Telegram Web Link
+ የመጽሐፍ ዮሴፍ +

       ዮሴፍ ግብፅ ወርዶ ፣ የግብፅን ንጉሥ የፈርኦንን ሕልም ፈትቶ ፣ ሀገረ ገዢ ሆኖ ነበር፡፡ ግብፅን ከረሃብ ከማዳንም አልፎ የዓለም የእህል ጎተራ እንድትሆን አድርጓት ነበረ፡፡ ይህንን የዮሴፍን ውለታ ያልዘነጋው የግብፅ ንጉሥ ፈርኦን ለዮሴፍና በቁጥር ሰባ ለነበሩት የዮሴፍ ዘመዶች የክብር ማረፊያ ሠጥቶ እንደ ሀገራቸው ተስፋፍተው እየተዋለዱ በግብፅ እንዲኖሩ አደረጋቸው፡፡ በፈርኦን ላይ ፈርኦን ፣ በትውልድ ላይ ትውልድ ሲተካ ግን ድንገት ‘ዮሴፍን የማያውቅ ፈርኦን ተነሣ’ (ዘጸ. 1፡8)

ከዚያ በኋላ የሆነውን ምኑን ልንገራችሁ? ፳ኤል ልጆቻቸውን ከሲሚንቶ ጋር ለውሰው ፒራሚድ እስኪሠሩ ድረስ የወረደባቸው መከራ ምኑ ይነገራል? ለዚህ ሁሉ መከራ መነሻው ግን ‘ዮሴፍ ደግሞ ማን ነው?’ የሚል ትውልድ መምጣቱ ነው፡፡

       ‘ዮሴፍን የማያውቅ ፈርኦን ተነሣ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ያስጠቀሰኝ የመጽሐፍም ዮሴፍ አለ ለካ የሚያሰኝ የሰሞኑ አንድ ገጠመኝ ነው፡፡ ከዐሠርት ዓመታት በላይ ከገበያ ጠፍቶ የቆየውን ውድ መጽሐፍ ‘ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት’ እኮ ታተመ!’  የሚል ዜና የነገርናቸው ሰዎች ሁሉ ብዙም አለመደነቃቸውን ሳይ ለካ የመጽሐፍም ዮሴፍ አለ? ብዬ እንድተክዝና ይህንን የመጽሐፍ ዮሴፍ ለማስተዋወቅ ብእሬን እንዳነሣ ግድ ሆነብኝ፡፡

       ‘ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት’ የሚለውን [በወቅቱ በሚጠራበት ስም] የዲያቆን አንዱዓለም ዳግማዊ መጽሐፍ ውለታ እንዴት ልንገራችሁ? ይህ መጽሐፍ የአዲሱ ትውልድ የነገረ ማርያም ሥነ ጽሑፍ የተወለደበት እጅግ አንገብጋቢ (critical) ሥራ መሆኑን ለመግለጽ ቃላት ሊያጥረኝ ይችላል፡፡ ስለተጻፈበት ዘመን ሁኔታ ብቻ ላስታውስ፡፡

       ያ ጊዜ መንፈሳዊ ኮሌጆች በእንግዳ ትምህርቶች ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ የወደቁ በሚያስመስል ሁኔታ ላይ ነበርን፡፡  ‘ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ የገባ ሰው ጤነኛ ሆኖ አይወጣም’ የሚል ድምዳሜ ላይ እስኪደረስ ድረስ ብዙዎች ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ነን እያሉ ከኦርቶዶክሳዊ መንገድ የወጣ ትምህርት ያስተምሩ ነበረ፡፡ በቅርቡ ያረፉት ባለቅኔው መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒን የመሳሰሉ ሊቃውንት ሳይቀር ‘የሀገር ውስጥ ቦንኬ ማምረቻ’ ብለው መንፈሳዊ ኮሌጁን እስኪያማርሩ ድረስ የተደረሰበትና ቤተ ክርስቲያን በራስዋ በጀት ጠላት እንዴት ታፈራለች የሚባልበት ዘመን ነበረ፡፡ (ቦንኬ ልጆች ሳለን የብዙ ውዝግብ ምክንያት የነበረ ፈረንጅ ፓስተር ስም ነው) ያ ጊዜ የአብነት ትምህርት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርት ጋር እንደ እሳትና ጭድ ተደርጎ የሚቆጠርበት ፣ ቀሚስ ለባሹ ነጠላ ለባሹን በንቀት ፣ ነጠላ ለባሹ ቀሚስ ለባሹን በጥርጣሬ የሚያይበት ወቅት ነበር፡፡

በዚያን ወቅት ራሳቸው ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ስላልመጣላቸው መንፈሳዊ ኮሌጅ የገቡና መመረቂያ ጽሑፋቸውን ሳይቀር በሰው የሚያሠሩ አንዳንድ ድኩማን ተማሪዎች ‘traditional’  በሚል በጉባኤ ቤት ያለፉ  ሊቃውንትን የማሸማቀቂያ ቃል ነባሩን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥልቅ ነገረ ሃይማኖት ሳይረዱ የሚያናንቁ ወጣቶች የተነሡበት ጊዜ ነበር፡፡ ‘Salvation, redemption, Christology’ የሚሉ ቃላትን ከማዘውተራቸው ውጪ የጠለቀ theological እውቀት ሳይኖራቸው በትዕቢት የተወጠሩ ሰዎች የመንፈሳዊ ኮሌጅን ገጽታና ምንነት የሸፈኑበት ዘመን ነበረ፡፡

በተለይ ነገረ ማርያምን ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ አቅጣጫ መስማት እንደ ሶምሶን እንቆቅልሽ ‘ከበላተኛ መብል ወጣ ፣ ከሚያፈራውም ጥፍጥ ወጣ’ (እምአፈ በላዒ ወጽአ መብልዕ ፤ ወእምአፈ ግሩም ወጽአ ጥዑም)ን የሚያስጠቅስ ክስተት ነበር፡፡ የጉባኤ ቤት ትምህርትና ቴዎሎጂን ማዋሐድም ዘይትና ውኃን የማዋሐድ ያህል ከባድ እንደሆነ ተደምድሞ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ሆነው ሁለት ዓይነት ጎራዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ  በወቅቱ ገና ልጆች ለነበርነው ግራ የሚያጋባና የቱን መስመር ልከተል የሚያሰኝ መንታ መንገድ ነበረ፡፡

       በዚህን ወቅት ነው የዲያቆን አንዱ ዓለም ዳግማዊ ዓይነት ዘይትና ውኃን ያዋሐዱ ፣ ቴዎሎጂን ከአብነት ትምህርት ፣ እንግሊዝኛን ከግእዝ ፣ ፋዘር ጆሲን ከመምህር ደጉ ዓለም ፣ ነገረ ክርስቶስን ከነገረ ማርያም ፣ የሰባኪ ቀሚስን ከልብሰ ተክህኖ ያስታረቁ ልጆች ከዚያው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አብራክ ተወልደው ብቅ ብቅ ሲሉ አይተን ልባችን ማረፍ ጀመረ፡፡ የዲያቆን አንዱዓለም ዳግማዊ ዓይነቶቹ ከመንገድ ሲያልፉ ውዳሴ ማርያም ዜማ ሲደርስ በፍርሃት ቆመው ሰአሊለነ ቅድስት እስኪባል የሚጨርሱ ፣ በወጣትነታቸው የአንደበታቸው ላህይ የቀደምት መምህራን የሆነ ፣ ትሕትናቸው የሊቃውንት የሆነላቸውን ‘በማር ላይ ቅቤ’ የሆኑ ጥንቅቅ ያሉ  ሰባኪያንን ቆመው ሲያገለግሉ ማየት በዚያን ወቅት ለብዙዎቻችን ተስፋና መነሻ ነበረ፡፡

       ይህ በሆነበት ሁኔታ በተሐድሶ (የጲጥፋራ ሚስት) የሐሰት ክስ ምክንያት በግፍ የታሰረውን ነገረ ማርያም (ዮሴፍን) ከእስር ቤት ያስፈታ የብዙዎቻችን እውነተኛ የሕልም ፍቺ ፣ የወላዲተ አምላክን ፍቅር ለተራብን ሁሉ ምግብ የሆነ ‘ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት’ የተሰኘ መጽሐፍ ታተመ፡፡

ይህ መጽሐፍ የነገረ ማርያም (Mariology) ድንቅ ምሁራዊ ጥናት ከመሆኑ ባሻገር ውዳሴ ማርያም ትርጓሜን ከቤተ ክርስቲያን ቀደምት አበው ሥነ ጽሑፍ (Patristic Litrature) ጋር ያጣመረ አባ ጊዮርጊስን ከቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ፣ ቅዱስ ያሬድን ከዮስጦስ ሰማዕት ፣ አባ ህርያቆስን ከቅዱስ ጄሮም ጋር ለምስክር የጠራ ቴዎሎጂ ከአብነት ትምህርት ጋር ሲጣመር እንዴት ያለ ውበት እንዳለውና ለክህደት የሚዳርጋቸው በአግባቡ ያልተማሩና ያላነበቡትን ሰዎች ብቻ እንደሆነ በተግባር ያስመሰከረ ፣ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን ያስከበረ እጅግ እጅግ ውብ ሥራ ነበረ፡፡

በዛሬው መጠሪያቸው የመጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዶ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ  ‘ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት’ መጽሐፍ ያለ ምንም ማጋነን ይሄ ትውልድ ተሳልሞ ሊያነበው የሚገባ እጅግ ድንቅ መጽሐፍ ጸሐፊውን ለPHD ያበቃ እኛን ደግሞ ለጥልቅ ንባብ ያነቃ ታሪካዊ መጽሐፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን በጸሐፊያን ዘንድ የተሻሉ ሥራዎችን አይቶ እንዳላየ የመሆን በሽታ (Silent conspiracy) የጸናበት ዘመን ቢሆንም በመጽሐፉ የተጠቀማችሁ ጸሐፍት ሁሉ ስለዚህ መጽሐፍ ውለታ ዝም ልትሉ አይገባም::

መጽሐፉ ከገበያ ጠፍቶ አሁን ሲታተም ‘ዮሴፍን የማያውቅ ፈርኦን ተነሣ’ እንዲል ብዙ ሰው የዚህን መጽሐፍ ምንነት አልተረዳም፡፡ ወዳጄ ይህ መጽሐፍ ትናንት ባይኖር የዛሬዎቹ እነ ‘የብርሃን እናት’ ጨርሶ ባልኖሩም ነበረ፡፡ በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ቤት ሊኖር የሚገባና በማንበብህ የምትኮራበት ውድ መጽሐፍ መሆኑን ስታነቡት ታምኑኛላችሁ፡፡ መጽሐፉን በይፋ ግንቦት ላይ እስክንመርቀው ድረስ ‘ይህን መጽሐፍ ብላ’ ብዬ ስናገር እንደ ሕዝቅኤል ‘በላሁት ጣፈጠኝ’ እንደምትሉ በመተማመን ነው፡፡  አሁን በገበያ ላይ ያለው ውስን ኮፒ ሳያልቅ እጃችሁ አስገቡ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መጋቢት 13 2015 ዓ.ም.
✞የጴጥሮስን ዕንባ✞
♡የመዝሙር ግጥሞች♡
✞የጴጥሮስን ዕንባ✞

የጴጥሮስን እንባ ስጠኝ እልሃለሁ
ኃጢአቴን ልናዘዝ ፍቅርህን እያየሁ
በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ብሄድ ጌታሆይ(፪)
ልቤን በፍቅር ውሃ እጠበው እባክህ

ቸርነትህ በዝቶ ምህረት ቢያሰጠኝ
እጀቼን ዘርግቼ እማጸናለሁኝ
ደምህ የፈሰሰው ለኔ ስለሆነ(፪)
በኃጢአት ልተወኝ ልብክ አልጨከነም
አዝ= = = = =
ዓለማዊ ምግባር ልቤ ቢከተልም
ከዚህ ሁሉ ማዳን ጌታ አይሳንህም
ኃጢአት እየሰራሁኝ ባስቀይምህም(፪)
በሄሶጵ እርጨኝ ጌታ እጠበኝ እባክህ
አዝ= = = = =
ዲያቢሎስ ያመጣው ጸጸት የውድቀት ነው
የይሁዳ ምሬት የሞት ነው ፍፃሜው
ይህንን መማረር እኔ አልፈልግም(፪)
የውድቀት ጉዞ እንጂ ትንሳኤ የለውም

ጴጥሮስ አባብሎ የተማጸነበት
ፍቅሩን በንስሐ ስቦ ያመጣበት
ፍፃሜው የሚያምር ንስሐ ስጠኝ(፪)
የለቅሶ አምሀ የእንባን ይወት ስጠኝ

መዝሙር
ይልማ ኃይሉ

"ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።"
ሉቃ፳፪፥፷፪
2024/09/30 23:41:06
Back to Top
HTML Embed Code: