Telegram Web Link
🇦🇹#የፋሲል_ከነማ_ስፖርት_ክለብ_ታሪካዊ_ቀን_ሐምሌ_13_2008_ዓ_ም🇦🇹

ዛሬ ሐምሌ 13 ነው...ወደኋላ 8 ዓመት ስንመለስ የምናገኘው ታሪክ የዛሬዋ ''ሐምሌ 13'' ቀን ፋሲል ከነማ ምናልባትም ከምስረታው ቀን ጋር የምትስተካከል አንፀባራቂና የማይረሳ ድል የተጎናፀፈባት ቀን ናት፡፡ ዛሬ በምናብ ወደ ኋላ 8 አመት ተመልሰን በአፄዎቹ መንደር ''ሐምሌ 13'' የሆነውን ሁሉ ሳይሆን አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ያችን ታሪካዊ ቀን "የሐምሌ 13" ትውስታዎቻችን በጨረፍታ ልናስታውሳችሁ ወደድን። ታዲያ እናንተም በሀሳብ መስጫ ቦታው ላይ የእናንተን ትውስታ በፁሁፍና በምስል እንድታካፍሉን ከወዲሁ ተጋብዛችኋል።

ፋሲል ከነማ ከተመሰረተበት 1960 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፈ ብዙ መሰናክሎችን፣ በርካታ ውጣ ውረዶችን እና የተለያዩ ስያሜዎችን በማስተናገድ በልጆቹ ፅናት አስደሳች የአሸናፊነት ጊዜዎችን በማሳለፍ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል፡፡

ፋሲል ከነማ ለበርካታ አመታት ፕሪሚየር ሊግ ለመቀላቀል ጫፍ ላይ በመድረስ ሳይሳካለት በሩን እያንኳኳ የሊጉ መግቢያ በር እንዲገባ ሳይከፈትለት ሲመለስ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል። ድንበር ተሻጋሪ ዓላማ የሰነቀው ፋሲል ከነማ ባሳለፋቸው ውጣ ውረዶችና መሰናክሎች ሳይበገር ያሁሉ ድካምና ጥረት ፍሬ ያፈራው ልክ የዛሬ ሰባት አመት በዛሬዋ ቀን ''ሐምሌ 13/2008 ዓ/ም'' ነበር !! ይህ ጊዜ በተለይም ጎንደር ከፍተኛ የጭንቅ ምጥ ውስጥ የነበረችበት ወቅት ሲሆን እንኳን ለሰላማዊ እግር ኳስ ጨዋታ ቀርቶ ወጥቶ ለመግባት እንኳ አስጊ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
ጎንደር ከቀለሟ በተጨማሪ መዓዛዋ አፄዎቹን ዝማሬዋ ደግሞ ፋሲል ከነማን ይሰብካል። ከተማዋ የአብራኳን ክፋይ ከደሟ ጠልቃ ከአጥንቷ ፍቃ አምጣ የወለደችውን የበኩር ልጇን ፋሲል ከነማን በድል ልትሞሽር ሽር ጉዷን አሳልጠዋለች። ደጋፊዎችም ከሚኖሩበት አካባቢ ወደ አፄ ፋሲለደስ ስታድየም መትመም ጀመሩ..በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ደጋፊዎች ድልን አጭደው የደስታ ምርትን ከሚሰበስቡበት ስፍራ ከትተዋል።

ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከ400 በላይ የሚሆኑ የስታድየም አስተባባሪዎች ባለ አንፀባራቂ መለያ ልብስ ለብሰው በተጠንቀቅ ቆመዋል። እነዚህ አስተባባሪዎች በኢትዮጵያ የሊግ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

በወቅቱ አፄዎቹ ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል ጫፍ የደረሱበት ጊዜ ነው። ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በዚች ቀን ፋሲል በሜዳው ከጠንካራው ኢትዮጵያ መድህን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ አሸንፎ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድግበትን ትኬት የሚቆርጥበት ቀን የነበረ ሲሆን ግን ደግሞ የፋሲልን ህልም ለማጨናገፍ በርካታ የተግባር እንቅፋቶች ነበሩ...

ጨዋታው እስኪጀምር ከተማውንና ህዝቡን ስትቃኝ የዋለችው ፀሀይ ዝናብ ላረገዘው ደመና ቦታዋን ለቀቀች..ዝናብ ያረገዘው ደመና የከበደው የሚመስለው ሰማይ ሆዱን ከፍቶ አፄ ፋሲለደስ ስታድየምና በከተማዋ ላይ አንዠቀዠቀው በዚህ ጊዜ ከወደ ቋራ መቀመጫ የሚታየው የደጋፊዎች ትይንት አይንን የሚስብና በግርምት እጅን በአፍ የሚያስጭን ነበር። ለዶፉ አንበገርም ያሉት ቋረኞቹ ተቃቅፈው የውቅያኖስ ሞገድ በሚመስል ጭፈራ ሲዘሉ ሰማዩ ከሚያወርደው ዝናብ ጋር ተደምሮ ወደ ላይ የሚያወጡት ጢስ የአርባ አራቱ ቤተክርስቲያን ካህናት ቋራን ከበው ከርቤና ዕጣን እያጠኑት ይመስል ነበር።

ከፍተኛ ዝናብ በመዝነቡ ምክኒያት ሜዳው ላያጫውት ይችላል ቢባልም ደጋፊዎች ሜዳ ላይ የተኛውን የዝናብ ቋት በጆንያ ፣ በስፖንጅ ፣ በጀሪካን ፣ በሳፋ በመጥረጊያና በተለያዩ ቁሳቁሶች ውሃውን ከሜዳው ማስወገድ ተያያዙት። ጨዋታው በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ሲጀመር ደጋፊዎቹ ፋሲልዬ አንተን ባየው አይኔ ሌላው ለምኔ ፣ እናሸንፋለን በፋሲል ሙሉ እምነት አለን እና በሌሎች ዝማሬዎች ድጋፋቸውን ቀጥለዋል።

ጨዋታው ያለግብ በጭንቅ ቀጥሎ 77ኛው ደቂቃ ላይ ውጤትና ታሪክ የቀየረች የጭንቅላት ጎል በአመለ ሸጋው አማካይ ይስሐቅ መኩሪያ ተቆጠረች። በዚያን ቅፅበት ደጋፊዎች ያሰሙት ድምፅ ከተማዋን ከጫፍ እስከ ጫፍ አናጣት።
ጨዋታው በአፄዎቹ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ!! በዚህ ጊዜ ደጋፊዎች ተቃቅፈው የደስታ እንባ አነቡ ፣ ዘመሩ ፣ በአፄዎቹ ቤት ታሪክ የፃፉ ተጫዋቾች እና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በጨቀየው ሜዳ ላይ በደረታቸው ተንሸራተቱ ፣ ደጋፊዎች ሜዳ በመግባት ደስታቸውን ከተጫዋቾቹ ጋር ገለፁ ፣ ሜዳው የሰራውን የጭቃ ሸማ ለብሰው ጮቤ ላስረገጣቸው ክለብ የደስታ ምንጭ ነህ ብለው ዘመሩለት!!

አፄዎቹ ''ሐምሌ 13'' ቀንን በልባቸው ላይፍቁ አተሟት!!

የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ታሪካዊ የቡድን አባላት ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኝ እና ኮችንግ ስታፉች እንዲሁም አመራሮች ለዚህች ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ!!

#እንኳን_አደረሳችሁ!!

🇦🇹 #ፋሲል_ከነማ_ከክለብም_በላይ_ነው🇦🇹

@FASILSC
በጎፋ ዞን ውስጥ በምትገኘው በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት ናዳ በርካታ ወገኖች ህይወታቸውን አጥተዋል

ነብስ ይማር፣ ለወዳጅ ቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን እንመኛለን

@FASILSC
2024/11/16 12:57:21
Back to Top
HTML Embed Code: