Telegram Web Link
በጸሎት ውስጥ በመትጋት ብዛት ወደ እግዚአብሔር መድረስ ትችላላችሁ !!

እግዚአብሔርን ከወደዳችሁት ትጸልያላችሁ። አብዝታችሁ የምትጸልዩ ከሆናችሁ ከቀን ወደ ቀን ለእርሱ ያላችሁ ፍቅር እየጨመረና እየጠለቀ ይሄዳል። ይህ ደግሞ የተለመደ ነገር ነው ምክንያቱም አንድ ሰው ከወደዳችሁ ከእርሱ ጋረ መነጋገርን ትወዱታላችሁና። ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ጸሎት ነው።

በመጸለይ እንዴት መጸለይ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ። ለማለት የፈለግሁት ወደ እርሱ ፍቅር በሚመራችሁ መንገድ ከእርሱ ጋር እንዴት መነጋገር እንዳለባችሁ ትማራላችሁ ለማለት ነው።

በጸሎት ውስጥ በመትጋት በጸሎታችሁ ውስጥ ወደ ምትናገሩት ወደ እያንዳንዱ ቃል ጥልቀት ልትደርሱ ትችላላችሁ። ከዚህ በተጨማሪ ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር እየተጠጋችሁ ትመጣላችሁ ከእርሱ ጋር ለመነጋገርም ትናፍቃላችሁ። ስለሆነም ጸሎት እንዴት እግዚአብሔርን መውደድ እንዳለባችሁ ያስተምራችኋል።

እንዲህ ባለ ጠባይ በጸሎታችሁ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገሩ አንደበታችሁ ከእርሱ ጋር እንዴት መነጋገር እንዳለባችሁ እየለመደ ይመጣል። ይህ ደግሞ አዲስ ቋንቋ መማር የሚፈልግ ሰው ይመስላል። ይህ ሰው ይህን ቋንቋ በሚገባ ባያውቅና መጀመርያ ላይ ቢሳሳትም እንኳ ይህን ቋንቋ መናገር አለበት። ብዙ ጊዜ በመደጋገም ግን አንደበቱ ቋንቋውን ይለማመደዋል በሚገባ እስከሚጠቀምበት ድረስም ቀላል እየሆነለት ይመጣል።

በእናንተም ቢሆን እንዲሁ ነው ይበልጥ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገራችሁ ስትመጡ አንደበታችሁ ይበልጥ ከእርሱ ጋር መነጋገርን እየለመደ ይመጣል። ከዚህ በኋላ በፍቅር ስሜት ውስጥ ሆናችሁ ከእርሱ ጋር መነጋገርን ታውቃላችሁ።

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፭


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር አምስት በዚች ቀን በከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን የከበረ አውስግንዮስ ምስክር ሁኖ ሞተ።

   
❖ ይህም ከንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ጭፍሮች ውስጥ ነው እርሱም እግዚአብሔርን የሚያመልከው ለድኆችና ለምስኪኖች የሚመጸውት ነው መስቀልም እንደ ክዋክብት በሰማይ እያበራ ለንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማመኑ በፊት በተገለጠለት ጊዜ ይህ ቅዱስ አውስግንዮስ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲህ አለው።
❖ ይህ ለክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምልክቱ ነው በዚህም ጠላቶችህን ታሸንፋለህ፤ ያን ጊዜ ከቈስጠንጢኖስ ሠራዊት ውስጥ ከዚህ ቅዱስ ሰው በቀር የክርስቶስን ስም ይጠራ ዘንድ የደፈረ የለም፤ ቈስጠንጢኖስ በከበረ መስቀል ምልክት ጠላቶቹን ድል በአደረገ ጊዜ ዕውነተኛ ክርስቲያን ሆነ የሃይማኖትንም ሥልጣን አቁሞ ከፍ ከፍ አደረገ።
❖ ይህም ቅዱስ አውስግንዮስ እድሜው መቶ ዐሥር ዐመት እስከ ሆነው ከቈስጠንጢኖስና ከልጆቹ ዘመነ መንግሥት በኋላ እስከ ከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን ኖረ፤ በአንዲት ዕለትም በአንጾኪያ ከተማ በአደባባይ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አግኝቷቸው ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላም ሊያአደርግ ወዶ አስታረቃቸው በመታረቃቸውም ደስታ አደረጉ እርሱ የከበረ አረጋዊ ሰው ነውና።

❖ ከዚያም አንድ ክፉ ሰው ወደ ንጉሥ ዑልያኖስ ሒዶ ነገር ሠራበት እንዲህም አለው አውስግንዮስ በራሱ ፈቃድ ገዥና ፈራጅ ዳኛ ሆነ፤ ንጉሥም ይህን ቅዱስ ወደርሱ አቅርቦ ገሠጸው ገዥና ፈራጅ ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማነው አለው፤ የከበረ አውስግንዮስ መልሶ ነፍስህ በእጁ የተያዘች የእግዚአብሔርን አምልኮት ትተህ አንተ ለረከሱ ጣዖታት ለምን ሰገድክ ከአንተ በፊት የነበሩ ነገሥታትን ለምን አልተከተልካቸውም እኔም እንዳንተ ወታደር ሁኜ ከቈስጠንጢኖስ ጋር ሃያ ዓመት ኖርኩ ከልጆቹም ጋር ነበርኩ ከእነርሱ ውስጥ እንዳንተ ያለ ጠባየ ክፉ የለም አለው።
❖ ዑልያኖስም በቅዱስ አውስግንዮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ይሰቅሉት ዘንድ በጐኖቹም ውስጥ መብራቶችን አስገብተው እንዲለበልቡት አዘዘ እርሱም ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህን ሁሉ ታገሠ፤ ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ወታደሮችም ሊቆርጡት በመጡ ጊዜ እስኪጸልይ ይታገሡት ዘንድ ለመናቸው ጸሎቱንም ሲፈጽም የከበረች ራሱን ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
                 

📌 በዚችም ዕለት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ማቴዎስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰማንያ ሰባተኛው ነው፤ የዚህም የአባ ማቴዎስ ወላጆቹ ከእስራኤል ነገድ የሆኑ ክርስቶስን የሚያምኑ በበጎ ሥራዎችም ፍጹማን የሆኑ ናቸው የአባቱም ስም ስምዖን የእናቱም በርባራ ይባላል እግዚአብሔርም ሁለት ዘርን ሰጣቸው የታላቁም ስም ያዕቆብ የታናሹም ማቴዎስ ነው።

❖ እነሆ ማቴዎስም በእናቱ ሆድ ሳለ የአቡፌስ አገር ኤጲስቆጶስ አባ ጴጥሮስ እናቱን አገኛት በአያትም ጊዜ ከበቅሎው ላይ ወርዶ ሆድዋን ሳመ አንቺ ሴት የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው እነሆ እንደ ወንጌላዊ ማርቆስ በትምህርቱ ለሰው ሁሉ የሚያበራ ብሩህ ኮከብ ካንቺ ይወጣልና አላት።
❖ አባ ማቴዎስም ከተወለደ ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሆነው ወላጆቹ አረፉ ከዚህም በኋላ በቅዱስ አቡፋና ገዳም ወደአለ ቆሞስ ወደ አባ አብርሃም ሒዶ የምንኵስና ልብስ እንዲአለብሰውም ለመነው፤ እርሱም ከታላቅ ወንድምህ ተስማማ አለው አባ ማቴዎስም ሰምቶ በልቡ እየተከዘ ተመለሰ በጐዳናም የከበረ መልአክ ሚካኤል በመነኰስ አምሳል ተገናኘው እርሱ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን በእጆቹም ድንቆች ተአምራቶች እንደሚደረጉ ነገረው።

❖ ወደ ወንድሙ ወደ ያዕቆብም ደርሶ እንዲመነኵስ ያሰናብተው ዘንድ ለመነው አባበለውም እምቢ ባለውም ጊዜ የአባ አሞኒ ወደ ሆነ ወደቶና ገዳም ሒዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተማጸነ መነኰሳቱም ወንድሙን በለመኑለት ጊዜ የወደደውን ያደርግ ዘንድ ተወው በዚያንም ጊዜ ወደ ቅዱስ አቡፋና ገዳም ሒዶ አባ አብርሃም አመነኰሰው ከመነኰሳት ሁሉ እስከ አየለ ድረስ በጾምና በጸሎት ተጋደለ።

❖ አንድ ዓመትም ከሆነው በኋላ ኤጲስቆጶሱ አባ ጴጥሮስ ወደ አባ አብርሃም መጣ የአባ ማቴዎስንም ትዕግሥቱንና ብልህነቱን አይቶ ለርሱ ረዳት ይሆነው ዘንድ እንዲሰጠው አባ አብርሃምን ለመነው ኤጲስቆጶሱም ያለ ውዴታው ከርሱ ጋር ወሰደው ፀሐይ ስትገባ ጀምሮ እስከምትወጣ ድረስ መላ ሌሊቱን እየተጋ በኤጲስቆጶሱ ዘንድ ኖረ።
❖ ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆን ሳይወድ በግድ ኤጲስቆጶሱ ቅስና ሾመው፤ ሰይጣንም ቀናበት ፊቷንም እስካሳየችውና ለክፉ ፍትወት ሥራ እስከተናገረችው ድረስ በአንዲት ደም ግባት ባላት ሴት ልብ አድሮ አነሣሣት እርሱ ግን ሞትን እስከተመኘ ድረስ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
❖ ከዚህም በኋላ ወደ ገዳሙ ያሰናብተው ዘንድ ወደ ኤጲስቆጶሱ ገብቶ ማለደው፤ ኤጲስቆጶስም መሔድን በከለከለው ጊዜ ወደ ዕቃ ቤት ገብቶ ዋጋው ብዙ የሆነ የኤጲስቆጶሱን መቀደሻ ልብስ ተክህኖ አንሥቶ በየጥቂቱ በምላጭ ቆረጠውና መልሶ ከቦታው አኖረው።

❖ በማግሥቱም ኤጲስቆጶሱ አባ ማቴዎስን መቀደሻዬን ልብሰ ተክህኖ አምጣልኝ ዛሬ እቀድስ ዘንድ አለው፤ በአቀረበለትም ጊዜ እንደ ዕንጨት ጥራቢ ሁኖ በፊቱ ወደቀ ኤጲስቆጶሱም ተቆጥቶ ይህን የሠራ ማነው አለ አባ ማቴዎስም እኔ ነኝ አሁንም ወደ ቦታዬ ካላሰናበትከኝ በዚህ ቦታ በዝሙት ከምወድቅ ከዚህ የበለጠ እሠራለሁ አለ።
❖ ከዚህም በኋላ በየቀኑ ሦስት ሦስት መቶ እንዲሰግድ በሌሊትም በቤትና በዋሻ ውስጥ ገብቶ እንዳያድር በቤተ ክርስቲያንም ከጸሎት ጊዜ በቀር እንዳይገባ ለገዳሙ ሰዎች ስለርሱ የውግዘት ደብዳቤ ጽፎ በቁጣ አሰናበተው። አባ ማቴዎስም ይህን ቅጣት ተቀብሎ ሁለት ዓመት ያህል ተጋደለ ኤጲስቆጶሱም ትዕግሥቱንና ቅንነቱን ሰምቶ የፍትሐትና የቡራኬ ቃል ላከለት።

❖ ከዚህም በኋላ ወንድሙ ያዕቆብ ወደ ገዳም ወጥቶ መነኰሰ ሰይጣንንም እስከ አሸነፈው ድረስ ተጋደለ፤ አባ ማቴዎስም ወደ አባ እንጦንዮስ ገዳም ሒዶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ ከዚያም ስሙ ያዕቆብ የሚባል ጻድቅ መነኰስ ነበረ ብርሃናዊ መልአክ ወደ አባ ማቴዎስ መጥቶ እጅ ሲነሣው በራሱም ላይ ወንጌልን ሲያኖር በእጁም መክፈቻን ሲሰጠው ራእይን አየ አባ ያዕቆብም በነቃ ጊዜ ይህን ራእይ ለአባ ማቴዎስ ነገረው።
❖ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ከንቱ ውዳሴን በመጥላት ከሀገር ወደ ሀገር የሚዘዋወር ሆነ፤ በአንዲት ዕለትም በቊርባን ቅዳሴ ላይ ሲያገለግል ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ አየው በታናሽ ሕፃን አምሳል በፃሕል ውስጥ ተኝቶ ነበር ኅብስቱንም በሚፈትትበት ጊዜ እጆቹን ዘርግቶ ከታላቅ ልቅሶ ጋር ፈጽሞ እያደነቀ በመፍራትም ለረጅም ጊዜ ይቆማል ይህንንም ራእይ ለማንም ለማን አይናገርም።
❖ መምህሩም ለረጅም ሰዓት ሲቆም በአየ ጊዜ ያደንቅ ነበር ይህንንም ይገልጽለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በአንዲትም ዕለት አባ ማቴዎስ እንደልማዱ ሊቀድስ ገባ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሕፃን አምሳል በጻሕሉ ውስጥ ተኝቶ ኅብስትንም መስሎ በአባ ማቴዎስ እጅ ሲቈረስ ለመምህሩ ለአበምኔቱ ታየው አበ ምኔቱም አደነቀ ለእኛ ለሰው ልጆች ይህን ታላቅ ጸጋ የሰጠኸን አቤቱ ለአንተ ምስጋና ይገባል አለ።

❖ አባ ማቴዎስም ይህን በአየ ጊዜ የብረት ችንካር አመጣ ተልቶ ከእርሱ ትል እስቲወጣ ድረስ በጉልበቱ ውስጥ በዓርብ ቀን ቀረቀረው፤ ከዚህም በኋላ ወደ ደብረ ቊስቋም ሒዶ አብዝቶ እየተጋደለ በዚያ ኖረ ወደ ላይ ቀና ብሎ ሲመለከት ጌታችንን የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ የሚያየው ሆነ ወደታችም ሲመለከት በውቅያኖስ ጥልቅ ውስጥ በጌትነቱ ክብር የሚያየው ሆነ።
❖ ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል በአረፈ ጊዜ ያለ ውዴታው ይህን አባት ሾሙት እምቢ በአላቸውም ጊዜ ጠባቂዎችን በላዩ አደረጉ በማግሥቱም ሊቀ ጵጵስና እንደሚገባው ያዩትን ራእይ ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉም ነገሩት አባ ማቴዎስም እንደማይተዉት አውቆ በሥውር ምላጭ ወስዶ ምላሱን ጐትቶ ቆረጣት በዚያችም ሌሊት እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም ወደርሱ መጥታ የሚያድን ቅባትን ቀብታ ምላሱን እንደ ቀድሞዋ አድርጋ መለሰችለት።
❖ ወደ እስክንድርያም ወሰዱት በነሐሴ ዐሥራ ስድስት አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በበዓልዋ ቀን ሊቀ ጵጵስና በሾሙት ጊዜ ሦስት ጊዜ ይገባዋል የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ በክንዱ ላይም ያደርጉ ዘንድ የወንጌላዊ ማርቆስን ራስ አመጡ እርሷም ወደ ላይ በረረችና አፉን ሳመች።
❖ ከዚያንም ጊዜ ወዲህ በቊርባን ጊዜ በወንበር ላይ አልተቀመጠም በዓርብና በረቡዕ ቀን ከሰው ማንም ወደርሱ ቤት የሚገባ የለም፤ ወንድሙ ውድም አስፈሬ ንግሦ ሳለ የኢትዮጵያ ንጉሥ ዳዊት እንደሚነግሥ ትንቢት ተናገረ፤ ይህም አባት ከራሱ ላይ በሚያደርገው ቀጸላ በሽተኞችን በመፈወስ ሙታንን በማስነሣት በዘመኑ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ።

❖ በዘመኑም ከምስር ሥልጣን በታች ክፉ ሹም ተሾመ ሊቀ ጳጳሳት ማቴዎስን አስቀድሞ የሌለ ግብርን ሊቀበለው ሽቶ ግድ አምጣ አለው በከለከለውም ጊዜ ታላቅ የሆነ ድብደባን ደበደበው ተሸክመውም ወደ ቤቱ ወሰዱት።

❖ በዚያችም ቀን ከዚህ ዓለም ፃዕር ታሳርፈው ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለመናት እርሷም ተገልጻ አትዘን ከስምንት ቀን በኋላ ታርፋለህ ብላ ተናገረችው፤ በማግሥቱም አባ ማቴዎስ ኤጲስቆጶሳቱን ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ሕዝቡንም ሁሉ አስጠራቸውና የዕረፍቱን ቀን ነገራቸው የሃይማኖትንም ነገር መከራቸው ባረካቸውም።

❖ ከዚህም በኋላ ጊዜው ደርሶ ሕማሙ በጸናበት ጊዜ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አንሥቶ ይዞ ለረጅም ጊዜ ጸለየ ሥዕሊቱንም ተሳልሞ ሳማት ፊቱንም በመስቀል ምልክት አማተበ ክርስቶስን የሚያምኑ ምእመናን ያሉበትን ሀገር ሁሉ ባረከ በዕሑድ ቀንም በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

         

📌 በዚችም ቀን የያሬውንዮስ የሌሎችም የሴቶችና የወንዶች የሮማዊው ለንጊኖስ አባ አርሳኒን የጐበኘችው የእለስክንድርያ የአውስያ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

            

📌 ጥር 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ማቴዎስ
2.ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ (ሰማዕት)
3.ቅድስት እስክንድርያ
4.ቅድስት አውስያ ሰማዕት

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
Daniel:
:
:
†† እንኳን ለታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ: ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤልያስ እና ለጻድቁ ቅዱስ ኖኅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††  ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ †††

††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ "አርእስተ ሊቃውንት" ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ (ባስልዮስ የሚሉም አሉ): እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባል እና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው 5 ወንድና አንዲት ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ (ቅድስት ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን 5ቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው::

የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች (websites) እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::

ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ: ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ: የብዙ ምዕመናን አባት: የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት: ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ያስገነባ እርሱ ነው::

እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴውንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል::

በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::

እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::

ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት 6 ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::

ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::

በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: አንዲት ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::

እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር : ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ "ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ : ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::

ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::

እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ: በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ40 ቀን በኋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::

በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ4 አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ3 ቀን በኋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ3ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::

በ6ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ:: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ9ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::

እንዲህ በ3: በ3 ቀናት እየተመላለሰ ለ13 ጊዜ ጠየቀው:: በ39ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ40ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት: ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ: ያን ሰው ከመሃል አቁሞ: "እግዚኦ በሉ" አላቸው::

ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ40 ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::

የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 6 ቀን ዐርፏል::

አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::

††† ታላቁ ቅዱስ ኤልያስ †††

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች:: "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች:: እርሱ ሰማይን የለጐመ: እሳትን ያዘነመ: ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እሥራኤል (10ሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ ኢያስኑዩ : እናቱ ደግሞ ቶና (ቶናህ) ይባላሉ:: በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማሕጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ::

ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል:: ብርሃን የለበሱ 4 ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው::

ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእሥራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል:: ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ: ቁም ነገረኛ: ንጽሕናንም የሚወድ እሥራኤላዊ ነው::
ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት: እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር::ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤል ገብተው ነበር::

ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ: የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር::

በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው:: እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ:: ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል: ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ::

በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር:: በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ:-
1.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)
2.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)
3.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል::

መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን: በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን: በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም:: በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእሥራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት::

ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሐሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት:: ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም: አልለውጥም" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል::

ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም:: የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል" አላቸው:: በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም::

በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች:: 900ው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው:: በእሥራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ:: የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ::

ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ:-
"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል: ዘቆምኩ ቅድሜሁ: ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ:: ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ሰማይ ዝናም ለዘር : ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ::

ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ:: እርሱን ቁራ ይመግበው: ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር:: ይሔው ቢቀርበት ጸለየ:: እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው:: በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ::

ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት:: ቀጥሎም 7 ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል:: ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል::

ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል:: መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ 850ውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል::

ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው:: "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ: እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው::

ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው:: እንጐቻ ባገልግል: ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው:: በላ: ጠጣ: ተኛ:: እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው:: በ3ኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ" አለው::

ኤልያስም ለ40 ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል:: ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም:: እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ 2 ጊዜ እሳትን አዝንሟል::

የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን" አለው:: ሦስት ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ:: ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው:: ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው:: ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት::

ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል:: (ራዕይ) ለተጨማሪ ንባብ ( ከ1ነገ. 17-2ነገ. 2 / እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ:: )

††† ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!

††† አምላከ ኤልያስ ለሃገራችንና ለሕዝቧ ርሕራሔውን ይላክልን::

††† ጻድቅ ኖኅ †††

††† የዚህን ታላቅ ቅዱስ ሰው ክብር የሚያውቅና የሚያከብረው ሁሉ ንዑድ ነው:: አባታችን ኖኅ ዛሬ በዓለም የሚመላለሰው ሰው ሁሉ አባት ነው:: ደግ ጻድቅና ነቢይ ሰው ነው::

ከአባታችን አዳም 10ኛው ጻድቅ ሲሆን ከ15ቱ አበው ነቢያትም አንዱ ነው:: ከአባቱ ከላሜሕ ተወልዶ: በደብር ቅዱስ አድጐ: ንጽሐ መላእክትን ገንዘብ አድርጐ: ለ500 ዓመታት በድንግልና ኑሯል::

በእነዚህ ጊዜያትም አጽመ አዳምን እየጠበቀና መስዋዕትን ለልዑል አምላክ እየሰዋ ያመልክ ነበር:: የሴት ልጆች ከቃየን ልጆች ጋር ተባብረው ዓለም በረከሰች ጊዜም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷል:: ከሚስቱ (እናታችን) ሐይከል (አምዛራ) ጋር 3 ጊዜ አብሮ አድሮ ሴም: ካምና ያፌትን ወልዷል::

የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜም የእመቤታችን ምሳሌ በሆነች መርከብ ድኗል:: ከመርከብ ወጥቶም ከጌታ ጋር በቀስተ ደመና ምስክርነት ቃል ኪዳን ተጋብቷል:: ከዚያም ዓለምን ለ3 ልጆቹ አካፍሎ ለ350 ዓመታት በበጐ አምልኮ ኑሯል:: በዚህች ቀንም ዕድሜን ጠግቦ በ950 ዓመቱ ዐርፏል::

††† የአባታችን በረከት ይደርብን።

††† ጥር 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ግዝረቱ ለክርስቶስ
2.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
3.ቅዱስ ኖኅ ጻድቅ
4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
5.አባ ሙሴ ገዳማዊ
6.አባ ወርክያኖስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
4.ቅድስት ሰሎሜ
5.አባ አርከ ሥሉስ
6.አባ ጽጌ ድንግል
7.ቅድስት አርሴማ ድንግል

††† "እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል::" †††
(ዮሐ. ፲፬፥፲፪)

††† "ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝኩትን: የባሪያየን የሙሴን ሕግ አስቡ:: እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላቹሃለሁ:: መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች: የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል::"  ††† (ሚል. ፬፥፬)

††† "እግዚአብሔርም:- 'የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ:: ከሰው እስከ እንስሳ: እስከ ተንቀሳቃሽም: እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና' አለ:: ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ::
የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው:: ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ: ፍጹምም ሰው ነበር:: ኖኅ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ::" †††
(ዘፍ. ፮፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
5•­3- ØÈ- %- 5õ5u - Ý(p ¥ Ú¥
ASR by NLL APPS
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ስድስት -ግዝረተ እግዚእ
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
Daniel:
እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም "ሥላሴ" እና "ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ሥሉስ ቅዱስ "*+

=>ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::

+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::

+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በሁዋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::

+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርሕ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::

+እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል::

=>በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም:: የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን : በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ: መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::

=>በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::

+*" ሕንጻ ሰናዖር "*+

=>ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::

+ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::

+ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::

+መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::

+ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::

+ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::

+" ቅዳሴ ቤት "+

=>ልክ የዛሬ 324 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (በ1684 ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::

+ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ ንጉሥ ነውና::

+ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::

+*" ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ "*+

=>የሊብያው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

+ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

+እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

+እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና መገለጫ እንመልከት::

1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለ22 ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው)

2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለ50 ዓመታት የተጋደለና ለ15 ዓመታት በስደት የኖረ ነው)

3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው)

4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው)

5.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጉዋድ ውስጥ ለ15 ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው)

6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕጻንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው)

7.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው)

8.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ: ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው)

9.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው)
+እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::
+ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ:-
(ኢሳ. 9:6, መዝ. 46:5, 77:65, ዘካ. 14:4, ዮሐ. 1:1, 10:30, ራዕይ. 1:8, ሮሜ. 9:5 . . .)
አርዮስና የዛሬ መሰሎቹአንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

+በወቅቱም በመወገዙ አርዮስ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

+በ325 ዓ/ም (በኛው በ318 ዓ/ም) ለ40 ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በ4ቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ: ሶል ዼጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

+በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት::

+በጉባኤው መጨረሻም አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ:: አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል::

+ቅዱስ ሶል ዼጥሮስም ከጉባዔው ከተመለሰ በሁዋላ በጐ ጐዳናውን አቅንቶ ቀጥሏል:: ብዙ ድርሳናትን ደርሶ: በድካም ሰብኮ ኢአማንያንን መልሷል:: ፈላስፎችንም ድል ነስቶ አሳምኗል:: መናፍቃን ደግሞ ፈጽመው ይፈሩት ነበር:: ሊቀ ዽዽስናን በተሾመ በ11 ዓመቱም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁንና ጥር 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.በዓለ ሥሉስ ቅዱስ
2.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ
3.ቅዱስ ኤፍሬም
4.ቅዱስ ሰሎሞን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
2.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
3.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
4.አባ ባውላ ገዳማዊ
5.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+ (ቆሮ. 13:14)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ሰባት(፯)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን:: †††

=>+"+ እንኩዋን ለቅዱሳን አበው "አባ መቃርስ" እና "ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ታላቁ ቅዱስ መቃርስ "*+

=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::

+በ4ኛው መቶ ክ/ዘ አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል::

+በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

+ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::

=>ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ) የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::

+በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት አደረጉት::

+ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::

+በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::

+ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::

+መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::

+ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል::

=>ይህቺ ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ስትሆን የተቀደሰችውም በ7ኛው መቶ ክ/ዘ በአባ ብንያሚን እጀ ነው::

+*" ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ "*+

=>ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

+ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27)

+ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ:: ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር:: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

+ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

+ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

+ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት 15ቱ አበው ነቢያት: 4ቱ ዐበይት ነቢያት: 12ቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

=>"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ

*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

=>"4ቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

=>"12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

=>"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

=>ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና

*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ:: በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)

*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
+ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
+ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ 1 ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::+ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::

+ቅዱሱ ነቢይ ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በ3ቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::

+አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ::"
(አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ካንቺ ዘንድ ይወጣልና) አለ::

+ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በሁዋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::

+ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: 7 ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹም ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን ለተፋቅሮ ይበለን: ከበረከታቸውም ይክፈለንና

ጥር 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ
2.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
3.አባ እንድራኒቆስ ሊቀ ዻዻሳት
4.አባ ብንያሚን ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን? +"+ (ሚክ. 6:6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር ስምንት(፰)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
2024/09/30 08:36:18
Back to Top
HTML Embed Code: