Telegram Web Link
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

✞   የሰኔ ፳፫ [ 23 ]   ✞

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ  ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

🕊 † ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል †  🕊

መፍቀሬ ጥበብ :

¤ ጠቢበ ጠቢባን:
¤ ንጉሠ እሥራኤል:
¤ ነቢየ ጽድቅ:
¤ መስተሣልም [ ሰላማዊ ]  . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትና የቅድስት ቤርሳቤህ [ቤትስባ] ልጅ ነው:: ከ ፫ [3] ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ ፲፪ [12] ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

ቅዱስ ዳዊት ፸ [70] ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም:: እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ፲፪ [12] ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው::

"ልጄ ሆይ ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን: ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ: ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት: ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም: አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ፵ [40] ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

ግሩም በሆነ ፍትሑ: በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ ንግስተ ሳባ /አዜብ/ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን [እብነ መለክን] ጸነሰች:: በኋላም ታቦተ ጽዮንና ሥርዓተ ኦሪት መጣልን:: ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን ድንግል ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

ነገር ግን :-

¤ አንደኛ ሰው [ሥጋ ለባሽ] ነውና:
¤ ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ እመ ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ
[ከፈርዖን ልጅ] ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ: አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን ፭ [5] መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም :-

፩. መጽሐፈ ጥበብ
፪. መጽሐፈ ተግሣጽ
፫. መጽሐፈ መክብብ
፬. መጽሐፈ ምሳሌ
፭. መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ: ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ፶፪ [52] ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል::

🕊  †   አባ ኖብ    †    🕊

ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ አርፏል:: በዚሕ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ቢኖሩም ዋናው ይኼው ቅዱስ ነው::

አባ ኖብ እንደ ገዳማውያን በበርሃ የተጋደለ: እንደ ሊቃውንት መጻሕፍትን ያመሰጠረ: በተለይ ደግሞ በዘመነ ሰማዕታት ጭንቅ ጭንቅ መከራዎችን የተቀበለ አባት ነው:: ስለ ገድሉ ብዛት "ኃያል ሰማዕት": አንገቱን ስላልተቆረጠም "ሰማዕት ዘእንበለ ደም" ይባላል:: ዘመነ ሰማዕታትን ካለፉ ፸፪ [72] ቱ ከዋክብትም አንዱ ነው::

ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን: ከኃያሉ ሰማዕት አባ ኖብ በረከትን አምላካችን ይክፈለን::

🕊

[ †  ሰኔ ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፪. ቅዱስ አባ ኖብ [ሰማዕት ወጻድቅ]
፫. ቅዱሳን መርቆሬዎስ: ፊልዾስና ቶማስ [ሰማዕታት]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩ ፡ ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
፪ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫ ፡ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬ ፡ አባ ሳሙኤል
፭ ፡ አባ ስምዖን
፮ ፡ አባ ገብርኤል
፯ ፡ ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ

" የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ: ፀሐይ: ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ: ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ:: ሰባኪው :- "ከንቱ: ከንቱ: ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::" [መክ.፲፪፥፩-፱]  (12:1-9)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

=>ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ): ሐጋይ (በጋ): ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

+በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ብሎናልና (ማቴ. 24:20) ልንጸልይ ይገባናል:: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ: አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ:-

"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)

=>ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን:: ተረፈ ዘመኑንም የንስሃ: የፍሬና የበረከት ያድርግልን::

=>በዚሕች ዕለት እነዚህ ቅዱሳን ይከበራሉ:-

+" ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ "+

+በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር:: እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች:: አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር::
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከ72ቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል:: ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል:: (ዮሐ. 14:22)

+ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር 3 ዓመት ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል:: አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል:: አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው:: ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል::

+" ቅዱሳን ዺላጦስና አብሮቅላ "+

=>ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን:: የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል:: የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም::

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል:: ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል:: በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል::

+ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው:: ጌታችንን ተከትላ: ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ: ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች:: ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ::

=>ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ: ከዺላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን::

=>ሰኔ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ሰማዕቱ ዺላጦስ መስፍን
3.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
4.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት
5.የጸደይ መውጫ / የክረምትመግቢያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ /አባ ቡላ/
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

=>+"+ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:1)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን †††

††† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ "አውሴ" ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ : ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር::

ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምሕሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም::

አውሴን "ኢያሱ" ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው:: ኢያሱ ማለት "መድኃኒት" ማለት ነው::
ለዚሕም ምክንያቶች አሉት:- ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል:: ምድረ ርስትን አውርሷል::
ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው::

ቅዱስ ኢያሱ በበርሃ ለ40 ዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዝዞታል (አገልግሎታል):: እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል::

በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን : ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው 80 እየሆነ ነበር::

††† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:
¤ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ
¤ሕዝቡን አሻግሮ
¤የኢያሪኮን ቅጥር 7 ጊዜ ዙሮ
¤በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ
¤የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::

የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዚያን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል : በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚያች ዕለትም ለ12ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ::

ሰባት አሕጉራተ ምስካይ (የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ40 ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ አላቸው:-
"እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: (ኢያ. 24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::

ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ 3 ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ3 ወገን (በነፍስ: በሥጋ: በልቡና) ድንግል ናት:: አንድም በ3 ወገን (ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ) ሲል ያመሰገናት::

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ80 ዓመት: በተወለደ በ120 ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ110 ዓመቱ ይላል) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ30 ቀናት አለቀሱለት::

††† በወዳጁ በኢያሱ እጅ የአሕዛብን ቅጥር ያፈረሰ እግዚአብሔር የእኛንም የኃጢአታችንን ግንብ በወዳጆቹ ምልጃ ያፍርስልን:: ከቅዱሱ ነቢይም በረከትን ያሳትፈን::

††† ሰኔ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን
2.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (ቅዳሴ ቤቱ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" †††
(ኢያሱ. 24:14)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ † እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

🕊 † ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ † 🕊

† ሐናንያ ቁጥሩ ከ፸፪ ቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው:: ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ : በሕገ ኦሪት አድጐ : ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው:: እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከ፸፪ ቱ አርድእት ደመረው::

ለ፫ ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ : ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር:: ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን" ማለታቸውን አስቀምጦልናል:: [ሉቃ.፲፥፲፯] ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ፶ ኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር:: በሁዋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ዻዻስ አድርገው ሹመውታል:: ጌታ ባረገ በ፰ ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል [የሁዋላው ቅዱስ ዻውሎስ] ወደ ደማስቆ የተጉዋዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር::

ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዐይኑን አጠፋው:: ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው:: ከ፫ ቀናት በሁዋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል::

ሳውል [ዻውሎስ] ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር:: ፪ ቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው : ፈወሰው : አጠመቀው : በጐ መንገድንም መራው:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ ይሰኛል:: [ሐዋ.፱፥፩-፲፱]

ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ:: መከራንም ተቀበለ:: በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል::

🕊 † ቅዱስ ቶማስ ዘሰንደላት † 🕊

† በ፫ ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ሰማዕታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ ሰማዕትነት ሕይወት የገባው በ፲፩ ዓመቱ በመላእክት መሪነት ነው:: ገና ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደ ቀረበ መኮንኑ "ክርስቶስን ካድና ልሹምህ" ቢለው ሕጻኑ ቅዱስ ቶማስ ተቆጥቶ : "አንተ ሰነፍ መኮንን" ብሎ ገስጾ : በጐችን ይመልስባት በነበረችው ጅራፍ ገርፎታል:: ይሔም በዘመኑ የመጨረሻው የድፍረት ደረጃ ነበር::

† በዚህም ምክንያት በሕጻን ገላው ላይ የተቀበለው መከራ ሊናገሩት ይከብዳል::

¤ ግርፋት
¤ እሳት
¤ አራዊት በእርሱ ላይ አልፈዋል::

አካሉ ተቆራርጧል:: አንድ ጊዜም "ለጣዖታችሁ እንድሰግድ አምጡት" ብሏቸው ልክ ከፊቱ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢጸልይ መሬት ተከፍታ ውጣቸዋለች:: እሱን ያሰቃየው የነበረውን መኮንንም ከደዌው አድኖ ከነ ሠራዊቱ አሳምኖታል:: ሕጻኑን ቅዱስ ቶማስን ግን ያላመኑ አረማውያን በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔዷል::

† አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያው በረከት : ከሰማዕቱም ምልጃ አይለየን::

🕊 † ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ  †  🕊

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው: በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

ሊቁ የተወለደው መጋቢት ፳፯ ቀን በ፬፻፴፫ ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በ፫ ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ-እኔስ ፫ ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም :-

፩. ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
፪. ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
፫. ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ ፯ ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ፭ ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ፲፪ ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል:: ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በሁዋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን: ዕጸበ ገዳምን: ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ: ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ [በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት] ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል:: በዘመኑም:-

፩. የ፬፻፶፩ ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል
፪. ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል
፫. በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል
፬. ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በሁዋላ በተወለደ በ፸፪ ዓመቱ በ፭፻፭ ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ ፳፯ ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ::  ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሰኔ ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ [ከ፸፪  ቱ አርድእት]
፪. ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት [ዘሰንደላት]
፫. ቅዱስ አልዓዛር ነዳይ [በነዌ ደጅ የወደቀ : ቀጥሎ ደግሞ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ የተገኘ ጻድቅ - ሉቃ.፲፮፥፲፱]
፬. ቅዱስ ማማስ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪. አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
፫. ቅዱስ መቃርስ [የመነኮሳት ሁሉ አለቃ]
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯. ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

" በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ:: ጌታም በራዕይ :- "ሐናንያ ሆይ!" አለው:: እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ" አለ:: ጌታም :- ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ:: በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ:: እነሆ እርሱ ይጸልያልና:: ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል" አለው::" † [ሐዋ.፱፥፲-፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር
† ወለወላዲቱ ድንግል
† ወለመስቀሉ ክቡር

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †            †            †
▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬
💖               🕊                  💖
2024/11/19 23:23:57
Back to Top
HTML Embed Code: