Telegram Web Link
5•­3- ØÈ- è«ru 5 •u---
ASR by NLL APPS
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት ስምንት (፰)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

🛎 ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፱

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ዘጠኝ በዚች ቀን የከበረ በሶርያ አገር ላሉ መነኰሳት አባት የሆነ ታላቁ አባ በርሱማ አረፈ።
   
❖ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ሳሚሳጥ ከሚባል አገር ሰዎች ውስጥ ናቸው አንድ በዋሻ ውስጥ የሚኖር ሰው በእርሱ ላይ ትንቢትን ተናገረ ከመወለዱ አስቀድሞ ለአባቱ እንዲህ አለው የትሩፋቱ ዜና በሶርያ ሀገር ሁሉ የሚሰማ ጣዕም ያለው ፍሬ ከአንተ ይወጣል ከእርሱ የሚሆነውንም አስረዳው።

❖ ተወልዶም አድጎ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ በደረሰ ጊዜ ከወላጆቹ ሸሽቶ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ደርሶ በዚያ ስሙ አብርሃም ከሚባል ሰው ዘንድ ተቀመጠ እርሱም ወላጆቹን ስለፈራ ከዚያ ገዳም ሰደደውና ሒዶ በአለት ውስጥ ኖረ በዚያም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ወሬውም በሶርያ አገሮች ሁሉ በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ደቀመዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ የዚያ ቦታ ውኃ ግን እጅግ መራራ ነበር በላዩ በጸለየ ጊዜ ተለውጦ ጣፋጭ ሆነ።

❖ እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ከእርሳቸውም በአንዲት ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከበአቱ ርቆ ሳለ የፀሐይ መግቢያ ሰዓት ተቃረበ የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ወደ በአቱም እስቲደርስ ያን ጊዜ ፀሐይን አቆመለት፤ በሌላ ጊዜም እንዲህ ሆነ ረዓም የምትባል አገር ነበረች ስዎቿም ከሀዲዎች ናቸው፤ በላያቸውም ዝናብ ተከለከለ በተጨነቁም ጊዜ ወደ ከበረ አባ በርሱማ መጥተው ለመኑት እርሱም ገሠጻቸው እንዲህም አላቸው ከክህደታችሁ ተመልሳችሁ በእግዚአብሔር ብታምኑ እርሱ ብዙ ዝናብን ያዘንብላችኋል እነርሱም እናምንበታለን አሉት።

❖ በዚያን ጊዜ ጌታችንን ለመነውና ብዙ ዝናብ ዘነበላቸው የሀገር ሰዎችም ሁሉ በጌታችን አመኑ፤ እንዲሁም ሰዎቿ ከሀድያን የሆኑ ሌላ ሀገር ነበረች እነርሱንም ገሥጾ መክሮ አስተምሮ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የጣዖቶቻቸውንም ቤቶች አፈረሰ፤ ይህም ቅዱስ ለራሱ ቦታ አዘጋጅቶ በዚያ ሳይቀመጥ ሃምሣ አራት ዓመት ቁሞ ኖረ ከመትጋት የተነሣ ሲደክመው ከናሱ ግድግዳ ላይ ተደግፎ ያሸልባል በየሰባት ቀንም ይጾማል።

❖ የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ ሊያየው ወዶ ወደርሱ ላከ የትሩፋቱንና የቅድስናውን ዜና ከብዙዎች ሰዎች ሰምቶ ነበርና እርሱም ወደ አባ ስምዖን መጥቶ እርስበርሳቸው በረከትን ተቀባበሉ ከዚህም በኋላ ወደ ገዳሙ ተመለሰ፤ በሶርያ አገርም አስተማረ በፊታቸው ተአምራትን በአደረገ ጊዜ በትምህርቱ ብዙዎች አመኑ።
❖ ዳግመኛም ወደ ታናሹ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ሒዶ በቀናች ሃይማኖት አጸናው ንጉሡም ብዙ ገንዘብን ሰጠው እርሱ ምንም ምን አልወሰደም በአንጾኪያም አገር በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው ንጉሥ ጻፈለትና ኀቲም ቀለበቱን ሰጠው፤ በከሀዲው ንስጥሮስ ምክንያት ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት በኤፌሶን ከተማ በተሰበሰቡ ጊዜ ከእሳቸው ጋር ይህ ቅዱስ አለ፤ ከእርሳቸውም ጋር ንስጡርን አወገዘው ዳግመኛም በአንጾኪያ አገር ያሉ መኳንንት መሳፍንት ሹማምንት ሁሉም ይታዘዙለት ዘንድ ንጉሥ ደብዳቤን ጻፈለት እርሱም በጎ ሥራ እንዲሠሩ በሃይማኖት እንዲጸኑ የሚያዝዝ ደብዳቤ በመጻፍ በንጉሥ ኀቲም ቀለበት እያተመ ለሀገሮች ሁሉ የሚልክ ሆነ።

❖ ክፋዎች ሰዎችም ጠሉት በንጉሥም ዘንድ ነገር ሠሩበት እንዲህም አሉት እነሆ አባ በርሱማ እንደ ዓለም ሰው ሁኖ ይበላል ይጠጣል መልካም ልብስንም ይለብሳል ንጉሥም ሰለ አባ በርሱማ የተነገረውን ያረጋግጥ ዘንድ ከባለሟሎቹ አንዱን ላከ፤ የንጉሡም ባለሟል ወደ አባ በርሱማ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ ከተነገረው ምንም ምን ያገኘው የለም ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ወሰደው ንጉሥም ቀድሞ ከሚያውቀው ከመንፈሳዊ ሥራው ልውጥ ሆኖ ያገኘው ነገር የለም ንጉሡም ታላቅ ክብርን አከበረው ወደ ቦታውም መለሰው።
❖ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያንም የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ ጊዜ የንጉሥ አማካሪዎች አባ በርሱማን እንዳያስመጣ ንጉሡን መከሩት እንደማይፈራና እንደማያፍር ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ተከራክሮ ረትቶ እንደሚያሳፍራቸውም ስለሚያውቁ ነው።
           
❖ አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት የከፋፈሉበት ይህ ጉባኤ በተፈጸመ ጊዜ የከበረ አባ በርሱማ ተጣላቸው ነቀፋቸው ቃላቸውንም በመሻር አወገዛቸው እነርሱም ወደ ንጉሥ ወንጅለው በጽሑፍ ከሰሱት ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀረበው ግን በላዩ ስለ አደረ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሊቃወመው አልቻለም በሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ሰለ አደረገችው ክፋት ንግሥቲቱን ረገማት ከጥቂት ቀንም በቀር አልኖረችም በክፉ አሟሟትም ሞተች።

❖ ከዚህም በኋላ መናፍቃን የሚቃወሙት ሆኑ ምእመናን እንዳይታዘዙለት ወደ ሀገሮች ሁሉ ጽፈው የሚልኩ ሆኑ እነርሱ ግን አልተቀበሏቸውም ለእርሱ መታዘዛቸውንም አልተዉም።

❖ ዳግመኛም በጐዳና ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ ሁለት መቶ መናፍቃን ሰዎች ከመናፍቃን ኤጴስቆጶሳት ጋር ተስማምተው ወደ እርሳቸው እንዲመጣና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሔዱ ሁነው ላኩበት መጥቶም አብሮ በተጓዘ ጊዜ ደንጊያዎችን አንሥተው ጣሉበት ደንጊያዎቻቸውም ወደ ራሳቸው የሚመለሱ ሆኑ በፍርሃትም ከእርሱ ሸሹ።
❖ እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም እሥረኛነት ሊአወጣው በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደርሱ ልኮ ከአራት ቀን በኋላ ከዓለም እንደሚፈልስ ነገረው በዚያንም ጊዜ በዙሪያው ወዳሉ አገሮች ምእመናንን ያጽናናቸው ዘንድ ረድኡን ላከው እርሱም ሲዞር የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ ወደምትኖርበት ቦታ ደረሰና የከበረች የቅዱስ ዮሐንስን ራስ እጅ ነሣት ስለ ከሀዲው ስለ ንጉሥ መርቅያን በማልቀስ ለመነ፤ እንዲህ የሚልም ቃል ከመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ወጣ አባ በርሱማ ወደ እግዚአብሔር ስለ ከሰሰው ያ መርቅያን ሙቷልና አትፍራ፤ የከበረ አባ በርሱማ ረድኡን ባረከውና በሰላም አረፈ።
❖ ከበአቱም ደጃፍ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን መሰሶ ተተክሎ ታየ፤ ምእመናንም ሁሉ ከሩቅ አይተው ወደርሱ መጡ አርፎም አገኙት፤ ከሥጋውም ተባረኩ በላዩም አለቀሱ ከእርሱም ስለመለየታቸው እጅግ አዘኑ እንደሚገባም አየዘመሩና እያመሰገኑ ገንዘው በመቃብር አኖሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

   
🛎 በዚችም ዕለት የከበረ ሶርያዊ ጳውሎስ በሰማዕትነት ሞተ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የሶርያ ሰዎችና በእስክንድርያ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው ከዚህም በኋላ በእስሙናይን ከተማ የሚኖሩ ሆኑ።
❖ ወላጆቹም ሲሞቱ ብዙ ገንዘብ ተዉለት ከዚህም በኋላ ከሀድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቶስ የሚያምኑ ምእመናንን እንደሚያሠቃዩአቸውና እንደሚገድሏቸው ሰማ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ።
🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀🥀

ከየት እንጀምር ?

ወዳጄ ሆይ ለምን ከሌለህ ነገር ትጅምራለህ? በሰው ላይ ኀዘን የሚጨምረው፣ ተስፋ መቁረጥም የሚያደርሰው፣ የበታችነትንም የሚያመጣው፣ ቅዠትንም የሚያባብሰው ከሌለ ነገር መጀመር ነው፡፡ እስኪ ራስህን አስበው? ስላላገኘሃቸውና ስላልደረስክባቸው፤ ስላመለጡህና ስላልተደረጉልህ ነገሮች ከማሰብ በእጅህ ስላለውና ስለደረስክበት ነገር ለምን አታስብም፡፡ በአንተ እጅ ያለው ነገር በአንተ እጅ ከሌለው ነገር ይበልጣል ወይስ ያንሳል? በእጄ ያለው ትንሽ ነገር ነው፣ በእጄ የሌለው ግን ዓለም በሙሉ ነው አትበል። በእጅህ ያለው ነገር በእጅህ ከሌለው ነገር ይበልጣል፡፡ እንዴት? አልክ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በእጅህ ያለው ነገር ያንተ ነው፡፡ በእጅህ የሌለው ግን ገና ያንተ አይደለም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር መጠቀም ትችላለህ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትጠቀም አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልታዝዝ ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልታዝ አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ማግኘትህን ርግጠኛ ሆነሃል፡፡ ያንተ ያልሆነውን ማግኘትህን ግን ርግጠኛ መሆን አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልትወስንበት ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትወስን አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ለሌላው መስጠት ትችላለህ፤ ያንተ ያልሆነውን ግን መስጠት አትችልም፡፡ ካለህ ነገር ላይ ቆመህ የሌለህን ማየት ትችላለህ፤ ከሌለህ ነገር ላይ ቆመህ ግን ያለሀን ነገር ማየት አትችልም፡፡
እናም ወዳጄ ስትቆጥር ካገኘኸውና ከሆነልህ ነገር ጀምረህ ቁጠር፡፡ ባላገኘኸው ነገር ከምትበሳጭ ባገኘኸው ነገር ተደሰት፡፡ ባልሆንከው ነገር ከምታዝን በሆንከው ነገር ሐሴት አድርግ፡፡ ባልያዝከው ነገር ከመበሳጨት በያዝከው ነገር ሥራበት፡፡ ባልሆንከው ማንነት ከመቃዠት በሆንከው ማንነት መኖር ጀምር፡፡ ይህ ማለት ምን ይመስልሃል? ስትጓዝ እያረጋገጠክ ተጓዝ፡፡ መጀመርያ ያለህን ዕወቀው፣ ከዚያም ባለህ ነገር ምን ያህል እንደ ተጠቀምክበት ርግጠኛ ሁን፡፡ ላለህ ነገር ዋጋ ስጠው፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር አክብረው፡፡ ያን ጊዜ የሌለህን ታገኘዋለህ፡፡ የሌላውን ሰው ትዳር አይተህ፣ እርሱን ተመኝተህ፣ እንደዚያ በሆንኩ እያልክ በሌለህ ነገር ከማዘን፤ እስኪ በአንተ ትዳር ውስጥ ምን መልካም ነገሮች አሉ? የትኞቹን ተጠቅመህባቸዋል? የትኞቹን አድንቀሃቸዋል? ለየትኞቹስ ዋጋ ሰጥተሃቸዋል፡፡ የሌለህን ብቻ የምታይ ከሆነ ያለህን ማወቅ አትችልም፡፡ ስለ ሌለህ ነገር ብቻ የምታስብ ከሆነ ባለህ ነገር መጠቀም አትችልም፡፡ አሁን የምትሠራበትን ሞያ ወይም ቢሮ ወይንም መስክ በሚገባ ተጠቅመህበታል? ሠርተህበታል? ከዚያስ ማግኘት ያለብህን አግኝተሃል? ወይስ ሌላ ሞያ ነው የምትፈልገው፣ ሌላ ቦታ መቀጠርም የምትመኘው፣ ሌላስ መስክ ላይ መዋል የምትጓጓው ሰዎች አደረግነው ሲሉ ስለሰማህ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ታች ከፍል በተማሩት ምንም ሳይሠሩበት ወደ ላይ ይወጣሉ፡፡ በመጀመርያ ዲግሪያቸው አንዳች ሳይፈይዱ ሁለተኛና ሦስተኛ ይይዛሉ፡፡ አኗኗራቸውንና አስተሳሰባቸውን ስታየው ግን ታች ክፍል ናቸው፡፡ ለምን ይመስልሃል? መጀመርያ በያዙት ነገር ሳይረኩና ሳይጠቀሙ፣ የያዙትን ነገር ፈጽመው ማወቃቸውን ሳያረጋግጡ ሰው ስላደረገው ብቻ ሌላውን አደረጉ፡፡
በቤታችን ውስጥ ይህኮ የለንም ብለን የገዛናቸው የማንጠቀምባቸው አያሌ ዕቃዎች አሉ፡፡ በየቁም ሳጥናችን ውስጥ ስለሌለን ብቻ የገዛናቸው የማንለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉ፡፡ ምናልባት ግን እነርሱን ከመግዛታችን በፊት ምን እንዳለን ብናስብ ኖሮ እነርሱን የሚተካ ወይንም የሚያስከነዳ ነገር በቤታችን ነበረ፡፡ እስኪ ሰዎችን ስማቸው፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት የተቀጠሩ የሚሠሩበትን እያማረሩ ያኛውን መሥሪያ ቤት ያደንቃሉ፡፡ እዚያ ያሉት ደግሞ ያሉበትን እየረገሙ እዚህ ያለውን ያመሰግናሉ፡፡ ለምን? ሁሉም ሌላ ያያሉ እንጂ ያላቸውን አያዩም፡፡ የት እንደምትሄድ ሳታውቅ አትሂድ፡፡ የት እንደምትሄድ ለመወሰን ደግሞ ከየት እንደተነሳህ ማወቅ የግድ ነው፡፡ ምናልባትምኮ አለመሄዱ ከመሄዱ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት መሄድ ብቻውን ዓላማህ ይሆናል? ለአንዳንዶች መማር ብቻ ዓላማቸው ነው፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ማግባት፡፡ለአንዳንዶች መነገድ፡፡ ለአንዳንዶች ውጭ ሀገር መሄድ፡፡ ለአንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን መሄድ፤ እነዚህ መንገዶች እንጂ መድረሻዎች አይደሉም፡፡
የት እንደሚሄድ ያልወሰነ ሰው ያለበትን የማያውቅ ነው፡፡ የት እንደምትሄድ ለመወሰንኮ ከየት እንደተነሳህ ማወቅ የግድ ነው፡፡ እንዴት መሄድ ብቻውን ዓላማህ ይሆናል? ለአንዳንዶች መማር ብቻ ዓላማቸው ነው፡፡ ምን? ለምን? እስከየት? ከዚያስ ምን ለመሥራት? መልስ የላቸውም፡፡ የሚሄድበትን በትክክል የማያውቅ ሰው ምንጊዜም ባለው ነገር ሳይሆን በሌለው ነገር ላይ ይመሠረታል፡፡ ምናልባትም የሚሄደው ወደመጣበትም ሊሆን ይችላል። ያለውን የማያውቅ የሌለውንም ሁሌ የሚናፍቅ ሰው እንደዚህ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜኮ የምናማርረው ችግር ስለደረሰብን ብቻ ሳይሆን ያለንን ስለማናውቀው ጭምር ነው፡፡ ችግር በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ችግር ችግር የሚሆነው መፍትሔ መስጠት ለማይችል ሰው ብቻ ነው፡፡ መፍትሔ መስጠት ለለመደ ችግር ትምህርት ቤት ነው፡፡ "ችግርኮ የፍች፣ የመለያየት፣ የጠብ፣ የኩርፊያ፣ የክስ፣ የመልቀቂያ፣ መንገድ የሚሆነው ለዐቅመ ቢስ ሰው ነው"፡፡ ለብርቱ ሰው ግን ሞት የትንሣኤ መቅድም ነው፡፡ የሌለህን ነገር ብቻ ካሰብክ ያለህንም ታጣዋለህ፡፡ ያለህን ነገር ካሰብክ ግን የሌለህንም ታገኘዋለህ፡፡
ቤትህ ውስጥ ከፍተህ የረሳኸው ባንቧ ቢኖርና ድንገት ሌሊት ከእንቅልፍህ ስትነቃ መሬቱ እንዳለ በውኃ ተጥለቅልቆ ብታገኝ በቅድሚያ ምን ታደርጋለህ? የፈሰሰውን ውኃ ለመጥረግ ወይስ የሚፈሰውን ቧንቧ ለመዝጋት ነው የምትቸኩለው?

ቧንቧውን ሳትዘጋ መሬት ላይ ያለውን ውኃ ለማፈስ ብትሞክር ትርፉ ድካም ነው። ቀኑን ሙሉ ስትዝቅ ብትውል ቤትህ የሞላውን ውኃ አታጎድልም። እናስ? ቧንቧውን ዝጋዋ!

በኃጢአት በወደቅህ ጊዜ መፍትሔ በማታገኝበት ነገር ላይ ጊዜህን አታባክን። ለዚህ የሚዳርገኝ መነሻው ምክንያት ምንድን ነው? ብለህ ራስህን ጠይቅ። አእምሮህ ውስጥ የሞሉትን ክፋቶች ከመቁጠር በላይ እነዚያ ክፋቶች የገቡበትን አንድ ቀዳዳ ወይም ሽንቁር ለማወቅ ጣር። እርሱን ያወቅኸው ቀን ለችግርህ ትልቁን መፍትሔ አብረህ ታገኛለህ። ያን ቀዳዳ ከዘጋህ ወይም ምንጩን ካደረቅኸው የቀረው ቀስ እያለ ተኖ መጥፋቱ አይቀርም። ከመውደቅህ በላይ የውድቀትህ ምክንያት ያስጨንቅህ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
††† እንኳን ለአባታችን ታላቁ ቅዱስ በርሱማ ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ አባ በርሱማ †††

††† ታላቁ (THE GREAT ይሉታል) አባ በርሱማ በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ምንኩስናና ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው::

በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ምድረ ሶርያን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች የቅድስና ሕይወትን ያስፋፋው ቅዱስ በርሱማ ለቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ከሆኑላት አበው አንዱ ነው:: እርሱ ከተጋድሎው ብዛት ለ54 ዓመታት ያለ እንቅልፍ ቆይቷል::

በእነዚህ ዘመናትም ግድግዳ ላይ ጠጋ ብሎ ከማረፉ በቀር መቀመጥን እንኩዋ አልመረጠም:: በመዓልትም በሌሊትም በፍቅር አብዝቶ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ በመጸለዩ የብዙዎቹን ነፍስ ወደ ሕይወት ማርኩዋል::

ገዳማትን ከማስፋፋትና ደቀ መዛሙርትን ከማብዛቱ ባለፈ በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረለት አባት ነበር:: በ431 (423) ዓ/ም በኤፌሶን በተደረገው የቅዱሳን ጉባኤ ላይ ከተገኙ ሊቃውንትም አንዱ ነው:: በቅድስና ሕይወቱ የተገረመው የቁስጥንጥንያው ንጉሥ (ትንሹ ቴዎዶስዮስ) የንግሥና ቀለበቱን እና ማኅተሙን ሸልሞታል::

ቅዱሱም የዋዛ አልነበረምና በንጉሡ ማኅተም እያተመ "ተፋቀሩ" የሚሉ ብዙ አዋጆችን ወደ መላው ዓለም ልኩዋል:: በ451 (443) ዓ/ም በኬልቄዶን 636 ሰነፍ ዻዻሳት ጉባኤ አድርገው አባ ዲዮርስቆሮስን እንደ ገደሉት ሲሰማም ወደ ቤተ መንግስት ሒዶ ከሃዲዎቹን (መርቅያንና ሚስቱ ብርክልያን) በአደባባይ ዘልፏቸዋል::

ስለ አዘነባቸውም ተቀስፈዋል:: ታላቁ ቅዱስ አባ በርሱማ ፀሐይን ማቆሙን ጨምሮ በርካታ ተአምራትን ሠርቶ በዚህች ቀን ዐርፏል::

††† ቸር አምላኩ ከበረከቱ ይክፈለን::

††† የካቲት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ) የመነኮሱበት በዓል
3.ቅዱስ ዻውሎስ ሶርያዊ (ሰማዕት)
4.ቅዱስ ዼጥሮስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
2.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
3.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
4.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

††† "ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" †††
(ሚክ. 6:6)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን። ✞✞✞

=>+"+ እንኩዋን ለቅዱሳን አባቶቻችን ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ: ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕትና አባ ኤስድሮስ ገዳማዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

"† ቅዱስ ያእቆብ †"

=>ቅዱስ ያዕቆብ (የእልፍዮስ ልጅ)
ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ.10:1) ብዙ አሕጉር አስተምሮ በዚህ ቀን በሰማዕትነት ወደ ፈጣሪው ሔዷል::

=>ቅዱስ ዮስጦስ በ3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ምድራዊ የንግሥና ዙፋንን ንቆ በክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ከሚስቱ ቅድስት ታውክልያና ከአንድ ልጁ ቅዱስ አቦሊ ጋር ሰማያዊ ክብርን ተቀዳጅቷል::

=>አባ ኤስድሮስ ግብፃዊ ሲሆኑ ሹመትን ጠልተው ፈርማ በሚባል ገዳም ለ60 ዓመታት በበርሃ ውስጥ ከ18,000 በላይ ድርሳናትን ፅፈዋል:: ይሕም በዓለም ታሪክ ብዙ መጻሕፍትን በመጻፍ ቀዳሚው ያደርጋቸዋል:: ከድርሳናቱ መካከል 2,000 ያህሉ ዛሬም ድረስ በግብፅ በርሃ ውስጥ ይገኛሉ::

=>ከስንክሳር

    †አባ ፌሎ †

በዚች ቀን የፋርስ ሀገር ኤጲስቆጶስ አባ ፌሎ በሰማእትነት አረፈ ። ይህንንም ቅዱስ ለእሳት እንዲሰዋ ለፀሀይም እንዲሰግድ የፋርስ ንጉስ አዘዘው እምቢ በአለውም ጊዜ ታላቅ ስቃይን አሰቃይቶ እራሱን በሰይፍ ቆረጠው በመንግስተ ሰማያት የሰማእትነትን አክሊል ተቀበለ ።
በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር።

† አባ ኤስድሮስ †

በዚችም እለት በገድል የተጠመደ ምሁር የሆነ የአለሙ ሁሉ መምህር አባ ኤስድርስ ፈርማ ከሚባል አገር አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በምስር አገር የከበሩ ባለፀጉች ናቸው።

ለእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳትም አባ ቴዎድሮስና አባ ቄርሎስ ዘመዶች ናቸውከእርሱም በቀር ልጅ የላቸውም መንፈሳዊ ትምህርትን ሁሉ አስተማሩት ።

ግልፅ አድርጎ አጠናቸው ጠበቃቸውም ዳግመኛም የዮናናውያንን የፍልስፍና ትምህርት የከዋክብትን አካሄድና አለምን መዞራቸውን ተማረ በእውቀቱና በጥበቡም ከብዙዎች ከፍ ከፍ አለ በገድልም የተጠመደ ትሁትና የሚተጋ ሆነ።

በሀገሮችም ያለ ሰዎች ሰለርሱ በሰሙ ጊዜ በእስክንድርያ  አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ይሾመት ዘንድ ተማክረው ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር ተስማሙ ። በሌሊትም ወጥቶ ሽሽ ወደ ፈረማ ገዳም ደርሶ በዚያ መነኮሰ።

ከዚያም ወጥቶ ወደ አንዲት አነስተኛ ዋሻ ገብቶ ብቻውን በወስጧ ብዙ ዘመናት ኖረ ብዙ ድርሳናትንና ተግሳፃትንም ደረሰ ከዕርሳቸውም ስለ ነገስታትና ስለ መኳንንት የደረሳቸው አሉ   የቤተ ክርስቲያንን መፃህፍቶችን ብሉያትና ሀዲሳትን ተረጉመ።

የመፅሀፍታቹም ቁጥራቸው አስራ ስምንት ሺህ ነው።  እነዚህም ድርሳናት ተግሳፃት ጥያቄዎችና መልሶች ወደ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት የተላኩ መልእክቶች ናቸው። ወደ ምእመናንም ወንዞች ውኃዎችን እንደሚያፈልቁ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ የሚያስፈልቃቸው ሆኗልና።

ይህንንም በጎ ስራውን ሲፈፅሙ መልካም ጉዞውንም አከናውኖ ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ እግዚአብሄርንም አግልግሎ በሰላም አረፈ።

=>የካቲት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
2.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት
3.አባ ኤስድሮስ ጻድቅ (ዘሃገረ ፈርማ)
4.አባ ፌሎ ሰማዕት
5.ቅዱስ ስምዖን
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዕፀ-መስቀል
2.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
4.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ

=>+"+ . . . ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ በእናንተ ላይ ከሚሆነው: ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ይናፍቁዋቹሀል::
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን:: +"+ (2ኛ ቆሮ. 9:14)

=>+"+ ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ: ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ:: +"+ (ኤፌ. 5:3)

✞ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ወለመስቀሉ ከቡር አሜን ✞
††† እንኳን ለጻድቁ አባ አውሎግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
*
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አውሎግ አንበሳዊ †††

††† አባ አውሎግ ማለት:-
*ከቀደመው ዘመን ጻድቃን አንዱ::
*እንደ ገዳማውያን ፍፁም ባሕታዊ::
*እንደ ሐዋርያት ብዙ ሃገራትን በስብከተ ወንጌል ያሳመኑ::
*በግብፅና በሶርያ በርሃዎች ለ90 ዓመታት የተጋደሉ ጻድቅና ሐዋርያ ሲሆኑ የሚጉዋዙበትና የሚታዘዛቸው ግሩም አንበሳ ነበር::
*በዚህም አባ አውሎግ "አንበሳዊ" ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠራቸዋለች::

አባ አውሎግ ከሚታወቁበት አገልግሎት አንዱ ስብከተ ወንጌል ነው:: ምንም እንኩዋ ገዳማዊ ቅዱስ ቢሆኑም ያላመኑትን ለማሳመን : ያመኑትንም ለማጽናት ተጋድለዋል::

እግዚአብሔር በሰጣቸው አናብስት በአንዱ ላይ ተጭነው (መዝ. 90) : በሌላኛው ላይ እቃቸውን አስቀምጠው በየአኅጉራቱ ከመምህራቸው ቅዱስ አውሎጊን ጋር ይዘዋወሩም ነበር:: የጌታ ቸርነት ሆኖም አናብስቱ የቅዱሳኑን ፈቃድ ሳይነገራቸው ያውቁ ነበር::

ሲርባቸውም ተግተው ይመግቧቸው ነበር:: እንዲያውም አንዴ ቅዱሳኑ እንደራባቸው አንዱ አንበሳ ሲያውቅ ከበርሐ ወደ ገበያ መንገድ ወጥቶ ተመለከተ:: በአህያ ላይ ልጁንና ስንቁን (ዳቦ) ጭኖ የሚሔድ ሽማግሌ ነበርና ዳቦውን አንስቶ ወስዶ ለእነ አባ አውሎግ ሰጣቸው::

ከድንጋጤ የተነሳም ሕጻኑ ሙቶ ነበርና ሽማግሌ አባቱ አዘነ:: አንበሳው ግን ሕጻኑንም ወደ ቅዱሳኑ ወስዶ አስረከበ:: ቅዱሳኑም ከሕብስቱ በመጠናቸው በልተው ቢባርኩት እንዳልተበላ ሆነ:: ሕጻኑንም ከሞት በጸሎታቸው አስነስተው ለአንበሳው ሰጥተውታል::

አንበሳውም ስንቁንና ልጁን ለአረጋዊው ሰጥቶት በደስታ ወደ ሃገሩ ተመልሷል:: ቅዱስ አባ አውሎግና መምህሩ አውሎጊን ከ90 ዓመታት በላይ በዘለቀ ተጋድሏቸው አጋንንትን ያሳፍሩ ዘንድ : ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ መስዋዕት ይሆኑለት ዘንድ በትጋት ኑረዋል::

¤ብዙ ተአምራትን ሠርተው ፈጣሪያቸውን አክብረዋል::
¤እንደ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ባሕር ከፍለዋል::
¤እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙት አንስተዋል:: ድውያንን ፈውሰዋል::
¤እንደ ቅዱስ ዳንኤል አናብስትን ገዝተዋል::
¤ይህች ቀን ዕለተ ዕረፍታቸው ናት::

†††  ቅዱስ በላትያኖስ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያዊ ዻዻስ የቀድሞዋ ሮም ሊቀ ዻዻሳት ሲሆን ቸር : ትጉህና በጐ እረኛ ነበር:: መናፍቃንን ሲያርም : ምዕመናንን ሲመክር : ስለ መንጋው እንቅልፍ አጥቶ ኑሯል:: በፍጻሜውም በዚህች ቀን የሮም ንጉሥ ለ1 ዓመት አሰቃይቶ ገድሎታል:: ዕሴተ ኖሎትን (የእረኝነት ዋጋንም) ከጌታችን ተቀብሏል::

††† አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† የካቲት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አውሎግ አንበሳዊ
2.አባ አውሎጊን ጻድቅ (የአባ አውሎግ መምሕር)
3.አባ በትራ (የጻድቁ አባ ስልዋኖስ ደቀ መዝሙር)
4.አባ በላትያኖስ ሰማዕት (የሮም ሊቀ ዻዻሳት የነበረ)
5.አባ አብርሃም ኤዺስ ቆዾስ
6.አባ መቃቢስ
7.አባ ኮንቲ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
5.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

††† "በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምንም ከኁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ነው::" †††
(ኤፌ. 1:19)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት አሥራ አንድ(፲፩)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
††† እንኳን ለኢትዮዽያውያን ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ኢትዮዽያውያን ሰማዕታት †††

††† በ1929 ዓ/ም: የካቲት 12 ቀን ከ30,000 በላይ ኢትዮዽያውያን አባቶች: እናቶች: ወጣቶችና ሕፃናት በሮማዊው የፋሽስት ጦር ደማቸው ፈሷል:: እነዚሕ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ጐርፍ አዲስ አበባ ላይ የፈሰሰው ስለ ሃገር ፍቅር ብቻ አልነበረም:: ስለ ቀናች ሃይማኖት ተዋሕዶ ጭምር ነው እንጂ::

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ግፃዌ ላይ ስማቸውን ጽፋ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር እንዲህ ታስባቸዋለች::

"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ::
ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::"
(መዝ. 78:1)

††† ሰማዕታቱን እናስባቸው!

††† ሶምሶን ረዓይታዊ †††

††† እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ: በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ርሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ:: እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ:: ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,200 ዓመታት በሁዋላ መሆኑ ነው::

በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር:: የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን: አማሌቅ: ኢሎፍሊ ስንኩዋ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው::

በጊዜውም የእሥራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) 40 ዓመት በባርነት ገዟቸው:: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) : በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው::

እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት : በአምላኩ ኃይል ታደገ:: ከኃይሉ ብዛት የተነሳም:-
¤አንበሳን እንደ ጠቦት ይገድል (መሣ. 14:5)
¤300 ቀበሮዎችን አባሮ ይይዝ (መሣ. 15:3)
¤በብርቱ ገመዶች ሲያስሩት እንደ ፈትል ይበጣጥሰው (መሣ. 15:14)
¤በአህያ መንጋጋ ሽህ ሰው ይገድል (መሣ. 15:15)
¤ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር:: (መሣ. 16:3)

ውሃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል:: (መሣ. 15:18) በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል:: ጠላቶቹም ዐይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል::

በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ : አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል:: (መሣ. 13--16)
ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው::

††† በዘመኑ ሁሉ ቅዱስ ሚካኤል ረድቶታልና በዚህች ቀን መታሠቢያው ይደረግለታል::

††† የካቲት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."30,000" ሰማዕታተ ኢትዮዽያ (ሮማዊው ፋሽስት የገደላቸው)
2.ቅዱስ ሶምሶን ረዓይታዊ (የእስራኤል መስፍን)
3.ቅዱስ አባ ገላስዮስ ገዳማዊ
4.ቅድስት ዶርቃስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ድሜጥሮስ
4.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
6.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
7.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
8.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ

††† አምላከ አበው ቅዱሳን መዓዛ ቅድስናቸውን ያሳድርብን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† "ሶምሶንም:- 'ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል : እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አስበኝ? አምላክ ሆይ! . . . እባክህ አበርታኝ?' ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ:: . . . ሶምሶንም:- 'ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት' አለ:: ተጐንብሶም ምሰሶዎችን በሙሉ ኃይሉ ገፋ:: . . . በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ::"
(መሣ. 16:28)

††† "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ . . ." †††
(ዕብ. 11:32)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Audio
ድርሳን ዘቅዱስ ሚካኤል ዘወርሃ የካቲት
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት አሥራ ሁለት(፲፪
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
2024/09/29 22:19:13
Back to Top
HTML Embed Code: