Telegram Web Link
ሰይጣን በጣም የሚወደው እና በጣም አምርሮ የሚጠላው
(ጽሑፉ በጣም አጭር ነው፣ ጊዜን አይሻማም ግንቀስ ብላችሁ በዝግታ አንብቡትና ለተወሰኑ ሰከንዶች አሰብ እናድርግ)

አንድን ሰው ለማስደሰት በሚወደው በኩል መቅረብ ጥሩ እነደሆነ ሁሉ ለማናደድ ለመቃወምና ለማበሳጨትም በሚጠላው ነገር መሄድ የተለመደ ፈሊጥ ነው። የእኛም አባቶች እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ብቻ ሳይሆን ሰይጣንን የሚያናድደውንም ጭምር ነግረውናል። ለነገሩ የሰማያት ምስጢር ለተገለጠለት የሰይጣንን የልቡን ማወቅ ብርቅ አይደለም።
ለዛሬ ሰይጣንን እንጨት እያስለቀመና እያስቆረጠ፣ ሸክም እያሸከመና ሌላም የጉልበት ሥራ እያሰራ እንደ ሎሌ ሲያሽከረክረው የነበረው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰይጣን ጸሎት ማስታጎልን በጣም እንደሚወድና እመቤታችንን አምርሮ እንደሚጠላ በአርጋኖን መጽሐፉ እንዲህ ይለናል።
1. ጸሎት ማስታጎልን እንደሚወድ
"ሰይጣን ከቶ እንደ ጸሎት ማስታጎል የሚወደው የለም። ጸሎት ፍላጻ ነውና ዓይኑን ይወጋዋል፣ ከሚጸልይ ሰው አንደበት እሳት ወጥቶ ሰይጣንን ያቃጥለዋልና፣ ሰይጣንም ስለዚህ ከበጎ ሥራ ሁሉ ጸሎትና ትጋትን ይጠላል።" /አርጋኖን ዘሠሉስ/
2. እመቤታችንን ከምንም በላይ አምርሮ እንደሚጠላት
"ድንግል ሆይ ... ይልቁንም ያንችን የምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፋጫል፣ የምስጋናሽ ወሬ በርሱ ዘንድ መራመጃ ነውና፣ ወገቡን ይሰብረዋል፣ ሰይፍ ነውና ራሱን ይቆርጠዋል።
ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደሰማ ሁሉ ይደነግጣል። አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም። ባንቺ ታመመ፣ በልጅሽም ተጨነቀ፣ ባንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፣ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣን አንቺን ይጠላል።" /አርጋኖን ዘሠሉስ/
ስለዚህ እኛም እርሷን ለመውደድ እርሱም እርሷን ለመጥላት ምክንያት አለን ማለት ነው።
እናም እናንት ከሰይጣን ጋር ደም የተቃባችሁ ልጆቿ ሆይ ደም ተቀብቶ ዝንብ አይፈራምና ሰይጣንን ሳትፈሩ እንደ መልአኩ ገብርኤል "ደስስስ ይበልሽ " እያልን ኑ ማርያምን እናመስግናት።
ሰይጣን ይደንግጥ፣ ዕረፍት ይጣ፣ ይታመም፣ ይጨነቅ፣ ... አሕዛብ ሆይ ኑ ማርያምን እናመስግናት። ኑ ኑ ኑ ... እናመስግናት።
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
መጽሐፍ ቅዱስን በዮኒዚም ትርጓሜ ስንፈታቸው
*
ባሻዬ ናማ እስኪ

መጽሐፍ ቅዱስን ገለጥ ስታደርገው....አውን እጅህ ላይ ያለውን ስልሳ ስድስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንባብ ስትከፍተው በሥጋ ንባብ አስደንጋጭ ነገር ግን በሃቅ እና በመንፈስ ሚዛን ላይ ትክክል የሆኑ እንዲህ አይነት ቃላትን ታገኛለህ።
*


“ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።....ዘዳ23፥2"

ይህን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ገድለ መርቆርዮስ ወይም ገደለ ተክለሃይማኖት ላይ ተገኝቶ ቢሆንስ? የስንት ሳምንት ኦርቶዶክሱን የመስደብያ የስብከት እንጅራህ ይሆን ነበር?
+++

ሌላም እስኪ እንመልከት ...

“ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፣ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ።...ምሳሌ 31፥6-7"

ይህ በጠቢቡ ስለምን እጅ በኩል የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በኦርቶዶክስ አንደኛው የጸሎት፣የታምራት፣የገድላት መጽሐፍ ላይ ብታገኘውስ? ህዝቡ ሰካራም የሆነው እንዲህ አይነት የስካር መንፈስ የያዙ መጽሐፍትን እየተሻሹ ነው ... ኡ ኡ ። ይህ ጣዖት አምላኪነት ነው ትለን ነበር አ?

+++
ባሻዬ

እባብ አዳኝ ነው የሚል ሐሳብ ያለው ንባብ ላሳይህ እስኪ..

“ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። ዘኍ21፥9" "

እባብ እያዪ ህዝቡ ዳኑ። ይህን ቃል በደንብ አድርገህ ደጋግመህ አንብበው ።

ይህ ቃል በታምረ ማርያም ላይ ቢኖርስ? እባብ አዳኝ የሆነበት የጥልቁ መንፈስ አሰራር ያለበት መቅደስ ውስጥ መኖር ጣዖት አምላኪነት ተብሎብን አዳራሽ ሙሉ መንጋ ይጮኸብን ነበር።ግን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው ያለው።
+++

“ደንቆሮዎች፥ ሉቃ11፥40//“ውሾች ፣ፊል 3፥2//“ጋለሞታ 1ኛ ቆሮ 6፥15// ወዘተ ተብለው የተጻፉ ቃላት ገድላት ላይ ቢገኙ,...

የዘንዶው የስድብ አፍ የተሰጣቸው ተብሎልን የ2 ወር የአዳራሽ ስብከት ማሞቂያ እንሆን ነበር

+++
ስለኢየሱስ በተጻፈው ሐሳብ ላይ

“በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ማቴ 10፥34"

የሚለው የወንጌል ልሳን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በአዋልድ መጽሐፍት ከሆኑት በአንዱ ላይ ቢኖርስ? የሰላሙን አለቃ ጠብ ጫሪ አደረጉት፣አዳኙን ገዳይ ነው አሉት፣ ተብሎልን በፍጩት እና በጩኸት በቀለጠ ኡኡታ ጆሯችን ይደማ ነበር።
+++
ስለኢየሱስ ክብር በሚያትተው የመጽሐፍ ክፍል ላይ

“ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስ... ዕብ 2፥9"

የሚለውን ሐሳብ ታምረ ማርያም ውስጥ ቢገኝ ምን አይነት ፉጩት እና ሁከት እንደሚፈጠር አስባችሁታል?

ኢየሱስን ከመላእክት አሳንሰው፣ክርስቶስን ከገብርኤል ከሚካኤል በታች አድርገው ተብሎ ሰማይ ሰንጣቂ ጩኸት ይሰማ ነበር።
+++
መርቆርዮስ ቀይ ባህርን ለሁለት ከፈለ፣ተክልዬ ጸሐይን በገባዖ አቆመ፣ቅዱስ ያሬድ ከእንስሳ ጋር ቃል በቃል አወራ፣ የሚሉ ሐሳቦች ገድላት ላይ ቢገኙ የምንዱባዮችን ጩኸት አስባቹታል...

ከፊደል ጋር በግርድፉ መጋጨት የመንፈስ ሞት ያስከትላል። እንኳን ገድላትን ይቅርና መጽሐፍ ቅዱስ በግርድፍ የቃል ዐረፍተ ነገር ልፍታው ብትል መገኛህ እንጦሮንጦስ ነው። ምክንያት ካልከኝ

“ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።”
— 2ኛ ቆሮ 3፥6 የሚል የእግዚአብሔር ህግ ስላለ።

እግዚአብሔር ይመስገን !
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
Audio
ምልክት ያላቸው በጎች ለያዕቆብ
                         
Size 19.1MB
Length 54:53

  በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#ከክርስቶስ_በፊት_የነበሩ_ክርስቲያኖች
(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)

#የቆሎ_ተማሪዎች

ንጉሥ ናቡከደነፆር እስራኤልን ድል ነሥቶ በግዞት ወደ ባቢሎን በወሰዳቸው ጊዜ ሕዝቡን ለአመጽ እንዳያነሣሡበት ከነገሥታትና መሳፍንት ወገን የሆኑትን ፣ መልከ መልካሞቹን ፣ ወጣቶቹንና ብሩሕ አእምሮ ያላቸውን መርጦ ከሕዝቡ ለይቶ በቤተ መንግሥቱ ሰበሰበ፡፡ ዓላማው ወጣቶቹ የሀገሩን ቋንቋ ከተማሩና በቤተ መንግሥት በምቾት ከኖሩ የወገኖቻቸው መከራ እንደማይሰማቸው በማሰብ ነበር፡፡ ከሰው ልጅ የሚበዛው እርሱ እስከተመቸውና ጥቅሙ እስካልተነካበት ድረስ የሌላው ወገኑ ጩኸት ስለማይሰማው ናቡከደነፆር እስራኤልን ለማፈን የተጠቀመው አደገኛ ስልት ነበረ፡፡ ይህ ስልት ግን በሦስቱ ወጣቶች በአናንያ በአዛርያና ሚሳኤል ላይ አልሠራም፡፡ ገና ከጅምሩ በቤተ መንግሥት የቀረበላቸውን ‹ጮማና ጠጅ አንበላም ጥሬ ይሠጠን› ብለው በድብቅ ‹የቆሎ ተማሪዎች› ሆኑ፡፡
መቼም የቤተ መንግሥትን እንጀራ አንዴ አትልመደው እንጂ የለመድከው እንደሆነ ንጉሡ ምንም አድርግ ቢልህ ታደርጋለህ፡፡ የቤተ መንግሥት ምግብ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ እንጀራ ተከትሎት ሄደ›› ተብሎ እንደተጻፈ እንኳን የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምግብ ይቅርና የንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥት ምግብም እንደ ኦርዮ ሞትን ሊያስከትልም ይችላል፡፡ ከቤተ መንግሥት የሚሠጥህን ምግብ አገኘሁ ብለህ ደስ ቢልህም ያ ምግብ የመጨረሻ ራትህ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ነገ ክፉ ነገር አድርግ ቢሉህ እምቢ ለማለት ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ጥሬ ቆርጥመው ሊማሩ ወሰኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሦስቱን ወጣቶች ከንጉሡ ጋር የሚያጋፍጥ ነገር የመጣው፡፡

ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር ሕልም አለመ ፤ ሆኖም ሕልሙ ጠፋበት፡፡ አስማተኞቹን ሰብስቦ ‹ሕልሜን ከነፍቺው ንገሩኝ› ብሎ አፋጠጣቸው፡፡ ግራ ገባቸው ፤ ሕልሙን ተናግሮ ቢሆን ‹ሲሳይ ነው ፣ ዕድሜ ነው ፣ ጸጋ ነው› ብሎ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን ‹ሕልሜን ውለዱ› አለ፡፡ አልነግር ሲሉት ሊገድላቸው ወሰነ፡፡ በዚህ መካከል ሦስቱ ወጣቶች ከአጎታቸው ዳንኤል ጋር ሆነው መፍትሔ አመጡ፡፡ እነርሱ በጸሎት ሲተጉ እግዚአብሔር ሕልሙን ከነትርጓሜው ለዳንኤል ገለጠለት፡፡
ንጉሡ በዘነጋው ሕልሙ ያየው ‹ራሱ የወርቅ ፣ የቀረው አካሉ የብር ፣ የናስ ፣ የብረትና ሸክላ የሆነ ትልቅ ምስል ነበር› ዳንኤል ሕልሙን ለንጉሡ ከነገረው በኋላ እንዲህ ብሎ ፈታለት፡፡ ‹ንጉሥ ሆይ ባየኸው ሕልም ላይ በሥልጣን ከሁሉ በላይ አድርጎሃልና የወርቁ ራስ አንተ ነህ ፤ ከዚያ በታች ያየኻቸው ደግሞ ከአንተ በኃይል የሚያንሡ ከአንተ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት ናቸው›› ብሎ እርሱና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት እንዴት መንግሥታቸው እንደሚያልፍ ሕልሙን ከነዝርዝር ፍቺው ነገረው፡፡ በዚህም ንጉሡ ደስ አለውና ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው ፤ ሦስቱን ወጣቶችም በአውራጃ ሥራ ላይ አዛዦች አድርጎ ሾማቸው፡፡

#እንደ_ንጉሡ_አጎንብሱ

ናቡከደነፆር ዳንኤል ከፈታለት ረዥም ሕልም ውስጥ ግን ከአእምሮው ያልጠፋችው ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለው ዓረፍተ ነገር ነበረች፡፡ መቼም እኛ ወርቅ የሆንንበት ቅኔ ከልባችን አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ራስ ወዳዱ ናቡከደነፆር ከረዥሙ ሕልም ውስጥ ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለዋ ብቻ ልቡን ነካችው፡፡ ባልንጀራህን ‹እንደ ራስህ ውደድ› ስለሚል ራስን መውደድ ጥፋት አይደለም፡፡ ራስን መውደድ በጣም ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ‹ፀሐይ የምትወጣው እኔን ለማየት ነው› እስከማለት ያስደርሳል፡፡ ናቡከደነፆር በራሱ ፍቅር ወደቀ ፣ ራሱን አቅፎ ለመሳም ቃጣው ፤ በመጨረሻም ‹እኔ ወርቅ ነኝ› የምትለው አሳቡ አድጋ በዱራ ሜዳ ላይ ትልቅ የወርቅ ሐውልት ሆነች፡፡ ‹ለዚህ ጣዖት የማይሰግድ ሰው ወደ እሳት ይጣላል› የሚል አዋጅ አወጀ፡፡ የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሀገሩ ተሰማ፡፡ ሕዝቡ ወደ ዕቶን እሳት ትጣላለህ ከሚል ማስፈራሪያ ጋር ስሜቱን የሚነካ ሙዚቃም ሲሰማ ያለማመንታት ታዘዘ፡፡ በዚህ አዋጅ ምክንያት በድፍን ባቢሎን የሚኖሩ እስራኤላዊያንም ጭምር ሁሉም ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

የአውራጃ ሹመኞች የሆኑት የቤተ መንግሥት ጾመኞች ሦስቱ ወጣቶች ግን አልሰገዱም፡፡ ሁሉም ሲሰግድ አለመስገድ ፣ ሁሉም ሲያጨበጭብ እጅን መሰብሰብ ፣ ሁሉ ሲስቅ መኮሳተር ጽናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹ከሀገሩ የወጣ ሰው እስኪመለስ ድረስ ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ› ብለው መተረት አልፈለጉም፡፡ ሀገሩ ሁሉ ከሰገደ በእነዚህ ወጣቶች ለይቶ የሚፈርድባቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከእስራኤል ወገን ብዙ ሽማግሌዎች ብዙ መጽሐፍ አዋቂዎች አገጎንብሰው ቢሰግዱም እነዚህ ወጣቶች አልሰገዱም፡፡ ‹‹ከእኛ ብዙ የሚያውቁት እነ እገሌ እነእገሌ ከሰገዱ እኛ ለምን እንጠቆራለን? ከሰው ተለይተን ምን እንፈጥራለን? የአውራጃ ገዢ አድርጎ ሾሞን የለ አሁን እንቢ ብንል ውለታ ቢስ መሆን አይሆንብንም? ስገዱ ያለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው እንጂ ጣዖት አምልኩ አላለንም ፤ እሳት ውስጥ ከምንገባ ይህችን ቀን አጎንብሰን ብናልፋትስ ፣ ዋናው ልብ ነው›› ብለው ራሳቸውን ሊያሞኙ አልፈለጉም፡፡ ሁሉ ባጎነበሰበት ቀን አንሰግድም ብለው ቆሙ፡፡

#የሚያድናችሁ_አምላክ_ማንነው?

ናቡከደነፆር ሦስቱ ወጣቶች እንዳልሰገዱ ሲነገረው ቁጣው ነደደና አስጠራቸው፡፡ ‹‹የምሰማው እውነት ነውን?›› አለ ፤ እንዲያስተባብሉ ዕድል ሲሠጥ፡፡ ‹አሁንም የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ብትሰግዱ መልካም ነው›› አለ፡፡ መቼም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ናቡከደነፆር የሙዚቃን ስሜት ቀስቃሽነት የተረዳ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ‹‹በሉ ሙዚቃው ድጋሚ ይከፈትልሃል ትጨፍራላችሁ›› የሚል ይመስላል፡፡ ስገዱ ከማለቱ ሙዚቃውን ስትሰሙ ማለቱ ይገርማል፡፡ ከዚያ ማስፈራሪያ ጨመረበት ‹‹ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ለሚለው ለንጉሡ ጥያቄ ሦስቱ ወጣቶች ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም›› አሉት፡፡ ምን ማለታቸው ነው? ለምን አይመልሱለትም? ይህንን ያሉበት ምክንያት ናቡከደነፆር ከጥቂት ጊዜ በፊት ሕልም አልሞ በተፈታለት ጊዜ ደስ ብሎት ‹‹አምላካችሁ የአማልክት አምላክ የነገሥታትም ጌታ ምሥጢርም ገላጭ ነው›› ብሎ መስክሮ ስለነበር ነው፡፡ (ዳን 2፡47) አሁን ደግሞ ተገልብጦ ‹ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?› አላቸው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ትናንት ያመሰገነውን አምላክ እንደማያውቀው ሲሆን ላንተ መልስ አያስፈልግህም አሉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትናንት ያመለኩትን አምላክ ዛሬ እንደማያውቁ ሆነው ሲጠይቁ ፣ ትናንት ያመኑበትን ዛሬ ክደው ሲያናንቁ ‹‹በዚህ ነገር እንመልስላቸው ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም››
ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ ሰው የለም፡፡ ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ላይ ለፈጣሪ መሰከረ ፣ ምዕራፍ ሦስት ላይ ካደ ፣ ምዕራፍ ሦስት መጨረሻ ላይ አምኖ መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጀመሪያ ላይ ለፈጣሪ እንደ መዘመር ቃጣው በሕልሙ መልአክ እስከማየት ደርሶ ስለ ፈጣሪ ኃያልነት መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ግን ‹‹ይህች በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?›› ብሎ ተኮፍሶ እንደ እንስሳ ሣር እስኪግጥ ድረስ ተቀጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹አምላካችሁ ማን ነው?› ሲላቸው መልስ ልንሠጥህ አያስፈልገንም ፤ አንተው ማን እንደሆነ ሣር ስትግጥ ታየዋለህ አሉት፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው ያሉ እነፈርኦን የደረሰባቸው ባይገባህ አንተ ላይ ደርሶ ታየዋለህ ሲሉ ‹እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም› አሉት፡፡

ሦስቱ ወጣቶች አምላካችሁ ማን ነው የሚለውን ባይመልሱም ይህንን ግን አሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ አምላካችን ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል› ንጉሥ ሆይ አምላካችን ኃይሉ ከእሳት በላይ ነው፡፡ ያለ እሳት ማንደድ ያለ ውኃ ማብረድ ይችላል፡፡ ከእሳቱ ያድነናል ፤ ‹ከእሳቱ ቢያድናችሁ ምን ዋጋ አለው ፤ ከእሳት ብታመልጡ ከእኔ አታመልጡም› ብለህ ታስብ እንደሆን ‹‹ከእጅህም ያድነናል›› አሉት፡፡

‹‹ነገር ግን ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነንም አማልክትህን እንደማናመልክ እወቅ›› አሉት፡፡ ወጣቶቹ ‹ባያድነንም› ያሉት ተጠራጥረው አይደለም፡፡ ለጣዖት ከመስገድ ሞት ይሻለናል፣ ለጣዖት በመስገድ የምንጎዳው ጉዳት በእሳት ተቃጥለን ከምንጎዳው አይብስም ፣ የዘላለም እሳት ከሚፈጀን የአንተ እሳት ቢፈጀን እንመርጣለን ለማለት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሦስቱ ወጣቶች ‹ያድነን ዘንድ ይችላል› አሉ እንጂ ‹እንድናለን› አላሉም፡፡ የፈጣሪያቸውን የማዳን ኃይል በእርግጠኝነት ተናገሩ እንጂ ከዚህ እሳት እንደሚድኑ በእርግጠኝነት አልተናገሩም፡፡ ይህም ከትሕትናቸው የተነሣ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለ እኔ ያዝዝልኛል ያድነኛል ብሎ ወደ ሞት ራስን መሥጠት ጌታችን ለዲያቢሎስ እንዳለው ጌታ አምላክን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹ባያድነን እንኳን› ሲሉ ምግባራችን ከልክሎት ባያድነን እንኳን ያልዳነው በኃጢአታችን ነው እንጂ አምላካችን ማዳን ተስኖት እንዳይመስልህ አሉት፡፡

እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ያስደንቃሉ ፤ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባልተሰበከበት በዚያ ዘመን ፣ ምንም እንኳን ሥቃይ የማይነካቸው ቢሆንም እንኳን ጻድቃንም ቢሆኑ ወደ ሲኦል በሚወርዱበት በዚያ ዘመን ተስፋ ሳይኖር ተስፋ አድርገው እንደ ሐዲስ ኪዳን ሰው ወደ ሞት የሔዱት እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ክቡራን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰማዕቱ ዮስጦስ (Justine the martyr) ‹‹ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች›› (Christians before Christ) የሚላቸው፡፡

#መርጦ_የሚያነድ_እሳት

ናቡከደነፆር በወጣቶቹ መልስ እጅግ ተበሳጨ ፤ የሚነድደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲያደርጉት አዘዘ፡፡ ልፋ ሲለው ነው እንጂ እሳቱ ሰባት እጅም ቢሆን ፣ አንድ እጅም ቢሆን ለሦስቱ ወጣቶች መቃጠል ያው መቃጠል ነው፡፡ የባቢሎንን ማገዶ ከማባከን በቀር ሦስቱ ወጣቶች የሚሞቱት ሞትም ያው አንድ ሞት ነው፡፡ የተፈለገው ግን እንዲፈሩ ነበር፡፡ ሰይጣን አሠራሩ እንዲህ ነው ፤ እምነታችን ሲጨምር እሳቱ ሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡ ‹ያድነናል› የሚለው ምስክርነታችን ናቡከደነፆሮችን ያስቆጣል፡፡ በሥልጣናቸው የሚነድደውን እሳት መጨመር እንጂ የእኛን እምነት መቀነስ አይችሉም፡፡ ሦስቱን ወጣቶች ከሰናፊላቸው ፣ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸው ከቀረው ልብሳቸውም ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡ ያ ሁሉ ልብስ አብሮአቸው እንዲታሰር የተፈለገው ሥቃያቸውን የበለጠ ለማብዛት ፣ እግራቸው መታሰሩም ሳይንፈራገጡ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱን ወጣቶች ወደ እሳት ጨመሯቸው፡፡ ከእሳቱ ኃይል የተነሣ ‹የጣሏቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው›

ሦስቱን ወጣቶች እሳት ውስጥ ሲገቡ ከእስራቸው ተፈትተው ሲመላለሱ ታዩ ፤ ናቡከደነፆር ባላዋቂ አነጋገር ‹የአማልክት ልጅ› ያለውን ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ተብለው ከሚጠሩት መላእክት አንዱ የሆነውን መልአኩን ልኮ የእሳቱን ኃይል አጠፋ፡፡ ‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል› የተባለውም ተፈጸመ፡፡ ‹የአማልክት ልጅ› የተባለው የመልአኩ መውረድ የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ፣ የመምጣቱና የሰውን ልጅ ከሲኦል እሳት የማዳኑ ሥራ ምሳሌ ሆኖ ይኖራል፡፡

ሦስቱ ወጣቶች ልብስ አልብሰው የጨመሯቸው እንዲሰቃዩ ነበር ፤ ሆኖም ለሥቃይ የለበሱት ልብስ ለዝማሬ ሆናቸው፡፡ መቼም ዕርቃን ሆኖ ዝማሬ የለም፡፡ አልብሰው ባይከቷቸው ኖሮ ሲወጡ ዕርቃናቸውን በወጡ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው እነዚህ ሦስት ዕፀ ጳጦሶች እንኳን ሊቃጠሉ ጭስ ጭስ እንኳን አይሉም ነበር፡፡
የባቢሎን እሳት አስደናቂ እሳት ነው፡፡ ከእሳቱ ውስጥ እያሉ እሳቱ ያቃጠለው የታሰሩበትን ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የጣሏቸውን ሰዎች ወላፈኑ ገደላቸው፡፡ ሰዎችን ወደ እሳት መገፍተር ቀላል ነው፤ እሳቱ ግን ገፍታሪዎቹን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ‹‹እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ወእሳት ማኅየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ›› (ስሙን ለሚክዱ ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው ፤ፈቃዱን ለሚሠሩ ልባቸው ለቀና የሚያድን እሳት ነው) የሚለው የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ በብሉይ ኪዳን ቢሆን ለባቢሎን እሳት ይሠራ ነበር፡፡

ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ገብተው የመውጣታቸው ታሪክ በጥላቻና በዘረኝነት እሳት እየነደድን ባለንበት በዚህ ዘመን ሆነን ስንመለከተው መልእክቱ ብዙ ነው፡፡ በሚነድደው እሳት ላይ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምንድር ነው? አንዳንድ ሰው ‹ይለይለት ካልደፈረሰ አይጠራም› ይላል፡፡ በስድብ በጥላቻ በነቀፋ ከሩቅም ከቅርብም ሆኖ የሚያባብስ ሰው እንግዲህ እሳቱን ሰባት እጥፍ ከሚጨምሩት የናቡከደነፆር አሽከሮች አይለይም፡፡ በዚያ ላይ ይለይለት ብለህ የምትጨምረው እሳት ወላፈኑ አንተኑ ማቃጠሉ አይቀርም፡፡ ያለነውም የምንኖረውም እሳቱ ውስጥ ሆነው ‹‹የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል›› ብለው በሚጸልዩ ሰዎች ነው፡፡ ጸሎት መፍትሔ ነው ሲባል በሚያስቀን በናቡከደነፆሮች ሳይሆን ዳዊቱን በማያስታጉሉ አናንያ አዛርያና ሚሳኤሎች ነው፡፡

እሳት ውስጥ ገብተው የወጡት እነዚህ አርበኞች ከጸሎቱ ባሻገር አንድ ልብ ነበሩ፡፡ በሙሉ ትንቢተ ዳንኤል ላይ ‹አናንያ እንዲህ አለ ፤ አዛርያም እንዲህ አለ› የሚል አልተጻፈም፡፡ ሦስት ሲሆኑ እንደ አንድ ሰው ሲናገሩ ሲሰሙ ፣ አብረው ሲጾሙ ፣ አብረው ሲሾሙ ፣ አብረው ሲታሰሩ ፣ አብረው ከእሳት ሲገቡ አብረው ሲወጡ ፣ አብረው ሲዘምሩ ነው ያየናቸው፡፡ አንድ ልብ ሳይሆኑ ከእሳት መውጣት አይቻልም፡፡ አናንያና አዛርያ ተፋቅረው ሚሳኤልን ቢጠሉት ኖሮ በሃሳብ ባይስማሙ ኖሮ ተቃጥለው ይቀሩ ነበር፡፡ ‹‹መልአኩን የላከ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል አምላክ ይባረክ›› (ዳን. 3፡28)
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
ባስልዮስ ሆይ! ንገረኝ...

በዚህ ዓለም የሥራ መስክ ገበሬ መርከብ ለመንዳት የማይነሣው፣ ወይም ወታደሩ የግብርናን ሥራ የማይሠራው፣ ወይም ሙያው መርከብ ነጂ የኾነ ሰው ጦር እንዲመራ እልፍ ጊዜ ቢጎተትም እንኳ እሺ የማይለው ለምንድን ነው? እያንዳንዱ ያለችሎታው ቢሰማራ የሚከተለውን አደጋ አስቀድሞ ስለሚያይ አይደለምን? ታዲያ ጥፋቱ ቁሳቁስና ንብረት በሚኾንበት ኹኔታ አስቀድመን ብዙ የምናስብና ግፊትና ግዴታን የማንቀበል ኾነን ሳለ፥ ክህነትን እንዴት እንደሚይዙትና እንደሚያገለግሉበት ለማያውቁ ቅጣቱ ዘለዓለማዊ በኾነበት ኹኔታ ግን ያለብዙ ማሰብና ማሰላሰል እንዲሁ በዘፈቀደ ወደዚህ ዓይነት ታላቅ አደጋ ውስጥ ዘለን እንገባለንን? የሌሎች ሰዎች ግፊትስ ምክንያት ሊኾነን ይችላልን? አንድ ቀን ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ የኾነው እግዚአብሔር ይጠይቀናል፡፡ ይህ ሰበብም አያድነንም፡፡ ከምድራዊ ነገሮች ይልቅ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ይበልጥ ጠንቃቆች ልንኾን ይገባናልና፡፡ በትንንሽ ነገሮች ላይ ጠንቃቆች ስንኾን እንታያለንና፡፡ እስኪ ንገረኝ! አንድ ሰው የቤት ሥራ ሙያ ሳይኖረው ብትሠራልን ስንለው እሺ ብሎ ቢመጣና ከዚያ በኋላ ግን ዕንጨቱንና ድንጋዩን ቢያበላሽና የሠራው ነገር ወዲያውኑ ተበታትኖ ቢወድቅ በራሱ ፈልጎ አለመምጣቱና በሌሎች ግፊት ሥራውን መጀመሩ በቂ ምክንያት ሊኾነው ይችላልን? በጭራሽ! የሌሎችን ግፊትና ጥሪ አልቀበልም ማለት ነበረበትና በርግጥም ተጠያቂ ነው፡፡

ታዲያ እንዲህ ዕንጨትና ድንጋይ ለሚያበላሽ ሰው በጥፋቱ ከመጠየቅና ከመቀጣት ለመዳን ምንም ምክንያት ከሌለው፥ ነፍሳትን የሚያጠፋ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በግድየለሽነት የሚያንጽ ሰው’ማ እንዴት? የሌሎች ግፊትና ማስገደድ በቂ ምክንያት ይኾነኛል ብሎ ሊያስብ ይችላልን? እንዲህ ብሎ ማሰብስ ሞኝነት አይደለምን?

ፈቃደኛ ያልኾነን ሰው ማንም ሊያስገድደው እንደማይችል ለማሳየት ብዬ ሐተታ መስጠት አያስፈልገኝም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደ ተናገርኩት ይህ ፈቃደኛ ያልኾነ ሰው እጅግ ተጭነዉትና ግድ ብለዉት ሌሎች ብዙ መንገዶችንም ተጠቅመው ወደዚህ ኃላፊነት አመጡት እንበል፡፡ ታዲያ ይህ ከቅጣት ሊታደገው ይችላልን? እማልድሃለሁ፤ በፍጹም ራሳችንን አናታልል! ሕፃናት ሳይቀሩ በቀላሉ በሚያውቁት ነገር ላይ እንደማናውቅ ኾነን አናስመስል፡፡ እንደማናውቅ ማስመሰላችን በዚያች ዕለት ላይ በእውነት ያለ ሐሰት ምንም አይጠቅመንምና፡፡

(በእንተ ክህነት፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ 4፥2
በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመው)

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
Forwarded from የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ("የአምር አቡክሙ ሰማያዊ ዘትፈቅዱ ዘእንበለ ትስአልዎ።" ማቴ. ፮፡፰)
👉አመ ዐሡሩ ወተሱዑ ለወርኀ ታኅሣሥ በ፳፻ ወ፲ ወ፭ ዓ.ም በዐሥራይ ሰዓተ ሌሊት #በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ዘተቀነይክዎ ቅኔ።

፩. ግእዝ ጉባዔ ቃና
°ስብሐት ወክብር ለእግዚአብሔር አብ፥
°እስመ አኰነኖ ሌሊተ ለቅኔ ያሬድ ኮከብ።

፪.፩. ዕዝል ጉባዔ ቃና
°በትንቢተ ነቢይ #ዕንባቆም ምጽአቱ ከመ እም ቀዲሙ ተነግረ፥ (ዕን. ፫፡፩-፫)
°ልዑለ መንበር ማሕሌት ፈጣሪ ከመ ያድኅነነ #ሠምረ

፪.፪. ዕዝል ጉባዔ ቃና
°መኑሂ በዊአ ውስተ ገነት ኢይከልአነ ለነ፥
°#መልአከ_ገነት በክብር ወጸጋ አምጣነ ሀሎ ምስሌነ።

፪.፫. ዕዝል ጉባዔ ቃና
°ለምሂረ ወንጌል ጳውሎስ እመኒ እስከነ
እልዋሪቆን ሖረ፥
°ሕያው ቅኔየ ኀሊፎ እስከ #አድማስ ተነግረ።

፪.፬. ዕዝል ጉባዔ ቃና
°ፍቁራን አኀው ጣዕመ ትዕግሥት በነፍስክሙ ታእምሩ፥
°ትዕግሥቶ #ለኢዮብ በኵሉ ዘተዐገሠ ነጽሩ። (ያዕ. ፭፡፲፩)

፪.፭. ዕዝል ጉባዔ ቃና
°መስቀለ ገብርኤል ኄርት ሠለስቱ ኀባውዝኪ እፎኑ፥
°ረቂቅ እሳት ምንተኒ ኢለከፎሙ አኮኑ።

፫. ዘአምላኪየ
°ማሕሌተ ሊቃውንት ለከ ዘይመስለከ መኑ፥
°ስምከ በቀለመ ወርቅ ተጽሕፈ አኮኑ፥
°#ወመልአከ_ገነት ረቂቅ በክንፉ ይጼልለከ እፎኑ።

፬. ሚ በዝኁ
°ከመ ኢይበሉነ ሕዝብ አይቴ ውእቱ ዘይረድኦሙ አምላኮሙ፥ (መዝ. ፻፲፬፡፪-፫)
°ተስፋ ቅቡጻን ርድአነ እስመ አንተ ተስፋሆሙ፥
°በከመ ይቤ ዳዊት ለእለ ውስተ ባሕር ርሑቅ ወአጽናፈ ምድር ኵሎሙ። (መዝ. ፷፬:፭-፮)

፭. ዋይ-ዜማ
°ይቤለነ ጳውሎስ እንበለ ይዕርብ ፀሐይ መዓተክሙ አቍርሩ፥ (ኤፌ. ፬፡፳፯)
°ወኀይለ እስከ ትለብሱ በተስፋ ንበሩ፥
°ወይቤለነ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ መምህሩ፥
°ደቂቅየ ሊተ እንዘ ትትፋቀሩ፥
°ከመ ኵሉ የሐልፍ አእምሩ።

፮. ኀፂር ዋይ-ዜማ
°ገብርኤል ለእመ ወለደ ሠለስተ ውሉደ፥
°መኑ ውእቱ ዘነአምኖ ገሃደ።

፯. ሥላሴ
°በይእቲ ኢትዮጵያ ዘኢይተረጐም ተተርጐመ ዓዲ ተገድፈ ተገድፎ ዘውስተ ወንጌል ተነግረ፥
°እስመ ዐብድ በመካነ ሊቅ በድፍረት ነበረ፥
°ወእም ይቅትለነ ዐብድ በከንቱ እንዘ ያለብስ ኀሳረ፥
°ይቅትለነ ሊቅ እንተ ተምህረ፥
°ወይቤ እግዚእ ይኩንክሙ ገብረ፥
°ዲቤክሙ ዘተሠይመ ምዕረ። (ዮሐ. ፳:፳፮-፳፯)

፰. ዘይእዜ
°ማሕሌተ ሊቃውንት እግዚእ ተሰብኦተከ እም ድሬዳዋ ድንግል ዘያስተሓቅር መኒኖ፥
°መዓልተ ወሌሊተ ያንኰርኵር ታሕተ ግበ ደይን ግዱፈ ከዊኖ፥
°ወእምነ ኵሉ ይኄይስ በእግዚእናከ ተአምኖ፥
°ወበቃለ ሰላም ንንሥኦ ወኢንትመየኖ፥
°ለቃለ ቅዱስ ያሬድ ዘእም ኀበ ላዕሉ ይትፌኖ።
(°ወበቃለ ሰላም ንንሥኦ ወኢንትመየኖ፥)

፱. ሣህልከ
°ገብርኤል አቍርር ነደ እሳት፥
°ዘይነድድ ወትረ በኢትዮጵያ ጽዕዱት፥
°ከመ ነደ ባቢሎን አ-ኅ-ጐልከ እስመ ትክል አቍርሮ እሳት በኵሉ ዕለት።

፲. ኀፂር ሣህልከ
°ኦ ገብርኤል መልአከ ኀይል፥
°ኀይለ ጸላእትነ አድክም በኀይለ ቅዱስ መስቀል።
(°ኦ ገብርኤል መልአከ ኀይል፥)

፲፩.፩. መወድስ
°ይቤለነ ጴጥሮስ ማሕሌተ ሱራፊ ለእግዚአብሔር እግዚእ ሕዝቦ ኢትትኀየሉ፥ (፩ ጴጥ. ፭፡፫)
°ወለእመኒ ጾርክሙ ዕፀ መስቀሉ፥
°ጠዐሙ እንከ ወተአምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር ወጻድቅ በቃሉ (መዝ. ፴፫:፰)
°ወክቡር በኀቤሁ ዘበኀበ ሰብእ ምኑን ወትሑት በውስተ ኵሉ፥
°ጸላእቱሰ ሶበ ከብሩ ወተላዐሉ፥
°የኀልቁ ከመ ሰምዕ ወበአምሳለ ጢስ ይትኀጐሉ፥
°ወኃጥእ፦ ሕዳጠ እንከ ኢይሄሉ፥ (መዝ. ፴፮፡፲)
°እስመ ኃጥኣን ይሰደዱ እንዘ ውስተ አድባር የዐይሉ። (መዝ. ፴፭፡፲፪)

፲፩.፪. መወድስ
°ፈልፈለ በረከት ማሕሌት እግዚአ ልዕልና ዘእም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ በብዝኀ ምሕረትከ ፈጠርከነ፥
°ሣህልከ ወትረ ይርከበነ፥
°ለነ ለነ ለአግብርቲከ ጸጋከ ወበረከተከ በምሕረት ክፍለነ፥
°ወኢታርእየነ ሙስናሃ ለሀገር ቅድስት በብዝኀ ጥበብከ ሰውረነ፥
°ጸላእትነሰ ጽልሕዋን ዘይኄይሉነ፥
◦ጽልአ ወእኪተ ህየንተ ሠናይት ፈደዩነ፥
◦ለነሰ ሰላመ ይትናገሩነ፥
◦ወበቍጽር ይመክሩ እም ውስተ ገጸ ምድር ያመንስዉነ። (መዝ. ፴፬፡፳)

፲፪.፩. ኵልክሙ መወድስ
°ትቤ ወላድ ቤተ ክርስቲያን ዐገቱኒ ሊተ ከለባት ብዙኃን፥
°ወአኀዙኒ አሥዋር ስቡሓን፥ (መዝ. ፳፩፡፲፪፣ ፲፮)
°እለሰ ይትቃጸቡኒ አዕጽምትየ ያጸነጵዉኒ በኲናት ልሳን፥
°ወእንዘ ከመ ዝ እትመነደብ ከመ የሀበኒ ፍትሐ አልብየ መኰንን፥
◦ዘሂ ያስተሓምም ቤተ ክርስቲያን፥
◦ትንቢተ ዕንባቆም ይትፈጸም እብን ዘዲበ እብን፥
◦እስመ ቀዲሙ ተብህለ በሳምናዊት ዘመን፥
◦መልእክተ ዮሐንስ ሐዋርያ እንተ ኢያንበበ ይትከሀን።
°ወኵሉ ምሁር እንዘ በኵሉ ምእመን።
(◦መልእክተ ዮሐንስ ሐዋርያ እንተ ኢያንበበ ይትከሀን።)

፲፪.፪. ኵልክሙ መወድስ
°ወንጌል ቅዱስ ከመ ነገረነ ተከብቶ ኢትክል ዘተሐንጸት ላዕለ ደብር፥ (ማቴ. ፭፡፲፬)
°ህሉና ሊቃውንት ዐባይ ዘአበዊነ ሀገር፥
°ወአናቅጸ ሲኦል እኩያን ኢይትኄየልዋ በምሴት ወቀትር፥
°ወጻድቅ በትዕቢቱ ለኃጥእ ይውዒ ወይነድድ ከመ ሣዕር፥
°ዳዊትሂ ይቤለነ በመዝሙር፥
°እለ ተአምሩ ኢታዕብዩ ርእሰክሙ በኀሣር፥
°ዘሂ፦ ይቤ አእመርኩ ምሥጢረ ሰማይ ወምድር፥
°ዓዲ ኢያ-እ-መረ ዘይደልዎ ከመ ያእምር። (፩ ቆሮ. ፰፡፪)
°እስመ ውስተ ምይንት ነፍስ ኢትተረጐም ምሥጢር። (ጥበ. ፩፡፬)
(°ዓዲ ኢያ-እ-መረ ዘይደልዎ ከመ ያእምር።)

፲፫. ኀፂር ኵልክሙ መወድስ
°ኦ ገብርኤል ዘታፈደፍድ ምሒረ፥
°ረቂቅ አስተብቍዖትከ ያዕድወኒ ባሕረ።

👉እም ኀበ መምህር ያሬድ ዘርአ-ቡሩክ

👉ለዘኄሰ ምርዳእ በዘይተሉ Link ይረክቡነ።
https://www.facebook.com/Yared.ZeraBuruk?mibextid=ZbWKwL
Audio
የተማራችሁትን ወግ ያዙ
                         
Size 36.8MB
Length 1:45:43

  በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/11/15 10:07:23
Back to Top
HTML Embed Code: