Telegram Web Link
ለጋብቻ መሠረቱ ሴትነት እና ወንድነት ነውና ጥቂት ስለ ሴትነት እና ወንድነት ማንሳት ተገቢ ይሆናል። አንድም የሴትነትና የወንድነት ትርጉሙን ማወቅ የትዳርን ሕይወት በተገቢው መልኩ የመገንባት አቅምን ያሳድጋልና የቤተ ክርስቲያንን መረዳት መግለጥ ተገቢ ይሆናል። ሴትነትና ወንድነት ለብዙዎቻችን የፆታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ፆታ የሴትነት እና የወንድነት አንዱ መገለጫ እንጂ ብቸኛ መግለጫ አይደለም። በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሴትነት እና ወንድነት ከፆታ እጅግ ከፍ ያለ ነው። በቤተክርስቲያን ሴት የመንፈስ ቅዱስ ወንድ ደግሞ የቃል (ወልደ እግዚአብሔር/የክርስቶስ) ምሳሌ(አምሳል) ናቸው። ምሳሌነታቸውም ግዑዝ(አካላዊ) ሳይሆን የሕይወት ነው።

ሴት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት ሲባል መንፈስ ቅዱስ ከተገለጠበት ግብር አንጻር ስለተገለጠች እና የሥራ ድርሻዋ በዚያ አንቀጽ (መሠረት) የተሰራላት ሥለሆነ ነው። መንፈስ ቅዱስን በግሪኩ ፓራቅሊጦስ (በተለምዶ ጰራቅሊጦስ) ይለዋል። በሶርያዎች የጥንት ጽሑፍ ሲፃፍ የሴት አንቀጽን ይዞ ነው (በእንግሊዝኛው she በሚለው ነው)። የቃሉን ትርጉም ብናይ ደግሞ ከሴት ግብር ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። በግሪኩ ፓራ (para) የሚለው በጎን፣አጠገብ (alongside) የሚለውን ትርጉም ሲይዝ ቅሊጦስ (kletos) የሚለው ደግሞ ረዳት የሚለውን ይተረጉማል፤ ስለዚህ ፓራቅሊጦስ ማለት ‹በጎን፣አጠገብ ያለ ረዳት› የሚልን ትርጉም የያዘ ነው። በተጨማሪም ደግሞ ፓራቅሊጦስ በጥቅል ትርጉሙ ‹ሕይወትን የሚሰጥ› የሚል አሳብን ይይዛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጎን ያለ እረዳት እና ሕይወትን የሚሰጥ የሚለው አሳብ ለማን ነው የተነገረ ካልን በግልጥ ለሔዋን እንደሆነ እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሔዋንን ‹የምትመች እረዳት እንፍጠርለት› ብሎ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን ሲሰራት እናነባለን (ዘፍ. 2፥18) ። ሔዋን የሚለውን ቃል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጉም ‹የሕያዋን ሁሉ እናት› ብሎ ነው (ዘፍ. 3፥20) ። ስለዚህም ሴት (ሔዋን) ከጎን የተገኘች እረዳት እና ሕይወትን የምትሰጥ ናት ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለተገለጠበት ማንነት የምትወክል ሴት መሆኑዋን በግልጥ የሚናገር ነው።

ወንድ የወልድ (የኢየሱስ ክርስቶስ) ውክልናው በክህነት ግብሩ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ከሰው ልጆች በፊት የፈጠራቸውን እንስሳት ስም ያወጣላቸው ዘንድ ወደ አዳም እንዳመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ዘፍ. 2፥19) ። አዳም ከእግዚአብሔር በተሰጠው ስልጣን ለእንስሳቱ ስም ሲያወጣ ክብሩን ለእግዚአብሔር መልሶ ሰጠ (ቅዳሴያችንም ዘአወፈይከኒ አወፈይኩከ እንዲል፤ የሰጠኸኝን ሰጠሁህ) ፤ ይህም የአዳም ተግባር ክህነታዊ መሆኑን የሚነግረን ነው ። በሥሉስ ቅዱስ ዘንድ የዘላለም ካህን የተባለ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ አዳም በግብሩ ክርስቶስን ይወክላል።

✍🏽 ሴት እና ወንድ
ከላይ ከተመለከትነው አንፃር ሴትና ወንድ የፆታ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን ለመገንዘብ እንችላለን። ሴትና ወንድ በውስጡ የግብር ማንነት የተቀመጠበት መለያ ጭምር ነው። ለዚህም ነው በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክህነትን ለወንድ የምንሰጠው። ክህነትን ለወንድ መስጠት ግን ወንድን ማስበለጥ አለመሆኑን ከላይ የሚወክሉት በግልጥ ይናገራል። ሴትና ወንድ የወከሉት መንፈስ ቅዱስን እና ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሆነ አንዱ ከአንዱ ይበልጣል አይባልም። ወልድ ሰው በመሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ አነሰ እንደማይባለው ሁሉ፤ ሴትም ካህን ባለመሆኗ ከወንድ አነሰች አትባልም።

ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሰው የአፈጣጠር ዝርዝር በዘፍጥረት ሁለት ከመተንተኑ በፊት ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ብሎ እኩልነታቸውን የነገረን:: (ዘፍ. 1፥27) በዝርዝር አፈጣጠሩም እንደ አባቶቻችን ትርጓሜ ሴትን ከአዳም ጎን የሠራት እኩልነቷን ሲያጠይቅ ነው፤ ምክንያቱም ከላይ ከፍ ብሎ ከራሱ፣ ከታች ዝቅ ብሎ ከእግሩ አልፈጠራትምና።

✍🏿 ትዳር መቼ ተጀመረ
ትዳር ከውድቀት በፊት ወይንስ በኋላ የሚለው አሳብ ሊቃውንቱን ብዙ ያወያየ አሳብ ነው። ምክንያቱ ሁለት ነው። የመጀመሪያው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት (ዘፍ. 1፥28) የሚለው አምላካዊ በረከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አይተፋፈሩም ነበር (ዘፍ. 2፥25) የሚለው ነው። ብዙ ተባዙ የሚለው መባዛትን በማምጣት አሁን ወዳለው ሥርዓት አሳብን ሲጎትት አይተፋፈሩም ነበር የሚለው ደግሞ እንዴት ብሎ ይሞግታል።

ግልጥ ለማድረግ ያክል የሰው ልጅ አሁን ባለው ሥርዓት ለመባዛት መተፋፈር መቅድሙ ነው። መተፋፈር ከሌለ ስሜት የለም ማለት ነው። ስሜት ከሌለ ደግሞ አሁን ያለው የመባዛት መንገድ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ብዙ ተባዙ የሚለው ትእዛዝ ስላለ ደግሞ መባዛት የግድ ነው። ሊቃውንት ይህን ሲያስማሙት የሰው ልጅ ባይወድቅ ኑሮ እግዚአብሔር ሌላ የሚባዛበት መንገድ ይሰጠው ነበር፤ ለእግዚአብሔር የሚያበዛበት መንገድ አንድ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ የእግዚአብሔርን ማንነት በውል አለመገንዘብ ነው። መላእክት፣ ዕፅዋት፣ እንስሳት የተባዙበት የተለያየ መንገድ የሚነግረን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደ ሌለ ነው። ድኅረ ዓለም ኢየሱስ ከርስቶስ ያለ አባት መወለዱም ሌላ አስረጂ ነው።

ትዳር አሁን ባለው ሥርዓት በአንቀጸ ፆታ (ከፆታ ጋር በተገናኝ) የተጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው። የአዳም ውድቀት በሰው ልጆች ላይ ያመጣው አንዱ ጥፋት ፍቃድን ለስሜት ማስገዛት ነው። ይህንንም የፍጥረቱን ሂደት አይተን እንረዳለን። የሰው ልጅ የተፈጠረው ከእንስሳት በኋላ ሲሆን በጠባዩ ደግሞ ከእነርሱ በላቀ መልኩ ነበር ። ይህም እንስሳትን እና ዓለሙን ይገዛ ዘንድ በተሰጠው ሥልጣን የተገለጠ ነው (1፥28) መግዛቱም ስም በማውጣት፣ ከእባብ ጋር በመነጋገር ተገልጦ እናነባለን። አባቶቻችን በትርጓሜያቸው ላይ ደግሞ እግዚአብሔር አዳምን ማዕከላዊ ፍጥረት አድርጎ እንደፈጠረው ይተረጉማሉ (በእንስሳት እና በመላእክት)። ትዕዛዙን በመጠበቅ ጸንቶ ጠላት ሰይጣንን ድል አድርጎት ቢሆን ኖሮ እንደ መላእክት ሊሆን፤ ስላልጠበቀ ግን ሲወድቅ እንደ እንስሳት ስሜታዊ ሆነ። በዚህ ጊዜ ሴትነት እና ወንድነትም ከግብሩ ወርዶ ፆታ ለይ አረፈ (ፆታ መገለጫው ሆነ) ።

በጥቅሉ ሴት እና ወንድን በፆታ አንቀጽ ብቻ አይቶ ትዳርን ማሰብ እና መመስረት ብሎም ለመምራት መድከም እጅግ ዋጋ የሚያስከፍል ነው። ወንድነት እና ሴትነት ፆታ ብቻ ሳይሆን ከፍ ባለው የቀደመ የሰው ልጅ ክብር የግብር መገለጫ ነው። ስለዚህም ትዳርን የሚጀምርም ሆነ ለመምራት የሚሞክር ሰው በውስጡ ያለውን የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታ እና የመሳሰሉት በጎ የሕይወት ስኬቶችን ያገኝ ዘንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የምትመክረው ትዳርን ከፆታ ከፍ ባለ መልኩ በግብሩ መረዳት እና በግብር ጎዳናው መምራት ነው። ትርጉሙ ከላይ የተገለጠ ሲሆን ጎዳናው ደግሞ ከታች/ቀጥሎ በሚቀርበው ዝርዝር/ በብዙ ህብር የሚገለጥ ይሆናል።

✍🏽 የትዳር ዓላማዎች
ትዳርን እግዚአብሔር ለሦስት ዓላማዎች መሥርቶታል (ሦስት ዓላማዎችን በውስጡ አኑሮበታል)። እነዚህም ለመረዳዳት፣ ዘር ለመተካት፣ እና ከዝሙት ጠንቅ እኛን ልጆቹን ለመጠበቅ ነው። እነዚህ ሦስት የትዳር ዓላማዎች በአግባቡ በያዙት ጽንሰ አሳብ መጠን በትምህርት ውስጥ በተገቢው ባለመገለጣቸው ተገቢው ትኩረት ተነፍጎአቸው ይታያሉ። ምክንያቱ ደግሞ ዓላማዎቹ በጽንሰ አሳብ ደረጃ ሳይሆን በቀጥታ ትርጉም ብቻ ለመረዳት እና ለማስረዳት የተሞከረበት መንገድ ነው። በመቀጠል እነዚህን ሦስት ጽንሰ አሳቦች (የትዳር ዓላማዎች) እንድ በአንድ እነንመለከታቸዋለን።

✍🏽 አንድ፤ ለመረዳዳት

መረዳዳት ተባብሮ መስራትን እና መተጋገዝን የሚያመለክት ጽንሰ አሳብ ነው። መረዳዳት በትኩረት ከተመለከቱት ደግሞ ብቻን የመስራት ድካምንና ፍሬ ቢስ መሆንን የሚያጠይቅ ነው። በትዳር አንቀጽ ስንመጣ ሴትና ወንድን በኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር እናገኛቸዋለን። ሴትና ወንድ ዘር መተካትን ለብቻቸው ስለማይችሉት ይጣመሩ ዘንድ ሕግ ሲሰራላቸው እግዚአብሔር ደግሞ መረዳዳታቸው ጥቅም ይሆንላቸው ዘንድ በበረከት ከእነርሱ ጋር ይሆናል።

መረዳዳት የተለያዩ አካላትን ለአንድ ተግባር የሚያስተሳስር ጽንሰ አሳብ ነውና የግብር ኃላፊነትን ማዘጋጀት ይጠይቃል። በትዳር ሕይወት ውስጥ ኃላፊነት ያለባቸው ሦስት አካላት ሲሆኑ የሥራ ድርሻቸውንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ አስቀምጦታል። የሥራ ድርሻውን የማያውቅ ሰው ለግጭት እና ለብጥብጥ ቅርብ ነውና የሰው ልጅ (ሴት፣ ወንድ) በትዳር ውስጥ ያለውን ድርሻ በተገቢው መንገድ ሊያውቅ ይገባል። የሥራ ድርሻውን አውቆ የሚሠራ ሰው ለሥራውም ሆነ አብሮት ለሚሰራው ሰው አጋዥ መሆንን ይችላል። ሥራውን በመስራት የድርሻውን በመወጣት መከናወኑን ሲያፋጥን አብሮት ለሚሰራው ሰው ደግሞ ብርታት ይሆናል። ነገር ግን በሌላው ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ ውጤቱ በሌለው ላይ የተመረኮዘ እንዲሁም ለምክንያት የተጋለጠ ይሆናል።

በትዳር ውስጥ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ለሴቷም ሆነ ለወንዱ የሥራ ድርሻ አላቸው። የቤተክርስቲያን ምክሯም ሁለቱም ያለመጠባበቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ነው። ይህንንም የሚመሰርቱበት የእግዚአብሔር ፍቅር ግድ ትላቸዋለች። ምክንያቱም ፍቅር መቀበል የሌለበት መስጠት ስለሆነ። መቀበልን በቅድመ ሁናቴ ያላስቀመጠ የሥራ ድርሻን መወጣት የትዳርን ኪዳን ለመወጣት ሲያግዝ በኪዳን ኑሮው የደከመውን ለማገዝ እድል ይሆናል። ሁለተኛ ወገኑን ተመልክቶ ለምን በማለት ከተግባሩ የሚዘገይ ግን ተግባሩን ባለመሥራቱ ሲከስር ለሁለተኛ ወገኑም ብርታት ሳይሆን ይቀራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሴት እና ለወንድ የተሰጣቸው የሥራ ድርሻ እንደ ግብራቸው ነው። በጎን (አጠገብ) ያለ እረዳት እና ሕይወት ሰጪ መሆን አንዱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ማፍቀርና እና ክህነት ናቸው። እረዳትነትን መጽሐፍ ቅዱስ የምትመች ብሎ (ዘፍ. 2፥18) እና ከግብረ እንስሳዊ ጠባይ አኳያ ደግሞ ጌታየ ብሎ መታዘዝን (1ጴጥ. 3፥1) ለሴት ይሰጣል። ማፍቀርና ክህነትን ደግሞ ለወንድ ይሰጣል (ዘፍ. 2፥24፣ዘጽ. 28፥41፣ ቲቶ. 1፥6-8፣ ኤፌ. 5፥25-26) ።

ከአምልኮተ እግዚአብሔር አንፃር ሲታይ የወንድም የሴትም የሥራ ድርሻ አገልግሎት ነው። አገልግሎት አገልጋይ እና ተገልጋይ ያለበት ተግባር ነው። በአገልጋይነት ያለውን ድርሻ ወንድ ሲይዝ የተገልጋይነቱን ደግሞ ሴት ትይዛለች። ፍቅር እና ክህነት ጠባያቸው አገልጋይነት ነው፤ እረዳትነት እና መታዘዝ ደግሞ የተገልጋይነት ጠባይ ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር አገልጋይነትን እና ተገልጋይነትን በዚህ ዓለም (በምድራዊ እውቀት) የአረዳድ ዘይቤ ወስደን ልንረዳው መሞከር ተገቢ አለመሆኑን ነው።

ምክንያቱም የዚህ ምድር አረዳድ አገልጋይነትን የማስበለጥ ዝንባሌ ስላለው ነው። አገላጋይ የሚኖረው (በትኩረት ከታየ) ተገልጋይ ሲኖር ነው። ያለ ተገልጋይ አገልጋይነት የለም። ያለ ሔዋን የአዳም አገልጋይነት በእንስሳት ብቻ ተገድቦ ከንቱ ይሆን ነበር። ሔዋን የአዳምን አገልጋይነት ምሉዕ ያደረገች ናት። በውክልናቸው አንፃር ሲታይ ደግሞ፤ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጠም፤ መንፈስ ቅዱስም ባለመሞቱ ከወልድ አይበልጥም፣ ትክክል ነው እንጂ። ስለዚህ አገልጋይነት እና ተገልጋይነት በአገልግሎት ሂደት የሥራ ድርሻ እንጂ የማበላለጫ መንግድ አይደለም። የአገልጋይነት እና የተገልጋይነት ማሰሪያው አገልግሎት ነው፤ አገልግሎት ውስጥ ሁለቱም አሉ። ያለ አገልግሎቱ የእግዚአብሔርን በረከት ማግኘት አይቻልም።

ወደ መረዳዳት ጽንሰ አሳብ ስናመጣው መረዳዳት በአገልግሎት ውስጥ ጌታየ ብሎ በመታዘዝ እና ራስን ለመስቀል ሞት እንኳን ሳይራሩ በማፍቀር የሚተገበር ሕይወት ነው። ሴቷ የሚመች እረዳት መሆንን እስከ ጌታየ ብሎ መታዘዝ የምትዘልቅበት ሕይወት ሲሆን፤ ወንድ ደግሞ የክህነት አገልግሎቱን እስከ ሞት ወደ ሚደርስ ፍቅር የሚያሳድግበት ነው። ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ትዳርን አንድ የአሳብ መስመር ብንሰራለት በአንደኛው ጫፍ ጌታየ ብሎ መታዘዝ ሲኖር በሌላኛው ጫፍ ደግሞ እስከ ሞት የሚያደርስ ፍጹም ፍቅር ይኖራል ማለት ነው። ትዳር በእነዚህ ሁለት ጽንሰ አሳቦች ውስጥ ሁኖ ሲመራ ጤናማ ይሆናል።

ነገር ግን ልንገነዘበው እና ልንረሳው የማይገባ ሴት ልጅ ባሏን አታፍቅረዉ ወንድ ልጅም ሚስቱን አይታዘዝ ማለት አለመሆኑን ነው። የዘመናችን ትልቁ በሽታ ያልተጻፈን ምንባብ ማንበብ ነው። ብዙዎች የተጻፈን ጉዳይ አንብቦ በትኩረት ከመገንዘብ ይልቅ በሚያነቡት ንባብ ላይ በጭንቅላታቸው የሚመጣውን ጊዜያዊ መረዳታቸውን ጨምረው ያነቡታል። ከዚህም የተነሳ የሚስቱ ብዙ ናቸው። አንዲህ ግን መሆን የለበትም። ስለዚህም ባል ሚስቱን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ይውደዳት አለ እንጂ ሚስት ባሏን አትውደድ የሚል አልተጻፈም። እንዲሁም ሚስተ ባሏን ጌታየ ብላ ትታዘዘው ተብሎ ተጻፈ እንጂ ባል ሚስቱን አይታዘዝ ተብሎ አልተጻፈም። ትዳራቸው ጤናማ ይሆን ዘንድ አፍቃሪ ባል የማትታዘዝ ሚስት ብትኖረው ይታዘዛት እና ትዳሩን ጤናማ ያድርግ። የምትታዘዝ ሚስት የሚያፈቅር ባል ባይኖራት ትዳራቸው ምሉዕ ይሆን ዘንድ ታፍቅረው። እንዲሁም ፍቅር የመታዘዝ ሥር ነውና ሃይማኖታዊ ለሆነው ኑሮው ባል ሚስቱን ይታዘዛል። መታዘዝም የፍቅር ውጤት ነውና የምትታዘዛ ሴት ባሏን የምታፈቅር ናት። መጽሐፍ ሴትን በአፍቃሪነቷ የመታዘዝን የሥራ ድርሻ ሲሰጣት፤ ለወንድ ደግሞ ሴትን በመታዘዝ የወደቀ ነውና ባዘዘችበት ፍቅር ያነሳት ዘንድ ፍቅር በሥራ ድርሻነት ተሰጠው።

በጥቅሉ ሲታይ ደግሞ አንድ ትዳር የደስታ መናኸሪያ ይሆን ዘንድ ፍቅር እና መታዘዝ ያስፈልገዋል። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መስሎ አስተምሮታል ‹‹ ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻችው ይገዙ። ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ … እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል›› ኤፌሶን 5፥22-28 ። ክርስቶስ ያለ ቤተክርስቲያን ክርስቶስ የሚባል ህልውና የለውም፤ ቃል፣ ወልድ ቢባል እንጂ። ቤክርስቲያን ደግሞ ያለ ክርስቶስ ፈጽሞ ምንም ህልውና
የላትም በክርስቶስ የተመሰረተች ናትና። ለባልና ለሚስት ሲሆን ደግሞ ሁለቱም ፍጡራን ናቸው እና የሚመሰርቱት ትዳር ያለ ሁለቱ ሕልውና የለውም። ሕልውናው የጸና ይሆን ዘንድ ቅዱስ ጳውሎስ በምሳሌ የሥራ ኃላፊነታቸውን አስተማረ።

በመረዳዳት አንቀጽ ውስጥ ያለው የሴት እና የወንድ የሥራ ድርሻ እግዚአብሔር ከአስቀመጠላቸው ተፈጥሮአዊ ማንንት ጋር በተገናዘበ የስራ ኃላፊነት እንጂ ደረጃ ወይንም ስልጣን አይደለም። ምክንያቱም በወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ደረጃ ወይንም ስልጣን ስለሌለ። ስለዚህም ሥነ ሕይወታዊ (Biological) እና መሰል አመክንዮዎችን በመደርደር በባልና በሚስት መካከል ደረጃ ወይንም ስልጣን ለማስቀመጥ መሞከር ኦርቶዶክሳዊ ጠባይ አይደለለም።

መረዳዳት በሕይወት ውስጥ በሦስት ነገሮች የተገለጠ(የሚገለጥ) ነው፤ በማሰብ፣ በመናገር፣ እና በማድረግ። ይህም በአባቶች የማሰር እና የመፍታት ስልጣን ውስጥ ተገልጦም እንሰማለን፤ በአሳብ (በሃሊዮ)፣ በንግግር (በነቢብ)፣ በተግባር (በገቢር) የማይሰራ ኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታህ። ይህም የሆነበት ምክንያት የሰው ልጂ በአምስቱ የስሜት ህዋሳት መነሻነት ወደ ሰውነቱ ያስገባውን ጽድቅም ሆነ ኃጢአት የሚከውነው በሦስቱ (በአሳብ፣ በንግግር፣ በድርጊት)ስለሆነ ነው።

✍🏽 በአሳብ
በአሳብ ባል ሚስቱን፣ ሚስት ባልዋን የያዙት ኪዳን እንጂ የምድራራዊ ስምምነት አለመሆኑን አውቀው ሊተጋገዙ ይገባል። የንግግርም ሆነ የድርጊት ዓይነተኛ ምንጭ አሳብ ነው ። አሳብ በስሜት እንዳይሸፈን(እንዳይሸነፍ) በእውቀት መከላከል ተገቢ ነው። ስለዚህ ባለትዳሮች ስለትዳር ያላቸውን አሳብ በስሜት እንዳይጎዳ በእውቀት ሊጠብቁት ይገባል። ይህ ከሆነ በአሳብ ትዳራቸውን ማገዝ ይችላሉ። ባል ሚስቱን ይረደታል (ይረዳታል)፤ ሚስትም ባልዋን ትረዳዋለች (ትረዳዋለች)። በአሳብ የተጀመረ ሚስትን ማፍቀር በንግግር የተገለጠ በድርጊት የሚታይ ይሆናል፤ በአሳብ የተጀመረ መታዘዝ በንግግር እንደ ሣራ ጌታየ (እንደ ጊዜ ግብሩ) ተብሎ የሚገለጥ በድርጊት የሚዳሰስ ይሆናል። መረዳዳት በአሳብ ካልተጀመረ ስሜት ስለሚወርሰው ፍሬያማ አይሆንም። ስሜት የአሳብ መፈጸሚያ አቅም ሊሆን ነው እንጂ የሚገባ በራሱ አሳብ መሆን የለበትም። ስሜት በራሱ አሳብ ከሆነ እንደ ጠላታችን ሰይጣን እና የአስቆርቱ ይሁዳ ይወርሰናል። ሰይጣንና የአስቆርቱ ይሁዳ ስሜትን በአሳባቸው ላይ ስለአነገሱት ለንስሐ ልባቸውን ተሰለቡ፤ አዳምና ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በአሳብ ሳይሆን በንግግር ወደ ስሜት ገብተዋልና ወደ አሳባቸው ሲመለሱ ንስሐ ገብተዋል። ስለዚህ ትዳርን በአሳብ መገንዘብ ተገቢ ነው።

የሰይጣን እና የአዳም ልዩነታቸው አሳብ ነው። ሰይጣን ዲያብሎስ ሲበድል እና ከዓለመ መላእክት ሲለይ የበደሉ ምንጭ አሳቡ ነበረች እና ወረሰችው። አዳም ግን የበደለው ሰምቶ ነውና የሰማው ባይሆንለት ተጸጸተ። በጄሮ የገባን ኃጢአትም በጀሮ በተሰማ ብሥራት አስወጣለት። በጀሮ የሰማው ኃጢአት ይህንን ብትበላ አምላክ ትሆናለህ የሚለው የዲያብሎስ ቅጥፈት ነው (ዘፍ. 3፥ 4-5) ። አዳም እጸ በለስን መብላትን እና አምላክ የመሆንን ፍላጎት እንደ ዲያብሎስ ከልቡ አላመነጫትም እና አምላክ መሆን ባይሳከለት የሰራው ኃጢአት ገብቶት/ ተረድቶት ንስሐ ገባ፤ ዲያብሎስ ግን ከልቡ አምላክ የመሆንን አሳብ አውጥቶአታልና ወረሰችው። ብሥራቱ ቅዱስ ገብርኤል ትጸንሻለሽ ብሎ ለእመቤታችን የተናገረው ነው (ሉቃ. 1፥28) ። አሳብ ከልብ ይመነጫል፤ በመቀጠል ሰውነትን/ማንነትን ይወርሳል። ስለዚህም በትዳር ሕይወት ውስጥ ስለ ትድር ያለንን አሳብ በተገቢው መንገድ ማነጽ ተገቢ ነው።

ብዙ ጊዜ በትዳር ውስጥ የሚሰተዋለው ፍች አሳብን በአግባቡ አስቀድሞ በኪዳን ላይ ካለማሳረፍ የሚመነጭ ነው። ትዳርን የምንመዝነው በሥጋ ሚዛን ብቻ ይሆንና አሳባችን በዚያ ላይ ይንጠለጠላል። በሥጋ ደረጃ ያሉ አሳቦች ደግሞ ለትዳር ሕይወት ተገቢውን ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ ማምጣት አይችሉምና መፈፍትሔ ይመስል ውደ መፋታት ይኬዳል። ይሁንና ትዳርን መፍታት ግን ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ለዘለቄታው የሚሆን ፍቅር፣ ሰላም፣ እና ደስታ ማምጣት አይችልም። ፍች በራሱ ለሌላ ትዳር ርሃብን የሚፈጥር እንጂ ለትዳር ችግር መፍትሔ መሆን የማይችል ነው። ስለዚህም ኣሳብን በተገቢው መንገድ መስመር ማስያዝ የትዳርን ሕይወት የሚያቀና የጠፋውን ፍቅር፣ ሰላምና፣ እና ደስታ መመለስ የሚያስችል ነው።

በአሳብ መረዳዳት ሲባል በድርጊት እና በንግግር የሚገለጡ የባልም ሆነ የሚስት አሳቦች ከፍቅር እና ከመታዘዝ መሆኑን መረዳት ማለት ነው። ባል ሚስቱ ለእርሱ የማይስማማው ነገር እንኳን ብትናገር ወይንም ብትሰራ ወደ ስሜት ከመግባት ይልቅ ስህተት የመሰለው ነገር የተሰራው ትዳራቸውን የሚያቆም መስሎአት መሆኑን በማሰብ መጀመር አለበት። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት መሰረት ያደረገ ሃይማኖታዊ መረዳት ነው። በቅን አስተሳሰብ (Postive thinking) የጀመረ ሰው ሌላውን የመረዳት (የመርዳት) አቅም ይኖረዋል። ለባል ብቻ ሳይሆን ለሚስትም እንደዚያው ነው።

ስለዚህ ሚስትም ሆነች ባል በንግግር እና በድርጊት በሚገለጥ ማንነታቸው ውስጥ ሊያዳብሩት የሚገባ የግንኙነት መስመር ቅን የሆነ አስተሳሰብን ነው። ባልም ሆነ ሚስት ለአጋራቸው እጅግ ቅን የሆነ አጋዥ አሳብ ማሰብን ሊያጎለብቱ ይገባል። ፍቅር እና መታዘዝን መሸከም የሚችል ቅን የሆነ አሳብ ብቻ ነው። አዳምና ሔዋን በቅንነት እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትዕዛዝ አስበውት ቢሆን ኖሮ በመታዘዝ የእግዚአብሔርን ፍቅር ገንዘብ ባደረጉ (በወረሱ) ነበር። ከዚህ ፍሬ ብትበሉ ‹‹ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምና ክፉን የምታውቁ እድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ ›. ባለቸው ጊዜ ከስሜታቸው ወጥተው በኣሳብ ጉዳዩን አይተውት ቢሆን ኑሮ ቀጥፈው ባልበሉ ነበር። ምክንያቱም እደ እግዚአብሔር የሚያደርግ እና እግዚአብሔር ያንን የማይፈልግ ቢሆን ኑሮ እጸ በለስን አጠገባቸው ባለስቀመጣት ነበር፤ ትዕዛዝም በመስጠት ስሜት ወደ አሳባቸው እንዲገባ ባልፈቀደ ነበር። ይሁንና ሰምተው አደረጉት፤ ከልብ ያሰቡበት አልነበረምና ንስሐ ገቡ። ከልብ በአሳብ ተጸንሶ ያልተወለደ ማንኛውም ንግግር ወይንም ደርጊት ጸጸት ሊከተለው የሚችል ነው። ስለዚህ በትዳር ውስጥ አሳብን መጠበቅ ተገቢ ነው።

ሁል ጊዜም ቢሆን ባለትዳሮች ለትዳር አጋራቸው በጎ ለማሰብ እራሳቸውን ማስለመድ አለባቸው። ማንኛውም ሰው ከትዳር አጋሩ በበለጠ ራሱን የሰጠው እና ሊሰጠው የሚችል የለም። እራስን እርቃን አድርጎ ከመስጠት በላይም የሚሆን የለም። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰው ራቁት የሆነ ገላማ በገንዘብስ እንደ ሴተኛ አዳሪ ቤት ባለው ይገኝ የለምን የሚል ጉንጭ አልፋ ከርከር ያነሳል። ሊገነዘቡት የሚገባ ግን ሴተኛ አዳሪ ቤት ያለው ለስሜት ሲሆን በትዳር ውስጥ ያለው ግን ለሕይወት መሆኑን ነው። ስሜት እንደ አዳም ሞትን ሲጠራ ለሕይወት የሆነ እርቃን ደግሞ እንደ ክርስቶስ ሕይወትን ያሰጣል።

✍🏽 በንግግር
ንግግር ከስሜት እና ከአሳብ ይፈልቃል። ሰው የተናገረው ሁሉ ከአሳቡ የፈለቀ የሚያምንበት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ቀላል የማይባለው የሰው ልጅ ንግግር ከስሜት ይፈልቃል። ስሜት ጠባዩ ሁለት ነው፤ ሀዘን ወይንም ደስታ። ሰው በስሜት ውስጥ ሲገባ የሚያምንበት አሳቡ በስሜቱ ይዋጥበታል። ስለዚህም በስሜት ውስጥ እያለ እንዳይወስን ይመከራል። በትዳር ውስጥም ስሜታዊ ንግግሮች አሉ፤ እንዲያውም ከሌሎች የኑሮ ኩነተች በትዳር ውስጥ የስሜት ንግገሮች ይበዛሉ። የስሜት ንግግሮችን የሚያበዛዉ የግንኙነቱ መሰረት እና አንዱ የፍቅር ጠባይ ስሜት ስለሆነ ነው።

ንግግር ደስ የሚያሰኘውን ያክል ያሳዝናልም። በትዳር ውስጥም የሚያስደስትም የሚያሳዝንም ንግግር ከሁለቱም ወገን ይመጣል። ስለዚህ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሁነት እንግዳ መሆን አይገባም። በተለይ የማያስደስቱ ንግግሮች ሲኖሩ ምንጫቸው ስሜት ወይንስ አሳብ የሚሉት ለመለየት መሞከር ተገቢ ነው።

ማስታወሻ:- ዲ/ን አርክቴክት አንተነህ ጌትነት Agora university: Holy Transfiguration college በTheological studies እንዲሁም Holy Sofia University
በOrthodox Christian Apologetics የማስተርስ ዲግሪዎቻቸውን እየሠሩ ይገኛሉ::

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ድንግል_ሆይ!
#ከዓይኖችሽ_በልጅሽ_ፊት_ላይ_የፈሰሰውን_መራራውን_የእንባ_ጎርፍ_አሳስቢ!!!

ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ኅዳር 5 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ ጽጌ፣ ወርኀ ጽጌ፣ መዋዕለ ጽጌ በመባል ይታወቃል።

ቀናቱ 40 ናቸው፣ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ምሥጢሩ እመቤታችንንም ጌታንም ይመለከታል፣ በዚህ ወቅት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደችው ስደት ይታሰባል፣ እሑድ እሑድ በማኅሌት ዘወትር በጸሎትና በስግደት እንዲሁም የእመቤታችን ፍቅር የበዛላቸው ደግሞ በጾም ያስቡታል።

የስደቱ የጊዜ መጠን በአጠቃላይ 3 ዓመት ከመንፈቅ ሲሆን 1260 ቀናት ናቸው።

በዚህ የስደት ጊዜ ውስጥ እመቤታችን ያልተቀበለችው ስቃይና መከራ የለም፣ እኛ በዓለም ላይ ምንም ዓይነት መከራ ብንቀበል በኃጢአታችን ምክንያት ነው እመቤታችን ግን ምንም ኃጢአት ሳይኖርባት ነው።

ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ ጀርባዋ ላይ ነበር እኛም ሁላችን በእርሱ መሃል እጅ ሆነን በእርሷ ትከሻ ላይ ነበርን፣ እርሱን ብቻ ሳይሆን እኛንም አዝላ ተሰዳለች፣
የግብፅ አሸዋ የንጽህት ድንግልን እንባ ጠጥቷል፣ መሬቱም ጥንተ አብሶ የሌለበትን ደም ጠጥቷል።

በሔዋን ምክንያት የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት የሔዋንን ባህርይ ይዛ እንደ ሔዋን ግን ሳትበድል መንከራተት የነበረባት ንጽሕት ሴት እመቤታችን ስለሆነች የድኅነታችን ሁሉ ምሥጢር በእርሷ በኩል አልፏል።

☞ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህን ሲገልጥ "ወኮነት ፈዳዪተ ዕዳሃ ለሔዋን"(የሔዋን ዕዳ ከፋይ ሆነች) ይላል፣ሃይ•አበ።

☞ቅዱስ ኤፍሬምም "አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ" (የባህርያችን መመኪያ ነሽ) ብሏታል፣ ቅዱስ ያሬድም "ትምክህተ ዘመድነ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም" (የባህርያችን መመኪያ እመቤታችን ማርያም ናት) በማለት ተናግሯል።

በስደት ጊዜ እመቤታችን አራት ጊዜ መራራ የሆነ ለቅሶ አንዳለቀሰች ሊቃውንት አባቶቻችን ይገልጣሉ፦

1. የዮሴፍ ልጅ ዮሳ የሄሮድስ ወታደሮች መቃረባቸውን ሲነግራት፤

2. የትዕማን ሴት አገልጋይ ጌታን መሬት ላይ ስትፈጠፍጠው፤

3. ሰብአ ሰገል የገበሩለት የወርቅ ጫማው ሲጠፋ፤

4. ጥጦስን ዳክርስ የሚባሉ ሺፍቶች ሲያገኟቸው፡፡ (ምንጭ:—ነገረ ማርያም፣ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)።

☞የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ብቻ እንመልከት!

ዮሳ የሄሮድስን ውሳኔ እና የወታደሮቹን መታዘዝ ከአልዓዛር ሰምቶ እነርሱ 40 ቀን የተጓዙትን እሱ በ 3 ቀን ገስግሶ ደርሶ እመቤታችን ጌታን እያጠባች ወንዝ ዳር ተቀምጠው አግኝቷቸዋል፣ እርሱም ሰይጣን በምትሀት ሽማግሌ መስሎ በነገረው መሠረት የሄሮድስ ጭፍሮች መድረሳቸውን ለእመቤታችን ነገራት ፣እመቤታችንም "ልጄ እንስሳት አራዊት የማይችሉትን መከራ የተቀበልኩ ከዚህ ላላድንህ ነው?" ብላ ዓይኗን ከዓይኑ ፣ አፏን ከአፉ ፣ እጇን ከእጁ ላይ አድርጋ ምርር ብላ ፅኑ ለቅሶ አልቀሳለች።

ደራሲው:—

"አመ ፈነወ ሄሮድስ ወአሊሁ ውስተ ደብረ ቊስቋም ይኅሥሣ
ሰሚኣ ድድቀተ እምቃለ ወልደ ዮሴፍ ዮሳ
ማርያም ደንገፀት ወተሀውከ ከርሣ
እምእደ ሰሎሜ ሶቤሃ ተመጠወቶ ለሮሳ
ከመ ትብክዮ ዐቍራ በልብሳ።"

ትርጉም:—
በደብረ ቊስቋም ይፈልጋት ዘንድ ሄሮድስ አሽከሮቹን በላከ ጊዜ እመቤታችን ከዮሴፍ ልጅ ዮሳ የሚያስደነግጥ ነገርን ሰምታ ደነገጠች፣ አንጀቷም ተላወሰ! ያን ጊዜም በልብሷ ጠቅልላ (ቋጥራ) ታለቅስለት ዘንድ ልጇን ከሰሎሜ እጅ ተቀበለችው" እንዲል።

ከዮሴፍና ከሰሎሜ በቀር ማንም በሌለበት በረሃ ማረፊያ እንደሌላት ወፍ የምትንከራተት ንጽሕት ድንግል እመቤታችን የሚያቃጥል መራራ እንባዋን በልጇ ፊት ላይ አፈሰሰችው፣ ጎረፈ፣ ፊቱን እያጠበው፣ እያቃጠለው ወረደ፣ንጹሕ እንባ ነው፣ ትኩስ እንባ ነው፣ ቁጡ እንባ ነው ፊት ይመልጣል ዓይን ያንጣጣል! ይህ እንባ ደግሞ በከንቱ የቀረ ሳይሆን ለመማፀኛ እንዲሆን የተረጨ እንባ ነው፣ የጌታን የልጇን ልብ የማንኳኳት ዓቅም ያለው እንባ ነው፣ እሱም ያውቀዋል መራራነቱን፣ የፈሰሰው ፊቱ ላይ ነው አላየሁትም አይልም፣ እናቱ ናት፣ ፈጥሯታል የልቧን አላውቅም አይልም፣ ብቸኝነቷን ከጽድቋ ጋር ያውቀዋል አላየሁሽም አይላትም፣ ይህ እንባ ከንቱ አልቀረምና በመስቀል እኛን በልጅነት እሷን በእናትነት አስተሳስሯል።

☞☞☞ እናትነት ጠባዩ እንዲህ ነው እያነቡ ለልጅ ደስታ መሆን ነው፣ ሀገር መሆን ፣ዓለም መሆን፣ ሁሉን ማያ መሆን ነው!!! እኛ ዛሬ ይህን እንባዋን"አዘክሪ" እያልን እንማፀንበታለን፣ "ድንግል ሆይ በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!"
(አባ ሕርያቆስ)።

የመጨረሻው ጥጦስና ዳክርስ ባገኟቸው ጊዜ ነው፣ ልብሱን ቀምተው እንመልስለት አንመልስለት እያሉ ሲከራከሩ አይታ እመቤታችን ልጄን ሊገሉብኝ ነው ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡

ደራሲውም ይህንን ጭንቀቷን በመንፈሳዊ ምናብ ተመልክቶ እንዲህ አለ፦

"ይጽብበኒ እግዝእትየ ከመ ጸበበኪ ዓለም በምልኡ
ሶበ ዐገቱኪ ፈያት ልብሰ ወልድኪ ይንሥኡ
ዓይንኪ ዘርግብ ነጸፍጻፈ አንብዕ ይክዑ፣ነጺሮ ዕርቃኖ ለሕፃንኪ በግዑ፣
እስከነ አግብአ ለኪ አሐዱ እምካልኡ
እንዘ ያነክር እምፄና ልብሱ ወአዳም መልክኡ"

ትርጉም:—

እመቤቴ ሆይ! የልጅሽን ልብስ ሊወስዱ ሽፍቶች በከበቡሽ ጊዜ ዓለም በሙሉ እንደጠበበሽ እኔን ይጥበበኝ ይጭነቀኝ! ከሁለቱ አንዱ የልብሱን ውበትና መልካም ሽታ እያደነቀ አስኪመልስልሽ ድረስ ርግባዊ ዓይንሽ የበጉ ልጅሽን ራቁትነት አይቶ እንባን ያፈስ ነበር" በማለት ተቀኝቷል።

ድንግል ሆይ! በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በስደት ወቅት የነበረውን የእናትና ልጅ ሁኔታ ሲገልጠው እንዲህ ይላል:—"ሐዊረ ፍኖት በእግሩ ሶበ ይስእን ሕፃንኪ፣
ያንቀዓዱ ኀቤኪ ወይበኪ እኂዞ ጽንፈ ልብስኪ እስከ ትፀውሪዮ በገቦኪ ወትስእሚዮ በአፉኪ"
(ልጅሽ በእግሩ መሄድ በደከመው ጊዜ ወዳንቺ ቀና ብሎ የልብስሽን ጫፍ ይዞ ያለቅሳል፣ እቅፍ አድርገሽ እስከምትስሚው ድረስ።)

☞ግሩም ነው!!! አምላኳን ፈጣሪዋን በእናትነት ልሳን ያወራች፣ የልጅነት ጥያቄውን ብቃት ባለው እናትነት የመለሰች፣እንደ ሕፃናት መኮላተፉን የተረዳች፣ እንደ አምለክነቱ የሚያደርገውን ደግሞ በልቧ ጨምራ ችላው የምትኖር እናት!

☞☞☞ይህም የእናትና የልጅ ቋንቋ የሰው ልጆች የመዳን ቋንቋ ነው፣ የሚያውቁትም ጌታና እመቤታችን ብቻ ናቸው። ክርስቶስ በዚህ መንገድ አልፎ ፣ በእቅፏና በጀርባዋ በስደትና በመከራ ተጋግሮና ተጠምቆ ፣ በመስቀል መሶብ፣በመስቀል ጽዋ ምግብና መጠጥ ሆኖ ለዓለም ተሰጥቷል!

☞☞☞ሞኞች የሆኑ ሰዎች ለጌታ ለእግዚአብሔር ወልድ እናት ሆነችው እያልናቸው ለእኛ እናት ሆነችን ስንል አልዋጥ አላቸው! የትኛው ይከብዳል??? የአምላክ እናት መሆን? ወይስ የእኛ እናት አማላጅ መሆን?

ለእኛ ግን እናታችን ናት!

በረከቷ ረድኤቷ፣ልጇ የሚቀበለው አማላጅነቷ፣በስደትና በመስቀል ሥር የፈሰሰው እንባዋ
• ሀገራችንን ይጠብቅልን፣
• ቤተ ክርስቲያናችንን ይታደግልን፣
• እኛንም በተዋሕዶ ሃይማኖት ያጽናን!!!
❖❖❖ድንግል ሆይ! በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!

አሜን!!!

መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው
ዘመካኒሳ ሚካኤል
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
እንኳን ለዘመነ ጽጌ በሰላም አደረሳችሁ !
Audio
ምን እንደምመርጥ አላውቅም 
                                                  
Size:- 17.8MB
Length:-51:06
       
     በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
- የሕይወት ዛፍ -

|ጃንደረባው ሚዲያ | መስከረም 2016 ዓ.ም.|
✍🏽 ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

እግዚአብሔር በምድር ላይ ለማየት ደስ የሚያሰኙ፣ ለመብላት መልካም የሆኑ ዛፎችን ማብቀሉን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ ከእነዚህ ዛፎች መካከል አንዱ የሕይወት ዛፍ ነው። ዘፍ 2፥9 ገነትን የሚያጠጡ አራቱ አፍላጋት ኤፌሶን፣ ግዮን፣ ጤግሮስ፣ ኤፍራጥስ የሚመነጩት ከዚህ የሕይወት ዛፍ ሥር ነው። ስለዚህ የሕይወት ዛፍ በነገረ ክርስቶስ ያለውን ጥልቅ አስተምህሮ በሌላ ጊዜ የምናነሣው ሆኖ ለዛሬ ግን ልነግራችሁ የወደድሁት በሰዎች መካከል ስለሚገኘው የሕይወት ዛፍ ነው።

ለቅድስና ራሳቸውን የሚያተጉ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ገነት ከመወሰዳቸው በፊት ልቡናቸው ተድላ ደስታ የሚፈስባትን ገነት ትሆናለች። አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለው ሊቅ “ልቡሰ ለባህታዊ ገነተ ተድላ ይዕቲ፤ የባህታዊ ልቡ ተድላ ደስታ የሚገኝባት ገነት ናት” ብሎ የተናገረውም ስለዚህ ነው። የጻድቅ ሰው ልቡ ገነት፣ አንደበቱም የሕይወት ዛፍ ናት። የማስተዋል መንፈስ የተሰጠው ሰው ሰሎሞን በገነት መካከል ስላለው ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ስላለው የሕይወት ዛፍ እንዲህ ሲል ይናገራል። “መፈውስ ልሳን ዕፀ ሕይወት ውእቱ፤ ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት” ምሳ 15፥4 ይላል።
ዛሬ በገነት መካከል ካለው የሕይወት ዛፍ ይልቅ የሚያስፈልገን ሰሎሞን የተናገረለት የሕይወት ዛፍ ነው። ያኛውማ ከዚህ በኋላ እንዳንፈልገው በክርስቶስ ተተክቷል። ፍሬውን በልተነው የዘለዓለም ሕይወትን የምናገኝበት እውነተኛው የሕይወት ዛፍ ሁልጊዜ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የተሳለው ክርስቶስ ነው። እሁን ለምድራችን ምን ያስፈልጋታል ካላችሁኝ ልቡ ገነት፣ አንደበቱም የሕይወት ዛፍ የሆነችለት ሰው ነው። አራቱ አፍላጋት የተባሉት አራቱ ወንጌላውያን ዙረው የሚያጠጡት ልቡ ገነት የሆነችለት አንደበቱም የሕይወትን ዛፍ የምትመስልለት ይህ ሰው ዛሬ ከወዴት ይገኛል?
ተፈጥሯችንን በእግዚአብሔር ቃል ብንጠብቀው እንዴት ያለ ድንቅ ስጦታ መሰላችሁ? ክርስትና ገነትን በመሻት ተጀምሮ ገነትን ወደ መሆን ማደግ የሚያስችል ሕይወት ነው። ፈውስን የሚሻ ሰው ፈዋሽ የሚሆንባት፣ ምድራዊው ሰው ሰማያዊ ምሥጢር የሚያይባት፣ ደካማው ሰው ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ ሁሉን የሚችልባት ድንቅ ሕይወት ናት ክርስትና። ቅዱስ ጳውሎስ ለራሱ ፈውስን የሚሻ ድውየ ሥጋ ነው 2ቆሮ 12፥7 ለሌሎቹ ግን በሄደበት ቦታ ሁሉ ፈውስን የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸው ተናግረው በእጃቸው ዳሰው ከዚያም አልፎ በልብሳቸውና በጥላቸው የፈወሷቸው ድውያን ብዙ ናቸው። ከዚያ ይልቅ በአንደበታቸው የፈወሷቸው ምዕመናን ይበዛሉ። ዓለምን ዙረው ካስተማሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ትምህርታቸውን የስሙ ሁሉ ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይደርሳሉ።

መልካሙን የምሥራች የሚናገሩ እውነተኛውን ቃል የሚያወሩ አንደበቶች ሁሉ ዛሬ በምድራችን ላይ የበቀሉ የሕይወት ዛፎች ናቸው። ልቡን ከኃጢአት የሚጠብቃት ሰው ለአዳም የተሰጠችውን ገነትን ያደርጋታል። አንደበቱንም ሀሰትን ከመናገር የሚከለክላት የሕይወትን ዛፍ ያስመስላታል። ለሚሰሟት ሁሉ ፈውስን የምትሰጥ እንደዚህ ያለች አንደበት እንድትኖረን ሀሰትና ቁጣን፣ ፌዝና ቧልትን የመሳሰሉ ነገሮችን ሁሉ ከቶውኑ ወደ አፋችን ማስገባት አይገባንም። ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ” መዝ 141፥3 ብሎ የጸለየው እንዳገኙ መናገር አንደበትን የሚያረክስ ስለሆነ ነው። እንዳገኙ መናገር እንዳገኙ ከመብላትና ከመጠጣት ይልቅ ሰውን የሚጎዳ ልማድ ነው።
ከአንደበታችን በሚወጣው ነገር እግዚአብሔር ሌሎችን የሚፈውስበት ከሆነ አንደበታችንን መጠበቅ ይገባናል ማለት ነው።

አንተ ሰው! እግዚአብሔር ገነትን ባንተ በኩል ሊገልጣት ይፈልጋል፤ አንደበትህም ለብዙዎች ፈውስ ትሆን ዘንድ የሕይወት ዛፍ ሊያደርጋት ይቻለዋል። ራስህን አዘጋጅ እግዚአብሔር ባንተ ልሳን ሊፈውሳቸው የተዘጋጁ ሕሙማን በዙሪያህ መሰብሰባቸውን አትርሳ። እንደዚያ የመቄዶንያ ሰው እርዳታህን ፈልገው የሚጠባበቁ ሰዎች መኖራቸውን አስብ ሥራ 16፥9 አንዲት የሰማርያ ሴት በተናገረችው ነገር ብዙዎች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን በመጽሐፍ ተመልከት ዮሐ 4፥39 የተናገረችው ብዙ አይደለም እሷ ስለክርስቶስ ብዙ ትናገር ዘንድ ጴጥሮስን ወይም ጳውሎስን አላደረጋትማ! ቃሉን በሙላት እንደሚናገሩ ሐዋርያት የማስተማር ጸጋን አልሰጣትማ! “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብቻ ነው ያለቻቸው። ነገር ግ ን ብዙ ሣምራውያን በክርስቶስ አመኑ። ከሁሉ ይልቅ የሚገርመው ትምህርትና ተአምራት ከጀመረባት ከገሊላ ሰዎች በልጠው በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር መለመናቸው ነው።

የሕይወት ዛፍ የሆነች ምላስ ማለት ይህች አይደለቸምን? ብዙዎችን ከሞት ወደ ሕይወት ያሻገረች። አንደበታቸው የሕይወት ዛፍ የሆነችላቸው ሰዎች ብዙ ተናግረው ሳይሆን አንድ ቃልም ቢናገሩ በቂ ነው። የሕይወት ዛፍ የሚያፈራው ፍሬ አንዱ በቂ ነውና። ብዙ መናገር ባትችልም የተናገርሃት አንዷ ቃል ትፈውሳለች ። አከናውነህ መናገር ባይሆንልህም እንደምንም ብለህ ከአንደበትህ ያወጣሃት ቃል እሷ መድኃኒት ትሆናለች ሙሴ ዲዳና ምላሰ ጸያፍ እንደነበረ አስብ እንጅ። አሮን ደግሞ ደኅና አድርጎ እንደሚናገርም አትርሳ ነገር ግን እስራኤልን ለሞት የሰጣቸው የሙሴ ቃል ሳይሆን የአሮን ነው ዘፀ 32፥2

“ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት” ለሰዎች ፈውስ የማይሆን ቃል አትናገር፤ አንደበትህ የሕይወት ዛፍ ትሆንልህ ዘንድ አስቀድመህ ልብህን እንደ ገነት በእግዚአብሔር ቃል የለመለመች መልካም ሥፍራ አድርጋ፤ የሕይወት ዛፍ ከገነት ውጭ በሌላ ሥፍራ አትገኝምና። ከዚህ የሚበልጥ ጸጋ ከወዴት ታገኛለህ? በምድር ሳለህ ልብህን ገነት አንደበትህን የሕይወት ዛፍ ካደረገልህ ሌላ ምን ትሻለህ?

ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::

የሕይወት-ዛፍ
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
"ሰማዕትነት ስር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚኽ ስር የሚያቆጠቁጡ ምርጥ ዘሮች ናቸው፡፡ ብዙ ዛፍ የሚያቆጠቁጥበት ስር በለም አፈር ስለሚሸፈን አይታይም፡፡ ከዚያ በሚያቆጠቁጡ ዛፎች ግን ስሩ እንዴት እንደተመቸው ይታወቃል፡፡ ሰማዕታትም በግዙፉ ዓይናችን እንደምን ያለ አክሊል ሽልማት እንደተቀበሉ አይታየንም፡፡ ፍሬያቸው ግን እነርሱን መስለው እነርሱን አኽለው በሚጋደሉ ምርጥ ዘሮች ይታወቃል፡፡

ሰማዕታት አክብሩን ብለው አይናገሩም፡፡ ነገር ግን በክርስቲያኖች ልብ የሚዘሩት ፍሬ ምእመናንን በፍቅር ያስገድዳል፡፡ እነርሱን እንዲመስሉ ያሳስባል፡፡

ሰማዕታት እንደ ፍቅረኛ ናቸው፡፡ አንድ ሰው የፍቅረኛውን ስም በየአጋጣሚው ያነሣል፡፡ በዓይነ ሕሊናው ያስባል፡፡ በተለያየ መልኩ ያያል፡፡ ሰማዕታትም ለክርስቲያኖች እንደዚያ ናቸው፡፡ እጅግ የተወደዱና በፍጹም ከሕሊና የማይጠፉ ተወዳጆች ናቸው፡፡ የልጆቻችንን ስም በነርሱ ስም የምንሰይመው፣ ሥዕላቸውን ሥለን የምንተሻሸው የምንስመው ለሰማዕታቱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር የምንገልጽበት መንገድ ስለኾነ ነው፡፡"

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ በረከት አይለየን!
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/09/22 20:19:26
Back to Top
HTML Embed Code: