Telegram Web Link
++ አበው ስለ እመቤታችን ዕረፍት እንዲህ አሉ ++

‹ሌሎች በድንግልና የኖሩ ሴቶች 'ለሞት የሚሆኑ ልጆችን አንሰጥህም" በማለት ሞትን ተቃወሙት፡፡ ድንግል ማርያም ግን አንድ ልጅ በመውለድ በልጅዋ ሞት ራሱ እንዲሞት አደረገችው፡፡ ከዐለት ጋር እንደተጋጨ የተፈረካከሰው በማሕፀንዋ ፍሬ ነውና ሞት ወደ እርስዋ ሲቀርብ ተብረከረከ›› ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ

‹‹ልጃቸው ተሰብስበው ወዳሉበት መጥታለችና አዳምና ሔዋን ዛሬ ደስ አላቸው … በዚህች ቀን ታላቁ ዳዊት በራሱ ላይ የተዋበ አክሊል የደፋችለትን ሴት ልጁን አይቶ ደስ አለው … በዚህች ቀን ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት የተናገረላት ድንግል ወደ ሙታን ሥፍራ ልትጎበኘው መጥታለችና ደስ አለው … በዚህች ቀን ብርሃን ሲበራባቸው አይተዋልና ነቢያት ሁሉ ከመቃብራቸው ራሳቸውን ቀና አደረጉ … አርያም በጣፋጭ የመላእክት ዝማሬ ተሞላ ፣ ምድር ደግሞ ኀዘንን በተሞሉ በሐዋርያት ለቅሶ ተሞላች፡፡ ሙታንም ሕያዋንም ትርጉሙን ሊገልጹት በማይችሉት [የተለያየ] ዜማ ሰውና መላእክት በዚያች ዕለት አብረው ጮኹ›› ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ (Homily on the Dormition)

‹‹የቃሉ አገልጋዮችና ምስክሮች የነበሩት ሐዋርያት በሥጋ የወለደችውን የእናቱን ዕረፍትና እርስዋን የሚመለከቱ የመጨረሻዎቹን ምሥጢራትም ማየት ነበረባቸው፡፡ ይህም የሆነው የክርስቶስ የዕርገቱ የዓይን ምስክሮች እንደሆኑ ሁሉ የወለደችውም እናቱ ወደዚያኛው ዓለም ለሸጋገርዋ ምስክሮች መሆን ስላለባቸው ነው›› ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ  (aka Doctor of Dormition)

(በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የተሰባሰበ)
Forwarded from Bketa @¥
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ቅዱስ ዑራኤል
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥



❖ በቅድስት ቤተክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል

⓵ ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጉዋታል፤ በሠረገላ ብርሃን ጭኖ በክንፎቹም ተሸክሞ አስቅድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል::

❖ በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ የምትለምንና የምትማልድ

ሆናለች፤ ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

⓶ ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮዽያ መርቶ አምጥቷታል፤ በክንፉ ተሸክሞ በ4 አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጉዋል::

⓷ ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮዽያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::

⓸ ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል::

አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን ከበረከቱ በረከት ከረድኤቱ ረድኤት ያካፍለን፤ በምልጃውና በጸሎቱ ይጠብቀን
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


🔔 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፳፪


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሃያ ሁለት በዚች ቀን በግብጽ አገር ከአቅማን ከተማ የከበረና የገነነ የመነኰሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖሩ እንደ ኮከብ የሚያበራላቸው አባት እንጦንዮስ አረፈ።

❖ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ንጹሐን ክርስቲያን ናቸው እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ተንኮል ሽንገላ በልቡ ውስጥ የለውም ከወላጆቹም ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሒዶ በቆረበ ጊዜ ከሕፃናት ጋር በመጫወት ከቶ አይሳሳቅም ነበር።

❖ ጥቂት በአደገም ጊዜ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለወላጆቹ ይታዘዝ ነበር ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ተማረ ያን ጊዜም የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ቲዎናስ የተሾመበት ዘመን ነበር የእንጦንዮስንም ወሬውን ሰምቶ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ባረከውና ስለርሱ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ይህ ሕፃን በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል ዜናውም በዓለሙ ሁሉ ይወጣል እጁንም በላዩ ጭኖ ዲቁና ሾመው።

❖ ከዚህም በኋላ ወላጆቹ በሞቱ ጊዜ ታናሽ ብላቴና እኅት ትተውለት ነበር። ከሰባት ወርም በኋላ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሔደ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በልቡ አደረበትና በኀሳቡ በዓለም የሚሠራውን ሁሉ አባቶቻችን ሐዋርያት ሁሉን የዓለምን ሥራ ትተው ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ተከተሉት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም እንደተጻፈ ጥሪታቸውን እየሸጡ የሽያጩንም ዋጋ በሐዋርያት እግር ሥር ያኖሩትን አሰበ እግዚአብሔር በሰማያት ያዘጋጀላቸው ዋጋቸው ምን ያህል ይሆን አለ ይህም ኀሳብ በልቡ ውስጥ የሚመጣ የሚወርድ ሆነ።


❖"ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደ የክብር ባለቤት ጌታችን በከበረ ወንጌል ለባለጸጋው የተናገረውን ሰማ እንዲህ ሲል ፍጹም ትሆን ዘንድ ከወደድክ ሒድ ጥሪትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኆች ስጥ በሰማይም ላንተ ድልብ አድርገው መጥተህም ተከተለኝ።

❖ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ይህን ልዩ ኀሳብ አግኝቶ ይህ ቃል ስለርሱ እንደተነገረ አሰበ በዚያንም ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ወጣ ለአባቱም ያማረ ሰፊ ምድር ነበረው ለአገሩም ሰዎች ሰጣቸው ለርሱ የተዉለትንም ጥሪታቸውን ሁሉ ሽጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው እኅቱንም ወስዶ ከደናግል ገዳም አስገባት።

❖ በዚያንም ወራት የምንኩስና ሥርዓት አልተገለጸም ነበር እግዚአብሔርንም ለማገልገል የሚሻ ከመንደር ጥቂት ወጣ ብሎ ብቻውን በመቀመጥ በጾም በጸሎት ተወስኖ ይጋደላል የከበረ እንጦንዮስም እንዲሁ አደረገ ሰይጣናትም በስንፍናና በዝሙት ጦር የሚዋጉት ሆኑ በሕልሙም የሴት ገጽ በማሳየት አብራውም እንደምትተኛ ያደርጓታል።

❖ ከዚህም በኋላ በባህር ዳርቻ ወዳለች የመቃብር ቤት ሒዶ በዚያ የሚኖር ሆነ በላዩ በአደረ በእግዚአበሔርም ረድኤት በተጋድሎ በረታ ምግቡንም ከዘመዶቹ ወገን ያመጡላት ነበር ሰይጣናትም ሲጋደል አይተው ቀኑበት ታላቅ ድብደባንም ደብድበው ጥለውት ሔዱ ዘመዶቹም ሲመጡ እንደ ሞተ ሆኖ ወድቆ አገኙት ተሸክመውም ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ጌታችንም አዳነው በነቃም ጊዜ ወደ ቦታው ተመልሶ ይጋደል ዘንድ ተጋድሎውን ጀመረ።

❖ በዚያንም ጊዜ ሰይጣናትን ወደርሱ ሲመጡ አያቸው በአራዊት አምሳል በአንበሶችና በተኩላዎች የተመሰሉ አሉ በእባቦችና በጊንጦችም የተመሰሉ አሉ ያስፈሩትም ዘንድ አንዱም አንዱ በላዩ ተነሣሡ እንጦንዮስም በእኔ ላይ ለእናንተ ሥልጣን ካላችሁ ከእናንተ አንዱ ያቸንፈኝ ነበር ብሎ ዘበተባቸው ወዲያውኑ እንደ ጢስ ተበተኑ በሰይጣናት ላይ ድልን እግዚአብሔር ሰጥቶታልና ሰይጣናትም ከሚያመጡበት መከራና ሥቃይ አረፈ።

❖ ምግቡንም በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ያበስላል በፀሐይም ያደርቀዋል ወደበዓቱም ማንም እንዲገባ አያሰናብትም የሚሻውም ሁሉ በውጭ ይቆምና ድምፁን ይሰማል እንጂ ሃያ ዓመትም እንዲህ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በገድል ተጠምዶ ኖረ።

❖ ከዚህም በኋላ ፍጹም የሆነ እግዚአብሔርን መፍራትንና አምልኮቱን ለሰዎች ወጥቶ ያስተምር ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው ስለዚህም ወደ ፍዩም አገር ወጥቶ ብዙዎች ደቀ መዛሙርትን ሰብሰቦ አስተማራቸው በእግዚአብሔርም ሕግ አጸናቸው ደቀ መዛሙርቶቹ በውስጣቸው የሚኖሩባቸው ብዙዎች ገዳማት ተሠሩለት።

❖ ስለ ሃይማኖትም ስደት በሆነበት ወራት በሰማዕትነት መሞትን ወዶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሔዶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ከቶ አልያዙትም በክርስቶስም ስም የታሠሩ እሥረኞችን በመጎብኘት ቢአረጋጋቸውና ቢአጽናናቸውም አልያዙትም መኮንኑም እንደማይፈራ በአየው ጊዜ ከፍርድ አደባባይ ውስጥ እንዳይታይ አዘዘው እርሱ ግን ሁል ጊዜ መታየቱን አልተወም እንዲአሠቃየውና በሰማዕትነትም እንዲሞት የሚያስቆጣውን ነገር ይናገረው ነበር መኮንኑም በእርሱ ላይ ምንም ክፉ ነገር አላደረገም አምላካዊት ኃይል ከልክላዋለችና።

❖ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ ለሰማዕታት ፍጻሜ ሁኖ የመከራው ወራት ከአለፈ በኋላ እንጦኒ ወደ ገዳሙ ተመለሰ ይህም በአምላክ ፈቃድ ሆነ የሚለብሰውም ማቅ ነበር በዘመኑ ሁሉ ገላውን በውኃ አልታጠበም ብዙዎች በሽተኞችም ወደርሱ ይመጣሉ በላያቸውም ሲጸልይ ይድናሉ።

❖ ብዙዎች ሕዝቦችም ትምህርቱን ሊሰሙ ወደርሱ ሲመጡ በአያቸው ጊዜ ብቻውንም ይኖር ዘንድ እንዳልተውት አይቶ ከእርሱ ስለሚደረገው ነገር ልቡ እንዳይታበይ ፈራ እነርሱ ወደማያውቁት ቦታ ወደላይኛው ግብጽ ይሔድ ዘንድ ወዶ ወደ ባሕሩም ወደብ ደርሶ መርከብ እየጠበቀ ተቀመጠ ከሰማይም ወደርሱ ቃል መጣ እንዲህም አለው እንጦንዮስ ሆይ ወዴት ትሔዳለህ ከዚህስ ምን ትሻለህ አለው እርሱም ብዙዎች ወደእኔ ስለሚመጡ እንደምፈልገው ለብቻ መኖር አልተቻለኝም ስለዚህም ወደ ላይኛው ግብጽ እሔድ ዘንድ ወደድኩ አለ ያም ቃል መልሶ እንዲህ አለው ወደ ላይኛው ግብጽ ብትሔድ ድካምህ ደግሞ እጥፍ ይሆናል ብቻህን መኖር ከወደድክ ግን የሦስት ቀን ጎዳና ያህል ወደ ውስጠኛው በረሀ ተጓዝ።

❖ በዚያንም ጊዜ በዚያች ጎዳና ሊጓዙ የሚሹ የዓረብ ሰዎችን አያቸው ወደ እርሳቸውም ሒዶ አብሮአቸው ይሔድ ዘንድ ለመናቸው እነርሱም በደስታ ተቀበሉት ወደ አንድ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ እስከሚደርስ የሦስት ቀን ጎዳና ተጓዘ በዚያም የጠራና የቀዘቀዘ ውኃ አለ ደግሞም የሰሌን የተምር ዕንጨቶች መቃዎችም በብዛት አሉበት እንጦንዮስም ያንን ቦታ ወደደው ዓረቦችም ምግቡን የሚያመጡለት ሆኑ ብዙዎች የከፉ አራዊትም ነበሩ በጸሎቱም እግዚአብሔር አስወገዳቸው ወደዚያም ቦታ ከቶ አልተመለሱም፤ አንዳንድ ጊዜም ወደ ባሕሩ ዳርቻ በመውጣት ደቀ መዛሙርቶቹን ጎብኝቶና አረጋግቶ በበረሀ ወስጥ ወደአለው ቦታው ይመለሳል።
❖"ከዚህም በኋላ በጻድቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ በጸሎቱ ያስበው ዘንድ ንጉሡ እየለመነዉ ደብዳበ ጻፈለት የከበረ እንጦንዮስ ግን ወደ ንጉሥ ደብዳቤ ዘወር አላለም ለወገኖቹ እንዲህ አላቸው እንጂ የንጉሠ ነገሥት ደብዳቤ እነሆ በላያችን ይነበባል ወንድሞችም እንዲህ ብለው ለመኑት ይህ ንጉሥ የክርስቲያንን ወገኖች የሚወድ ጻድቅ ሰው ነው ደብዳቤ ጽፈህ ልታጽናናው ይገባል ከዚህም በኋላ እያጽናናውና እየባረከው ቤተ መንግሥቱንና ሠራዊቱንም እየባረከ ጻፈለት።

❖ ዳግመኛም በአፍርንጊያ ንጉሥ ዘንድ ዜናው በተሰማ ጊዜ ወደ ከበረ እንጦንዮስ እንዲህ ብሎ ጻፈ ወደ እኛ መጥተህ በእኛ ላይ በአገራችንና በሠራዊታችን ላይ በረከትን ታሳድር ዘንድ ስለ ጌታችን ክርስቶስ መከራዎች እኔ ወዳንተ ፈጽሜ እማልዳለሁ።

❖ የከበረ እንጦንዮስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ቁሞም እንዲህ ብሎ ጸለየ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ በአፍርንጊያ ውስጥ ወዳለ ወደ በርኪኖን አገር እንድሔድ ፈቃድህ ከሆነ ምልክትን ግለጥልኝ ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይሁን ይህንንም ባለ ጊዜ ብርህት ደመና መጣች በዚያችም ሰዓት ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር አደረሰችው ንጉሡም ደስ አለው ሕዝቡና ሠራዊቱም ሁሉ በሽተኞችንም አቀረቡለትና ሁሉንም ፈወሳቸው የጽድቅና የሕይወትንም መንገድ እያስተማራቸው ከእነርሳቸው ዘንድ ስድስት ወር ኖረ።

❖ በእሑድም ዕለት ያቺ ብርህት ደመና ተሸክማ ወደ ገዳሙ ታደርሰውና ከልጆቹ ጋር ተገናኝቶ ያረጋጋቸዋል በማግሥቱም ዳግመኛ ተሸክማ ወደ አፍርንጊያ አገር ትመልሰዋለች። ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ በደመና ተጭኖ ወደ ገዳሙ አንደኛውን ተመለሰ።

❖ በአንዲት ዕለትም ስንፍና መጣበት እንዲህ የሚለውም ቃል መጣ ታይ ዘንድ ወደ ውጭ ውጣ በወጣ ጊዜም መልአኩን አየው በላዩም የምንኩስና ልብስ አለ መታጠቂያ፣ ቅናት፣ የመስቀል ምልክት ያለው ቀሚስ በወገቡም አስኬማ በራስ ቁር አምሳልም በራሱ ላይ ቆብ አለ እርሱም ተቀምጦ ሰሌን ይታታል ከዚያም ተነሥቶ ይጸልያል ዳግመኛም ተቀምጦ ሰሌኑን ይታታል በየሰዓቱም እንዲህ በማድረግ ይጸልያል።

❖ ሁለተኛም እንዲህ የሚል ቃል ወደርሱ መጣ እንጦንዮስ ሆይ እንደዚህ ሥራ አንተም ከሰንፍና ከሰይጣናት ጦርነት ታርፋለህ ያንን ያየውንም ተቀብሎ እንዲሁ አስመስሎ የሚሠራ ሆነ ከዚያችም ዕለት ወዲህ ስንፍናና የሰይጣናት ውጊያ አልመጣበትም።

❖ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ጊዜ ተገልጾ አረጋግቶታል አጽንቶታልም። አሁንም እንዲህ አለው የመረጥሁህ እንጦንዮስ ሆይ በእውነት እነግርሃለሁ እኔን ስለመውደድህ በዚች በረሀ ውስጥ ብቻህን በመጋደልህና በማገልገልህ ስለ ድካምህ ስምህን ከፍ ከፍ አደርጋለሁ ሥልጣንህንም በዓለም ዳርቻ ሁሉ ከፍ አደርገዋለሁ።

❖ ገዳማትንና አድባራትንም መነኩሳትን የተመሉ ሁነው ቅኖች የዋሃን ጻድቃን እንደሚኖሩባቸው አደርጋቸዋለሁ ይልቁንም ያንተ ገዳማት እነርሱ እስከ ፍጻሜ ይኖራሉ።

❖ መታሰቢያህንም የሚያደርገውን ሁሉ ለድኆች ምጽዋትን ለቤተክርስቲያን መባ በስምህ የሚሰጠውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ ከቶ ሥቃይን አያያትም በውስጡ ሥጋህ የሚቀበርበትንም ገዳም እጅግ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ በውስጡም እንደ መላእክት የሆኑ ደጋጎች መነኮሳት እንዲኖሩበት አደርጋለሁ ከእርሳቸውም እስከ ዓለም ፍጻሜ አለቃ የሚሆን አይታጣም የምድር ነገሥታት መሳፍንትና ሹማምንት ለገዳምህና ፍለጋህን ለሚከተሉ ልጆችህም እጅ መንሻ ተሸክመው እንዲመጡ አደርጋለሁ ጌታችንም ይህን ከተናገረው በኋላ ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማያት በታላቅ ክብር ዐረገ አባ እንጦኒም ፈጽሞ ደስ አለው።

❖"ከዚህም በኋላ ስለ ቤተክርስቲያን መፍረስ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ መናፍቃን በላይዋ ይሠለጥናሉ ከዚህም በኋላ ወደቀድሞ ሥርዓቷ ትመለሳለች ዳግመኛም ስለ መነኮሳት እነርሱ እጅግ እንደሚበዙ ገዳሞቻቸውንና አድባራቶችን በመተው ወርደው ከዓለማውያን መካከል በከተማዎችና በቦታዎች ውስጥ እንደሚኖሩ ስለ ዓለም ፍጻሜም ትንቢት ተናገረ።

❖ ይህም አባ እንጦንዮስ አባ መቃርስን አስኬማንና የምንኩስና ልብስን ያለበሰው ያረጋጋውና ያጽናናው ከእርሱ የሚሆነውንም ያስረዳው ነው ደቀ መዝሙሩና ልጁ ስለሆነ።

❖ ከዚህም በኋላ የገዳማውያን አለቃ ወደሆነ ወደ አባ ቡላ ሔደ እርሱም ለሥጋው ያሰበና በሐዋርያዊ አትናቴዎስ ልብስ የገነዘው ነው፤ ዕረፍቱም እንደቀረበ በአወቀ ጊዜ በትሩን ለልጁ ለአባ መቃርስ ምንጣፉን ለአባ አትናቴዎስ የፍየል ሌጦ ዐጽፉን ለልጁ ለኤጲስቆጶሱ ለአባ ስራብዮን እንዲሰጡ ልጆቹን አዘዛቸው።


❖ ከዚህም በኋላ ከምድር ላይ ጋደም አለ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ወደርሱም ሁሉም የመላእክት ማኅበር መጥተው በክብር በምስጋና ፍጹም ተድላ ደስታ ወዳለበት ዘላለማዊ ዕረፍት ተቀብለው አሳረጉት፤ሥጋውን ግን ልጆቹ እንዳዘዛቸው ሰወሩት እርሱ የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን የሚገልጡትን ይገሥጻቸው ነበርና ስለ እነርሱ ሥጋ ብዙ ገንዘብ እስከ መቀበል ደርሰው ዓለማዊ ጥሪት ያደርጉታልና።

❖ ይህም የከበረና የተመሰገነ አባት እንጢንዮስ እስከ መልካም ሽምግልና ደረሰ እጅግም አረጀ ግን ወደ ወደደውም ክርስቶስ እስከ ሔደ ድረስ መልኩ አልተለወጠም ብርታቱ ጽናቱም መላው ዕድሜውም መቶ ሃያ ዓመት ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።



📌 ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት - የበርሐው ኮከብ / ልደቱና ዕረፍቱ)

2.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ ልቡናን የሚያጠጣ ምሥጢር ገላጭ መልአክ)

3.ቅዱስ ሚናስ ኤዺስ ቆዾስ



📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ

2.ቅዱስ ደቅስዮስ ኤዺስ ቆዾስ

3.አባ ዻውሊ የዋህ
† እንኳን ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ: እና ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው:: ወደ ክርስትና የመጣው በ40ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ነው::

በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል:: ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር:: ቅዱስ ዻውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር:: በኤፌሶንም ዽዽስናን ሹሞ 2 መልዕክታትን ልኮለታል:: ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል::

ከሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን እንሳተፍ ዘንድ ጊዜ ካለን ቅዱስ ዻውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ ከላካቸው መልዕክቶች ጥቂት እናንብብ::

††† ቴዎዶስዮስ †††

††† በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ አበው አሉ:: ሰማዕታትም: ጻድቃንም: ሊቃውንትም: ነገሥታትም ተጠርተውበታልና:: ዛሬ የምናከብረውም ቴዎዶስዮስ ዘየዓቢ (ታላቁ) የሚባል ሲሆን ይህን የምንለው ከትንሹ ቴዎዶስዮስ (የልጅ ልጁ ነው) ለመለየት ነው::

ታላቁ ቴዎዶስዮስ በሮም የነገሠው በ370 ዓ/ም አካባቢ ሲሆን ከነ ቤተሰቡ ክርስቲያን ነበር:: እነዚህ ነገሮቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰብ አድርጐታል:-
1.በዓለም ታሪክ ክርስትና በሮም ግዛት ሁሉ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አውጇል::
2.የቤተክርስቲያንን ትልቁን 2ኛ ጉባኤ ቁስጥንጥንያን በ381 (373) ዓ/ም አሰናድቷል::
3.ከበጐነቱ የተነሳ የተቀደሱ ልጆችን አፍርቷል:: ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ: ቅዱስ አኖሬዎስ: ቅዱስ አርቃዴዎስ እና ቅድሰት ታኦድራ ልጆቹ ሲሆኑ አቡነ ኪሮስ ትንሽ ወንድሙ ናቸው::

ጻድቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በ390 ዓ/ም አካባቢ ዐርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ጥር 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጢሞቴዎስ (ሐዋርያና ሰማዕት-የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙር)
2.ቅዱስ ጌርሎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
4.ጻድቅ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ (ዘቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

††† "መድኃኒታችን እግዚአብሔር: ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ዻውሎስ: በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ::
ከእግዚአብሔር ከአባታችን: ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን: ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን . . ." †††
(1ጢሞ. 1:1)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
õ Eñ5 î- 5 Õ- `¨J
ASR by NLL APPS
ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምዕ፮ በከፊል
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ሃያ ሦስት(፳፫)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
† እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††

††† ልደት †††

††† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን
የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው::
እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ
እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ
ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ
አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን
መወለድ አብስሯቸዋል::

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት 24 ቀን
በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ 24 ቀን
በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት
ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

††† ዕድገት †††

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል::
ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው
አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት:
ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ
እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ
ተቀብለዋል::

††† መጠራት †††

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት
ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት
በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ
ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን::
ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር
ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ
ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም::
ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው
እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

††† አገልግሎት †††

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል
አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው
ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን
አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ 2 መልክ ነበራት::

1ኛ. ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች
ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን
ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ
አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ
መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን:
መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን
(ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል::

††† ገዳማዊ ሕይወት †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን
ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል::
እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት
አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት:
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ
ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26
ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ
(ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት
ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን
በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

††† ስድስት ክንፍ †††

ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት
ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ
መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው
ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ
ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ
ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም
ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት
የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
*በቤተ መቅደስ ብስራቱን
*በቤተ ልሔም ልደቱን
*በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
*በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
*በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ
ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት
ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና
ዓይናቸው ጠፋ::

በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ፈጥና ደርሳ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ
አሳረገቻቸው::

††† በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ
ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

††† ተአምራት †††

የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት
የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን
መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ
ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን
ታሥሯልና::

††† ዕረፍት †††

††† ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን
ሆነው: መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን
አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው
ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል
ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10
ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

††† በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ22 ዓመታት
የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው
ለ7 ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
ታስባለች::

††† ጥር 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
3.ታላቁ አባ ቢፋ
4.አባ አብሳዲ ቀሲስ
5.ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ ዘዮሐንስ (ዘክብራን ገብርኤል-ጣና)
2.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
4.ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
5.ቅዱስ አጋቢጦስ
6.ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ

††† "በድካም : አብዝቼ በመገረፍ : አብዝቼ በመታሠር :
አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት :
ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት : በራብና በጥም : ብዙ
ጊዜም በመጦም : በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . .
የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ
የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::" †††
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Encoderbot file id132185 64k
ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘወርሃ ጥር
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ሃያ አራት(፳፬)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ!

አንድን የሥጋ ቁስል ለመፈወስ ለእያንዳንዱ ሰው ከባድ ነው፤ የነፍስን ቁስል መፈወስ ግን ለኹሉም ቀላል ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ለመፈወስ መድኃኒት ብሎም ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነፍስን ለመፈወስ ግን ቀላል ብሎም ወጪን የማይጠይቅ ነው፡፡ ሥጋን ከዚያ ከሚያሰቃይ ቁስሉ ለመፈወስ አድካሚ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀዶ ጥገና ምላጭ መቀደድ አለበት፤ መራራ መድኃኒቶችም ሊጨመሩበት ይገባል፡፡ ነፍስን ለመፈወስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አያስፈልግም፡፡ ፈቃደኛ መኾን ብቻ በቂ ነው፤ ፍላጎቱ ካለ ኹሉንም ነገር ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የእግዚአብሔር መግቦቱም እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው፡፡ ሥጋ ቢቆስል ያን ያህል ከባድ ጉዳትን አያመጣብንም፤ ምክንያቱም ምንም ባንታመምም እንኳን ሞት መጥቶ ይህን ሥጋችን ያፈርሰዋል፤ ያበሰብሰዋልምና፡፡ ነፍሳችን ብትታመም ግን ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር የነፍስን ሕመም ለመፈወስ መድኃኒቱ ቀላል፣ ምንም ወጪና ስቃይ የሌለበት ያደረገውም ስለዚሁ ነው፡፡ ታዲያ ምንም እንኳን በሕመሙ ምክንያት የሚያገኘን ጉዳት ያን ያህል ብዙ ባይኾንም የገንዘብ ወጪን የሚጠይቀው፣ ሐኪም የሚያስፈልገው፣ ብዙ ስቃይ ያለበት ሥጋችን ሲታመም እርሱን ለማከም እጅግ የምንደክም ኾነን ሳለ፥ እጅግ ብዙ ጉዳት የሚያመጣውን፣ እርሱን ለመፈወስ ወጪ የማይጠይቀውን፣ ለማስታመም ሌሎች ሰዎች የማያስቸግረውን፣ እንደ ምላጩና እንደ መራራ መድኃኒቱ ስቃይ የሌለበትን ይልቁንም ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ሳይፈልግ በእኛ ኃይል ባሉ ምርጫና ፈቃድ ብቻ መዳን የሚችለውን፣ ይህን ማድረግ ሳንችል ስንቀርም ከባድ ፍርድና ቅጣት ስቃይም እንደሚያገኘን በእርግጥ እያወቅን የነፍሳችንን ቁስል ችላ የምንል ከኾነ ሊደረግልን የሚችል ምሕረት እንደ ምን ያለ ምሕረት ነው? እኮ የምናገኘው ይቅርታ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ነው?

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ትምህርት በእንተ ሐውልታት መጽሐፍ #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ የተተረጎመ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፳፭

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ሃያ አምስት በዚች ቀን በገድል የተጸመደ የከበረ ጴጥሮስ አረፈ


በዚችም ቀን የሮም ንጉሥ ልጅ የከበረ ስብስትያኖስ ምስክር ሁኖ ሞተ እርሱንም በተግሣጽና እግዚአብሔርን በመፍራት የአሳደጉት ነው።

❖ አባቱም ከሞተ በኋላ ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ ነገሡ ይህንንም ቅዱስ አገረ ገዥነት ሾሙት እንደ አባቱም እጅግ አከበሩት። እርሱም በጥበብና በማስተዋል ይጓዝ ነበር በሽተኞችን ሁሉ የዕውራንንም ዐይኖች በጸሎቱ ከፈተ።

❖ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ዲዮቅልጥያኖስ በካደው ጊዜ ለጣዖት ይሰግድ ዘንድ ይህን ቅዱስ ስብስትያኖስን ግድ አለው ባልሰማውም ጊዜ ከደረቀ ግንድ ጋር አሠረው ቊጥር በሌላቸው ፍላጻዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ እንደሞተም ጠርጥረው ትተውት ሔዱ ምእመናንም በሌሊት ሲመጡ በሕይወት አገኙት ፈትተውም ወደ ደሴት መካከል ወስደው በዚያ አኖሩት።
❖ ዲዮቅልጥያኖስም ሰምቶ ወደርሱ አስቀረበውና በብረት ዘንጎች ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ እየደበደቡትም ብዙ ቀኖች ኖሩ ከዚህም በኋላ ነፍሱን አሳለፈ ለቅድስት ውሉድስና በሕልም ተገልጦ ሥጋው ያለበትን ነገራት እርሷም ሒዳ ወደ ጴጥሮስና ጳውሎስ መቃብር ወስዳ ቀበረችው፤ ጌታችንም መታሰቢያውን ለሚያደርግና ስሙን ለሚጠራ የቸነፈር ሕመም እንዳይቀርበው ቃል ኪዳንን ሰጠው።

በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።

            

📌 በዚችም ዕለት የሰማዕት አስኪላ መታሰቢያው ነው። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።

            
✍️ ጥር 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
2.ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
3.ብፁዕ አባ ዼጥሮስ ጽሙድ (ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት)
4.ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
5.ቅዱስ አስኪላ ሰማዕት

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
2.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
3.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
4.አቡነ አቢብ
5.አባ አቡፋና
2024/09/29 22:33:23
Back to Top
HTML Embed Code: