዛሬ ያልቃል: ነገ ይደቃል የማይባለውን የድንግል እናቱን ፍቅር አብዝቶ ያድለን:: በረከቷም በእኛ ላይ ጸንቶ ይኑር::

††† ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት †††

††† በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው:: እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች::

ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር:: ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ:: እሱ ክርስትና ለማስነሳት: ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ:: ሚስት ወገኖቿ ባለስልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብጽ አሳደደችው::

ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ: ያለቅስም ገባ:: እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ:: ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ: ተጠመቀ:: ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ: ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር::

በዛው ልክ ደግሞ ገና በሃያ ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል: በውበቱም ደመ ግቡ: በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር:: ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት:: እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል::

ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም:: ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው:: እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል::

የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ" አላቸው:: እነርሱ ግን ተሳለቁበት:: ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ:: በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው::

አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ:: ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርቧቸው ተመለከተ:: በስመ ሥላሴ አማትቦ: በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው:: የዘንዶውም ርዝመት ሃያ አራት ክንድ ነበር::

ከነገር ሁሉ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ: ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው:: እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ: ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው::
ክርስቶስ ተክዶ:
ጣዖት ቁሞ:
አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው:
የክርስቲያኖች ደም ፈሶ:
ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ:: እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው:: የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ: ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ::

††† ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ:- "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ: ወእሠውዕ ሎቱ - እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ: ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ::" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ:: ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት::

በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት:: እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውኃ አደረገው:: ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ:: እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና: ታገሠ::

በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ: ያጻፈ: ያነበበ: ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::

በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ:: ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል:: እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል::

††† ቸሩ ፈጣሪ ከሰማዕቱ በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም (በሰማንያ ዕለት)
2.ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት (የሠራዊት አለቃ)
3.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ
4.አራት መቶ አራት ሰማዕታት (የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር)
5.ቅድስት አውስያ (የማር ቴዎድሮስ እናት - በልጇ ምክንያት ያመነች እናት ናት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

††† "እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን::" †††
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. ፸፫)

††† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ:: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
“… ያችኛይቱ ሔዋን ከአዳም ተገኝታ የተሠራችና አዳም ወደ እርስዋ እያየ ‘ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ናት’ የሚላት ናት፡፡

ይህችኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ግን ከአዳም የተገኘች ሳትሆን አዳምዋ ክርስቶስ ሥጋው በጅራፍ ግርፋት ሲቆስልና አጥንቶቹ ሲቆጠሩ በጭንቀት እያየች ‘ይህ አጥንት ከአጥንቴ ነው ፤ ይህ ሥጋም ከሥጋዬ ነው’ የምትል ሔዋን ናት፡፡

የቀደመችዋ ሔዋን አዳምዋ በእርስዋ ምክንያት ጠፍቶ ‘አዳም ሆይ ወዴት ነህ?’ ተብሎ ሲፈለግ በዛፎች መካከል ሆኖ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ‘ፈርቼ ተሸሸግሁ’ የሚል አዳም ነበረ::

ሁለተኛይቱ ሔዋን ድንግል ግን አዳምዋን ፍለጋ የምትጨነቅና ወዴት ነህ? ስትለው አዳምዋ ‘በአባቴ ቤት እኖር ዘንድ እንዲገባኝ አታውቁምን’ ብሎ የሚመልስላት ከአባቱ እቅፍ ያልተለየ አዳም እናት ናት፡፡

ለድንግል ማርያም ክርስቶስ ከእርስዋ የተገኘ አዳምዋ ብቻ ሳይሆን በቀናተኞቹ ቃየኖች አይሁድ በግፍ የተገደለባት አቤልዋም ጭምር ነው፡፡ ልዩነቱ የአቤል ደም ወንድሙን የሚከስስ ደም ሲሆን የእርስዋ ልጅ የክርስቶስ ደም ግን ‘ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር’ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ ደም’ ነው"

(የብርሃን እናት ገጽ 100 በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም : ቅዱስ ዑራኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊 † ድንግል እመቤታችን እና ቅዱስ ዑራኤል † 🕊

† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዚህች ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል :-

፩. ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም ተሸክሞ: አስቀድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ: የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

፪. ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በአራቱም አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል::

፫. ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::

፬. ለብዙ ቅዱሳን [አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ] ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል::


🕊 † አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮጵያዊ † 🕊

† ወላጆቻቸው ማርቆስ እና እግዚእ ክብራ ይባላሉ:: ተአምራትን ገና ከእናታቸው ማኅጸን ጀምሮ ይሠሩ የነበሩት ጻድቁ በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው መንነዋል:: በስብከተ ወንጌልም ትግራይና አካባቢውን አድርሰዋል:: በነዚህም ጊዜያት ብዙ አርድእትን አፍርተዋል::

በጋስጫ ገዳም መስርተው የወንድና የሴት ብለውም ለይተዋል:: ሲጸልዩም ሆነ ሲያስተምሩ ተደሞ ይመጣባቸው የነበረ ሲሆን አንድ ቀን እባቡን ዓሣ አድርገው ደቀ መዛሙርትን አስደንቀዋል::

ከጾም: ከጸሎትና ከስግደት ባሻገር ከወቅቱ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን መከራ በመቀበላቸው እንደ ሰማዕትም ይቆጠራሉ:: ከብዙ የገድል ዓመታት በኋላም በ1330 ዓ/ም በዚህች ቀን ትግራይ ውስጥ ዐርፈዋል:: በቆይታ ግን ወደ ጋስጫ ዐጽማቸው ፈልሷል::


🕊 †  ቅዱስ ላዕከ ማርያም ኢትዮጵያዊ †  🕊

† ቅዱሱ የአፄ ናዖድ የልጅ ልጅ : የቅድስት ሮማነ ወርቅ ልጅ : የልብነ ድንግል የእህት ልጅና የገላውዴዎስ አጐት ነው:: በግራኝ አህመድ ዘመን ተማርኮ ወደ የመን : ከዛም ቱርክ ተወስዷል::

ሃይማኖቴን አልክድም ስላለ ብዙ አሰቃይተው : አባለ ዘሩን ቆርጠው ጃንደረባ አደረጉት:: በድንቅ ተአምር ግን ወደ ሃገሩ ተመለሰ:: እስከ ዕለተ ሞቱም ነዳያንን ሲያበላ ኑሮ ዛሬ ዐርፏል::


🕊  †  ቅዱስ ሱስንዮስ  †   🕊

በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የኤፌሶን ሰው ሲሆን ጃንደረባም ነበር:: በ431 ዓ/ም ሁለት መቶውን የጉባዔ ኤፌሶን ሊቃውንት አገልግሎ በዛው ዓመት አርፏል:: ቅዱስ ቄርሎስ ገንዞ ቀብሮታል::


🕊  †  ብጹዕ አወ ክርስቶስ  †   🕊

ከተባረከች ሚስቱ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ : ግን ደግሞ በድንግልና ኑረዋል:: ቀን ቀን እንግዳ ሲቀበሉ: ነዳያንን ሲያበሉ ውለው ሌሊት ሲገሰግዱና ሲጸልዩ ያድሩ ነበር:: ጌታችን ከሰማይ መስክሮላቸው ዛሬ ዐርፈዋል::


🕊  †  ቅዱስ  ዮራኖስ    †    🕊

በሉቃስ ወንጌል ላይ [ሉቃ.፳፫፥፵፯] የምናገኘው የመቶ አለቃው ሲሆን በጌታችን ትንሣኤ ቀን የጠፋች ዓይኑ በርታለት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል::

† ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟን ፍቅሯን : ከቅዱሳኑ ሁሉ ጸጋ በረከትን እግዚአብሔር ያድለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፳፩ [ 21 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፫. አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጻድቅ [ኢትዮጵያዊ]
፬. ቅዱስ ላዕከ ማርያም ሔር [ኢትዮጵያዊ]
፭. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ [ኢትዮጵያዊ] ልደታቸው
፮. ብጹዕ አወ ክርስቶስና ሚስቱ [ጻድቃን]
፯. ቅዱስ ሱስንዮስ ጻድቅ
፰. ቅዱስ ዮራኖስ መኮንን [የመቶ አለቃው]

[  † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. አበው ጎርጎርዮሳት
፪. አቡነ ምዕመነ ድንግል
፫. አቡነ አምደ ሥላሴ
፬. አባ አሮን ሶርያዊ
፭. አባ መርትያኖስ ጻድቅ

"እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም : ስለ ዮፍታሔም : ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም : ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ:: . . ." † [ዕብ.፲፩፥፴፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለሰማዕታት አበው አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊ : ቅዱስ መቃርስ እና ቅዱስ ለውንትዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 † ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ †  🕊

† ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ምንም እንኳ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ያን ያህል ዋጋ ቢከፍሉም ትውልዱም : መንግስቱም : ራሷ ቤተ ክርስቲያናችንም ተገቢውን ክብር ሰጥተው እያሰቧቸው አይደለም:: እስኪ እንዲያው ቢያንስ እንደ ክርስቲያን : አንድም እንደ ኢትዮጵያዊ እነዚህ ነገሮቻቸውን እናስብ::

ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከልጅነታቸው ጀምረው ትምሕርት : ትሕርምትና ደግነት ወዳጅ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳሳት የምትሻበት ጊዜ ነበርና በፈቃደ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ የሃገራችን አራት አባቶች ጵጵስናን ተሾሙ::

እነርሱም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ እና አበው አባ ሚካኤል: አባ አብርሃም እና አባ ይስሐቅ ናቸው:: የተሾሙትም ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ/ም ነው:: አቡነ ጴጥሮስ ከተሾሙ በኋላ በሐዋርያዊ አገልግሎትና በጸሎት ተግተው ኑረዋል::

በ፲፱፻፳፰/1928 ዓ/ም ፋሺስት ጣልያን ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ቆራጡ ጳጳስ በዱር በገደል ለመሔድ ተነሱ:: በየበርሃው እየሔዱ አርበኞችን ሲያጽናኑ : ሲናዝዙ : ሲባርኩም ቆይተዋል:: ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ረሃብ : ጥም : እንግልትን ታግሰዋል::

በተያዙባት በዚያች ሌሊትም በጣልያኖች ለሮም እምነትና ለአገዛዙ እንዲያጐበድዱ ተጠየቁ:: ቆራጡ ሰው ግን እንቢ ቢሉ የሚደርስባቸውን እያወቁ "አይደረግም" አሉ:: በማግስቱ በአደባባይ መትረየስ ተደግኖባቸው አሁንም ጥያቄ ቀረበላቸው::

አቡነ ጴጥሮስ አፋቸውን ከፍተው ሊናገሩ ጀመሩ:- "የሃገሬ ሕዝብ ሆይ! ለሃገርህ : ለሃይማኖትህ ባትጋደል ትውልድ ይፋረድህ:: ለጣልያን ግን እንኳን ሰው ዛፍ ቅጠሉ መሬቱ እንዳይገዛለት አውግዣለሁ" አሉ:: በደቂቃዎች ልዩነት በግራዚያኒ ትዕዛዝ የመትረየስ ጥይት ዘነበባቸው::

አካላቸው ተበሳስቶ በሰንሰለት እንደ ታሠሩ መሬት ላይ ወደቁ:: አንዱ ወታደር ቀርቦ ቢመለከት ትንሽ ትንፋሽ ነበረቻቸው:: "ይሔ ቄስ አልሞተም" ብሎ ጭንቅላታቸው ላይ ተኮሰባቸው::

አቡነ ጴጥሮስ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ተሠው:: ነገሩ በአርበኞች ዘንድ ሲሰማ ትግሉ ተቀጣጠለ:: ይሄ የተደረገው ሐምሌ ፳፪ [22] ቀን በ፲፱፻፳፰/1928 ዓ/ም ነው:: አቡነ ጴጥሮስም በተ/መ/ድ [UN] የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት [MARTYR OF THE MILLENIUM] በመባል ይታወቃሉ::


🕊  †  ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት  †  🕊

† ሰማዕቱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ [ሶርያ] በ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስ እና የቅድስት ሶፍያ ልጅ ነው:: ምንም በቤተ መንግስት ውስጥ ቢያድግም ከወላጆቹ ፍቅረ ክርስቶስን : ንጽሕናንና ደግነትን ወርሷል::

በተለይ ነዳያንን ሰብስቦ ዕለት ዕለት ያበላ ነበር:: [መቃርስ ማለት በልሳነ ዮናኒ ብጹዕ : ንዑድ : ክቡር ማለት ነው::] ቅዱሱ ያ የመከራ ዘመን ሲመጣ ሁሉም ቤተሰብ ስለ ክርስቶስ መሞትን በመምረጡ እርሱም ደስ እያለው የመከራው ተካፋይ ሆኗል::

ያን የመሰለ የቤተ መንግስት ክብር ስለ ክርስትና ናቀው:: ተገረፈ:: ተሰቃየ:: በእሳትም ተቃጠለ:: አንድ ጊዜም በአደባባይ የሞተ ሰው በጸሎቱ አስነስቶ "መስክር" አለው:: ከሞት የተነሳውም የክርስቶስን አምላክነት በመመስከሩ በአደባባይ የነበሩ ብዙ አሕዛብ በክርስትና አምነው ተሰይፈዋል::

ቅዱስ መቃርስን ግን ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን አንገቱን ቆርጠውታል:: ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አጽሙን አፍልሶ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጾለታል::


🕊 †  ቅዱስ ለውንትዮስ ሰማዕት  †  🕊

† ቅዱሱ የተወለደው በተመሳሳይ ዘመን [በቅዱስ መቃርስ] ሲሆን ሃገሩ ጠራብሎስ ትባላለች:: በወቅቱ በወታደርነት ነገሥታቱን ያገለግል ነበር:: ድንግል : ደም ግባት የሞላለት ወጣት ስለ ነበር በሰዎች ፊት ሞገስ ነበረው::

እርሱ ግን ምንም ወታደር ቢሆን ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: በተለይ ደግሞ የዳዊትን መዝሙር እየመላለሰ ይጸልየው : ይወደው ነበር:: ንግግሩ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት የታሸ ነውና ብዙ ጓደኞቹን ከክህደት ወደ ሃይማኖት : ከክፋት ወደ ደግነት መልሷል::

የመከራ ዘመን በደረሰ ጊዜም በገሃድ ስመ ክርስቶስን ይሰብክ ነበር:: ክፉ ሰዎች ከሰውት በመኮንኑ ፊት በቀረበ ጊዜም አልፈራም:: ወታደሮቹ መሬት ላይ ጥለው እየደበደቡት : ደሙ እንደ ጐርፍ እየተቀዳ እርሱ ግን ይዘምር ነበር::

በመጨረሻም ስለ ክርስቶስ ፍቅር በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፏል:: ቅዱስ ለውንትዮስ እጅግ ተአምረኛ ሰማዕት ነውና በእምነት እንጥራው::

† እግዚአብሔር ዐጽመ ሰማዕታትን ይጠብቅልን:: ከሰማዕታቱ ጽናትን : ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት [ ኢትዮጵያዊ ]
፪. ቅዱስ መቃርስ ሰማዕት [ የፋሲለደስ ልጅ ]
፫. ቅዱስ ለውንትዮስ [ ክቡር ሰማዕት ]
፬. አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት [ ቅዳሴ ቤታቸው ]
፭. ቅዱስ መርካሎስ

[  †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫. ቅዱስ ደቅስዮስ [ የእመቤታችን ወዳጅ ]
፬. አባ ጳውሊ የዋህ

† "እንግዲህ አትፍሯቸው:: የማይገለጥ የተከደነ: የማይታወቅም የተሠወረ ምንም የለምና:: በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ:: በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን: ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም: ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ::" † [ማቴ. ፲፥፳፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/29 15:22:25
Back to Top
HTML Embed Code: