Telegram Web Link
#ጉባኤ_ሐዲስ_ኪዳን
(ለማስታወስ) 👇
ማቴ 8፥26-ፍጻሜ (የመጨረሻው ክፍል) 👇

#የእምነ_መጉደልና_ፍርሃት

"እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ" ማቴ 8 ፥ 26።

• ፍርሃት በሁለት ይከፈላል ፤ 1ኛ የተፈጥሮ ፍርሃት ሲሆን 2ኛ የእምነት ማነስ ነው
• የእምነት መጉደል ፍርሃትን ያመጣል
• ሐዋርያት ገና ፍጹማን አለመሆናቸውን ያሳያል
• እንደሚያድናቸው ቢያምኑም ከተኛ ግን እንደማያድናቸው ማሰባቸው ስህተት ነበር
• ስለዚህም ከማዕበለ ባህር አስቀድሞ የሐዋርያትን ልብ ባህር ሞገደ ፍርሃት ገሠጸ
• ከዚያም ማዕበለ ሞገዱን ጸጥ አደረገ ፤ በዚህ ወቅት ጸጥ ያለው በዓለማት ያሉ አብሕርት ውቅያኖሰ ማዕበል ሞገድ ነበር
• ለአበው ለነቢያት….ለሐዋርያት ለጸሎታቸው መልስ ሰጠ
• በዚህ ቃል የሰማዕታትን በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ፍርሃት ማስወገዱን እናምናለን
• ወአውየዉ ኀበ እግዚአብሔር ሶበ ተመንደቡ
• ወአድኀኖሙ እምንዳቤሆሙ
• አጥፍኣ ለአውሎ ወአርመመ ባሕር
• ወአርመመ ማዕበል
• ወተፈሥሑ እስመ አእረፉ
• ወመርሖሙ ውስተ መርሶ ኀበ ፈቀዱ… መዝ 106፤28-31
#ተደነቁ!

• ይህ ቃል በማቴዎስ ወንጌል ስድስት ጊዜ ያህል ተመዝግቧል፤ ማቴ 8፡27፤ 9፡8፤9፡33፤15፡31፤21፡20፡22፡22
• በአብዛኛው የተደነቁት በተአምራቱ ነበር

• ባህርና ነፋሳት የሚታዘዙለት ይህ ማነው ብለው ተደነቁ
• ተአምራቱ ከሙሴ ከኢያሱ ከኤልሳዕ ልዩ ነውና ይህ ማነው ብለው ተደነቁ
• ሙሴ በበትር፤ ኢያሱ በታቦት ፤ ኤልሳዕ በኤልያስ መጎናጸፊያ ነበር ባህር የከፈሉት፤ ጌታ ግን በቃል ብቻ !

• ይህ ማነው ብለው የተደነቁበትን ቃል ማቴ 16፡13 ላይ በክፍሉ እንመለከተዋለን
ማቴ 8፡28-ፍጻሜ (ንባብ)
• ወደ ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር በመጣ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤እነሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ

• እነሆም ኢየሱስ ሆይ! የእግዚአብሔር ልጅ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሳቀየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ
"ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር
አጋንንቱም ታወጣንስ እንደሆንህ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት፤ ሂዱ አላቸው
እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባህር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ
እረኞቹም ሸሹ ወደ ከተማዪቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ ፤ አጋንንትም ባደሩባቸው የሆነውን አወሩ
እነሆም ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ ፤ ባዩትም ጊዜ ከሀገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት "

#ጌርጌሴኖን

• ጌርጌሴኖን የአጋንንት ሰፈር/መንደር ነው

• የሙታን ነፍስ በሕያው አድራ የዘመዶቿን ጠላት ታጠፋለች የሚል ባህል ስለነበር ጠላቶቻቸውን ለማጥፋት ልጆቻቸውን የገደሉ ያረዱ ነበሩ፤ በዚህ ምክንያት አጋንንት ያንን ደም እየጠጡ ይኖሩ ነበር

ምሳሌነቱም ፡-
• የዚህ ዓለም(ምድረ ደይን/ፍዳ)
• የመቃብር
• የሲኦል ምሳሌ ነው ብለን ነበር

#አጋንንት_ያደሩባቸው_ሁለቱ_ሰዎች

• ጋኔን ማለት እሩቅ ውዱቅ ፤ ከማዕርጉ የወደቀ ከክብሩ የራቀ፤የተራቆተ ማለት ነው፤ አጋንንት ለብዙ ነው
• ጋኔን የሚለውን ቃል ለሰይጣንና ለማደሪያው እንጠቀምበታለን ፤ ሰው የሰይጣን መኖሪያ ሲሆን ጋኔን ተብሎ ይጠራል
• ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት አሉ እንደ ሰው ሥጋ የለበሱ በሥጋዊ ጥበብ የሚሠወሩ የሰይጣን ወዳጆች የሆኑ አሉ፤ በዋናነት እነሱ አጋንንት ይባላሉ
• በዚህ ዓውድ አጋንንት ያደሩባቸው ማለት መናፍስት ርኩሳን ያደሩባቸው ለማለት ነው፤ በመሳሪያዎቻቸው አጋንንት ብሎ ጠርቷቸዋል
• ርኩሳን መናፍስት ለሥነ ልቡናችን ቅርብ በመሆናቸው እውነቱን ሐሰት ሐሰቱን እውነት በማስመሰል የሚፈትኑን የሚያስቱን ናቸው፡፡
• አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች የአዳምና የሔዋን ምሳሌዎች ናቸው
• አጋንንት ያደሩባቸው ሁለቱ ሰዎች የኔፊሊም ምሳሌዎች ናቸው

• ባህር ገብተው መሞታቸው በማየ አይኅ መጥፋታቸውን ያሳያል
• እሪያዎቹ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ምሳሌ …አብረው ጠፍተዋልና

• ሁለቱ ሰዎች የፈርዖንና የሄሮድስ ምሳሌ

• እሪያዎቹ የግብፃውያን እንዲሁም የእኩያን እስራኤላውያን ምሳሌ…በባህር/በመከራ ሰጥመው ሞተዋልና

• አጋንንት በቁሙ እሪያዎቹ የኢአማንያን ምሳሌ

ጌታ ሆይ ሀገራችንን አስባት!
እኛን አትይ! ስለ ወዳጆችህ ፊት ብለህ ማረን!
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
ኢሬቻ/ዋቄፈና/ ለክርስቲያን ምኑ ነው?
(በዲ/ን ሕሊና በለጠ)

ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ የአንድ ማኅበረሰብን ባሕል ንቃም ኾነ ተቃውማ አታውቅም። በተቻላት መጠን ማኅበረሰቡ ከነ ባሕሉ ድኅነትን ያገኝ ዘንድ ሃይማኖቷንና ሥርዓቷን አስተምራ ታስተናግደዋለች እንጂ። ከእርሷ አምልኮ በተቃራኒው የሚያመልክ የአንድን ተገዳዳሪ የእምነት ተቋም አምልኮም በማይገባ መልኩ ተችታና አኮስሳ አታውቅም፤ እውነተኛውን መንገድ ግን በተገቢው መልኩ በጥብዓት ታስተምራለች። የዚያ የእምነት ተቋም አምልኮና እምነት ስሕተት ከኾነ ሰዎች ኹሉ ይድኑ ዘንድ እውነትን ትሰብካለች፤ ወደ እውነት ትመራለች፣ ታደርሳለች።

ኢሬቻ ምንድን ነው? ባሕል ነውን?

መልካም፣ ባሕልስ ከኾነ ቤተ ክርስቲያን የባሕሉን አክባሪ ባሕሉን ሳይዘነጋ ይቀበላት ዘንድ አይገዳትም። እርሷም ከነ ባሕሉ ዐቅፋና ደግፋ ትቀበለዋለች።

ግን ኢሬቻ ባሕል ነው?

አይመስለኝም። ሰሞንኛ ተናጋሪዎችን እንዘንጋቸውና እስኪ እንዴት እንደተከበረ እንመርምር። የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ውኃ ውስጥ ሣር እየነከሩ ወይም ዛፍን ቅቤ እየቀቡ ፈጣሪን ሲያመሰግኑ የሚያሳዩ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን ስናይ ነበር። ስለዚህ ይህ በዓል:-

#1ኛ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው (ይህም ተደጋግሞ በአክባሪዎቹ እየተነገረ ነው)። በፈጣሪ መኖር ማመን ደግሞ: ለሃይማኖት ህልውና የመጀመሪያው መስፈርት መኾኑን ልብ ይሏል። ስለዚህ ኢሬቻ/ዋቄፈና/ ለሃይማኖትነት ትልቁን መሥፈርት አሟልቷል ማለት እንችላለን።

#2ኛ የታወቀ የምስጋና (አምልኮ?) ሥርዓት (ለምሳሌ:- ሣር ውኃ ውስጥ መንከር፣ ቅቤ መቀባት ...) አለው። ይህም እስልምናም ኾነ ክርስትና የታወቀ የአምልኮ ሥርዓት እንዳላቸው ማለት ነው።

#3ኛ እስልምና መስጊድ፣ ክርስትናም ቤተ ክርስቲያን እንዳላቸው ኹሉ: ኢሬቻም /ዋቄፈናም/ ይህ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቦታ (Sacred Place, ለምሳሌ:- ውኃና ዛፍ ያለበት ሥፍራ) አሉት።

#4ኛ ሃይማኖታዊ የአምልኮ ሥርዓት በካህናት እንደሚመራ: ክብረ በዓሉን የሚመሩ የሥርዓት መሪዎች (አባ ገዳዎች?) አሉት።

ስለዚህ ወይ አምልኮ ነው፣ ወይም ደግሞ ከቆይታ ብዛት ወደ ባሕልነት የተቀየረ አምልኮ ነው።

#ዐቢይ_ነጥብ - ከላይ ከጠቀስናቸው ከዐራቱ ለጊዜው አንዱን ብቻ እንምረጥ -

-ፈጣሪ የሚመሰገንበት መኾኑ

ይህ ብቻ "ባሕል ነው" ለሚሉት ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያስገድድ ምክንያት ነው።

ፈጣሪን ማመስገን የሚቻለው በእምነት ነው። በመጀመሪያ ይህን ፈጣሪ ማመንና በጥቂቱም ቢኾን በእምነት ማወቅ ይገባል። ቢያንስ ፈጣሪ መኾኑን በእምነት መረዳት ያሻል። ከዚያም እርሱ በሚፈልገው ሥርዓት እርሱን ማመስገን/ማምለክ ይከተላል። እርሱን ማምለኪያ ውሱን ሥርዓት የለም ቢባል እንኳን: የማመስገኛ ሥርዓቱ "ሥርዓት የለሽ በመኾን" ይገለጻል፤ (non-religiousness is my religion) እንዲል አንድ የፍልስፍና መምህር /ፈላስፋ ላለማለት ነው/)።

ሙስሊሙ ፈጣሪን የሚያመሰግንበት ሥርዓትና ቦታ አለው፤ ሳምንታዊ(ጁምዓ) እና ዓመታዊ (ኢድ አል ፈጥር፣ ኢድ አልአድሃ) የበዓላት ዕለታትም አሉት። ክርስቲያኑም እንዲሁ ከሳምንታዊ ሰንበትን፣ ከዓመታዊ ልደትና ትንሣኤን የመሰሉ (ዕለታዊና ወርኃዊውን ጨምሮ) ብዙ በዓላት አሉት። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም በየበዓላቱና በየታወቀ ሥርዓቱ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፣ ያመልካሉ። ነገር ግን ክርስቲያኑ ኢሬቻ የሚል ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል በዚቁ (liturgical Calendar) ውስጥ የለም። ሙስሊሙም እንደዚያ።

ሌላው ነጥብ: ኹሉም እምነት ፈጣሪን የተመለከተ መሠረተ-ትምህርቱ (Doctrine/Creed) ከሞላ ጎደል ይለያያል። ሙስሊሙም (ካልተሳሳትኩ) "ላ ኢላህ ኢለላህ መሐመዱር ረሱለላህ" የሚል ሸሀዳ (Creed) አለው። ይህንን አዘውትሮ ያደርሳል። ፕሮቴስታንቱ "ክርስቶስ አማላጄ" (ሎቱ ስብሃት) ይላል። እኛ ኦርቶዶክሳውያን ደግሞ "ኹሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚኾን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን" ከሚለው ጀምሮ የክርስቶስንና የመንፈስ ቅዱስን አንድ የባሕርይ አምላክነትና ከአብ ጋር መተካከል፣ የቤተ ክርስቲያንን ኲላዊነት፣ አንድነት፣ ቅድስናና ሐዋርያዊነት፣ የጥምቀትን የኃጢአት ማስተሥሪያነት፣ የትንሣኤ ሙታንን ተስፋነት የምንመሠክርበት የዘወትር ጸሎተ ሃይማኖት (Creed) አለን።

እነዚህ እምነቶች ይለያያሉ ብቻም ሳይሆን ይቃረናሉ። እንዴት በአንድነት ምስጋናቸውን ለአምላክ ያደርሳሉ?

እኔ አምላክ የምለውን ክርስቶስን አንዱ ከአጠገቤ "አማላጄ" እያለው እንዴት አንድነት ይኖረኛል? አንዱስ "ነቢይ" እያለው እንዴት አብረን እናመሰግናለን? የኔን አምላክ አማላጅም ፣ ነቢይም ማለት እርሱን ማሳነስ ለእኔም ንቀት ነው።

ሙስሊሙም አላህን አምላክ ይላል። ኢሳን ነቢይ ይላል። እኔ ከጎኑ ቆሜ ኢየሱስ ክርስቶስን "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ስል እንዴት ይዋጥለታል?

አብረን ቡና የምንጠጣ፣ አብረን ኳስ የምንጫወት፣ በንግድ የምንተባበር ሙስሊሞችና ፕሮቴስታንቶች ይኖራሉ። በጣም የምንዋደድ ጓደኛሞችና የሥራ ባልደረቦች ልንሆን እንችላለን። ግን ለአምልኮ ሙስሊሙም መስጊድ፣ ፕሮቴስታንቱም "ቸርች" እኛም ቤተ ክርስቲያን እንሔዳለን እንጂ ፈጣሪን ለማመስገን መስጊድ ወይም ቤተ ክርስቲያን በአንድነት አንሔድም።

አንድ የምንኾንበትንና የማንኾንበትን እንለይ እንጂ! በኢትዮጵያዊነት አንድ ነን፤ በባሕል እንተባበራለን፤ በልማት አንድ መኾን እንችላለን፤ እንኳን በሀገር በቤተ ዘመድም በሃይማኖት መለያየት ይገጥመናል፤ ዝምድናን ጨምሮ ግን ብዙ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች አሉን። ኾኖም በሃይማኖት አንድ ካልኾንን ከእናቴም ጋር ለጸሎትና ለምስጋና አልቆምም።

እንኳን ከሙስሊምና ከፕሮቴስታንት ጋር ይቅርና በብሉይ ኪዳን በሃይማኖት አንድ ከነበርነው ከይሁዲውም ጋር ፈጣሪን ለማመስገን በአንድነት አንቆምም። የይሁዲው መሠረተ ሃይማኖት ( ሸማ፣ Creed) በእኛው ብሉይ ኪዳን ላይ ዘዳ.6÷4-9 ያለው ንባብ ነው። ይሁዲዎች ይህንን በእጃቸው ያሥሩታል (Teffilin)። በበራቸውም ይጽፉታል (Mezzuzah)። ንባቡ እኛም የምናምንበትና የምናነበው ነው። ነገር ግን ምንም ያኽል ብንወዳቸው ክርስቶስን ከማያምኑት ከይሁዲ እምነት (Judaism) ተከታዮች ጋር የሃይማኖት ኅብረት የለንም።

ወንጌላችንም ያዘናልና "ቢቻለንስ በእኛ በኩል ከሰው ኹሉ ጋር በሰላም መኖርና ሰላምን መከታተል" የክርስትና መርሐችን ነው። (ሮሜ 12÷18፣ ዕብ. 12÷14)። ኾኖም ፈጣሪን የምናመሰግንበት የሃይማኖት ኅብረት የሚኖረን ግን ከተጠመቁት ጋር ብቻ ነው።

#በተለይ_ለኦርቶዶክሳውያን

አምልኮ/ምስጋና/ ማለት ክርስቶስ ራስ ለኾነላት ቤተ ክርስቲያን ለተባለችው አንዲት አካል ብልት ለመኾን የምንጋደልበት ሰማያዊ ሥርዓት ነው። ኦርቶዶክሳውያን በአምልኮ ጊዜ እርስ በእርሳችን ብቻ ሳይኾን ከመላእክትም ጋር ረቂቅ አንድነት አለን። "በሰላም ማሠሪያ (ይህን) የመንፈስ አንድነት ለመጠበቅ እንድንተጋም" ታዘናል። (ኤፌ.4÷3)።

ወደዚህ ሰማያዊ ኅብረት ይመጡ ዘንድም ለዓለም ኹሉ እንደ ሐዋርያቱ እንጮኃለን፤ "ወደ ክርስቶስ ኅብረት በሃይማኖት ኑ" እንላለን። "እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው " እንዲል ሐዋርያው።
(1ኛ ዮሐ. 1÷3)።
ይህን በማድረግ ፈንታ ግን በማይመች አካሔድ ከማያምኑ ጋር መሰለፍ በሃይማኖታችን አይፈቀድም። ስለዚህ ማንም ኦርቶዶክሳዊ በሌላ ማኅበረሰባዊ ጉዳይ እንጂ በሃይማኖት ከማያምኑ ጋር ቢተባበር ራሱን ለካህን ያሳይ፣ በንስሐ ይመለስ።

ወንጌላችንም የሚለው የሚከተለውን ነው:-

"ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?" (2ኛ ቆሮ. 6÷14-15)።

እኔም እላለሁ - ኦርቶዶክሳዊ ከኢሬቻ/ዋቄፈና ጋር ምን ኅብረት አለው?

+ የኢሬቻና የኢኩሜኒዝም አካሔድ መመሳሰል - ሌላው ሥጋት?

የዓለማዊነት (Secularism) አቀንቃኞች ከፖለቲካ ዲሞክራሲን ፣ ከምጣኔ ሀብት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ፣ ከሃይማኖት ፕሮቴስታንቲዝምን ይመርጣሉ፣ ይደግፋሉ። እነዚህ ሦስቱም በዓለማዊነት አቀንቃኞች መደገፋቸው: ለአንድ ማኅበረሰብ በኹሉም መልክ ለዘብተኝነትን ( Liberalism) ስለሚያለማምዱ ነው። አንድ ማኅበረሰብእ ለዘብተኛ ከኾነ ደግሞ ቸልተኝነቱ ይጨምርና ኹሉን ችላ በማለት በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ለመዋል ምቹ ይኾናል። ስለዚህ ለዚህ አካሔድ ወግ አጥባቂ (Conservative) ኾነው የሚያስቸግሯቸው ኦርቶዶክሶች ኹሉ (Orthodox Christians, Orthodox Jews, Orthodox Muslims) ጥርስ ውስጥ የገቡ ናቸው። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመሰሉ በሥርዓትና በዜማ የደመቁ አብያተ ክርስቲያናትን ለዘብተኛ ለማድረግ በተሐድሶ እንቅስቃሴና በተለያዩ መንግሥታዊ ተጽዕኖዎችም ጭምር እንዲጎዱ ተደርጓል።

ለዚህ ለዓለማዊነት እንቅስቃሴ የተሸረበው ሌላው ሴራ ደግሞ (ምንም እንኳን ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም) የኢኩሜኒዝም (Ecumenism) እንቅስቃሴ ነው። ይህን እንቅስቃሴ በቅርቡ እነ ዶክተር ወዳጄነህን የመሳሰሉት እንደሚከተሉት በግልጽ አስረድተው ነበር። በዚሁ እንቅስቃሴ ስም የሚንቀሳቀሱት አንዳንዶች ታዲያ "ከኹሉም ሃይማኖት ጥሩ ጥሩውን ፣ የጋራውን እንውሰድ" በሚል መርሕ ሌላ ዓይነት ፕሮቴስታንቲዝምን ይዘውና ሃይማኖትን በልካቸው አበጅተው ብቅ ብለዋል። ይህንን የሚደግፉት በዋናነት ግላዊነትን የሚያበረታቱት ፕሮቴስታንቶችና ዓለማውያን ናቸው።

ኢሬቻም የዚሁ ኮፒ እየኾነ ነው። በኦሮሞ ፕሮቴስታንቶችና በፕሮቴስታንታዊው ኦዲፒ ከሞላ ጎደል ካለ ምንም ማንገራገር ይደገፋል። ኢኩሜኒዝም በክርስትና ስም የሚንቀሳቀሱትን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ ኢሬቻ/ዋቄፈና ደግሞ ሙስሊሙንም፣ ኦርቶዶክሱንም ፣ ፕሮቴስታንቱንም ማዕከል አድርጓል። ይህም በተለይ ኦርቶዶክሱን በኦሮሙማ ስም ከኦርቶዶክሳዊነት ለማለዘብ የተነደፈ ሴራ ይመስላል።

"ምን ችግር አለው?" የሚል ለዘብተኛ ኦርቶዶክስ ደግሞ በስም እንጂ በግብር የቤተ ክርስቲያን ሊኾን አይችልም። ስለዚህ በተለይ የኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ትልቅ አስተዋይነትን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ እንዳላችሁ ልትገነዘቡት ይገባል። ከኦርቶዶክሳዊነትና በተወዳጅ ባሕል ስም ከመጣ ሌላ እምነት መካከል ያላችሁ የምትወስኑበት ጊዜ እንደኾነ ይሰማኛል።

ኹለቱንም መኾን አይቻልም። ወይ ከጊዜ በኋላ በቅርቡ የሚበርደውን የወቅቱን ሞቅታ መምረጥ ወይም ደግሞ ካለችበት ከፍታ ላይ ሳትወርድ ለዘመናት የኖረችውን ተዋሕዶን መምረጥ ያሻል።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንንና ምዕመኖቿን፣ ሀገራችንንና ዜጎችን ይጠብቅልን። አሜን።
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
- የ“at least” ክርስትና -

|ጃንደረባው ሚዲያ - መስከረም 2016 ዓ.ም.|

✍🏽 ቀሲስ ታምራት ውቤ እንደጻፉት
(በእውነታ ላይ የተመሠረተ ምናባዊ ጽሑፍ)

በቅርብ በቅዱስ ጋብቻ አንድ ከሆኑ ጥንዶች ጋር ስለ ክርስትና ሕይወታቸው አባታችንን ለማወያየት ፈልገው በቤታቸው ተገናኘን፡፡ በውይይታችን ከተነሡት በርካታ ጉዳዮች የዘመኑን የክርስትና ሕይወት አጉልቶ የሚያሳዩ ሁለት ነጥቦችን እነሆ፡-

የመጀመሪያው ከእንግዶቹ የተነሣው ሐሳብ “ከአንዳንድ ወንድምና እኅቶች ጋር ስለ መንፈሳዊ ሕይወት ስንመካከር በክርስትና ሕይወት ስንኖር ‘at least’ እነዚህ የመሰሉ ነገሮችን ልንፈጽም እንደሚገባ ነግረውናል፡፡ እርስዎስ ምን ይመክሩናል?” በማለት አባታችንን በጠየቋቸው ጥያቄ ውይይታችንን ጀመርን፡፡

አባታችን በተቀመጡበት ትንሽ በዝምታ ከቆዩ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፡፡

“የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ የተገለጠባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በኅሊናዬ ለመዳሰስ ሞከርኩ፡፡ እናም ላገኘው ያልቻልኩት ነገር ቢኖር ‘ቢያንስ (at least)’ በሚል ቀዳሚ ቅጽል የተቀመጠን ትእዛዝ ነው፡፡ መንግሥተ እግዚአብሔርን ለመውረስ የተቀመጠ ‘አነስተኛ መሥፈርት (minimum requirement)’ ምን እንደሆነ ማወቅ ብችል ብዬ አሁንም ለማሰብ ሞከርኩ፤ ግን አሁንም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡” አሉን ትክዝ ባለ ድምፅ፡፡

“ምክንያቱም…” ሲሉ ቀጠሉ “ምክንያቱም ያ መሥፈርት መንግሥቱን ለመውረስ ካበቃ ‘ዝቅተኛ መሥፈርት’ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በተለምዶ አንዳንድ መምህራነ ወንጌል ‘ክርስቲያኖች ከሆንን ቢያንስ (at least) ይህን ልንፈጽም ይገባናል’ እያልን ስለምናስተምር፣ የነፍስ አባቶችም ልጆቻችንን ስንመክር ‘ልጆቼ ቢያንስ ይህንና ይህን ለማድረግ ሞክሩ’ ስለምንል ምእመኑን የ‘ቢያንስ (at least)’ ክርስትና ውስጥ አመቻቸነው፡፡ ምእመኑም ለሚበልጠው ጸጋ ከሚተጋ ይልቅ ‘at least’ ይህን ይህን እየፈጸምኩ ነው በማለት ለራሱ የጽድቅ መሥፈርት አስቀምጦ ተዘናጋ፡፡ ከእነቅዱስ ጳውሎስ የተማርነው ግን “ … እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፡፡ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፡፡” የሚል ነው፡፡ (ፊልጵ. 3÷13)

በመጽሐፍ ቅዱስ ‘አድርግ አታድርግ፤ ሁን አትሁን’ እንጂ፤ ‘at least’ ይህን አድርግ ይህን አታድርግ፤ ‘at least’ ይህን ሁን ይህን አትሁን’ የሚል የለም፡፡ወጥመድ የማይመስሉ የክፉውን ማዘናጊያና የምኞታችንን ማባበያ ትተን “ንቁ! በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ” (1ኛቆሮ. 16÷13) የሚሉትን የአባቶቻችን የሐዋርያትን ምክር መስማት ካልቻልን ሊውጠን ፈልጎ በዙሪያችን ለሚያገሳው አንበሳ ጥሩ ታዳኝ እንሆናለን፡፡

ለአባታችን ያነሣነው ሁለተኛው ነጥብ ዓለም ዛሬ የሚቀበለው ማስረጃ የሚቀርብበትን ጉዳይ ስለሆነ ይህን አካሄድ ከእምነት ጋር ማስማማት የሚቻልበት ምን መንገድ ሊኖር እንደሚችል ነበር፡፡ ከልምዴ እንደማውቀው አዲስ ነገር ሊነግሩን ሲሉ እንደሚያደርጉት ፈገግታ የተቀላቀለው ረዥም ትንፋሽ አወጡና “በየጊዜው የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰማት በቆምኩባቸው ጉባኤዎች ሁሉ እየታዘብኩ የመጣሁት ምእመናኑ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ‘ማስረጃ’ እንዲቀርብ ያለው ፍላጎትና መምህራንም ምእመኑን በማስረጃ እያበለጸግን በእምነት ግን እያደኸየን መምጣታችንን ነው፡፡ ይህ በሊቃውንት (በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ ብቻ ማለቴ አይደለም) ዘንድ ‘ቶማሳዊነት’ ይባላል፡፡ ‘ጌታ ተነሥቷል ሲባል ጣቴን በችንካሩ ካላገባሁ፤ በእጆቼም የተወጋ ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም’ ማለት ነው፤ ለሁሉ ማስረጃ ፍለጋ! ጌታችን ለዚህ መልስ ሲሰጥ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ነው ያለው፡፡ (ዮሐ. 20)

እምነትና ማስረጃ ፍጹም የተለያዩ መንገዶች ናቸው፡፡ እምነት የማስረጃ ጥገኛ አይደለም፡፡ በራሱ ጸንቶ የቆመና ጸንቶ ለማቆምም መሠረት መሆን የሚችል ነው፡፡ በክርስትና ለሁሉ ነገር ማስረጃ ከፈለግን ከማመን ይልቅ ለመካድ ቅርብ እንሆናለን፡፡ መምህራንም ያሳመንን እየመሰለን በማስረጃ ጋጋታ ከእምነት ምእመኑን እያራቆትነው ነው፡፡(ይህ ሲባል እንደው ጠቅሎ ማስረጃ አያስፈልግም ለማለት አይደለም፤ የማስረጃ ጥገኝነታችን ልኩን እያለፈ መምጣቱ ለእምነት የሚፈጥረውን እንቅፋት ለማመልከት እንጂ፡፡ ለሚያምን “ጸሎተ ሃይማኖት በቂው ነው” እንዲሉ አበው፡፡) ማስረጃ አንድን ነገር እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ያሳውቀናል፡፡ ማስረጃ ከዕውቀት ጋር እንጂ ከእምነት ጋር ባሕርያዊ መስመር አያገናኛቸውም፡፡ በክርስትና በእምነት እንጂ በማስረጃ ምንም ያህል ርቀት እንደማንሄድ ብዙ ማስረጃ ማምጣት ይቻላል፡፡ ግን ከዘረዘርኩ አሁንም ማስረጃ ላቀርብ ነውና በሐሳቤ ተቃርኖ ላይ ልቆም ነው፡፡ ስለዚህ እመን!!!

ይህ በሽታ ሲጀምር አንድ ቃለ እግዚአብሔር በተነገረ ቁጥር ‘ምን ላይ ተጽፏል?’ በማለት ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት በሚያስተምረን መምህር ላይ እምነት የለንም ማለት ነው፡፡ ግን እኮ መምህሩ ለጠቀሰው ጥቅስ እንጂ ለሰጠው ማብራሪያና ትንታኔ፣ ላመጣው ትርጓሜና ላመሠጠረው ምሥጢር ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ወይስ ጥቅሱን ማሳየቱ ብቻውን ያቀረበውን ትንታኔና የተረጎመውን ትርጓሜ ትክክል ያደርገዋል? ያለው አማራጭ አንድ ነው፡፡ መምህሩን ካመንከው አዳምጠው ካላመንከው አታዳምጠው፡፡ (የኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ዋና መለያ “understanding scriptures through the eyes of the fathers” - መጻሕፍትን በአበው የትርጓሜ ቅኝት መረዳት የሚል ነው፡፡ አበው ብለን የምንቀበላቸውም ከሐዋርያት ለጥቀው የተነሱ በይበልጥ “በሃይማኖተ አበው” ደገኛ እምነታቸው የተመሰከረላቸውን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና እነርሱን የመሰሉትን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን መምህር ለመለየት የአበውን መንገድና ትምህርተ ሃይማኖትን የሚገልጡበትን የአነጋገር ዘይቤ የሚጠቀሟቸውንም ቃላት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለአምልኮ መሥዋዕት የሚቀርቡ ከአትክልትም፣ ከአዝርዕትም፣ ከዕፅዋትም እንዳለ ሁሉ ለነገረ መለኮት ማመሥጠሪያ የተመረጡ ቃላትና የአነጋገር ዘይቤም አለ፡፡ እውነተኛ መምህር በኑሮው ብቻ ሳይሆን በንግግር ፍሬውም ይታወቃል፡፡)

በሽታው እያደገ ሲሄድ ምሥጢራትንና በምሥጢራት የምናገኘውን ጸጋ መጠራጠር እንጀምራለን፡፡ ይህም ‘እምነት አልቦ ክርስቲያኖች’ የምንሆንበት ደረጃ ነው፡፡ የሚታይብንም በልማድ የምንፈጽመው ሥርዓት እንጂ በመንፈስ በእውነትና በእምነት የሆነ አምልኮ አይደለም፡፡ የሥርዓት ክርስቲያኖች(Canonical Christians) እንጂ መንፈሳዊ ክርስቲያኖች (Spiritual Christians) ለመሆን እንቸገራለን፡፡ ፍጻሜውም የጸጋው ባለቤት የሆነውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን መጠራጠርን ያመጣል፡፡

ዛሬ በቤተክርስቲያን ለምናየው ፍሬ ሃይማኖትና መዓዛ ምግባር መታጣት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ አገልጋዩና ምእመኑ አይተማመኑም፡፡ (አገልጋዩ ከምእመኑ በትምህርተ ሃይማኖት የተሻለ ሆኖ ካልተገኘ፤ ለምእመናን ጥያቄ መልስ ለመስጠት ለሕይወታቸውም አቅጣጫ ለማሳየት የማይበቃ ከሆነ በሹመቱ እንጂ በትምህርቱ ቁጥሩ ከምዕመናን ይሆናል፡፡ “እልል በሉ” ንማ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ሁለተኛው በእምነት፣ በምግባርና በትሩፋት ከእነርሱ ተሽሎ ካልተገኘ ተግሣጹን ይንቁታል ምክሩን ያቃልሉታል፡፡ በመሆኑም ደግ የሃይማኖት መምህር በትምህርቱም በሕይወቱም ላቅ ብሎ መታየት ይኖርበታል፡፡) ስለዚህ የምንማረውም ሆነ
የምናስተምረው ወደ ክህደት ለመድረስ ነው፡፡ ሳናውቀው!!!”

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው::
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
- ትዳር ውል አይደለም -

| ጃንደረባው ሚዲያ | መስከረም 2016 ዓ.ም.|
✍🏽 ዲያቆን አርክቴክት አንተነህ ጌትነት እንደጻፉት

"ትዳር ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ቀላል የሚመስል ነገር ግን ለመመለስ ከባድ የሆነ ጥያቄ ነው። አንዳንዱ ሰው "የማኅበረሰብ ደህንነት የሚጠበቅበት ተቋም ነው" ሲል፣ ሌላው ደግሞ "ወንድና ሴት በአንድ ጣሪያ ለመኖር የሚያደርጉት ስምምነት ነው" የሚል አለ:: እልፍ ሲልም "ወንድና ሴት የፍቅር ሕይወትን በዘላቂነት ለመኖር የሚያደርጉት ውሳኔ ነው" የሚልም ይገኛል። በጥልቀት ቢመረመር ደግሞ ብዙ ምልከታዎች ይገኛሉ።

ነገር ግን ሁሉም ምልከታዎች የሚጋሩት አንድ ፅንሰ አሳብ አለ:: እርሱም "ትዳር ማለት ስምምነትና ውል ነው" የሚለው ነው። ትዳር በብዙዎች ዘንድ ሴትና ወንድ አንድ ላይ ለመኖር የሚያደርጉት ውል ስምምነት ነው። ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትዳር ውል አልያም ስምምነት ሳይሆን ኪዳን ነው።

ኪዳን የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገባው ውል፣ ስምምነት ነው። ውል፣ ስምምነት በምድር ለምድር የሚደረጉ ናቸው። ስለዚህም የጽሑፍ ሰነድ እና የቅጣት አንቀጾች አሉት። የጽሑፍ ሰነዱም ሆነ የቅጣት አንቀጾቹም ጠባያቸው ምድራዊ ነው። ኪዳን ግን ከእግዚአብሔር ጋር ፍቅርን ብቻ መሰረት ያደረገ፣ ለዘለዓለም የፍቅር ሕይወት የሚደረግ መለኮታዊ ጠባይን የተጎናጸፈ ውል፣ ስምምነት ነው።

ሰለዚህ ትዳር ወንድና ሴት ከእራሳቸውና ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅሩ ለዘለዓለም ለመኖር በእግዚአብሔር ፊት የሚገቡት ኪዳን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ለዘለዓለም በፍቅር ለመኖር የሚገቡት ውል ስምምነት ስለሆነ ትዳር ኪዳን እንጂ ውል፣ ስምምነት የሚሉት ሊገልጡት የማይቻላቸው ነው። ለዚህም ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ደረጃ ብሉይ ኪዳን፣ ሐዲስ ኪዳን ተብሎ የምናነብ፤ ምክንያቱም ውል፣ ስምምነት የሚለው ትርጉም ኪዳን የሚለውን በምልዓት መግለጥ ስለማይችል ነው።

ውል፣ ስምምነት ለዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረጉ ሲሆኑ ክብራቸው ወደ ኪዳን ያድጋል።
ኪዳን እግዚአብሔርን በትዳር ውስጥ ድርሻ የሚሠጥ ጽንሰ አሳብ ነው። እግዚአብሔር በትዳር ውስጥ ሲኖር የሰው ልጅ በትዳር የሚኖርበት ፍቅር ስሜትን የሚበልጥ እና ትርጉም ያለው ያደርገዋል። ስሜት ተለዋዋጭ እና ጊዜያዊ ነው፤ እንዲሁም ኑባሬን የተደገፈ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ከሌለ ሴት ለወንድ፣ ወንድ ለሴት ልጅ ከትዳር አንጻር የሚኖረው ስሜት (በተለምዶ ፍቅር የምንለው) ወደ ትክክለኛው ፍቅር ማደግ አይችልም። ከእግዚአብሔር በተለየ አኗኗር የሚኖሩትን ብዙዎችን በአንድ ጣራ ውስጥ አስማምቷቸው በትዳር የሚያኖረው ፍቅር ሳይሆን በፍቅር ስሜት የጀመሩትን ግኑኙነት በእውቀት እና በማኅበረሰባዊ እሴቶች ደግፈው በመያዝ ነው።

ዛሬ ዛሬ ላይ የእውቀት ክፍተት እና የማኅበራዊ እሴቶች መላላት ሲመጣ የፍች ቁጥር በከፍተኛው ጨምሯል፤ ስምምነት አልባ ትዳርም ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው። እግዚአብሔር በሌለበት የሚመሠረት ትዳር እና ሕይወት የሕይወት ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም ስለሚያንሰው ትርጉም ያለው ሕይወት ለማምጣት ይቸገራል።

ለምንድን ነው የማገባው፣ ለምንድን ነው ልጆች ወልጄ የማሳድገው ለሚሉት እና መሰል ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መስጠት በማያስችል ሁናቴ ወደ ትዳር መግባት ፊደል ለቆጠረ ሰው እጅግ አስቸጋሪ ነው። የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉንም ፈተናዎች አሸንፎ በፍቅር ለመኖር አመክንዮው ከዚህ ዓለም ከፍ ያለ መሆን አለበት። ስለዚህም ትዳሩን ከዚህ ዓለም አውጥቶ ከእግዚአብሔር ጋር በኪዳን የሚመሰርት ሰው የዚህን ዓለም የአሳብ ውጣ ውረድ አልፎ ፍቅርን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ትዳሩን በፍቅር የመምራት እድሉ በእጁ ላይ ይሆንለታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ፍቅር ብቻ ያይደለ የፍቅር መገኛም ነው። ፍቅርን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ያለ እግዚአብሔር ፍቅርን ለማግኘት መድከም ጉምን እንደ መጨበጥ፣ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው።

✍🏽 የትዳር ትርጉም
የትዳርን ሕይወት መተርጎም የሚያስፈልገው እንደ ሌሎች እውቀቶች ትዳርም በእውቀት ደረጃ በተገቢው መንገድ ይታወቅ ዘንድ ነው። ትዳር በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች በተገቢው መንገድ ትርጉሙን ይዞ የማናገኘው ተቋም ነው። ትርጉሙ ዓለሙ እንዳለበት ተጨባጭ ሁናቴ እና ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ የተለያየ ነው። ተገቢውን ትርጉም ባለማግኘቱ የተነሳ ሕይወቱም እውቀት በስፋት ፈሰሰበት በሚባለው በዚህ ዘመን እጅግ ጎስቁሎ ይታያል። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን የሰውልጅን ማንነት እና ለምን በዚህ ምድር በዚህ ዓይነት ሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳለው ተፈጥሮን መርምራ፣ መጽሐፍት አገላብጣ ትርጉሙን ታስረዳለች።

የትዳር ተገቢውን ትርጉም አለማግኘት የሰው ልጆች የጋብቻ ሕይወት በሚያስደስት የፍቅር እና የሰላም ሕይወት ውስጥ በደስታ እንዳይዘልቅ ሲገረግረው/ሲከለክለው ይታያል። ትርጉም መግቢያ በር እንደመሆኑ መግቢያው ጠፍቶበት በትዳር ሕይወቱ ብዙው የዓለም ሕዝብ በመባዘን ጠፍቶ ይታያል። ስለዚህ የትዳርን ትርጉም ማሳወቅ ሕይወቱን ለመጀመር ተገቢ በር ይሆናል።

የትዳር ትርጉም እንደ ትዳር ምንነት ሁሉ ቀላል የሚመስል ነገር ግን ተርጉሙ ብንባል የሚከብደን ጥያቄ ነው። እዘህ ላይ ምንነት (What it is) እና ትርጉም (definition) የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። በርግጥ ምንነት ለትርጉም በር ነው። ስለዚህም የትዳር ትርጉሙ ከምንነቱ (ኪዳን) የመነጨ ነው።

ትዳር በሦስት አሳቦች የሚመራ አንድ ጎጆ ነው ። አሳብ ባለቤት አለውና ለትዳርም ሦስት አሳቦች ሦስት ባለቤት አላቸው። ሦስቱ የትዳር ባለቤቶች ሴት(ሚስት)፣ ወንድ(ባል)፣ እና እግዚአብሔር ናቸው። የእግዚአብሔር አሳብ በፍቃዱ የተገለጠ ነው፤ ፍቃዱም አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ሁሉ የወደደበት ፍቅሩ ነው(ዮሐ. 3፡16) ። ይህም የእግዚአብሔር ፍቅር መንግሥቱን ወርሰን ከእርሱ ጋር በፍቅር በመንግሥተ ሰማይ እንኖር ዘንድ ነው። የሴትና የወንድ (የባልና የሚስት) ፍቃድ ደግሞ በኑሮ የሚገለጥ ሲሆን፤ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ ደግሞ ባለትዳሮች በተገለጠው የእግዚአብሔር ፍቃድ ይኖሩ ዘንድ ነው። ትዳርን ኪዳን ያስባለው የእግዚአብሔር ፍቃድ መኖሩ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ፍቃድ ትዳርን ከምድራዊ የስምምነት ሕይወት አውጥቶ የጽድቅ ሕይወት ያደርገዋል። ፍቅሩንም እንደ ሥላሴ ሦስትዮሽ ጠባይ እና አንድ ባሕርይ ያላብሰዋል። ሦስትዮሽ ጠባዩ ከሦስት ወገን የሚወጣ ስለሆነ፤ አንድ ባሕርይው ፍቅር ስለሆነ።

አንድ ጎጆ መምራት ማለት ማደሪያን የሚገልጥ ፅንሰ አሳብ ነው። ጎጆ ለሰው ልጅ ማደሪያ፣ መካተቻ እና ገመና ነው። እግዚአብሔር የሚገኝበት ማደሪያ፣ መካተቻ እና ገመና ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። ስለዚህ ትዳር በእግዚአብሔር መንግሥት እግዚአብሔርን ንጉሥ እና አባት አድርጎ የሚኖርበት ሕይወት ነው።

✍🏽 ሴትነት እና ወንድነት
ለጋብቻ መሠረቱ ሴትነት እና ወንድነት ነውና ጥቂት ስለ ሴትነት እና ወንድነት ማንሳት ተገቢ ይሆናል። አንድም የሴትነትና የወንድነት ትርጉሙን ማወቅ የትዳርን ሕይወት በተገቢው መልኩ የመገንባት አቅምን ያሳድጋልና የቤተ ክርስቲያንን መረዳት መግለጥ ተገቢ ይሆናል። ሴትነትና ወንድነት ለብዙዎቻችን የፆታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ፆታ የሴትነት እና የወንድነት አንዱ መገለጫ እንጂ ብቸኛ መግለጫ አይደለም። በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሴትነት እና ወንድነት ከፆታ እጅግ ከፍ ያለ ነው። በቤተክርስቲያን ሴት የመንፈስ ቅዱስ ወንድ ደግሞ የቃል (ወልደ እግዚአብሔር/የክርስቶስ) ምሳሌ(አምሳል) ናቸው። ምሳሌነታቸውም ግዑዝ(አካላዊ) ሳይሆን የሕይወት ነው።

ሴት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት ሲባል መንፈስ ቅዱስ ከተገለጠበት ግብር አንጻር ስለተገለጠች እና የሥራ ድርሻዋ በዚያ አንቀጽ (መሠረት) የተሰራላት ሥለሆነ ነው። መንፈስ ቅዱስን በግሪኩ ፓራቅሊጦስ (በተለምዶ ጰራቅሊጦስ) ይለዋል። በሶርያዎች የጥንት ጽሑፍ ሲፃፍ የሴት አንቀጽን ይዞ ነው (በእንግሊዝኛው she በሚለው ነው)። የቃሉን ትርጉም ብናይ ደግሞ ከሴት ግብር ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። በግሪኩ ፓራ (para) የሚለው በጎን፣አጠገብ (alongside) የሚለውን ትርጉም ሲይዝ ቅሊጦስ (kletos) የሚለው ደግሞ ረዳት የሚለውን ይተረጉማል፤ ስለዚህ ፓራቅሊጦስ ማለት ‹በጎን፣አጠገብ ያለ ረዳት› የሚልን ትርጉም የያዘ ነው። በተጨማሪም ደግሞ ፓራቅሊጦስ በጥቅል ትርጉሙ ‹ሕይወትን የሚሰጥ› የሚል አሳብን ይይዛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጎን ያለ እረዳት እና ሕይወትን የሚሰጥ የሚለው አሳብ ለማን ነው የተነገረ ካልን በግልጥ ለሔዋን እንደሆነ እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሔዋንን ‹የምትመች እረዳት እንፍጠርለት› ብሎ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን ሲሰራት እናነባለን (ዘፍ. 2፥18) ። ሔዋን የሚለውን ቃል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጉም ‹የሕያዋን ሁሉ እናት› ብሎ ነው (ዘፍ. 3፥20) ። ስለዚህም ሴት (ሔዋን) ከጎን የተገኘች እረዳት እና ሕይወትን የምትሰጥ ናት ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለተገለጠበት ማንነት የምትወክል ሴት መሆኑዋን በግልጥ የሚናገር ነው።

ወንድ የወልድ (የኢየሱስ ክርስቶስ) ውክልናው በክህነት ግብሩ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ከሰው ልጆች በፊት የፈጠራቸውን እንስሳት ስም ያወጣላቸው ዘንድ ወደ አዳም እንዳመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ዘፍ. 2፥19) ። አዳም ከእግዚአብሔር በተሰጠው ስልጣን ለእንስሳቱ ስም ሲያወጣ ክብሩን ለእግዚአብሔር መልሶ ሰጠ (ቅዳሴያችንም ዘአወፈይከኒ አወፈይኩከ እንዲል፤ የሰጠኸኝን ሰጠሁህ) ፤ ይህም የአዳም ተግባር ክህነታዊ መሆኑን የሚነግረን ነው ። በሥሉስ ቅዱስ ዘንድ የዘላለም ካህን የተባለ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ አዳም በግብሩ ክርስቶስን ይወክላል።

✍🏽 ሴት እና ወንድ
ከላይ ከተመለከትነው አንፃር ሴትና ወንድ የፆታ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን ለመገንዘብ እንችላለን። ሴትና ወንድ በውስጡ የግብር ማንነት የተቀመጠበት መለያ ጭምር ነው። ለዚህም ነው በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክህነትን ለወንድ የምንሰጠው። ክህነትን ለወንድ መስጠት ግን ወንድን ማስበለጥ አለመሆኑን ከላይ የሚወክሉት በግልጥ ይናገራል። ሴትና ወንድ የወከሉት መንፈስ ቅዱስን እና ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሆነ አንዱ ከአንዱ ይበልጣል አይባልም። ወልድ ሰው በመሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ አነሰ እንደማይባለው ሁሉ፤ ሴትም ካህን ባለመሆኗ ከወንድ አነሰች አትባልም።

ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሰው የአፈጣጠር ዝርዝር በዘፍጥረት ሁለት ከመተንተኑ በፊት ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ብሎ እኩልነታቸውን የነገረን:: (ዘፍ. 1፥27) በዝርዝር አፈጣጠሩም እንደ አባቶቻችን ትርጓሜ ሴትን ከአዳም ጎን የሠራት እኩልነቷን ሲያጠይቅ ነው፤ ምክንያቱም ከላይ ከፍ ብሎ ከራሱ፣ ከታች ዝቅ ብሎ ከእግሩ አልፈጠራትምና።

✍🏿 ትዳር መቼ ተጀመረ
ትዳር ከውድቀት በፊት ወይንስ በኋላ የሚለው አሳብ ሊቃውንቱን ብዙ ያወያየ አሳብ ነው። ምክንያቱ ሁለት ነው። የመጀመሪያው ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት (ዘፍ. 1፥28) የሚለው አምላካዊ በረከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አይተፋፈሩም ነበር (ዘፍ. 2፥25) የሚለው ነው። ብዙ ተባዙ የሚለው መባዛትን በማምጣት አሁን ወዳለው ሥርዓት አሳብን ሲጎትት አይተፋፈሩም ነበር የሚለው ደግሞ እንዴት ብሎ ይሞግታል።

ግልጥ ለማድረግ ያክል የሰው ልጅ አሁን ባለው ሥርዓት ለመባዛት መተፋፈር መቅድሙ ነው። መተፋፈር ከሌለ ስሜት የለም ማለት ነው። ስሜት ከሌለ ደግሞ አሁን ያለው የመባዛት መንገድ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ብዙ ተባዙ የሚለው ትእዛዝ ስላለ ደግሞ መባዛት የግድ ነው። ሊቃውንት ይህን ሲያስማሙት የሰው ልጅ ባይወድቅ ኑሮ እግዚአብሔር ሌላ የሚባዛበት መንገድ ይሰጠው ነበር፤ ለእግዚአብሔር የሚያበዛበት መንገድ አንድ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ የእግዚአብሔርን ማንነት በውል አለመገንዘብ ነው። መላእክት፣ ዕፅዋት፣ እንስሳት የተባዙበት የተለያየ መንገድ የሚነግረን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደ ሌለ ነው። ድኅረ ዓለም ኢየሱስ ከርስቶስ ያለ አባት መወለዱም ሌላ አስረጂ ነው።

ትዳር አሁን ባለው ሥርዓት በአንቀጸ ፆታ (ከፆታ ጋር በተገናኝ) የተጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው። የአዳም ውድቀት በሰው ልጆች ላይ ያመጣው አንዱ ጥፋት ፍቃድን ለስሜት ማስገዛት ነው። ይህንንም የፍጥረቱን ሂደት አይተን እንረዳለን። የሰው ልጅ የተፈጠረው ከእንስሳት በኋላ ሲሆን በጠባዩ ደግሞ ከእነርሱ በላቀ መልኩ ነበር ። ይህም እንስሳትን እና ዓለሙን ይገዛ ዘንድ በተሰጠው ሥልጣን የተገለጠ ነው (1፥28) መግዛቱም ስም በማውጣት፣ ከእባብ ጋር በመነጋገር ተገልጦ እናነባለን። አባቶቻችን በትርጓሜያቸው ላይ ደግሞ እግዚአብሔር አዳምን ማዕከላዊ ፍጥረት አድርጎ እንደፈጠረው ይተረጉማሉ (በእንስሳት እና በመላእክት)። ትዕዛዙን በመጠበቅ ጸንቶ ጠላት ሰይጣንን ድል አድርጎት ቢሆን ኖሮ እንደ መላእክት ሊሆን፤ ስላልጠበቀ ግን ሲወድቅ እንደ እንስሳት ስሜታዊ ሆነ። በዚህ ጊዜ ሴትነት እና ወንድነትም ከግብሩ ወርዶ ፆታ ለይ አረፈ (ፆታ መገለጫው ሆነ) ።

በጥቅሉ ሴት እና ወንድን በፆታ አንቀጽ ብቻ አይቶ ትዳርን ማሰብ እና መመስረት ብሎም ለመምራት መድከም እጅግ ዋጋ የሚያስከፍል ነው። ወንድነት እና ሴትነት ፆታ ብቻ ሳይሆን ከፍ ባለው የቀደመ የሰው ልጅ ክብር የግብር መገለጫ ነው። ስለዚህም ትዳርን የሚጀምርም ሆነ ለመምራት የሚሞክር ሰው በውስጡ ያለውን የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታ እና የመሳሰሉት በጎ የሕይወት ስኬቶችን ያገኝ ዘንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የምትመክረው ትዳርን ከፆታ ከፍ ባለ መልኩ በግብሩ መረዳት እና በግብር ጎዳናው መምራት ነው። ትርጉሙ ከላይ የተገለጠ ሲሆን ጎዳናው ደግሞ ከታች/ቀጥሎ በሚቀርበው ዝርዝር/ በብዙ ህብር የሚገለጥ ይሆናል።

✍🏽 የትዳር ዓላማዎች
ትዳርን እግዚአብሔር ለሦስት ዓላማዎች መሥርቶታል (ሦስት ዓላማዎችን በውስጡ አኑሮበታል)። እነዚህም ለመረዳዳት፣ ዘር ለመተካት፣ እና ከዝሙት ጠንቅ እኛን ልጆቹን ለመጠበቅ ነው። እነዚህ ሦስት የትዳር ዓላማዎች በአግባቡ በያዙት ጽንሰ አሳብ መጠን በትምህርት ውስጥ በተገቢው ባለመገለጣቸው ተገቢው ትኩረት ተነፍጎአቸው ይታያሉ። ምክንያቱ ደግሞ ዓላማዎቹ በጽንሰ አሳብ ደረጃ ሳይሆን በቀጥታ ትርጉም ብቻ ለመረዳት እና ለማስረዳት የተሞከረበት መንገድ ነው። በመቀጠል እነዚህን ሦስት ጽንሰ አሳቦች (የትዳር ዓላማዎች) እንድ በአንድ እነንመለከታቸዋለን።

✍🏽 አንድ፤ ለመረዳዳት

መረዳዳት ተባብሮ መስራትን እና መተጋገዝን የሚያመለክት ጽንሰ አሳብ ነው። መረዳዳት በትኩረት ከተመለከቱት ደግሞ ብቻን የመስራት ድካምንና ፍሬ ቢስ መሆንን የሚያጠይቅ ነው። በትዳር አንቀጽ ስንመጣ ሴትና ወንድን በኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር እናገኛቸዋለን። ሴትና ወንድ ዘር መተካትን ለብቻቸው ስለማይችሉት ይጣመሩ ዘንድ ሕግ ሲሰራላቸው እግዚአብሔር ደግሞ መረዳዳታቸው ጥቅም ይሆንላቸው ዘንድ በበረከት ከእነርሱ ጋር ይሆናል።

መረዳዳት የተለያዩ አካላትን ለአንድ ተግባር የሚያስተሳስር ጽንሰ አሳብ ነውና የግብር ኃላፊነትን ማዘጋጀት ይጠይቃል። በትዳር ሕይወት ውስጥ ኃላፊነት ያለባቸው ሦስት አካላት ሲሆኑ የሥራ ድርሻቸውንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ አስቀምጦታል። የሥራ ድርሻውን የማያውቅ ሰው ለግጭት እና ለብጥብጥ ቅርብ ነውና የሰው ልጅ (ሴት፣ ወንድ) በትዳር ውስጥ ያለውን ድርሻ በተገቢው መንገድ ሊያውቅ ይገባል። የሥራ ድርሻውን አውቆ የሚሠራ ሰው ለሥራውም ሆነ አብሮት ለሚሰራው ሰው አጋዥ መሆንን ይችላል። ሥራውን በመስራት የድርሻውን በመወጣት መከናወኑን ሲያፋጥን አብሮት ለሚሰራው ሰው ደግሞ ብርታት ይሆናል። ነገር ግን በሌላው ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ ውጤቱ በሌለው ላይ የተመረኮዘ እንዲሁም ለምክንያት የተጋለጠ ይሆናል።

በትዳር ውስጥ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ለሴቷም ሆነ ለወንዱ የሥራ ድርሻ አላቸው። የቤተክርስቲያን ምክሯም ሁለቱም ያለመጠባበቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ነው። ይህንንም የሚመሰርቱበት የእግዚአብሔር ፍቅር ግድ ትላቸዋለች። ምክንያቱም ፍቅር መቀበል የሌለበት መስጠት ስለሆነ። መቀበልን በቅድመ ሁናቴ ያላስቀመጠ የሥራ ድርሻን መወጣት የትዳርን ኪዳን ለመወጣት ሲያግዝ በኪዳን ኑሮው የደከመውን ለማገዝ እድል ይሆናል። ሁለተኛ ወገኑን ተመልክቶ ለምን በማለት ከተግባሩ የሚዘገይ ግን ተግባሩን ባለመሥራቱ ሲከስር ለሁለተኛ ወገኑም ብርታት ሳይሆን ይቀራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሴት እና ለወንድ የተሰጣቸው የሥራ ድርሻ እንደ ግብራቸው ነው። በጎን (አጠገብ) ያለ እረዳት እና ሕይወት ሰጪ መሆን አንዱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ማፍቀርና እና ክህነት ናቸው። እረዳትነትን መጽሐፍ ቅዱስ የምትመች ብሎ (ዘፍ. 2፥18) እና ከግብረ እንስሳዊ ጠባይ አኳያ ደግሞ ጌታየ ብሎ መታዘዝን (1ጴጥ. 3፥1) ለሴት ይሰጣል። ማፍቀርና ክህነትን ደግሞ ለወንድ ይሰጣል (ዘፍ. 2፥24፣ዘጽ. 28፥41፣ ቲቶ. 1፥6-8፣ ኤፌ. 5፥25-26) ።

ከአምልኮተ እግዚአብሔር አንፃር ሲታይ የወንድም የሴትም የሥራ ድርሻ አገልግሎት ነው። አገልግሎት አገልጋይ እና ተገልጋይ ያለበት ተግባር ነው። በአገልጋይነት ያለውን ድርሻ ወንድ ሲይዝ የተገልጋይነቱን ደግሞ ሴት ትይዛለች። ፍቅር እና ክህነት ጠባያቸው አገልጋይነት ነው፤ እረዳትነት እና መታዘዝ ደግሞ የተገልጋይነት ጠባይ ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር አገልጋይነትን እና ተገልጋይነትን በዚህ ዓለም (በምድራዊ እውቀት) የአረዳድ ዘይቤ ወስደን ልንረዳው መሞከር ተገቢ አለመሆኑን ነው።

ምክንያቱም የዚህ ምድር አረዳድ አገልጋይነትን የማስበለጥ ዝንባሌ ስላለው ነው። አገላጋይ የሚኖረው (በትኩረት ከታየ) ተገልጋይ ሲኖር ነው። ያለ ተገልጋይ አገልጋይነት የለም። ያለ ሔዋን የአዳም አገልጋይነት በእንስሳት ብቻ ተገድቦ ከንቱ ይሆን ነበር። ሔዋን የአዳምን አገልጋይነት ምሉዕ ያደረገች ናት። በውክልናቸው አንፃር ሲታይ ደግሞ፤ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጠም፤ መንፈስ ቅዱስም ባለመሞቱ ከወልድ አይበልጥም፣ ትክክል ነው እንጂ። ስለዚህ አገልጋይነት እና ተገልጋይነት በአገልግሎት ሂደት የሥራ ድርሻ እንጂ የማበላለጫ መንግድ አይደለም። የአገልጋይነት እና የተገልጋይነት ማሰሪያው አገልግሎት ነው፤ አገልግሎት ውስጥ ሁለቱም አሉ። ያለ አገልግሎቱ የእግዚአብሔርን በረከት ማግኘት አይቻልም።

ወደ መረዳዳት ጽንሰ አሳብ ስናመጣው መረዳዳት በአገልግሎት ውስጥ ጌታየ ብሎ በመታዘዝ እና ራስን ለመስቀል ሞት እንኳን ሳይራሩ በማፍቀር የሚተገበር ሕይወት ነው። ሴቷ የሚመች እረዳት መሆንን እስከ ጌታየ ብሎ መታዘዝ የምትዘልቅበት ሕይወት ሲሆን፤ ወንድ ደግሞ የክህነት አገልግሎቱን እስከ ሞት ወደ ሚደርስ ፍቅር የሚያሳድግበት ነው። ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ትዳርን አንድ የአሳብ መስመር ብንሰራለት በአንደኛው ጫፍ ጌታየ ብሎ መታዘዝ ሲኖር በሌላኛው ጫፍ ደግሞ እስከ ሞት የሚያደርስ ፍጹም ፍቅር ይኖራል ማለት ነው። ትዳር በእነዚህ ሁለት ጽንሰ አሳቦች ውስጥ ሁኖ ሲመራ ጤናማ ይሆናል።

ነገር ግን ልንገነዘበው እና ልንረሳው የማይገባ ሴት ልጅ ባሏን አታፍቅረዉ ወንድ ልጅም ሚስቱን አይታዘዝ ማለት አለመሆኑን ነው። የዘመናችን ትልቁ በሽታ ያልተጻፈን ምንባብ ማንበብ ነው። ብዙዎች የተጻፈን ጉዳይ አንብቦ በትኩረት ከመገንዘብ ይልቅ በሚያነቡት ንባብ ላይ በጭንቅላታቸው የሚመጣውን ጊዜያዊ መረዳታቸውን ጨምረው ያነቡታል። ከዚህም የተነሳ የሚስቱ ብዙ ናቸው። አንዲህ ግን መሆን የለበትም። ስለዚህም ባል ሚስቱን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ይውደዳት አለ እንጂ ሚስት ባሏን አትውደድ የሚል አልተጻፈም። እንዲሁም ሚስተ ባሏን ጌታየ ብላ ትታዘዘው ተብሎ ተጻፈ እንጂ ባል ሚስቱን አይታዘዝ ተብሎ አልተጻፈም። ትዳራቸው ጤናማ ይሆን ዘንድ አፍቃሪ ባል የማትታዘዝ ሚስት ብትኖረው ይታዘዛት እና ትዳሩን ጤናማ ያድርግ። የምትታዘዝ ሚስት የሚያፈቅር ባል ባይኖራት ትዳራቸው ምሉዕ ይሆን ዘንድ ታፍቅረው። እንዲሁም ፍቅር የመታዘዝ ሥር ነውና ሃይማኖታዊ ለሆነው ኑሮው ባል ሚስቱን ይታዘዛል። መታዘዝም የፍቅር ውጤት ነውና የምትታዘዛ ሴት ባሏን የምታፈቅር ናት። መጽሐፍ ሴትን በአፍቃሪነቷ የመታዘዝን የሥራ ድርሻ ሲሰጣት፤ ለወንድ ደግሞ ሴትን በመታዘዝ የወደቀ ነውና ባዘዘችበት ፍቅር ያነሳት ዘንድ ፍቅር በሥራ ድርሻነት ተሰጠው።

በጥቅሉ ሲታይ ደግሞ አንድ ትዳር የደስታ መናኸሪያ ይሆን ዘንድ ፍቅር እና መታዘዝ ያስፈልገዋል። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መስሎ አስተምሮታል ‹‹ ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻችው ይገዙ። ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ … እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል›› ኤፌሶን 5፥22-28 ። ክርስቶስ ያለ ቤተክርስቲያን ክርስቶስ የሚባል ህልውና የለውም፤ ቃል፣ ወልድ ቢባል እንጂ። ቤክርስቲያን ደግሞ ያለ ክርስቶስ ፈጽሞ ምንም ህልውና
የላትም በክርስቶስ የተመሰረተች ናትና። ለባልና ለሚስት ሲሆን ደግሞ ሁለቱም ፍጡራን ናቸው እና የሚመሰርቱት ትዳር ያለ ሁለቱ ሕልውና የለውም። ሕልውናው የጸና ይሆን ዘንድ ቅዱስ ጳውሎስ በምሳሌ የሥራ ኃላፊነታቸውን አስተማረ።

በመረዳዳት አንቀጽ ውስጥ ያለው የሴት እና የወንድ የሥራ ድርሻ እግዚአብሔር ከአስቀመጠላቸው ተፈጥሮአዊ ማንንት ጋር በተገናዘበ የስራ ኃላፊነት እንጂ ደረጃ ወይንም ስልጣን አይደለም። ምክንያቱም በወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ደረጃ ወይንም ስልጣን ስለሌለ። ስለዚህም ሥነ ሕይወታዊ (Biological) እና መሰል አመክንዮዎችን በመደርደር በባልና በሚስት መካከል ደረጃ ወይንም ስልጣን ለማስቀመጥ መሞከር ኦርቶዶክሳዊ ጠባይ አይደለለም።

መረዳዳት በሕይወት ውስጥ በሦስት ነገሮች የተገለጠ(የሚገለጥ) ነው፤ በማሰብ፣ በመናገር፣ እና በማድረግ። ይህም በአባቶች የማሰር እና የመፍታት ስልጣን ውስጥ ተገልጦም እንሰማለን፤ በአሳብ (በሃሊዮ)፣ በንግግር (በነቢብ)፣ በተግባር (በገቢር) የማይሰራ ኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታህ። ይህም የሆነበት ምክንያት የሰው ልጂ በአምስቱ የስሜት ህዋሳት መነሻነት ወደ ሰውነቱ ያስገባውን ጽድቅም ሆነ ኃጢአት የሚከውነው በሦስቱ (በአሳብ፣ በንግግር፣ በድርጊት)ስለሆነ ነው።

✍🏽 በአሳብ
በአሳብ ባል ሚስቱን፣ ሚስት ባልዋን የያዙት ኪዳን እንጂ የምድራራዊ ስምምነት አለመሆኑን አውቀው ሊተጋገዙ ይገባል። የንግግርም ሆነ የድርጊት ዓይነተኛ ምንጭ አሳብ ነው ። አሳብ በስሜት እንዳይሸፈን(እንዳይሸነፍ) በእውቀት መከላከል ተገቢ ነው። ስለዚህ ባለትዳሮች ስለትዳር ያላቸውን አሳብ በስሜት እንዳይጎዳ በእውቀት ሊጠብቁት ይገባል። ይህ ከሆነ በአሳብ ትዳራቸውን ማገዝ ይችላሉ። ባል ሚስቱን ይረደታል (ይረዳታል)፤ ሚስትም ባልዋን ትረዳዋለች (ትረዳዋለች)። በአሳብ የተጀመረ ሚስትን ማፍቀር በንግግር የተገለጠ በድርጊት የሚታይ ይሆናል፤ በአሳብ የተጀመረ መታዘዝ በንግግር እንደ ሣራ ጌታየ (እንደ ጊዜ ግብሩ) ተብሎ የሚገለጥ በድርጊት የሚዳሰስ ይሆናል። መረዳዳት በአሳብ ካልተጀመረ ስሜት ስለሚወርሰው ፍሬያማ አይሆንም። ስሜት የአሳብ መፈጸሚያ አቅም ሊሆን ነው እንጂ የሚገባ በራሱ አሳብ መሆን የለበትም። ስሜት በራሱ አሳብ ከሆነ እንደ ጠላታችን ሰይጣን እና የአስቆርቱ ይሁዳ ይወርሰናል። ሰይጣንና የአስቆርቱ ይሁዳ ስሜትን በአሳባቸው ላይ ስለአነገሱት ለንስሐ ልባቸውን ተሰለቡ፤ አዳምና ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በአሳብ ሳይሆን በንግግር ወደ ስሜት ገብተዋልና ወደ አሳባቸው ሲመለሱ ንስሐ ገብተዋል። ስለዚህ ትዳርን በአሳብ መገንዘብ ተገቢ ነው።

የሰይጣን እና የአዳም ልዩነታቸው አሳብ ነው። ሰይጣን ዲያብሎስ ሲበድል እና ከዓለመ መላእክት ሲለይ የበደሉ ምንጭ አሳቡ ነበረች እና ወረሰችው። አዳም ግን የበደለው ሰምቶ ነውና የሰማው ባይሆንለት ተጸጸተ። በጄሮ የገባን ኃጢአትም በጀሮ በተሰማ ብሥራት አስወጣለት። በጀሮ የሰማው ኃጢአት ይህንን ብትበላ አምላክ ትሆናለህ የሚለው የዲያብሎስ ቅጥፈት ነው (ዘፍ. 3፥ 4-5) ። አዳም እጸ በለስን መብላትን እና አምላክ የመሆንን ፍላጎት እንደ ዲያብሎስ ከልቡ አላመነጫትም እና አምላክ መሆን ባይሳከለት የሰራው ኃጢአት ገብቶት/ ተረድቶት ንስሐ ገባ፤ ዲያብሎስ ግን ከልቡ አምላክ የመሆንን አሳብ አውጥቶአታልና ወረሰችው። ብሥራቱ ቅዱስ ገብርኤል ትጸንሻለሽ ብሎ ለእመቤታችን የተናገረው ነው (ሉቃ. 1፥28) ። አሳብ ከልብ ይመነጫል፤ በመቀጠል ሰውነትን/ማንነትን ይወርሳል። ስለዚህም በትዳር ሕይወት ውስጥ ስለ ትድር ያለንን አሳብ በተገቢው መንገድ ማነጽ ተገቢ ነው።

ብዙ ጊዜ በትዳር ውስጥ የሚሰተዋለው ፍች አሳብን በአግባቡ አስቀድሞ በኪዳን ላይ ካለማሳረፍ የሚመነጭ ነው። ትዳርን የምንመዝነው በሥጋ ሚዛን ብቻ ይሆንና አሳባችን በዚያ ላይ ይንጠለጠላል። በሥጋ ደረጃ ያሉ አሳቦች ደግሞ ለትዳር ሕይወት ተገቢውን ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ ማምጣት አይችሉምና መፈፍትሔ ይመስል ውደ መፋታት ይኬዳል። ይሁንና ትዳርን መፍታት ግን ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ለዘለቄታው የሚሆን ፍቅር፣ ሰላም፣ እና ደስታ ማምጣት አይችልም። ፍች በራሱ ለሌላ ትዳር ርሃብን የሚፈጥር እንጂ ለትዳር ችግር መፍትሔ መሆን የማይችል ነው። ስለዚህም ኣሳብን በተገቢው መንገድ መስመር ማስያዝ የትዳርን ሕይወት የሚያቀና የጠፋውን ፍቅር፣ ሰላምና፣ እና ደስታ መመለስ የሚያስችል ነው።

በአሳብ መረዳዳት ሲባል በድርጊት እና በንግግር የሚገለጡ የባልም ሆነ የሚስት አሳቦች ከፍቅር እና ከመታዘዝ መሆኑን መረዳት ማለት ነው። ባል ሚስቱ ለእርሱ የማይስማማው ነገር እንኳን ብትናገር ወይንም ብትሰራ ወደ ስሜት ከመግባት ይልቅ ስህተት የመሰለው ነገር የተሰራው ትዳራቸውን የሚያቆም መስሎአት መሆኑን በማሰብ መጀመር አለበት። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት መሰረት ያደረገ ሃይማኖታዊ መረዳት ነው። በቅን አስተሳሰብ (Postive thinking) የጀመረ ሰው ሌላውን የመረዳት (የመርዳት) አቅም ይኖረዋል። ለባል ብቻ ሳይሆን ለሚስትም እንደዚያው ነው።

ስለዚህ ሚስትም ሆነች ባል በንግግር እና በድርጊት በሚገለጥ ማንነታቸው ውስጥ ሊያዳብሩት የሚገባ የግንኙነት መስመር ቅን የሆነ አስተሳሰብን ነው። ባልም ሆነ ሚስት ለአጋራቸው እጅግ ቅን የሆነ አጋዥ አሳብ ማሰብን ሊያጎለብቱ ይገባል። ፍቅር እና መታዘዝን መሸከም የሚችል ቅን የሆነ አሳብ ብቻ ነው። አዳምና ሔዋን በቅንነት እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትዕዛዝ አስበውት ቢሆን ኖሮ በመታዘዝ የእግዚአብሔርን ፍቅር ገንዘብ ባደረጉ (በወረሱ) ነበር። ከዚህ ፍሬ ብትበሉ ‹‹ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምና ክፉን የምታውቁ እድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ ›. ባለቸው ጊዜ ከስሜታቸው ወጥተው በኣሳብ ጉዳዩን አይተውት ቢሆን ኑሮ ቀጥፈው ባልበሉ ነበር። ምክንያቱም እደ እግዚአብሔር የሚያደርግ እና እግዚአብሔር ያንን የማይፈልግ ቢሆን ኑሮ እጸ በለስን አጠገባቸው ባለስቀመጣት ነበር፤ ትዕዛዝም በመስጠት ስሜት ወደ አሳባቸው እንዲገባ ባልፈቀደ ነበር። ይሁንና ሰምተው አደረጉት፤ ከልብ ያሰቡበት አልነበረምና ንስሐ ገቡ። ከልብ በአሳብ ተጸንሶ ያልተወለደ ማንኛውም ንግግር ወይንም ደርጊት ጸጸት ሊከተለው የሚችል ነው። ስለዚህ በትዳር ውስጥ አሳብን መጠበቅ ተገቢ ነው።

ሁል ጊዜም ቢሆን ባለትዳሮች ለትዳር አጋራቸው በጎ ለማሰብ እራሳቸውን ማስለመድ አለባቸው። ማንኛውም ሰው ከትዳር አጋሩ በበለጠ ራሱን የሰጠው እና ሊሰጠው የሚችል የለም። እራስን እርቃን አድርጎ ከመስጠት በላይም የሚሆን የለም። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰው ራቁት የሆነ ገላማ በገንዘብስ እንደ ሴተኛ አዳሪ ቤት ባለው ይገኝ የለምን የሚል ጉንጭ አልፋ ከርከር ያነሳል። ሊገነዘቡት የሚገባ ግን ሴተኛ አዳሪ ቤት ያለው ለስሜት ሲሆን በትዳር ውስጥ ያለው ግን ለሕይወት መሆኑን ነው። ስሜት እንደ አዳም ሞትን ሲጠራ ለሕይወት የሆነ እርቃን ደግሞ እንደ ክርስቶስ ሕይወትን ያሰጣል።

✍🏽 በንግግር
ንግግር ከስሜት እና ከአሳብ ይፈልቃል። ሰው የተናገረው ሁሉ ከአሳቡ የፈለቀ የሚያምንበት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ቀላል የማይባለው የሰው ልጅ ንግግር ከስሜት ይፈልቃል። ስሜት ጠባዩ ሁለት ነው፤ ሀዘን ወይንም ደስታ። ሰው በስሜት ውስጥ ሲገባ የሚያምንበት አሳቡ በስሜቱ ይዋጥበታል። ስለዚህም በስሜት ውስጥ እያለ እንዳይወስን ይመከራል። በትዳር ውስጥም ስሜታዊ ንግግሮች አሉ፤ እንዲያውም ከሌሎች የኑሮ ኩነተች በትዳር ውስጥ የስሜት ንግገሮች ይበዛሉ። የስሜት ንግግሮችን የሚያበዛዉ የግንኙነቱ መሰረት እና አንዱ የፍቅር ጠባይ ስሜት ስለሆነ ነው።

ንግግር ደስ የሚያሰኘውን ያክል ያሳዝናልም። በትዳር ውስጥም የሚያስደስትም የሚያሳዝንም ንግግር ከሁለቱም ወገን ይመጣል። ስለዚህ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሁነት እንግዳ መሆን አይገባም። በተለይ የማያስደስቱ ንግግሮች ሲኖሩ ምንጫቸው ስሜት ወይንስ አሳብ የሚሉት ለመለየት መሞከር ተገቢ ነው።

ማስታወሻ:- ዲ/ን አርክቴክት አንተነህ ጌትነት Agora university: Holy Transfiguration college በTheological studies እንዲሁም Holy Sofia University
በOrthodox Christian Apologetics የማስተርስ ዲግሪዎቻቸውን እየሠሩ ይገኛሉ::

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ድንግል_ሆይ!
#ከዓይኖችሽ_በልጅሽ_ፊት_ላይ_የፈሰሰውን_መራራውን_የእንባ_ጎርፍ_አሳስቢ!!!

ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ኅዳር 5 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ ጽጌ፣ ወርኀ ጽጌ፣ መዋዕለ ጽጌ በመባል ይታወቃል።

ቀናቱ 40 ናቸው፣ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ምሥጢሩ እመቤታችንንም ጌታንም ይመለከታል፣ በዚህ ወቅት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደችው ስደት ይታሰባል፣ እሑድ እሑድ በማኅሌት ዘወትር በጸሎትና በስግደት እንዲሁም የእመቤታችን ፍቅር የበዛላቸው ደግሞ በጾም ያስቡታል።

የስደቱ የጊዜ መጠን በአጠቃላይ 3 ዓመት ከመንፈቅ ሲሆን 1260 ቀናት ናቸው።

በዚህ የስደት ጊዜ ውስጥ እመቤታችን ያልተቀበለችው ስቃይና መከራ የለም፣ እኛ በዓለም ላይ ምንም ዓይነት መከራ ብንቀበል በኃጢአታችን ምክንያት ነው እመቤታችን ግን ምንም ኃጢአት ሳይኖርባት ነው።

ጌታችን አየሱስ ክርስቶስ ጀርባዋ ላይ ነበር እኛም ሁላችን በእርሱ መሃል እጅ ሆነን በእርሷ ትከሻ ላይ ነበርን፣ እርሱን ብቻ ሳይሆን እኛንም አዝላ ተሰዳለች፣
የግብፅ አሸዋ የንጽህት ድንግልን እንባ ጠጥቷል፣ መሬቱም ጥንተ አብሶ የሌለበትን ደም ጠጥቷል።

በሔዋን ምክንያት የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት የሔዋንን ባህርይ ይዛ እንደ ሔዋን ግን ሳትበድል መንከራተት የነበረባት ንጽሕት ሴት እመቤታችን ስለሆነች የድኅነታችን ሁሉ ምሥጢር በእርሷ በኩል አልፏል።

☞ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህን ሲገልጥ "ወኮነት ፈዳዪተ ዕዳሃ ለሔዋን"(የሔዋን ዕዳ ከፋይ ሆነች) ይላል፣ሃይ•አበ።

☞ቅዱስ ኤፍሬምም "አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ" (የባህርያችን መመኪያ ነሽ) ብሏታል፣ ቅዱስ ያሬድም "ትምክህተ ዘመድነ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም" (የባህርያችን መመኪያ እመቤታችን ማርያም ናት) በማለት ተናግሯል።

በስደት ጊዜ እመቤታችን አራት ጊዜ መራራ የሆነ ለቅሶ አንዳለቀሰች ሊቃውንት አባቶቻችን ይገልጣሉ፦

1. የዮሴፍ ልጅ ዮሳ የሄሮድስ ወታደሮች መቃረባቸውን ሲነግራት፤

2. የትዕማን ሴት አገልጋይ ጌታን መሬት ላይ ስትፈጠፍጠው፤

3. ሰብአ ሰገል የገበሩለት የወርቅ ጫማው ሲጠፋ፤

4. ጥጦስን ዳክርስ የሚባሉ ሺፍቶች ሲያገኟቸው፡፡ (ምንጭ:—ነገረ ማርያም፣ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)።

☞የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ብቻ እንመልከት!

ዮሳ የሄሮድስን ውሳኔ እና የወታደሮቹን መታዘዝ ከአልዓዛር ሰምቶ እነርሱ 40 ቀን የተጓዙትን እሱ በ 3 ቀን ገስግሶ ደርሶ እመቤታችን ጌታን እያጠባች ወንዝ ዳር ተቀምጠው አግኝቷቸዋል፣ እርሱም ሰይጣን በምትሀት ሽማግሌ መስሎ በነገረው መሠረት የሄሮድስ ጭፍሮች መድረሳቸውን ለእመቤታችን ነገራት ፣እመቤታችንም "ልጄ እንስሳት አራዊት የማይችሉትን መከራ የተቀበልኩ ከዚህ ላላድንህ ነው?" ብላ ዓይኗን ከዓይኑ ፣ አፏን ከአፉ ፣ እጇን ከእጁ ላይ አድርጋ ምርር ብላ ፅኑ ለቅሶ አልቀሳለች።

ደራሲው:—

"አመ ፈነወ ሄሮድስ ወአሊሁ ውስተ ደብረ ቊስቋም ይኅሥሣ
ሰሚኣ ድድቀተ እምቃለ ወልደ ዮሴፍ ዮሳ
ማርያም ደንገፀት ወተሀውከ ከርሣ
እምእደ ሰሎሜ ሶቤሃ ተመጠወቶ ለሮሳ
ከመ ትብክዮ ዐቍራ በልብሳ።"

ትርጉም:—
በደብረ ቊስቋም ይፈልጋት ዘንድ ሄሮድስ አሽከሮቹን በላከ ጊዜ እመቤታችን ከዮሴፍ ልጅ ዮሳ የሚያስደነግጥ ነገርን ሰምታ ደነገጠች፣ አንጀቷም ተላወሰ! ያን ጊዜም በልብሷ ጠቅልላ (ቋጥራ) ታለቅስለት ዘንድ ልጇን ከሰሎሜ እጅ ተቀበለችው" እንዲል።

ከዮሴፍና ከሰሎሜ በቀር ማንም በሌለበት በረሃ ማረፊያ እንደሌላት ወፍ የምትንከራተት ንጽሕት ድንግል እመቤታችን የሚያቃጥል መራራ እንባዋን በልጇ ፊት ላይ አፈሰሰችው፣ ጎረፈ፣ ፊቱን እያጠበው፣ እያቃጠለው ወረደ፣ንጹሕ እንባ ነው፣ ትኩስ እንባ ነው፣ ቁጡ እንባ ነው ፊት ይመልጣል ዓይን ያንጣጣል! ይህ እንባ ደግሞ በከንቱ የቀረ ሳይሆን ለመማፀኛ እንዲሆን የተረጨ እንባ ነው፣ የጌታን የልጇን ልብ የማንኳኳት ዓቅም ያለው እንባ ነው፣ እሱም ያውቀዋል መራራነቱን፣ የፈሰሰው ፊቱ ላይ ነው አላየሁትም አይልም፣ እናቱ ናት፣ ፈጥሯታል የልቧን አላውቅም አይልም፣ ብቸኝነቷን ከጽድቋ ጋር ያውቀዋል አላየሁሽም አይላትም፣ ይህ እንባ ከንቱ አልቀረምና በመስቀል እኛን በልጅነት እሷን በእናትነት አስተሳስሯል።

☞☞☞ እናትነት ጠባዩ እንዲህ ነው እያነቡ ለልጅ ደስታ መሆን ነው፣ ሀገር መሆን ፣ዓለም መሆን፣ ሁሉን ማያ መሆን ነው!!! እኛ ዛሬ ይህን እንባዋን"አዘክሪ" እያልን እንማፀንበታለን፣ "ድንግል ሆይ በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!"
(አባ ሕርያቆስ)።

የመጨረሻው ጥጦስና ዳክርስ ባገኟቸው ጊዜ ነው፣ ልብሱን ቀምተው እንመልስለት አንመልስለት እያሉ ሲከራከሩ አይታ እመቤታችን ልጄን ሊገሉብኝ ነው ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡

ደራሲውም ይህንን ጭንቀቷን በመንፈሳዊ ምናብ ተመልክቶ እንዲህ አለ፦

"ይጽብበኒ እግዝእትየ ከመ ጸበበኪ ዓለም በምልኡ
ሶበ ዐገቱኪ ፈያት ልብሰ ወልድኪ ይንሥኡ
ዓይንኪ ዘርግብ ነጸፍጻፈ አንብዕ ይክዑ፣ነጺሮ ዕርቃኖ ለሕፃንኪ በግዑ፣
እስከነ አግብአ ለኪ አሐዱ እምካልኡ
እንዘ ያነክር እምፄና ልብሱ ወአዳም መልክኡ"

ትርጉም:—

እመቤቴ ሆይ! የልጅሽን ልብስ ሊወስዱ ሽፍቶች በከበቡሽ ጊዜ ዓለም በሙሉ እንደጠበበሽ እኔን ይጥበበኝ ይጭነቀኝ! ከሁለቱ አንዱ የልብሱን ውበትና መልካም ሽታ እያደነቀ አስኪመልስልሽ ድረስ ርግባዊ ዓይንሽ የበጉ ልጅሽን ራቁትነት አይቶ እንባን ያፈስ ነበር" በማለት ተቀኝቷል።

ድንግል ሆይ! በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በስደት ወቅት የነበረውን የእናትና ልጅ ሁኔታ ሲገልጠው እንዲህ ይላል:—"ሐዊረ ፍኖት በእግሩ ሶበ ይስእን ሕፃንኪ፣
ያንቀዓዱ ኀቤኪ ወይበኪ እኂዞ ጽንፈ ልብስኪ እስከ ትፀውሪዮ በገቦኪ ወትስእሚዮ በአፉኪ"
(ልጅሽ በእግሩ መሄድ በደከመው ጊዜ ወዳንቺ ቀና ብሎ የልብስሽን ጫፍ ይዞ ያለቅሳል፣ እቅፍ አድርገሽ እስከምትስሚው ድረስ።)

☞ግሩም ነው!!! አምላኳን ፈጣሪዋን በእናትነት ልሳን ያወራች፣ የልጅነት ጥያቄውን ብቃት ባለው እናትነት የመለሰች፣እንደ ሕፃናት መኮላተፉን የተረዳች፣ እንደ አምለክነቱ የሚያደርገውን ደግሞ በልቧ ጨምራ ችላው የምትኖር እናት!

☞☞☞ይህም የእናትና የልጅ ቋንቋ የሰው ልጆች የመዳን ቋንቋ ነው፣ የሚያውቁትም ጌታና እመቤታችን ብቻ ናቸው። ክርስቶስ በዚህ መንገድ አልፎ ፣ በእቅፏና በጀርባዋ በስደትና በመከራ ተጋግሮና ተጠምቆ ፣ በመስቀል መሶብ፣በመስቀል ጽዋ ምግብና መጠጥ ሆኖ ለዓለም ተሰጥቷል!

☞☞☞ሞኞች የሆኑ ሰዎች ለጌታ ለእግዚአብሔር ወልድ እናት ሆነችው እያልናቸው ለእኛ እናት ሆነችን ስንል አልዋጥ አላቸው! የትኛው ይከብዳል??? የአምላክ እናት መሆን? ወይስ የእኛ እናት አማላጅ መሆን?

ለእኛ ግን እናታችን ናት!

በረከቷ ረድኤቷ፣ልጇ የሚቀበለው አማላጅነቷ፣በስደትና በመስቀል ሥር የፈሰሰው እንባዋ
• ሀገራችንን ይጠብቅልን፣
• ቤተ ክርስቲያናችንን ይታደግልን፣
• እኛንም በተዋሕዶ ሃይማኖት ያጽናን!!!
❖❖❖ድንግል ሆይ! በልጅሽ ፊት ላይ የፈሰሰውን መራራውን የእንባ ጎርፍ አሳስቢ!

አሜን!!!

መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ ከፍያለው
ዘመካኒሳ ሚካኤል
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
እንኳን ለዘመነ ጽጌ በሰላም አደረሳችሁ !
2024/09/24 20:32:02
Back to Top
HTML Embed Code: