Telegram Web Link
_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፬__
አንቀጽ 16 ስለ ምጽዋት ይናገራል።
፩) ምጽዋት ከርኅራኄ ወገን የሚሆን ርኅራኄ ነው። ይኽውም ሰው አበድሬ እቀበላለሁ ሳይል በገንዘቡ የሚያደርገው ርኅራኄ ነው።
_
፪) ምጽዋት የማያልፍ የማይጠፋ ሰማያዊ ድልብ ነው። የተቻለውን ያህል በመስጠት ሰው ፈጣሪውን ይመስላል። የጌታ የባሕርይ የሰው የጸጋ ነውና።
_
፫) ምጽዋት ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖራት የብልህ አደራ ናት።
_
፬) ለለመነህ ስጠው። ለሰው የሚያዝኑ የሚራሩ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው። ለእነርሱም ሥላሴ ይራሩላቸዋልና። ጌታ በምጽዋት ለሰው ለሚራሩ ሰዎች ንዑ ኀቤየ ብሎ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባቸዋል።
_
፭) ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ ለተጠሙ፣ ለታረዙ፣ ለእንግዶች፣ ለታመሙ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለታሠሩ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሰደዱ ሊመጸውቱ ይገባል። እንግዳ መቀበል ከምጽዋት ወገን ነው።
_
፮) አሥራቱን፣ በኩራቱን፣ ስለቱን እግዚአብሔርን ለሚያገለግሉ ካህናት ከፋፍለው ይስጧቸው።
_
፯) በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ታገኙ ዘንድ፣ አሥራቱን፣ ስለቱን፣ እጅ መንሻውን፣ መጀመሪያ የደረሰውን እህል (ቀዳምያቱን) ስጡ። በረከት በሚመጸውት ሰው አትጠፋምና።
_
፰) ምጽዋት መጀመሪያ ሃይማኖታችንን አንክድም ብለው ለታሠሩ ሰማዕት ትገባለች። ከዚህ ቀጥሎ ለካህናት፣ ከዚያ ቀጥሎ ለዘመድ፣ ከዚያ ቀጥሎ ለምእመናን፣ ከዚያ ቀጥሎ ላላመኑ ሰዎች ትገባለች።
_
፱) ምጽዋትን ለተቸገረ ሁሉ ሊሰጧት ትገባለች። እግዚአብሔር ለኃጥአንም ለጻድቃንም ዝናምን እንደሚያዘንብ።
_
፲) ተመጽዋቾች ምጽዋቱን ስለ ሰጧቸው ሰዎች መጸለይ ይገባቸዋል። አብዝቶ ይጸልይላቸው።
_
፲፩) ያልተቸገሩ ሰዎች ምጽዋት መቀበል አይገባቸውም። እየተቻለው ምጽዋት የማይሰጥ ሰው እንደ ከሓዲ፣ እንደ ወንበዴ፣ እንደ ሌባ ነው።
_
፲፪) ምጽዋት ከኃጢአት ታነጻለች። ከመቅሠፍትም ታድናለች። ምጽዋት መስጠት እጥፍ ድርብ ዋጋን ያስገኛል።
_
፲፫) ምጽዋትን ከሰጡ በኋላ መጸጸት አይገባም። (ጸጸትን እንዳያመጣ አስቦ መስጠት ይገባል)።
_
፲፬) ምጽዋት የሚሰጥ ሰው በሚሰጠው ሰው ላይ መታበይ የለበትም።
_
፲፭) የሚመጸወተው ገንዘብ ነውር ነቀፋ የሌለበት ይሁን። ይኽም ላለፈው የተሰረቀ የተቀማ፣ ለሚመጣው ውዳሴ ከንቱ ያለበት አይሁን።
_
፲፮) ደስ ብሎት ደስ አሰኝቶ የሚሰጠውን ሰው እግዚአብሔር ይወደዋል።
_
፲፯) ከክፉዎች ምጽዋት ትቀበሉ ዘንድ አትውደዱ። ከእነርሱ ምጽዋትን ከምትቀበሉ በረኀብ ብትሞቱ ይሻላችኋል።

__አንቀጽ ፲፯___
ይህ አንቀጽ በምጽዋትና በቤተክርስቲያን ገንዘብ እንዲሁም በመብዓው ስለሚሾሙ ሰዎች ይናገራል
፩) ኤጲስ ቆጶስ በቤተክርስቲያን ገንዘብ ሁሉ ማዘዝ ይገባዋል። ለራሱ የሚሻውን፣ ከካህናት ወገን ለተቸገሩ ሰዎች ማወጣጣት ይገባዋል።
_
፪) ኤጲስ ቆጶስ የቤተክርስቲያንን ገንዘብ ምንም ድሆች ቢሆኑ ለዘመዶቹ መስጠት አይገባውም።
_
፫) የቤተክርስቲያን ገንዘብ፣ ልብስ፣ እርሻ፣ የተክል ቦታ፣ ላም፣ በሬ፣ ፈረስ እግዚአብሔርን በሚፈሩ በታመኑ ሰዎች እጅ ይጠበቅ።
_
፬) የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሸጠ፣ ገዝቶም የያዘ ሰው ይመልሱ። ባይመልሱ በኤጲስ ቆጶሱ እጥፍ አድርገው ይክፈሉ።
_
፭) ከምእመናን አንዱ ገንዘቤን ለቤተክርስቲያን ስጡ ብሎ አዝዞ ቢሞት የቤተክርስቲያኑ ገበዝ ይቀበል። የሚቀበለው ገንዘብ የንጉሥ ግብር ያለበት ከሆነ አይቀበሉት። ቤተክርስቲያን ከነገሥታት ሥልጣን በታች ልትሆን አይገባምና።
_
፮) በቤተክርስቲያን በገቢው ገንዘብ የተሾመው በወጭ ገንዘብ ከተሾመው ይለይ።
_
፯) በየሀገሩ ሁሉ ለታመሙ ለድኆች ለእንግዶች የሚያድሩበት ቤት ይለዩላቸው። እነርሱን ያስተዳድርለት ዘንድ ኤጲስ ቆጶሱ መነኩሴ ይሹም። ለሹሙ ቤት ምግብ ይመቻችለት። የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ቢያንስ ከምእመናን ሁሉ እንደአቅማቸው በየጊዜው ምግብ ይሰብስብላቸው። ስለዚህ ነገር ብዙ ኃጢአት ይሠረያል።
_
፰) አሥራት ሁሉ ለካህናት ሊሆን ይገባል።
_
፱) በሾላ፣ በሽንኩርት፣ በዱባ፣ በቅል እና እነዚህ በሚመስሉ አትክልት ከቤተክርስቲያን አግብተው አይጸልዩባቸው። በጽጌረዳ፣ በወይን፣ በበለስ፣ በሮማን፣ በዘይት፣ በሙዝ፣ በእንኮይ ግን ይጸልዩባቸው።
_
፲) ከመሥዋዕት የተረፈውን ለኤጲስ ቆጶሱ 4 ክፍል፣ ለቀሳውስት 3 ክፍል፣ ለዲያቆናት 2 ክፍል፣ ከዚያ በታች ላሉት እስከ ዲያቆናዊት ድረስ 1፣ 1 ክፍል ይስጧቸው።

__አንቀጽ 18____
ይህ አንቀጽ ስለ አሥራት፣ ስለ በኩራት፣ ስለ ስለት፣ ስለ ጉልት ይናገራል።
፩) አሥራት፣ በኵራት፣ ስለት፣ ጉልት የምጽዋት ወገኖች ናቸው።
_
፪) በኩራት (ቀዳምያት) መጀመሪያ የተቀዳውን ዘይት፣ መጀመሪያ የተቆረጠውን ማር፣ መጀመሪያ የታለበውን ወተት፣ መጀመሪያ የተሸለተውን ጸጉር፣ ጽፈው ደጉሰው መጀመሪያ ያገኙትን ገንዘብ ለቤተክርስቲያን መስጠት ነው። ካህኑ ላመጡት ሰዎች ከመጋረጃ ውጭ ሆኖ እግዚአብሔርን ያመስግነው።
_
፫) ስለት ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ በጎ ነገርን ለማግኘት ሰው በራሱ፣ በልጆቹ፣ በገንዘቡ የተሳለውን ለመፈጸም ከፈጣሪው ጋር የተማማለው መሓላ ነው። የሚሻውን ነገር ባገኘ ጊዜ ስለቱን እንዲፈጽም ሰው ከመሳሉ በፊት በደንብ ያስብ።
_
፬) ይህ ዓለም ኃላፊ ያ ዓለም ኗሪ እንደሆነ አውቆ መሳል በጎ ነገርን ለማግኘት ነው።
_
፭) መከራ ባገኘው ጊዜ ተሳለ እንጂ የተሳለውን ስለት መፈጸም የማይቻለው ድኃ ቢሆን ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ወደ ቄሱ ይሂድ። ቄሱ ወይም ኤጲስ ቆጶሱም የሚችለውን መጠን አይተው ይወስኑለት።
_
፮) ስለትን አለመፈጸም ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍዳን ያመጣብናል።
_
፯) ሴት ልጅ በአባቷ ቤት ሳለ በራሷ ላይ ብትሳል ማለትም ንጽሕ ጠብቄ ሰውነቴን ለእግዚአብሔር ልዩ ገንዘብ አደርገዋለሁ ብላ የተሳለችውን ስለት መፈጸም ይገባታል። አባቷም ስለቷን አያፍርስባት። ስትሳል ሰምቶ ስለቷን ቢያፈርስባት ግን ስለቷ አይጸናላትም። እግዚአብሔርም በዚህ አይመራመራትም። ባል ብታገባ ግን በተሳለችው ስለት ባሏ ሊያዝበት ይገባል። ባሏ ስትሳል ቸል ብሎ ከዚህ በኋላ ቢከለክላት ኃጢአቱ በእርሱ ይሆናል።
_
፰) ጉልት ፍጽምት የሆነች ምጽዋት ናት። በዚህ ዓለምም በሚመጣው ዓለምም ዋጋን ታስገኛለች።ለቤተክርስቲያን ጉልት መጎለት መልካም ነው።
_
፱) የሚጎለተው ጉልት ለሚጎለትላቸው ሰዎች እየኖረ ጥቅም የሚገኝበት ሊሆን ይገባል። ጉልት ዘወትር የሚኖር መሆን አለበት። ይኽውም ምሳሌ የእርሻ ቦታ፣ ቤት፣ አዝርዕት አትክልት ያሉበት ቦታ ወዘተ ይሁን። ባሮችን፣ ከብቶችን፣ ንብ ወዘተ መጎለት አይገባም። እነዚህ ሁሉ ዘወትር አይኖሩምና።
_
፲) የሚጎልተው ሰው ከገንዘቡ የሚያዝበትን እንጂ የማያዝበትን መጎለት አይገባውም። የሚጎልት ሰው አካለ መጠን ያደረሰ፣ አዋቂ፣ ራሱን የቻለ፣ በልቡ በጎ ነገርን የሚያስብ ሊሆን ይገባል። የሚጎልቱለት ሰውም ሃይማኖት ከምግባር ያለው ሊሆን ይገባል።
_
፲፩) የተጎለተለት ሰው ከጉልቱ ምንም ምን አይሽጥ። ሩቅ ሀገር ለሄደ ሰው ጉልት ቢጎለትለት መታጣቱ (መሞቱ) ቢታወቅ ለእርሱ የታዘዘው ጉልት ለቤተክርስቲያን ይግባ። የተቸገሩ ሰዎች ይረዱበት ዘንድ።
_
፲፪) ጥቅም የሚገኝበት ሥርዓት ቢፈርስ መልሶ ሊያጸኑት ይገባል።
_
፲፫) ጎላቹ ቢቸገር ከጉልቱ ከርቦው ከአምሾው ሊሰጡት ይገባል።
_
፲፬) የሚጎለተው ጉልት የንጉሥ ግብር ያለበት መሆን የለበትም።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲፭ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፭__
አንቀጽ ፲፱ ስለ ዕለተ እሑድና ስለ ቅዳሜ እንዲሁም ስለበዓላተ እግዚእ ይናገራል።
፩) ክርስቲያኖች እንደ አይሁድ በዕለተ ቀዳሚት ሥራ ፈትተው መዋል አይገባቸውም። በዕለተ ቀዳሚት እንደ ክርስቲያን ሥራ ይሥሩ እንጂ። (ሐተታ) የታመመ መጠየቅ፣ የሞተ መቅበር ይገባልና።
_
፪) በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቅዳሜ፣ በክቡራን በዓላት ስግደት አይገባም። የተድላ የደስታ ዕለታት ናቸውና። ይህ አንቀጽ ውግዘት የሌለበት ነው። ባሕታዊ ፆር ተነስቶበት ቢሰግድ ዕዳ የለበትምና።
_
፫) በዕለተ እሑድ ፍርድ ቤት አይሂዱ። እሑድ ቀን አያሟግቱ አያፋርዱ። በእሑድ ቀን ማንም ማን ገንዘቤን አምጣ ብሎ አይያዝ። ሁሉም ወደ ቤተክርስቲያን ይሂዱ እንጂ። ምእመናንም ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን፣ ኤጲስ ቆጶስ አሥራት በኩራት፣ ነጋድራስ ቀረጥ አምጡ ይለናል ብለው ሳይፈሩ በንጽሕና በትህትና ሁነው ወደ ቤተክርስቲያን ይምጡ።
_
፬) በዕለተ እሑድ ከነጋድራሶች አንዱስንኳ ወደቤተክርስቲያን ከሚሄዱ ሰዎች ቀረጥ ይቀበል ዘንድ የድፍረት ሥራ የሠራ ቢሆን እጥፍ አድርጎ ይክፈል።
_
፭) ሁልጊዜ በቤተክርስቲያን ተሰብሰቡ። ይልቁንም በዕለተ እሑድና በዕለተ ሰንበት እንዲሁም በጌታ በዓላት ወደ ቤተክርስቲያን ተሰብሰቡ።
_
፮) ጥቅም የሌለው ነገር አትናገሩ። የማይገባ ሥራም አትሥሩ።
_
፯) ባሮች (የቤት ሠራተኛዎች) አምስቱን ቀን ሠርተው ቅዳሜና እሑድ ግን የእግዚአብሔርን አንድነቱን ሦስትነቱን ይማሩ ዘንድ ከቤተክርስቲያን ሆነው ይዋሉ።
_
፰) ቅዳሜ መከበሯ ጌታ ፍጥረትን ከመፍጠር አርፎባታልና ነው። እሑድ መከበሯ ደግሞ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶባታልና ነው።
_
፱) የጌታ ዐበይት በዓላት የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው (ዐቢይነታቸው በአከባበራቸው ነው):-
√ በዓለ ጽንሰት (ትስብእት) መጋቢት ፳፱
√ በዓለ ልደት (ታኅሣሥ ፳፱)
√ በዓለ ጥምቀት (ጥር ፲፩)
√ በዓለ ሆሣዕና
√ በዓለ ትንሣኤ
√ በዓለ ዕርገት
√ በዓለ ጰራቅሊጦስ
√ በዓለ ደብረ ታቦር (ነሐሴ ፲፫)
√ በዓለ ስቅለት
፲) የጌታ ንዑሳት በዓላት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው
® መስቀል (መስከረም ፲፯ & መጋቢት ፲)
® ስብከት
® ብርሃን
® ኖላዊ
® ጌና (ታኅሣሥ ፳፰)
® ግዝረት (ጥር ፮)
® ልደተ ስምዖን (የካቲት ፰)
® ደብረ ዘይት
® ቃና ዘገሊላ (ጥር ፲፪)
፲፩) የልደትና የጥምቀት ቁርባን በመንፈቀ ሌሊት ይሁን። ይኽውም ስለ ክብረ በዓሉ ነው።
_
፲፪) የትንሣኤን በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ አታክብሩ። እኛን ለማዳን አንድ ጊዜ ስለሞተ በዓመት አንድ ጊዜ አክብሩ እንጂ። የትንሣኤን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታክብሩ። በዶሮ ጩኽት ብሉ። ያም ባይሆን በነግህ ብሉ።
_
፲፫) መዓርገ ቁርባን አምስት ናቸው። እነዚህም:-
√ የትንሣኤ፣የልደት፣የጥምቀት ሌሊት በ፲ ሰዓት
√ በዓለ ኃምሳ እና ቅዳሜ ጠዋት ፫ ሰዓት
√ እሑድ ጠዋት ፩ ሰዓት
√ በሰባቱ አጽዋማት በ፱ ሰዓት
√ የጸሎተ ኃሙስ በሠርክ (፲፪ ሰዓት)
፲፬) በበዓላት ጊዜ በቤተክርስቲያን ተሰብስባችሁ መጻሕፍተ ነቢያትን ኦሪትን እያነበባችሁ፣ ዳዊት እየደገማችሁ አቡነ ዘበሰማያት እያላችሁ ጸልዩ። ለምእመናኑ ሊድኑበት የሚገባውን ንገሯቸው።
_
፲፭) ከትንሣኤ በኋላ በስምንተኛው ቀንም በዓል አክብሩ (ዳግማይ ትንሣኤን ነው)።
_
፲፮) ከሰሙነ ሕማማት እስከ ሰሙነ ትንሣኤ (እስከ ዳግማይ ትንሣኤ) አንድ በዓል ነውና ሥራ አትሥሩ።
_
፲፯) ሐዋርያት ባረፉበት ቀን ሥራ አትሥሩ። ሐዋርያት ክርስቶስን ለማወቅ ያስተማሯችሁ መምህሮቻችሁ ናቸውና። ሀብተ መንፈስቅዱስንም ለመቀበል አብቅተዋችኋልና።
_
፲፰) የተቻለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶድ በሰውነቱ መከራ የተቀበለባቸውን መካናት እጅ ይንሣ። የተነሣበትንም ቦታ ይይ። አምላክ በሠራቸው ግብራት ይከብር ዘንድ። (ሐተታ) መካነ ልደቱን አይቶ በረከተ ልደቱን፣ መካነ ጥምቀቱን አይቶ በረከተ ጥምቀቱን፣ መካነ ትንሣኤውን አይቶ በረከተ ትንሣኤውን ያገኛልና። ለመሄድ የማይቻለው ግን መብዓ ይስደድ። በዚያው የሚኖሩ ሰዎች ይረዱበት ዘንድ።
_
አንቀጽ ፳
አንቀጽ ፳ ስለ ሰማዕታት ይናገራል።
፩) ሰማዕታት በእናንተ ዘንድ የከበሩ ይሁኑ። በጌታ ስም ስላመነ በሃይማኖት ስለፀና ወደ መከራ ሥጋ የሚያገቡት ክርስቲያናዊን ከመርዳት ቸል አትበሉ። ምንም የሌላችሁ ብትሆኑ እንኳ ስለእነርሱ እናንተ ግማሽ እየበላችሁ የምግባችሁን ግማሽ ስጧቸው።
_
፪) ሰማዕታት የክርስቶስ የመከራው ተሳታፊዎች፣ የመንፈስቅዱስ ማደሪያዎች ናቸው። የሰማዕታት ምስክራቸው ክርስቶስ ነው። ሰማዕታትን ከሚረዳቸው ሰዎች አንዱን መከራ ቢያገኘው ንዑድ ክቡር ይባላል። የሰማዕታት የመከራቸው ተባባሪ ሆኗልና። ክርስቶስን መስሎታልና።
_
፫) ሃይማኖት አንለውጥም ስላሉ ከሀገር አስወጥተው የሚሰዷቸውን (የሚያሳድዷቸውን) ተቀብላችሁ ከረኀብ ከጥም አሳርፏቸው። በተቀበላችኋቸው ጊዜ ደስ ይበላችሁ።
_
፬) ጌታ በዚህ ዓለም መከራ ኀዘን ያገኛችኋል ብሎናል። እስከመጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል። ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን የወደደ ሰው ይቅርታውን አያገኝም። የሰው ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ሊሆን ወዷልና።
_
፭) ሥጋችሁን የሚገድሉትን ሰዎች አትፍሯቸው። ነፍሳችሁን ግን መግደል አይቻላቸውም። ይህንን ዓለም አትውደደው። በሰው መመካትን ተው። ከአለቆች ውዳሴ ከንቱን አንቀበል።
_
፮) ለሌሎች ሰዎች የክህደት አብነት እንዳንሆን ወንድሞቻችንን በሃይማኖት በምግባር እናጽናቸው። በመከራ ብንጨነቅ በኃላፊው ዘመን የሚሆነውን መከራ ፈርተን ሃይማኖታችንን አንለውጥ።
_
፯) ሰው አምኖ ሳይጠመቅ መከራ ቢደርስበት አይዘን። በክርስቶስ ስም አምኖ የተቀበለው መከራ የተወደደ ጥምቀት ይሆንለታልና። እስመ ተጠምቀ በደሙ (ለክርስቶስ) እንዲል።
_
፰) ዓላውያንን ፈርቶ በግድ የካደ ሰው ቢኖር በኋላ ንስሓ ቢገባ ንስሓውን ይቀበሉት። ካህን ከሆነም ቅዳሴ ከመግባት አይከልከል። ይህን ወዶ አላደረገውምና። መከራ ሳያጸኑበት ገንዘቡን ሳይወስዱበት ፈርቶ አስቀድሞ የካደ ቢኖር ብዙ ዘመን በንስሓ ይኑር። ከዚያ በፍጹም ልቡናው ቢመለስ ሥጋውን ደሙን ሊቀበል ቢወድ ያቀብሉት።
_
፱) በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ደማቸውን ስላፈሰሱ ሰዎች ሁሉ በአረፉባት ቀን መታሰቢያ ያድርጉላቸው። የሰማዕታት መቃብር በቤተክርስቲያን ዙሪያ ይሁን። አንድም በቅድስት ይሁን። ቤተክርስቲያን በሰማዕታት አፅም የምትከብር ሆና አይደለም። ሰማዕታት ከቤተክርስቲያን ክብርን ያገኛሉ እንጂ። ቤተክርስቲያን ክብር አላትና።
_
፲) የሰማዕታት ገድላቸው ታሪካቸው ሰማዕት በሆኑባት ዕለት ይነበብ።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲፮ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፮___
አንቀጽ ፳፩ ስለ ድውያን (በሽተኞች) ይናገራል።
፩) የታመመ ሰው ቢኖር ይጸልዩለት ዘንድ ቀሳውስትን ይጥራ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ይቀቡት ዘንድ። አምነው የሚጸልዩት ጸሎት የታመመውን ሰው ያድነዋልና። ኃጢአትም ቢኖርበት ይሠረይለታል።
_
፪) ቀሳውስት ለሕሙማን መጽሐፈ ቀንዲልን እየደገሙ ይቀቧቸው። የታመመን መጠየቅ በምጽአት ጊዜ በቀኝ የሚያስቆም ግብር ነው።
_
አንቀጽ ፳፪
አንቀጽ ፳፪ ስለሙታን ይናገራል።
፩) ሰው ሲሞት ያለ ሀኬት ወደ ቤተክርስቲያን ተሰብሰቡ። ክቡራት መጻሕፍትን አንብቡ። ስላረፉ ሰዎች ዳዊት ድገሙ።
_
፪) ግንዘት ዘሰማዕታት፣ ግንዘት ዘአበው፣ ግንዘት ዘወራዙት፣ ግንዘት ዘሕፃናት፣ ግንዘት ዘአንስት፣ ግንዘት ዘመነኮሳት፣ ግንዘት ዘመምህራን አለ። መዋቲ ሕያውን እኔ እንደእናንተ ነበርኩ እናንተም እንደ እኔ ትሆናላችሁ መሰናበት ይገባዋል። ሕያው መዋቲውንም ሊሰናበት ይገባዋል።
_
፫) ስላረፉ ሰዎች ዳዊት ድገሙ፣ በቤተክርስቲያን መሥዋዕት ሠውላቸው። ዕጣን አቅርቡላቸው። በክርስቶስ አምኖ ለሞተ ክቡር ሞቶሙ ለጻድቃኒሁ በቅድመ እግዚአብሔር፣ ግብኢ ነፍስየ ውስተ ዕረፍትኪ እስመ እግዚአብሔር አሠነየ ለኪ እያልን እንዘምርለታለን።
_
፬) በእግዚአብሔር አምነው የሞቱ ሰዎች ሞተ ነፍስ የለባቸውም። በእግዚአብሔር አምነው የሞቱ ሰዎች አጽማቸው የተናቀ ርኵስ አይደለም። የሞቱ ሰዎችን በድን አጥበን ገንዘን እንቅበር።
_
፭) ሴት በወሊድ በኅርሷ ወራት በሞተች ጊዜ በአራስነቷ ወራትም ብትሞት አጥበው ባልወለደችበት ልብስ ገንዘው ከቤተ እግዚአብሔር አግብተው ይጸልዩላት።
_
፮) ሳይገንዙ መዋቲውን ማጠብ ይገባል። ጴጥሮስ ያነሳት ጣቢታን ከሞተች በኋላ አጥበዋት ነበርና።
_
፯) መዋቲው ካህን ቢሆን ከቤተ መቅደስ አግብተው በታቦቱ ፊት ያሰግዱት። ሟቹ ሕዝባዊ ቢሆን ከቅድስት ከቅኔ ማኅሌት አግብተው ያሰግዱት
_
፰) መዋቲን በመዓርግ በዕድሜ እንደእርሱ ያሉ ሰዎች በተቀበሩበት በክቡር ቦታ ይቅበሩት።
_
፱) ስለሞቱ ሰዎች ተዝካር አድርጉላቸው።
√ በዕለቱ
√ በሦስተኛው ቀን
√ በሰባተኛው ቀን
√ በዘጠነኛው
√ በአሥራ ሁለተኛው
√ በአሥራ አራተኛው
√ በሠላሳው
√ በአርባው
√ በስልሳው
√ በሰማንያው (መጽ. ግንዘት)
√ በመንፈቅ
√ በዓመቱ
ዕለት የሁሉ ነው። በሣልስት ቢታጎል በሦስተኛው ሣልስት በዘጠነኛው ቀን ያስቆርቡለት። በሰባት ቢታጎል በሁለተኛው ሱባዔ በአሥራ አራተኛው ቀን ያስቆርቡለት። አሥራ ሁለት የሁሉ ነው። ሠላሳው ቢታጎል በሁለተኛው ሠላሳ በስሳ ቀን ያስቆርቡለት። በአርባ ቢታጎል በሁለተኛው አርባ በሰማንያ ያስቆርቡለት። በመንፈቅ ቢታጎል በዓመት ያስቆርቡለት ማለት ነው።
_
፲) መታሰቢያ ሊሆነው ከሟች ገንዘብ ለነዳያን ስጡ መጽውቱ። ከተቻላቸው 40ውን ቀን ሁሉ ያስቆርቡለት።
_
፲፩) ሲገንዟቸው ባሕታውያንን እጃቸውን ከዓይናቸው ላይ ጥለው ይገንዟቸዋል። ቀሳውስትን እጃቸውን አመሳቅለው ይገንዟቸዋል። ዲያቆናትን እጃቸውን ከአንገታቸው ላይ ጥለው ይገንዟቸዋል። ሕጋውያንን እጃቸውን ከአባላ ዘርዓቸው ላይ ጭነው ይገንዟቸዋል።
_
፲፪) መቃብር ስለሚቆፍሩ ሰዎች ዋጋቸውን ከመስጠት አንዱስ እንኳ ቸል አይበል። መቃብሩን ለሚቆፍሩት፣ መቃብሩን ለሚጠብቁት ሰዎች ዋጋቸውን ይስጧቸው። ኤጲስ ቆጶሱ ለቤተክርስቲያን ከሚሠጠው ገንዘብ ይመግባቸው።
_
፲፫) ስለሞቱ ሰዎች የቀቢጸ ተስፋ ኀዘን እንደሚያዝኑ አሕዛብ ልናዝን አይገባንም። ካህን ከዘመዶቹ አንዱ ቢሞትበት ልብሱን አይቅደድ፣ ዘወትር ዬ ዬ ብሎ አያልቅስ፣ ራሱን አይላጭ ፊቱን አይንጭ፣ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያመስግነው እንጂ።
_
ፍትሕ መንፈሳዊ ተፈጸመ
አነሳስቶ ላስጀመረን
አስጀምሮም ላስፈጸመን
ልዑል እግዚአብሔር
ምስጋና ይገባል አሜን
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
መ/ር በትረማርያም አበባው።
©©©© ©©©©
__ፍትሐ ነገሥት የፍቅር ሕግ ነው_
እነሆድ አምላኩ ጹሙ ሲባሉ የተጨቆኑ ይመስላቸዋል። ሰነፎች ጸልዩ ሲባሉ ጭቆና ይመስላቸዋል። አንዳንዶች ፍትሐ ነገሥትን እንደ ጨቋኝ አድርገው ሲያቀርቡ ሳይ አዝናለሁ። ፍትሐ ነገሥት አካሏ ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነላት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ፍትሐ ነገሥትን ጨምሮ ሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት መሠረታቸው ክርስቶስ ነው። በጠቅላላው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጠባብ በር ናት። በሥርዓት በመንፈስ የሚመሩባት ናት እንጂ በሥጋ ፍላጎት የምትመራ አይደለችም። የልቆች ሃይማኖት አይደለችም። ሑሩ እንተ ጸባብ አንቀጽ እንዳለ ክርስቶስ። ቅዱሳን ሊቃውንት በመንፈስቅዱስ መሪነት የሠሩልን ሥርዓት ነው።

ሥርዓት እንደየዘመኑ ሊቀየር ይችላል የምትለዋን ብቻ ይዞ በራስ ፈቃድ ለመቀየር የሚፈልጉ ትንንሽ ሰዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል። በዚህ ሥርዓት ቤተክርስቲያን ከ1600 ዓመታት በላይ ስትመራበት ቆይታለች። ለመሆኑ አሁን ይህንን ለመቀየር የሚያበቃ ምን ምክንያት ተገኝቶ ይሆን!? ሠለስቱ ምእት ለዘመናቸው ምእመናን ይህንን ከሠሩ በአሁኑ ዘመን ያሉ ምእመናን በዚያ ዘመን ካሉ ምእመናን በምን ያንሳሉ? የፍትሐ ነገሥቱን ሥርዓት እንዳንፈጽም የሚያደርገን ምን ምክንያት ተገኘ!? በእርግጥ ፍትሐ ነገሥቱ ደረቴ ይቅላ ሆዴ ይሙላ ለሚሉ ሰባክያን አይመችም። ታዲያ ፍትሐ ነገሥቱን ወደእነዚህ ሰዎች ስሜት ማውረድ ይገባል ወይስ ሰዎችን ወደፍትሐ ነገሥት ሥርዓት ከፍ ማድረግ!?

እስኪ ከፍትሐ ነገሥት ከባድ ነው የምትሉት ሥርዓት አንድ ጥቀሱ!? እውነት ከባድ ሆኖ ነው ወይስ ለሥጋ ስላልተመቸ!? ለሥጋ የሚመች ሥርዓት ፈልጋችሁ ነው ይሆን!? ጾም የከበደው ሰው ስለ ሰማዕትነት ለማስተማር ምን ሞራል አለው?? ንጉሥ የወደደውን ዘመን ያነሣውን የሚል ሰባኪ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ለመስበክ ምን ሞራል ይኖረዋል!? እንደ ጳውሎስ መኑ የኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል! ተሰዶኑ መጥባሕትኑ ረኀብኑ ለማለትኮ የበቃ አይደለም። ትክክለኛ ሰባኪ ክርስቶስ ለሰበከው እውነትና ፍቅር ይኖራል እንጂ በአድርባይነትና በአጨብጫቢነት እውነትን አይጨቁናትም። ለእውነት ይኖራል። እውነትን ይዞ ይሞታል እንጂ ስለሰው ብሎ እግዚአብሔርን አይክድም።

ፍትሕ ሥጋዊን ከበዓል በኋላ እንማማረዋለን። ውድ ክርስቲያኖች መልካም በዓል ይሁንላችሁ።
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#የሰሙነ_ሕማማት_ሰኞ

#መርገመ_በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

#አንጽሆተ_ቤተ_መቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፦

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/09/24 16:34:20
Back to Top
HTML Embed Code: