Telegram Web Link
- የማይታወቅ አምላክ (Ἄγνωστος Θεός) -

|ጃንደረባው ሚዲያ - መስከረም 2016|
✍🏽 መ/ር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ፈለቀ እንደጻፉት

ክርስትና በመላው ዓለም መሰበክ ከጀመረ ከዐሥር ዓመት በላይ ቆየት ብሎ ወደ ሐዋርያት ተልእኮ ከተቀላቀሉት የጌታችን ምስክሮች ደቀመዛሙርት አንዱ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአሕዛብ ዘንድ ስሜን የሚሸከም ምርጥ (ኅሩይ) ንዋይ የተባለ የተጠራበትን ተልእኮ እስከ መጨረሻው ዳርቻ ለማድረስ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የወንጌልን ቃል በቃል፣ በጽሑፍና በተግባር አዳርሷል፡፡ የሐዋርያው የወንጌል ተልእኮ ለእኛ ትውልድ ትልቅ መልእክት አለው፡፡ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ተልእኮ ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ በዘመኑ ለነበሩት የዕውቀት ደረጃዎች፣ የማኅበራዊና ባህላዊ ክስተቶች፣ የቋንቋና የአገዛዝ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት አገልግሎቱን እየመጠነ የፈጸመ ታላቅ ተልእኮ መሆኑ ነው፡፡

የሐዋርያው የወንጌል ተልእኮ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በመላው የግሪክ ወሮም ግዛት ለሚኖሩ ከልጅ እስከ አዋቂ የእድሜ ክልል ላላቸው ነዋሪዎች፣ የወቅቱን የሥልጣኔ ትምህርት ለተማሩም ላልተማሩም፣ ለባለሥልጣኖቹም ሆነ ሥልጣን ለሌላቸው፣ ለአይሁድ ሊቃውንትም ሆነ ሕግ እናውቃለን ብለው ለሚመኩ ፈሪሳውያን፣ ለብሉይ ኪዳን ተርጓሚዎችም ሆነ ለጸሐፍት፣ ለወታደሮችም ሆነ ለልዩ ልዩ ባለሙያዎች፣ በዘመኑ የረቀቀ የፍልስፍና ትምህርት እንከተላለን ለሚሉት ሳይቀር እንደየዕውቀትና ሥልጣን ደረጃቸው፣ እንደየማኅበራዊ ኑሮ ክፍላቸው የሚሆን ትምህርት ማስተማሩ እና የወንጌልን ዕውነት ማሥረጹ፣ የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብርና ጌትነት በአስደናቂ የቋንቋና የንግግር ችሎታ መግለጹ ለእኛ ትውልድ ትልቅ አርኣያነትና ምትክ የሌለው አንድምታ አለው፡፡

ያለንበት ዘመን በመላው ዓለም ማለት ያቻላል በርካታ መንፈሳዊና ቁሳዊ፣ ዓለማዊና አምላካዊ፣ ምድራዊና ሰማያዊ፣ ትምህርቶች በየቦታው ሳይለያዩ የሰፈኑበት፣ ዕውነቱ ከሐሰቱ ፣ የሚጠቅመው ከማይጠቅመው፣ በአንድነት ተዘበራርቆ፣ ተሰበጣጥሮ የሚገኝበት ነው::

በአንድ የቴሌቪዥን ሥርጭት ወይም በአንድ የመረጃ ማሰራጫ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች፣ የማኅበራዊ ፍልስፍናዎች፣ ወቅታዊ ዜናዎች በልዩ ልዩ ቋንቋና አገላለጽ፣ ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው ፍርዱ ለሰሚና ለተመልካች ተብለው ይቀርባሉ:: የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ሊያገኛቸው የሚገቡ የመረጃ አቅርቦት ፍትሐዊነትን ለማሳካት ሲባል መንግሥታት ለሁሉም እኩል እድል በመስጠት አንዱ አንዱን ሳይነቅፍ፣ ሳይተችና በሌላው ላይ ተጽኖ ሳይደርግ የራሱን ትምህርት መግለጽ እንዲችል መብት በመስጠት ፣ በማቻቻልና በማከባበር ላይ የተመሠረተ መድረክ በዓለም ላይ በመፈጠሩ ሃይማኖቱን በጥልቀት የተረዳ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር በቃልና በሕይወት መግለጽ የሚችል፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቀት ክህነት በተጨማሪ የዘመኑን አስተሳሰብ የተረዳ አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ሳንወድ በግድ በዓለማዊ ፍልስፍናም ሆነ ከእኛ ባዕድ በሆነ ትምህርት ተጽዕኖ ሥር መወደቃችን አይቀርም፡፡

ለዚህ የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌ መከተል ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታችን ዕርገት ጥቂት ዓመታት ቆይቶ በፍልስፍና ትምህርት የበለጸገች፣ የገናኖቹ የግሪክ መንግሥታት መናኽሪያ፣ የዛሬው የምዕራባውያን ሥልጣኔ ምንጭ ተደርጋ ወደምትወሰደው እና በዘመኑ የዕውቀቶች ሁሉ ቁንጮ ወደ ሚገኘባት ወደ አቴና ደረሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና ሌሎች ደቀመዛሙርትን ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር። (የሐዋ17፡17)፡፡

በዚህ ዘመን ገናና የነበሩ ሁለት የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ደቀመዛሙርት በአቴና ነበሩ፡፡ እነርሱም ኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢክ የተባሉት ፈላስፎች ሲሆኑ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጋር ተገናኙ። ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜም አንዳንዶቹ "ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል?" አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። "አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል" አሉ። (የሐዋ 17፡18)

ኤፊቆሮስ እና ኢስጦኢክ የተባሉት ፈላስፎች እነማን ናቸው? ቅዱስ ጳውሎስስ እነዚህን ፈላስፎች እንዴት ሊገናቸው ቁርጥ ውሳኔንን ወሰነ? የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኤፊቆሮስ ያላቸው የቀድሞው የግእዝ ስያሜን በመያዝ ሲሆን በራሳቸው አጠራር Epicureanism ኤፒሬክሬንዝም ይባላሉ፡፡ እነርሱም እንደ ፕላቶ (አፍላጦን)፣ አሬስቶትል (አርስጣጣሪስ)፣ የመሰለ የፍልስፍና ትምህርትን ባስተማረ ኤፒኩረስ በተባለ ፈላስፋ ከክርስቶስ ልደት 307 ዓመታት በፊት የተጀመረ ትምህርት ነው፡፡ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየዘመኑ በነገሡ የግሪክ ነገሥታት ተሰሚነት የነበራቸው፣ ከግል ጥቅማቸው ይልቅ ለማኅበረሰብ ጥቅም የሚያደሉ ያንንም በማድረግ ደስታ የሚሰማቸው፣ ደስታም የሕይወታቸው ዐቢይ ትርጉም አድርገው የሚያምኑ ተናጋሪዎችና በየጊዜው የአቴና ነዋሪዎችን በሕይወት ፍልስፍና እየማረኩ አዳዲስ ነገሮችን የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡

በተጨማሪ በዚሁ አኳያ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኢስጦኢክ ብሎ ያስቀመጣቸው ሌሎቹ የፍልስፍና ቡድኖች እንዲሁ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጆች በኤስጦይኮች ዘንድ ግን ባላንጣዎች የነበሩ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ ከሮም፣ ወይም ከአረብ ወይም ከአፍሪካ ወደ አቴና ለሚመጣ ለመጤ ትምህርት ግን ተባብረው መልስ ይሰጡ ነበር፡፡ Stoicism (ስቶይሲዝም) የሚባለው የአሕዛብ የፍልስፍና ትምህርት የተመሠረተው በአቴና ከተማ ነዋሪ በነበረው በዜኖ ነው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት 300 ዓመት በፊት ነበር፡፡ የእነዚህ ፈላስፎች ትምህርትም ከፍትሕ መጉደል የሚመጣው የአጥፊነት ባሕርይ የሰውን የተረጋጋ አኗኗርና ዘለቄታዊ ደስታ ስለሚነሱ የሰው ልጅ እነዚህ ነገሮች በግሉ ለማስወገድ የተረበሸ ስሜትንና የተመሰቃቀለ የአእምሮ ፍትሕንና ሚዛናዊ ያልሆነ አስተሳሰብን መለማመድ የለበትም ይላሉ፡፡

እነዚህ ፈላስፎች እና የፍልስፍና ትምህርት ቤታቸው ከክርስትና ሦስት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ባላቸው ቅድምናም ይሁን ተሰሚነት በዘመናቸው በነበረውም ኅብረተሰብ የአዋቂዎች ሁሉ ዳርቻ ተደርገው መወሰድ ለቅዱስ ጳውሎስ አስፈሪ አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህ የአቴና ጠበብት ለመጋፈጥ ያስቻለውን ወኔ ከየት አገኘ ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የመጀመሪያው ምንም እንኳ የቦታ ርቀት ቢወስነው የእነዚህ ፈላስፎች ትምህርት ለኢየሩሳሌምና ከኢየሩሳሌም ውጭ ለነበሩ አይሁድ እንግዳ አልነበረም ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹን የፍልስፍና ደቀመዛሙርት በአይሁድ የታልሙድ ድርሰቶች ሳይቀር የታወቁ ነበር፡፡

ይልቁንም ዕብራውያን የትርጓሜ መጻሕፍት የኤፊቆሮስ ትምሀርትና ተከታዮች (አፒቆሮስ) ወይም መ*#* በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከታዋቂው የረበናት ወገን ምሁር ገማልያል ሥር የተማረ ስለነበር ስለ እነዚህ ሰዎች በመጠኑ ሊያውቅ ይችላል፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የቋንቋ ችሎታው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህ ፈላስፎች የሚናገሩትን የግሪክ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሚፈላሰፉበትን የዕውቀት ቋንቋ ሳይቀር ያውቅ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ግን መሠረታዊ ትምክህቱ በክርስትና ያገኘው የሐዲስ ኪዳን ዕውቀትና በጌታን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ትምክህት ነው፡፡ ስለሆነም የክርስትና ትምህርት ዓለም ለሚያነሣው ጥያቂ ብቁ
መሆኑን ከመረዳት አልፎ በተግባር አሳይቶበታል፡፡

ይልቁንም ሐዋርያው የሚያስተምረው የትምህርት ርቀት ከእነርሱ ፍልስፍና በላይ ስለሆነና የሚረዱትም ስላልመሰላቸው በትምህርቱ የተገረሙት እነዚህ ፈላስፎች ቅዱስ ጳውሎስን ይዘውት "ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና፤ እንግዲህ ይህ ነገር ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እንፈቅዳለን" ብለው አርዮስፋጎስ ወደ ተባለው ስፍራ ወሰዱት። (የሐዋ ሥራ 17፡20)

ሐዋርያውን ወደ አርዮስፋጎስ የወሰዱበት ዋና ምክንያት የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና ነው። (የሐዋ ሥራ 17፡21)፣ አርየስፋጎስ (Areopagus) የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት የተገኘ Areios (Ἄρειος) (ትርጉም ቋጥኝ/ፀሐይ) እና Pagos (Πάγος) ምኩራብ፣ ሸንጎ ማለት ነው፡፡ በጥንታዊቷ ግሪክ የፍርድ ሸንጎ በመሆን አገልግሏል፡፡ ስለዚህ በዚህ ኮረብታማ አካባቢ በየቀኑ አዳዲስ የፍርድ ውሳኔዎች ከመሰማት በላይ የተለያዩ የግሪክ ጥንታውያን የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ደቀ መዛሙርት እና መምህራኖቻቸው የፍልስፍና ትምህርታቸውንም ያሰሙበት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን ወደዚህ ቦታ የወሰዱበት ምክንያት ግን የተናገረውን ልዩ ትምህርት ለመሰማት ከመፈለግ ያላለፈ ነበር፡፡

ምናልባትም የትምህርቱ አዲስነት ብቻ ሳይሆን ከእነሱ የተሸራረፈና በተፈጥሮ ምረምርና መላምት ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና የሚያፈራርስ የአዲስ ኪዳን ብሥራት ወንጌልን ይዞ በመሄዱ ባልተገባ ስሕተት ወንጅለው ፍርድ ለማሳለፍ ጭምር መሆኑ ወደ ሸንጎ በመውሰዳቸው ይታወቃል፡፡

የክርስቶስ ሐዋርያ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ይሸከም ዘንድ የተመረጠ፣ በሰይፍ ስለት ፊት ቆሞ የጽድቅ አክሊሉን የተቀበለ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም ዓለማዊው ፍልስፍና እና የአቴና ባለ ሥልጣናት ግርማ ሳያስፈራው በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ
"የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ :- ለማይታወቅ አምላክ (Ἄγνωστος Θεός) የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ" አላቸው፡፡ (የሐዋ ሥራ 17፡ 22-23)

ቅዱስ ጳውሎስ የእነዚህ ፈላስፎች የትምህርት መሠረት በሚገባ የተረዳ መሆኑን የሚያሳየው ዐቢይ ጉዳይ በመጀመሪያ የተናገረው ‹‹አማልክትን እንደምትፈሩ›› የሚለው ሐረግ ነው፡፡ አንድ ሐዋርያ ትምህርቱን ከመጀመሩ በፊት የሚያስምራቸውን ሰዎች የዕውቀትና የኑሮ እንዲሁም የአምልኮትና የአስተሳሰብ ሁኔታ በሚገባ መረዳት አለበት፡፡

ሐዋርያው በመጀመሪያ በከተማዎ የሞላውን የብዝኀ አማልክት ሥርጭት እና ለአማልክቱ ሕዝቡ፣ ሹማምንቱና ሊቃውንቱ ያላቸውን መሠጠት በሚገባ ተረድቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛዎቹ የግሪክ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአማልክት የሚሰጠውን ከበሬታ ከትምህርታቸው ተረድቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቱን ከመጀመሩ በፊትም ከተማዋን ተዘዋውሮ መጎብኘቱን ‹‹በከተማዋ የማምለኪያ ቦታዎች ማለፉን›› ገልጧል፡፡ ከማለፍም አልፎ ተርፎ መሥዋዕት ወደሚቀርብላቸው የአማልክት ምስሎች ሲመለከት አንድ ምልክት ቀልቡን ስቦታል፡፡ ይኽውም ምልክት በመስቀል ላይ የተሰቀለ ሰው ምስል ያለበት መንበር እና ከመንበሩ ሥር የተጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ አቴና ከመድረሱ ዐሥር ዓመት በፊት የአቴና ፈላስፎች በእሥራኤል አንድ ከሰማይ የወረደ ደግ መምህር ተነሥቶ ብዙ መልካም ነገሮችን እንዳደረገ ከዚያም ክፉ ሰዎች ሰቅለው እንደገደሉት፣ እሱም ከሞታን እንደተነሣ ሰምተው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ስለዚህ ሰማያዊ ደግ ሰው አምላክነት፣ በአስደናቂ ተአምርና በተዋሕዶ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን፣ የመሰከረላቸው፣ የጌታችንን ትምህርቱን፣ የፈውስ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን፣ የመንፈስ ቅዱስን መላክ የነገራቸው ስለሌለ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ መሰቀሉን በሰሌዳ ብርሃን፣ አይተው ነበርና ያንኑ ቅርጽ ሠርተው የማይታወቅ አምላክ ብለው በመጻፍ ለሌሎች አማልክቶቻቸው እንደሚያቀርቡት ያለ መሥዋዕትን ያቀርቡ ነበር፡፡

በግሪኮች የማያውቋቸውን አማልክት፣ ወይም ከሌላ ዓለም የሰሟቸውን አማልክት፣ በርግጥ የተመደ ነበር ግን ይህንን በተለየ መልኩ የማይታወቅ አምላክ ያሉትን የተሰቀለውን የክርስቶስን ምስል ከማምለክ አልፈው የማይታወቅ አምላክን ወይም በማይታወቅ አምላክ ስም (Νὴ τὸν Ἄγνωστον፤ ኔ ቶን አግኖስቶን) እያሉ ይምሉበት ጀምረው ነበር::

ሐዋርያው ያንን ሲመለከት "እኔ እናንተ የማይታወቅ ያላችሁትን አምላክ አውቀዋለሁ፣ ሳታውቁት የምታመልኩትንም አውቃችሁ እንድታመልኩት አስተምራችኋለሁ" አላቸው፡፡ ሐዋርያው በዚህ ጉዳይ ትምህርቱ ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ ሲል ብዙ ምሥጢርን ነግሮናል፡፡ እነዚያ ግሪኮች የአቴና ሰዎች አማልክትን ከመፍራት አንፃር ብቻ የማያውቁትንም አምላክ ምስሉን አቁመው ያመልካሉ፡፡ ስሙን አያውቁትም፣ ትምህርቱን አልሰሙም፣ በተአምራቱ ከሥጋ ደዌ አልተፈወሱም፣ በትምህርቱ ከነፍስ ቁስል አልዳኑም፣ በጥምቀቱ ልጅነትን፣ በትንሣኤው ተስፋን አላገኙም፡፡ ግን የማይታወቅ አምላክ ብለው መሥዋዕት ይሰዋሉ፣ ይምላሉ ቃልኪዳን ይገባሉ፡፡

ወደኋላ እንመለስበታለን አንጅ ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት አለው፡፡ ስሙን ከማወቅ አልፈን ክርስቲያን ተብለን እየተጠራንበት አቤት ካላልን፣ ትምህርቱን እያነበብን፣ እየሰማንና እያሰማን ካልተለወጥን፣ ከዓለማዊ የሥጋ አስተሳሰብ ሳንወጣ፣ የመንፈስ ልጅነትን ሥራ ሳንሠራ፣ ለትንሣኤ የሚያበቃንን ምግባር ስንቅ ሳንይዝ እንዲሁ በአካላዊ አፍአዊ እንቅስቃሴ ከተወሰንን ዛሬ የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ለአሕዛብ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ያስፈልገናል፡፡

እኔ ክርስቶስን እንደመሰልኩት እናንተም እኔን ምሰሉ ብሎ የክርስቶስን ምስል በሕይወቱ ቁመና ሥሎ አምላኩን በመምሰል ለሚያስምራቸው ሁሉ የክርስቶስ ምስል በሕይወቱ መስታወት የሚገለጽ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ የግሪክ ፈላስፎችን የሦስት መቶ ዓመታት ረቂቅ ፍልስፍና ሳያስፈራው ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። (የሐዋ ሥራ 17፡24- 27)

ሐዋርያው በዚህ ትምህርት የሁሉ መገኛ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ እንጅ ብዙ አማልክት አለመሆናቸውን፣ እሱም ከሰዎች ሕይወት ርቆ በጠባብ ቤት ብቻ ተወስኖ በዚያ አትክልትና ፍራፍሬ ሻማና ጧፍ እየቀረበለት በትናንሽ ሥጦታዎች ብቻ እየተገለገለ የሚኖር ሳይሆን በሰዎች ሕይወት ውስጥ የልጅነት ሀብትን ሰጥቶ፣ እሱ የዘላለም አባት ሆኖ፣ የሚመለክ፣ በቅዱሳን ሕይወት ለዘለዓለም እያበራ የዘለዓለም መንግሥትን የሚያወርስ አምልክ ሰዎችንም ከአንድ ዘር ፈጥሮ ያበዛ ሁሉንም በጊዜና በቦታ ወስኖ እርሱ ግን
ዘለዓለማዊ እና በሁሉ ቦታ የሰፍኖ የሚኖር፣ አምላክ መሆኑን ተናገረ፡፡

ይህንን ያለበት ሁለት ምክንያች አሉት፡፡ በሁለቱ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ትምህርት መሠረት "ቁስ አካል፣ አማልክትም ሆኑ ነፍስ ከአንድ ነጠላ ሕዋስ የተፈጠሩ ናቸው" ብሎ ያምናል" ይሁን አንጅ የአማልክት ነፍስ ከረቂቅ አካላቸው ጋር እንዳታመልጥ ሆና የተሰፋች ስለሆነች አማልክት ለዘላለም ይኖራሉ የሰው ነፍስ ግን ከግዘፍ አካሉ ጋር ያላት ግንኙነት የላላ ስለሆነ ነፍስን ለዘለዓም ይዞ መቆት አይችልም ስለዚህ ሰው ይሞታል ዳግመኛም አይነሣም" ብለው ያምናሉ፡፡

በተጨማሪም "ደስታን የሕይወት መለኪያ አድርጎ መውሰድ በሥነ ምግባር የታጀበ፣ ያልተወሳሰበ ሕይወት የትልቅ ደስታ ምንጭ ነው" ብለው ያስተምራሉ፡፡ "ምኞትን መቀነስ ፍላጎትን መግታት፣ ከአካላዊ ደስታ ይልቅ የሥነ ልቦና ደስታን መሻት፣ ለሰው ልጅ የሕይወት ትርጉም ብቻ ናቸው እንጅ ቁስ የተባለ ሁሉ በቦታና በጊዜ የተወሰኑ በመሆኑ የደስታ ምንጭ ሊሆን አይችልም" ይላሉ፡፡

ቁስ አካላት ከተወሰነላቸው ጊዜና ቦታ ውጭ መሆን አይችሉም እድሜያቸው በጊዜ እንቅስቃሴአቸው በቦታ የተገደበ ነው፡፡ ሰው በራሱ ቁሳዊ ነው ነፍሱ ስትለየው ሕይወትን ያቆማል፣ ሌሎቹ ቁስ አካላት የራሳቸው የሆነ ገደብ አላቸው አማልክት ከቁሳዊ ሰዎች ጋር በነፍስ ይዛመዳሉ፣ እነሱ ግን ነፍስ ከረቂቅ አካላቸው ጋር እጅግ የተጣበቀች ስለሆነች ዘለዓለማውያን ናቸው፡፡ አማልክትንም የምንፈራው እነሱ የማይሞቱ ስለሆነና እኛ ሞት አጥብቀን ስለምንፈራ ነው ይላሉ፡፡

ሁለቱ ትምህርት ቤቶች በብዙ ጉዳዮች የሚለያዩ ሲሆን በእነዚህ ትምህርቶች መጠነኛ መቀራረብ አላቸው ስለዚህ ሐዋርያው ለእነዚህ ፈላስፎች ሊያስተላልፍ የፈለገው እጅግ ብዙ ረቂቅ ትምህርት ቢኖርም ዋናዎቹና ከላይ በግልጽ የምናያቸው አንደኛው "ሰዎች ከአምላክ ጋር ዝምድና ካላቸው አምላክን ከእነሱ አሳንሰው በወርቅና በብር ወስነው ማስቀመጥ እንደሌለባቸው" ሲሆን፡፡ ቅኔያቸውንም ሳይቀር በመጥቀስ "ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም" (የሐዋ ሥራ 17፡ 28-30) ሲል የሥነ ፍጥረቱ በጊዜና በቦታ መወሰን የፈጣሪ ፈቃድ እንጅ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የማነስ ጉዳይ አለመሆኑን በመግለጽ ክርስትና ከአቴና ፍልስፍና የተሻለና ፍጹም የሆነ የሥነ ፍጥረት ትንታኔ እንዳላት በማሳየት ፈላስፎቹን ከነተከታዮቻቸው መማረክ ነው፡፡

ዕብራዊው ቅዱስ ጳውሎስ የአሕዛብን በጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ ቅኔ ውስጥ የተደበቀ ፍልስፍናና ትምህርት ሳይቀር ፈትቶ ሰው ከፈጣሪ ጋር ያለውን ዝምድና በምሥጢረ ሥጋዌ አስተማረ፡፡
ስለዚህ ሐዋርያው ቀጥሎ እንዲህ አለ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። አላቸው፡፡ (የሐዋ 17፡31)

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው የቅዱስ ጳውሎስ የትንሣኤ፣ የእውነተኛ ፍርድ፣ የአምላክ ኃያልነት ትምህርት በእነዚህ ፈላስፎች ዘንድ እጅግ የማይወድ ይልቁንም የሰውን ልጅ ደስታ ከሚፈታተኑት ነገሮች ውስጥ ሁለቱ ትላልቅ ጉዳዮች የአማልክት ፍርሃትና የሞት ጭንቀት ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ሊሰሙት አልፈለጉም፡፡ በተለይ ስጦይቆች ስለ ፍርድ እጅግ ይጨነቃሉ፣ ፍርድ ከተዛባ ደስታ አይኖርም ስለዚህ ሕይወት ግቧን አትመታም ይላሉ፡፡ ኤፌቅጠሮሶች ደግሞ ስለሞት መጨነቅ እና ማሰብ ደስታን ይፈትናል፣ ተስፋ ያስቆርጣል ብለው ስለሚያምኑ ስለተንሣኤ መመራመር አይፈልጎም፣ በትምህርታቸው ነፍስ ከሥጋ ከተለየች በኋላ ተመልሳ የመዋሐድ ዕድል የላትም ይላሉ ስለዘህ ትንሣኤ ሙታንን አያምኑም፣ ከዚህ የተነሣ የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ ጉዳዩ ያልገባቸው ወይም የትንሣኤ ሙታንን ማመን ማለት ከአሁን ቀደም አምነው ሲያስተምሩት የነበረውን የፍልስፍና ትምሀርት በሙሉ የሚያፈራረስባቸው ስለመሰላቸው አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን በአዲስ ኪዳን ትምህርት የተመሰጡት በይበልጥም ወደ ውስጥ ገብተው ለመመርመር ፍላጎት ያላቸው ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። (የሐዋ 17፡ 33)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ባስተማረበት በዚህ ቀን ወዲያው ያመኑ ነበሩ፣ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠትና በማፌዝ የዘገዩ ነበሩ፣ በሦስተኛ ደረጃም ደግመን እንሰማሃለን ብለው ቀጠሮ የሰጡ ነበሩ፡፡ በወንጌል ተልእኮ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል አንዳስተማረን በገር መሬት ላይ እንደወደቀ ዘር ወዲያው ሰምተው በቃሉ ተማርከው ራሳቸውን የሚለውጡ ይኖራሉ፣ አንዳንዶቹ ካስተማርነው ትምህርት ላይ ሲያጉረመርሙ፣ ሲተቹ፣ ሲከራከሩ በአለት ወይም በጭንጫ ላይ እንደወደቀ ዘር ሳይጠቀሙበት ወይ በአእዋፍት ተለቅሞ ወይም የትችትና የፌዝ ቁጥቋጦ ውጦት የሚቀር ይኖራል፣ አንዳንዶች ደግሞ ቆይ እስኪ በደንብ እናጢነው ብለው ወደ ቤታቸው ይዘውት የሚሄዱም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮ መንፈሱን የረበሸውን የአማልክት መንጋ ገሥፆ ከመካከላቸው ወጣ። አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። (የሐዋ ሥራ 17፡ 33-34)

በእኛም ዘመን የማያውቀውን በማምለክ፣ የሚያውቀውን ደግሞ የማይታወቅ በማለት መሥመር በሚያስለቅቁ ትምህርቶችና ልምዶች የተወጠረ ብዙ ሰው አለ፡፡ በተለይ ከምዕራቡ ዓለም በሚፈጠረው የባህል ወረራ፣ በዓለማዊና ቁሳዊ ሐሳብ የሚባክን፣ ዘመናዊው እና ሳይንሳዊ ተብሎ የሚታወቀው ዕውቀት ይበቃኛል ብሎ የሚመካ፣ የዚህ ዓለም ገዥ የተባለው ገንዘብ የደስታ ሁል ምንጭ የፈለጉትን ለማድረግ ቁልፍ መሣሪያ አድርጎ የሚቆጥር፣ መልካም የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ለማግኝት በረሀብ የሚቃትት፣ ዕውነቱንም ሐሰቱንም አንድ ላይ ሰምቶ በመካከል የቆመ፣ በሥነ ምግባር ሥነ ልቦና ሁከት የሚሠራውን ክፉ ሥራ የራሱ መገለጫ አድርጎ የሚታበይ እና ብዙ ዓይነት ሰው ያለበት ትውልድ ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደየአካባቢው የጎሉበት፣ የግልና ጋራ ፍላጎቶች የተምታቱበት ብዙ የኅብረተሰብ ክፍል አሁንም አለ፡፡

ስለዚህ በቋንቋ የበሰሉ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተካኑ፣ ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን ሥልጣኔና የማኅበራዊ ክንውን ደረጃ የተረዱ፣ ሌላውን የሚያከብሩ፣ የራቸውን የሚጠብቁ የወንጌል ልዑካን ያስፈልጉናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ሊቃውንትና ደቀመዛሙርት አድናቂዎችና ተከታዮች ፊት እንዲናገር ሞገስ የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ አገልግሎታችንን ይባርክልን ያስፋልን፡፡

አኮቴት ለስሙ::

ማስታወሻ :- መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የኢኦተቤ የውጪ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ ናቸው::

#የሚከለክለኝ_ምንድን_ነው
#ወደ_ሠረገላው_ቅረብ

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
069
+ መርጦ መወለድ +

ከእገሌ ልወለድ ብሎ መርጦ የተወለደ የለም:: ምረጡ ብንባል ምን ዓይነት ወላጅ እንመርጣለን? ቀድመን የመገምገም ዕድል ቢኖረን ምን ዓይነት ወላጆች እንመርጣለን። መቼም በወላጆቼ ደስተኛ ነኝ የሚል ሰው "እኔ ደግሜም ብወለድ ከአባዬ ከእማዬ ነው መወለድ የምፈልገው" ማለቱ አይቀርም። ግን ደግሞ ዕድሉን ቢያገኝ መቼም ትንሽም ቢሆን የሚያስተካክለው ነገር አይጠፋም። መርጦ መወለድ አይቻልም እንጂ ቢቻል የምንመርጠው ልዩ ምርጫ ይሆናል።

መርጦ የተወለደ ክርስቶስ ብቻ ነው። በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ተመልክቶ መዓዛዋን መርጦ ፣ በቅድስናዋ ውበት ተማርኮ ከእርስዋ ሊወለድ የመረጣት የተመረጠች እናት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። የፈጣሪ ምርጫ እንደ ሰው አይደለም። ሰው ፊትን ያያል እርሱ ግን እስከ ልብ ድረስ ዘልቆ ይመለከታል። እንዴት ብትነጻ ፣ እንዴት ብትቀደስ ነው? እስከ ውስጥዋ ዘልቆ አይቶ ከእርስዋ ሊወለድ የመረጣት? ንጉሥ ውበትዋን የወደደላት ፣ ለእናትነት የመረጣት ቅድስት እንዴት የከበረች ናት?
አዎ መርጦ የተወለደ የለም ፣ ክርስቶስ ግን መርጦ ብቻ ሳይሆን ፈጥሮ የተወለደ ነው። መቅደሱን አንጾ የገባባት እርሱ ነው። መርጦ ለተወለደብሽ ለአንቺ በጸጒራችን ቁጥር ምስጋና እናቀርባለን።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2012 ዓ ም
የግሸንዋን ንግሥት በረከት በመናፈቅ
ሜልበርን አውስትራሊያ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
+ ረቢ ወዴት ትኖራለህ? +

ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::

"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39

ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::

"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)

እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::

የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::

"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::

ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)

ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::

ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ::

አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::

የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2016 ዓ.ም.
ለእመብዙኃን ዝክር የተጻፈ

"ንዒ ማርያም ለዕውር ብርሃኑ
ወንዒ ድንግል ለጽሙዕ አንቅዕተ ወይኑ
ኦ ኦ ተኃድግኒኑ ኦ ኦ ትመንንኒኑ
ኀዘነ ልብየ እነግር ለመኑ"
ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያም
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
††† እንኩዋን ለአበው ሰማዕታት #ቅዱስ_ዮልዮስና_ቅዱስ_ኮቶሎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

†††

††† #ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት †††

=>ከሁሉ አስቀደሞ ስለ ሰማዕታት ዜና ሲሰማ ለዚህ ቅዱስ አንክሮ (አድናቆት): ክብርና የጸጋ ውዳሴ ይገባዋል:: ምክንያቱም ገድለ ሰማዕታትን የጻፈልን እርሱ ነውና:: ነገር ግን መጻፍ ሲባል: ነገሮች እንዲህ እንደ እኛው ዘመን ቀላል እንዳይመስሏችሁ:: ቅዱሱ ዜና ሰማዕታትን ለማዘጋጀት ሃብቱን: ንብረቱን: ቤተሰቦቹንና ሕይወቱንም ሰውቷል::

+ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በመጨረሻው ዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘ) ዓለም በደመ ሰማዕታት ስትሞላ የሰማዕታቱን ዜና የሚጽፍ: ሥጋቸውን እንኩዋ የሚቀብር አልተገኘም:: "ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ-የሚቀብራቸውም አጡ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት:: (መዝ. 78:3)

+#እግዚአብሔር ግን ስለ ወዳጆቹ #ሰማዕታት ይህንን ቅዱስ አስነሳ:: ቅዱስ ዮልዮስ በዘመኑ ደግ ክርስቲያን: ትዳርና ልጆች ያሉት: እጅግ ባለ ጸጋና 300 አገልጋዮች ያሉት: ምጽዋትንም የሚወድ ሰው ነበር::

+በወቅቱ ክርስቲያኖች በየመንገዱ ወድቀው መታየታቸው ዕረፍት ቢነሳው ከቤተሰቦቹ ጋር መክሮ መልካም ግን ደግሞ ከባድ ውሳኔን አስተላለፈ:: ውሳኔውንም ታጥቆ ይተገብረው ጀመር:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

1.የታሠሩ ክርስቲያኖችን ቁስላቸውን እያጠበ ያጐርሳቸዋል::

2.ቀን ቀን አገልጋዮቹን አስከትሎ የሰማዕታቱን ሥጋ እየሰበሰበ: ሽቱ ቀብቶ ይገንዛቸዋል:: አንዳንዶቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲልክ ሌሎቹን ራሱ ይቀብራቸዋል::

3.ሌሊት ሌሊት በ300ው አገልጋዮቹ እየታገዘ የሰማዕታቱን ዜና: ቀለም በጥብጦ: ብራና ዳምጦ: ብዕር ቀርጾ: ሲጽፍና ሲጠርዝ ያድራል:: በተረፈችው ጥቂት ሰዓት ደግሞ ይጸልያል:: ቅዱስ ዮልዮስ በእውነት ድንቅ ሰው ነው:: በምን እንመስለዋለን! እርሱን የፈጠረውን ጌታ "ዕጹብ ዕጹብ" ብለን ከማድነቅ በቀር::

+ሰማዕታቱም ስለ ደግነቱ የሚመልሱለት ቢያጡ ዝም ብለው ይመርቁት ነበር:: ምርቃናቸውም "ለሰማዕትነት ያብቃህ" የሚል ነው:: በእርግጥ ይህ ለዘመኑ ሰዎች ምርቃት ላይመስለን ይችል ይሆናል:: እርሱ ግን ይህንን ሲሰማ ሐሴትን ያደርግ: እጅም ይነሳቸው ነበር:: በዘመኑ ትልቁ ምርቃት ይሔው ነበርና::

+እንዲህ: እንዲህ እያለ ዘመነ ሰማዕታት ሊፈጸም ወራት ቀሩት:: በዚህ ጊዜ ለሰማዕትነት ከመነሳሳቱ የተነሳ ጌታችንን ተማጸነ:: ጌታችንም ተገልጾለት "ሒድና ሰማዕት ሁን: ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: እርሱም ደስ እያለው ዜና ሰማዕታቱን ለሁነኛ ሰው ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን ለነዳያን አካፈለ::

+ቀጥሎም ቤተሰቦቹንና አገልጋዮቹን ጨምሮ 500 ሰዎችን አስከትሎ ወደ ሃገረ #ገምኑዲ ሔደ:: በመኮንኑ ፊት የክርስቶስን አምላክነት ቢመሰክር ፈጽመው አሰቃዩት:: በማግስቱም ወታደሮቹ ለጣዖት ካልሰገድክ ሲሉት "ቆዩማ ላሳያችሁ" ብሎ በጸሎቱ ጣዖታትን ከነ ካህናቶቻቸው ምድር ተከፍታ እንድትውጣቸው አደረገ::

+በዚህ ተአምር የደነገጠው መኮንኑ #አርማንዮስ ከነ ሠራዊቱ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንም ትቶ ቅዱስ ዮልዮስን ተከተለው:: ቀጥሎም ጉዞ ወደ ሃገረ #አትሪብ ሆነ:: በዚያም ብዙ መከራን ተቀብሎ ጣዖታቱን አወደማቸው::

+እዚህም የአትሪብ መኮንን ደንግጦ ከነ ሠራዊቱ አምኖ ቅዱሱን ተከተለው:: በመጨረሻ ግን ሰማዕትነት እንዳይቀርበት ስለሰጋ ቅዱስ ዮልዮስ ተአምራት ማድረጉን ተወ:: በፍጻሜውም የ3ኛው ሃገር መኮንን ቅዱስ ዮልዮስ ከቤተሰቡና ከ1,500 ያህል ተከታዮቹ ጋር: 2ቱን የሃገረ ገዥዎች ጨምሮ አንገታቸውን አሰይፏቸዋል:: ቅዱሱም የክብር ክብርን አግኝቷል::

+"+ #ቅዱስ_ኮቶሎስ_ሰማዕት +"+

=>ይህ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ አረማዊ ሲሆን የክርስቶስን ስም ሰምቶ አያውቅም:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘ በፋርስ (አሁን #ኢራን) ሳቦር የሚባል ክፉ ንጉሥ ነግሦ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ ነበር:: እርሱ የሚያመልከው ፀሐይና እሳት ነውና::

+የዚህ ንጉሥ ልጆቹ 'ልዑል ኮቶሎስና ልዕልት አክሱ' ይባላሉ:: በቤተ መንግስት ውስጥ ስላደጉ የሚያመልኩት የአባታቸውን ጣዖት ነበር:: በፋርስ መንግስት ውስጥ ከነበሩ የጦር አለቀቆችና ሃገረ ገዥዎች አንዱ #ጣጦስ ይባላል::

+ይህ ሰው እጅግ ብሩህ የሆነ ክርስቲያን ነበርና ዘወትር ከንጹሕ አገልግሎቱ ተሰነካክሎ አያውቅም:: ትንሽ ቆይቶ ግን ክርስቲያን መሆኑን ሳቦር ስለ ሰማ ሠራዊት ይልክበታል:: "ሒዱና ጣጦስን መርምሩት: ክርስቲያን ከሆነና አማልክትን እንቢ ካለ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሉት" አላቸው::

+በአጋጣሚ የንጉሡ ልጅ ኮቶሎስና ጣጦስ በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ነበሩና ሊያስጥለው ወዶ ሔደ:: ኮቶሎስ ቅዱስ ጣጦስ ታስሮ በእሳት ሊቃጠል ሲል ደረሰ:: ወዲያውም ወደ እሳቱ ውስጥ ጨመሩት:: እነርሱ ፈጥኖ አመድ ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር:: ግን አልሆነም::

+ቅዱስ ጣጦስ በእሳት መካከል ቁሞ አላቃጠለውም:: እንዲያውም በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት እሳቱ ብትንትን ብሎ ጠፋ:: ኮቶሎስ ተገርሞ ቅዱሱን ባልንጀራውን "ወንድሜ! ሥራይ (መተት) መቼ ተማርክ ደግሞ?" ሲል ጠየቀው::

+እርሱ እስከዚያች ሰዓት ኃይለ እግዚአብሔርን አልተረዳምና:: ቅዱስ ጣጦስ ግን "ወንድሜ! አትሳሳት: እኛ ክርስቲያኖች መተትን አናውቅም:: በፈጣሪያችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን ሁሉን ማድረግ እንችላለን" ሲል መለሰለት::

+ኮቶሎስ ተገርሞ "አሁን እኔ በክርስቶስ ባምን እንዳንተ ማድረግ እችላለሁ?" ቢለው ቅዱሱ "አዎ ትችላለህ!" አለው:: ወዲያውም "እሳት አንድዱልኝ" አለና እጣቱን በመስቀል ምልክት አስተካክሎ ወደ እሳቱ ቢያመለክት እሳቱ 12 ክንድ ርቆ ተበትኖ ጠፋ::

+በዚያችው ሰዓት ቅዱስ ኮቶሎሰ በክርስቶስ አመነ:: ክብሩንና የአባቱን ቤተ መንግስት አቃሎ ወደ እስር ቤት ገባ:: አባቱ ሳቦር ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ "ምከሪው" ብሎ እህቱን አክሱን ላከበት::

+ቅዱስ ኮቶሎስ ልትመክረው የመጣችውን እህቱን አሳምኖ የክርስቶስ ወታደር አደረጋት:: አስቀድሞ #ቅዱስ_ጣጦስ: አስከትሎም #ቅድስት_አክሱ ተገደሉ:: በፍጻሜው ግን ቅዱስ ኮቶሎስን እግሩን አስረው በየመንገዱ ጐተቱት:: በጐዳናም አካሉ እየተቆራረጠ አለቀ:: ክርስቲያኖች በድብቅ መጥተው የ3ቱንም ሥጋ በክብር አኑረዋል::

=>አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታትን ባጸናበት ጽናት ሁላችንም ያጽናን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

=>መስከረም 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
2."1,500" ሰማዕታት (የቅዱስ ዮልዮስ ማሕበር)
3.ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕት
4.ቅድስት አክሱ ሰማዕት
5.ቅዱስ ጣጦስ ሰማዕት
6.ቅዱስ ባላን ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ዻውሊ የዋህ

=>+"+ ሰውን ከአባቱ: ሴት ልጅንም ከእናቷ . . . እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና:: ለሰውም ቤተሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል:: ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: መስቀሉን የማይዝ በሁዋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም:: +"+ (ማቴ. 10:35)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
EOTC ቤተ መጻሕፍት pinned «+ መርጦ መወለድ + ከእገሌ ልወለድ ብሎ መርጦ የተወለደ የለም:: ምረጡ ብንባል ምን ዓይነት ወላጅ እንመርጣለን? ቀድመን የመገምገም ዕድል ቢኖረን ምን ዓይነት ወላጆች እንመርጣለን። መቼም በወላጆቼ ደስተኛ ነኝ የሚል ሰው "እኔ ደግሜም ብወለድ ከአባዬ ከእማዬ ነው መወለድ የምፈልገው" ማለቱ አይቀርም። ግን ደግሞ ዕድሉን ቢያገኝ መቼም ትንሽም ቢሆን የሚያስተካክለው ነገር አይጠፋም። መርጦ መወለድ አይቻልም…»
Audio
የወርቅ መቅረዝ 
                                                  
Size:- 61.4MB
Length:-2:56:12
       
     በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery

አመ ፳ወ፯ ለመስከረም ዘቀዳማይ ጽጌ በዓለ መድኃኔዓለም ማህሌት
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
ለማንኛውም ወርኃዊ እና አመታዊ ሥርዓተ ማኅሌት መጀመሪያ
.....................................................
ስምዓኒ እግዚኦ ጸሎትየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ወይብጻሕ ቅድሜከ ገዓርየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ወኢትሚጥ ገፀከ እምኔየ፡ በዕለተ ምንዳቤየ አጽምእ ዕዝነከ ኃቤየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ አመ ዕለተ እጼውአከ ፍጡነ ስምዓኒ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም፡ ሃሌ ሉያ ዘውእቱ ብሂል፡ ንወድሶ ለዘሃሎ እግዚአብሔር ልዑል፡ ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኲሎ ዓለመ፡ በአሐቲ ቃል።

መልክዓ ሥላሴ፦
ሰላም ለኵልያቲክሙ እለ ዕሩያን በአካል፤ዓለመክሙ ሥላሴ አመ ሐወፀ ለሣህል፤እምኔክሙ አሐዱ እግዚአብሔር ቃል፤ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል፡፡

ዚቅ፦
እግዚኦ በሰማይ ሣህልከ፤ ወበደመናትኒ አንተ አርአይከ ኃይለከ፤ወበምድርኒ ዘሠናየ ጽጌ ወጥዕመ ፍሬ አንተ አርአይከ፤ወበቀራንዮ አንተ አርአይከ ትሕትናከ፤በዲበ ዕፀ መስቀል

ዓዲ(ሌላ) ዚቅ፦
ሐፁር የዓውዳ ወጽጌ ረዳ ፤ብእሲ ተወልደ በውስቴታ፤ንጉሠ እስራኤል ፤ አልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ ፤ንጉሠ እስራኤል ህየ ማህደሩ ለልዑል ፤ንጉሠ እስራኤል ፤መድኃኔዓለም እግዚአብሔር ኀደረ ላዕሌሃ፤ ኪያሃ ዘሠምረ ሀገረ

መግቢያ ዘማኅሌተ ጽጌ

ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት፤ተሠርገወት ምድር  

(🌹#በህብረት_ሁሉም🌹)
በስነ ጽጌያት፤ለመርዓዊሃ ትብሎ መርዓት፤ወልድ እኁየ ወረደ ውስተ ገነት።

ማኅሌተ ጽጌ፦
ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ  እምዓጽሙ፤ለዘአምኃኪ ጽጌ ለገብርኤል ምስለ ሰላሙ፤ወበእንተዝ ማርያም ሶበ  ሐወዘኒ ጣዕሙ፤ለተአምርኪ አኀሊ እሙ፤ማኅሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ፡፡

ወረብ
መዓዛ ጣዕሙ ለተአምርኪ ሶበ ሶበ ሐወዘኒ/፪/
ወበእንተዝ ማርያም አኅሊ ለተዓምርኪ/፪/

ዚቅ፦
ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ናሁ አስተርአየ ጽጌ መርዓቱኒ ትቤ ወልድ እኁየ ይምዕዝ ከርቤ፤ ዕንባቆም ነቢይ ግብረ ምግባሩ ለወልድ አንከርኩ ይቤ፤ ንጉሠ ሰላም ክርስቶስ ዓቢይ ልዕልናከ ወመንክር ስብሐቲከ፤ለዕረፍት ሰንበት ሠራዕከ፤

ማኅሌተ ጽጌ፦
ዓይኑ ዘተገብረ ፈውስ እንበለ ትትወለዲ ድንግል እምቤተ ክህነት ወንግሥ፤ መድኃኒተ ዓለም ኮነ ደመ ክርስቶስ፤ እሰግድ ለተአምርኪ በአብራከ ሥጋ ወነፍስ፤ በከመ ሰገደ ለወልድኪ ዮሐንስ በከርሥ

ወረብ፦
ዓይኑ ዘተገብረ ዘተገብረ ፈውስ ድንግል እንበለ ትትወለዲ/፪/
መድኃኒተ ዓለም ኮነ ደመ ጽጌኪ ክርስቶስ/፪/

ዚቅ፦
መድኃኒት ኮነ ለአሕዛብ፤መድኃኒተ ኮነ መድኃኒተ ኮነ፤ ለአሕዛብ መድኃኒተ ኮነ

ማኅሌተ ጽጌ
እንዘ  ተሐቅፊዮ ለሕጻንኪ ጽጌ ፀዓዳ ወቀይሕ ፣አመ ቤተ መቅደስ ቦእኪ በዕለተ ተአምር ወንጽሕ፣ንዒ  ርግብየ  ትናዝዝኒ  እምላህ፣ወንዒ  ሠናይትየ ምስለ ገብርኤል ፍሡሕ፣ወሚካኤል ከማኪ ርኅሩኅ

ወረብ
እንዘ ተሐቅፊዮ ለሕጻንኪ ጽጌ ፀዓዳ ወቀይሕ /፪/
አመ  ቤተ  መቅደስ  ቦእኪ ሠናይትየ በዕለተ ተአምር ወንጽሕ/፪/

ዚቅ፦
ንዒ ርግብየ ሰላማዊት፤ ተመየጢ ወንርአይ ብኪ ሰላመ፤ በአምሳለ ወርቅ ይግበሩ ለኪ ኮሰኮሰ ዘብሩር፤ አመ ወለደቶ አርአያ ወሰደቶ፤ በትእምርተ መስቀል፤ ትፍሥሕትኪ ውእቱ፤ ብርሃንኪ ውእቱ ሰላምኪ።

ማኅሌተ ጽጌ
ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ  ዘየኃቱ፤ዘተጽሕፈ ብኪ  ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ፤አክሊለ ጽጌ ማርያም  ለጊዮርጊስ ቀጸላ  መንግሥቱ፤አንቲ  ኵሎ ታሰግዲ ሎቱ፤ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ፡፡

ወረብ
ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ/፪/
አክሊለ ጽጌ ማርያም ቀጸላ  መንግሥቱ/፪/

ዚቅ
ነያ ሠናይት ወነያ አዳም፤ አግዓዚት ማርያም ጽርሕ ንጽሕት፤ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ ማ፦ ወዲበ ርእሳኒ አክሊል፤ ፅሑፍ በትምህርተ መስቀል

ዓዲ(ሌላ) ዚቅ፦
አክሊል ዘእምጳዝዮን ተደለወ :ጌራ ባሕሪይ ወቀጸላ ወርቅ ጽሩይ በቤተልሔም ተወልደ እምድንግል በብስራትክሙ መሐይምናን እምአፈ ዮሐንስ ሥርግው ተቀሰመ አፈው ሰባኬ ወንጌል ነዋ በማዕከለ አኃው

ሰቆቃወ ድንግል
በስመ እግዚአብሔር ሥሉስ ሕፀተ ግጻዌ ዘአልቦ፤ሰቆቃወ ድንግል እጽሕፍ በቀለመ አንብዕ ወአንጠብጥቦ፤ወይሌ ወላህ ለይበል ዘአንቦ፤ከማሀ ኀዘን ወተሰዶ ሶበ ለኩለሄ ረከቦ፤ርእዮ ለይብኪ ዓይነ ልብ ዘቦ

ወረብ፦
ከማሀ ኀዘን ከማሀ ኀዘን ወተሰዶ ኀዘን/፪/
ርእዮ ለይብኪ ዓይነ ልብ ዘቦ ዓይነ ልብ ዘቦ/፪/

ዚቅ፦
እወ አማን እምውሉደ ሰብእ አልቦ፤ምንዳቤ ወግፍዕ ዘከማኪ በዉስተ ኩሉ ዘረከቦ፤

መዝሙር

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፤ሃሌ ሃሌ ሉያ፤ትዌድሶ መርዓት፤እንዘ ትብል ነዓ ወልድ እኁየ፤
ንፃዕ ሐቅለ፤ትዌድሶ መርዓት ንርዓይ ለእመ ጸገየ ወይን፤ወለእመ ፈረየ ሮማን፤ትዌድሶ መርዓት አሠርገወ ሰማየ በከዋክብት፤ወምድረኒ በስነ ጽጌያት፤ትዌድሶ መርዓት
እስመ ውእቱ ወልድ ዋሕድ፤እግዚአ ለሰንበት፤ማ፦ትዌድሶ መርዓት ወትብሎ፤
ወልድ እኁየ ቃለከ አዳም።

አመላለስ፦
ትዌድሶ መርዓት ወትብሎ/፪/
ወልድ እኁየ ቃለከ አዳም/፬/
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
#መስከረም_23

መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የክርስቶስ ሙሽራው የሆነች #ቅድስት_ቴክላ መታሰቢያ በዓሏ ነው፤ ዳግመኛም #ቅዱሳን_አውናብዮስ_እና_እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ቴክላ_የክርስቶስ_ሙሽራው

መስከረም ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት የክርስቶስ ሙሽራው የሆነች ቅድስት ቴክላ የመታሰቢያ በዓሏ ነው፡፡

ይህችውም ቅድስት ለሐዋርያው ለቅዱስ ጳውሎስ ረድእ ሆና ያገለገለች ታላቅ ሐዋርያዊት እናት ናት፡፡ የመቄዶንያ ሀገር ባለጸጎች የነበሩት ወላጆቿ ጣዖት አምላኪ ነበሩና በሕጋቸውና በሥርዓታቸው አሳደጓት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚህች ሀገር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ሰበከ፡፡ ቅድስት ቴክላም ትምህርቱን በሰማች ጊዜ በቤቷ ሆና ሳትበላና ሳትጠጣ 3 ቀን ቆየች፡፡ ከዚህም በኋላ ለሚጠብቃት ዘበኛዋ እንዳይናገርባት በማለት የወርቅ ወለባዋን ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሄደች፡፡ እርሱም በደስታ ተቀብሎ የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት፡፡ በማግሥቱም ቅድስት ቴክላን እናቷ ስትፈልጋት ከቅዱስ ጳውሎስ እግር ሥር አገኘቻት፡፡ ከዚያም ወደ መኰንኑ ዘንድ ሄዳ ልጇ ክርስቲያን መሆኗን በመናገር ከሰሰቻትና ለመኰንኑ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡

መኰንኑም ሁለቱን ቅዱስ ጳውሎስንና ቅድስት ቴክላን እንዲያመጧቸው ወታደሮቹን ላከ፡፡ ካመጧቸውም በኋላ መጀመሪያ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት ወረወሩት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በተአምራት አዳነው፡፡ ቅድስት ቴክላን ግን ለሀገሩ ልጆች መቀጣጫ ትሆን ዘንድ መኰንኑ ሰውን ሁሉ ከሰበሰበ በኋላ ወደ እሳቱ እንዲወረውሯት አዘዘ፡፡ እርሷ ግን በመስቀል ሦስት ምልክት ካማተበች በኋላ በራሷ ፈቃድ ማንም ሳይነካት ዘላ ከእሳቱ ውስጥ ገባች፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እርሷም ማንም ሳያያት ከእሳቱ ውስጥ ወጥታ ቅዱስ ጳውሎስ ካለበት ደረሰች፡፡ የራሷንም ጸጉር ቆርጣ በእርሱም ወገቧን ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው፡፡

መኰንኑም በሕይወት መኖሯን ሰምቶ ድጋሚ አስፈልጎ አስያዛትና ሃይማኖቷን እንድትለውጥ አስገደዳት፡፡ እሺ እንዳላለችው ባወቀ ጊዜ በተራቡ አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጨመራት ነገር ግን አንበሶቹ ሰግደው የእግሯን ትቢያ ሲልሱላት ተመለከተ፡፡ መኰንኑም ይህንን በተመለከተ ጊዜ እርሱና ወገኖቹም ሁሉ አምነው ተጠመቁና የክርስቶስ መንጋዎች ሆኑ፡፡ ቅድስት ቴክላም የጌታችንን ወንጌል በማስተማርና ቅዱስ ጳውሎስንም በማገልገል ብዙ ከተጋደለች በኋላ መስከረም 27 ቀን ዐርፋለች፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አውናብዮስ_እና_እንድርያስ

ዳግመኛም በዚች ቀን ቅዱሳን ጻድቃን መነኰሳት አውናብዮስና እንድርያስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህ ቅዱሳንም ከልዳ ሀገር ከታላላቆቹ ተወላጆች ናቸው ከታናሽነታቸውም በአምላካዊ ምክር ተስማምተው በሶርያ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት ወዳንዱ ገዳም ሒደው መነኰሳት ሆኑ።

ከዚህም በኋላ ወደ ከበረ ወደ ተመሰገነ አባ መቃርስ ሔዱ ደቀ መዛሙርቱም ሁነው ታዘዙለት ምክሩንም በመቀበል በጾም በጸሎት በገድል ሁሉ ተጠምደው የሚኖሩ ሆኑ በእንዲህ ያለ ሥራም በዚያ ሦስት ዓመት ኖሩ በጎ የሆነ ተጋድሎአቸውና የአገልግሎታቸው ዜና በተሰማ ጊዜ አውናብዮስን መርጠው ኤጲስቆጶስነት፣ እንድርያስን ቅስና ሾሙአቸው በበጎ አጠባበቅም የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቋቸው።

ከዚህም በኋላ ሥጋቸውን ፈጽሞ እስከ አደከሙ ድረስ ተጋድሎአቸውንና አገልግሎታቸውን እጅግ አበዙ። ከሀዲ ንጉሥ ዮልዮስም ስለእርሳቸው በሰማ ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ወደ ረከሰች አምልኮቱ እንዲገቡ አዘዛቸው ያን ጊዜ እርሱንና የረከሱ ጣዖታቱን ረገሙ እርሱም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ወደ ብዙ ክፍልም ቆራርጦ ከፋፈላቸውና ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። እያንዳንዳቸውም ሦስት ሦስት አክሊላትን ተቀበሉ አንዱ በገድል ስለ መጸመድና ስለ ምንኲስና ዋጋ፣ ሁለተኛው ስለ ክህነት አገልግሎት፣ ሦስተኛው ደማቸውን ስለ ማፍሰሳቸው ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም
@petroswepawulos
@petroswepawulos
@petroswepawulos
ቅድስት_ድንግል_ማርያም_ሕይወቷ_ተአምራቷ_መገለጧ.pdf
3.6 MB
ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወቷ ተአምራቷና መገለጧ

በአቡነ_ሺኖዳ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
Forwarded from Quality move bot
ተዋህዶ ሀይማኖቴ ነው ስለ ሀይማኖቴ ማወቅ መረዳት መጻህፍትን ማንበብ እፈልጋለው የየእለቱን ስንክሳር ማንበብ እፈልጋለው ያለ ሁሉ ሊቀላቀላቀላቸው ሚገባ ድንቅ ኦርቶዶክሳዊ ቻናል 3 ቻናሎች
👇 ከታች Join በሉ
2024/09/24 14:34:31
Back to Top
HTML Embed Code: